Tag Archives: CPJ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበት ክስ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት

የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና መስራች፣ የአዲስ ታየምስ መፅሔት፣ የልዕልና ጋዜጣ በመጨረሻም የፋክት መፅሔት ባልደረባና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበትና ጥፋተኛ በተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ጋዜጠኛው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ የሚል ብይን ከሰጠ በኋላ ቅጣት የተጣለበት በ2004 ዓ.ም. በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በፃፋቸው ፅሑፎችን መሰረት አድርጎ መሆኑ ታውቋል፡፡

temesegen dጋዜጠኛው የተፈረበት፤ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎትም ጋዜጠኛው ጥፋተኛ ከተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ተመስገን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ፤ወደ አቃቂ ቂሊንጦ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ተወስዷል፡፡

የጋዜጠኛው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ቅጣቱን እና ፍርዱን በሚመለከት ይግባኝ እንደሚጠይቁ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅጣት ፍርዱ አቃቤ ህጉም ሆኑ ተከላካይ ጠበቃው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ አለመጠየቃቸው ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ቁጥር 18 መድረሱ ታውቋል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በፃፉት ፅሑፍ የተከሰሱ፣የታሰሩም ሆነ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችም የሉም የሚል ተደጋጋሚ ማስተባበያ ቢሰጥም፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጨምሮ ከታሰሩት 18 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች መካከል 15ቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የቀረበባቸው ክስናም ሆነ ፍርድ ከስራቸው ጋር በተያያዘ በፃፉትና በተናገሩት መሆኑ የተመሰረተባቸው ክስ ያመለክታል፡፡

ጋዜጠኞቹ እና የዞን 9 ብሎገሮቹ ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

  • ኤዶምና ማህሌት የመብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ቅሬታ አቅርበዋል

የዞን 9 ብሎገሮቹና ሶስቱ ጋዜጠኞች ያቀረቡት መቃወሚያ ‹‹ተቀባይነት የለውም›› ተብሎ ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጠረባቸው፡፡ ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ የተከፈተባቸው ክስ አግባብ አለመሆኑን የሚገልጽ ስምንት ገጽ የክስ መቃወሚያ አቅርበው የነበረ ቢሆንም አቃቢ ህግ ‹‹ክሱ ምንም ችግር የለበትም፣ የሚሻሻል ነገር የለውም፡፡›› በሚል መቃወሚያውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

zone9 & journalismቃሊቲ እስር ቤት ታስረው የሚገኙት ኤዶም ካሳዬና ማህሌት ፋንታሁን ማረሚያ ቤቱ ውስጥ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ሁለቱ ታሳሪዎች በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ቢሆንም እስር ቤቱ ውስጥ ‹‹አሸባሪ›› የሚል ስም እንደሚሰጣቸው ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ቤተሰብ ብቻ ነው የሚጠይቀን፡፡ ከቤተሰብ ውስጥም የምንጠየቅው ስማቸውን ባስመዘገቡት ብቻ ነው፡፡ ያም ሆኖ የምንጠየቀው ለ10 ደቂቃ ነው፡፡ ለመጠየቅ የሚመጡ ቤተሰቦቻችንም ድብደባ ይፈጸምባቸዋል፡፡›› በሚል ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ባለፈው ችሎቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ታሳሪዎቹ ይደርስብናል በሚሉት በደል ዙሪያ ለዛሬ ቀርበው እንዲያስረዱ ተጠይቀው የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ ዛሬ ያልተገኙት የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ለጥቅምት 25/2007 ዓ.ም ቀርበው ያስረዳሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ኤዶምና ማህሌት ‹‹ይህ የመብት ጉዳይ ስለሆነ አጭር ቀጠሮ ሊሰጥልን ይገባል፡፡›› በማለታቸው ማረሚያ ቤቱ ውስጥ እየተፈጸመብን ነው ያሉትን በደል ብቻ ለማየት ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም.ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ የማረሚያ ቤት ኃላፊው ቀርበው ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኤዶምና ማህሌት ለዋናው ክስም ጥቅምት 25 ደግመው ይቀርባሉ፡፡

በዛሬው ችሎት የታሰሪዎቹ ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የኤምባሲና የተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ በርከት ያለ ታደሚ ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም አቃቢ ህግ ያቀረበው ክስና ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ምርመራ ተደርጎ ሌላ የፍርድ ሂደት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ

የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በአምስት ሺህ ብር ዋስ መለቀቁ ተሰማ

 

ቀደም ሲል መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ለምሳ ሲወጡ ቢሯቸው ታሽጎ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከፈተው እና ለሰባት ሳምንታት ህትመቷ የተቋረጠው የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ማዕከል ማዕከላዊ ፖሊስ ቃሉን እንዲሰጥ በተደረገለት ጥሪ መሰረት ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ማዕከላዊ መቅረቡ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ማዕከላዊ የተጠራው የቀድሞው መኢአድ አመራር የነበረው አቶ ማሙሸት አማረ ክስ መሰረት ቃሉን እንዲሰጥ የነበረ ቢሆንም፤ ማዕከላዊ ምርመራ ክፍልም የጋዜጠኛውን ቃል ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩ አስፈላጊ ሲሆን እንደሚቀርብ በመጠቆም በ5,000.00 (አምስት ሺህ ) ብር ዋስ መለቀቁ ተጠቁሟል፡፡

Getachew workuኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መንግስት በጋዜጠኞች፣ በመፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚወነጅል ዘጋቢ ፊልም በተደጋጋሚ መስራቱን ተከትሎ አታሚ ቤቶች የነፃ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን እንዳያትሙ በተለያዩ የመንግስት አካላት ጫና በማሳደሩ ለ7 ሳምንታት ከህትመት መቋረጧን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የጋዜጣው አዘጋጆች በተደጋጋሚ ስራውን አጠናቀው ቀድም ሲል የሚያትምላቸው አታሚ ድርጅትና ሌሎች አታሚዎች ጋር በተደጋጋሚ ቢኬድም እስካሁን ለማተም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግስት የነፃ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችን፣ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን በተደጋጋሚ መወንጀሉ እና መክሰሱን ተከትሎ የተለያዩ በርካታ ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ከህትምት እና አንባቢ ውጭ እንዲሆኑ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም.  እስከ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከ25 ያላነሱ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የግፍ እስርና ስቃዩን በመሸሽ መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 3 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ከ17 ያላነሱ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች በግፍ ታስረው ይገኛሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቢሮ ታሸገ

ethi-mihedarየኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለምሳ ከቢሮ እንደወጡ መታሸጉን ዋና አዘጋጁ አቶ ጌታቸው ወርቁ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ህትመት ካቋረጥንበት ነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ወደ ተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ሄደን ለማተም ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ከ2 ሳምንት በፊት ማተሚያ ቤት አግኝተን ዝግጅታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ህትመት ልንገባ ስንል ፊውዝ ተቃጠለ በሚል ሰበብ ልትታተም አልቻለችም፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት በመሄድ ለማተም ተስማምተው ዝግጅት በምናደርግበት ሰዓት ከማዕከላዊ ተደውሎ ትፈለጋላችሁ እንድትመጡ የሚል የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ ለምን እንደተፈለጉ ቢጠይቁም በስልክ አልነግርክም ማዕከላዊ ቢሮ ቁጥር 75 አቶ አለበል ብለህ እንድትመጣ እንደተባሉ እሳቸውም ሰኞ እንደሚመጡ ለደዋዩ እንደገለጹላቸው ነገር ግን በዛሬው ዕለት ለምሳ እንደወጡ ቢሮዋቸው እንደታሸገ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በጋዜጠኞችና ብሎገሮች ጉዳይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት በሶሊያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ክስ የመሰረተባቸው ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ዞን 9 ብሎገሮች ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋዓለም ወልደየስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዞን 9 ድህረ-ገፅ ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላ እና ናትናኤል ፈለቀ በአካል ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በአካል ልትቀርብ ስላልቻለች በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ የተሰጠው ትዕዛዝ አቃቤ ህጉ ማስፈፀም ባለመቻሉ ዛሬ ክሳቸው ሊታይ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡:

zonይህ በእንዲህ እንዳለ ተከላካይ ጠበቆች በአቃቤ ህግ የተመሰረተው ክስ የህገ መንግስት ጉዳይ ስለሆነ ፤ለህግ መንግስት አጣሪ ጉባዔ እንዲመራ፣አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ የህግ ስነስርዓቱን ባለመከተሉና ግልፅ ባለመሆኑ መቃወሚያ በማቅረብ ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ አሊያም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር በሚል ያቀረቡት ክርክር ከፍርድ ቤቱ መቅረፀ- ድምፅ ተገልብጦ አልቀረበም በሚል ፍርድ ቤቱ ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

ጉዳያቸው ክስ ሳይመሰረት ከ10 ወራት በላይ እንደፈጀ የሚነገርላቸውና እስካሁን ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳይም በዕለቱ ችሎት ውሎ ነበር፡፡ በዚህም 8ቱ ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ፣ ያለፈው ጥቅምት 2006 ዓ.ም.ለአረፋ በዓል ሲሄዱ፣8ቱ ደግሞ አዲስ አበባ እያሉ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት የነ ኤልያስ ከድር የክስ መዝገብ የሚገኙ 15 ወንዶችና አንዲት ሴት በአጠቃላይ 16 ወጣቶች ጉዳይ ለነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ወቅት እንደታሰሩ የሚነገርላቸውና ከአዳማ 4 ወንድ እና አንዲት ሴት በአጠቃላይ 5 ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በፀጥታ ኃሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ለነሐሴ 12 ቀን 2006 ዓ..ም. ተለዋጭ ቀነቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከተከላካይ ጠበቃ በተለይም በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት ተጠርጣሪ ላይ በማረሚያ ቤቱ አያያዝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል ቅሬታ ቢቀርብም፤ ፍርድ ቤቱ በቀጠሮ ቀን መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መቼ እንደሚጀመር ባይገልፅም ከነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. በኋላ ዝግ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

%d bloggers like this: