24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን ባህር ሰጥመው ሞቱ
ባለፈው ሰኞ ታህሣሥ 20 ቀን 2007 ኣ.ም. በጀልባ ወደ የመን ሊገቡ የሞከሩ 24 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞቻ በምትባል የየመን ወደብ ከተማ አቅራቢያ በደረሰባቸው የጀልባ መስጠም አደጋ መሞታቸውን የየመን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለፃ ከሆነ በጀልቧ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ በህይወት የተረፉ ስለመኖራቸውም ሆነ በአደጋው የሞቱትን በለመለየት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተደረገ ጥረት አለመኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በቅርቡ ህዳር 28 ቅን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ በየመን የወደብ ከተማ በሆነችው ሞቻ አቅራቢያ 70 ኢትዮጵያውያን በሚጓዙበት ጀልባ በደረሰ አደጋ ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ባህር አቋርጠው የምን ሊገቡ ሲሉ ህይወታቸው ላለፈው 94 ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በአቅራቢያው ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንፅላ ፅህፈት ቤት አምባሳደሮች ያሉት ነገር የለም፡፡ በየ ዓመቱ የህንድ ውቅያኖስን እና ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው ወደ የመን ሊገቡ የሚሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እየሞቱ ቢሆንም አደጋውን ለመቀነስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመንን ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር ለመሸጋገር የሚጠቀሙባት በመሆኑ የስተኞች ጣቢያ እንደማይመዘገቡና እገዛም እንደማይደረግላቸው ተጠቁሟል፡፡ የመን ባህር አቋርጠው ከሚገቡ አብዛኞቹ ስደተኞች መካከል ጥቂቶች ብቻ በተለይም በፈረንጆቹ 2014 መጨረሻ የመን በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን እገዛ የተደረገላቸው 9,500 ኢትዮጵያውን እነደነበሩ የድርጅቱ መረጃ አመልክቷል፡፡
ከመንግስት በሚደርስባቸው የፖለቲካ ጫና እና በሀገሪቱ ከተከሰተው የኢኮኖሚ ችግር በተፈጠረው የኑሮ ውድነት የተነሳ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር በየ ዓመት እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች የጦር ሄሊኮፕተር ይዘው ስርዓቱን መክዳታቸውን መንግሥት አመነ
ባለፈው አርብ ታህሣሥ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከድሬዳዋ የአየር ኃይል ምድብ የጦር ልምምድ ላይ የነበሩት የኢትዮጵያ የአየር ኃይል አብራሪዎች እና አንድ መካኒክ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት በመክዳት ኤም አይ-35 የሆኑ ሁለት ዘመናዊ የጦር ሄሊኮፕተሮችን ይዘው ኤርትራ መግባታቸው ተረጋገጠ፡፡ ይሄንንም የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ታህሣሥ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ማመኑን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ አብሪዎቹ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝ እና የሄሊኮፕተሩ ቴክኒሻን ፀጋብርሃን ግደይ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
አብራሪዎቹ ይዘዋቸው የጠፉት የጦር ሄሊኮፕተሮች የአንዱ ዋጋ 36 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ሲሆን፤በኢትዮጵ ከ720 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ እንደ ኢሳት ዘገባ ከሆነ የአርብ ዕለቱን ጨምሮ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ 11 የመከላከያ ሚኒስቴር የአየር ኃይል አብራሪዎችና ባለሟሎች ከድተው ስርዓቱን በኃይል ለመጣል ወደ ሚታገሉ ታጣቂዎች መቀላቀላቸው ተጠቁሟል፡፡
ብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞቹ ተጨማሪ 20 ቀናት ቀነ ቀጠሮ ተሰጣቸው
∙ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየት ተሰጥቶበታል
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ተጨማሪ 20 ቀናት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ለ13ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ጦማርያኑና ጋዜጠኞች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ቀደም ብሎ ተሻሽሎ በቀረበባቸው ክስ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆችም ተሻሻለ በተባለው ክስ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ጠበቆቹ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ከማቅረባቸው በተጨማሪ በቃል ለችሎቱ ለማስረዳት ጠይቀው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹በጽሑፍ ካቀረባችሁ በቃል መድገም አያስፈልግም›› በሚል ሳይፈቅድላቸው ቀርቷል፡፡
ጠበቆቹ ‹‹ተሻሻለ የተባለው ክስ ምንም መሻሻል የለውም›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ቢሞክሩም፣ ችሎቱ ንግግራቸውን አቋርጦ ‹‹ክሱ በታዘዘው መሰረት መሻሻል አለመሻሻሉን መርምሮ የሚወስነው ፍርድ ቤቱ ነው›› ሲል አስረድቷል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠቦቆች የቀረበውን አስተያየትና ቀደም ብሎ ለአቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል የሰጠውን ትዕዛዝ በማገናዘብ ጉዳዩን መርምሮ ክሱ በምን አግባብ እንደተሻሻለ አይቶ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል የነገረ- ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከታህሣሥ 3-4 ቀን 2007 ዓ.ም. ያደረገው አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ፡፡ ፓርቲው በተከታታይ ቀናት መዋቅሩን ከዘረጋባቸው ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች በመጡ አባላቱ ባደረገው ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተለያዩ አጀንዳዎችን በማፅደቅ ውሳኔዎችን ያሳላፈ ሲሆን፤ በተለይም የቀድሞው የፓርቲው ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የተመረጡትን ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱን ስልጣን ከነ ስራ አስፈፃሚዎቹ አፅድቋል፡፡ ሌላው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ቁጥር በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በአባላቱ ተወስኖና የፀደቀው ደንቡ ላይ ሰፍሮ ይቅረብልኝ ባለው መሰረት ተወስኖ እንዲሰፍር መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዋና አጀንዳዎቹ መጠናቀቅ በኋላ ፓርቲው በአመራር አባላቱ ለጠቅላላ ጉባኤ አባላት በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች(የአርሶ አደሩ ፤የከተማው ነዋሪ፤የባለሐብቱ ሁናቴ) በዳግማዊ ተሰማ፣ የተማሪውና የምሁሩ ነባራዊ ሁኔታ በጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ፣ የአንድነት የምርጫ ስትራቴጂ ግብ በፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ መቅረቡ ታውቋል፡፡

በመቀጠልም የስልጠናው ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት በመስጠት ስልጠና ተጠናቆ፣ በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይና የአንድነትፓርቲምክትል ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በምርጫ ስትራቴጂ ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡አባላቱ የፓርቲው የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳይ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ገበየሁ ይርዳው የአባላት መብትና ግዴታ ከፓርቲው ደንብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንጻር ስልጠና ከሰጡ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆኖ በስልጠናዎቹና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደረጉን የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በመጨረሻም የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ የጉባኤውን የመዝጊያ ንግግር በማድረግ አንድነት በብሔርም ሆነ በህብረብሔር ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት መዘጋጀቱንና ከአንድነት ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ላላቸው ፓርቲዎች ሁሉ የውህደት ጥያቄ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ተክሌ አንድነት ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. ምርጫን በአሸናፊነት ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝና አባላቱም በያሉበት ጠንክረው የበኩላቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ ጉባዔው በስኬት መጠናቀቁን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት አጀንዳዎችን አፀደቀ
ትናንት አርብ ታህሳስ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) በጠራው ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት አጀንዳዎችን በመወያየት ማፅደቁ ተሰማ፡፡ በመጀመሪያ አጀንዳነት የተነሳው የኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ከፓርቲው ፕሬዘዳንትነት ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሰየመውን ፕሬዝደንት ተወያይቶ ያፀደቀ ሲሆን፤ በሁለተኛ አጀንዳነት የተያዘው እና ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥራችሁን አሳውቁኝ ባለው መሰረት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥርን ወስኗል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው ከሁለቱ አጀንዳዎች በተጨማሪ በተጓደሉ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ምክንያት የማሟያ ምርጫንም ማድረጉ ታውቋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አሁንም በተለያዩ የፓርቲውና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከሩን እንቀጠለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከውይይቱ በኋላም የተለያዩ ተጨማሪ አጀንዳዎችን ከማፅደቅ በተጨማሪ አንገብጋቢ በሆኑ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ አባላትም ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ተጠቁሟል፡፡