Tag Archives: Ethiopian Journalist

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ብስራት ወልደሚካኤል

በስደት ላይ የነበረው ታዋቂው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ጋዜጠኛው ከነሐሴ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በስደት ይኖርበት ከነበረው ጎረቤት ሀገር ኬንያ ናይሮቢ እያለ ባጋጠመው ህመም ምክንያት ረቡዕ ታህሣሥ 25 ቀን 2010 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተወለደ በ38 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በትውልድ ከተማው አዲስ አበባ በሚገኘው ኮልፌ የሙስሊሞች መካነ መቃብር ሥፍራ ቤተሰቦቹ፥ ወዳጆቹ፥ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ዛሬ አርብ ታህሣሥ 27 ቀን 2010 ዓ. ም. ተፈፅሟል።

Ibrahim Shafi Ahmed
ፎቶ፡ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ (ከጋዜጠኛው ማኅበራዊ ገፅ የተወሰደ)

ጋዜጠኛው ቀደም ሲል በ1997 ዓ. ም. ተደርጎ የነበረውን ምርጫ ውጤት ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ከታሰሩና ጉዳት ከደረሰባቸው በርካታ ዜጎች መካከል ኢብራሂም ሻፊ አንዱ የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ ሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ተወስዶ በመንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበት አካሉ ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ያኔ የደረሰበት ድብደባ ህመሙ ፀንቶበት በመጨረሻም ለህይወቱ ማለፍ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።

የጋዜጠኝነት ሥራ ከጀመረበት ኢትዮ – ስፖርትና መዝናኛ ጋዜጣ በተጨማሪ ኤፍ ኤም አዲስ ሬዲዮ ቶክ ስፖርት፥በሸገር ኤፌ ኤም ሬዲዮ ኳስ ሜዳ እንዲሁም እንዳልክና ማኀደር ፕሮግራም ሰርቷል። በመጨረሻም በምክትል ዋና አዘጋጅነት ይሰራበት የነበረው አዲስ ጉዳይ መፅሔት በተለይም ምርጫ 2007 ዓ. ም. ዋዜማ ተከትሎ መንግሥት በስራ ላይ የነበሩ 5 ምፅሔቶችና 1 ጋዜጣ ላይ ክስ በመመስረት አዘጋጆቹ ላይ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱ ከታወቀ በኋላ ባልደረቦቹን ጨምሮ ከተሰደዱ ከ30 በላይ የሀገሪቱ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሰኞ መስከረም 2 ቀን 1972 ዓ.ም. ከአባቱ አቶ ሻፊ አህመድ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ኬሪያ ጀማል አዲስ አበባ ልዩ ቦታው ከለገሐር ጀርባ በሚገኘው በተለምዶ ቂርቆስ በሚባል አካባቢ ተወለደ። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስም በመጀመሪያ ፈትህ የሙስሊም ትምህርት ቤት፤ በመቀጠልም ፈለገ ዮርዳኖስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት፤ በ1993 ዓ. ም. በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ከዩኒቭርስቲ ከተመረቀ በኋላ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ተመድቦ የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ለአጭር ጊዜ ካገለገለ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል ። አዲስ አበባ ከተመለ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር በመቀጠር ከፍተኛ 12 አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ዳሎል ኮሌጅ በመምህርነት በማገልገል ላይ ሳለ ነበር ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የተቀላቀልው ። ጋዜጠኛ ኢብራሂም ምንም እንኳ ስራውን የጀመረው ብስፖርት ጋዜጠኝነት ቢሆንም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፥ ማኅበራዊና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ሐሳቦቹን በመሰንዘር የሚኢታወቅ ሲሆን፤ ለተወሰ ጊዜም የአዲስ አበባ ዩኒቭርስቲ እግር ኳስ አሰልጣኝ በመሆንም አገልግሏል።

ብዙዎች የሚያውቁት በስፖርት ትንታኔው እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚሰነዝራቸው ሐሳቦቹ ቢሆንም በተለያዩ ማኀበራዊ በጎ አድራጎት ተግባራት ላይም ንቁ ተሳታፊ ነበር። በተለይም ሀገር ቤት ተወልዶ ባደገበትና በኖረበት አዲስ አበባ ቂርቆስ ሰፈር አቅመ ደካማ ወላጆች ያላቸውና እገዛ የሚሹ ህፃናት በየ ዓመቱ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና እንዲያጠናቅቁ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን ድጋፍ በማስተባበርና በመለገስም የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም አዲሱ የትምህርት ዓመት ከጀመሩ በፊት ነሐሴ ወር ላይ ገንዘብና ለትምህርት የሚያስፈልጉ ደብተር እስክሪብቶ፥ እርሳስና የመሳሰሉትን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በመለገስ ተሳትፎ ላይም ዋና ተዋናይ እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል።

ጋዜጠኛው ከቤተሰቦቹ በተጨማሪ በሙያ ባልደረቦቹ፥ ጓደኞቹና አድናቂዎቹ የሚወደድና ተግባቢ ጋዜጠኛ እንደነበር ይታወቃል። ለሀገሩ እና ለህዝቡ ያለው ፍቅርና ተቆርቋሪነትም በስፋት የሚታወቅበት መለያው ነበር። በተለይ ከመደበኛው የጋዜጠኝነት ስራው በተጨምሪ ከሀገሩ እስኪሰደድ ድረስ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኀበር ስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካና ብራዚል የተካሄዱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ የቀጥታ ዘገባዎች በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም ዓለም አቀፍ ዘገባዎችን በአካል በመገኘት ለሀገር ውስጥ አድማጭና አንባብዎች መረጃዎችን ያቀርብም እንደነበር ይታወቃል።

ዳጉ ሚዲያም በጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለገፀ፤ ለጋዜጠኛው ነፍስ እረፍትን፥ ለወዳጅ ቤተሰቦቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።

ጋዜጠኛ ግሩም ተክለኃይማኖት በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ዋለ

በየመን ሰንዓ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ግሩም ተክለኃይማኖትበየመን ሁቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ፡፡ ጋዜጠኛው እንዲታሰር ጠቁሞ ያስያዘው ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀ ኢትዮጵያዊ ጥቆማ ሲሆን፤ ለእስር ሲዳረግ የተገለፀለት ምክንያት በየመን የሚገኘውን መረጃ ከየመን ወደ ውጭ ታወጣለህ እና በተደረጂ ስደተኞች ስም ገንዘብ ትቀበላለህ የሚል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ኃይማኖት ከልጁ ጋር

ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ኃይማኖት ከልጁ ጋር

ጋዜጠኛው በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በየመን ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን ለህዝብ በማሳወቅ የሚታወቅ ሲሆን፤ በየመን ኢትዮጵያውን ስደተኞች የደረሰባቸውን ችግርናወቅታዊ ሁኔታም ለህዝብ በማድረስ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኛ ግሩም ከመታሰሩ በስተቀር እስካሁን ፍርድ ቤት ይቅረብ አይቅረብ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ በአሁን ሰዓት በየመን የተረጋጋ መንግሥትም ሆነ ሁኔታ እንደሌለ ይታወቃል፡፡
ምንጭ፡፤ ነብዩ ሲራክ

በህይወት እስካለሁ ከመስራት ወደ ኋላ አልልም!

ብስራት ወልደሚካኤል

ሰሞኑን እንደፋሽን ይሁን በቂልነት ኢህአዴግዎች የተደናበሩ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ባዶ ሰው ሁሌም ደንባራ መሆኑ የሚጠበቅ ቢሆንም፡፡ ግን አንድ ነገር አለ፤ ያም የእኛን ባላገርነት(ኢትዮጵያዊነት) እንኳን እራሳቸውን መሆን ያልቻሉ ሆድ አምላኪዎች ቀርቶ ሰለጠንን ያሉ ምዕራባውያንም ለሰከንድ ተጠራጥረው አያውቁም፤ ጠንቅቀው በበቂ መረጃ ያውቁናልና፡፡ እራሳቸውን መሆን ያልቻሉ የኢህአዴግ ሰዎች ግን ይህንን ሐቅ የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ ከእነሱ ውጭ ኢትዮጵያዊ እና ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቅ ያለ አይመስላቸውም፡፡ ግን እንዲህ ባዶ አድርጎ የሚሞላቸው ማን ይሆን? ደግሞስ ማንበብና መፃፍ የሚችሉትስ ዝም ብለው ነው እንዴ የተነገራቸውን ብቻ የሚጋቱት? ይገርማል ኸረ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ባካችሁ፤ አንብቡ፣ መርምሩ፣ጠይቁ፣ እወቁ፡፡ ያኔ እራሳችሁን እንጂ ሮኆቦት አትመስሉም፡፡Bisrat3

ደግሞም አለማቅ ወንጀል አይደለም፤ ለማወቅ አለመፈለግና አለመሞከር ግን ለእኔ ድንቁርና ነው የሚመስለኝ፡፡ ምክንያቱም ሰው የመሆን አንዱ ተፈጥሯዊ ምስጢር ሁሌም ለማወቅ መሯሯጥ፣ መዘጋጀትና በተሻለ መንገድ ለመለወጥ መሞከር ብልህነት ነው ብዬ አምናለሁና፤ ካልሆነ ግን ከሌሎች እንሰሳት በምንም አንለይማ፡፡ ይህንን እንድል ያስቻለኝ ሰሞኑን የታዘብኩትና በራሴ ላይ የደረሰው እንዲሁም እየደረሰ ያለው ነገር አስገርሞኝ ነው፤ ግን ፈርቼ አይደለም፣ ለእውነት እና ላመንኩበት ነገር ከመቆም በስተቀር ፍርሃትን ቀድሞውንም አልፈጠረብኝምና፡፡
ባለፈው እንደወትሮ ከጓደኞቼ ጋር 4 ኪሎ አካባቢ የወጉን ተጫውተን ከተለያየን በኋላ በዕለቱ ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡10 ሰዓት ላይ ታክሲ ቀጥታ ወደ እኔ መኖሪያ ሰፈር ስለሌለ እንደ አማራጭ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ እጠቀማለሁ፡፡ ያኔ እንደ አማራጭ የተጠቀምኩትም ከሽሮ ሜዳ በ4 ኪሎ ቄራ የምትሄደውን 75 ቁጥር የከተማ አውቶቡስ ነበር፡፡
እኔም እንደከዚ ቀደሙ ተራ ነገር ካልሆነ ሀገር አማን ነው ብዬ በመሳፈር በዕለቱ ልክ ከምሽቱ 2፡35 ሰዓት ላይ ለመዳረሻዬ በሚቀርበኝ ጎተራ ሞሐ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ጋ ባለው ፌርማታ ወረድሁ፡፡ እንደአጋጣሚ በቦታው ከእኔ ጋር መዳረሻቸው ሆኖ የወረዱት ከ5 ሰዎች አንበልጥም፡፡ ከዛም ወደሳሪስ ታክሲ ለመያዝ የተሻለ አማራጭ ወዳለው ሼል ነዳጅ ማደያው ጋ በጎተራ ማሳለጫ የእግረኛ መንገድ ዘና ብዬ እየተጓዝኩ ሳለሁ ወደ ሙገር ሲሚንቶ አቅጣጫ ባለው የቀድሞው ባቡር ሐዲድ አማካይ ጎተራ ማሳለጫ ጋ ስደርስ ማንነታቸውን የማላውቃቸው 3 ሰዎች (2ቱ ጥቁር ጃኬት፣መነፅርና ኬፕ፣ አንዱ ግራጫ ሱሪና ሹራብ ለብሰዋል፤ ሹራብ የለበሰውን ልደታ ፍርድ ቤት የነ አንዱዓለም አራጌን፣ የነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ የነ በቀለ ገርባን፣…የችሎት ጉዳይ ለመዘገብ ስሄድ በአካል በደንብ አውቀዋለሁ፤ እዛ አይጠፋም ) “ይቅርታ ወንድም ትተባበረናለህ?” አሉኝ፡፡
እኔም ምናልባት አቅጣጫ ጠፍቶባቸው፣ መንገድ ስተው አሊያም የታክሲ ጎድሏቸው ሊሆን ይችላል ብዬ በመገመት የምችለው ከሆነ ችግር የለውም፤ እና ምን ልተባበራችሁ? ስል ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለስኩ፡፡ ወዲያው ከእኔ ጋር ከ75 ቁጥር አውቶቡስ የወረደ ቆዳሞኝ ከኋላዬ በመምጣት ተቀላቀለ፤ ለካ ከእነሱ ጋር ትውውቅና ግብብነት ነበረው፡፡ ስለዚህ 4 ሆኑ ማለት ነው፡፡እዛ አካባቢ ያለው የመንገድ መብራት(ፓውዛ) በፊት ይጠፋል፣አይኖርም ነበር፤ የዛን ቀን ግን ወገግ ብሎ በርቷል ደስ ይላል፤ ሰው ይተላለፍበታልና፡፡
ከዛም በቅርብ ርቀት እያናገሩኝ የነበሩ ሰዎች በቁጥር 4 ሆነው ይበልጥ ወደ እኔ ተጠጉ፡፡ ኬፕ ና መነፅር ካደረጉት 2ቱ መካከል አንዱ ከመቅፅበት ሴንጢ አወጣና ሆዴ ላይ ደግኖ አሁን ምንም ትንፍሽ እንዳትል፣ ለትንሽ ደቂቃ ለጥያቄ ስለምንፈልግህ ከመንገድ ላይ ትንሽ ወረድ እንበል አለኝ፡፡ እኔም እንዴ አታውቁኝ አላውቃችሁ ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የምትጠይቁኝ? ደግሞስ ለማላውቀው ሰው ጥያቄ ለመመለስ እንዲህ ዓይነት ነገር ተገቢ ነው? ምናልባት ከእኔ ጋር የተመሳሰለ ሰው ፈልጋችሁ እንዳይሆን በቅድሚያ ማንነቴን አውቃችኋል ስል ደገምኩላቸው፡፡
እነሱም የምንፈልገው አንተን ነው፣አሁን ጊዜያችንን አትግደል፣ ከዚህ በኋላ የተባልከውን ብቻ ማድረግ ነው አለበለዚያ ላንተ ጥሩ አይሂንም አለኝ ሴንጢውን የደገነው፡፡ ግብር አበሩ ባለኬፕ ደግሞ ወገቡ ላይ የታጠቀውን ሽጉጥ እንዳይለት ከፈት አድርጎ በግርምት ይመለከተኝ ጀመር፡፡ እውነት ለመናገር ገንዘብና ስልክ የሚዘርፉ ሌቦች መስለውኝ ደነገጥኩ፤ ያልጠበኩተ ነውና፡፡ ምክንያቱም የሚረባ ስልክም ሆነ ገንዘብ ስለሌለኝ ካላገኙ አይለቁኝም በሚል ዘዴ ወደማሰላሰሉ ገባሁ፤ ግን በ4 ሰው ያውም አንድ ሽጉጥና አንድ ሴንጢ ይዞ በምሽት ባይሞከርም፡፡
ከዛም እንዳሉት ወረድ አልን፤ አካባቢው ላይ ሁለት ኮንቴይነሮች አሉ፡፡ አንዱ ላይ መብራት ይታያል ሰዎችም እንዳሉ በኋላ አረጋግጫለሁ፡፡ ከነበርንበት የእግረኛ መንገድ ከኮንቴይነሩ ጀርባ ከወሰዱኝ በኋላ የመንገድ ላይ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ይመስል በርካታ ጥያቄዎችን ከበርካታ ፀያፍ ስድብና ዘለፋ ጋር ውርጅብኝ አስተናገድኩ፡፡ ያኔ ከነፃነትና ዜግነት ክብር በስተቀር የገንዘብ ዘራፊ ወይም ሌቦች አለመሆናቸውን አረጋገጥኩ፡፡ እዚህ ላይ ዘለፋና ስድቦቻቸውን አልነግራችሁም፣ በጥሩ ማኀበረሰብና ቤተሰብ አድጌያለሁና ይቅርባችሁ፡፡
ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በቅርቡ ከግንቦት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በኢቦኒ መፅሔት ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኜ መስራት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ከወጡ ፅሑፎች መካከል የአቶ መለስ ዜናዊ 3 ቢሊዮን ዶላር፣ የልጃቸው ሰመሃል መለስ 5 ቢሊዮን ዶላር ጉዳይ እንዲሁም የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ እንዴት ከህገ መንግስቱ ጋር ፍፁም እንደሚጋጩ የተወሰኑ አንቀፆችን ቃል በቃል በማስቀመጥ ስለተፃፈው ጉዳይ በዋናነት ደጋግመው ያነሱ ሲሆን ስለ ስጀኳር ፕሮጀክትና ስለመብራት ጉዳይም ጣል አድርገዋል፡፡ እነሱንም በተመለከተ አንተ ማን ነህ በማያገባህና በማይመለከትህ ነገር ትዘበዝባለህ፣ ደግሞስ የመለስንም ሆነ የሰመሃልን ገንዘብ አንተ ነህ ያስቀመጥከው? በሚል ተናደው ሲናገሩ አደመጥኳቸው፡፡
ከዛም የተፃፉ ነገሮች በሙሉ መረጃና ምንጭ ተጠቅሶባቸው እንጂ በስማ በለው የተፃፈ አንዳች ነገር የለም፤ ቢኖር እንኳ መብቴ ተነካ የሚል አካል በህግ ሊጠይቀኝ ይችላል ስል፤ ሴንጢ የደገነው በግራ ጉንጬ አንድ ጥፊ አላሰኝ፡፡ የበለጠ ተናደድኩና ለምን ትመታኛለህ? ስል ጉረኛው ባለሽጉጥ “ከዚህ በኋላ እናንተን መክሰስና ማሰር አያስፈልግም ከፈለግን እዚሁ እንጨርስሃለን፤ እኛ ግን እስከዛሬ ዝም እያስጠነቀቅንህ ዝም ያልንህ ትመለሳለህ ብለን ነው እንጂ” አለኝ፡፡
እኔም ወስጤ በጣም እየበገነ እኔ ጋዜጠኝነትን ወድጄና ፈልጌ የተማርኩበት፣ አሁንም ሆነ በህይወት እስካለሁ ወደፊትም የምሰራበት ሙያ እንጂ ተገድጄና ተመድቤ የማከናውነው አይደለም፣ በስራዬም ሙያው ከሚጠይቀው ውጭ አልሰራሁም አልሰራምም፣ በስራዬም ሀገራችንና እኔን ጨምሮ ህዝባችንን የሚጎዳ ተግባር ካገኘው እንደማኝኛውም ጋዜጠኛ እና ሀገር ወዳድ ዜጋ ከመዘገብ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ስለዚህ ምን አድርግ ነው ምትሉኝ? አልኳቸው:: በዚህ ንግግሬ የተናደደው ባለሽጉጥ ጉረኛ በካልቾ ሊመታኝ እግሩን ሲሰነዝር መጀመሪያ አንድ ጥፊ ያቀመሰኝ ባለሴንጢው ከለከለው፤ ገረመኝም፡፡
ማንነቱንና በስም የማላውቀው ግን ልደታ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የማየው ሹራብ ለባሹ ንግግሩን ቀጠለ ከዚህ በኋላ በየትኛውም ጋዜጣ፣ መፅሔትም ሆነ ብሎግ ላይ ብትሰራ በህይወትህ ፍረድ፣ ከእንግዲህ እናንተን(ኢህአዴግን የሚያበሳጩ ጋዜጠኞችን ማለቱ መሰለኝ) ማሰር አያስፈልግም፡፡ በህይወት መኖር ከፈለክ በቅርቡ መልዕክት ይመጣልሃል፤ ከዛም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ድርጅት ጉዳይ ሲል ከባስ አብሮኝ የወረደው የህዝብ አደረጃጀት ሲል አረመውና ትሄድና የመጨረሻ ውሳኔህንና ምርጫህን ታሳውቀናለህ፤ ከዛ እንተያያለን አለ፡፡
የአማርኛ አነጋገር ዘይቤው ወደ ትግርኛ የሚመራው ጉረኛው ባለ ሽጉጥ ቀጠል አደረገና ከዚህ በኋላ ድጋሚ ላንተ የሚነገርህ የለም፤ እንደውም አላርፍም ብለህ ብትሰራ(ብትፅፍ ለማለት ነው) ባንተ ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦችህ በተለይም በምስኪን አባትህ እንጀራና ህይወት ላይ ነው የምትፈርደው ሲል(ውስጤን ሳቅ አፈነው) አስጠነቀቀኝ፡፡ ባለሴንጢው አጋች ደግሞ ይሄንን ነገር ለማንም እንዳትናገር፣ ብትናገር በራስህ ላይ ነው የምትፈርደው፤ ደግሞም አራዳ አይደለሽ ይገባሻል ብለን እናስባለን ሲል ዛቻን በቂልነት አወረደው፡፡ ወይ ማባበል፡፡ ለካ እንዲህ ተራ መሐይሞች ኖረዋል ጎበዝ፡፡ የእኔ አባት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ገና ተማሪ ሳለሁ ገና የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነሐሴ 13 ቀን 1989 ዓ.ም. ሲሆን አሁን 16 ዓመታት አልፎታል፡፡ ይሄ አነጋገሩ ሀገራችንን ምን ዓይነት ደህንነት እየጠበቃት እንዳለ የበለጠ ስጋጥ ውስጥ ከተተኝ፤ ምክንያቱም ስለ ደህንነት ስራ ካነበብኳቸው የስለላ መፅሐፎች በጥቂቱም ቢሆን አውቃለሁና፡፡ የማያውቁትን መረጃ መዘላበድስ ምን አመጣው? እንዲህም ማስፈራራት የለ፡፡
በመጨረሻም ከ50 ደቂቃ በላይ ከወሰደው እገታ፣ጥያቄ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ በኋላ ሳልፈ፤ጋቸውና ሳልከፍላቸው ጊዜያዊ አጃቢዎቼ(አጋቼ) ጋር ወደ ሼል ማደያው በእነሱ ፊትና ኋላ መሪነት አብረን ሄድን፡፡ ከዛም የታክሲ መያዣው ጋር ስንደርስ አራቱም መንገዱን አቋርጠው ጎተራ ተዋበች(አቦኝ) ህንፃ ጋር ባለችው መንገድ ሲገቡ ተመለከትኩ፡፡ በርግጥ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ከተመሰረተ ጀምሮ አዘጋጅ ሆኜ በሰራሁበት ወቅት በርካታ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን እስከ ተራው የኢህአዴግ ካድሬ ደርሶኛል፡፡ እንደውም ነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. የችሎት መረጃ ይዤ ወደቢሮ ስሄድ ልደታና ባምቢስ አካባቢ በጠራራ ፀሐይ በማላውቃቸው ተመሳሳይ ሰዎች ሁለቴ መታገቴን አልረሳሁትም፡፡ ይሁን እንጂ እኔ ህዝብና ሀገርን የሚጎዳ አንዳች ነገር እስካልፈፀምኩና ህግ እስካልተላለፉ በስተቀር እውነት ያልኩትንና ያመንኩበትን ከመስራት ወደ ኋላ እንደማልል ያኔም በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ፤ ባይሰሙኝም፡፡
እኔም ታክሲ አግኝቼ ቀጥታ ወደ ሳሪስ በመሄድ ሳሪስ ፖሊስ ጣቢያ ገባሁ፡፡ በወቅቱ የሚተባበረኝ ፖሊስ ቢኖር ኖሮ(ለወጉም ቢሆን) የገቡበትን ስለማውቅ በራሴ የኮንትራት ታክሲ ይዤም ቢሆን ብንሄድ አጋቾቹን እናገኛቸው ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ በዕለቱ በፖሊስ ጣቢያው የነበረው ቃል ተቀባይና ወንጀል ምርመራ ክፍል የነበረው ኮንስታብል ጥላሁን ታዴ ሁኔታውን በደንብ ከጠየቀኝ በኋላ አንድም ቃል ሳይፅፍና መፍትሄ ያለውን ሳይጠቁመኝ ያንተን ጉዳይ ነገ ጠዋት(ነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.) የጣቢያው ዋና ኢንስፔክተር አበበ ሲመጡ ትነግራቸውና እሳቸው ያዩልሃል አለኝና አሰናበተኝ፡፡ ያኔ ይበልጥ ተናደድኩ፡፡ ከዛም በተነገረኝ ሰዓት ጠዋት ወደ ጣቢያው ስሄድ ዋና ኢንስፔክተሩ ለስብሰባ ስለሄዱ ከሰዓት እንድመለስ በሌላ ፖሊስ ተነገረኝ፡፡ የሚገርመው የእኔን ጉዳዩ ቀድሞንም እንደ ሰማ የማክሰኞ ተረኛው ፖሊስ ሲነግረኝ የምርመራ ቢሮ የነበረው ሌላው ተረኛ ፖሊስ ደግሞ የአንተ ጉዳይ ተራ ስለሆን ምን እንዲደረግለህ ትፈልጋለህ፣ ስለማይሆን ነውና ቤትህ ብትሄድ ይሻላል፤ጨረስን ሲል አመናጨቀኝ ፤ ይሄ ደግሞ እኔ ያልነገርኩት ጉዳዩን የሰማ ፖሊስ መሆኑ ነው፡፡
ቀናው ፖሊስ በነገረኝ መሰረት ዋና ኢንስፔክተሩ ከሰዓት ስሄድ አሁንም ከስብሰባ እንዳልመጡና ነገ ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2005ዓ.ም. ጠዋት እንድመለስ ነገረኝ፡፡ በድጋሚ በተነገረኝ መሰረት ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠዋት ወደፖሊስ ጣቢያው ስሄድ ዋና ኢንስፔክተሩ አሉ፤ ግን ከቢሮ ውጭ ግቢ ውስጥ ናቸው፡፡ በአካል ስለማላውቃቸው ያኔ ሰኞ ሁኔታውን የነገርኩት ፖሊስ በርቀት አይቶኝ ወደ እኔ በመምጣት “ዋና ኢንስፔክተር አበበ አያሌው እሳቸው ናቸው፣ አናግራቸው” አለኝ፡፡ እኔም ቀርቤ ስለ ሁኔታው በሙሉ ነገርኳቸው፡፡
እሳቸውም “ይህ ጉዳይ ከባድ ስለሆነ ኢንስፔክተር አበበ ነው የላከኝ በልና ጉዳዩን ቀድመህ እዚህ ማሳወቅህን ንገራቸውና ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መመሪያ ዋና የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ወደ ሆኑት ምክትል ኮማንደር ስዩም አስፍሃ ጋር ሂድና ንገራቸው አሉኝ፡፡” ከዛም ጥንቃቄ እንዳደርግና “በየትኛውም ቦታ ሆነህ የምትጠራጠረው ተመሳሳይ ድርጊትም ሆነ ሰዎቹን ካገኘሃቸውና ካስታወስካቸው ወዲያውኑ ደውልልኝ፣አይዞህ ብለው ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ሰጡኝ፣ በሳቸው ሁኔታም ከምር ፖሊስ ናቸው ስል ተደሰትኩ፡፡
ረቡዕ ዕለት ወዲያው ኢንስፔክተሩ እንዳዘዙኝ ወደ ክፍለከተማው ፖሊስ መመሪያ ዋና የወንጀል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ስዩም ጋር ሄድኩና ሁኔታውን በሙሉ ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም “ድርጊቱ ሲፈፀም ምስክር የሚሆንህ ሰው ካለ አሁኑኑ ክስ መስርተህ ልንከታተላቸው እንችላለን፤ ምስክር ከሌለ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ በአካል አውቀዋለሁ የምትለውን ሰው በደንብ ተከታተለው፤ ሲከታተልህም ሆነ አንድ ነገር ለማድረግ በምትጠራጠርበት ጊዜ ወዲያው በጣቢያው ስልክ ደውልልንና ፖሊስ እናዛለን፤ እስከዚያ ግን ድርጊቱን በዕለት ሁኔታ በዝርዝር አስመዝግብና ይቀመጥ፣ ነገ ሰዎቹንም ሆነ ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ ድርጊት ለመፈፀም የሚሞክሩ ካሉ አንዱ እንኳ ቢያዝ ሊሎችን መያዝና አስፈላጊውን ማድረግ ይቻላል፤ አንተም ለእራስህ ጥንቃቄ አድርግ አሉኝ፡፡” እኔ በኮማንደሩ በተባልኩት መሰረት ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2005ዓ.ም. በፖሊስ መመሪያው የእለት ሁኔታ ቁጥር 3 ላይ አስመዝግቤ አጋቾቹ በቅርቡ መልዕክት ይመጣልሃል ያሉትን እየጠበቅሁ ነው፡፡
ትሄዳለህ የተባልኩበት ቦታ ኃላፊ ስምም ተጠቅሶልኛል(ጅሎች አይደሉ)፣ መልዕክት ሲመጣልህ ትሄዳለህ የተባልኩበት ሰው በተጠቀሰው ኃላፊነት ደረጃ ሳይሆን ከዛ አነስ ባለ የኢህአዴግ ማዕረግ እየሰራ መሆኑን አጣርቼ ደርሼበታለሁ፤መልዕክቱ ሲመጣም ቀድሜ ለፖሊስ ስላስመዘገብኩ ያኔ ፖሊስም ይፈተንበታል ብዬ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ግን እስካሁን የተባለው መልዕክት ሳይመጣ ሳምንት ቢያልፈውም ትናንት ደግሞ በሌላ ሁለት የወጣት ሸበቶዎች ነገር ፍለጋ ሲሞከር መልስም ሳልሰጣቸው ጥያቸው ሄድኩ፡፡ ምክንያቱም አጠገቤ በርካታ ሰዎች ስለነበሩ ምንም ደፍረው እንደማያደርጉ በመገመትና ሆን ብለው ጥል በመፍጠር ለሌላ ዘዴ መዘጋጀታቸው ሌላኛው ስልት መሆኑን ከሌላ የሙያ ባልደረባዬ የተማርኩ ስለሆነ ነቄ ብዬ ሸወድኳቸው፤ ነገር እንዳላበዛ እንጂ እሱም ቀላል አልነበረም፡፡ ከዛም አንዱ ትንሽ እራቅ ካሉ በኋላ ወደ ኋላ በመዞር የማትገኝ መስሎህ ነው አይደል? እናገኝሃለን ብሎ የሚመጥናቸውን የለመዱትን ተራ ስድብ ጣል አድርጎ ያሰቡት እንዳልተሳካ ገብቷቸው ነኩት፡፡
በጡንቻ ለሚያስቡ ፤ እውነት ነው፣ ለሀገራችንና ለወገናችን ይጠቅማል ያልኩትንና ሙያዊ ስነምግባርና ህግን ሳልጥስ መቼም ቢሆን ከመፃፍና በምችለው ሁሉ ከመስራት ወደ ኋላ እንደማልል አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ ያውም በሀገሬ! በቻልኩት መጠን ሁሉ መብቴን አሳልፌ እንደማልሰጥና ሁሌም ቢሆን ህገወጥ ድርጊትን አጥብቄ እንደምቃወም መግለፅ እወዳለሁ፡፡ ምንም እንኳ http://www.addismedia.wordpress.com ድህረ-ገፄ (ብሎጌ) ከሰኔ 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር ውስጥ እንዳይነበብ ቢደረግም እድሜ ለቴክኖሎጂ መፃፌንና ፖስት ማድረጌን አላቆምም፡፡ በምችለው መጠንና ባለኝ ጊዜ ሁሉ ባገኘሁት ጋዜጣና መፅሔትም ቢሆን ከመስራት ወደ ኋላ አልልም፤ መኖርን ብፈልግም የእናንተን የሞት ማስፈራሪያና ዛቻ ፈርቼ የፈፀማችሁትን እንዳልናገር ብታስጠነቅቁኝም፤ድርጊታችሁንም ቢሆን ከቅደም ተከተሉ ያስቀመጥቁት ፍርሃት ስለሌለብኝ እንደሆነ የሚገባችሁ ይመስለኛል፡፡
እስካሁን ግን የሚጠበቅብኝን ያህል እስካሁን እንዳልሰራሁ እንጂ እንዲህ በትንሹ መደናበራችሁን ከወቅሁማ ኸረ ገና ብዙ ይሰራል፡፡ ስለዚህ መሰማትና ማስተዋል ከቻላችሁ(ማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ በብዛት እንዳሉ ስለማውቅ ነው) ከምር ነው የምላችሁ ህሊናዬን በሆዴ ስለማልሸጥና ስለማልፈራ ብዙ ባትለፉ ይሻላል ስል ወንድማዊ ምክሬን ጀባ ብያለሁ፡፡ ባይሆን እናንተም ቢያንስ ሰው ሁኑ እና እንደ ሰው በማሰብ እራሳችሁን ነፃ ብታደርጉ እንዲሁም ክፉ ሲያዟችሁ መልካሙን በማድረግ መልካም እንዲሰሩ ብታደርጉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ወደ ዓይነ ህሊናችሁ እንድትመለሱና መልካም እንድትሆኑ እና መልካሙ እንዲገጥማችሁ መልካሙን ሁሉ እመኝላኋለሁ፤ችርስ፡፡

%d bloggers like this: