Tag Archives: Ethiopian press

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ብስራት ወልደሚካኤል

በስደት ላይ የነበረው ታዋቂው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጠኛው ከነሐሴ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በስደት ይኖርበት ከነበረው ጎረቤት ሀገር ኬንያ ናይሮቢ እያለ ባጋጠመው ህመም ምክንያት ረቡዕ ታህሣሥ 25 ቀን 2010 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተወለደ በ38 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በትውልድ ከተማው አዲስ አበባ በሚገኘው ኮልፌ የሙስሊሞች መካነ መቃብር ሥፍራ ቤተሰቦቹ፥ ወዳጆቹ፥ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ዛሬ አርብ ታህሣሥ 27 ቀን 2010 ዓ. ም. ተፈፅሟል።

Ibrahim Shafi Ahmed
ፎቶ፡ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ (ከጋዜጠኛው ማኅበራዊ ገፅ የተወሰደ)

ጋዜጠኛው ቀደም ሲል በ1997 ዓ. ም. ተደርጎ የነበረውን ምርጫ ውጤት ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ከታሰሩና ጉዳት ከደረሰባቸው በርካታ ዜጎች መካከል ኢብራሂም ሻፊ አንዱ የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ ሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ተወስዶ በመንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበት አካሉ ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ያኔ የደረሰበት ድብደባ ህመሙ ፀንቶበት በመጨረሻም ለህይወቱ ማለፍ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።

የጋዜጠኝነት ሥራ ከጀመረበት ኢትዮ – ስፖርትና መዝናኛ ጋዜጣ በተጨማሪ ኤፍ ኤም አዲስ ሬዲዮ ቶክ ስፖርት፥በሸገር ኤፌ ኤም ሬዲዮ ኳስ ሜዳ እንዲሁም እንዳልክና ማኀደር ፕሮግራም ሰርቷል። በመጨረሻም በምክትል ዋና አዘጋጅነት ይሰራበት የነበረው አዲስ ጉዳይ መፅሔት በተለይም ምርጫ 2007 ዓ. ም. ዋዜማ ተከትሎ መንግሥት በስራ ላይ የነበሩ 5 ምፅሔቶችና 1 ጋዜጣ ላይ ክስ በመመስረት አዘጋጆቹ ላይ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱ ከታወቀ በኋላ ባልደረቦቹን ጨምሮ ከተሰደዱ ከ30 በላይ የሀገሪቱ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሰኞ መስከረም 2 ቀን 1972 ዓ.ም. ከአባቱ አቶ ሻፊ አህመድ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ኬሪያ ጀማል አዲስ አበባ ልዩ ቦታው ከለገሐር ጀርባ በሚገኘው በተለምዶ ቂርቆስ በሚባል አካባቢ ተወለደ። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስም በመጀመሪያ ፈትህ የሙስሊም ትምህርት ቤት፤ በመቀጠልም ፈለገ ዮርዳኖስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት፤ በ1993 ዓ. ም. በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ከዩኒቭርስቲ ከተመረቀ በኋላ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ተመድቦ የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ለአጭር ጊዜ ካገለገለ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል ። አዲስ አበባ ከተመለ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር በመቀጠር ከፍተኛ 12 አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ዳሎል ኮሌጅ በመምህርነት በማገልገል ላይ ሳለ ነበር ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የተቀላቀልው ። ጋዜጠኛ ኢብራሂም ምንም እንኳ ስራውን የጀመረው ብስፖርት ጋዜጠኝነት ቢሆንም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፥ ማኅበራዊና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ሐሳቦቹን በመሰንዘር የሚኢታወቅ ሲሆን፤ ለተወሰ ጊዜም የአዲስ አበባ ዩኒቭርስቲ እግር ኳስ አሰልጣኝ በመሆንም አገልግሏል።

ብዙዎች የሚያውቁት በስፖርት ትንታኔው እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚሰነዝራቸው ሐሳቦቹ ቢሆንም በተለያዩ ማኀበራዊ በጎ አድራጎት ተግባራት ላይም ንቁ ተሳታፊ ነበር። በተለይም ሀገር ቤት ተወልዶ ባደገበትና በኖረበት አዲስ አበባ ቂርቆስ ሰፈር አቅመ ደካማ ወላጆች ያላቸውና እገዛ የሚሹ ህፃናት በየ ዓመቱ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና እንዲያጠናቅቁ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን ድጋፍ በማስተባበርና በመለገስም የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም አዲሱ የትምህርት ዓመት ከጀመሩ በፊት ነሐሴ ወር ላይ ገንዘብና ለትምህርት የሚያስፈልጉ ደብተር እስክሪብቶ፥ እርሳስና የመሳሰሉትን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በመለገስ ተሳትፎ ላይም ዋና ተዋናይ እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል።

ጋዜጠኛው ከቤተሰቦቹ በተጨማሪ በሙያ ባልደረቦቹ፥ ጓደኞቹና አድናቂዎቹ የሚወደድና ተግባቢ ጋዜጠኛ እንደነበር ይታወቃል። ለሀገሩ እና ለህዝቡ ያለው ፍቅርና ተቆርቋሪነትም በስፋት የሚታወቅበት መለያው ነበር። በተለይ ከመደበኛው የጋዜጠኝነት ስራው በተጨምሪ ከሀገሩ እስኪሰደድ ድረስ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኀበር ስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካና ብራዚል የተካሄዱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ የቀጥታ ዘገባዎች በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም ዓለም አቀፍ ዘገባዎችን በአካል በመገኘት ለሀገር ውስጥ አድማጭና አንባብዎች መረጃዎችን ያቀርብም እንደነበር ይታወቃል።

ዳጉ ሚዲያም በጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለገፀ፤ ለጋዜጠኛው ነፍስ እረፍትን፥ ለወዳጅ ቤተሰቦቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ዋስትና ተከለከለ

ከሽብርተኝነት ክስ ነጻ ተብሎ በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንዲከላከል ብይን የተሰጠው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበታል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ከቀረበበት የሽብር ክስ ነጻ በማለት ክሱ ወደ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተቀይሮ አንቀጽ 257 (ሀ) ላይ የተመለከተውን እንዲከላከል ሲል ብይን መስጠቱ ይታወሳል፡፡

Getachew Shiferaw

ይህን ተከትሎ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ እንዳለውና ለአንድ አመት በእስር መቆየቱን በማንሳት አሁን ተከላከል የተባለበት የህግ ክፍል የዋስትና መብት እንደማይከለክል ጠቅሶ የዋስ መብቱ እንዲከበርለት ታህሳስ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ በዕለቱ አቃቤ ህግ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ከሀገር ሊወጣ ስለሚችል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በተነሳው የዋስትና ጥያቄ ላይ መርምሮ ብይን ሰጥቷል፡፡ በዚህ መሰረት ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ‹‹ከሀገር ሊወጣ እንደሚችል ግምት የተወሰደ በመሆኑ›› የዋስትና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም ሲል ፍርድ ቤቱ ዋስትና ከልክሎታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚለውን ግምት ለመውሰድ የቀረበለት ማስረጃ ስለመኖሩ በብይኑ ላይ አላመለከተም፤ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን ባስመዘገበበት ወቅትም ተቃውሞውን በማስረጃ አስደግፎ አላቀረበም ነበር፡፡

‹‹ተከሳሹ ተከላከል የተባለበት የህግ አንቀጽ በመርህ ደረጃ ዋስትና ባያስከለክልም፣ በሁኔታ የሚከለከልበት ጊዜ ግን ስለመኖሩ ተመልክቷል፡፡ እኛም ይህን ተከሳሹ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚለውን ሁኔታ አይተን በሙሉ ድምጽ ተከሳሹ ዋስትናው ይነፈግ ብለን ወስነናል›› ብሏል ችሎቱ የዳኞችን ውሳኔ በተመለከተ ሲገልጽ፡፡

ፍርድ ቤቱም መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለየካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፦ EHRP

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቢሮ ታሸገ

ethi-mihedarየኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለምሳ ከቢሮ እንደወጡ መታሸጉን ዋና አዘጋጁ አቶ ጌታቸው ወርቁ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ህትመት ካቋረጥንበት ነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ወደ ተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ሄደን ለማተም ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ከ2 ሳምንት በፊት ማተሚያ ቤት አግኝተን ዝግጅታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ህትመት ልንገባ ስንል ፊውዝ ተቃጠለ በሚል ሰበብ ልትታተም አልቻለችም፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት በመሄድ ለማተም ተስማምተው ዝግጅት በምናደርግበት ሰዓት ከማዕከላዊ ተደውሎ ትፈለጋላችሁ እንድትመጡ የሚል የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ ለምን እንደተፈለጉ ቢጠይቁም በስልክ አልነግርክም ማዕከላዊ ቢሮ ቁጥር 75 አቶ አለበል ብለህ እንድትመጣ እንደተባሉ እሳቸውም ሰኞ እንደሚመጡ ለደዋዩ እንደገለጹላቸው ነገር ግን በዛሬው ዕለት ለምሳ እንደወጡ ቢሮዋቸው እንደታሸገ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡

%d bloggers like this: