Tag Archives: Hossana Ethiopia

በሀዲያ ዞን በምርጫ 2007 ዓ.ም. ቅስቀሳ ምክንያት የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

በደቡብ ክልል በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ ጊምቢቹ ከተማ በህዝብና በራሱ ላይ በሚፈፀመው አስተዳደራዊ በደል የተማረረውና በተደጋጋሚ በሚፈፀሙት አስተዳደራዊ በደሎች ላይ ቅሬታ አቅርቦ መፍትሄ ያላገኘው የአካባቢው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ የመድረክ ዕጩ የነበረው መምህር ጌታቸው አብርሃም ሚያዝያ 17 ቀን 2007ዓ.ም በጊምቢቹ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ራሱን ያቃጠለ ሲሆን በሆሳዕና ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም ህይወቱ እንዳለፈች ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ቡሬ ለንጌ ትምህርትር ቤት የሲቪክስ መምህር የነበረው መምህር ጌታቸው በአካባቢው ባለው የከፋፍለህ ግዛና የጎሳ ፖለቲካ ተጠቂ ከመሆኑም ባሻገር በህዝብና በእሱ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም መፍትሄ እንዲሰጥ ለባለስልጣናት ሲያሳውቅ መቆየቱን፣ ሆኖም ህዝቡ እና በራሱ ላይ የሚፈፀምበት በደል በመባባሱና መፍትሄ ማግኘት ባለመቻሉ አስተዳደሩ ግቢ ውስጥ ራሱን ማቃጠሉ ታውቋል፡፡
መምህር ጌታቸው ራሱና ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም በከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ራሱ ላይ ጋዝ በማርከፍከፍ ራሱን ባቃጠለበት ወቅት ግቢው ውስጥ የነበሩት ሰዎች ደርሰው እሳቱን በማጥፋታቸው ህይወቱን ለማዳን ጥረት አድርገው የነበር ቢሆንም የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ህይወቱ አልፏል፡፡

Hossana hospital

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው በሀድያ ዞን አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ እየዋሉ በመሆኑ ህመምተኞች በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች ህክምና ሳያገኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ነዋሪዎቹ ገለፁ፡፡ ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አንዲት ምጥ የተያዙ እናት በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጎምበራ የጤና ጣቢያ በሄዱበት ወቅት ‹‹ከአቅማችን በላይ ነው!›› ተብለው ወደ ሆሳዕና ሪፈራል ሆስፒታል ሄደው እንዲታከሙ ሪፈር ቢፃፍላቸውም በትራንስፖርት ችግር ነፍሳቸው አልፋለች፡፡

ለጤና ጣቢያው የተመደበችው አምቡላንስ በጎምበራ ወረዳ ኦሌ ቀበሌ ለገዥው ደኢህዴን/ኢህአዴግ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በመውጣቷ ቤተሰብ ነፍሰጡሯን ከጎምበራ ክሊኒክ ወደ ሆሳዕና ሪፈራል ሆስፒታል በቃሬዛ ለመውሰድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ሆሳዕና ሆስፒታል በቶሎ መድረስ ባለመቻላቸው የነፍሰ ጡሯ ህይወት መንገድ ላይ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ በመዋላቸው ምክንያት በርካታ ህመምተኞች በተለይም እናቶችና ህፃናት በቶሎ ወደ ሆስፒታል መድረስ ባለመቻላቸው ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በምርጫ 2002 ዓ.ም ወቅትም በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ በሀዲያ ዞን አምቡላንሶች ለኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ ወጥተው ነፍሰ ጡር እናቶች ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡

በእሳት አደጋ የወደመውን ታሪካዊ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ

የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም.  በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቃጠሎ ምክንያት 106 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ታሪካዊው የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ህንፃ ሙሉ ለሙሉ መውደሙ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በተቃጠለው ቤተክርስቲያን ምትክ አዲስ ህንፃ ቤተክርስቲያን ለማሰራት በይፋ እንቅስቃሴ በመጀመሩ፤ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለምትፈልጉ፡-

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣

ባቴና ቅርንጫፍ፤ ሆሳዕና

ዝግ የባንክ አካውንት ቁጥር  100 011 0719 969

መርዳት እንደሚቻል በመጠቆም፤ ለምታደርጉት ድጋፍ ሁሉ በቤተክርስቲያኗ ስም ከወዲሁ ማመስገኑን የህንፃ አሰሪው ኮሜቴ አስታውቋል፡፡

ለበለጠ መረጃ 

ሀገር ውስጥ ላሉ በስልክ ቁጥር 0912- 446829 ወይም 0913-750229

ከውጭ ሀገር ከሆነ  +254 912-446829 ወይም +254 913 750229  ማነጋገር እንደሚቻል የህንፃ አሰሪው ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት

በሆሳዕና ከተማ የመብራት ኃይል ገመድ ተበጥሶ የሰው ህይወት አጠፋ

 

power1በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ የኤልክትሪክ ገመድ ተበጥሶ የ13 ዓመት ልጅ ህይወት ማጥፋቱ ተገለፀ፡፡ አደጋው የደረሰው በጎፈር ሜዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ቦቢቾ በተባለ ቀበሌ ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ለረጅም ጊዜ ምሰሶው ሊወድቅ የደረሰ የኤሌክትሪክ ገመድ ተበጥሶ አንድ የ13 ዓመት ልጅ ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ሳለ በደረሰ አደጋ ወዲያው ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡ hossana

አዲስሚዲያ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት ከሆነ ምሰሶው በመንገድ ጥገና ቁፋሮ ምክንያት በመላላቱ የኤሌክትሪክ ገመዱ ረግቦ እንደነበርና ይህንንም በመፍራት በተደጋጋሚ ለከተማው መስተዳደርና በከተማው ለሚገኝ የመብራት ኃይል ዲስትሪክት ቅሬታ ቢያቀርቡም ሰሚ ባለማግኘታቸው አደጋው መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ ከሟቹ ልጅ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ላደረሰው የቸልተኝነት አደጋ ምን ምላሽ እንዳለው ለማጣራት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደ ሆኑት አቶ ምስክር ነጋሽ ደውለን ለማጣራት ብንሞክርም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡