አያት የመኖሪያ ቤቶች ስራ ድርጅት በሊዝ ወስዶ መሠረቱ ወጥቶ ያለቀ ቦታ ለኢሊሌ ሆቴል ተወሰነ
ታምሩ ጽጌ
–መሠረቱን ለማውጣት ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣበት ተገልጿል
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ ከኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ወረድ ብሎ የሚገኘውን፣ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አያት አክሲዮን ማኅበር በሊዝ የወሰደውና መሠረቱ ወጥቶ ያለቀ ቦታ፣ ፊት ለፊቱ ለሚገኘው ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጠ፡፡
ከ20 በላይ ክሶች ተመሥርቶባቸውና ጥፋተኛ ተብለው 11 ዓመታት የእስርና የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አያሌው ተሰማ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት አያት አክሲዮን ማኅበር፣ ቦታውን በሊዝ የወሰደው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ስፋቱም 1,696 ካሬ ሜትር ነው፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ቦታውን በሊዝ የወሰደው ባለ16 ፎቅ ለመኖሪያና ለቅይጥ የንግድ ሥራ ሕንፃ ለመገንባት ነበር፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቦታውን በሊዝ ያስተላለፈው ለልማት መሆኑን በመግለጽ፣ አያት አክሲዮን ማኅበር ምንም ዓይነት ግንባታ አላካሄደም በማለት በሊዝ አዋጁ የተፈቀደው የመጠበቂያ ጊዜ እንዳለፈ አስታውቆ ካርታውን ማምከኑም ተጠቁሟል፡፡
የኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ ቦታው ከሆቴላቸው ፊት ለፊት በቅርበት ላይ መሆኑን በመግለጽ፣ መሰጠት ያለበት ለመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ለእሳቸው መሆኑን ለክፍለ ከተማው በማመልከታቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱም ተገልጿል፡፡ የሆቴሉን ባለቤት አቶ ገምሹንና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደርን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት የከሰሰው አያት አክሲዮን ማኅበር፣ ለመሠረት ማውጫ ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳወጣበትና ካርታው ከመምከኑ በፊት ሊነገረው ሲገባ፣ በድብቅ ማምከኑ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ሲከራከር ከርሟል፡፡
ጉዳዩን ሲመረምር የከረመው ፍርድ ቤቱ ማኅበሩ ቦታውን በተነጠቀ ወይም ካርታው በመከነ በ15 ቀናት ውስጥ ለአስተዳደሩ የቦታ አመላለስ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ማቅረብ እንደነበረበት አስታውቋል፡፡ ያንን ሳያደርግ ወደ ፍርድ ቤት መምጣቱ (ክስ መመሥረቱ) ሕጉን ያከበረ አካሄድ አለመሆኑን በመጠቆም፣ 1,696 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ለኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን በውሳኔው አስታውቋል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት በደረሰባቸው ችግር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
የህዳር 27 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የጠራው የአዳር ሰልፍ ወቅት ተይዘው በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ እና ለሶስት ቀን የስኳር በሽታ መድሃኒት እንዳይገባላቸው በመከልከላቸው ለህመም የተዳረጉት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ፀኃፊ መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ ከእስር ከተፈቱበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወር ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ይዘውት የነበረውን የስኳር በሽታ መድሃኒታቸውን በመቀማታቸው፣ እንዳይገባላቸው በመከልከላቸውና በወቅቱም ህክምናም ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ህመም በመዳረጋቸው ለሁለት ወር ያህል ዘውዲቱ ሆስፒታል ቆይተዋል፡፡
መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ዘውዲቱ ሆስፒታል ከገቡበት ታህሳስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም በቦሌ ሚካኤል እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በፊት ከኬንያ በህወሓት ደህንነት ታፍነው አዲስ አበባ ቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት ታስረው በህወሓት ፖሊሶችና ደህንነቶች በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ድብደባ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ያላወጣቸው የተለያዩ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ይታወቃል፡፡
አይካ-አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መቱ
በቱርክ ባለሃብቶች የተያዘው የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች ከጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምረው የስራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ኩባንያው በየ አመቱ በሚያደርገው የደመወዝ ጭማሬ መሰረት በዘንድሮው አመት የተሻለ የደመወዝ ጭማሬ እንደሚያደረግ የገለጸበትን ወረቀት ለሰራተኞቹ በትኖ የነበር ቢሆንም ቅዳሜ ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለሰራተኞቹ በተበተነው ሌላ ወረቀት የደመወዝ ጭማሬው ከተጠበቀው በታች ሆኖ በመገኘቱ ሰራተኞች ‹‹ስራ አንሰራም›› ብለው ፋብሪካው ግቢ ውስጥ ተቀምጠው ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ከሰኞ 25 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የድርጅቱ ሰራተኞች አድማውን አጠናክረው እንደቀጠሉ ታውቋል፡፡
ቅዳሜ ጥር 23/2007 ዓ.ም ሰራተኞቹ የደመወዝ ጭማሬውን ከሰሙ በኋላ “ስራ አንሰራም” በማለታቸው የፋብሪካው ኃላፊዎች “የአንድ ወር ገደብ ስጡንንና እናስተካክል” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰራተኞቹ በበኩላቸው “በሳምንት ጊዜ ውስጥ ይስተካከል” የሚል ሀሳብ አቅርበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም በሁለቱ መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ሰራተኞቹን እየነጠሉ ለማናገር ያደረጉት ሙከራም እንዳልተሳካላቸው ተገልጾአል፡፡
ቅዳሜ ጥር 23 ዓ.ም ዝቅተኛ ነው የተባለው የደመወዝ ጭማሬ ምክንያት ስራ ሳይገቡ መስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው የዋሉት የአይካ አዲስ ሰራተኞች ከትናንት ሰኞ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ መምታታውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አይካ አዲስ ከ8 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት የገለጸችው አንዲት የድርጅቱ ሰራተኛ ድርጅቱ ተመሳሳይ ስራ ላይ በተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች መካከል ደመወዝን ጨምሮ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለና በኢትዮጵያውያን ላይ መድሎ እንደሚፈጽም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡ ከዚህ በደል በተጨማሪ ፋብሪካው የገባውን ቃል አለመፈፀሙ ሰራተኞቹ ስራ እንዲያቆሙ ምክንያት እንደሆነም ሰራተኞቹ ገልፀዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ በድብደባ ትግሉን እንደማያቆም በመግለፅ በድጋሚ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የምርጫ ቦርድ በፓርቲው ላይ የሚያሳየውን ጣልቀ ገብነትና ፓርቲውን ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ነበር፡፡ በዕለቱም በደብረ ማርቆስ፣ በጋሞ ጎፋ ከንባ እና በሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ በአዲስ አበባ የሰልፉ ጅማሮ ላይ ከ26 በላይ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እና በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ የነበሩ የ70 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የዓይን እማኞች፣ የህክምና እና የምስል ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በዕለቱ በፖሊስ ከተፈፀሙ ድብደባዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ነፍሰጡር ሴት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው የዕለቱን ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ እንቋረጥ ቢደረገም ፤ ለጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. መነሻውን ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ጽህፈት ቤት አንስቶ በፒያሳ በዳረሻውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ አደባባይ በድጋሚ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ በተመሳሳይ ዕለትም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች በደሴ፣ በባህርዳር ፣በደብረ ታቦርና በሌሎች የክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የጠርቷል፡፡
በተለይ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በፓርቲው አባላት፣ደጋፊዎችና ቤተክርስቲያን ለፀሎት የተቀመጡ አዘውንት ምዕመናን በፖሊስ የተፈፀመባቸውን ድብደባ በማውገዝ፣ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችንም በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ይህንንም ሰላማዊ ትግሉ በጭፍጨፋና በውንድብና ለማቆም መሞከር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው! ሲል አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከታች ይመልከቱ፡-
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
=============================
ሰላማዊ ትግሉ በጭፍጨፋና በውንድብና ለማቆም መሞከር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው!
ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
የተሰጠ መግለጫ
================================
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰልፍ መጥራቱ ይታወቃል። ነገር ግን ስርዓቱ ህገ ወጥ ሰልፍ ነው በማለት በአንድነት አመራሮችና አባለት ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ድብደባ ወደር የማይገኝለት ነው። እርጉዞች፣ ህፃናት፣ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ደማቸው ፈሷል፤ አጥንታቸው ተሰብሯል። ሰላማዊ ሰልፉ ስርዓቱ እንደሚለው ህገ ወጥ አልነበረም፤ ስልፍ እንደምናደርግ ደብዳቤ ስንልክላቸው አንቀበለም ብለው ሲያንገራግሩ ደብዳቤውን እዚያ አስቀምጠንላቸዋል፤ ይህ ብቻ አይደለም በሬኮማንድ በድጋሚ ተልኮላቸው ተቀብለዋል። ህጉ አስተዳደሩ በአስራ ሁለት ሰዓት ውስጥ መልስ መስጠት አለበት ቢልም ከሰባ ሁለት ሰዓት በኋላ በሚዲያ “ሰልፉ ህገወጥ ነው” የሚል መግለጫ ከማውጣት ውጪ በደብዳቤ የመለሱት ነገር አልነበረም። በመሰረቱ በስብሰባና በሰልፍ አዋጁ መሰረት አንድ ፓርቲ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለአስተዳዳሩ ማሳወቅ ነው ያለበት። አስተዳደሩ ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንጂ ሰልፍ መፍቀድም ሆነ መከልከል አይችልም።
አምባገነኑ የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱንም ጭምር በማበላሸት ጠንክራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ ላይ ታች እያለ ነው። በተለይ አንድነት ፓርቲ ላይ በምርጫ ቦርድ፣ በኢቲቪ እና በሬዲዮ ፋና የሶስትዮሽ ግንባር በመክፈት በህዝቡ ዘንድ ብዥታ እንዲፈጠር፣ ምርጫው ያለጠንካራ ተዋዳደሪ እንዲካሄድ በማድረግ የምርጫውን ዋጋ ቢስነት ከማረጋገጡም በተጨማሪ ፓርቲውን ለማፍረስ ቀን ከሌሊት እየሰራ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ስርዓቱና ምርጫ ቦርድ የጥቅም ምንደኞች በማዘጋጀት ተለጣፊ አንድነትን በመጠፍጠፍ ፓርቲውን ከእውነተኛ አባላቱና ደጋፊዎቹ ለመቀማት እጅግ አሳፋሪ የሆነ የሽፍትነት ስራ በመስራት ላይ ይገኛል።
አሁንም ቢሆን አንድነት ይህን የህወሀት/ኢህአዴግ ሴራና ውንብድና በመቃወም ለሚቀጥለው እሁድ ጥር 24/2007 በአዲስ አበባና በሌሎች የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ሰልፍ ያድርጋል። በአዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው ሰልፍ በተለምዶ ኢትዮ ኩባ አደባባይ (ድላችን ሀወልት) ሲሆን በትናንትናው ጥር 18/2007 ለአስተዳደሩ በደብዳቤ አስገብተናል። ይህ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሰልፍ አስተዳደሩ አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ ተለዋጭ የጊዜ ወይም የቦታ አማራጭ እስካላቀረበ ድረስ በምንም ሁኔታ የሚታጠፍ አይደለም። አንድነት ስብሰባና ሰልፍ የማድርግ ህገመንግስታዊ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ በህዝባዊ ንቅናቄና በሰላማዊ መንገድ ትግሉን ይቀጥላል።
ድል የሕዝብ ነው!!
ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ስልክ ቁ. ዐዐ11-1- 22-62-88
ፖ.ሣ.ቁ 4222
አዲስ አበባ በሚገኝ ትምህርት ቤት አጥር በመደርመሱ ከተጎዱት መካከል የአንዲት ተማሪ ህይወት አለፈ
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው ፍሬህይወት አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠገብ ከባቡር መንገድ ስራ ጋር በተያያዘ በተደረገ ቁፋሮ የትምህርት ቤቱ አጥር ተደርምሶ 11 ተማሪዎች ላይ ጉዳት አድርሶ የነበረ ሲሆን፤ ከተጎዱት መካከል ተማሪ ፅዮን ንጉሴ ሆስፒታል ውስጥ የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላት በደረሰባት ከባድ ጉዳት ምክንያት ህይወቷ ማለፉ ተሰምቷል፡፡ የተማሪ ፅዮን ንጉሴ የቀብር ስነስርዓትም ዛሬ ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው ብሔረ ፅጌ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን መፈፀሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
የትምህርት ቤቱ አጥር የተደረመሰው ቻይናዎች ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ አጥሩ ጥግ ቁፋሮ በሚያደርጉበት ወቅት ተማሪዎች ዕረፍት ላይ ስለነበሩ አንዳንዶቹ ሲጫወቱ ሌሎች ደግሞ በአጥሩ ጥቅ ሲያጠኑ አደጋው መድረሱን በወቅቱ የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግራዋል፡፡ በወቅቱ በቻይናዎቹ ድርጊት የተበሳጩ ተማሪዎቹ ቁጣቸውን ሲገልፁ በስፍራው በነበሩ ቻይናዎችና የአዲስ አበባ ፖሊሶች በርካታ ተማሪዎች መደብደባቸውም ተጠቁሟል፡፡ ስለተፈጠረው አደጋም ሆነ ስለተማሪዎቹ ጉዳት የመንግስት አካላት እስካሁን ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡




