የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
ቀን 02/06/2007 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡ የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡
ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡
በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡
ግልባጭ
_ ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
_ የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
_ ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት
_ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)
_ ለእምባ ጠባቂ
_ ለአሜሪካ ኢምባሲ
_ ለእንግሊዝ ኢምባሲ
ከሰላምታ ጋር
ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መሆኑ ተገለፀ
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት የሶስት ዓመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ደህንነቱ አደጋ ላይ መሆኑ የቅርብ ቤተሰቦቹ ገለፁ፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በዝዋይ ወህኒ ቤት ኮማንደር ቢኒያም ተብሎ በሚጠራው የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ጠዋትና ማታ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሚገኝና በተጨማሪነትም በቀን ለአምስት ጊዜ ያህል ሌሊትን ጨምሮ በሰበብ አስባቡ ከክፍሉ እየተጠራ እንደሚወሰድ የቅርብ ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን፣ በኮማንደር ቢኒያም እየተጠራ “እንገልሃለን፣ ከዚህ አንተ ሳይሆን ሬሳህ ነው የሚወጣው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ዛቻው እና ማስፈራሪያው እየደረሰበት የሚገኘው በቅርቡ ለንባብ ባበቃው “የኢትዮጵያ መንግስት ገመና” በሚለው መጣጥፉ እንደሆነ የቅርብ ቤተሰቦቹ አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ከያዝነው ሳምንት ጀምሮም ምግብ እንዳይገባለትም ሆነ በቤተሰብ፣ በወዳጅ እና በስራ በባልደረቦቹ እንዳይጎበኝ መደረጉን ፍኖተ ነፃነት ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን፣ ፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሁፎች የተነሳ የሶስት ዓመት እስር ተፈርዶበት ከጥቅምት ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና (ክፍል 2)
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
(ከዝዋይ እስር ቤት)
በዚህ አውድ ለማቅረብ የተገደድኩበትን ዘግናኝ ታሪክ፣ ወደር በሌለው አስከፊነቱ የተነሳ ለንባብ ባላበቃው በወደድኩ ነበር፡፡ ግና! ይህ መንግስታዊ የጭካኔ ተግባር፣ ዛሬም በምስኪን ዜጎች ላይ እየተፈፀመና ብዙዎችን ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ህዝቡ ይህን ሊሸሸግ እየተሞከረ ያለውን መከራ ተረድቶ ሥርዓቱን በአደባባይ ዓመፅ “ሃይ!” ይል ዘንድ ትርክቴን ለማጠናቀር ተገድጄያለሁ፡፡ ለእስር ያበቃኝ የጋዜጠኝነት ሙያዬም ተጨማሪ ዕዳ ጭኖብኛል፡፡
“ጄል-ኦጋዴን”
ጄል ኦጋዴን በሱማሌ ክልል ርዕሰ-መዲና የሚገኝ፤ ለ800 እስረኞች ታቅዶ በ1992 ዓ.ም የተገነባ እስር ቤት ነው፡፡ የግቢውን ዙሪያ ከከበበው አጥር በግምት 15 ሜትር ፈንጠር ብሎ ሌላ ተደራቢ የድንጋይ አጥር ተበጅቶለታል፡፡ እስከ ሚያዝያ 24 1999 ዓ.ም ድረስ እስር ቤቱ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ካሉ መሰል ማጎሪያዎች ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ በዚህ በተጠቀሰው ቀን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች፣ አቦሌ እና ሰንደሬ ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ፣ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቻይናውያን ባለሙያዎች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሰነዘሩትን ከባድ ጥቃት ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞች ብቻ የሚታጎሩበት እስር ቤት ከሆነ ወዲህ ግን በዋይታ የሚናወፅና በደም ጅረት የሚጥለቀለቅ ምድራዊ ሲኦል ለመሆን በቅቷል፡፡ መንግስት በጥቃቱ ከዘጠኙ ቻይናውያን ጋር 74 ሲቪል ዜጎችና ወታደሮች መገደላቸውን ቢያምንም፤ የአካባቢው የአይን እማኞች ከሰራዊቱ ብቻ እስከ 300 እንደተሰዉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦብነግ እንደ አል-ቃይዳ እና አል-ሸባብ የአባላቱን አስከሬን ትቶ የመሸሽ ልምድ ስለሌለው በቡድኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
የሆነው ሆኖ ከዚህ ጥቃት በኋላ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የሚመራ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የደህንነትና (ጄነራል ሳሞራ የኑስ እና ጌታቸው አሰፋ ያሉበት) የፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚከተሉትን (ዛሬም ድረስ እየተተገበሩ ያሉ) አስቸኳይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ‹‹ከጅጅጋ ውጭ ባሉ በክልሉ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ፣ ትዕዛዙን ጥሶ የተገኘ ከነጭነቱም ሆነ ተሳፋሪዎቹ በከባድ መሳሪያ እንዲመታ፤ አብዛኛውን ህዝብ በፍጥነት ከመኖሪያ ቀዬው በማፈናቀል ለቁጥጥር ወደሚያመቹ ከተሞች ማስፈር (በ2006 ዓ.ም መጀመሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን 2300 መንደሮችን ወደ ተመረጠ ቦታ ማስፈሩ እንደተሳካ መናገሩን ልብ ይሏል)፤ ወታደራዊ መኪና ላይ ምንም አይነት የደፈጣ ጥቃት ከደረሰ በአቅራቢያው የሚገኝ መንደርን ያለርህራሄ ማውደም (ለማሳያ ያህልም ፍልቼ፣ ቃሙዳ፣ ሳስባኒ፣ ሁለሌ፣ ለንካይርተ፣ ቻለሌን… የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን መጥቀስ ይቻላል) እና ከአንድ ሻምበል ያነሰ ኃይል ለአስቸኳይ ጉዳይም ቢሆን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ›› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላም ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በክልሉ የሚገኘውን የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ወታደራዊ አዛዦችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሰብስቦ ማብራሪያ ሰጥቶ ሲያበቃ ውሳኔውን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ እንዲያደርጉት በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ደቡብ ምስራቅ ዕዝ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (ከ1993 ዓ.ም) በኋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሰፈረ ሲሆን እስከ ታህሳስ 1999 ዓ.ም ድረስ በሜ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ከታህሳስ 1999 እስከ 2000 ዓ.ም ደግሞ ብርጋዴር ጄነራል ስዩም አስተዳድሮታል፤ በዚሁ ዓመት ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ ድረስ ባሉት ጊዜያትም በብ/ጄነራል ሙሉጌታ በርሄ ስር የቆየ ሲሆን፤ ከሚያዚያ 2000 ዓ.ም አንስቶ አሁን ድረስ እየተመራ የሚገኘው በሌ/ጄነራል አብርሃም ወ/ማርያም (ቅፅል ስሙ ‹‹ኳርተር››) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ዕዝ ውስጥ በዋናነት ሶስት ክፍለ ጦሮች (12ኛ፣ 13ኛ እና 32ኛ) ክልሉን ሶማሊያ ድንበር ድረስ እንዲቆጣጠሩት ተመድበዋል፡፡ ሰፈራቸውን ነገሌ ቦረና ያደረጉት 43ኛ እና 44ኛ ክፍለ ጦሮችም፣ ኦጋዴን ድረስ እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአናቱም የአግአዚ ኃይል በቀድሞ ምክትል አዛዡ ብ/ጄኔራል ገ/መድህን ፈቀደ (‹‹ወዲ ነጮ››) ስር ሆኖ አልፎ አልፎ በተደራቢነት እየተላከ በነዋሪዎቹ ላይ በደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ እና ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፈ ስለመሆኑ ከወታደራዊ መረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ለደረሱ እልቂቶችና ጭፍለቃዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ ተደርገው የሚጠቀሱት ከጄነራል ሳሞራ፣ ከጀኔራል ‹‹ኳርተር›› እና ከክልሉ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ በብ/ጄነራል በየነ ገ/እግዚአብሔር (‹‹ወዲ አንጥር››) የተመራው 12ኛ ክ/ጦር እና በብ/ጄነራል ፀጋዬ ገ/ጨርቆስ (‹‹ጀብጀብ››) ዕዝ ስር የነበረው 13ኛ ክ/ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኦብነግ በስፋት ይንቀሳቀስባቸዋል ተብለው የሚታሰቡት፡- ደገሃቡር፣ ቀብሪደሃር፣ ዋርደር፣ ጎዴ እና ቪቅ ከተሞች መደበኛ የጦር ቀጠናዎች ከሆኑ 15 አመት ያለፋቸው በመሆኑ፣ ከሌሎች የክልሉ አውራጃዎች በተለየ ሁኔታ የችግሩ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የሚፈፅማቸውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊቶች ለመሸፈን እንደ ቀይ መስቀል፣ ዓለም-አቀፍ ሚዲያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መሰል ተቋማት ከጅጅጋ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ በኃይል አግዷል፡፡ ይህ ኩነትም በ ዙ-23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ተደብድበው ከምድረ-ገፅ የጠፉ መንደር ነዋሪዎች፣ የቤት እንስሳት እና ቁሳዊ ንብረቶች በአንድነት ተቃጥለው መውደማቸውን ዛሬም ድረስ በምስጢርነት ሸሽጎ ለማቆየት አስችሎታል፡፡
የሆነው ሆኖ የመከላከያ ሰራዊቱ እና በክልሉ ከ70-80 በመቶ በሚሆኑ አካባቢዎች ላይ መንቀሳቀስ የቻለው ኦብነግ፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከባድ ውጊያ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ግጭቱ አሁንም ሳያበራ የመቀጠሉ ምክንያት አማፂው ቡድን ያን ያህል ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የጄነራሎቹ እጅ በዘወርዋራ ስላለበት መሆኑን ወታደራዊ ምንጮቼ ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹የኦብነግ ህልውና በተለይም ለከፍተኛ መኮንኖች ዋነኛ ንግድ (ቢዝነስ) ነው›› ይላሉ፡፡ የክልሉ መንግስት ‹‹የመረጃ እና ፀጥታ ባጀት›› በሚል ሽፋን በዓመት የሚመድበውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ሀብት እንዲያወራርዱ አዛዦቹ አይገደዱም፡፡ መከላከያ ራሱም ‹‹የመረጃ እና የበረሃ ፍሳሽ›› በሚል የሚበጅተው አመታዊ ወጪ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በጀት እስከ ኃይል አመራሮች ድረስ ወርዶ እንደየድርሻቸው መጠን የሚመዘበርበት አሰራርም ተዘርግቶለታል፡፡ እናም ጀነራሎቹ ኦብነግ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ የገቢ ምንጫቸው እንዳይደርቅም ሆነ፤ ከአቅም በላይ ተጠናክሮ በብቃት ማነስ እንዳያሳጣቸው (እንዳያስወቅሳቸው) ተቆጣጥረው ለመዝለቅ የቻሉበትን ቀመር እንዲከተሉ ይህ የገቢ ምንጭነት ገፊ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
ሌላው ቀርቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ በቀጥታ የክልሉ አስተዳደር የሚያዝዘውና ‹‹ልዩ ኃይል›› ተብሎ የተቋቋመው ታጣቂ ቡድን ዛሬም ድረስ የሎጅስቲክ አቅርቦቱን ያለጨረታ ጠቅላላ የያዘችው የሜ/ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ (በአሁኑ ወቅት ጀነራል አበባውን ተክቶ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነው) ባለቤት ሃዋ መሆኗ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ክልሉን የሚያስተዳድሩት በህዝብ የተመረጡት ሳይሆኑ ‹‹የፀጥታ አማካሪ›› በሚል በየወረዳው የተመደቡ የሻለቃ ወይም የሻምበል አዛዦች ከጀርባ ሆነው ነው፡፡ ለነርሱ ያልተመቸ ኃላፊን በሌላ እስከመቀየር ድረስ የሚንጠራራ ስልጣን አላቸው፡፡ የፕሬዚዳንት አብዲና እና የጄነራል ‹‹ኳርተር››ን የ‹‹ሥራ ግንኙነት›› መመልከቱ ጉዳዩን ፍንትው አድርጎ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በርግጥም አስራ ሦስት ፕሬዚዳንቶች የተፈራረቁበት ክልል ዛሬ እንዲህ በጨካኙ አብዲ መርጋት መቻሉ እንቆቅልሽ ሊሆን አይችልም)፡፡
‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ከደረቅ ወንጀለኞች ማረሚያነት፣ በኦብነግ አባልነት የሚጠረጠሩ ንፁሃንን ወደማሰቃያ እስር ቤት እንዲቀየር የተደረገበት መግፍኤ ከላይ የጠቀስኩትን (የ1999 ዓ.ም የኃይል ጥቃትን) ተከትሎ ሟቹ አምባ-ገነን ጠ/ሚኒስቴር በደህንነት ኮሚቴው ስም የሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ መቼም ዕድል ፊቷን አዙራበት ወደዚህ ግቢ የተላከ ምስኪን፣ በቀን አንድ መናኛ እንጀራ እየተወረወረለት፣ በ‹‹ምርመራ›› ስም የተወለደበትን ቀን ከመርገም አልፎ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚያጎናፅፈው መልአከ-ሞት ቶሎ መጥቶ እንዲገላግለው እስከመናፈቅ ለሚያደርስ ስቀየት (ቶርቸር) ይዳረጋል፡፡ እስር ቤቱ የተገነባው 800 ታሳሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ ወደምድራዊ ገሃነም ከተቀየረ ወዲህ ግን ከ5000 በላይ ሰዎች የሚታጎሩበት የሰቆቃ ግቢ ሆኗል፡፡ ሁሉም ታሳሪዎች ከጠዋት 2፡30 እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ አንድ ቦታ ተሰብስበው ክብርን፣ ሞራልን እና ሰብዕናን የሚያጎድፍ ግፍ ይፈፀምባቸዋል፡፡
በተለይም ሴት እስረኞች በየተራ እንዲቆሙ ይደረግና ወንዱ አንድ በአንድ እየተነሳ ሴተኛ አዳሪ መሆኗን፣ እሱ እና ጓደኞቹ ከእርስዋ ጋር ግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀማቸውን፣ ወዘተ እንዲናገር ይገደዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኖ ካልተገኘም በጨካኝ ታጣቂዎቹ ፍዳውን ይበላል፡፡ ሁኔታውን መራር የሚያደርገው ደግሞ ‹‹ስብሰባው›› ሲጠናቀቅ፣ ሰብሳቢው እስረኞቹ ወደየክፍላቸው እንዲገቡ ትዕዛዝ የማይሰጥ መሆኑ ነው፤ ይልቁንም ወፋፍራም ዱላ ጨብጠው ዙሪያውን ለከበቡት ፖሊሶች በአይኑ ምልክት ያስተላልፋል፤ ይሄኔ በያዙት ቆመጥ ከአቅራቢያቸው ያገኙትን ሁሉ መቀጠቀጥ ይጀምራሉ፤ እስረኛውም ከዱላው ውርጅብኙ ለማምለጥ ባገኘው አቅጣጫ ይተራመሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በየቀኑ የተለመደ በመሆኑ የዕለቱ ፕሮግራም ሊገባደድ በተቃረበ ቁጥር፣ ሁሉም ለመሸሽ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቃል፤ ከድብደባው ማምለጡ ግን ብዙም የሚሳካ አይሆንም፡፡
በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈር፣ ሙዝ ልጦ እንደመብላት ቀላል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም በርካቶች በየጊዜው ለውርጃ ወደሆስፒታል ሲላኩ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ እዚያው ለመውለድ የሚገደዱ እህቶችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሴት እስረኞች ፀጉራቸውን ከማሳደግ ይልቅ መላጨትን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈፀምባቸው ስቅየት የበሰበሱ ቆሻሻዎችንና ፈሳሽ-ሰገራዎችን ፀጉራቸው ላይ መደፋትን ስለሚያካትት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ቦታ ሴቶች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እና ልብሶቻቸውን እንዲያወልቁ ከተደረገ በኋላ እርቃናቸውን የሚገረፉበት ጊዜም እንዳለ ከአይን እማኞች ሰምቻለሁ፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ንፅህናን ካለመጠበቅና በምግብ እጥረት የሚነዛው ወረርሽኝ ነው፡፡ በ2004ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በሽታው ተከስቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ 700 ያህል ሰዎች በሞት መቀጠፋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ አስከሬን ቶሎ ስለማይነሳ እስረኞቹ ከአስከሬኑ ጋር እስከ 3 ቀን ድረስ ጋር ለመቆየት ይገደዱ ነበር፡፡
በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ግቢ ከሚገኙ ማጎሪያዎች መካከል 3ኛ፣ 4ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ‹‹የቅጣት ቤት›› ሲሆኑ፤ አሰራራቸውም ሶስት በሶስት ሜትር የሆነ እጅግ በጣም ጠባብ፤ ውስጣቸውም ሃምሳ ሳንቲ-ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ የተሞላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍልም የግድ ከ25 እና ከዚያ በላይ እስረኞች እንዲይዝ ስለሚደረግ ለቅጣት ወደግቢው የተላከ እስረኛ ለሳምንት ያህል እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ለመሰንበት ይገደዳል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደዚህ ግቢ እየተላኩ ስቅየትም ሆነ ግድያ እንደሚፈፀምባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በግቢው ለአራት ወራት ገደማ ያሳለፈው ሀሰን፣ በውል በማያስታውሰው በአንድ የተረገመ ቀን 3 ወታደሮች ሲረሸኑ ማየቱንና ከመካከላቸው አንዱም ‹‹እባካችሁ አትግደሉኝ! የ3 ልጆች አባት ነኝ!›› እያለ ሲማፀን መስማቱን ያስታውሳል፡፡
እስረኞቹ ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ከዚህ ቀደም ‹‹አል-ኢትሀድ አል-ኢስላሚያ›› በሚል ስም ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ፤ በኦብነግ ተሸንፎ ከኦጋዴን የተባረረው አማፂ ቡድን አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግስት ምህረት አድርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት ከተመለሱ በኋላ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዛኛውን አሰባስቦ ‹‹ልዩ ኃይል›› ብሎ አደራጅቷቸው ሲያበቃ፤ ከኦብነግ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ እስረኞች ላይ ያሻቸውን እንዲፈፅሙ ባልተፃፈ ሕግ ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም የቀድሞ ሽንፈታቸውን ለመበቀል እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በክልሉ ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ የእስር ቤት ግቢዎች ውስጥ የጅምላ መቃብር መመልከት አስገራሚነቱም አስደንጋጭነቱም እየቀረ የመጣው ከዚህ አኳያ ይመስለኛል፡
እናታችን ፋናዬና ጋዜጠኛ ተመስገን በዝዋይ…
ታሪኩ ደሳለኝ
(የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም)
ያቺ የስምጥ ሽለቆ ከተማ ይበልጥ መንደድ ከጀማመራት አንድ ወር አልፏታል:: በፍትህ መዛባት ስሜቱ የተጎዳ፣ በወገኖቹ ስቃይ መንፈሱ የታመመ፣ ሀገራቸውን ከስቃይ መታደግ በሚችሉበት እድሜያቸው በታሰሩ፣ በተሰደዱና በተገደሉ ወገኖቹ ልቡ ያዘነ፣ ለሀገሩና ለባንዲራው ያለው ፍቅር ጥልቅ የሆነ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በውስጧ ይዛለች፡፡ ዝዋይ፡፡
ከዚህች ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው የዝዋይ እስር ቤት ለመሄድ የአስፓልት ዱካ እንዳረፈበት በሚያሳብቀው ኮሮኮንቻማ መንገድ ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ከረጅም ዓመታት በፊት ተሰርቶ ዛሬ አስታዋሽ ያጣው ይህ ጎዳና እስረኞችን የመጠየቁን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከፀሐዩ ግለት ትይዩ ያለው የመሬቱ አቧራ በእግሩ ቆሞ ይሄዳል ብል አይበዛበበትም፡፡ ይህን አልፈን ግዞት ቤቱን እናገኛለን፡፡ የእስር ቤቱን መግቢያ ያለበሰው አቧራ ደግሞ ቅጥሩን በቁፋሮ የተገኘ ጥንታዊ ከተማ አስመስሎታል፡፡ የግቢው ገፅታ ለዕይታ በማይስቡ ነገሮች ቢከበብም፣ ተናፋቂውን ብዕረኛ ግን ደጋግሜ እንድጠይቀው ከወንድምነት የሚዘለው ጥንካሬው ይስበኛል፡፡
በአቧራውና በንዳዱ መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀድሞ ይልቅ በጠነከረ ፅናቱ ስለመኖሩ ሳስብ ደስተኛ እሆናለሁ፡፡ እናታችንስ ምን ታስብ ይሆን? የማይበርድ፣ የማይዳፈንና የማይጠፋ የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከአቧራውና ከንዳዱ በላይ መሆኑ ለእርሷ ምን ስሜት ያጋባባታል?
እናታችንና ተሜን ሲገናኙ…
ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 20/07 ዓ.ም ነው፡፡ እናቴ አብረዋት ከኖሩ ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን፣ ዝዋይ እስር ቤት ከከተመ አንድ ወር ያለፈውን ተመስገንን ልታየው ተሰናድታለች፡፡ ዝዋይ ከሄደ ወዲህ አይታው አታውቅም፡፡ እንደናፈቃት ግን የፊቷ ገፅታ ይመሰክራል፡፡ እንደ ልጅነቱ ፀጉሩን ባትደባብሰውም፤ እጁን ልትነካውና በዕርጅና አንደበቷ ‹እንዴት ነህ?› ልትለው ወደዚያው እያቀናች ነው፡፡ ጠዋት ወጥተው ማታ እንደሚገቡት፣ ክፍለ-ሀገር ሰንብተው እንደሚመለሱት እንደ ጓደኞቿ ልጆች ተመስገን እንደማይመለስ የተረዳችው እናታችን ልጇ ጋር እየሄደሰች ነው፡፡
ለሊት 11፡30 ከጀሞ ኮንዶሚኒየም የተነሳችው መኪና ዝዋይ የደረሰችው ከጠዋቱ 2፡20 ላይ ነበር፡፡ አስፋልት መሰል ፍርስራሽ መንገዱን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ዛሬ አልሰጠኝም፡፡ ፍተሻውን አልፈን እስረኛና ጠያቂ የሚገናኘበት ቦታ ላይ ደረስን፡፡ ከነበርነው ሰዎች ይልቅ እናታችን ጉጉት እንዳደረባት ለመናገር ሁኔታዋን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡
እናታችን ተመስገን በልጅነቱ ከዕኩዮቹ ጋር ተጫውቶ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ስራ ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፤ አንዳንዴም ሲያመሽ ደውላ ‹‹አልመሸም፤ የቀረው ለነገ ይቆይህ›› ትለዋለች፤ እርሱም ሁሌ እንደሰማት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ልጇን የምትጠብቀው ከትምህርት ቤት አልያም ከጨዋታ ወይም ከስራ አይደለም፡፡ ከእስር ቤት ውስጥ እንጂ!
እናታችን እስረኞች ከሚወጡበት በር ላይ ከተቀመጠችበት ደቂቃ ጀምሮ አይኗን አላነሳችም፡፡ በሩ ሲከፈት የወታደር ልብስ የለበሰ ወጣት ወጣ፡፡ ከወታደሩ በኋላ ተሜ እስካርፉን እንዳደረገ ተከተለ፡፡ እናቴ ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ ዐይኗቿ እንባ አዘሉ፡፡ በዕስረኛና በጠያቂ መሀል ያለውን አጥር ተደገፈች፡፡ ሌላ ጊዜ አጥሩን መደገፍ የሚከለክሉት ወታደሮች እናታችንን ግን ጥቂት ታገሷት፡፡ ምን ያድርጉ? እነሱም እኮ እናት አላቸው፡፡ ከተመስገን ኋላ ሌላ ወታደር አለ፡፡ በሁለት ወታደሮች መካከል ሆኖ ተሜ እናቱን አያት፤ ፈገግ አለ፡፡ እየቀረበ ሲመጣ ግን ፈገግታው ከፊቱ ላይ ጠፍቶ በሀሳብ ተተካ፡፡ እናቴን በዚህ እድሜዋ አንከራተትኳት ብሎ እንዳላሰበ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ከዚህ ይልቅ ስንትና ስንት እናቶች በየቦታው እየተንከራተቱና እየተሰቃዩ ስለመሆናቸው እያሰበ የተጨነቀ ይመስላል፡፡ እናትና ልጅ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ቆዩ፡፡ ምን አለ ባይለያዩ? እንዲሁ እንዳሉ ወደ ቤት ቢሄዱስ ምን ነበረበት?
ይሄ ግን አይሆንም፤ ይሄ ቦታ ተሜ ለሀገሩ የከፈለውን፣ እየከፈለ ያለውንና የሚከፍለውን መስዋዕትነት ማቅረቢያው ቦታ ነው፡፡ ተሜ ወደ ቤት አይሄድም፡፡
ተሜና እናቴ የተጫወቱት ብዙ ነው ፡፡ ሲገናኙ የነበረው ድባብ ጠፍቶ ሁለቱም ደስ ብሏቸዋል፡፡ ተሜ ትንሽ አይቷት ‹‹ከስተሻል›› ሲላት ፈገግ እንዳለች ‹‹አረ አልከሳሁም፤ አንተ ግን ጤናህ እንዴት ነው?››፤ ‹‹ደህና ነኝ››… እናቴ በየመሀሉ ጨዋታቸውን ገታ እያደረገች በስስት ታየዋለች፡፡ እናትና ልጅ የሆድ የሆዳቸውን እንዲያወሩ የፈቀዱት ወታደሮችም ሁለቱን በስስት የሚያዩ ይመስላሉ፡፡
ሳይታወቀን 6፡00 ሆነ፡፡ የመሰነባበቻ ጊዜ ደረሰ፡፡ እናቴ እየሳቀች አቀፈችው፤ ተሜም እየሳቀ ተሰናበታት፡፡ እንደ አመጣጡ በሁለቱ ወታደሮች መካከል ሲሄድ ከጀርባው ትክ ብላ አየችው፡፡ የሆነ ነገር ልትል የፈለገች ትመስላላች፡፡ ‹‹ተመስገን›› አለች፤ አልሰማትም፡፡ በሩን አልፎ ገባ፡፡ እሱ ፊት የደበቀችውን እንባ ማቆም አልቻለችም፡፡ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ከፈገግታዋ ጋር አለቀሰች፡፡
እሁድ ህዳር 21/07 ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት፡፡ እናቴ ልጇ እስኪፈታ አልጋ ላይ አልተኛም ብላ መሬት መተኛት ከጀመረች 1 ወር ከ17 ቀኗ ነው፡፡ የዛሬውን ለሌት እንዳለፉት ጊዜ አንዴም ተነስታ ‹አይ ልጄ› ወይም ‹እህህ….እህህ….› ሳትል በሰላም ተኝታ በማደሯ ሳልተኛ እያየኋት አደርኩ፡፡ ልክ 12፡10 ሲል ነቃች፡፡ ስታየኝ እያየኋት ነው፡፡ ‹‹ስንት ሰዓት ሆነ?›› ነገርኳት፡፡ አላመነችም፡፡ ተሜ ከታሰረ ጀምሮ እንደ ዛሬ ተኝታ አታውቅም፡፡ ተነሳች፡፡ ‹‹እስከዚህ ሰዓት ስተኛ ዝም ትላለህ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹እንዴት ዝም አልልም?›› አልኳት፡፡ ‹ዛሬ የዓመቷ ማሪያም ነች› አለችኝ፡፡ ፊቷ ላይ ድካም አይታይባትም፡፡ … ከደቂቃዎች በኋላ የሀገር ባህል ጥበብ ቀሚስ ለብሳ አየኋት፤ አምሮባታል፡፡ የደስታ ሲቃ ይዞኝ ‹ትላንት እንዴት ነበር?› አልኳት፡፡ በፈገግታ እያየችኝ ‹‹ልጄ ጀግና ነው፤ ጀግና›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም በመስማማት ራሴን ነቀነኩ፡፡ እናቴ በንጋት ፀሐይ ታጅባ የሀገር ባህል ልብሷን እንደለበሰች ስትሄድ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ይሄ ብርታቷ እስከመቼ እንደሚቆይ እያሰብኩ ነበር፡፡
ተሜ ለሀገሩ ሲልና ሀገሩ እንድትሆን የሚመኝላትን በመፃፉ በግዞት እስር ቤት በአቧራና በንዳድ መሀል እንዲሰነብት ተፈርዶበታል፡፡ ፍትህ የነገሰባት፣ ልጆቿ የማይገደሉባትና የማይሰደዱባት ኢትዮጵያ እንደምትመጣ በተቃጠለ ስሜት እያሰበ፣ በማለዳ የወጣችውን የንጋት ፀሐይ በፈገግታ እያያት እንደሆነ ሳስብ እኔም በደስታ ተሞላው፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበት ክስ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት
የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና መስራች፣ የአዲስ ታየምስ መፅሔት፣ የልዕልና ጋዜጣ በመጨረሻም የፋክት መፅሔት ባልደረባና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበትና ጥፋተኛ በተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ጋዜጠኛው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ የሚል ብይን ከሰጠ በኋላ ቅጣት የተጣለበት በ2004 ዓ.ም. በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በፃፋቸው ፅሑፎችን መሰረት አድርጎ መሆኑ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው የተፈረበት፤ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎትም ጋዜጠኛው ጥፋተኛ ከተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ተመስገን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ፤ወደ አቃቂ ቂሊንጦ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ተወስዷል፡፡
የጋዜጠኛው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ቅጣቱን እና ፍርዱን በሚመለከት ይግባኝ እንደሚጠይቁ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅጣት ፍርዱ አቃቤ ህጉም ሆኑ ተከላካይ ጠበቃው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ አለመጠየቃቸው ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ቁጥር 18 መድረሱ ታውቋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በፃፉት ፅሑፍ የተከሰሱ፣የታሰሩም ሆነ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችም የሉም የሚል ተደጋጋሚ ማስተባበያ ቢሰጥም፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጨምሮ ከታሰሩት 18 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች መካከል 15ቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የቀረበባቸው ክስናም ሆነ ፍርድ ከስራቸው ጋር በተያያዘ በፃፉትና በተናገሩት መሆኑ የተመሰረተባቸው ክስ ያመለክታል፡፡