እውነት እና ፖለቲካዊ ትክክለኛነት
አቤል ዋበላ
እውነትን ለማስረዳት የሄግሊያን ትንታኔን መሰረት ማድረግ መርጣለው፡፡ እንደ ሄግሊያን ትንታኔ እውነት በወቅታዊ ሁኔታው የተረጋጋ የሚመስል እና ለውጥን በራሱ አቅጣጫ የሚያስተካክል ነው፡፡ ከታሪክ ፣ከትምህርት እና በአስተውሎት የሚገኙ እውነቶች አሉ፡፡ እነዚህ እውነቶችን መሰረት ያደረገ የቡድንም ሆነ የግለሰብ እንቅስቃሴ በስኬት የመጠናቀቅ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ በዙርያችን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ለእነዚህ እውነቶች ከመቆም ያግዱናል፡፡ ወይ እነርሱን የሙጢኝ ብለን የቀረን እንደሆን እኛን እሰከመጥፋት የሚያደርሱ ጉዳቶች ያስከትላሉ፡፡ ስለዚህ ህልውናችን ከሁሉም ነገር ስለሚበልጥን እያወቅን ዝም እንላለን፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ እውነቱን ብንናገር ለማኀበረሰቡም የማይጠቅም ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ይሆንና በሆድ ይፍጀው እናልፈዋለን፡፡
ከዚህ ጋር አያይዤ ማንሳት የምፈለገው ሌላው ነጥብ ደግሞ በእንግሊዘኛው Political Correctness የሚባለውን ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ግርድፍ ትርጉሙ ሌሎችን ሊያስቆጣ ይቻላል በማለት እንቅስቃሴን እና ንግግርን መገደብ ወይም ለሌሎች በሚመች መልኩ ማስተካከል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ጥሩ ፖለቲከኛ የሚባለውም እንደ እውነቱ የሚያደርግ ሳይሆን እንደጊዜው የሚናገር እና የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ለህዝቦች በሰላም፣ በእኩልነት፣ በነጻነት አብሮ መኖር እና ወንድማማችነት ሲባል የተደረገ ሲሆን ለአድራጊው ክብር የሚያጎናጽፍ እና አስተዋይነቱን የሚያስረዳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለዕኩይ ዓላማ፣ ለፍቅረ ነዋይ፣ ለስልጣን ጥማት፣ ለእዩኝ እዩኝ ባይነት(Publicity) አልያም በማስተዋል እጦት እና በሞኛሞኝነት ሲሆን ደግሞ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ እውነትን ስላልተከተለ የስኬት መጠኑ የተገደበ ይሆናል፡፡ ማኀበረሰቡም ከእውነት እና ከታቀደለት ስኬት ስለሚርቅ ድርብ ኪሳራ ይደርስበታል፡፡
ይህንን ሳስብ ሁልጊዜ ወደ ህሊናዬ የሚመጣው መለስ እና ኢሳያስ የሄዱበት መንገድ ነው፡፡ መለስ እና ኢሳያስ ለዕኩይ ዓላማቸው ሲሉ እውነትን ያጣመሙ እና በተንኮል ብዙዎችን ያሳቱ ናቸው፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ በትውልድ ከመለስ ዜናዊ የበለጠ የትግራይ ተወላጅ ሆኖ ሳለ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ነፍጥ አነሳ፡፡ (የመገንጠል ጥያቄ እንዲነሳ ያደረጉ ሌሎች ታሪካዊ እውነታዎች መኖራቸውን እየካድኩኝ አለመሆኑ ይሰመርበት) የኤርትራ ህዝብ በደም፣ በ ስነ ልቦና ቅርጽ፣ በኢኮኖሚ እና በባህል ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር እንደማይችል ሳይረዳው ቀርቶ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህንን እውነት ከአደባባይ ገሸሽ አድርጎ አትራፊ የመሰለውን ለግለሰባዊ ፍላጎቱ የተመቸውን መንገድ መረጠ፡፡ የኤርትራ እና ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የእርስ በርስ ጥገኝነት በትዕቢቱ ብቻ ሊለውጠው እንደማይችል ሲረዳ ይህንን የሚያስቀጥልበት ሸር ጎነጎነ፡፡ ለዚህም ወያኔን እንደ አሻንጉሊት በኢትዮጵያ በማንገስ እንደፈለገው እየጠመዘዘ ኤርትራን በቀጥታ ኢትዮጵያን ደግሞ በእጅ አዙር መግዛት ፈለገ፡፡ ይህ ለተወሰኑ አመታት የተሳካለት መሰለ፡፡ በመጀመሪያዎቹ የወያኔ አገዛዝ ዓመታት የኢትዮጵያ የደህንነት እና ፖሊስ የመሳሰሉ ወሳኝ የፖለቲካ ሀይል ማዕከሎች በኤርትራውያን የበላይነት ነበር የሚመሩት፡፡ በኢትዮጵያ የሚበቅሉ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ኤርትራ ከአንጋፋ አቅራቢ ሀገሮች አንዷ የሆነችበት አመታትም ነበሩ፡፡ ይህ ከእውነት ርቆ ያዋቀረው ደባ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ፈረሰበት፡፡ ለዚህም ይመስላል ከጦርነቱ ወዲህ ኢትዮጵያን የኤርትራ ዋነኛ ጠላት አድርጎ ብዙኃኑን ኤርትራዊ ለስደት ዳርጎ ካርታው ጠፍቶበት የተቀመጠው፡፡ ህዝቡም ይህንን ‘አጋሜ አምባገነን’ የሚያስወግድበት መላ ጠፍቶት እየባከነ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ መለስ ዜናዊ መጀመሪያ አከባቢ ምንም እንኳን ከኢሳያስ አፈወርቂ የበለጠ የኤርትራ ደም ቢኖረውም በትግራይ ብሔርተኝነት እና “ትግራይ-ትግሪኝ” በምትባል ሐሳባዊ ማንነት ሲዋልል እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ትግራይንም ሆነ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የተነጠሉ ሀገሮች ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚበልጥ በመረዳቱ ከኢሳያስ በመንፈሱ አንድ የሆነ ነገር ግን በቅርጹ የተለየ ሴራን ሸረበ፡፡ ትግራይ ብቻዋን በመሆኗ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የምታጣውን ነገር ለማካካስ ከትግራይ ዘውግ ውጪ ያሉ ደካማዎችን በመሰብሰብ እነርሱን የሌላው ህዝብ የይስሙላ እንደራሴ በማድረግ በመላው ኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ አዛዥ ሆነ፡፡ እውነትን ትቶ በተንኮል መንገድ ስለሄደ ሁሉንም የሚያስማማው ስኬት ላይ ባይደርስም እርሱ እና ቤተሰቡ፣ በርከት ያሉ ከአንድ ዘውግ የተገኙ እና ሌሎች ጥቂት ሰዎች የሀገሪቱን ሀብት እንዲበዘብዙ መንገድ ከፈተ፡፡ እርሱን ሞት ቢወስደውም ይህ የብዝበዛ መንገድ በቅርቡ የሚዘጋ አይመስልም፡፡
ይህ የተንኮል መንገድ እና የደረሰብን ሀገራዊ ኪሳራ ብዙ ሊያስተምረን ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአንዳንድ ሁኔታዎች ለመረዳት እንደሞከርኩት የገባን አልመሰለኝም፡፡ በውሽት እና በሸር መንግስት የሚባል ነገር ተቋቋመ ያንን ተከትለን ፈሰስን፡፡ የወንበዴ ስብስብ ፓርቲ ነኝ ሲል እንዳልሆነ እያወቅን ለፖለቲካዊ ትክክለኝነት ስንል ተቀበልነው፡፡ ይባስ ብሎ ይህ የወንበዴ ቡድን ራሱ ጠፍጥፎ ካዘጋጃቸው ሦስት ቡድኖች ጋር ሆኖ ሀገራዊ ፓርቲ ነኝ ሲል አንዴ መስመሩ ስለገባን ይህንንም ከመቀበል በቀር አማራጭ አልነበረንም፡፡ ከፕሮፌሰር አስራት ጀምሮ ብዙዎች ለዚህ ወንበዴ ቡድን እውቅና ሰጥተው ወንበዴው ባዘጋጀው ቀመር መሰረት መጫወትን መረጡ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉ ጥቂቶች ገና ስርዓቱ ሲጀመር አንስቶ ይህ ስርዓት ቅንነት እና መዋቅራዊ ርዕቱነት ይጎለዋል ቢሉም የሰማቸው አልነበረም፡፡ ለዚህ ለወንበዴ ቡድን የሚሰጥ ዕውቅና ጫፍ ላይ የደረሰው በ97 ምርጫ ነው፡፡ገና ከጫካ ያልወጣውን ቡድን ሀገር በሙሉ ተሰብስቦ የዴሞክራሲ አዋላጅ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ በባህሪው ያልነበረውን ነገር መሸከም ስላልቻለ እውነተኛ ማንነቱ ገሀድ ወጣ፡፡ ከጠብመንጃ አፈሙዝ በቀር ሌላ ቋንቋ እንደሌለው ከህጻናት እስከ አረጋውያን በመግደል አረጋገጠ፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት አመታት ማስመሰሉን ቀንሶ እንዳሻው እያሰረ፣ እያሰቃየ አንዳንዴም እየገደለ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ድፍን ሀያ አምስት የተንኮል አመታት፡፡
ከላይ በመግቢያዬ እንዳነሳኹት ለህዝብ ጥቅም በጎ ዓላማ ሲባል እያወቅን እውነትን ብንጎዳትም ከሰው የሚበልጥ ነገር በምድር ስለሌለ ይኹን ብለን ማለፉ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን እንዲህ እውነትን እየጎዳን፣ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን እየመረጥን ሀያ አምስት አመታትን አሳልፈን ህዝቡን ለብሔራዊ ጭቆና፣ ችጋር እና ስደት ከዳረግነው ሀገሪቱን ለመጠን አልባ ምዝበራ ከተውናት የሄድንበትን መንገድ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የዱር እንሰሳ ስላባበልነው ብቻ ለማዳ ይሆናል ማለት ዘበት ነው፡፡ አንዳንድ የዱር እንስሳት ፈጽሞ ሰው አይለምዱም፡፡ ወያኔም እንደነዚያ አራዊት መሆኑን ባለፉት ሀያ አምስት አመታት አስመስክሯል፡፡ እስኪ እውነት ይዘን ደግሞ እንሞክረው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም እውነት ወደ ስኬት ለማድረስ የተሻለ ዕድል አለው፡፡
ለግለሰባዊ ፍላጎቱ የቆመ ሰው ምንም አይነት አሳማኝ ነጥቦች ብንደረድርለት ፖለቲካዊ ትክክለኝነቱን የሙጢኝ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱ የእንጀራ ገመዱ በዚያ የታሰረ ሰለሆነ ነው፡፡ አሁን እኔ ለመሞገት እየሞከርኩኝ ያለኹት በማስተዋል እጥረት ወይም በሞኛሞኝነት እንደው በዚህ መንገድ ብንሞክር ብለው ለሚያስቡ የዋሃን ነው፡፡ ይህንን ሙከራ የሚወልደው ህዝባዊ እምቢተኝነት እና ሰላማዊ ትግልን በትክክል አለመረዳት ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰላማዊ ተጋይ ገዢው በፈቀደለት ቦይ ብቻ የሚፈስ ከሆነ ትግሉን ይጀምረዋል እንጂ አይጨርሰውም፡፡ ሰላማዊ ትግል ግን የህዝብን እውነት መሰረት አድርጎ በተፈቀደለትም ባልተፈቀደለትም የሚጓዝ ነው፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት ቀመር ያለው ሳይሆን እንደየሀገሮች ሁኔታ ባልተለመደ(unorthodox) መልኩ የሚደራጅ ነው፡፡ይህ ያልተለመደ መልክ ምዕራባዊ ቀመር አያስፈልገውም፡፡ ይህ ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚጀምረው ጨቋኙ ስርዓት ከህዝቡ የሚፈልገውን እውቅና በመንፈግ ነው፡፡ የህዝብን እውነት የያዘ በቂ ሰው እውቅና እሰኪነፍገው ድረስ ስርዓቱ በሁለት እግሩ እንደቆመ ይቀጥላል፡፡
በሀገራችን ያለውን ጨቋኝ ስርዓት ዕድሜውን የሚያራዝመው ሲጨንቀው ሀይል (Force) ከመጠቀሙ በቀር ብዙኃኑን ኢትዮጵያዊ እና ዓለምአቀፉን ማኀበረሰብ በማታለል (fraud) ነው፡፡ ይህንን ማታለል ደግሞ መስበር የሚቻለው ዕውቅና በመንፈግ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚባል የአራት ፓርቲዎች ስብስብ አይደለም ሕወኃት የሚባል የፖለቲካ ማኀበር ሀገሪቱን እየመራት እንዳልሆነ ለፖለቲካዊ ትክክለኝነት ብለን ካልሆነ በቀር ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ይህ ቡድን ስሙ “ወያኔ” ነው፡፡ እውቅና መንፈግ የሚጀመረው ይህንን ጭምብል በማውለቅ ነው፡፡ ማን ትዕዛዝ እያስተላለፈ የሰብዓዊ መብት ረጋጣ እንደሚፈጸም እነርሱ እጅ ገብቶ የነበረ ሰው ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ወያኔ የሚለውን የትግርኛ ቃል እየጠቀሱ ትርጉሙ እንዲህ ነው እንዲያ ነው የሚል ሁሉ የዚህን ቡድን የተረት ጅብድ አጽዳቂዎች ናቸው፡፡ ወያኔ የሚለው ቃል የትግርኛ ትርጉሙን ተሻግሮ በሕገ ወጥ መንገድ የፖለቲካ ሀይልን ለሀያ አምስት አመታት ይዞ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ሲገፍ የቆየ ቡድን መጠሪያ ሆኗል፡፡ ስለ ነጻነት የምር ግድ የሚለው ሁሉ ከዚህ ቡድን እና መጠሪያው ‘ወያኔ’ መሻገር ይገባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢዮብ ባልቻ እንዳስተዋለው ‘የዘመኑ ወጣት በጭፍን የ “ያ ትውልድ”ን ታሪክ በጭፍን ከማድነቅ ወጥቶ በጥንቃቄ ወደ መመልከት እንደገባው’ የትግራይ ወጣትም ለህዝቦች በሰላም፣ በእኩልነት፣ በነጻነት አብሮ መኖር እና ወንድማማችነት ሲል ከባዶ ተረት ወደ እውነታ መምጣት ይገባዋል፡፡ የዚህ ቡድን ሰዎች ላለፉት ሀያ አምስት አመታት በሀገሪቱ ላይ የፈጸሟቸውን ተግባሮች ተመልክቶ ትምህርታቸውን ጥለው ጫካ ገብተው ያንን የትግራይ ገበሬ ብዙ የህይወት መስዋዕትነት ያስከፈሉት ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ይገባዋል፡፡
በመጨረሻም የወያኔ አገዛዝ እውነትን ሳይከተል ነገር ግን ሌሎቻችን በሰጠነው የፖለቲካ ትክክለኛነት ይሁንታ ሀያ አምስት አመታትን ተጉዟል፡፡ ወደ መፍትሔው ስንመጣ ወደኋላ መመለስ አለብን ማለት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ስርዓቱ ቅንነት ቢጎለውም በእነዚህ ዓመታት በጎም ሆነ መጥፎ ነገሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ በጎ ነገሮች እና ከመጥፎዎቹ ውስጥ ደግሞ ወደኋላ ለመመለስ የሚከብዱ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመለየት ሰፊ ጥናት እና የሰከነ ውይይትን አድርገን ነገን ማሰብ መጀመር ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ይህ ለወያኔ እውቅና መስጠትን አይጨምርም፡፡ ምክንያቱም ወያኔን ያለስሙ ኢህአዴግ ወይም ሕወሓት ብለን ስንጠራው ጭቆናው ለሚቀጥሉት ሀያ አምስት እና ሐምሳ አመታት እንዲቀጥል እየወሰንን ነው፡፡
እንደኔ ቆሻሻ ፊት ከማነስ ይሰውራችኹ!
አቤል ዋበላ
“እያዩ ፈንገስ” ወይም “ፌስታሌን” የተሰኘውን ትያትር ብዙዎቻችኹ አይታችኹታል ብዬ ገምታለው አልያም ስለ ማኀበራዊ እና ፖለቲካ ቀመስ ትችቶቹ በወሬ በወሬ ሰምታችኃል፡፡ እኔ ዝናውን የሰማኹት እስር ቤት ሳለኹኝ ነበር፡፡ ወያኔ እግዜር የስራዋን ይስጣትና እኔ ከወህኒ እስክወጣ ድረስ መድረክ ላይ አቆየችው፡፡ በትያትር ቤት ታድሜ እንደተዋራለት ሆኖ አገኘኹት፡፡ ይህን ጥበብ ለመድረክ እንዲበቃ ያደረጉትን እና በመድረክ እንዳይታይ ለማስተጓጎል ያልሞከሩትን አመስግኛለው፡፡
የትያትሩ አንድ ገቢር ግን እስካኹን ድረስ ውስጤ ቀርቷል፡፡ የተነሳኹበትን ሐሳብ ለማስረዳት ይረዳኛልና ይህንን ክፍል እንድተርከው ይፈቀድልኝ፡፡ እያዩ ፈንገስ ውድ ንብረቶቼ የሚላቸው ዕቃዎቹን የያዘ አንድ ፌስታል እንደጠፋበት ይናገር እና ለፍለጋ ይሰማራል፡፡ በሚኖርበት ሰፈር አቅራቢያ በሚገኙ ገንዳዎች፣ ቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ፈልጎ ያጣዋል፡፡ የክፍለ ከተማው ቆሻሻ መጣያ ስፍራ ሄዶ ቢፈልግም እንዳላገኘው ለተመልካቹ በሞኖሎግ ያስረዳል፡፡ በመጨረሻም የአዲስ አባባ ቆሻሻ በሙሉ “ቆሼ” እንደሚጣል እንደሰማ ተናግሮ ለፍለጋ ወደ መድረክ በስተጀርባ (ወደ ቆሼ) ይሄዳል፡፡ ከዚያ ሲመለስ የተናገረው ነገር ነው የኔን ቀልብ የማረከው፡፡ እያዩ አንዲት ፌስታሉን ፍለጋ ቆሼ ቢሄድ እራሱን ተራራ ከሚያክለው ቆሻሻ ጋር አወዳድሮ ወደተመልካቹ ተንበርክኮ “ዛሬ በቆሻሻ ፊት አነስኩላችኹ፤ እንደ እኔ በቆሻሻ ፊት ከማነስ ይሰወራችኹ” ሲል ሲቃ በተመላበት ድምጽ ተናገረ፡፡
ይህንን እንደተናገረ እኔ ከዚያ ትያትር ቤት ወጣኹኝ፡፡ በሐሳብ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ማዕከላዊ፣ አዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኛ ማረፊያ ቤት ቂሊንጦ እና ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አስራ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ሄጃለው፡፡ ለአንድ አመት ከስድስት ወር በቆሻሻ ፊት ያነስኩባከቸውን ጊዜያት አስታውስኩኝ፡፡ እየታመመኩኝ ውስጤ የሚሰማኝን ነገር አውጥቼ እንዳልናገረው የመግለጽ አቅም እያነሰኝ እያለ እያዩ ፈንገስ ደረሰልኝ፡፡
በቆሻሻ ፊት ማነስ እንዲህ ነው በሀገርህ እንደሁለተኛ ዜጋ ስለምትታይ የመብት ጥያቄዎችን አታነሳም ስለዚህ ከስርዓቱ አገልጋዮች ጋር ያለህ ግንኙነት የተገደበ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው ነንና መሰረታዊ፣ ሰብዓዊ ፍላጎቶች ይኖሩናል፡፡ እነዚህን ለማግኘት ከማንም ጋር ይሁን መነጋገር፣ እርዳታን መጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ለምሳሌ ሳይቤሪያ እያለን ከእስረኞቹ መሀል አንድ ሰው ይታመማል፡፡ አንዳንዴ ህመሙ እንደአተት(የሆድ ህመም) የሚደርግ ይሆንና እንቸገራለን፡፡ በር ደብድበን ይህ ሰው ሽንት ቤት ደርሶ እንዲመጣ ካላደረግን ማታ መጥተው ለአስር ደቂቃ ሽንት ቤት እንድንሄድ እስኪፈቅዱልን ድረስ የማይሆን ነገር እያየን እና እያሸተትን መቆየታችን ነው፡፡ በር ስንደበድብ ሰላማዊ ዋርድያ ካጋጠመን ታማሚውን “ቶሎ ደርሰህ ተመለስ” ይለውና ለእኛ ደግሞ ትንሽ ንጹህ አየር እንዲገባ በሩን ከፈት አድርጎት ይቆማል፡፡ ሁልጊዜ ግን ሰላማዊ ሰው ላያጋጥም ይችላል፡፡ “እዛው ቁጭ ይበል” ብሎ የሚል ይኖራል፡፡ ውጤቱ የከፋ ስለሚሆን ‘አረ ባክህ እረዳን . . . እና ሌሎች ኢትዮጵያዊ የልመና ዘዴዎችን’ ተጠቅመን ልቡን ለማለስለስ እንሞክራለን፡፡ ብዙ ጊዜ አይሳካም፡፡ ከዚህ በታች ከቆሻሻ በታች ማነስ ከየት ይመጣል፡፡ ባለ ማዕረግ ከሆነ ደግሞ ኮማንደር ወይም ሳጅን ማለትም ይጠበቅብናል፡፡
ቅሊንጦም እንዲሁ በቆሻሻ ፊት ሳንስ ከርሜ ነው የወጣኹት፡፡ ታመህ ቤተሰብ መድሃኒት እንዲያስገባልህ ለመጠየቅ ወይም ለሌላ በጣም አስፈላጊ ሰብዓዊ ጉዳይ አጋጥሞህ ሱፐር ኢንቴንዳንት፣ ኦፌሰር ምናምን ብለህ ያልተከበረውን አክብረህ መጥራት ይጠበቅብሃል፡፡ ሌላው ይቅርና “ካቴናው እጄን አጥብቆ ይዞታል ትንሽ አላላልኝ” ማለት በራሱ ለስድብ እና ማንጓጠጥ ሊዳርግ ይችላል፡፡ አንዳንድ በቆሻሻ ፊት ማነስን እና ንትርኩን የጠሉ ወዳጆቼ ካቴናው እጃቸውን እየሰረሰረው ችለው ይቀመጣሉ፡፡
ፍርድ ቤት ደግሞ ሌላው መተናነሻ ቦታ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ጠበቃ ባላቆም፣ ባልከራከር እና የተውኔቱ አካል ባልሆን እመርጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በጓደኛ እና ቤተሰብ ግፊት የማልሆነውን ሆኜ ነው የከረምኩት፡፡ የዐቃቤ ህግ በሬ ወለደ ክስ እና ሙያዊ ብቃት ማነስ አእምሮ ሊገምተው ከሚችለው በላይ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ያለህ ብቸኛ ምክኒያታዊ ድርጊት ከት ከት ብሎ መሳቅ ነው፡፡ ነገር ግን ችሎት በመድፈር እስከስድስት ወር እስራት ስለሚፈረድብህ ከቆሻሻ አንሰህ ሰብዓዊነትህን ለቀህ ምንም እንዳልተገረመ ሰው ለመሆን ትሞክራለህ፡፡ ለማይረባ ጉዳይ አንድ ወር ወይም ሁለት ወር ሲቀጥርህ የተከበረ ዳኛ እና ፍርድ ቤት እንደሌሉ እያወቅክ “የተከበረው ፍርድ ቤት፣ ክቡር ዳኛ ይህ ነገር ትንሽ አልዘገየም? በማረሚያ ቤት ሆነን እየተንገላታን ስለሆነ ቀኑን አጠር ቢያደርጉት” ልትል እጅህን ብታነሳ አይተው እንዳላየ ያልፉሃል፡፡ እንድትናገር ዕድሉን እንዲሰጡህ ድምጽህን ስታሰማ ስነ ስርዓት የጎደላቸው ሰዎች “ስነ ስርዓት፣ ስነ ስርዓት” ብለው ይገስጹሃል፡፡
እያዩ ተራራ በሚያክል ቆሻሻ ፊት ማነሱን ሲናገር እነዚህን እና ሌሎች በርካታ ህሊናን የመፈታተኑ ቅጽበታቶችን ነው ያስታወስኩት፡፡ ነገም ቆሼ መውረድ አልቀረልኝም፡፡ ነገ ከጓደኞቼ BefeQadu Z. Hailu, Natnail Feleke, Atnaf Brhane እና Soleyana Shimeles Gebremichael (በሌለችበት) ጋር ጠቅላይ ፍርድ ቤት እቀርባለው፡፡ ያው እያዩ ከክፍለ ከተማ ወደ ከተማ ሲሄድ የቆሻሻ ተራራው ግዝፈት እንዳስደነገጠው እኔም እንዲሁ ክው ብያለው፡፡ ክርክር ተሰምቶ ስላለቀ የመጨረሻውን ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወይ ቂሊንጦ አለያም ፒያሳ እንገናኝ፡፡ ምንም እንኳን አረጋዊ ሁኜ ለምርቃት ባልበቃም መልካም ምኞቴን ትቼላችኹ ልሂድ፡- እንደኔ በቆሻሻ ፊት ከማነስ ይሰውራችኹ!
ገራፊዬን አየኹት
አቤል ዋበላ
ቀልድ ያለፈበት ጨዋታ ሆኗል፡፡ አሁን ዘውጉ ተቀይሯል፡፡ ፍጥጥ ግጥጥ ያለ ዕውናዊ ድርሰትን መመልከት ይዘናል፡፡አይን አያየው የለም፡፡ አሁን ደግሞ ገራፊዬን አሳየኝ፡፡ በኮምፒዩተር የኤሌክትሪክ ገመድ ጀርባዬ እስኪቀደድ የገረፈኝን፣ በመጥረጊያ እንጨት ውስጥ እግሬን ያነደደኝን፣ እጄ በካቴና ታስሮ ወለል ላይ ያንከባለለኝን፣ ጨለማ ቤት ውስጥ አስገብቶ ከየት እንደመጣ በማላውቀው ጅራፍ አሳሬን ያበላኝን፣ እናቴን ከመቃብር ጠርቼ “አንቺ እናቴ ለምን ጥሩ ሁን ብለሽ አሳደግሽኝ? ብዙ ክፉ ሰዎች እንዳሉ ለምን አልመከርሽኝም?” ብዬ እንድወቅሳት ያደረገኝን፣ ወንድ፣ የወንዶች ቁና በካቴና የታሰረን ሰው በዕኩለ ሌሊት ጠርቶ አፉ ውስጥ ጨርቅ ወትፎ የሚደበድብ በአይኔ በብረቱ አየኹት፡፡
ዮናታን ተስፋዬ ለጊዜያዊ ቀነ ቀጠሮ አራዳ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ሰምቼ ነው ወደዚያ የሄድኩት፡፡ ይህችን የተለመደች ሰርከስ ሁሉም የፖለቲካ እስረኛ ይወዛወዛታል፡፡በማዕከላዊ ይጀመራል ከዚያ አራዳ ፍርድ ቤት ይቀጥላል፡፡ የማዕከላዊ ደብዳቢዎች በጨለማ የሚያሰቃዩትን እስረኛ በቀን ሰው መስለው (ወገኞች ናቸው አንዳንዴማ ዩኒፎርምም ያጠልቃሉ) ፍርድ ቤት ያቀርቡታል፡፡ ውሸት ውሸቱን ይቀባጥራሉ፡፡ “ግበረ አበሮቹን በኢንተርፖል እያሳደድን ነው፣ ክቡር ዳኛ በዋስ ከተለለቀቁ ልማታችንን ያደናቅፋሉ፡፡ ወህኒ ሰብረው እስረኛ ያስፈታሉ” የመሳሰሉትን በጠራራ ጸሐይ ይቀባጥራሉ፡፡ እየቀለድኩኝ አይደልም የምሬን ነው እንዲህ አይነት በሬ ወለደ ምክንያት በጆሮዬ ሰምቻለው፡፡ ዳኛውም አብሮ ይተውናል፡፡ የፈለጉትን ቀን ያህል ያራዝማል፡፡
ገራፊዬንም ያየሁት እኔንና ጓደኞቼን እንደነዳው እንዲሁ ተረኛውን ገፈት ቀማሽ ሲያመጣ ነው፡፡ ላንዳፍታ አይኖቻችን ተጋጩ፡፡ አስተውሎኝ ይሁን አይሁን አላውቅም በፍርድ ቤቱ ቢሮዎች መሐል ገብቶ ተሰወረ፡፡ እኔ ግን በእርግጠኝነት ለይቸዋለው፡፡ ውስጤ ዳግም ተቆጣ፡፡ እስር ቤት ብቻዬን ደጋግሜ ባሰብኩት ቁጥር እንደአዲስ የልቤ ቁስል ያመረቅዝ ነበር፡፡ ቂም ስቋጥር እና ስፈታ ከአመት በላይ ቆይቻለው፡፡ ቂም ይዣለው በውድም ሆነ በግድ ኢትዮጵያዊ በሆነ ሁሉ ላይ ቂም ይዣለው፡፡ እንዴት ሰው በሀገሩ ይህንን ጉድ ተሸክሞ ይኖራል? እንዴት እንደዚህ አይነት ተቋም በመዲናይቱ እምብርት ላይ አስቀምጦ ዝም ይላል? ይህን ባርቤሪዝም ጌጡ ካደረገ ማኀበረሰብ ጋር በቀላሉ የማይበርድ ግጭት ውስጥ ነኝ፡፡ ስለዚህ በመንገድ ስታገኙኝ ፊቴ ጥቁር ብሎ ብታገኙኝ “ምን ሆነህ ነው?” አትበሉኝ፡፡ ቂም ይዤ ነው፡፡ ተራ ማኩረፍ አድርጋችኹ አትውሰዱት ስር የሰደደ ከነፍስ የሚቀዳ ጸብ ነው፡፡
በግርፋት የተሰነጠቀውን ጀርባዬ በቅባት ላሹኝ ዕድሜ ለእነ ኤባ ቁስሉ እዛው ማዕከላዊ ነው የዳነው፡፡ የልቤ ስንጥቅ ግን አልዳነም ፡፡ ያ ዘላለም ክብረት “ምድር ብዙ ክፋት የሚፈጸምባት ቦታ ናት በእኛ ላይ የደረሰውም አዲስ ነገር አይደለም” እያለ ብዙ እንዳላዝን ቢመክረኝም ያቄመው ልቤን ሊያሸንፈው አልቻለም ነበር፡፡ የተገኘሁበት፣ ያሳደገኝ ማኀበረሰብ ላይ እንዳቄምኩኝ ከእስር ወጣኹኝ፡፡ ባለፉት አራት ወራት በአንጻራዊ ነጻነት ማሳለፌ ግን ትንሽ እንዳዘናጋኝ የገባኝ ግን በቀደም ገራፊዬን ያየኹት ቀን ነው፡፡ወይ ጊዜ ስንቱን ያስረሳል አልኩኝ፡፡ አሁን ከእስር መፈታት ብርቅ የሆነበት ጊዜ አልፏል፡፡ ቁስሌ ዳግም አመርቅዟል፡፡ ገራፊዬን እና አለቆቹን የያዘው ህንጻ ካልፈረሰ አልያም ሙዚየም ካልሆነ ዕርቅ የማይታሰብ ነው፡፡ ድሮ እስር ቤት ሳለኹኝ በእስረኛ ማጓጓዣ መኪና ወደ ፍርድ ቤት ስንመላለስ በመስኮት ስመለከተው የዕለት ጉርሱን ለማብሰል የሚራኮተው አዳሜ አሁንም ውስጡ ሁኜ ስመለከተው ከሆዱ በቀር የኔ ቁስል ግድ የሰጠው አይመስልም፡፡ ስለዚህ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ ብዬ ይቅር እላለው? ውስጤ የበለጠ ስለሻከረ እምቢኝ ብያለው፡፡ ይህ የአንዲት ነጠላ ነፍስ መብት ነው፡፡ በገዛ ነፍሴ ጥላቻን ማርገዝ መብቴ ነው፡፡ ከፈለጋችኹ ለዐቃቤ ሕግ ንገሩትና በፊት ‘የማኀበረሰቡን ጤና እና ደህንነት ለአደጋ በማጋለጥ’ እንደ ከሰሰኝ አሁን ደግም ‘በማኀበረሰቡ ላይ ስር የሰደደ ጥላቻና ቂም በመቋጠር’ ይክሰሰኝ፡፡
እነ ኤቢሳ አካላዊ ቁስሌን እንደሳምራዊው ሰው በቅባት እንዳሹልኝ አሁን ደግሞ ዘመዶቻቸው የተሰበረ መንፈሴን የቆሰለ እኔነቴን ሊጥገኑ ተነስተዋል፡፡ የእነኤቢሳ፣ የእነቶፊቅ እና የእነ ቶላ ዘመዶች እኔን ከህመሜ ሊያድኑኝ ደማቸውን እየከፈሉ መሆናቸውን ድፍን ፌስቡክ እየተመለከተው ነው፡፡ አዲስ አበቤ “አገር ሊያፈርሱ ነው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም” ቅብርጥሴ ቅብርጥሴ ቢልም እኔ ግን ከሚፈርሰው አገር ከፒያሳ ከፍ ብሎ ያለው ማዕከላዊ ጎልቶ ይታየኛል፡፡ ስለዚህ በመሬት ላይ ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን ወገኖቼን ይቅር ብያለው፡፡ ከነዚህ በቀር ሌላው ማኀበረሰብ “እርሱ” አይደለም “እኔ” ራሱ ይቅርታን አያገኛትም፡፡ አራዳ ፍርድ ቤት መሄዴ አይቀርም፡፡ በማዕከላዊ በርም አልፋለው፡፡ በየጊዜው እየሄደኩኝ ከገራፊዎቼ አንዱን እያየው ጥላቻዬን እያደስኩኝ እመጣለው፡፡ ቁስሉ ይበልጥ እንዲቆጠቁጠኝ ወደገራፊዬ ተጠግቼ አይኖቹን በአይኖቼ አድናለው፡፡ አይገርምም ግን ………….…ገራፊዬ እስካሁን እዚያው ነው፡፡
የእኔና አየር መንገዳችን ክርክር – የኢ-ፍትሓዊነት ማሳያ?!
በአቤል ዋበላ
ያኔ ይደብረኝ ነበር፡፡ መሥሪያ ቤቱ ይደብረኛል፡፡ አለቆቼ ይደብሩኛል፤ የሚጠገ’ኑት አውሮጵላኖች ሽታ ይደብረኛል፡፡ አቧራ የጠገቡት የጥገና መሳሪያዎቼ ይደብሩኛል፡፡ ለምን ይህንን ስህተት ሠራሁ እያልኩኝ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ለምን በኮሌጅ የተማርኩትን የመሀንዲስነት ሙያ ትቼ ስለምን የአውሮጵላን ጥገና ሙያ ውስጥ ገባሁኝ እያልኩኝ ራሴን እጠይቃለው፡፡ ከኮሌጅ እንደወጣሁኝ ሥራ የጀመርኩት በቢሾፍቱ ከተማ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ የተወሰኑ ወራት ጫንጮ የሚገኝ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠርቻለው፡፡ ጥግ ጥግ ከመዞር ገላግሎ አዲስ አበባን እንድከትምባት ዕድሉን ያመቻቸልኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ያኔ የትውልድ ከተማዬ ውስጥ፣ አዲስ አበባ መሆን እፈልግ ነበር፡፡ አራት ኪሎ ከቤተ መንግሥቱም፣ ከቤተ ክህነቱም መራቅ አልፈልግም ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ የማወቅ የመማር ነበር፡፡ ጫንጮ ብርዳማ ናት፡፡ እንደ አየር ንብረቷ የዐሳብ ገበያዋም ለእኔ ፍላጎት የሚያመረቃ አልነበረም፡፡ በወቅቱ በስስት የምትነበበውን አዲስ ነገር ጋዜጣን ለማግኘት እንኳን ወደ መዲናዋ የሚመላለሱ ሹፌሮችን መለማመጥ ግዴታዬ ነበር፡፡
ህወሓት መራሹ ስርዓት እንዳይሆን-እንዳይሆን ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የዚህ የተሳከረ ፖሊሲ ግንባር ቀደም ሰለባ ከሆኑት መካከል የቴክኖሎጂ ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት መጠንና ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በገፍ ከሚያስመርቁት ተማሪ ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ በቴክኖሎጂ ምሩቃን እና ቀጣሪዎቻቸው መካከል የተዛባ ግንኙነት በግልጽ ይታያል፡፡ ከተማሪዎች መካከል በኮሌጅ በብዙ ትጋት የቀሰሙትን ወደ ንድፈ ሐሳብ የሚያደላ ትምህርት በተግባር የሚያውሉበት ዕድል የሚያገኙት እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛው ግን የዕለት እንጀራውን ለማብሰል በተገኘው የሥራ መስክ መሰማራት ዕድል ፈንታው ነው፡፡ አንዳንድ ቀጣሪዎች ይህንን ዕድል ተጠቅመው ለሥራ መደቡ ከሚያስፈልገው በላይ የሰለጠነ (overqualified) ምሩቅን በዝቅተኛ ክፍያ ይቀጥራሉ፡፡ ‘ስለአፈር እና ድንጋይ ምንነት አጥንተው በሲቪል ምህንድስና የተመረቁ ልጆች ኮብል ስቶን ለመጥረብ መርቴሎ ጨበጡ’ ተብሎ በከተማው መነጋገሪያ ከመሆኑ በፊት ብዙ ምሩቃን ከሠለጠኑበት የቴክኖሎጂ ዕውቀት እጅግ በጣም ጥቂቱን ብቻ በሚሻ የሥራ መደብ ተሰማርተው ነበር፡፡ ከነዚህ overqualified የሆኑ ምሩቃንን ባልተገባ መልኩ ከሚቀጥሩ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኝበታል፡፡ አየር መንገዱ በርካታ ባለዲግሪዎችን ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቻ በሚገኝ ዕውቀት በሚሠሩ የሥራ መደቦች ላይ ቀጥሮ ያሠራ ነበር፡፡ አሁንም ይህ ተቀይሯል ብዬ አልገምትም፡፡
እኔም አዲስ አበባ መሆንን አጥብቄ ፈለግሁኝ፡፡ማስታወቂያ ሲወጣ ጠብቄ አመለከትኩኝ፡፡ አየር መንገዱም ወግ ወጉን ይችልበታል፡፡ የጽሑፍ፣ የቃልና የህክምና የመሳሰሉ ፈተናዎችን አሳልፎ የአውሮጵላን ጥገና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱን እንድቀላቀል ፈቀደልኝ፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን የዐሥራ አንድ ወራት ሥልጠና ተከታትዬ አየር መንገዱን ለሰባት ዓመታት እንዳገለግል ይህን ባልፈጽም ግን ከሰባ ሺሕ በጥቂቱ ከፍ የሚል የኢትዮጵያ ብር ለመክፈል ተስማምቼ ፈረምኩኝ፡፡ ሥልጠናው ተጀመረ፡፡ ሁሉም ነገር የዓይን አዋጅ፤ ጽዱው የትምህርት ቤቱ ግቢ፣ የደንብ ልብስ ለብሰው አጀብ ሠርተው የሚጓዙ ተማሪዎች፣ ቆነጃጅቱ እጩ የበረራ አስተናጋጆች . . . ምኑ ይወራል ሁሉም ነገር አዲስ ሆነብኝ፡፡ ስለትምህርት ቤቱና አየር መንገዱ ገለጻ ተደረገልን፡፡ ዎርልድ ክላስ ኩባንያ እንደተቀላቀልን ተደሰኮረልን፡፡ ጀብድ የሚወደው ልቤ የምር ነገር የተገኘ መስሎት ቋመጠ፡፡ ትምህርት/ሥልጠና ተጀመረ፡፡
Deserve
በሥልጠናው የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት የተማርነው አንድ ክብደት ያለውን ነገር ከመሬት ከፍ በማድረግ አየር ላይ ማንቀሳቀስና መቆጣጠር እንዴት እንደሚቻል የሚያስረዳው የኤሮዳይናሚክስ (aerodynamics) ትምህርት ነበር፡፡ በጣም የሚያስደስትና የሰው ልጅን አእምሮ ምጥቀት እንድናደንቅ የሚያስገድድ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የወሰድናቸው ትምህርቶች ግን የኔን ቀልብ የሚስቡ ሆነው አልተገኙም፡፡ በአብዛኛው ከጥገና ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ዕወቀቶችን የሚያስጨብጡ ተደጋጋሚና ውስብስብነት የሌላቸው ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ አስቸጋሪ የምህንድስና ችግሮችን ከነመፍትሔዎቻቸው ለቃረመ አእምሮ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ከእኔ ጋር አቪየሽን ትምህርት ቤት ከነበሩ ሀያ አምስት ተማሪዎች መካከል ካልተዘነጋኝ ሀያ ሶስቱ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምህንድስና የተመረቁ በመሆናቸው ስለጥገናው ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ ከኔ ብዙም የሚርቅ አልነበረም፡፡ ከአንዳንድ እድሜያቸው ከገፋ መምህራን በስተቀር መምህራኑ የኛን ሥነ ልቦና ስለሚረዱ ብዙም አላስጨነቁንም፡፡ እኛም ጥሩ ታዛቢዎች ነበርን፡፡ ዳግም ሥራ ፍለጋ መውጣትን በመስጋት የትምህርት ቤቱ መምህራንና አስተዳደርን ላለማስቆጣት ተጠንቅቄ በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ባልገኝም ትምህሩቱን አጠናቅቄ በአውሮጵላን ስትራክቸር ጥገና ክፍል ተመድብኩኝ፡፡
ወደሥራ ገበታ ስሄድ በሁለት ጉዳዮች ላይ የራሴን ግምት ወስጄ ነበር፡፡ ከመጀመሪያውና ልክ ከሆነው ግምቴ ልጀምር፡፡ ከልጅነት ጀምሮ መጽሐፍ ከማንበብና ኳስ ከመጫወት በዘለለ የአካልና የአእምሮ ቅልጥፍናን በሚጠይቁ ሥራዎች ደካማ ነበርኩኝ፡፡ እናታችንን በመርዳት የቤት ወስጥ ሥራዎች የሚያከናውኑት ታላላቅ እህቶቼ ነበሩ፡፡ አሁን ሳስበው በሚያሳፍረኝ ሁኔታ ያኔ ግቢያችን የቧንቧ ውሃ በሌለበት ጊዜ ከቦኖ ውሃ በባሊ ሲቀዱ እንኳ አላግዛቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ የአውሮጵላን ጥገና ባለሙያነት አካላዊ ብቃትና ዲሲፕሊን እንዲኖረኝ ያደርገኛል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ይህ ግምቴ ልክ ነበር፡፡ በብዙ መልኩ ተለውጫለው፡፡ በትዕግስት መካኒካል ችግሮችን የመፍታት ክህሎት አዳብሪያለሁ፡፡ ምን አልባት አንድ ባለሙያ የሆነ ሰው አሁን ነገሮች የምሠራበት አኳኋን ላይጥመው ይችላል፡፡ እኔ ግን የነበርኩበትን አውቃለውና በአሁኑ ቅልጥፍናዬ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሁለተኛው ግምቴ የሥራው ከባቢ ባለሙያነት የሚበከበርበትና ከስልጠናው ደግሞ የተሻለ ሳቢ ይሆናል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ይህ ግምቴ ፈጽሞ ከእውነታው እጅግ የራቀ ነበር፡፡ በአለቆችና የበታች ሠራተኞች መሐል ያለው ግንኙነት ያለሁት ያ ስመ ገናናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ወይስ ሌላ ቦታ ያሰኛል፡፡ ይህን ጤናማ ያልሆነ የሥራ ግንኙነት ተከትሎ ሠራተኛውም በሥራው የሚለግም፣ አለቆቹን ሲያይ ብቻ ሠራተኛ ለመምሰል የሚሞክር ሀሜተኛና ብሶት የሚያበዛ ነው፡፡ አለቆቹም ከበታች ሠራተኛ የተሻለ ስብዕና ስለሌላቸው ጎበዝ ሠራተኛን ሳይሆን ወሬ የሚያቀብልን የሚወዱ፣ በጥቅማጥቅም እየደለሉ የራሳቸውን አንጃ የሚያደራጁ፣ ሰራተኛ የተመቸው ሲመስላቸው የሚከፋቸው፣ ትልቅ የሚመስሉ ነገር ግን የህጻናት ተግባር ሲፈጽሙ የሚገኙ ናቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ገለጻ የማይመለከታቸው ጥቂት ደህና ሰዎችን እንዳያሰከፋብኝ እሰጋለሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በዚያ ስፍራ ጥሩ ለመሆን ሲሞክሩ ከእኔ በላይ ችግር ገጥሟቸዋል ብዬ ስለማምን መግለጽ የፈለግኹትን ዐሳብ ይርረዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡ በዚህ በተበከለ የሥራ ከባቢ ከሠለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ያነሰ ብዙ የአእምሮ ጉልበት የማይጠይቅ ሥራን መከወን ከባድና ስለ አስቸጋሪነቱ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የሚስማቡበት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አብዮተኛው ልቤን ምቾት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይህን ቅሬታዬን በአንድ በዲፓርትመንት ደረጃ በተደረገ ስብሰባ ላይ አነሳኹት፡፡በዚያ ቀን በአለቆቼ ጥርስ ውስጥ ገባሁኝ፡፡ በቅንነት መሥሪያ ቤቱን ሀገራችንን የምናገለግልበት፣ ለብዙ ዓመት በሥራ ላይ ከነበሩ አንጋፋ ሠራተኞች ልምድ የምንቀስምበትና የምንማርበት፣ እኛም የምንጠቀምበት ምቹ ስፍራ እናድርገው ባልኩኝ ጠላት አፈራኹኝ፡፡ ከዚያ እኔም ደበረኝ ከአየር መንገዱም ጋር ሆድና ጀርባ ሆንን፡፡ አየር መንገድ ትቼ የምወጣበትን ቀን መናፈቅ ጀመርኩኝ፡፡
በዚህ በደበረኝ ወቅት ነበር አየር መንገዱ ሥራ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞቹ ከዘመኑ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ጋር በየጊዜው እንዲተዋወቁ (Recurrent) ሲል ያዘጋጀውን ሥልጠና እንድወስድ የታዘዝኩት፡፡ አለቆቼ ለእኔ አስበው ሳይሆን የፎርማሊቲ ጉዳይ ሆኖባቸው ይህንን ሥልጠና እንድከታተል ፈቀዱ፡፡ እኔም ከዚያ ከማልወደው የሥራ አከባቢ ገለል ማለትን ፈልጌ ስለነበር በደስታ ወደ ሥልጠናው አመራኹኝ፡፡ በሥልጠናው ከዚህ በፊት እንዳሠለጠኑኝ መምህራን ከዚህ በፊት የማውቀውን ነገር በተሰላቸ መንገድ የሚደግም ሰው አልገጠመኝም፡፡ ሰውየው ዓለም ዐቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሚገባ የተረዳ ነው፡፡ በዚህ ውድድር በበዛበት መድረክ አየር መንገዱ ውጤታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ሠራተኛ በተመደበበት የሥራ መደብ ምን እንደሚጠበቅበት በመተንተን ያስረዳል፡፡ የኢንዱስትሪውን ፓለቲካ፣ የተቆጣጣሪ ድርጅቶችን ጸባይ፣ እንደ አይካዎ ያሉ አለም አቀፍ የአቪዬሽን ማኅበራት ፍላጎቶች፣ አየር መንገዱ ያሉበትን ተግዳሮቶች፣ ኢንዱስትሪው በዘመኑ የደረሰበትን ዕውቀት በከፍታ(experts with excellence)የሚያውቁ ሠራተኞች እንዴት ለአየር መንገዱ ጉልበት እንደሚሆኑ ነገር ግን አየር መንገዳችን የነጠረ (refine) ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት እንዳለበት ተጨባጭ በሆነ መልኩ አስረዳን፡፡ ያን ጊዜ ከእንቅልፌ እንደመባነን አልኩኝ፡፡ ተዳፍኖ የነበረውን ሀገሬን በባለሙያነት የማገልገል ስሜቴን ቆሰቆሰው፡፡ ወደቢሮው ሄጄ ላመሰግነው ብቋምጥም አየር መንገዱን ከተቀላቀልኩኝ ጀምሮ ያዳበርኩት የባይተዋርነት ስሜት ቀፍድዶ ያዘኝ፡፡ ለራሴ ግን ያለሁበትን ሁኔታ ለመቀየር ቃል ገባኹኝ፡፡
የምህንድስና ክፍል ክፍት የሥራ ቦታ ሲያወጣ ተወዳድሬ ለማለፍ በቦሌም በባሌም መንገድ ጥረት አደረግኹኝ፡፡ ዕድል ዘግይታም ቢሆን ከእኔ ጋር ሆነች፡፡ አስፈላጊውን ፈተና እና ቃለ መጠይቅ በማለፌ በአየር መንገዱ የአውሮጵላን ጥገና እና ዕድሳት ክፍል የጥገና መሳሪያዎች አስተዳደር እና ምህንድስና ክፍል በመሀንዲስት እንዳገለግል ተመደብኩኝ፡፡ በአጋጣሚ የቅርብ አለቃዬም የሚሠራውን የሚያውቅ፣ ትጉሕና የሚመራው ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ የተረዳ ነበር፡፡በርካታ ሥራዎችን ለመከወን ዕቅድ ያዝን፡፡ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሮዬ ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ ጠዋት ቀድሞ መግባት፣ ማታ ደግሞ አርፍዶ መውጣት እና በእረፍት ቀኔም ወደቢሮ መሄድ ልማዴ ሆነ፡፡ የተወሰኑ ወራት ደስ ብሎኝ ሠራሁ፡፡ አለቃዬም ስገምት በሥራችን ከሞላ ጎደል ደስተኛ የነበረ ይመስለኛል፡፡
በዕለተ ዓርብ ሚያዝያ 17/2006 ዓ.ም. ከ ቀኑ 10፡30 አከባቢ ነው፡፡ የተለመደ ሥራዬን ለማከናወን ኮምፒዩተሬ ላይ አፍጥጫለው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ደኅንነት ከሁለት የማላውቃቸው ሰዎች ጋር ወደቢሮ ገብተው “አቤል ዋበላ . . . አንዴ ውጭ ፈልገንህ ነው” ሲሉ ጠሩኝ፡፡ ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንገሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በመሞከር ተጠርጥሬ በፌደራል ፓሊስ ቁጥጥር ስር መዋሌ ነው፡፡ ዞን ዘጠኝ ላይ ከሚጽፉ አምስት ጦማሪዎች እና ሌሎች ሦስት ጋዜጠኞች ጋር በአባሪነት የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ገባን፡፡ በሂደት ፓሊስ ጥርጣሬውን ወደ ሽብር አሳደገው፡፡ ጭራሽ ይግረማችሁ ብሎ በፌደራል ዐቃቤ ሕግ ታግዞ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ መሠረተ፡፡ ክሱ እንኳን ለዳኞቹ እና ለእኛ ለተከሳሾቹ አይደለም ለራሱ ለዐቃቢ ሕጉም የሚገባ ስላልሆነ በጠበቆቻችን አማካኝነት የክስ መቃወሚያችንን አቀረብን፡፡ ዳኞቹ ፈራ ተባ እያሉ የተወሰነ ነጥቦች ብቻ እንዲያስተካከል አድርገው አሻሽል ያሉት ነጥብ ሳይሻሻል ክሱ እንዲቀጥል ወሰኑ፡፡ እኛም በፀረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ ፫/፪ “የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ” ለማጋለጥ “በመሞከር፣ በማሴር፣ በማነሳሳት” በሚል ተከሰን ፍርዳችንን መጠባበቅ ያዝን፡፡ ከዚያም ዐቃቤ ህግም አስቂኝ የሆነውን የሰውና የሰነድ ማስረጃውን አቀረበ፡፡ ይህ ሂደት አንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ፈጅቶ ጥቅምት 05/2008 ዓ.ም. መከላከል ሳያስፈልገን በነጻ ተለቀቅን፡፡
ከፍርድ ቤት በቀጥታ ለአየር መንገዱ የተጻፈ በነጻ መለቀቄን የሚገልጽ ማስረጃ ጥቅምት 10/2008 ዓ.ም. ተቀብዬ ድርጅቱ በነጻ መሰናበቴን ተመልክቶ ወደ ሥራ እንዲመልሰኝ ጥቅምት 15/2008 ዓ.ም. አመለከትኩኝ፡፡ ውሳኔ ላይ አልደረስንም በሚል ሲያመላልሱኝ ከቆዩ በኋላ ሕዳር 16/2007 ዓ.ም. ከዓመት በፊት በኖቨምበር 4/2015(ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም.) የተጻፈ ከሥራ መታገዴን የሚገልጽ የስንብት ደብዳቤ ሰጡኝ፡፡ ደብዳቤው የሥራ ውሌ እንዲቋረጥ ምክንያት የሆነው ለስድስት እና ከዚያ በላይ ለተከታታይ ወራት በእስር ምክንያት ከሥራ ገበታዬ መቅረት መሆኑን ጠቅሶ ይህ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢ.አ.መ. መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር 10ኛ የኅብረት ስምምነት አባሪ 1 ክፍል አንድ ተ.ቁ 6(111) እና የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377(2003) አንቀጽ 27(1)(ተ) አንድ ላይ በመሆን የሥራ ቅጥር ውል ወዲያው እንዲቋረጥ ያደርጋል ይላል፡፡
በሕግ ከኅብረት ሥምምነቶች በላይ ተቀባይነት ያለው የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ ፳፯ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ስለማቋረጥ በቁጥር (፩) “በኅብረት ስምምነት ካልተጠቀሰ በሌላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ የሚቻለው በሚከተሉት ሁኔታዎች ብቻ ነው፡፡” ይልና ከፊደል ተራ ሀ-ቀ ከእስራት ጋር ያልተያያዙ የሥራ ውልን የሚያቋርጡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ይዘረዝራል፡፡ በፊደል ተራ (በ) ደግሞ “በሠራተኛው ላይ ፴ ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእስራት ፍርድ ተወስኖበት ከሥራ ሲቀር” ይላል፡፡ እኔ በሕግ አንድም ቀን እንድታሰር ‹የጥፋተኝነት ብይን› ስላልተላለፈብኝ አይመለከተኝም፡፡ በድርጅቱ የተጠቀሰው በፊደል ተራ (ተ) “ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ለማቋረጥ ያስችላሉ ተብለው በኅብረት ስምምነት የተወሰኑ ሌሎች ጥፋቶች መፈጸም” የሚለው ነው፡፡ በዚህ መሠረት አዋጁ ሥልጣኑን ለኅብረት ስምምነቱ ስለሚሰጥ ያንን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡
የኅብረት ስምምነቱ አባሪ 1 ክፍል አንድ “ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ የሚያሰናብቱ ከፍተኛ የሥነ-ስርዓት ግድፈቶች/ጥፋቶች እና የሥነ-ስርዓት እርምጃዎች” ይልና ከ ተ.ቁ 1-30 ያሉ ከወሲብ ትንኮሳ አንስቶ በድርጅቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ጠብና አምባጓሮ እስከመጫር የሚደርሱ የጥፋት ዓይነቶችን ይዘረዝራል፡፡እኔን የሚመለከተው 6(111) “ወንጀል ፈጽሞ የ6 ወር እስራት ወይም ከዚያ በላይ እስራት ተፈርዶበት በፍርዱ መሠረት የሚታሰር መሆኑ ሲታወቅ ወይም በማንኛውም ምክንያት ሳይፈረድበት 6 ወር ወይም ከዚያ በላይ ታስሮ የቆየ ” የሚለው ነው፡፡ እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ሕገ-መንግሥታዊ መብቴ የተጣሰው፡፡ አዋጁ ለኅብረት ስምምነቱ ሥልጣን ቢሰጥም አሠሪዎች የሠራተኛ ማኅበራትን እየጠመዘዙ የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት በሚጥስ መልኩ የፈለጉትን ነገር በኅብረት ስምምነት እያሰፈሩ ሠራተኛውን እንዲድበሉ አይፈቅድም፡፡ የኅብረት ስምምነቱ ሕገ-መንግሥቱንና ሌሎች የሀገሪቱን ሕጎች የማይጥስ፣ በመንፈሱ ፍትሓዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ በግልጽ አንድ ሰው በፍርድ ቤት እስካልተወሰነበት ድረስ እንደ ነጻ ሰው እንደሚቆጠር በአንቀጽ 20 ላይ ሰፍሯል፡፡ በመጠ’ርጠሬ ምክንያት ብቻ የሥራ ውሌን ማቋረጥ ሕገ-መንግሥታዊ ታዛዥነትን ያፈረሰ ነው፡፡ ‹በማንኛውም ምክንያት ሳይፈረድበት 6 ወር እና ከዚያ በላይ የቆየ› የሚለው የሀገራችንን የፍርድ ቤቶች ‹ፍትሕን ከሰጡ አዘግይተው የመስጠት› ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡
ይህንን የመብት ጥሰት ከሕግ ባለሙያው አመሐ መኮንን ጋር ተማክሬ ሕዳር 24/2008 ዓ.ም. በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ሥራ ክርክር ችሎት ወደ ሥር እንድመለስ ወይም ድርጅቱ ወደሥራ የምልመለስበት በቂ ምክንያት አለ ሚባል ከሆነ ከሕግ ውጭ ለተቋረጠው የሥራ ውል በሕጉ መሠረት አስፈላጊውን ክፍያ እንዲፈጽም በመጠየቅ ክስ መስርቻለሁ፡፡ ይህን ክሴን ተከትሎ መሥሪያ ቤቱ በደረሰው መጥሪያ መሠረት በታኅሣሥ 22/2008 ዓ.ም. የጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚህ መልሱም የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ እንዲሉ ድርጅቱ ስህተቱን ለማረም ዝግጁነት እንደሌለው አሳይቷል፡፡ የሚገርመው በማይመለከተው ጉዳይ ላይ በመግባት የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በእኔ እና ጓደኞቼ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የጠየቀውን ይግባኝ በማንሳት ከሳሽ ገና ለገና ተከሳሽ በድጋሚ ሊታሰር ይችላል በሚል ወደ ሥራ ልመልሰው ልገደድ አይገባኝም ብሏል፡፡ ሰሚት የሚገኘው ፍርድ ቤትም ክርክሩን ለመስማት ለየካቲት 24/2008 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ቀጠሮ ይዟል፡፡
ጉዳዩ በዚህ ቢያበቃ መልካም ነበር፡፡ ድርጅቱ በሕገ-ወጥ መንገድ የሥራ ውሌን አቋርጦ ሳለ ድርጅቱ የሚሰጠውን ሥልጠና ስወስድ ቃል የገባኹት የሰባት ዓመት አገልግሎት በግሌ ያልተወጣኹኝ በማስመሰል ሰባ ሺ የኢትዮጵያ ብር ከነወለዱ እንድከፍለው ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ ችሎት ክስ መስርቶብኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ድርጅቱ ምን ያህል ኢ-ፍትሓዊነት ቀለባቸው በሆኑ ሰዎች እንደሚመራ ነው፡፡ ከሥራ ለምን ቀረው? በእስራት ምክንያት እስራቱ የማን ስህተት ነው? የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳረጋገጠው የፖሊስ ሐሰተኛ ክስ ነው:: የሥራ ውሌን ማን አቋረጠው? የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሥራ ገበታ ለምን ቀረህ በማለት በመጨረሻም የገባኸውን ቃል አልፈጸምክም በሚል የከሰሰኝ ራሱ አየር መንገድ ሆኖ አዙሪት ውስጥ ገብቼያለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም የልደታውን፣ የአራዳውን፣ የስድስት ኪሎውን ፍርድ ቤት ነበር የማውቀው አሁን ደግሞ የካ ፍርድ ቤት በታህሳስ 26/2008 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 እንድቀርብ ታዝዣለው፡፡ የምቆመው ብቻዬን ከመሰላቸው ተሳስተዋል፡፡ የምቆመው እንደ አየር መንገዱ ከሕግ በላይ በሆኑ አሠሪዎች በደል ከደረሰባቸው ሠራተኞች ጋር ነው፡፡ የምቆመው ኢ-ፍትሓዊነት በሀገራችን እንዲወገድ ከሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ጋር ነው፡፡ ከዚህ በፊት አየር መንገዱ ብዙ ሠራተኞችን በድሎ በዝምታ እንደታለፈው(የጽሑፉ ዓላማ ይሄ አይደለም እንጂ ስለበደሉ ብዙ ማለት ይቻላል) ከእኔ ዝምታን ቢፈልግ አያገኛትም፡፡ ከእስር እንደወጣኹኝ አንዳንድ ወዳጆቼን ሥራ እንዴት ነው ብዬ ጠይቄ ነበር የብዙዎቹ ምላሽ “ቀንበሩ ከበዷል” የሚል ነው፡፡ ይህንን መሰል ዘመናዊ ባርነቶች እንዲወገዱ ምኞቴ ነው፡፡ እኔ ግን ፍትሕ ባላገኝ እንኳን ለታሪክ ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ስል ይህን እናገራለሁ፡፡