Tag Archives: Journalist Bisrat Woldemichael

ይድረስ ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለኢህአዴግ አመራሮች!

ብስራት ወልደሚካኤል

afrosonb@gmail.com

 Image

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፤ ምንም እንኳ እናንተ ብዙውን ሰላም እየነሳችሁ ብታስቸግሩም፡፡ ዛሬ ግን እስኪ በእናንተ እና በቤተሰባችሁ ላይ እንዳይፈፀም የምትፈልጉትን በሌላው ላይ ስላደረጋችሁት ከብዙው አንዲት እውነት ብቻ አንስቼ ልጠይቃችሁ ወደድሁ፡፡ የጥያቄው መልስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለህሊናችሁ፣ እናንተ በምትመሩት አስከፊ፣ አፋኝ እና ጨቋኝ ስርዓት ሰለባ ለሆኑ እንዲሁም አሁንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተለመደውን እኩይ ተግባር ለምትፈፅሙባቸውና ለቤተሰቦቻችሁ ይሆን ዘንድም አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡

ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እርስዎ ተወልደው ባደጉበት የደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ቦለሶ ሶሬ ወረዳ መዲና በሆነችው አረካ ከተማን መቼም የሚረሷት አይመስለኝም፡፡ እርስዎ አሁን የደረሱበት የይምሰልም ይሁን ተግባር የጠቅላይሚኒስትርነት በትረ ስልጣን ከመጨበጦ በፊት እዛው አረካ ከተማ አካባቢ እንደ አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ በግብርና እርሻ ሙያ ዕየተዳደሩ ነው እንበል፡፡ ታዲያ በዚህ ሙያ ሳሉ ልክ አሁን እንዳሉት ባለትዳር እና የ3 ልጆች አባት ሆነው፤ እርስዎ በሚመሩት ኢህአዴግም ይሁን 24 ሰዓት በምትኮንኑት ደርግ ስርዓት አርዓያ “ሞዴል” አርሶ አደር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተብለው የትውልደ ቀዬዎትን ወክለው በደቡብ ክልል መንግስት ቢሸለሙ ምን ይሰማዎታል? ያው ደስታ እንደሚሉኝ አልጠራጠርም፡፡

አለበለዚያም ገበሬ ሆኜ አላውቅም ካሉም፤ ያኔ አርባምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ተቋም (የአሁኑ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተመረቁበት ሲቪል ምህንድስና(Civil Engineering) አሊያም ከፊንላንድ በተመረቁበት የአካባቢ ንፅህና ምህንድስና(Sanitory Enegineering) እስተማሩና እያስተዳደሩ ሞዴል መምህር ተብለው በወቅቱ ገዥ ስርዓት ቁንጮዎች ቢሸለሙ ምን ይሰማዎታል? አሁንም ያው ደስታ ነው እንጂ ሀዘን ሊሉኝ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው በሙያው ጥሮ ግሮ ላበረከተው አስተዋፅዖ እና ለሌሎች መልካም አርዓያ በመሆኑ የሚጠላ አይኖርምና፡፡ ይሄንን ምሳሌ ለራስዎ መቀበል ካልቻሉም ከቤተሰብዎ እጅግ መልካም ነው ብለው አብልጠው የሚወዱት ወንድምዎ ካሉም በእርስዎ ምትክ እርሳቸውን ተክተው እርስዎን በታዛቢነት ያስቀምጡ፤ ስሜቶንም ያሰላሱ፣ ይግለፁ፡፡

በሙያዎ  ለብዙ ዓመታት ሰርተው ለሌሎች አርዓያ ተብለው ሽልማት፣ እውቅና እና ሙገሳ ከተሽጎደጎደልዎ 3 ወር ሳይሞላ፤ ከትዳር አጋርዎ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እና የበኩር ልጅዎን ተማሪ ዮሐና ኃይለማርያምን ጨምረው ከሌሎች ልጆቾ ጋር አምላኬ በሰላም አሳድረኝ ብለው ተቃቅፈው ተኝተው በሸለሞት አካል አሸባሪ ተብለው ሌሊት በቤትዎና በቤተሰብዎ ላይ በ 16 “የፀረ-ሽብር” ግብረ ኃይል የጥይት እሩመታ ሲሰሙስ ምን ይሰማዎታል? አሁን ልክ እንደቅድሙ ደስታ ሊሉኝ አይችሉም፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ እርስዎን በቤተሰብዎ ፊት በሸለሞት አካል በ 16 ግብረ ኃይል ሽፍታ ነው ተብለው በክብር አርፈው ከተኙበት ቤት በሚተኮሱ የጥይት ናዳዎች በቤተሰብዎ ፊት ህይወትዎ እስከወዲያኛው ቢያልፍ እና እንደው ግማሽ ነብስ የለም እንጂ በከፊል ድርጊቱን ቢታዘቡት ምን ይላሉ; ከእርስዎ በተጨማሪ ለፍተው ጥረው ግረው ያቆሟት ቤት፣ ያፈሯቸው ላሞች ፣በጎችና በሬዎች በማያውቁት ነገር የጥይት ናዳ ሲያርፍባቸውስ;

ከላይ በተጠቀሱት ሳያበቃ ግብረ ኃይሉ አሁን የሰው ህክምና ሳይንስ የምታጠናው የበኩር ልጅዎ ተማሪ ዮሐና ሌሊቱን ገና በ8 ዓመቷ ከእቅፎ ተኝታ እርስዎ ሲገደሉ እርሷ የምትፅፍበት፣ አሊያም በትርፍ ጊዜዋ ከብቶች የምታግድበት ወይንም እንደሌሎች ህፃናት ከአቻዎቿ ጋር ለመጫወት የምትጠቀምበት የቀኝ እጇ ሙሉ ለሙሉ በጥይት ቢቆረጥስ ምን ይሰማዎታል? በዚህም ደስታ እንደማይሉኝ ግልፅ ነው፡፡ ልክ በውጊያ አውድማ እንዳለ ወታደር ከወላጆቿ እቅፍ ሳለች ቀኝ እጇ የተቆረጠችው ልጅ ስታድግስ ምን ይሰማት ይሆን? ፍርዱን ህሊና ላለው ሁሉ ልተወው፡፡

 ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች እና አባላት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ቢፈፀም ምን ይሰማችኋል; እናንተም ደስታ እንደማትሉኝ አልጠራጠርም፡፡ ይህንን ሁሉ የጠቀስኩት በማንም የሰው ሰብኣዊ የሰው ልጅ ላይ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት እንዲፈፀም ፈልጌ አይደለም፤ ይሄንንም አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ ሌሎች ግብር አበሮእዎ በቅን ልቦና እንድትረዱልኝ እሻለሁ፡፡

ክቡርነትዎ፤ ከላይ ብእርስዎ የጠቀስኩት ምሳሌ በሌላ ኢትዮጵያዊ ላይ በእናንተ ስርዓት አመራር የተፈፀመ እውነተኛ ድርጊት መሆኑንን ከዚህ እንደሚከተለው በአጭሩ ልነግሮት እወዳለሁ፡፡Image

ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አረቦር ቀበሌ ልዩ ቦታው ደቀፉቀር በሚባል ስፍራ  ከሌሊቱ 12 ሰዓት ከነ መላው ቤተሰቦቻቸው አምላኬ በሰላም አሳድረኝ ብለው የተኙ፤በእነ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስርዓት ሞዴል አርሶ አድር ተብለው የተሸለሙ ታታሪ ገበሬ አቶ ማስረሻ ጥላሁን  በ 16 የፀረ ሽብር ግብረኃይል በተተኮሱ የጥይት ናዳዎች እዛው እቤታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ የሚያሳዝነው ለግድያ የተላከው ግብረ ኃይል አቶ ማስረሻን ከገደሉ በኋላም በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ተከታታይ የጥይት ናዳ በማውረድ ቤታቸውን የጥይት ጌጥ ሲያደርጉት ጥረው ግረው ያፈሯቸው ከብቶችንም ከመግደል እና ከማቁሰል አልቦዘኑም ነበር፡፡ የሚገርመው እንዴት የአንድ ሰው መኖሪያ ቤት የቀድሞ የአድዋ ወይም ባድመ፣…የውጊያ ስፍራ ሊመስል እንደቻለ ግልፅ አይደለም፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ እጅግ የሚዘገንነው እና የሚያሳዝነው በተመሳሳይ ሰዓት የአቶ ማስረሻ ጥላሁን የ 8 ዓመት ልጅ ስለእናት ማስረሻ እዛው በሞት ከተነጠቀው ወላጅ አባቷ እና በፀረ ሽብር ግብረኃይል ከተሸበሩ ምስኪን ቤተሰቦቿ እቅፍ ሆና ሲነጋ ጥቅምት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ከአቻዎቿ ጋር ትምህርት ቤት ስለመሄድ እና ስለመጫወት ስታልም ብዙ ስራዎችን የምትሰራበት ቀኝ እጇ በግብረ ኃይሉ ጥይት ሙሉ ለሙሉ ተቆርጧል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በእርስዎ እና በግብር አበርዎ የሚመራው ኢህአዴግ ሞዴል አርሶ አደር ያላችኋቸውን አቶ ማስረሻ ጥላሁንን በ 16 “የፀረ ሽብር” ግብረ ኃይል ለማስገደል በወረዳውና በዞኑ አመራሮች ሽፍታ ነው የሚል ለባለቤታቸውና በህይወት ለተረፉ ልጆቻቸው መልስ ተሰጥቶ ፍትህ እንጦርጦስ ገብቷል፤ ቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ እስካለ ፍትህ እና ርትዕ ከማግኘት ሰማይ ቤት ደርሶ መመለስ የቀለለ ይመስል ሰው ተስፋ ቢቆርጥም፤ ለወጉም ቢሆን ፍርድ ቤት መኳተኑ አልቀረም፡፡ ነገር ግን እሮጣ ያልጠገበች፣ክፉና ደጉን የማታውቅና ቂም በቀል የሌለባት፣ ዓለማችንንም ይሁን ሀገራችንን ኸረ እንደውም አካባቢዋን በቅጡ ለይታ የማታውቅ የ 8 ዓመቷ ህፃን ስለእናት ማስረሻ ጥላሁንን ምን ብላችሁ ይን እጇ እንዲቆረጥ የተደረገው? ነው ወይስ ይህቺን ህፃንም ሽፍታ ነች ልትሉን ነው? ኸ…ረ…ረ..የፍትህ ያለህ፣…የህፃን ልጅ ያለህ፣…ቢያንስ ሰብዓዊነት እንኳ እንዴት ይሳናችኋል?

እስኪ አቶ ኃይለማርያም ስለእናት ማስረሻ ላይ የተፈፀመው በእርስዎ የበኩር ልጅ ዮሐና ኃይለማርያም ላይ ቢፈፀም ምን ይሰማዎታል; ስለ እናንተ ልጆች እንደምታስቡ ሁሉ ስለሌሎች ህፃናት ያላችሁ አስተሳሰብና አመለካከት ወይም ግንዛቤ የት ድረስ ነው? ዛሬ በዚህ ግፈኛ ስርዓት ቀኝ እጇ የተቆረጠው ስለእናት ማስረሻ ነገ እንደማንኛውም ልጅ አራሷን፣ ቤተሰቧን፣ ሀገሯን ብሎም የዓለምን ማኀበረሰብ ልታገለግል ምትችል፣ ብዙ ተስፋ የሰነቀች ነች፡፡

አሁን ግን ገና የ !ኛ ክፍል ትምህርቷን  በጀመረች አንድ ወር ከአስር ቀን የመመህሮቿን የፊደል አጣጣል ትዕዛዝ የምትቀበልበት ቀኝ እጇ ገና ከጅምሩ ተቆርጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰኞ ማክሰኞ እያለች ትምህርቷን መከታተል ሲገባት ፍትህ አጥታ ከምትኖርበት ዳባት ወረዳ፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ከዚያም የአማራ ክልል ፍትህ ፅፈት ቤት እስከ ህፃናት ጉዳይ በጥይት ናዳዎች ከተረፉ ቤተሰቦቿ ጋር ፍትህን ፍለጋ እየተንከራተተች ትገኛለች፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ልጅ ዮሐና ኃይለማርያም በተደላደለ ሰላም፣ ጤናና እና ሁኔታ የህክምና ትምህርት ትከታተላለች፣ የብአዴኑ ሊቀመንበር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ልጆችም የተሸለ ትምህርት ቤት ከዚሁ ደህ ህዝብ በሚገኝ ገንዘብ ይማራሉ፣ የአቶ በረከት ስምዖንን ፣ የዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የአቶ ሙክታር ከድር፣ የነ ሀሰን ሽፋ፣ የነ ጌታቸው አሰፋ ፣ የነ አያሌው ጎበዜ፣ የነ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የነ ግዛቱ አብዩ እና የሌሎች የኢህአዴግ ሹማምንት ልጆች በህዝብ ሃብት ተንደላቀው በተመቻቸ ሁኔታ ይማራሉ፡፡  የዳባት ወረዳ ነዋሪዋ ህፃን ስለ እናት ማስረሻ ደግሞ ለትምህርት ባልተመቻቸ ሁኑታ እንኳ የጀመረችውን ትምህርት እንዳትማር ቀወላጅ አባቷን በግፍ ከማጣቷ በተጨማሪ ቀኝ እጇን ተቆርጣ ፍትህን ፍለጋ ትኳትናለች፡፡

ታዲያ ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች የኢህአዴግ ሹማምንት ሆይ፤ የምትመሩት ስርዓት በህፃናት ስም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረብጣ ዶላሮችን እንደሚያገኝ የምትዘነጉት አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በህፃናቱ ስም የሚመጣው እርዳታ ቢያንስ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ባይችል እንኳ ለምን አንዲትን ህፃን በፀረ-ሽብር ግብረኃይል በጥይት ለማስመታት ዋለ? በዚህች ህፃን ልጅ እና ወላጅ አባቷን ጨምሮ በቤተሰቦቿ ላይ የተፈፀመው ግፍ የት ድረስ ያስኬዳችኋል? ይህችን ደብዳቤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አቶ ኃለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ይህቺ ደብዳቤ ደረሳችሁ ሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች ፤ ስለ ህፃናት ልጆቻችሁ፣ ስለ እናቶቻችሁ ፣ ስለሚስቶቻችሁ እና ስለራሳችሁ ብላችሁ የዚህቺን ህፃን እና ቤተሰቦች ጊዜ ሳትሰጡ ፍትህን ፍለጋ እየደከሙ ነውና ፍትህን ይሻሉ፡፡

እነ አቶ ኃለማርም ደሳለኝ የእውነት ከልብ አዝናችሁና እና ተሰነምቷችሁ ፍትህን መስጠት ከቻላችሁ የድርጊቱ ፈፃሚዎች  ብዙ በምታወሩበት ኢቴቪና  በሌሎች መድረኮች ሌሎች አመራሮችም ሆኑ ህዝብ እንዲማሩበት ጭምሩ ተገቢው ፍርድ በግልፅ በአደባባይ ሊሰጥ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ የሴቶች እና ህፃነት ጉዳይ ቢሮዎች፣ አቃቤ ህግ፣ ጠበቆች ፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት የድርሻችሁን ትወጡ ዘንድ ተግባሩ የት አለ? ስል መልሳችሁን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

ታህሣሥ 2006 ዓ.ም.  ተፃፈ

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

ወጣቱ ወዴት እየተመራ ነው?

ብስራት ወ/ሚካኤል

ልማት ትርጓሜው እጅግ ሰፊ ቢሆንም ጥቅል ሐሳቡ ግን ለሰው ልጆችም ሆነ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ በማኀበረሰቡ ዘንድ ይሁንታን ያስገኘ ለኑሮ ተስማሚ ሁኔታን በመፍጠር ውጤታማ የሆነ ተጨባጭ እውነታን ያዘለ ክንውን ነው፡፡ ይህም ሰብዓዊና ቁሳዊ ይባላል፡፡ ይህን በተመለከተ በተለይ ሰብዓዊ ልማት የሚባለው ቁሳዊ የሚባለውን ልማት ሊያመጣ የሚችል የሰው ልጆች የባህሪ አስተሳሰብ አዎንታዊ ለውጥ ነው፡፡ ይህ ለውጥ የማኀበረሰቡን በጎ አሴቶችን አጠናክሮ በመቀጠል አሉታዊ የሚባሉትን በማረምና አዳዲስ አዎንታዊ ለውጦችን ከልማዳዊ አኗኗር ጋር በማስማማት በስልጣኔ ቀላልና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ ያኔ ቁሳዊ ልማቱን በሚፈለገው ደረጃ ማምጣት ይቻላል፡፡ የዚህ ልማት ውጤታማ ተግባርና የስልጣኔ ዝመና ሽግግር ትልቁን ሚና የሚጫወተው ወጣቱ ሲሆን ለዚህም አበረታች የሞራል ስንቅ ያስፈልጋል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ከሀገሪቱ አብላጫው የህዝብ ቁጥር ልቆ የሚታየው ወጣቱ ነው፡፡ የዛን ያህል ደግሞ ከምርታማነት ይልቅ ጥገኛ እንዲሆን የተፈረደበት ይመስላል፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን ተስኖት ሌሎች የሚመርጡለትን፣ የመረጡለትን በመጠበቅ ጊዜውን ሲያባክን ይታያል፡፡ ይህ ማለት ግን አኩሪ ተግባር እየፈፀሙ ያሉ ወጣቶች ጭራሽ የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ከለው ቁጥር አንፃር ሲታይ አብዛኛው ወጣት በብዙ ነገሮች ጥገኛ እንዲሆን በመገደዱ እራሱን እንዳይመለከት ጋርዶታል፡፡
ድሮ ድሮ እንኳን ስለራሱ፣ ስለሀገሩ ከዛም አለፍ ሲል ስለሌሎች ይጨነቅ የነበረው ወጣት ዛሬ ስለራሱ በራሱ መወሰን ተስኖት የተመረጠለት ካልተስማማው የመጨረሻ ምርጫውን ስደት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በዚህም መሐል ህጋዊና ህገወጥ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለስደት የዳረገውን ምክንያት ግን ደፍሮ የሚገልፅ አካል አልተገኘም፡፡ እንግዲህ እንዲህ የተፈረደበትን ወጣት ሀገር እያሳጡት ሀገር ተረካቢ እየተባለ ይቀለድበታል፡፡
ወጣትነት እጅግ ፈተና የበዛበት የተፈጥሮ የእድሜ ሂደት አካል ቢሆንም በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ግን ከየትኛውም የዕድሜ ክልል የተሻለ ነው፡፡ የመኖሪያም ሆነ የመዋያ ምርጫው በሌሎች መልካም ፈቃድ ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ በተለይ በኢትዮጵያ ያለው ክስተት ወጣቶች ሆን ተብሎ ምርታማ እንዳይሆኑ የሚሰራ ይመስላል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆነን ዘንድ ጥቂቶቹን እንይ፡፡
የወጣት ማዕከላት
ቀደም ባለው የደረግ ስርዓት ግልፅና ቀጥተኛ ሶሻሊስት የነበረ ቢሆንም ወጣቱን በእስፖርትና በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለማጎልበት ይረዳ ዘንድ በርካታ የተለያዩ የወጣት ማዕከላት ነበሩ፤ አሁን በነበሩ ቀረ እንጂ፡፡ በወቅቱ በተለያዩ ከተሞች ከስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ እስከ ሙዚቃና ቴአያትር (ድራማ መለማመጃ) በየከተማ ቀበሌው ይገኝ ነበር፡፡ለወጣቶቹ ታስቦ በተሰሩት ሜዳዎችና አዳራሾች ወጣቱ በአግባቡ ይጠቀምበት የነበረ ቢሆንም ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነፃ የሐሳብ መንሸራሸርን በተመለከተ ግን ከስርዓቱ ውጭ እንደማይፈቀድ በግልፅ ስለሚታወቅ ጎጅ ቢሆንም ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡
ዛሬ ደግሞ በአንፃሩ የነበሩ ሜዳዎች ዳግም ባናያቸውም በወጣቱ መዝናኛ ሰም የኢህአዴግ ካድሬ መመልመያ ሆነው አርፈዋል፡፡ የወጣት ማዕከል ተብሎ በተሰሩ አዳራሾች ምንም ከቀድሞ የተለየ ነገር የለም፡፡ ምክንቱም ዛሬም በአዳራቹ ስለ ኢህአዴግ ጥሩነት ለማውራትና የርካሽ ባዶ ፖለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን ውጭ ወጣቱ ነፃ የሆነና ያመነበትን ርዕስ አንስቶ መወያየት አይችልም፡፡ ይህ የሆነው ግን በህግ ሳይሆን ከመጋረጃ በስተጀርባ ባልተፃፈው ትዕዛዝ ነው፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ የቀበሌ አዳራሾች ቢገነቡም እየሰጡት ያለው አገልግሎት ግን ሁሉንም ወጣት ሊያካትት በሚችል የተለያዩ ሐሳቦች ሊንሸራሸሩ በሚያስችል ሁኔታ ሳይሆን በኢህአዴግ ጥላ ለተሰበሰቡት ብቻ ነው፡፡ እንዲህም ቢሆን የሚሰጡት አገልግሎት ቢበዛ ቤተመፅሐፍ፣ ጂም እና የገላ መታጠቢያ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህም የወጣቱ ፍላጎት በሁሉም የአዲስ አበባ ከተማም ይሁን በሀገር አቀፍ ምርጫው ሁሉን ያሳተፈ የወጣቱ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ወጣቱ በፍላጎቱ በልማት ላይ ተሳታፊ ነው ማለት አይቻልም፡፡ምክንያቱም ቁሳዊ የአዳራሽ ግንባታ የወጣቱን አስተሳሰብ በመቀየር ሰብዓዊ ልማት ማምጣት አልቻለምና፡፡
አስተሳሰብን ያህል ነገር ሁሉም በሌሎች ፍላጎትና ምርጫ ተፈጥሮን በሚሽር መልኩ አንድ እንዲሆን እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎዓዊ የተደረገበት አሳታፊ ቁሳዊ ልማትን ማምጣት አይቻልም፡፡ ሰርተናል እየተባለ የሚዘፈንለት ቁሳዊ ልማትም ቢሆን የወጣቱን የመንፈስ ልዕልና ሊገነባ ባልቻለበት ሁኔታ በሀገሪቱ ላይ ሁለንተናዊ እምርታ ለውጥ ማየት ይናፍቃል፡፡ ቀድሞ በየአካባቢው የነበሩ ሜዳዎችም ቢሆኑ አንዳንዶቹ በነበሩበት ቢቀጥሉም አብዛኞቹ ባለመኖራቸው፣ አዳዲስ የመኖሪያ ቤት ግንባታ የተደረገባቸውም ሆነ እየተደረገባቸው ያሉ አካባቢዎች የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያዎች ባለመታየታቸው ዋቱን ወደ አልባሌ ቦታ እንዲውል እያስገደዱት ይገኛሉ፡፡
ጎጂ የደባል ሱስ ግብዣ
በአሁን ሰዓት ወጣቱ በራሱ ጉዳይ እራሱ እንዲወስን ከማድረግ ይልቅ በደባል ሱስ ጥገኛ እንዲሆን የሺሻና ጫት ግብዣ እየቀረበለት ይገኛል፡፡ ይሄም በፊት እንደ ነውር ይታይባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሳይቀር ዛሬ ዛሬ እንደመልካም እየታየ እስከ ዩኒቨርስቲዎች መዝለቁ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነኚህን ድርጊቶች የሚያበረታታ የመንግስት አካል ባይኖር ኖሮ መኖሪያ መንደር ድረስ ዘልቀው ባልታዩ ነበር፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም የተመረቁና የሚመረቁ ወጣቶችም ቢሆኑ ከ15ዓመታት በላይ በእውቀት ግብይት በትምህርት ቢያሳልፉም ዛሬ ግን 15 ቀናት በማይፈጅ ስልጠና ያውም ጥቂቶችን በኮብል ስቶን ድንጋይ ጠረባ ስራ እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡ በርግጥ ማንኛውም ሙያም ሆነ ስራ የሌሎችን ሰዎች መብትና ጥቅም እስካልነካ ድረስ የሚናቅ ባይሆንም ለዘመናት ያካበቱት እውቀት ግን ሜዳ ላይ ሲወድቅ የሀገር ሀብት በከንቱ መባከኑን ማሳየቱ አይቀርም፡፡ በአሁን ወቅትም የያዝነው 2005ዓ.ም.ን ጨምሮ በየዓመቱ ከ 80 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ወጣቶች በተለያየ የትምህርት ዘርፍ ቢመረቁም በሙያቸው የሚሰማሩት ግን 10ሺህ እንዳማይሞሉ ይገለፃል፡፡ ይሄ ደግሞ የእውቀት፣የገንዘብና የጉልበት ብክነት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
በሙያቸው ተደራጅተው የስራ ዕድል እንዳይፈጥሩም ስርዓቱ እና የስነ ህዝብ ፖሊሲው ዜጎችን ሙሉ በሙሉ የመንግስት ኢኮኖሚ ጥገኛ ስላደረገ በሚፈልጉት ሙያ መሰማራት አይችሉም፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ የገንዘብ ብድር ቢፈልጉ እንኳ የግድ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ተቀብለው በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በኢህአዴግ አባልነት ቅድመ ሁኔታ በየቀበሌ ያሉ ተራ ካድሬዎች ከላይ በሚወርድ መመሪያ መሰረት ለማደራጀት ይሚክራሉ፡፡ ውጤቱ ግን ወጣቱን አምራች ኃይል ከማድረግ ይልቅ የሙያና የኢኮኖሚ ነፃነት ስለሌለው ጥገኛ እንዲሆን አስችለውታል፤እያስቻሉትም ነው፡፡ ይሄ ካልተቀየረ ደግሞ የሀገሪቱ ወጣት ጊዜውን፣እውቀቱንና ጉልበቱን በከንቱ እንዲያባክን ያደርጉታል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በየመንደሩ እየፈሉ ያሉት የአልኮል መጠጥ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች አንዱ የልማት አካል እንጂ የሰብዓዊ ልማትን ወደ ኋላ የሚያስቀር ተደርጎ አልተወሰደም፡፡ በዚህ ምክንያት ወጣቱ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ የሰራበትንም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውል ምቹ ሁኔታ እንኳ ሲፈጠርለት አይታይም፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ለወጣቱ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆኑ የሚታወቁት የሐሳብ የበላይነት ላይ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ቦታ ባለመሰጠታቸው እንደ ሚዩዚክ ሜዴይ የመሳሰሉት የንባብን ባህል ለማዳበር የሚረዳው የመፅሐፍ ሐሳብ መወያያ አዳራሽ አጥተው አምስት ኪሎ በሚገኘው በጠባቧ ብሔራዊ ሙዝየም አዳራሽ ማየት ልማት ወዴት ወዴት ያሰኛል፡፡ ባንፃሩ አብዛኛውን ጊዜ የገዥው ኢህአዴግ ካድሬዎች መፈንጫ እየሆነ ያለውና በህዝብ አንጡራ ሃብት የተገነቡት የቀበሌ/የወረዳ አዳራሾች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ከኢህአዴግ ስራና ካድሬዎች በስተቀር ኸረ የሰው ያለህ እያሉ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ለሰብዓዊ ልማት ትኩረት ባለመሰጡ ነገ ሀገር ተረካቢ በሚባለው ወጣት ላይ ይነገድበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፊት የወጣቶች መዝናኛ የነበሩ የስፖርት ሜዳዎችና የመናፈሻ ቦታዎች አንዳንዶቹ የህንፃ ግንባታ ሲሰራባቸው እንደነ ሂልተን አዲስ ሆቴል ፊትለፊት የነበሩ መናፈሻዎች ደግሞ ተከልለው ወጣቶች ዝር እንዳይሉባቸው ተደርገዋል፡፡
ከሌሎች መጠበቅንና መቀበልን መምረጥ
የተሻለ ነገርን በራስ ከመወሰን፤ እንዲሳካም ከመጠየቅ ይልቅ በሌሎች ላይ ጥገኛ በመሆን በሁሉም ነገር የመጠበቅና የመቀበል ብቻ አዝማሚያ በስፋት በወጣቱ ያስተዋላል፡፡ በዚህም የራሱን ጉዳይ ሌሎች እንዲወስኑለት በመፍቀዱ የራሱን ሚና አሳልፎ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ምርጫውን ከመፈለግ ይልቅ የመጣውን ብቻ የመቀበል ጉዳይ በስፋት ይስተዋላል፡፡
አማራጭ ሐሳቦችን ከራስ ጋር አስማምቶ ለመያዝም ሆነ የራስን ምርጫ ለማስተናገድ ይረዳ ዘንድ ነፃ የሆነ የሐሳብ ፍጭት ዕድል በመነፈጉ አሉታዊም ቢሆን ተቀብሎ የራስ ማድረግ እንደ አዋቂነትና ብልህነት እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ የትውልድ የአስተሳሰብ ብክነትንና ምክነትን በማንፀባረቅ ተተኪው ትውልድ ከማለት ይልቅ ጠባቂው ቢባል የሚስማማው ይመስላል ፡፡
ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በተለይ በወጣቶች ላይ እየተሰራ ያለው ሰብዓዊ ልማት በቁሳዊ በመሸፈኑ የሚመጣ ኋላቀር እሳቤ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዥው ስርዓት የልማትን አስፈላጊነትና ምንነት በቅጡ ካለመረዳት የሚመጣ ደጋማ እሳቤ ሲሆን እራሱ ወጣቱም ቢሆን በእራሱ ላይ አሉታው ድርሻ እንዳለው ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ስለዚህ እምርታዊ |የሀገር ዕድገትና ለውጥ ለማምጣትና ሁሉን አቀፍ ገቢራዊ ልማት ለማስመዝገብ ቅድሚያ ሰብዓዊ ልማት መቅደም ይኖርበታል፡፡ ያኔ ቁሳዊ ልማትን በሚፈለገው መጠንና ዓይነት ማምጣት ይቻላል፡፡

የ‹‹ደሃው›› አቶ መለስ 3 ቢሊዮን ዶላር የት ነው?

ቴዎድሮስ ባልቻ

አቶ መለስ ዜናዊ የእረፍታቸው ዜና ከተነገረ በኋላ በህይወት ሳሉ የሌላቸውን ባህርይ ሳይቀር በመግለፅ ደጋፊዎቻቸው ጣዖት ማምለክ እስኪመስል ድረስ እንዲመለኩ ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን አቶ መለስ የኢህአዴግ ደጋፊዎች የሚያወሩላቸውን ያህል ግለሰብ ስላለመሆናቸው የማይረሱ በርካታ ስራዎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን አንዳችም ጥሩ ስራ የላቸውም ማለት ሳይሆን በንፅፅር ሲቀርብ ግን ጥሩ መሪ ነበሩ ማለት በገለልተኛ አካላት ሰፊ ጥናት መደረግ ያስፈልገዋል፡፡

 melesአመራሮቹማ ከቤተ መንግስት እስከ ገጠር ቀበሌ የእሳቸውን ሞት ተከትሎ ምስላቸውን የያዙ ፖስተሮች መለጠፋቸው ሰውየውን ‹‹ቅዱስ›› ለማስመሰል ከመሞከር ባለፈ ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ያሳብቃል፡፡ ይህንን ለማርከስም ሆነ ህዝቡ ስለ እሳቸው ትክክለኛ ማንነት እንዲያውቅ አማራጭ የሀገር ውስጥ ነፃ ሚዲያ ያለመኖር በመጋረጃ ውስጥ ያሉት መለስ ተዘንግተዋል፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ ስለሳቸው ትክክለኛ ማንነት የተወሰኑ ተግባራቸው የአደባባይ ምስጢር ቢሆንም እሳቸው ከሚያደንቋቸው የውጭ ሚዲያ መዳሰሱ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በቅርቡ የዓለም መሪዎችንና ባለሃብቶችን ሃብትና የግል ታሪክ በማስነበብ የሚታወቀው ድህረ ገፅ ስለእሳቸው በአጭሩ ያስቀመጠውን እንመልከት፡፡ የመረጃው መረብ ሰውዬውን ከልደት ዘመን እስከሞታቸው ከመግለፁ በተጨማሪ አንድ አስደንጋጭ (ለኢህኢዴግዎች) መረጃም አክሎበታል፡፡ ይህም ያላቸውን የሃብት መጠን ከዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከከል ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትርና የታወቁ ባለሃብት ከሆኑት ሲልቪዮ በርሎስኮኒ በመቀጠል በ3 ቢሊዮን ደላር (56 ቢሊዮን ብር ገደማ) 2ኛ ደረጃን እንደያዙ www. therichest.org በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም http://www.therichest.org/celebnetworth/politician/minister/meles-zenawi-net-worth/ መጎብኘት ይቻላል፡፡

በተለይ ነገሩን አስደንጋጭና አሳፋሪ የሚያደርገው በህይወት ያሉት ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በባህርዳሩ የኢህአዴግ ጉባዔ ሳይጠየቁ የአቶ መለስን ድህነት ሲናገሩ ነበርና፡፡ ያኔ ባለቤታቸው ከመንግስት መደበኛ 6 ሺህ ብር ደመወዛቸው ላይ ተቆራርጦ 4 ሺህ ብር ያህል እንደሚደርሳቸውና በዚህም ይተዳደሩ እንደነበር መግለጣቸው አይዘነጋም፡፡ በርግጥ ያኔ ባለቤታቸው የተናገሩትን ህዝቡ ተቀብሏቸዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም 21 ዓመታትን ሙሉ ያለመላከ ሞት ከቤተመንግስት አልወጣም ብለው የመሸጉትን የህዝብና የሀገርና የወገን ፍቅር ኖሯቸው እንዳልነበረ እንቅስቃሴያቸው ያሳብቅ ነበርና፡፡

  ‹‹ደሃው ›› አቶ መለስ

ዛሬ እንደጣዖት ፎቶአቸውን በየቦታው ተለጥፎ የምናገኛቸው አቶ መለስ ዝናዊ  ምናልባት በመሪ አስተሳሰብ ካልሆነ በቀር በገንዘብ በኩል ደሃ ነበሩ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ያለባህርበር ከማስቀረት አልፈው በታሪክ የኢትዮጵያ እንደሆነ የሚታወቀውን አሰብ ወደብንና አካባቢውን ትውልዱ ያንን እንዳያስብ በማድረግ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስንቶች የሞቱለትን የሀገሪቱን ሰንደቅዓላማ ‹‹ጨርቅ ነው›› ብለው አራክሰዋል፡፡ የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው ሲሉም ከመናገር ያለፈ የአስተሳሰብ ድህነት የለም፡፡

እሳቸውም በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው እንደድሮ (ጫካ ሳሉ) እንደማይርባቸውና የቆሸሸ እንደማይለብሱ ከማስታወስ ውጭ በገንዘብ በኩል ያኔ ደሃ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ እውነታው ግን ያ ስለመሆኑ ህዝቡ መርምሮ እንዲያውቅ ዕድል አልሰጡትም፡፡ ዛሬ ግን ተከታዮቻቸው ከእራሳቸው አልፈው መላው ህዝብ ንፁህና ቅዱስ አድርጐ እንዲመለከታቸው በየመድረኩ የሚነገረው አሰልቺ ወሬ ገመናቸውን ሊደብቅ እንደማይችል የተረዱት አይመስልም፡፡

በተለይ በገንዘብ ደረጃ ምንም ያልነበራቸውና ይሄንንም ራሳቸው የተናገሩ ቢሆንም ስለ እሳቸው ዝርዝር የህይወት ታሪክ በግልፅ በማስቀመጥ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ መሆናቸውን ግን በህይወታቸውም ሆነ በሞታቸው አላስተባበሉም፡፡ ስለዚህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በባዶ እጃቸው ጫካ ገብተው የወጡት አቶ መለስ ነግደው ሳያተርፉ ቢሊየነር ባለጠጋ የሆኑት ከህዝብ ሃብት ዘርፈው ካልሆነ ከየትም ሊያመጡ እንደማይችሉ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሰውዬው ይወራ እንደነበረው ዓይነት እንዳልሆኑ ውሎ ሲያድር እየጠራ ነው፡፡

 የግል ማኀደራቸው በአጭሩ

አቶ መለስ (ለገሰ) ዜናዊ በወርሃ ግንቦት 1947 ዓ.ም. በአድዋ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአድዋ ንግስት ሳባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲከታተሉ የሁለተኛ ደረጃን አዲስ አበባ በሚገኘው ጀነራል ዊንጌት ተከታትለው በመጨረስ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በቀድሞ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በሁለተኛው ዓመት አቋርጠው ወደጫካ ከመግባታቸው ውጭ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ማጠናቀቃቸውን የሚገልፅ የምስክር ወረቀት የላቸውም፡፡

ነገር ግን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በምን ዘርፍ፣ ከየትና መቼ እንዳገኙ የሚያሳይ ማስረጃ እስካሁን ባይገለፅም ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር ማስተርስ ዲግሪ ማግኘታቸው ተገልጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከሚገኘው ኤራስመስ ዩኒቨርስቲ  በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት ከመሆን ውጭ በትምህርት ሌላ ደረጃ እንደሌላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 አቶ መለስ ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ጋብቻ በመመስረት ሰናይ፣ ሰመሃል እና ማርዳ የሚባሉ የሶስት ልጆች አባት እንደሆኑም በመካነ ድሩ የመረጃ መረብ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በመጨረሻም ለ21 ዓመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ 57 ዓመታቸው ነሐሴ 14 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም (እንደ መንግስት ገለፃ) መሞታቸውን፤ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ እንደነበሩ ደግሞ http://www.therichest.org›› የተሰኘው ድህረ- ገጽ በግልፅ አስፍሯል፡፡

ሌላው ደቀመዝሙሩ ከመምህሩ እንደሚማር ሁሉ የታችኞቹ ሙሰኞች መሰረት የላይኞቹ ባለስልጣናት ልምድና ተሞክሮ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች›› እንዲሉ የታችኞቹ ሙሰኞች (ከቀበሌ እስከየ መስሪያ ቤቶች ባለስልጣን) ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስን እና መሰሎቻቸውን ፈለግ ተከትለው  ባይተማመኑ እነ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በቤታቸው የዶላርና የብር ክምችት ባልተገኘ ነበር፡፡

 ስለዚህ በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ተግባር በእጅጉ ለመቀነስ ከተፈለገ ወኔውና ድፍረቱ ካላቸው አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝና የፌደራሉ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ በ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ እንደሆኑ ከተነገረላቸው ከቀድሞው የቤተመንግስት የስልጣን ባህታዊ ከሆኑት ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን እስከ ሚኒስትሮችና የጦር ጀነራሎች መዝለቁ የግድ ይላል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው አቶ መለስ አላቸው ከተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር ውጭ የሃብት ምንጫቸው ያልታወቁ ጊዜ አመጣሽ ከበርቴዎችን መዳሰሱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ በዚህም አለ የተባለው ሃበት እውነትነት መርምሮ ለህዝብ የማሳወቅም ግዴታ አለበት፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሀገሪቱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት በወረቀት በህገመንግስቱ ከማስፈር ውጭ በተግባር የሚረጋገጥ ከሆነ በርካታ የሙስና ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ የኮሚሽኑንና የሌሎች የፍትህ ተቋማትን ስራ ያቀላል፡፡

 ከዚህም በተጨማሪ ከመካላከያ ሚኒስቴር፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች)፣ የከተማ መስተዳድሮች ውስጥን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉ የብልሹ አሰራሮች ምን ያህል ለሙስና እንደተጋለጡም የፌዴራሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት የመረጃ ዘገባዎችን /ሪፖርቶቹን / እንደግብዓት መጠቀም አስፈላጊ ቢሆንም እስካሁን በተግባር የታየ እርምጃ ግን የለም አለበለዚያ እንደ ዳዊት ‹‹ሙስና›› እያሉ መደጋገሙና ትናንሾቹ ላይ ብቻ ጃስ ማለት የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ከማስቀየር ባለፈ ለሀገርና ለህዝብ ሃብት ተቆርቋሪነትን አያሳይም፡፡

 እሳቸውስ ሞቱ 3 ቢሊዮን ዶላሩስ?

በተለይ ወደ ፖለቲካው የሀገር አስተዳደርነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የሳይንሱን ትምህርት በርቀት ሳይሆን በመደበኛ ተከታትለው የህግ ምሁሩና ድምፃዊ የነበሩት የኤሲ ሚላኑ እግርኳስ ክለብ ባለቤት ከሆኑት ከ76 ዓመቱ የጣሊያኑ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሎስኮኒ የ6 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ቀጥለው ከጫካ በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን የወጡት አቶ መለስ በ3 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛነትን ይዘዋል፡፡ በመቀጠልም የሊባኖሱ የሐርቫርድና የቤሩት ዪኒቨርስቲ ምሩቅና ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተለያዩ ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት የ57 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ አዝሚ ሚካቲ በ 3 ቢሊዮን ዶላር 3ኛነትን ይዘው ይከተላሉ፡፡

 አቶ መለስ ግን ከጫካ ወደ ፖለቲካ ስልጣን ከመውጣት ውጭ የተጠቀሰው ሃብታቸው ከየት መጣ? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ህዝብ ከሚያውቀው እውነታ ውጭ እሳቸውም ምንም እንደሌላቸው ከመሞታቸው በፊት ተናግረዋልና፡፡ በጣም የሚገርመው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ዊሊያም ዶናልድ ካሜሩን እንኳ ያላቸው ሃብት ሲታይ  6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ እንደሆነ እና የዚህም ሃብታቸው ምንጭ ፖለቲካ እንደሆነ ድህረ-ገፁ ሲጠቁም የአቶ መለስ ዜናዊ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ምንጭም ፖለቲካ እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚህም ሟቹ አቶ መለስ ይህን ያህል ሃብት በፖለቲካ ስራ ባለቤት ከሆኑ የሌሎቹ ባለስልጣናት ቢጣራ ስንት ይሆን የሚል ጥያቄን ከማስነሳቱ በተጨማሪ ሀገሪቷ ምን ቀራት ያሰኛል፡፡

 በርግጥ የአቶ መለስንና ባለቤታቸውን ከፍተኛ ባለጠግነትን (ቢሊየነርነትን) በተመለከተ ምስጢራዊ መረጃዎችን በመልቀቅ የሚታወቀው  ‹‹wikleaks›› የተሰኘው ድህረ- ገፅ ‹‹Ethiopian Super rich persons›› ሲል የተለያዩ የቅርብ ወዳጆቻቸውን የቃለመጠይቅ ምስክርነት ማስረጃ ሳይቀር አስደግፎ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ‹‹therichest›› ድህረ – ገፅ ያላቸውን የገንዘብ መጠን 3 ቢሊዮን ዶላር ብሎ ባይገልፅም ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለጠጋ መሆናቸውን አልሸሸገም ነበር፡፡

 በአሁኑ ሰዓት አቶ መለስ ሞተዋል፤ አላቸው የባለው 3 ቢሊዮን ዶላርስ የት ገባ? ምን እየሰራስ ነው? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ቢሆንም እዚህ ላይ ቀን ከሌት ስለመለስ ሙገሳና አድናቆት አውርተው የማይጠግቡት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያ ደሳለኝ ከባድ የቤት ስራና ፈተና ነው፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ የፌደራሉ የሥነ – ምግባርና ፀረ – ሙስና ኮሚሽን ቁርጠኝነትንና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የአቶ መለስ አላቸው የተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር የት እንዳለና ምን እየሰራ እንደሆነ ከነምንጩ ከመረጃ መረቦቹም ሆነ በራሳቸው ዘዴ አጣርተው የመግለፅ ትልቅ ፈተና ይጠበቅባቸዋል፡፡

 የገንዘቡ መገኘት ከተረጋገጠ በኋላም ገንዘቡ ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ ተነጥቆ የተዘረፈ ስለመሆኑ ማንም ሊጠራጠር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከራስ በላይ ምስክር የለምና ሁለቱም የህወሐት ኢህአዴግ እና የሀገሪቱ የስልጣን ቁንጮዎች በገንዘብ አቅም ድሃ ስለመሆናቸው ተናግረዋልና፡፡ ስለዚህ እነኛ ታማኝ የመረጃ ምንጮች የገፁት በተለይ ‹‹therichest›› ያሰፈረው 57 ቢሊዮን ብር (3 ቢሊዮን ዳላር ) ወደ ተዘረፈው ህዝብ ተመልሶ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል፡፡

 ‹‹ ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው››

 አበው ሲተርቱ ‹‹ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው ›› ይላሉ፡፡ ዓሳ ከምግቦች ሁሉ የተሸለና ሁሉንም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ተወዳጅ ምግብ ቢሆንም ለምግብነት ከመሰናዳቱ በፊት ከመኖሪያው ውሃ ውስጥ እንደወጣ የማይወደድ ሽታ አለው፡፡ የዚህ ‹‹መጥፎ ሽታ›› መነሻው ደግሞ ጭንቅላቱ እንጂ ሌላው አካሉ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ በዚህም ዓሳ ከውሃ ውስጥ ከወጣ በኋላ ያለው መጥፎ ጠረን ጭንቅላቱ ስለሆነ ተቆርጦ መጣል እንዳለበትና ያኔም ሌላው አካሉ ከመጥፎ ሽታ እንደሚፀዳ አመላካች ንግግር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ስላለው ቅጥ ያጣ የሙስና ተግባርም ሆነ ብልሹ አሰራር መነሻው ገዥው ኢህአዴግና ቁንጮዎቹ እንደሆኑ የሰሞኑ መረጃ በራሱ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ከሚኒስትር አቶ መላኩ ፈንታና ረዳታቸው የሙስና ተግባር መጠርጠር በተጨማሪ በወ/ሮ አዜብ መስፍን ‹‹ድሃ›› ስለመሆናቸው የተመሰከረላቸው ግን በዓለም 2ኛው ባለጠጋ ጠቅላይ ሚኒስትር(በ3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር) እንደሆኑ የተነገረላቸው ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ አለ የተባለው ሃብት ምንነት ካልተጣራና ካልተመለሰ የመንደር ሌቦችን ብቻ ማሳደድ ሙስናን ሊገታ አይችልም፡፡

 ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት(ሰኔ በ2005ዓ.ም.)

 

 

እውን የሀገሪቱ ችግር እንዲህ በቀላሉ ይፈታ ይሆን?

ብስራት ወልደሚካኤል

afrosonb@gmail.com

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ከዕለት ወደዕለት እየባሰበት በመሄዱ የችግሮቹን ውስብስብነት ከመባባሱ በስተቀር ለነዋሪው የፈየደ አንዳች የመፍትሄ ሐሳብም ሆነ ተግባር የለም፡፡ ችግሮቹ በገጠርም ሆነ በከተማ ተባብሰው በመቀጠላቸው ከብዛታቸው አንፃር በተናጥል መጥቀሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሉ ከሚባሉት መካከል  የተወሰኑትን ችግሮች እንኳ ለማየት እንሞክር፡፡

በአዲስ አበባ ያለው የመጓጓዣ እጥረት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱ እስካሁን መፍትሄም ሆነ ትኩረት ስላልተሰጠው  የሀገሪቱ ሃበት ላይ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበትና የሞራል ኪሳራ ማድረሱ አይቀሬ ቢሆንም “እኛን ብቻ አድምጡን፣ ችግራችሁን ደብቁትና ቁጭ በሉ፣ ግዴታችሁን ተወጡ እንጂ መብታችሁን አትጠይቁ!” በሚል ግትር አቋሙ የፀናው የኢህአዴግ መንግስት ችግሩን የመፍታት አቅም እንደሌለው ያረጋገጠ ቢመስልም የስልጣን ጥሙ ግን ቀፍድዶ ይዞታል፡፡ በዚህም ምክንያት የታክሲ ሰልፉ፣ የከተማ አውቶቡስ፣ የሎንችንና የሃይገር ግፍያን ጨምሮ የመንገዶች መጨናነቅን ላየ እውን በሀገሪቱ መንግስት አለን? ያስብላል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ የመጣ እንጂ ቅፅበታዊ ክስተት አይደለም፡፡

ምናልባት አሁን እየተሰራ ያለው የከተማ ውስጥ ቀላል የባቡር ሃዲድ ግንባታና አገልግሎት እየተካሄደ ነው፣ ይሄ ሲጠናቀቅ ችግሩ ይፈታል የሚል መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ሊኖሩ ቢችሉም የባቡር አገልግሎት ቢጀመርም የነዋሪው ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሩን ሊፈታ የሚችለው ብቃት ያለው አመራር መኖርና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ህዝብን ያላማከለና ያላሳተፈ ስራ ግልፀኝነት ስለሌለው ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር ውጭ የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ለመፍትሄው ከህዝብ ጋር በግልፅ መድረክ መወያየቱ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡

የኑሮ ውድነቱ አንዱ ዋነኛ ችግር ሲሆን ለዚህም መንግስት እንዳሻው የሚያደርገው የገበያ ጣልቃ ገብነትና የዋጋ ተመን ዕቃ እንዲጠፋና ጥራታቸው የጎደሉ ሸቀጦች ለህዝቡ ኢንዲደርሱ ከማድረጉ በተጨማሪ ወደፊት በውድድር ገበያ ዋጋቸው የሚወርዱ ዕቃዎች ባሉበት በመቀጠል ወደፊት በዛው ዋጋቸው እየጨመረ እንዲሄድ ያስገድዳል፡፡ ስለዚህ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣትና መንግስት እጁን ከገበያ ማውጣት ካልቻለ ችግሮቹ ከአሁን በባሰ እንደሚቀጥሉ ጥርጥር የለውም፡፡

በክልል ከተሞችና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ያለው የኢህአዴግ ቅጥ ያጣ አፋኝነት(በአዲስ አበባ የለም ማለቴ አይደለም) ህዝቡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጭ መብቱን እንዳይጠይቅ በመደረጉ ችግሮች ሳይባባሱ በጊዜ እንዳይታረሙ በመደረጉ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሰቆቃ ህይወት እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በተለይ ገበሬው ያልፍላጎቱና ያለ አቅሙ ለግብርና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች( ማዳበሪያ፣ አረም ማጥፊያ፣ ዘር) ኢህአዴግ በተመነው ከፍተኛ ዋጋ እንዲገዙ በመደረጉ ምርቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ሸጠው ለኢህአዴግ በመክፈል፤ መሬት እያላቸው እንደሌላቸው በመሆን  የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገበሬውም በንብረቱ የማዘዝ ስልጣኑ በመገፈፉ የእኔነት ስሜት ስለማይኖረው ውጤታማ ስራ ሊሰራ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡ የዚህ ችግር ደግሞ ከባዶ የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ በስተቀር  በምግብ እራሷን እንዳትችል ያደረጋት ከመሆን ባለፈ ድሬ በምግብ እራሳቸውን የቻሉ ገበሬዎች ዛሬ ለልመና ወደ አዲስ አበባና ትላልቅ የክልል ከተሞች ጎዳና በመውጣት ለልመና ተዳርገዋል፡፡

በሀገሩቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ከፍተኛ አምራች ኃይል የሆኑት ወጣት ምሁራን ከዩንቨርስቲ ተመርቀው ወጥተው በሙያቸው እራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ማኀበረሰቡንና ሀገራቸውን ማገልገል ሲገባቸው አነስተኛ የትምህርት እድል ያላቸው ዜጎች ሊሰሩት የሚገባውን የድንጋይ ፈለጣ(ኮብልስቶን ስራ) ላይ እንዲሰማሩ በመደረጉ ለትምህርት ያወጡት፣ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ሞራል በከንቱ እንዲባክን ተደርጓል፡፡ የዚህም ውጤት የሀገሪቱ ዜጎች ተስፈኛ ከመሆን ይልቅ ተስፋ ወደመቁረጥ በመዳረጋቸው ለተለያዩ ጎጂ ሱሶች ተጋልጠው በየመንገዱ ሲንቀዋለሉ ላየ “የየት ሀገር ቱሪስቶች ናቸው?” ሳያስብል አይቀርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ  አስከፊ የስደት መንገዶችን ምርጫ በማድረግ የሚሞቱ ወጣት ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ በመሄዱ “ሀገሪቱ እውን መንግስት አላትን?” ያስብላል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ምክንያት ገዥው ኢህአዴግ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲና ግትር አቋም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በመላው ሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከትን እንደሆነ በዓለም ላይ እጅግ አምባገነንና ጨቋኝ መንግስት መኖሩን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ቢቻልም ይበልጥ ግን ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሊያገለግሉ የሚገባቸው፣ ከየትኛውም የፖለቲካና የግለሰብ ተፅዕኖ ገለልተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው የዴሞክራሲያዊ ተቋማት (የፍትህ አካል የሆኑ  ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃይሎች፣…) በኢህአዴግ መዳፍ ወድቀው ወገንተኝነታቸው ለፍትህ፣ ለህግና ለህዝቡ ከመሆን ይልቅ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወገንተኛ በመሆናቸው የሀገሪቱን ችግር ይበልጥ ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል፡፡ በዚህም በህግ የተሰጣቸውን መብት የተጠቀሙና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የጠየቁ በርካቶች ወደ ወህኒ ቤት ተወርውረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ጋዜጠኞች(እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፣ የሱፍ ጌታቸው፣…)፣ፖለቲከኞች(አንዱዓለም አራጌ፣ናትናኤል መኮንን፣በቀለ ገርባ፣ኦልባና ሌሊሳ፣…)፣ የኃይማኖት ነፃነት መብት እንዲከበር የጠየቁ (የሙስሊሙ  ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ የዋልድባ መነኮሳት፣…) ይገኙበታል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ኢህአዴግ “ለስልጣኔ ያሰጉኛል” በሚል ብቻ በሀገር ስም ክስ ስለመሰረተ ሁሉም ተከሳሾች ወንጀለኛ የሚባሉ ሲሆን  በአንፃሩ በኢህአዴግ ባለስልጣናትና አባላት በደል ተፈፅሞባቸው “የፍትህ ያለ” የሚሉ “ፍትህ በኪሴ ብይን” ተሰጥቷቸው በኋላ ወንጀለኛ እንባላለን በሚል በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት በማጣታቸው “የማርያም ጠላት” የሚባሉ በርካቶች ናቸው፤እነኚህንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ የተፈቀዱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የመሰብሰብ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞን የመግለፅ፣…በሙሉ ባልተፃፈና ባልታወቀ ህግ የተሻሩ ሲሆን ይበልጥ እነኚህ እንዳይተገበሩ ለገዥዎች ብቻ በሚመች ህገመንግስቱን በግልፅ የጣሱ በርካታ አንቀፆችን የያዘ የፀረ ሽብር አዋጅ በማውጣት ተጨማሪ የአፈና ገደቦች ተጠለዋል፡፡ የእነኚህ አፈናዎች ውጤት ችግሮች በጭሩና በቀላሉ እንዳይፈቱ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ እጅግ የታፈነ ቁጣ እንዲኖር አስችሎታል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ወደፊት በሀገሪቱ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግልፅ ቢሆንም ኢህአዴግ በያዘው ግትር አቋም ችግሮች እየተባባሱ ከመሄድ በስተቀር የሀገሪቱን ውስብስብ ችግር ሊፈታ አይችልም፤ምክንያቱም ኢህአዴግ አቅሙም ቁርጠኝነቱም የለውምና፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የታፈኑ ጩኸቶች ድምር ውጤት ድንገት ከፈነዳ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን(ምስራቅ አፍሪካን) ሊያናውጥ  ስለሚችል ኢህአዴግና አመራሮቹ ከጭፍንና ግትር አቋም ወጥተው የህዝቡን ጥያቄ ማድመጥና ተገቢውን መልስ መስጠት፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ የተቆለፈበትን ነፃ ፕሬስ በተግባር ላይ እንዲውል ከፍተኛ የሆነ የወረቀት ታክስን ከማስቀረት በተጨማሪ ህዝቢ መረጃ የማግኘት መብቱ ያለምንም ገደብ እንዲከበር ማድረግ፣ ለአፈና የዋሉ ህገወጥ ህጎችን ማሻሻል/መሻር፣1 ለ 5 እያሉ የሚጠቀሙባቸውን ህገወጥ የአፈና መዋቅር መበተንና ማቆም፣ በህገመንግስቱ የተቀመጡ ያወጧቸውን ህጎች በማክበር ለሌሎች አርዓያ በመሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ በባዶ ሜዳ “በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እየሰራሁ ነው…” በሚል የእንቁልልጭ ፈሊጥ  የዜጎችን መብት ማዳፈን የዲያቢሎስ የህልም ሩጫ ካልሆነ ለፖለቲካ ፍጆታ ተጀምረው ከመቆም ያለፈ ተፈፃሚ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም  ከምንም ከማንም ቀድሞ መልማት ያለበት የዜጎች ነፃነት የተላበሰ የአስተሳሰብ አድማስ እንጂ ቁስ አይደለም፤ ቁሳዊ ልማቶች ሊሰሩ የሚችሉት በነፃና ጤናማ የዳበረ አስተሳሰብ ባለው የሰው ኃይል ነውና፡፡ ያኔ የምንመኘውና የሚዘመርለት ቁሳዊ ልማትም እውን ይሆናል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፐርቲዎችም ሆኑ ድርጅቶች ከእርስ በርስ መጠላለፍና ከፍርሃት ተላቀው ከቢሮ ፖለቲካ በመውጣት ሰላማዊ ትግል ምን እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ወደህዝቡ መውረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በየቢሮው በሚደረግ የድርጊቶች መቃወሚያ ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ለህዝብና ለሀገር ቆሜያለሁ ማለት ከቀን ቅዥት ባለፈ ጠብ የሚል ነገር ማምጣት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም  የፖለቲካ ትግል የተጠና ስልታዊ የተግባር ስራ እንጂ የወንበር ማድመቂያ አይደለምና፡፡ እዚህ ላይ ፖለቲከኞች አምነውበት እችላለሁ ብለው ወደፖለቲካው ትግል እስከገቡ ድረስ በሚከተሉት የትግል ስልት የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻል አለባቸው፤ ካልሆነ ግን ከትግሉ እራሳቸውን ማግለልና ለሚሰራ ሰው መስጠቱ ለፖለቶከኞችም ሆነ ለሀገሪቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን ወደባሰ ችግር ከመሄድ እራሱን ከፍርሃት ድባብ በማውጣት ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመቃወም ከድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋር ባለመተባበር የራሱን እርምጃ በመውሰድ ለመብቱ ሊሎች እንዲቆሙለት ከመጠየቅ ይልቅ ራሱ መታገል አለበት፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እያንዳንዱ ሰው እገሌ ምን ሰራ ከማለት በተጨማሪ እኔ ምን ሰራሁ በሚል ሁሉም የድርሻውን ካልተወጣ የችግሩ ማዕበል ሁሉንም እንደሚያጠቃ እሙን ነው፡፡ አሁን ባለው የመጠባበቅና የማጉረምረም እንዲሁም የመፈራራት ሁኔታ ችግሮችን ከማባባስ ባለፈ የሀገሪቱ ችግር በቀላሉ ይፈታል ማለት የህልም እንጀራ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱ ችግር ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ስለሄደ ሁሉም ዜጋ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊነጋገርና መፍትሄውን በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ ሊተጋ ይገባል፤አለበለዚያ የችግሮቹ መንስኤ ኢህአዴግም ሆነ ተጠቂው ህብረተሰብ ከሚመጣው አስከፊ የፖለቲካ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማምለጥ ስለማይቻል ስለሀገራችን ሁኔታ በግልፅ ሊመከርበትና መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፡፡

ማፈናቀሉ እስከመቼ?

ብስራት ወልደሚካኤል

ህወሓት/ኢህአዴግ በህይወቱ ከሚፈራውና ከሚጠላው ነገር አንዱ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ዜጋ ማየትና መስማት ነው፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱ አባላት በባህሪያቸው በውሸት፣ በተንኮልና በዕውቀት አስተሳሰብ አድማስ ደካማ ስለሆኑ የዜጎችን አንድነትና ብሔራዊነት ስሜትን አጥብቀው ይጠላሉ፤ ይህንንም በማሰራጨት የማሃይሞችን ርካሽ ፖለቲካ አራምደውበታል፣እያራመዱም ይገኛሉ፡፡ የዚህ ዋነኛ ተባባሪ ደግሞ በህወሓት የሚነዱት ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የሀገሪቱን አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ በመጣላቸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዝምታ ሊያልፍ ስለማይገባ እስካሁን ለፈፀሙት ሁሉ አስፈላጊውን ሰነድ በእጃችን ማስገባት፣ ድርጊቱን የፈፀሙትንና ተባባሪዎቹን ስም ዝርዝር ከነ ሙሉ አድራሻቸው መያዝ፣ ጉዳት የደረሰባቸውና ሚደርስባቸው ዜጎችን መርዳትና መንከባከብ እንዲሁም ወንጀለኞችን በተለያዩ ማኀበራዊ ሚዲያዎች(Facebook, blog, twitter,….) ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በማጋለጥ ለህግ እንዲቀርቡና ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ የሁላችንም ኢትዮጵያዊያን የውዴታ ግዴታ መሆን ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በሰፊው የአማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ላይ በህወሓት/ኢህአዴግ  እየደረሰ ያለው ግፍ በተመሳሳይ መልኩ ነገ በሌሎችም ላይ ይደርሳል፤ ከዚህ በፊትም ደርሷልና፡፡

ስለዚህ በቅርቡ በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ለረጅም ጊዜ ሀብት ንብረት አፍርተውና ተዋልደው የኖሩ የአማርኛ ተናጋሪዎችን የማፈናቀል ስራ የተሰራውን መረጃ በሚመለከት ፣

አሁን ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ እንዲፈናቀሉ የተደረጉት የአማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ለሞት.ለስቃይና ለመከራ እንዲደረጉ የተደረገበትን ምክንያት በዝርዝር በማጣርት መረጃውን ይፋ በማድረግ ሁሉም ዜጋ በጋራ ሊያወግዝና የተፈናቀሉትም ወደነበሩበት ስፍራ በክብር እንዲመለሱ ለማድረግ በሀግር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም በሀገር ውስጥ ያሉ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ወደስፍራው በመሄድ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ መረጃውን ለህዝብ ይፋ ማድረግና የድርጊቱ ፈፃሚዎችም በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ፣

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በማጋለጥ ለኢህአዴግ የሚደረገው የለጋሾች ድጋፍ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚውል ማረጋገጥና ድጋፉ እንዲቋረጥ ከማድረግ በተጨማሪ መረጃውን ለሚሰበስቡ  ሀገር ውስጥ ላሉ ሀገር ወዳድ ሰባዓዊ ባለሙያዎች የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የሙያ ድጋፍ ማድረግ፣

በተለይ ወንጀሉ የሚፈፀምባቸው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖቻችን ወኪል ነኝ የሚለውን ብአዴን/ኢህአዴግ አባላት ጉዳዩን አጥብቀው በመጠየቅ ለድርጅቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ በማቋረጥ ለህዝብ እና ለሀገር ያላቸውን ወገንተኝነት ማረጋገጥ፣ ከፓርቲውም በይፋ በመልቀቅ ህዝባዊ ዓላማ ያለውን ትግል መቀላቀልና የወንጀል ተባባሪ አለመሆናቸውን በተግባር በማሳየት ከነገ ተጠያቂነት እራሳቸውን ነፃ ማድረግ፣

የሌላው ማኀበረሰብ ኢትዮጵያዊያን ድርጊቱን በጋራ በማውገዝ አሁን እየተፈፀመ ያለው ዘግናኝና አሰቃቂ ወንጀል ወደ ሌሎችም መዛመቱ ስለማይቀር “ማፈናቀሉ እስከመቼ?” በሚል ሁሉም በጋራ በመንቀሳቀስ በራሱ ተስፋ የቆረጠውን ዘረኝነት አገዛዝ እርቃኑን በማስቀረት ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በማፅናት የዜጎች ሰብዓዊ መብት በሙሉ መከበሩን ለማረጋገጥ የዜጎች ከሀገራቸው መፈናቀል፣ መሰደድ፣ በግፍ መታሰርና መገደል ማብቃት አለበት እላለሁ፡፡ አለበለዚያ ነገ ሁላችንም ከሀገራችን መፈናቀላችን አይቀሬ ስለሆነ ዛሬውኑ ቆም ብለን በማሰብ ማድረግ ያለብንን መወሰን ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ማንም ኢትዮጵያዊነታችንን ሲፈልግ ወስዶ እንካችሁ፤ ሳይፈልግ ዜግነታችሁን እኔ የምሰጣችሁ ስፍር ብቻ ነው ሲሉ መፍቀድ ባርነትን ከመምረጥ ውጭ  ምን ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን? እኔ በበኩሌ ባርነትን በፍፁም አልመርጥም፣ አልደግፍምም፡፡

%d bloggers like this: