Tag Archives: Journalist Getachew Worku

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የአንድ ዓመት እስር እና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት

ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣም 10ሺህ ብር ቅጣት ተፈረደበት

getachew-worku

(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም.  የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ አንድ ዓመት እስራትና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት፡፡ ከጋዜጠኛው በተጨማሪ ድርጅቱ ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣም የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

ጋዜጠኛው እና ጋዜጣው ላይ የዛሬ ፍርድ ውሳኔ የተላለፈው አዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተፈፀመ የተባለውን ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በጋዜጣው መሰራጨቱን ተከትሎ፤ የደብሩ እና የቤተክህነቱ ኃላፊዎች ”በጋዜጣው ስማችን ጠፍቷል” በሚል በመሰረቱት ክስለ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ቅጣት ውሳኔ በኋላም ጋዜጠኛው በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የእስር ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መታሰሩ ታውቋል፡፡ በችሎቱ ላይ ከወዳጆቹ እና ጋዜጠኞች በተጨማሪ ከሳሾቹ ካህናት እና የደብሩ ኃላፊዎች ተገኝተው እንደነበር የተጠቆመ ሲሆን፤ ጋዜጠኛውም በመጨረሻ ”እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም፤እውነቱ አንድ ቀን ይወጣል፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደብኝ ጋዜጣውን ለመዝጋት ታቅዶ ነው፡፡” ማለቱ ተሰምቷል፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ቀደም ሲል ሐዋሳ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ላይ የተፈፀሙ የሙስና መረጃዎችን በጋዜጣው ለህዝብ በማድረሱ ተከሶ ከፍተኛ መጉላላት፣ እስርና እንግልት እንዲሁም በባልደረባው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው በአዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈፀመ ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በቂ መረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም፤ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ጋዜጠኛው ለቀጣይ አንድ ዓመት በእስር ቅጣት እንዲያሳልፍ በመወሰኑ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ለንባብ ይበቃ የነበረው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ህትመትም እንደማይቀጥል መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ከኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት በተጨማሪ በመንግሥት እውቅና የተነፈገውና በ2004 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መብትና ጥቅም እንዲሁም በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ ለመስራት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

እነ ጌታቸው ሺፈራው 28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፤ በሽብር ተጠርጥረው መያዛቸውን መርማሪያቸው ተናግሯል

‹‹ካሁን በፊት ይዝቱብኝ ነበር፤ ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው የታሰርኩት›› ጌታቸው ሺፈራው

Getachew Shiferaw

ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም በያሉበት ታድነው የታሰሩት ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ዳንኤል ተስፋየ እና ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል ታህሳስ 16 ቀን 2008 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በሽብር ተጠርጥረው መታሰራቸውን በመግለጽ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፖሊስ ታሳሪዎቹ የተጠረጠሩበትን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎች ‹‹የአርበኞች ግንቦት 7 አባል በመሆን፣ በመመልመል፣ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ወንጀል ሊፈጽሙ ሲሉ ተይዘዋል›› ብሏል፡፡

ተጠርጣሪዎች ስለተጠረጠሩበት ወንጀል እና ስለተጠየቀባቸው የጊዜ ቀጠሮ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ‹‹ካሁን በፊት በተደጋጋሚ ይዝቱብኝ ነበር፤ እኔ ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው የተያዝኩት፡፡ ቤቴ ሲፈተሽ የተገኘውም የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሰማያዊና መድረክ) መግለጫዎችና ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ከተባለው ወንጀል ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም፤ በነጻ ልሰናበት ይገባል›› ሲል ተናግሯል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ አባሉ አቶ ዳንኤል ተስፋየ በበኩሉ ‹‹በፍተሻ የተያዙብኝ ባንዲራ፣ ሲዲ እና ስልክ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለምርመራ የተጠየቀውን ያህል ጊዜ መፈቀድ የለበትም፤ አጭር ቀጠሮ ይሰጠን›› ሲል ጠይቋል፡፡
ሦስተኛው ተጠርጣሪ አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል ደግሞ ‹‹እኔ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በኢህአዴግ ተደራጅቼ የምሰራ ሰው ነኝ፡፡ ፖሊስ ከገለጸው ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም፤ ድርጅቱን ጭራሽ አላውቀውም፤ የልጅ አባት ስለሆንኩ አጭር ቀጠሮ ይሰጠኝ›› በማለት አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግን ፖሊስ የጠየቀውን 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለጥር 14 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ከሁለት ወራት በፊት ከአርባምንጭ ተይዘው ወደማዕከላዊ የመጡት በአርባምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እነ ሉሉ መሰለ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ትናንት ለእስር ከተዳረጉት መካከል የሆኑት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አቶ ኤርሚያስ ጸጋየ፣ አቶ ፍሬው ተክሌ እና አቶ ቴዎድሮስ አስፋው ዛሬ ከሰዓት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በአምስት ሺህ ብር ዋስ መለቀቁ ተሰማ

 

ቀደም ሲል መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ለምሳ ሲወጡ ቢሯቸው ታሽጎ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከፈተው እና ለሰባት ሳምንታት ህትመቷ የተቋረጠው የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ማዕከል ማዕከላዊ ፖሊስ ቃሉን እንዲሰጥ በተደረገለት ጥሪ መሰረት ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ማዕከላዊ መቅረቡ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ማዕከላዊ የተጠራው የቀድሞው መኢአድ አመራር የነበረው አቶ ማሙሸት አማረ ክስ መሰረት ቃሉን እንዲሰጥ የነበረ ቢሆንም፤ ማዕከላዊ ምርመራ ክፍልም የጋዜጠኛውን ቃል ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩ አስፈላጊ ሲሆን እንደሚቀርብ በመጠቆም በ5,000.00 (አምስት ሺህ ) ብር ዋስ መለቀቁ ተጠቁሟል፡፡

Getachew workuኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መንግስት በጋዜጠኞች፣ በመፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚወነጅል ዘጋቢ ፊልም በተደጋጋሚ መስራቱን ተከትሎ አታሚ ቤቶች የነፃ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን እንዳያትሙ በተለያዩ የመንግስት አካላት ጫና በማሳደሩ ለ7 ሳምንታት ከህትመት መቋረጧን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የጋዜጣው አዘጋጆች በተደጋጋሚ ስራውን አጠናቀው ቀድም ሲል የሚያትምላቸው አታሚ ድርጅትና ሌሎች አታሚዎች ጋር በተደጋጋሚ ቢኬድም እስካሁን ለማተም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግስት የነፃ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችን፣ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን በተደጋጋሚ መወንጀሉ እና መክሰሱን ተከትሎ የተለያዩ በርካታ ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ከህትምት እና አንባቢ ውጭ እንዲሆኑ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም.  እስከ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከ25 ያላነሱ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የግፍ እስርና ስቃዩን በመሸሽ መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 3 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ከ17 ያላነሱ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች በግፍ ታስረው ይገኛሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

%d bloggers like this: