አንዱዓለም አራጌ በእስር ቤት…
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ የመጀመሪያ ልጁን የሩህ አንዱዓለምን 5ኛ ዓመት የልደት በዓል እሁድ ግንቦት 11 ቀን 2005ዓ.ም. አከበሩ፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌ የልጃቸውን የልደት በዓል እቤታቸው ማክበር ባለመታደላቸው እሁድ ከቀኑ 4፡00 ሰዓት ለባለቤታቸው ሳያሳውቁ ለመጠየቅ ሲሄዱ በድንገት ለማስደሰት ሲሉ ተዘጋጅተው በመጠበቃቸው በሰዓቱ ባለቤታቸው ዶ/ር ሰላም አስቻለው፣ልጃቸው ሩህ አንዱዓለም፣እህታቸው ወ/ት አበሩ አራጌ በተገኙበት በመጠየቂያ ጠባብ ክፍል በጋራ የልጃቸውን ልደት አክብረዋል፡፡
ይህ ልጃቸው ያኔ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2003ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት ልኮት ማታ ሲመጣ ውሎውን ለማዳመጥ በናፍቆት እየጠበቀና ይህንንም ለባልደረቦቹ ለአንድነት ፓርቲ አመራሮችና ሰራተኞች የነገረ ቢሆንም በዕለቱ የልጁን ውሎ እንደናፈቀ ከቀኑ 9፡20 ሰዓት ላይ በፖሊሶች ከሚሰራበት ከፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት አቅራቢያ ካለ ካፍቴሪያ ከአንድ የፓርቲው ወጣት አመራር ጋር በመሆን ሻይ ቡና ብለው ሲወጡ ተይዘው መታሰራቸው ይታወቃል፡፡
በዕለቱ የዛሚ ሬዲዮ ባለቤት ሚሚ ስብሐቱ የእነ አንዱዓለም ፓርቲ ልሳን የሆነውን ፍኖተ ነፃት ጋዜጣን ዋቢ አድርጋ በመጥቀስ ብጥብጥ እየቀሰቀሱ ነው፤ ዝም ሊባሉ አይገባም ብላ በተለመደቀው በቀትር የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በሚል የሬዲዮ መርሃ ግብር አቅርባ የነበረ ሲሆን አንዱዓለምም ይህንን ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር አዳምጦ ጨርሶ ከወጣ በኋላ መያዛቸው አዘነጋም፡፡ በአሁን ወቅትም ወጣቱ ፖለቲከኛ አቶ አንዱዓለም አራጌ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው በቃሊቲ እስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት(ግንቦት 2005ዓ.ም.)
በኢትዮጵያ ስኳር ፕሮጀክት ላይ የተጋረጠው አደጋ
ብስራት ወ/ሚካኤል
ጨዋማው የኢትዮጵያ ሐይቅ 15 እጥፍ ይዘቱና ስፋቱ እየጨመረ በሀገሪቱ ታላላቅ ወንዞች መካከል አንዱ በሆነው ወንዝ ላይ ስጋትን ጭሯል፡፡ ይህ ስጋት በቡና አምራችነቷ ከአፍሪካ ታላቅ በሆነችው ሀገር ላይ አደጋ እያንዣበበ ነው፡፡
ጨዋማው ውሃ ታማኙንና ታላቁን አዋሽ ወንዝን በመበከል በኢትዮጵያ መንግስት ባለቤትነት በሚተዳደረው ስኳር ፋብሪካ እና ከህንድ ድጋፍ በማግኘት ስኳር ወደ ውጭ ላኪ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ያለው ዕቅድ ላይ አደጋ ተጋርጧል፡፡ ስጋትን የጫረው ይህ ጨዋማው ሐይቅ የበሰቃ ሐይቅ ነው፡፡
የበሰቃ ሐይቅ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝና ባለፉት ዓመታትም እጅግ እተስፋፋ ወደ መስኖው ውሃ እየተቃረበ ነው፡፡ ይህ ሐይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ የሚገባ ከሆነ በኢትዮጵያ ግዙፍ የስኳር አምራችነት ዕቅድ ላይ የአደጋ ጥላ ያጠላል፡፡
እዚህ ላይ የውሃና ማዕድን ሚኒስቴር የከርሰ ምድር ውሃ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ታደሰ ‹‹ለወንዙ ነው የምንሰጋው፤ ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ በራሱ ጊዜ ወደ ወንዙ የሚደባለቅ ከሆነ እስከወዲያኛው ወንዙን እየበከለው ይሄዳልና” ሲሉ መስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
አባይ ተፋሰስን ጨምሮ ከሀገሪቱ ከፍታ ቦታዎች የሚመነጩ ወንዞች ኢትዮጵያን ከአህጉራቱ አፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የውሃ ኃይል ባለቤት አድርጓታል፡፡ መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ ከህንድ የገንዘብ፣ የሳውዲው ቢሊየነር እና ከቻይናው አበዳሪ ስኳር፣ ሩዝ፣ ሙዝና ብርቱካን ምርትን ለማስፋፋትና ወደ ውጭ ለመላክ ያለነዳጅ ዘይት በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አስባለች፡፡
የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የቴክኒክ ኃላፊ የሆኑት እንደሻው ታደሰ እንዳሉት ከሆነ የሰኔው ወቅታዊ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት ሐይቁ ወደወንዙ እንዳይፈስ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፍሰቱ ከሀገሪቱ ዋና መናገሻ አዲስ አበባ በስተምስራቅ የጎርፍ መጥለቅለቅን በማስከተል በአካባቢው የነበሩትን አርብቶ አደሮች እንደሚያርቅ ይጠበቃል፡፡
በሰቃ ከ954 ሜትር የሚመነጭ ፍልውሃ በ1960ዎቹ ዓ.ም.(እ.ኤ.አ) 3 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሸፍን የነበረው በአሁን ሰዓት 5 እጥፍ በማድረግ ወደ 45 ኪሎ ሜትር ስፋት በመጨመር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ወደብ ዋና የንግድ መስመር የሆነውን መንገድ አቅጣጫ ማስቀየሩም ግድ ይላል፡፡
ያልተሳኩ ጥረቶች
መንግስት ላለፉት 14 ዓመታት በየጊዜው ስፋቱና ይዘቱ እየጨመረ የመጣውን የበሰቃ ሐይቅ የማስቀየሻ ቦይ ግንባታ በመስራት እንዲፈስ ቢያደርግም ሐይቁን እንደባህር ባለበት ማስቀረት አልቻለም፡፡
በዚህ ላይ በ2009 (እ.ኤ.አ) እና ባለፈው ዓመት ጥናታቸውን ያቀረቡት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት መገርሳ ኦኩማና ደንቃ እንዳሉት ከሆነ በአካባቢው የመስኖ ፕሮጀክቱ መጨመር ውሃ ወደ ሐይቁ በመግባት ተመጋጋቢነት ይኖረዋል፡፡ ይህም በሚደረጉ የመስኖ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡
አሁን ባለው የበሰቃ ዕድገት ባህርይ መተሐራ አካባቢ ያለውን መስኖ ከጥቅም ውጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በያዝነው ዓመት የተገዛውና ንብረትነቱ የመሐመድ አል አሙዲ የሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ከመንግስት የገዛው የላይኛው አዋሽ የግብርና ኢንዱስትሪንም አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ ይህን በተመለከተ የሆራይዘን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ ከሐይቁ ምንጭ ዕድገት ጋር ተያይዞ የተደረገውን ጥናት አላረጋገጥንም፣ ምናልባት በአካባው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖር ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
ኢንቨስትመንት
አል አሙዲ የግብርና ምርት ወደሆኑት ሩዝ፣ ሙዝና የተጠናቀቀ ቡና ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ሆራይዘን በላይኛው አዋሽ 432 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ የብርቱካን ምርትን በእጥፍ በማሳደግ ወደ 50,000 ቶን ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ 380 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከህንድ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በተገኘ 640 ሚሊዮን ዶላር ብድር እየተገነባ ያለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም የበሰቃ ሐይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ በመግባት ወንዙ ጨዋማ የሚሆን ከሆነ አደጋ ይገጥመዋል፡፡ እንደሚታወቀው ህንድ በዓለም ሁለተኛ የስኳር አምራችና ከፍተኛ ተጠቃሚ ነች፡፡
ሌላው ወደ 30,000 ነዋሪዎች የሚገኙበት መተሐራ እና አዲስ ከተማ፣ መተሐራ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአፋር ክልል እየተገነባ ያለው ግዙፍ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሐይቁ መስፋት እየቀጠለ ከሄደ ለአካባቢው አደገኛ ነው፡፡
ስኳርና ጥጥ
ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ የመሰረት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ 90 ሚሊዮን የሚደርሰው የሀገሪቱ ነዋሪ ወደመካከለኛ ገቢ እንዲያድግ የጥጥ እርሻን አቅርቦት ተንተርሶ የሚገነቡት የጨርቃጨርቅ እንዱስትሪዎች ማደግ እንዳለባቸው ዕቅድ ነድፈዋል፡፡ ይህ የጥጥ እርሻ ልማት ደግሞ ለመካከለኛው አዋሽ በአሚባራ ቢዝነስ ግሩፕ የሚመራው ኢንዱስትሪም የበሰቃ ሐይቅ ከአዋሽ ወንዝ ጋር በመቀየጥ ጨዋማ የሚሆን ከሆነ እሱም አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ እንደዓለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ተቋም መሰረት ከ1984 ዓ.ም.(እ.ኤ.አ) ጀምሮ በፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረ 2,000 ሄክታር በጨዋማ ውሃ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡
አሚባራ መካከለኛው አዋሽ የግብርና ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ውብሸት ይልማ እንዳሉት ከሆነ ‹‹ከዝናቡ በፊት የሐይቁ መስፋፋት ያሳስበናል፤ ምክንያቱም ሐይቁ ወደ አዋሽ የሚገባ ከሆነ ለአማባራ ጥጥ እርሻ ችግሩ ከፍተኛ ነው የሚሆነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤት መስጠም
በኢትዮጵያ መንግስት ንብረት የሆነውና በአፋር አካባቢ የተቋቋመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአዋሽ ወንዝ ግድብ ግንባታ ላይ መሰረት በማድረግ ከ600,000 ቶን በላይ የሸንኮራ እገዳ በዓመት ለማልማት የነበረው እቅድ ላይ ጨዋማ ውሃ የሚፈስ ከሆነ አሁንም እቅዱ ይጨናገፋል፡፡
በተለይ አቶ እንደሻው እንደተናገሩት ከሆነ “ዝናብ የሚዘንብ ከሆነ በቃ” ሲሉ ባለፈው ዓመት በሐይቁ ሙላት ምክንያት የሰጠሙ ሁለት ትምህርት ቤቶችን አስታውሰዋል ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐይቁን ስፋት ተከትሎ በተፈጠረ ድርቅ በተወሰደ እርምጃ በ2008 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ክልላዊው መንግስት በ467 ሚሊዮን ብር የፈንታሌ መስኖ ቦይ ግንባታ መደረጉን የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት የውሃ ምህንድስና ኃላፊው እንግዳ ዘመዳገኘሁ ተናግረዋል፡፡
በተለይ እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ወንዙ 4 በመቶ የሐይቅ ውሃ የሚይዝ ቢሆን እንኳ በማንኛውም መልኩ አደገኛ ነው፡፡ ለዚህም በሚል በፓንፕ (ውሃ መሳቢያ መሳሪያ) ብዙ ውሃ ለመቀነስ ጥረት ብናደርግም መስፋፋቱን ግን ሊቀንስ አልቻለም ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
በማኛውም አጋጣሚ ሐይቁ እየጨመረ ከሄደ “ሐይቁ ወደ አዋሽ ወንዝ የመፋሰስ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሚቀጥሉት ቅርብ አመታት የመተሐራ ስኳር ፋብሪካን ያወድማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተንዳሆን ጨምሮ በአዋሽ ተፋሰስ በሚገነቡ በሁሉም ግዙፍ መስኖ ልማቶችም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል” ሲሉ ፕሮፌሰር መገርሳ ተናግረዋል፡፡
የእሾሃማ ዛፎች እጣ ፈንታ
በመንግስት ባለቤት ከሚገነባው ተንዳሆ ስኳር ውጭ በኬንያ አቅራቢያ በደቡብ ኦሞ የሚገነቡትን 6 የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች ጨምሮ 10 ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በቻይና ዴቨሎፕመንት ባንክ የሚደረግ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር ድጋፍ በአዋሽ አካባቢ የሚገነባ የከስም ስኳር ፕሮጀክት ይገኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ የስኳር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ ቃል አቀባይ አቶ ይልማ ጥበቡ ከመጋቢት አጋማሸ ጀምሮ አስተያየት ቢጠየቁም ምላሽ እንዳልሰጡ የብሉምበርጉ ዘጋቢ ዳቪሰን አስታውሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ከፍታ ቦታዎች በመመንጨት በሰሜን ምስራቅ ወደ አፋር በመፍሰስ ጅቡቲ አካባቢ ከመድረቁ በፊት አዋሽ ወንዝ 1,200 ኪ.ሜትር ይጓዛል፡፡ ከመተሐራ አካባቢ ጀምሮ ባሉ በአካባቢው ያሉ እሾሃማ ዛፎች(ግራርና ቆንጥር) በተጨማሪ በአካባቢው ሞቃታማ ስፍራ የሚበቅሉ የምግብ እህሎችን ተንተርሰው እየኖሩ ያሉ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡ ለነዚህ ህዝብ በተለይም የአፋር አርብቶ አደሮች ለረጅም ጊዜ ህይወታቸውን እዚህ ወንዝ ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው ፡፡ ስለዚህ የአዋሽ ወንዝ በበሰቃ ሐይቅ ብክለት የሚያጋጥመው ከሆነ ለእነኛ ነዋሪዎች አደገኛ ነው የሚሆነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው የከፍተኛ ባለሙያዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ስብስብ ስለሐይቁ እንዴት እያደገ እንደመጣ ጥናትና ምክክር እየተደረገ ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ግን ምን መደረግ እንዳለበት የተያዘ አቅጣጫም ሆነ የተወሰደ እርምጃ የለም ሲሉ ማከላቸውን ሚያዚያ 24 ቀን 2013 (እ.ኤ.አ) በብሉምበርግ ድህረ-ገፅ ዊሊያም ዳቪሰን አስነብቧል፡፡
አሁንም ቢሆን ከአዲስ አበባ ወደምስራቅ 195 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የመተሐራ በሰቃ ሐይቅ ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘለት በአዋሽ ተፋሰስ ላይ በብዙ ቢሊየኖች ብር ግንባታቸው ተካሂደው በስራ ላይ ያሉ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ፤ በቅርቡ ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ በስራ ላይ ያሉት የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ የግብርና እንዱስትሪዎች እንዲሁም በእቅድ ላይ ያለው የከሰም ስኳር ፕሮጀክት በተጨማሪ የመተሐራን ከተማ ነዋሪዎችና አዋሽ ወንዝን ተጠግተው የሚኖሩ የአፋር ክልል ነዋሪዎችን በነበሩት ዳግም ላናገኛቸው እንችላለን፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የብሎምበርግ ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ ሲያደርግ ከሚፈልገው ገንዘብ ውጭ አካባቢያዊ ጥናት የማድረግ ትኩረትም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መጨው ትውልድ ላይ ጭምር ዕዳ ተጥሎ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የሚጠበቅባቸውን ውጤት ሳያስገኙ በሚደርስባቸው የአካባቢ አደጋ በሀገር ላይ ከፍተኛ የሃብት ውድመት ማስከተላቸው የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት የግብር ውጣ ስራ የሚያደርገውን የዘመቻ የልማት ፕሮጀክቶች ስራ አካባቢውንና ተፈጥሯዊ ሁነቶችን ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ማጤንና ማገናዘብ አለበት፡፡
እውን የሀገሪቱ ችግር እንዲህ በቀላሉ ይፈታ ይሆን?
ብስራት ወልደሚካኤል
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ከዕለት ወደዕለት እየባሰበት በመሄዱ የችግሮቹን ውስብስብነት ከመባባሱ በስተቀር ለነዋሪው የፈየደ አንዳች የመፍትሄ ሐሳብም ሆነ ተግባር የለም፡፡ ችግሮቹ በገጠርም ሆነ በከተማ ተባብሰው በመቀጠላቸው ከብዛታቸው አንፃር በተናጥል መጥቀሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሉ ከሚባሉት መካከል የተወሰኑትን ችግሮች እንኳ ለማየት እንሞክር፡፡
በአዲስ አበባ ያለው የመጓጓዣ እጥረት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱ እስካሁን መፍትሄም ሆነ ትኩረት ስላልተሰጠው የሀገሪቱ ሃበት ላይ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበትና የሞራል ኪሳራ ማድረሱ አይቀሬ ቢሆንም “እኛን ብቻ አድምጡን፣ ችግራችሁን ደብቁትና ቁጭ በሉ፣ ግዴታችሁን ተወጡ እንጂ መብታችሁን አትጠይቁ!” በሚል ግትር አቋሙ የፀናው የኢህአዴግ መንግስት ችግሩን የመፍታት አቅም እንደሌለው ያረጋገጠ ቢመስልም የስልጣን ጥሙ ግን ቀፍድዶ ይዞታል፡፡ በዚህም ምክንያት የታክሲ ሰልፉ፣ የከተማ አውቶቡስ፣ የሎንችንና የሃይገር ግፍያን ጨምሮ የመንገዶች መጨናነቅን ላየ እውን በሀገሪቱ መንግስት አለን? ያስብላል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ የመጣ እንጂ ቅፅበታዊ ክስተት አይደለም፡፡
ምናልባት አሁን እየተሰራ ያለው የከተማ ውስጥ ቀላል የባቡር ሃዲድ ግንባታና አገልግሎት እየተካሄደ ነው፣ ይሄ ሲጠናቀቅ ችግሩ ይፈታል የሚል መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ሊኖሩ ቢችሉም የባቡር አገልግሎት ቢጀመርም የነዋሪው ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሩን ሊፈታ የሚችለው ብቃት ያለው አመራር መኖርና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ህዝብን ያላማከለና ያላሳተፈ ስራ ግልፀኝነት ስለሌለው ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር ውጭ የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ለመፍትሄው ከህዝብ ጋር በግልፅ መድረክ መወያየቱ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱ አንዱ ዋነኛ ችግር ሲሆን ለዚህም መንግስት እንዳሻው የሚያደርገው የገበያ ጣልቃ ገብነትና የዋጋ ተመን ዕቃ እንዲጠፋና ጥራታቸው የጎደሉ ሸቀጦች ለህዝቡ ኢንዲደርሱ ከማድረጉ በተጨማሪ ወደፊት በውድድር ገበያ ዋጋቸው የሚወርዱ ዕቃዎች ባሉበት በመቀጠል ወደፊት በዛው ዋጋቸው እየጨመረ እንዲሄድ ያስገድዳል፡፡ ስለዚህ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣትና መንግስት እጁን ከገበያ ማውጣት ካልቻለ ችግሮቹ ከአሁን በባሰ እንደሚቀጥሉ ጥርጥር የለውም፡፡
በክልል ከተሞችና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ያለው የኢህአዴግ ቅጥ ያጣ አፋኝነት(በአዲስ አበባ የለም ማለቴ አይደለም) ህዝቡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጭ መብቱን እንዳይጠይቅ በመደረጉ ችግሮች ሳይባባሱ በጊዜ እንዳይታረሙ በመደረጉ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሰቆቃ ህይወት እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በተለይ ገበሬው ያልፍላጎቱና ያለ አቅሙ ለግብርና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች( ማዳበሪያ፣ አረም ማጥፊያ፣ ዘር) ኢህአዴግ በተመነው ከፍተኛ ዋጋ እንዲገዙ በመደረጉ ምርቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ሸጠው ለኢህአዴግ በመክፈል፤ መሬት እያላቸው እንደሌላቸው በመሆን የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገበሬውም በንብረቱ የማዘዝ ስልጣኑ በመገፈፉ የእኔነት ስሜት ስለማይኖረው ውጤታማ ስራ ሊሰራ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡ የዚህ ችግር ደግሞ ከባዶ የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ በስተቀር በምግብ እራሷን እንዳትችል ያደረጋት ከመሆን ባለፈ ድሬ በምግብ እራሳቸውን የቻሉ ገበሬዎች ዛሬ ለልመና ወደ አዲስ አበባና ትላልቅ የክልል ከተሞች ጎዳና በመውጣት ለልመና ተዳርገዋል፡፡
በሀገሩቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ከፍተኛ አምራች ኃይል የሆኑት ወጣት ምሁራን ከዩንቨርስቲ ተመርቀው ወጥተው በሙያቸው እራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ማኀበረሰቡንና ሀገራቸውን ማገልገል ሲገባቸው አነስተኛ የትምህርት እድል ያላቸው ዜጎች ሊሰሩት የሚገባውን የድንጋይ ፈለጣ(ኮብልስቶን ስራ) ላይ እንዲሰማሩ በመደረጉ ለትምህርት ያወጡት፣ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ሞራል በከንቱ እንዲባክን ተደርጓል፡፡ የዚህም ውጤት የሀገሪቱ ዜጎች ተስፈኛ ከመሆን ይልቅ ተስፋ ወደመቁረጥ በመዳረጋቸው ለተለያዩ ጎጂ ሱሶች ተጋልጠው በየመንገዱ ሲንቀዋለሉ ላየ “የየት ሀገር ቱሪስቶች ናቸው?” ሳያስብል አይቀርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ አስከፊ የስደት መንገዶችን ምርጫ በማድረግ የሚሞቱ ወጣት ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ በመሄዱ “ሀገሪቱ እውን መንግስት አላትን?” ያስብላል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ምክንያት ገዥው ኢህአዴግ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲና ግትር አቋም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
በመላው ሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከትን እንደሆነ በዓለም ላይ እጅግ አምባገነንና ጨቋኝ መንግስት መኖሩን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ቢቻልም ይበልጥ ግን ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሊያገለግሉ የሚገባቸው፣ ከየትኛውም የፖለቲካና የግለሰብ ተፅዕኖ ገለልተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው የዴሞክራሲያዊ ተቋማት (የፍትህ አካል የሆኑ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃይሎች፣…) በኢህአዴግ መዳፍ ወድቀው ወገንተኝነታቸው ለፍትህ፣ ለህግና ለህዝቡ ከመሆን ይልቅ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወገንተኛ በመሆናቸው የሀገሪቱን ችግር ይበልጥ ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል፡፡ በዚህም በህግ የተሰጣቸውን መብት የተጠቀሙና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የጠየቁ በርካቶች ወደ ወህኒ ቤት ተወርውረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ጋዜጠኞች(እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፣ የሱፍ ጌታቸው፣…)፣ፖለቲከኞች(አንዱዓለም አራጌ፣ናትናኤል መኮንን፣በቀለ ገርባ፣ኦልባና ሌሊሳ፣…)፣ የኃይማኖት ነፃነት መብት እንዲከበር የጠየቁ (የሙስሊሙ ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ የዋልድባ መነኮሳት፣…) ይገኙበታል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ኢህአዴግ “ለስልጣኔ ያሰጉኛል” በሚል ብቻ በሀገር ስም ክስ ስለመሰረተ ሁሉም ተከሳሾች ወንጀለኛ የሚባሉ ሲሆን በአንፃሩ በኢህአዴግ ባለስልጣናትና አባላት በደል ተፈፅሞባቸው “የፍትህ ያለ” የሚሉ “ፍትህ በኪሴ ብይን” ተሰጥቷቸው በኋላ ወንጀለኛ እንባላለን በሚል በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት በማጣታቸው “የማርያም ጠላት” የሚባሉ በርካቶች ናቸው፤እነኚህንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ የተፈቀዱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የመሰብሰብ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞን የመግለፅ፣…በሙሉ ባልተፃፈና ባልታወቀ ህግ የተሻሩ ሲሆን ይበልጥ እነኚህ እንዳይተገበሩ ለገዥዎች ብቻ በሚመች ህገመንግስቱን በግልፅ የጣሱ በርካታ አንቀፆችን የያዘ የፀረ ሽብር አዋጅ በማውጣት ተጨማሪ የአፈና ገደቦች ተጠለዋል፡፡ የእነኚህ አፈናዎች ውጤት ችግሮች በጭሩና በቀላሉ እንዳይፈቱ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ እጅግ የታፈነ ቁጣ እንዲኖር አስችሎታል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ወደፊት በሀገሪቱ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግልፅ ቢሆንም ኢህአዴግ በያዘው ግትር አቋም ችግሮች እየተባባሱ ከመሄድ በስተቀር የሀገሪቱን ውስብስብ ችግር ሊፈታ አይችልም፤ምክንያቱም ኢህአዴግ አቅሙም ቁርጠኝነቱም የለውምና፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የታፈኑ ጩኸቶች ድምር ውጤት ድንገት ከፈነዳ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን(ምስራቅ አፍሪካን) ሊያናውጥ ስለሚችል ኢህአዴግና አመራሮቹ ከጭፍንና ግትር አቋም ወጥተው የህዝቡን ጥያቄ ማድመጥና ተገቢውን መልስ መስጠት፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ የተቆለፈበትን ነፃ ፕሬስ በተግባር ላይ እንዲውል ከፍተኛ የሆነ የወረቀት ታክስን ከማስቀረት በተጨማሪ ህዝቢ መረጃ የማግኘት መብቱ ያለምንም ገደብ እንዲከበር ማድረግ፣ ለአፈና የዋሉ ህገወጥ ህጎችን ማሻሻል/መሻር፣1 ለ 5 እያሉ የሚጠቀሙባቸውን ህገወጥ የአፈና መዋቅር መበተንና ማቆም፣ በህገመንግስቱ የተቀመጡ ያወጧቸውን ህጎች በማክበር ለሌሎች አርዓያ በመሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ በባዶ ሜዳ “በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እየሰራሁ ነው…” በሚል የእንቁልልጭ ፈሊጥ የዜጎችን መብት ማዳፈን የዲያቢሎስ የህልም ሩጫ ካልሆነ ለፖለቲካ ፍጆታ ተጀምረው ከመቆም ያለፈ ተፈፃሚ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከምንም ከማንም ቀድሞ መልማት ያለበት የዜጎች ነፃነት የተላበሰ የአስተሳሰብ አድማስ እንጂ ቁስ አይደለም፤ ቁሳዊ ልማቶች ሊሰሩ የሚችሉት በነፃና ጤናማ የዳበረ አስተሳሰብ ባለው የሰው ኃይል ነውና፡፡ ያኔ የምንመኘውና የሚዘመርለት ቁሳዊ ልማትም እውን ይሆናል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፐርቲዎችም ሆኑ ድርጅቶች ከእርስ በርስ መጠላለፍና ከፍርሃት ተላቀው ከቢሮ ፖለቲካ በመውጣት ሰላማዊ ትግል ምን እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ወደህዝቡ መውረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በየቢሮው በሚደረግ የድርጊቶች መቃወሚያ ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ለህዝብና ለሀገር ቆሜያለሁ ማለት ከቀን ቅዥት ባለፈ ጠብ የሚል ነገር ማምጣት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ትግል የተጠና ስልታዊ የተግባር ስራ እንጂ የወንበር ማድመቂያ አይደለምና፡፡ እዚህ ላይ ፖለቲከኞች አምነውበት እችላለሁ ብለው ወደፖለቲካው ትግል እስከገቡ ድረስ በሚከተሉት የትግል ስልት የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻል አለባቸው፤ ካልሆነ ግን ከትግሉ እራሳቸውን ማግለልና ለሚሰራ ሰው መስጠቱ ለፖለቶከኞችም ሆነ ለሀገሪቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን ወደባሰ ችግር ከመሄድ እራሱን ከፍርሃት ድባብ በማውጣት ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመቃወም ከድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋር ባለመተባበር የራሱን እርምጃ በመውሰድ ለመብቱ ሊሎች እንዲቆሙለት ከመጠየቅ ይልቅ ራሱ መታገል አለበት፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እያንዳንዱ ሰው እገሌ ምን ሰራ ከማለት በተጨማሪ እኔ ምን ሰራሁ በሚል ሁሉም የድርሻውን ካልተወጣ የችግሩ ማዕበል ሁሉንም እንደሚያጠቃ እሙን ነው፡፡ አሁን ባለው የመጠባበቅና የማጉረምረም እንዲሁም የመፈራራት ሁኔታ ችግሮችን ከማባባስ ባለፈ የሀገሪቱ ችግር በቀላሉ ይፈታል ማለት የህልም እንጀራ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱ ችግር ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ስለሄደ ሁሉም ዜጋ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊነጋገርና መፍትሄውን በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ ሊተጋ ይገባል፤አለበለዚያ የችግሮቹ መንስኤ ኢህአዴግም ሆነ ተጠቂው ህብረተሰብ ከሚመጣው አስከፊ የፖለቲካ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማምለጥ ስለማይቻል ስለሀገራችን ሁኔታ በግልፅ ሊመከርበትና መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፡፡
የነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ ይግባኝ ላይ ውሳኔ ተሰጠ
በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተመሰርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም 6 ኪሎ በሚገኘው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ውሳኔ ለመስጠት ለ5 ጊዜ ተደጋጋሚ ቀነ ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ሚያዚያ 24 ቀን 2005ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ላይ በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በአንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 24 ተከሳሾች መካከል ይግባኝ የጠየቁት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ሌላው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ናትናኤል መኮንን፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈ እና የቀድሞ ፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ አንዱዓለም አያሌው በተጨማሪ እውቁ የፖለቲካ ተንታኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ ዕድሜ ልክ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ 18 ዓመት፣ አቶ ናትናኤል መኮንን ላይ 18ዓመት፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም 15ዓመት፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈ 13ዓመት፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው 14ዓመት፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ 25ዓመት ፅኑ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሐሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2005ዓ.ም. የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ተከሳሾች በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ክስ የአቶ ክንፈሚካቼል ደበበን የቅጣት ውሳኔ ከ25ዓመት ወደ 16 ዓመት ዝቅ ከማድረግ በስተቀር ከላይ የተጠቀሱትን የሌሎቹን ይግባኝ ክስ ተቀባይነት ሳያገኝ የስር ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔን(ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ) እንዲፀና በመወሰን የፌደራሉ ማረሚያ ቤት ቅጣቱን እንዲያስፈፅም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በዕለቱ በችሎት ተሰይመው የነበሩትና ይግባኙን ሲመረምሩ የቆዩት ዳኛ ሽመክት አሰፋ፣ ዳኛ በላቸው አንሺሶ እና ዳኛ ዳኜ መላኩ ሲሆኑ የፍርድ ውሳኔውን በንባብ ያሰሙት የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ናቸው፡፡ ውሳኔው በንባብ ከመሰማቱ በፊት የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ተከሳሾችና የችሎት ታዳሚዎች ውሳኔው በሚሰማ ሰዓት ስነስርዓት እንዲይዙ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በችሎቱ ላይ ውሳኔውን ያነበቡት የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ በተደጋጋሚ የመጨናነቅ ስሜት የታየባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ፊታቸውን በመሃረም እየጠራረጉና ያነበቡትን አረፍተ ነገር በመደገሃገም ይቅርታ ያዘወተሩ ሲሆን የግራና ቀኝ ዳኞች የነበሩት ሽመክት አሰፋና በላቸው አንሺሶም በከፍተኛ ትካዜ ላይ ሆነው ተከሳሾችን በመመልከት የተለመደው የፊታቸው ገፅታ በወቅቱ አልነበረም ነበር፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ከፍተኛ የሚለውን ወደመካከለኛ ያወረደው መሆኑን፣ በተከሰሱበት 2ኛው ክስ ላይ ደግሞ ተከሳሾቹ በነፃ ያሰናበተ መሆኑን በመግለፅ ነገር ግን የቅጣት ውሳኔ ዓመቱ ላይ ምንም ለውጥ እንደማይኖረው አስታውቋል፡፡
በችሎቱ ላይ የተገኙት ተከሳሾች አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን እና አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹ አቶ አንዱዓለም አያሌው ፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈ እና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም ረቡዕ ሚያዚያ 23 ቀን 2005ዓ.ም. ይግባኝ ቀጠሮ እንዳላቸው እየታወቀ ወደ ዝዋይ ወህኒ ቤት በመወሰዳቸው ሊገኙ ባይችሉም በሌሉበት የይግባኝ ውሳኔው ተሰጥቷል፡፡ በሰዓቱ ከአቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ብቻ የተገኙ ሲሆን ከተከላካይ ጠበቆች አቶ አበበ ጉታ፣ አቶ ደርበው ተመስገን እና አቶ ሳሙኤል አባተ ተገኝተዋል፡፡
በመጨረሻም በውሳኔው ዙሪያ ከተከሳሾቹ መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ”እውነት ተደብቆ አይቀርም፣ይህን ህዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ…”፤ አቶ ናትናኤል መኮንን “መጀመሪያም ቢሆን የተከራከርናው ፍትህ እናገኛለን ብለን አይደለም” ሲል ባለቤቱ ወይዘሮ ፍቅርተ በበኩላቸው “እኔ ቀድሞውንም ለውጥ ይኖራል ብዬ አልጠበኩም” ብለዋል፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌ በበኩላቸው “…ፍትህ በኢትዮጵያሞተ ይህንንም ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ሊያውቀው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ችሎቱን ለመከታተል በርካታ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የተለያዩ ፖለቲከኞችና አድናቂዎቻቸው እንዲሁም የዓለም አቀፉ ዲፕሎማቶች የተገኙ ሲሆን ወደ ችሎት የገቡት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ በነበረው ሁኔታና በውሳኔውም በተለይ እጅግ ማዘናቸውንም ያነጋገርናቸው የታሳሪ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂዎቻቸው ገልፀዋል፡፡
ስለአቡነ ጴጥሮስ ፍቅር ስል…
በእውቀቱ ስዩም
ማለዳ መነሣት አልወድም፡፡ዛሬ ግን አቡነ ጴጥሮስ ከመታሰቢያቸው ዙፋን ሲወርዱ ለመታዘብ በማለዳው ካልጋየ ጨክኘ ወረድሁ፡፡ለአቡነ ጴጥሮስ ፍቅር ስል የማለዳ እንቅልፌን ብሰዋ አይቆጨኝም፡፡በቅርቡ በሚከፈተው ጦማሬ ላይ ስለ ጀግናው ጴጥሮስ በሰፊው የመጻፍ ሐሳብ አለኝ፡፡

በቦታው ስደርስ፣የጴጥሮስ ሀውልት በጣውላ ተገንዞ ቆሟል፡፡ድብርት ተጫጫነኝ፡፡ምናልባት አያቶቼ አቡኑ ሲረሸኑ በተመለከቱበት ሰአት የተሰማቸው ስሜት እንዲህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የራስ ቁር የደፉ የቀን ሠራተኞች በአቡኑ ትክሻ ላይ እንደ ወፍ ሰፍረዋል፡፡ ወደ መርካቶ በሚሄዱ ተሳፋሪዎች የተሞሉ ሚኒባሶች አደባባዩን ታክከው ሽው ይላሉ፡፡ ተሳፋሪዎቹ፣ በመስታውት አሻ…ግረው የሚመለከቱት ትእይንት ብዙ የመሰጣቸው አይመሰልም፡፡በፋሲካ አስፈሪ የዶሮ ዋጋ ለተጠመደ አእምሮ ታሪክ ምኑ ነው??
ከተመልካቹ በላይ የፖሊሱ ቁጥር የሚበልጥ መሰለኝ፡፡አንድ ፒካፕ መኪና ስትበር መጣችና ቁና ሙሉ ፌደራል ፖሊስ አራገፈች፡፡ሰብሰብ ብለን በቆምንበት አንዱ ፖሊስ ጠጋ አለና‹‹ እናንተን አይመለከታችሁም ከዚህ ሂዱ›› አለ፡፡ካጠገቤ የቆመ ጎበዝ ‹‹ማየት መብታችን ነው›› ብሎ መልሶ ጮከበት፡፡አሀ! የጴጥሮስ መንፈስ አልከሰመም ማለት ነው፡፡ፖሊሱ ምንም ሳይመልስ ከሬድዮ መገናኛው ጋር እየተመካከረ ካካባቢው ራቀ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጋዜጠኛ ጓደኞቼ ካሜራቸውን ታጥቀው ደረሱና ተቀላቀሉኝ፡፡ ሀውልቱን ማስቀረት ስላልቻሉ ምስሉን ቀርጸው ለማስቀረት ተሯሯጡ፡፡
ድንገት ቀና ብየ ሳይ ከሀውልቱ ፊትለፊት ጅማ በር የሚባል ፣ጣልያን የሠራው አሮጌ ሕንጻ ይታየኛል፡፡ባቡሩ የአቡነ ጴጥሮስን መታሰቢያ ደቅድቆ ሲያልፍ፣ጣልያን ሠራሹን ግንብ ንክች አያደርገውም፡፡ጉደኛ ባቡር!!!
በጣውላ የተገነዘውን የአቡኑን ሀውልት ለመሸከም አንድ አዳፋ ረጅም ተጎታች መኪና ብቅ አለ፡፡ዳይኖሰር የመሰለ ክሬን ሀውልቱን ነቅሎ ሲያንጠለጥለው፣ሀውልቱ የነበረበት ቦታ ጥርስ የወለቀበት አፍ መሠለ፡፡ቀሪውን የማየት ፍላጎት ስላልነበረኝ ከጓደኛየ ጋር ወደ ፒያሳ አቀናሁ፡፡ብዙ ነገር እዬተለወጠ መሆኑን አየሁ፡፡የጥንቱ መሀሙድ መዚቃ ቤት ወደ ቡቲክ መቀየሩን አስተዋልሁ፡፡የጥንቱ አያሌው ሙዚቃ ቤት ፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ ሆኗል፡፡ከጥቂት ወራት በፊት ብርቱካኔ የሚለው ሙዚቃ ይንቆረቆርበት የነበረው ቦታ ፣አሁን ብርቱካን በኪሎ ይሸጥበታል፡፡
አዲስአበባ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያለጥርጥር፣ባቡር ይኖራታል፡፡ቀለበት መንገዶች ይኖሯታል፡፡አሪፍ ህንጻዎች ይኖሯታል፡፡ነገር ግን፣ ትናንት የሚባለው ነገር አይኖራትም፡፡ A city without past ላዲስ አበባ የተገባ ቅጽል ነው፡፡
ወደ ሰፈሬ የሚሄድ ታክሲ ስፈናጠጥ፣ የሚከተሉት የጸጋየ ገብረመድህን ግጥሞች ሽው አሉብኝ፡፡
….መጭው ደመና ጥቁረቱ፣
ጮቁ ፣ማጡ፣የክረምቱ፣አቤት ዝቅጠቱ ማስፈራቱ
የኛስ ትውልድ አከተመ፣አገራችንን አምክነን
የነገስ ዘር ምን ይበለን፣ስንተወው ሲኦል አውርሰን
