Tag Archives: Ethiopian zone 9 bloggers

ሰበር ዜና፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሶስት ጋዜጠኞችን እና ሁለት የዞን 9 ብሎገሮችን ከእስር መልቀቁን አስታወቀ

ከሚያዚያ አጋማሽ 2007 ዓ.ም. በፌደራሉ አቃቤ ህግ በ”ሽብርተኝነት” ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ እየታየ ከነበረው የዞን 9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች መካከል፤ ሶስቱን ጋዜጠኞች እና ሁለቱን ብሎገሮች ክሳቸው በፍትህ ሚኒስቴር ውድቅ ተደርጎ መፈታታቸውን የገዥው መንግሥት ደጋፊ የሆነው ሬዲዮ ፋናን ዋቢ በማድረግ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
ዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር የተፈቱት ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ፤ የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን እንደሆኑ ታውቋል፡፡
እንደሬዲዮ ፋና ዘገባ ከሆኑ ቀሪዎቹ የዞን 9 ብሎገሮች መካከል በእስር ላይ የሚገኙት በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እና በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ሶሊያና ሽመልስ የክስ ጉዳዩን እንደሚቀጥል የፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ ማስታወቁን ጨምሮ ዘግቧል፡፡

ከግራ ወደቀኝ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን

ከግራ ወደቀኝ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን

ጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮች ቀደም ሲል በፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ በ”ሽብር ወንጀል” ተከሰው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለብይን ተቀጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የዞን 9 ብሎገሮችና ሦስቱ ጋዜጠኞች ለብይን ተቀጠሩ

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች እና ሶስቱ ጋዜጠኞች የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ያስፈልጋቸዋል ወይስ በነጻ ይሰናበቱ የሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም ብሎገሮቹና ጋዜጠኞቹ ጥቁር ለብሰው ችሎት ፊት ቀርበው ነበር፡፡ መዝገቡ ለሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቀጥሮ የነበረው አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ ላይ የሲ.ዲ ዶክሜንተሪ ማስረጃ ማቅረቡን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በጽ/ቤት አይቶ ሲ.ዲው በግልጽ ችሎት ይታይ ወይስ በዝግ የሚለውን ብይን ለመስጠት ነበር፡፡
በዚህም ፍርድ ቤቱ ሲ.ዲው በችሎት መታየቱ ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው በሚል ዳኞች ብቻ ተመልከተውት በማስረጃነት እንዲያዝ ሲል መግለፁ ታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎ ተከሳሾች በብይኑ ላይ አለን ያሉትን አቤቱታ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያሰሙ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ግን ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ አቤታቱውን ከመመዝገብ ውጭ ለውጥ እንደማይኖረው መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡

ዞን9
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ወይስ በነጻ ይሰናበቱ በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ጋዜጠኞቹ እና የዞን 9 ብሎገሮቹ ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

  • ኤዶምና ማህሌት የመብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ቅሬታ አቅርበዋል

የዞን 9 ብሎገሮቹና ሶስቱ ጋዜጠኞች ያቀረቡት መቃወሚያ ‹‹ተቀባይነት የለውም›› ተብሎ ለጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጠረባቸው፡፡ ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ የተከፈተባቸው ክስ አግባብ አለመሆኑን የሚገልጽ ስምንት ገጽ የክስ መቃወሚያ አቅርበው የነበረ ቢሆንም አቃቢ ህግ ‹‹ክሱ ምንም ችግር የለበትም፣ የሚሻሻል ነገር የለውም፡፡›› በሚል መቃወሚያውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

zone9 & journalismቃሊቲ እስር ቤት ታስረው የሚገኙት ኤዶም ካሳዬና ማህሌት ፋንታሁን ማረሚያ ቤቱ ውስጥ የመብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ሁለቱ ታሳሪዎች በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ቢሆንም እስር ቤቱ ውስጥ ‹‹አሸባሪ›› የሚል ስም እንደሚሰጣቸው ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ቤተሰብ ብቻ ነው የሚጠይቀን፡፡ ከቤተሰብ ውስጥም የምንጠየቅው ስማቸውን ባስመዘገቡት ብቻ ነው፡፡ ያም ሆኖ የምንጠየቀው ለ10 ደቂቃ ነው፡፡ ለመጠየቅ የሚመጡ ቤተሰቦቻችንም ድብደባ ይፈጸምባቸዋል፡፡›› በሚል ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ባለፈው ችሎቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ታሳሪዎቹ ይደርስብናል በሚሉት በደል ዙሪያ ለዛሬ ቀርበው እንዲያስረዱ ተጠይቀው የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ ዛሬ ያልተገኙት የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ለጥቅምት 25/2007 ዓ.ም ቀርበው ያስረዳሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ኤዶምና ማህሌት ‹‹ይህ የመብት ጉዳይ ስለሆነ አጭር ቀጠሮ ሊሰጥልን ይገባል፡፡›› በማለታቸው ማረሚያ ቤቱ ውስጥ እየተፈጸመብን ነው ያሉትን በደል ብቻ ለማየት ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም.ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ የማረሚያ ቤት ኃላፊው ቀርበው ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኤዶምና ማህሌት ለዋናው ክስም ጥቅምት 25 ደግመው ይቀርባሉ፡፡

በዛሬው ችሎት የታሰሪዎቹ ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የኤምባሲና የተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ በርከት ያለ ታደሚ ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም አቃቢ ህግ ያቀረበው ክስና ጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ምርመራ ተደርጎ ሌላ የፍርድ ሂደት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ

ዞን 9 ብሎገሮች ሌላ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፤ የፖሊስየ28 ተጨማሪ ቀናት ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠረጠርኳቸው ያላቸውን 9 ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ሚያዝያ 2006 ዓ.ም.ቢያስርም እስካሁን ምንም ዓይነት ህጋዊ ክስ ሳይመሰርት፤ ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2006ዓ.ም. በድጋሚ ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ፖሊስ ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ቀጠሮ የነበራቸውን እና በማዕከላዊ ያሰራቸውን የዞን 9 ብሎገሮች መካከል በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማህሌት ፋንታሁን እና አቤል ዋበላን ይዞ ቢቀርብም፤ እንደተለመደው የቴክኒክ ምርመራዬን አልጨረስኩም፣ ከተሰከሳሾች የተገኙ መረጃዎች ተተርጉመው አላለቁም፣…የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ ተጨማሪ የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

hgtፍርድ ቤቱ እስካሁን የተሰጠው ጊዜ በቂ ነው በማለት የተጠየቀውን የ28 ቀናት ውድቅ ቢያደርግም፤ ፖሊስ ምርመራው አጠናቆ እንዲቀርብ የ14 ቀናት ጊዜ በመስጠት ለሐምሌ 6 ቀን 2006ዓ.ም.ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ይሁን እንጂ ዕለቱ እሁድ ቀን የሚውል በመሆኑ እና መዝገቡ ከእንግዲህ በተዘዋዋሪ ተረኛ ዳኛ ሳይሆን በመደበኛ ችሎት መታየት ስላለበት ለሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00ሰዓት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ መሰጠቱን ከተከላካይ ጠበቃቸው አቶ አምሃ መኮንን መረዳት ተችሏል፡፡ ጉዳዩ ሲታይ የነበረው ከሌሎች ቀናት በተለየ ዛሬ ቤተሰብም በችሎቱ ላይ እንዳይታደም ተከልክሏል፡፡

በፍርድ ቤቱ ግቢ በርካታ የእስረኞቹ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና ጋዜጠኞች ቢገኙም አንዳቸውም ችሎቱን እንዲከታተሉ አልተፈቀደም ነበር፡፡ ፖሊስ ያሰራቸውን ተጠርጣሪዎች ይዞ ወደ ችሎት ሲገባ በፍርድ ቤቱ ግቢ ችሎቱን ለመታደም ከመጡት መካከል ዮናታን ተስፋዬ እና ምኞት የሚባሉ ወጣቶችን በሞባይል ፎቶ ለማንሳት ሞክራችኋል በሚል ወደ ማዕከላዊ ይዟቸው የሄዱ ሲሆን፤ ከሰዓታት በኋላ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እስካሁን ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙት ቀሪዎቹ 6ቱ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች የፊታችን ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ቀነ ቀጠሮ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

%d bloggers like this: