ፍርድ ቤቱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ላይ ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮዎችን ሰጠ
∙ለጥር 7 እና ለጥር 26/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡
ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ የስድስት ተከሳሾችን ሁለት ጉዳዮች ለማየት ነበር ችሎቱ የተሰየመው፡፡
አንደኛው ጉዳይ ተከሳሾቹ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ተከትሎ ማረሚያ ቤቱ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የሰጠውን ትዕዛዝ በተመለከተ መልስ ለመስማት ነበር፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርበው ስለነበር በክስ መቃወሚያቸው ላይ አቃቤ ህግ የሚሰጠው የመቃወሚያ መቃወሚያ ካለ ለመስማት ነበር፡፡
በመሆኑም አንደኛው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ በወረቀት ተገልብጦ ስላልደረሰ ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግን የተከሳሾች መቃወሚያ ላይ የቀረበ መቃወሚያን ተቀብሏል፡፡ በመሆኑም በተከሳሽ መቃወሚያ ላይ የቀረበውን የፌደራል አቃቤ ህግ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ
24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን ባህር ሰጥመው ሞቱ
ባለፈው ሰኞ ታህሣሥ 20 ቀን 2007 ኣ.ም. በጀልባ ወደ የመን ሊገቡ የሞከሩ 24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቻ በምትባል የየመን ወደብ ከተማ አቅራቢያ በደረሰባቸው የጀልባ መስጠም አደጋ መሞታቸውን የየመን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለፃ ከሆነ በጀልቧ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ በህይወት የተረፉ ስለመኖራቸውም ሆነ በአደጋው የሞቱትን በለመለየት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተደረገ ጥረት አለመኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በቅርቡ ህዳር 28 ቅን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ በየመን የወደብ ከተማ በሆነችው ሞቻ አቅራቢያ 70 ኢትዮጵያውያን በሚጓዙበት ጀልባ በደረሰ አደጋ ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ባህር አቋርጠው የምን ሊገቡ ሲሉ ህይወታቸው ላለፈው 94 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በአቅራቢያው ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንፅላ ፅህፈት ቤት አምባሳደሮች ያሉት ነገር የለም፡፡ በየ ዓመቱ የህንድ ውቅያኖስን እና ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው ወደ የመን ሊገቡ የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እየሞቱ ቢሆንም አደጋውን ለመቀነስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመንን ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር ለመሸጋገር የሚጠቀሙባት በመሆኑ የስተኞች ጣቢያ እንደማይመዘገቡና እገዛም እንደማይደረግላቸው ተጠቁሟል፡፡ የመን ባህር አቋርጠው ከሚገቡ አብዛኞቹ ስደተኞች መካከል ጥቂቶች ብቻ በተለይም በፈረንጆቹ 2014 መጨረሻ የመን በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን እገዛ የተደረገላቸው 9,500 ኢትዮጵያውን እነደነበሩ የድርጅቱ መረጃ አመልክቷል፡፡
ከመንግስት በሚደርስባቸው የፖለቲካ ጫና እና በሀገሪቱ ከተከሰተው የኢኮኖሚ ችግር በተፈጠረው የኑሮ ውድነት የተነሳ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር በየ ዓመት እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል፡፡
እናታችን ፋናዬና ጋዜጠኛ ተመስገን በዝዋይ…
ታሪኩ ደሳለኝ
(የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም)
ያቺ የስምጥ ሽለቆ ከተማ ይበልጥ መንደድ ከጀማመራት አንድ ወር አልፏታል:: በፍትህ መዛባት ስሜቱ የተጎዳ፣ በወገኖቹ ስቃይ መንፈሱ የታመመ፣ ሀገራቸውን ከስቃይ መታደግ በሚችሉበት እድሜያቸው በታሰሩ፣ በተሰደዱና በተገደሉ ወገኖቹ ልቡ ያዘነ፣ ለሀገሩና ለባንዲራው ያለው ፍቅር ጥልቅ የሆነ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በውስጧ ይዛለች፡፡ ዝዋይ፡፡
ከዚህች ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው የዝዋይ እስር ቤት ለመሄድ የአስፓልት ዱካ እንዳረፈበት በሚያሳብቀው ኮሮኮንቻማ መንገድ ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ከረጅም ዓመታት በፊት ተሰርቶ ዛሬ አስታዋሽ ያጣው ይህ ጎዳና እስረኞችን የመጠየቁን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከፀሐዩ ግለት ትይዩ ያለው የመሬቱ አቧራ በእግሩ ቆሞ ይሄዳል ብል አይበዛበበትም፡፡ ይህን አልፈን ግዞት ቤቱን እናገኛለን፡፡ የእስር ቤቱን መግቢያ ያለበሰው አቧራ ደግሞ ቅጥሩን በቁፋሮ የተገኘ ጥንታዊ ከተማ አስመስሎታል፡፡ የግቢው ገፅታ ለዕይታ በማይስቡ ነገሮች ቢከበብም፣ ተናፋቂውን ብዕረኛ ግን ደጋግሜ እንድጠይቀው ከወንድምነት የሚዘለው ጥንካሬው ይስበኛል፡፡
በአቧራውና በንዳዱ መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀድሞ ይልቅ በጠነከረ ፅናቱ ስለመኖሩ ሳስብ ደስተኛ እሆናለሁ፡፡ እናታችንስ ምን ታስብ ይሆን? የማይበርድ፣ የማይዳፈንና የማይጠፋ የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከአቧራውና ከንዳዱ በላይ መሆኑ ለእርሷ ምን ስሜት ያጋባባታል?
እናታችንና ተሜን ሲገናኙ…
ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 20/07 ዓ.ም ነው፡፡ እናቴ አብረዋት ከኖሩ ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን፣ ዝዋይ እስር ቤት ከከተመ አንድ ወር ያለፈውን ተመስገንን ልታየው ተሰናድታለች፡፡ ዝዋይ ከሄደ ወዲህ አይታው አታውቅም፡፡ እንደናፈቃት ግን የፊቷ ገፅታ ይመሰክራል፡፡ እንደ ልጅነቱ ፀጉሩን ባትደባብሰውም፤ እጁን ልትነካውና በዕርጅና አንደበቷ ‹እንዴት ነህ?› ልትለው ወደዚያው እያቀናች ነው፡፡ ጠዋት ወጥተው ማታ እንደሚገቡት፣ ክፍለ-ሀገር ሰንብተው እንደሚመለሱት እንደ ጓደኞቿ ልጆች ተመስገን እንደማይመለስ የተረዳችው እናታችን ልጇ ጋር እየሄደሰች ነው፡፡
ለሊት 11፡30 ከጀሞ ኮንዶሚኒየም የተነሳችው መኪና ዝዋይ የደረሰችው ከጠዋቱ 2፡20 ላይ ነበር፡፡ አስፋልት መሰል ፍርስራሽ መንገዱን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ዛሬ አልሰጠኝም፡፡ ፍተሻውን አልፈን እስረኛና ጠያቂ የሚገናኘበት ቦታ ላይ ደረስን፡፡ ከነበርነው ሰዎች ይልቅ እናታችን ጉጉት እንዳደረባት ለመናገር ሁኔታዋን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡
እናታችን ተመስገን በልጅነቱ ከዕኩዮቹ ጋር ተጫውቶ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ስራ ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፤ አንዳንዴም ሲያመሽ ደውላ ‹‹አልመሸም፤ የቀረው ለነገ ይቆይህ›› ትለዋለች፤ እርሱም ሁሌ እንደሰማት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ልጇን የምትጠብቀው ከትምህርት ቤት አልያም ከጨዋታ ወይም ከስራ አይደለም፡፡ ከእስር ቤት ውስጥ እንጂ!
እናታችን እስረኞች ከሚወጡበት በር ላይ ከተቀመጠችበት ደቂቃ ጀምሮ አይኗን አላነሳችም፡፡ በሩ ሲከፈት የወታደር ልብስ የለበሰ ወጣት ወጣ፡፡ ከወታደሩ በኋላ ተሜ እስካርፉን እንዳደረገ ተከተለ፡፡ እናቴ ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ ዐይኗቿ እንባ አዘሉ፡፡ በዕስረኛና በጠያቂ መሀል ያለውን አጥር ተደገፈች፡፡ ሌላ ጊዜ አጥሩን መደገፍ የሚከለክሉት ወታደሮች እናታችንን ግን ጥቂት ታገሷት፡፡ ምን ያድርጉ? እነሱም እኮ እናት አላቸው፡፡ ከተመስገን ኋላ ሌላ ወታደር አለ፡፡ በሁለት ወታደሮች መካከል ሆኖ ተሜ እናቱን አያት፤ ፈገግ አለ፡፡ እየቀረበ ሲመጣ ግን ፈገግታው ከፊቱ ላይ ጠፍቶ በሀሳብ ተተካ፡፡ እናቴን በዚህ እድሜዋ አንከራተትኳት ብሎ እንዳላሰበ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ከዚህ ይልቅ ስንትና ስንት እናቶች በየቦታው እየተንከራተቱና እየተሰቃዩ ስለመሆናቸው እያሰበ የተጨነቀ ይመስላል፡፡ እናትና ልጅ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ቆዩ፡፡ ምን አለ ባይለያዩ? እንዲሁ እንዳሉ ወደ ቤት ቢሄዱስ ምን ነበረበት?
ይሄ ግን አይሆንም፤ ይሄ ቦታ ተሜ ለሀገሩ የከፈለውን፣ እየከፈለ ያለውንና የሚከፍለውን መስዋዕትነት ማቅረቢያው ቦታ ነው፡፡ ተሜ ወደ ቤት አይሄድም፡፡
ተሜና እናቴ የተጫወቱት ብዙ ነው ፡፡ ሲገናኙ የነበረው ድባብ ጠፍቶ ሁለቱም ደስ ብሏቸዋል፡፡ ተሜ ትንሽ አይቷት ‹‹ከስተሻል›› ሲላት ፈገግ እንዳለች ‹‹አረ አልከሳሁም፤ አንተ ግን ጤናህ እንዴት ነው?››፤ ‹‹ደህና ነኝ››… እናቴ በየመሀሉ ጨዋታቸውን ገታ እያደረገች በስስት ታየዋለች፡፡ እናትና ልጅ የሆድ የሆዳቸውን እንዲያወሩ የፈቀዱት ወታደሮችም ሁለቱን በስስት የሚያዩ ይመስላሉ፡፡
ሳይታወቀን 6፡00 ሆነ፡፡ የመሰነባበቻ ጊዜ ደረሰ፡፡ እናቴ እየሳቀች አቀፈችው፤ ተሜም እየሳቀ ተሰናበታት፡፡ እንደ አመጣጡ በሁለቱ ወታደሮች መካከል ሲሄድ ከጀርባው ትክ ብላ አየችው፡፡ የሆነ ነገር ልትል የፈለገች ትመስላላች፡፡ ‹‹ተመስገን›› አለች፤ አልሰማትም፡፡ በሩን አልፎ ገባ፡፡ እሱ ፊት የደበቀችውን እንባ ማቆም አልቻለችም፡፡ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ከፈገግታዋ ጋር አለቀሰች፡፡
እሁድ ህዳር 21/07 ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት፡፡ እናቴ ልጇ እስኪፈታ አልጋ ላይ አልተኛም ብላ መሬት መተኛት ከጀመረች 1 ወር ከ17 ቀኗ ነው፡፡ የዛሬውን ለሌት እንዳለፉት ጊዜ አንዴም ተነስታ ‹አይ ልጄ› ወይም ‹እህህ….እህህ….› ሳትል በሰላም ተኝታ በማደሯ ሳልተኛ እያየኋት አደርኩ፡፡ ልክ 12፡10 ሲል ነቃች፡፡ ስታየኝ እያየኋት ነው፡፡ ‹‹ስንት ሰዓት ሆነ?›› ነገርኳት፡፡ አላመነችም፡፡ ተሜ ከታሰረ ጀምሮ እንደ ዛሬ ተኝታ አታውቅም፡፡ ተነሳች፡፡ ‹‹እስከዚህ ሰዓት ስተኛ ዝም ትላለህ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹እንዴት ዝም አልልም?›› አልኳት፡፡ ‹ዛሬ የዓመቷ ማሪያም ነች› አለችኝ፡፡ ፊቷ ላይ ድካም አይታይባትም፡፡ … ከደቂቃዎች በኋላ የሀገር ባህል ጥበብ ቀሚስ ለብሳ አየኋት፤ አምሮባታል፡፡ የደስታ ሲቃ ይዞኝ ‹ትላንት እንዴት ነበር?› አልኳት፡፡ በፈገግታ እያየችኝ ‹‹ልጄ ጀግና ነው፤ ጀግና›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም በመስማማት ራሴን ነቀነኩ፡፡ እናቴ በንጋት ፀሐይ ታጅባ የሀገር ባህል ልብሷን እንደለበሰች ስትሄድ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ይሄ ብርታቷ እስከመቼ እንደሚቆይ እያሰብኩ ነበር፡፡
ተሜ ለሀገሩ ሲልና ሀገሩ እንድትሆን የሚመኝላትን በመፃፉ በግዞት እስር ቤት በአቧራና በንዳድ መሀል እንዲሰነብት ተፈርዶበታል፡፡ ፍትህ የነገሰባት፣ ልጆቿ የማይገደሉባትና የማይሰደዱባት ኢትዮጵያ እንደምትመጣ በተቃጠለ ስሜት እያሰበ፣ በማለዳ የወጣችውን የንጋት ፀሐይ በፈገግታ እያያት እንደሆነ ሳስብ እኔም በደስታ ተሞላው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ምግብ እንዳይገባላቸው ተከለከሉ
-ህዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል
9ኙ ፓርቲዎች በትብብር ለሚያዘጋጁትና ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያስተባብረው የህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚደረገው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ሲቀሰቅሱ እና ታሳሪዎቹን ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሄዱበት ወቅት የታሰሩት 6 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ምግብ እንዳይገባላቸው ተከለከሉ፡፡
በሌላ በኩል ለነገው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በአብዛኛው የአዲስ አበባ ክፍሎች ስኬታማ ቅስቀሳ መደረጉን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ገልጸዋል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ አገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን፤ ህዝቡ በአደባባይ ስብሰባው እንዲሳተፍ በስልክ (በመደወልም ሆነ መልዕክት በመላክ)፣ በማህበራዊ ድህረገጽና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ፣ ለአንድ ወሩ መርሃ ግብርም ሆነ በሌላ የትግሉ አካል ሁለገብ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጥሪ አድርጓል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅስቀሳው ጋር በተያያዘ የታሰሩትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ባቀኑበት ወቅት የታሰሩት አቶ ወሮታው ዋሴና አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድም በምሽት መለቀቃቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እሁድ ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በአዲስ አበባ ቀበና ቤለር የጠሩት ህዝባዊ ስብሰባ በፖሊስ መበተኑ ተገለፀ፡፡
በምርጫ ሥም የነጻነት ትግሉን ማዘናጋት አይቻልም!!
የ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› ህዝባዊ ትግል ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር እንቅስቃሴ
በፓርቲዎች ትብብር በህዳር ወር ይጀመራል!
ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ትብብር የመሰረትን ዘጠኝ ፓርቲዎች ስለምስረታችን በሰጠነው መግለጫ የስምምነታችን ‹‹ … ዘላቂ ግብ ማንም ተጎጂ የማይሆንበትና ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን አቅጣጫ የተከተለ እንደመሆኑ ገዢው ፓርቲ/መንግስት እኔ ከሥልጣን ከለቀቅሁ በቀጣይ በሚመጣው ለውጥ አገር ትበታተናለች በማለት ህዝብን ከሚያስፈራራበት፣ ካድሬዎቹን ፣መከላከያ ሠራዊቱንና የፀጥታና ደህንነት ኃይሉን ተቃዋሚዎች ካሸነፉ አንድም ለወህኒ ካነሰም ‹‹ለልመናና የጎዳና ተዳዳሪነት›› ትዳረጋላችሁ… በሚል ሽብር ከሚነዛበት ፕሮፖጋንዳና አካሄድ እንዲመለስና እንዲታረም ዕድል የሚሠጥ›› መሆኑን ፣ ለትብበሩ አባላት ‹‹ ከምንም እና ከማንም በላይ ቀዳሚው አገርና ህዝብ ›› መሆኑንና በህዝባዊ ሠላማዊ ትግል በምትገነባው ሉዓላዊነቷ የተከበረ ዲሞክራሲዊት ኢትዮጵያ ‹‹ በሁለት ጽንፎች የተወጠረው የአገራችን የአሸናፊ-ተሸናፊ የጠቅላይ ሥልጣን ፖለቲካ ልምድ እንደሚቀየርና በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ለመበጣጠስ የተዘራውን አጥፊ ዘር ማድረቅ፣ የተሰራጨውን መርዝ ማርከስ ›› መቻሉን መግለጻችን ይታወሳል፡፡
አካሄዳችንን በሚመለከትም ‹‹…ለጋራ ዓላማችን እውን መሆን ያለፈው አካሄዳችን የትም እንዳላደረሰንና እንደማያደርሰን ከውድቀታችን ልምድ ቀስመን በአዲስ አስተሳሰብና የአመራርና አሰራር ሥርዓት ለማይቀረው ሥር ነቀል ሁለንተናዊ ለውጥ በግልጽነት በተጠያቂነት መርህ በጽናት ለመታገልና ለማታገል የደረስንበትን ስምምነት ስናበስር ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት በመገንዘብ ›› መሆኑን ገልጸን ለዓላማችን ማስፈጸሚያ ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ የአጭርና የረጅም ጊዜ የዕቅድ አቅጣጫ ማስቀመጠችንንም ገልጸን ነበር፡፡ የዛሬው መግለጫችን ዓላማም ባስቀመጥነው የአጭር ጊዜ ዕቅድ – ምርጫ 2007 ላይ ትኩረት ያደረገና ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ፕሮግራም በተከታታይ የሚካሄደውን ህዝባዊ ሠላማዊ ትግል የመጀመሪያውን ዙር የአንድ ወር እንቅስቃሴ መርሀ-ግብር ከባለቤቱ ዘንድ ማድረስ ነው፡፡
በዚህ መግለጫ በአገራችን ነባራዊና ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እውነታዎች ዝርዝር ውስጥ ለመግባት አይሞከርም ፣ በየቤታችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚታየውን ፣በአራቱም የአገሪቷ አቅጣጫዎች በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሥቃይና የሰላምና ፀጥታ ፣የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት… ላይ የደረሰውንና የፈጠረውን ሥጋት ማንሳት ‹‹ ቀባሪን የማርዳት›› ሙከራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን በምርጫና በመጪው ምርጫ 2007 ላይ ይሆናል፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በመጪው ግንቦት ወር አምስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳ እንደተለመደው ለማወያየት በሚል ለማሳወቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ስብሰባ አስቀድሞ የዚህ ትብብር አባላትን ጨምሮ አስራ ሁለት ፓርቲዎች ለቦርዱ ጥቅምት 5 ቀን 2005
‹‹ 1ኛ/ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ያቀረብናቸው ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ፤
2ኛ/ ገዢውን ፓርቲና አጋሮቹን ጨምሮ ሁሉም ህጋዊ ፓርቲዎች በጋራ ተገናኝተው በምርጫና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚወያዩበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ ››
የሚሉ የጋራ ጥያቄዎችን በማቅረብ ‹‹የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ማለት ለሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር / የነጻ፣ ፍትሃዊና ተኣማኒና አሳታፊ የምርጫ ውድድር ሥርዓት/ ሠላማዊ ትግል/ ዕድል ከመስጠትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከማረጋገጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ማለትም በሌሎች አምባገነን መንግስታትና ሥርዓቶች በጦር መሣሪያ ኃይልና በደህንነት አቅም በመመካት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ያሳዩትን እምቢተኝነትና ማንአለብኝነት ተከትሎ የተከሰቱ ህዝባዊ እምቢተኝነትና በውጤታቸውም የተከተሉ ቀውሶችን በጋራ በመከላከል ከአሸናፊ/ተሸናፊ ጠቅላይ የፖለቲካ ሥልጣን አስተሳሰብ በመውጣት ለዲሞክርሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የመጣልና ለዘላቂ ሠላምና ልማት ዋስትና መስጠት ማለት ነው፡፡ በዚህ ማንም ተጎጂ አይሆንም፡፡›› ብለን ሌላው አማራጭ ደግሞ ‹‹በተቃራኒው እነዚህ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት የሚደረግ የምርጫ ተሳትፎ ለኢህገመንግስታዊነትና ኢዲሞክራሲያዊነት ዕውቅና በመስጠት አገሪቷንና ህዝብን ወደባሰ አዘቅት መወርወር በመሆኑ በታሪክና ትውልድ ፊት የሚያስጠይቅ ይሆናል፤በዚህ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፣ በዚህ መተባበርም ከተጠያቂነት አያተርፍም፡፡›› ብለን የእኛ ምርጫ የመጀመሪያው በመሆኑ ቦርዱ ‹‹ ከምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በፊት ባለበት አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት መሠረት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠውና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሚዛናዊነቱን. ከወገንተኝነት የጸዳ፣ በምርጫ ህጉ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሚሰራ መሆኑን እንዲያረጋግጥ በድጋሚ አበክረን እንጠይቃለን፡፡›› በማለት አሳውቀናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በስብሰባው ወቅት ( እዚህ ላይ ይህ ዓይነቱ ስብሰባ በ2005 አዳማ ላይ ስለምርጫ 2005 የጊዜ ሰሌዳ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተሰብስበን 33ቱ ‹‹ከጊዜ ሠሌዳው በፊት የፖለቲካ ምህዳሩ ይስተካከል›› የሚል ፔቲሽን ከተፈራረሙ በኋላ ባለው ጊዜ ቦርዱ ፓርቲዎችን በሦስት ቦታ በመከፋፈል እንጂ በአንድ ላይ የማይጠራ መሆኑን ያጤኑኣል) በሦስቱም የስብሰባ ቦታዎች የተገኙ ከኢህአዴግና አጋሮቹ እንዲሁም የኢህአዴግ ቀለብ የሚሰፈርላቸው የ‹‹ስለት›› ልጅ የሆኑ ለአጃቢነት የታጩ ፓርቲዎች በቀር ሁሉም የተቃውሞ ጎራ ፓርቲዎች በተመሳሳይና ተደጋጋፊ መንገድ ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ማሳያዎችን በማቅረብ፣በማብራራትና የጥያቄዎቹን ምክንያታዊነትና ባልተመለሱበት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለቦርዱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ቦርዱም እነዚህን ጥያቄዎች በዝርዝር እየመዘገበ መሆኑን በኦዲዮ ቪዥዋል መሳሪያዎችም እየተቀረጹ መሆናቸውን በመግለጽ ለቦርዱ ስብሰባ ቀርበው መልስ እንደሚሰጣቸውና መፍትሄ እንደሚበጅላቸው፣ይህንንም ተገናኝተን እንደምንነጋገር ቃል ገብቶ ስብሰባዎቹ ተጠናቀው ነበር፡፡
በተገባው ቃል መሰረት የሚሰጠውን መልስና የሚበጀውን መፍትሄ በመጠባበቅ ላይ እያለን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች በጥያቄኣችን ላይ ያነሳነውን ለገዢው ፓርቲ ያላቸውን ‹‹ ወገናዊነትና የጉዳይ ፈጻሚነት ሚና›› ፍንትው አድርጎ በሚያሳይ መልኩ የጊዜ ሰሌዳውን ማጽደቅ ብቻ ሣይሆን በምርጫ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱትን ጥያቄዎቻችንን የቢሮ ጥያቄዎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በማስመሰል አሳንሶ በማቅረብ ፕሮፖጋንዳ በመስራት በለመደው መንገድ ለመቀጠል መወሰኑን አውጀዋል፡፡ በዚህም ሳያበቃ በትብብር በጋራ ለመስራት በምናደርገው ግንኙነትና በተፈራረምነው ስምምነት መሰረት በቀጣይ ለምንቀሳቀሰውም ቦርዱ በህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር (ከዚህ በፊት ተመሳሳይ መግለጫ ይሰጡ የነበሩት የኢህአዴግ አባልና የደብረ ብርሃን ከተማ ዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩ መሆኑን እያስታወስን) በኩል ‹‹ በዚህ ትብብር አማካይነት ነገ ወደ ሥራ ሲገቡ ችግር ቢያጋጥማቸው ቦርዱ ሊቆምላቸው የሚችልበት የሥራ አግባብ የለም ››፣ በዚህም ተጠያቂ ‹‹ እንደግለሰብም ሆነ እንደፓርቲ ራሳቸው ነው የሚሆኑት›› የሚፈጠረው ችግርም ‹‹ከህግ ማክበር ጋር ›› የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ (ሪፖርተር ጥቅምት 29 ቀን 2007) ለማን መሆኑን ባናውቅም (ለኢህአዴግ ይህን መምከር ስድብ ይሆናልና) በማስፈራሪያ መልዕክት የታጀበ የወንጀል ክስ ኃሳብና ጥሪ አስተላልፏል፡፡
ከላይ የገለጽናቸው ሁሉ በጋራ ትግላችን ላይ ለማሳረፍ የተፈለገውን የፖለቲካ ጫናና አንድምታውን የመረመረው የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ‹‹ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ ›› እንዲሉ በህገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተቀመጠው መብታችን መጣስ/መጨፍለቅ፣ ቦርዱም ሆነ በሥሩ ያሉት መዋቅሮች ነጻና ገለልተኛ ያለመሆን፣ የምርጫ ሜዳው (የተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል በህዝብ ውስጥ የመንቀሳቀስ መብት፣የአማራጭ ኃሳብ ማራመጃ ሚዲያ ፣ የመራጩ ህዝብ ዲሞክራሲዊ መብትና ሳይሸማቀቅ በነጻ የመምረጥ መብት፣ የምርጫ አስተዳደሩ፣…) በሚመለከት ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች መልስ የማይሰጥ፣ቦርድ በህግ ‹‹ጥፋት›› ለሆነ ድርጊት ከለላ ሊሰጠን እና መከታ ሊሆነን መከጀሉ (መቼ፣ለማን፣እንዴት፣ተደርጎ እንደነበር በጥያቄ ታልፎ) ምጸት መሆኑን ተረድቷል፡፡ የቦርዱም አካሄድ ከተለመደውና በድህረ ምርጫ 2002 ግምገማ ከደረስነው ድምዳሜ ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል›› ከሚለው አልፎ ‹‹ ተዘግቷል›› ወደሚል ድምዳሜ የሚያሸጋግር ሆኖ መገኘቱን በተጨባጭ አረጋግጠናል፡፡ ዛሬ ላይ የእምነት ነጻነት ጠያቂዎች፣ጋዜጠኞች፣ጦማሪያን፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ አልፎም ከገዢው ፓርቲ የተለየ ኃሳብ ያላቸው ዜጎች በአፋኝ ህጎች በፈጠራ ወንጀል ተከሰው የት እንደሚገኙ ከእኛ አልፎ የዓለም ህዝብ ያውቀዋል፤ አንድም በወህኒ ያሊያም በስደት፡፡
ስለዚህ ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለማስከፈት ትግሉን የ ‹‹ ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል የፕሮግራም መርህ ለመግፋት ወስኖ የመጀመሪያውን ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ የአንድ ወር ዕቅድ አዘጋጅቶኣል፡፡ በዕቅድ ዝግጅቱ የፕሮግራሙ የአፈጻጸም ስልት ፣የጊዜ ሰሌዳ፣ የቦታ ሽፋን፣የፋይናንስ ምንጭ፣ ዓላማዎች፣ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮችና መንግስታዊና የህዝብ ክፍሎች፣ዋና ዋና ተግባራት ፣በተጨማሪም በታሳቢነት በአፈጻጸም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች/ደንቃራዎችና ሥጋቶች እንዲሁም ለፕሮግራሙን ስኬት አጋዢ ሁኔታዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
በዚህ መሠረት ይህ ዙር የሚያተኩርባቸው ዋና ዋና ተግባራትም–
1. በየቤተ እምነቱ ጸሎት ፕሮግራም እንዲደረግ ጥሪ ማድረግና አባላት እንደየእምነታቸው ተሳትፎ ማድረግ፤
2. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግ፤
3. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ፤
4. ለመንግሥታዊ ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት፤
5. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት፤
6. የህዝብ ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ፤ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ ሊታወቅ የሚገባው አቢይ ጉዳይ ይህን ዕቅድ ስናዘጋጅ ነጻነታችንና መብታችን ከገዢው ፓርቲ ለምነን የምናገኘው ሣይሆን በእያንዳንዳችን እጅ ውስጥ መሆኑንና በማመን እኛ የዕቅዱ አስተባባሪዎች እንጂ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት፣ የዕቅዱ ፈጻሚና ዋና ተዋናይ እያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ/ት ዜጋ ነው/ናት በሚል ሙሉ እምነት ላይ ቆመን መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ዕቅድ ተፈጻሚነት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ/ት በጋራ/በትብብር ከጀመርነው ሠላማዊ ትግል ጎን በመቆም ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ አይኖርምና በምርጫ ሥም ሠላማዊ የነጻነት ትግሉን ማዘናጋት ያብቃ/ማለትና ለዕቅዱ ተፈጻሚነት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ራስን ከባርነት ነጻ የማውጣት፣አገርን ከጥፋት የመታደግ የዜግነት ግዴታ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም ከላይ በገለጽናቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ገዢው ፓርቲ በጉዳይ ፈጻሚው የምርጫ ቦርድ በኩል በተለመደው መንገድ በምርጫ ሥም ለመሥራት የተያያዘውን ቧልት ራቁቱን በማስቀረት ለ ነጻ፣ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የምርጫ ሜዳውን እንዲያስተካክል በሠላማዊ ትግል አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳረፍ በእኛ በኩል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈልና እስከ መጨረሻው በጽናት ለመቆም የተዘጋጀን መሆኑን እያረጋገጥን ፡-
1ኛ/ የችግሩ ገፈት ቀማሽና የጉዳዩ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት የሆናችሁ በአገር ቤት ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ አገራችን ከገባችበት ፈተና ህዝባችን ከሚደርስበት ሥቃይ ለማውጣት የራሳችን የዜግነት ክብር ባለቤት ለመሆን ያለን ምርጫ በጽናትና ቆራጥነት የተባበረና የተቀናጀ ሠላማዊ ትግል ስለሆነ ለዚህ ፕሮግራም ስኬት ሁለንተናዊ የፋይናንስ ፣የማቴሪያል፣የጊዜና ጉልበት፣ የዕውቀትና ሙያ፣ የትግል አስተዋጽኦ (በማድረግ የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ) እንድታደርጉና እንቅስቃሴኣችንን በመከታተል የአመራርና አፈጻጸም እገዛችሁ እንዳይለየን ፤
2ኛ/ ከአገዛዝ ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች ለስደት የተዳረጋችሁ፣በውጪ ለመኖር የተገደዳችሁ ባላችሁበት ሆናችሁ የአገራችሁ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳችሁ ኢትዮጵያዊ የዲያስፖራ አባላት በሙሉ ከላይ የእናንተ ተሳትፎ ከትብብርና ድጋፍ ያለፈ አገራዊ ኃላፊነት የመወጣት ነውና በአገር ቤት ላሉት ካቀረብነው በተጨማሪ ድምጹ ለታፈነውና የሰቆቃ ህይወት ለሚገፋው ወገናችሁ ድምጽ ሆናችሁ የዲፕሎማሲውን ትግል በኃላፊነት ስሜት እንድታከናውኑ፤
3ኛ/በትብብሩ ያልታቀፋችሁ በተለይም በሂደቱ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው ተሳትፋችሁ በተለያየ ምክንያት የስምምነቱን ሰነድ ያልፈረማችሁም ሆነ የአገርና ህዝብን ጉዳይ ከፓርቲ ጥቅምና ዓላማ በላይ ስለሆነ በጋራ ለመሥራት ዝግጅቱና ቁርጠኝነቱ ያላችሁ ሌሎች ሠላማዊ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከጋራ ትግሉ እንድትቀላቀሉ እና/ወይም የፕሮግራሙ አካል እንድትሆኑ፤
4ኛ/ የዓለም አቀፉና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት መንግስታት ተለዋዋጭና ኃላፊ፣ ህዝብ ግን ቋሚ ነውና በግንኙነታችሁ የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ጥቅምንና ታሪካዊና ፖለቲካ አንድምታን ከግምት እንድታስገቡ፤ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በተቀናጀ የጋራ አመራር የተባበረ ህዝባዊ ሠላማዊ ትግል በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን//
ጥቅምት 25/2007፣ አዲስ አበባ