በቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ክስ በቀረበባቸው እስረኞች ላይ የተፈፀመ በደል
ጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ያሬድ ሁሴን ኢብራሂም የክስ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው 25 ተከሳሾች በአዲስ አበባ ቀጠሮ ማረፊያ ቤት( ቂሊንጦ) ቃጠሎ ሰበብ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደው የደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰትን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽ አጣርቶ እንዲያቀርብ በማዘዙ ኮምሽኑ ምርመራውን ለፍርድ ቤት ልኳል።
ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ:_
የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ በተፈጠረው ቃጠሎ ምክንያት በቃጠሎው እጃችሁ አለበት ተብለን ነሃሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለይተን ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደን ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሞብናል። በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ያልፈፀምነውን ድርጊት እመኑ እየተባልን ለሰው ልጅ በማይመጥን፣ ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት ተፈፅሞብናል። ለአንድ ወር ያህል በካቴና ከአልጋ ጋር ታስረናል። ተገልብጠን ተገርፈናል። የውስጥ እግራችን ተገርፈናል። አንጠልጥለው በማሰር ውሃ እየደፉብን፣ በኤሌክትሪክ ሾክ እየተደረግን ተመርምረናል። በእምነትና ማንነታችን ጥቃት ደርሶብናል። በደረሰብን ድብደባና ስቃይ ብዛት ያልፈፀምነውን ድርጊት ፈፅመናል ብለን ለማመን ተገደናል።
ወደ ቀጠሮ ማረፊያ ቤት (ቂሊንጦ) ከተመለስን በኋላ ቢሆን በደረሰብን ድብደባ ብዛት ላጋጠመን ጉዳት ህክምና አላገኘንም። በቃጠሎው ወቅት አልባሳትን ጨምሮ ንብረቶቻችን በማረሚያ ቤቱ የተወረስን ሲሆን እንዲመለሱልን ስንጠይቅ ተቃጥለዋል የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል።
በምርመራ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ተከሳሾች:_
1) ፀጋዬ ዘውዱ:_ቀኝ እግር ከጉልበቱ በታች ጠባሳ፣ ግራ እግር ላይ የግርፋት የሚመስል ጠባሰ፣ ጀርባ ላይ ጠባሳ ፣ የአውራ ጣት ጥፍር መነቀል፣ የካቴና የታሰረበት ምልክት
2) ያሬድ ሁሴን:_ ግራ እግር ላይ ጠባሳ፣ቀኝ እጅ ላይ ጠባሳ፣ የካቴና እስር ምልክቶች፣
3) ኃይለ መስቀል ፀጋዬ:_ ሁለት እጆቹ ላይ ጠባሳ
4) ሁሴን አህመድ:_ የግራ እጅ ጠባሳ
5)ሰለሞን ጫኔ:_የቀኝ እጅ የመሃል ጣት ስብራት፣ የቀኝ እግር ደም ስር መዛባት
6)ስማቸው አርጋው:_ የግራ እጅ የመጀመርያ ጣት ስብራት፣ ሁለት እጆቹ ላይ ጠባሳ፣ ሁለት እግር ታፋዎች ላይ የግርፋት ጠባሳ ምልክቶች
7)ዋሲሁን አየለ:_ በካቴና የመታሰር ምልክቶች
8) ሀቢብ ከድር:_ሁለት እጅ ላይ የጠባሳ ምልክቶች፣ ቀኝና ግራ ክንድ ላይ የጠባሳ ምልክቶች፣
9) ግሩም አስቀናው:_ ሁለት እጆቹ ላይ በካቴና የታሰረበት ጠባሳ ምልክቶች፣ ከቀኝ ታፋ በላይ ትልቅ ጠባሳ
10) ሻሾ አድማሱ:_ ወገቡ ላይ ትልቅ ጠባሳ
11)ማናዬ መንገሻ:_ የአውራ ጣት ጥፍር መነቀል
12) ቢንያም አሰፋ:_ የቀኝና ግራ እጅ ላይ በካቴና መጥበቅ ምክንያት የጠባሳ ምልክቶች
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ከላይ የተጠቀሱት እስረኞች ወደ እስር ቤት ሲገቡ የተጠቀሱት ጉዳቶችና ምልክቶች እንዳልነበረባቸው አረጋግጧል። የኮምሽኑ ምርመራው የተካሄደው ድብደባው ከተፈፀመ 10 ወር በኋላ ቢሆንም የግርፋት ምልክቶች በግልፅ እንደሚታዩ በሪፖርቱ ላይ ተገልፆአል። በመሆኑም ተከሳሾች ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደው በአቤቱታው ላይ የተጠቀሰው ለሰው ልጅ የማይመጥንና ኢ ሰብአዊ የሆነ ድርጊት እንደተፈፀመባቸው ተረጋግጧል።
ይሁንና አቤቱታ ያቀረቡት 25 ተከሳሾች ሆነው ኮምሽኑ የጠቀሰው የ12 ተከሳሾችን በደል ብቻ ነው። በሌሎች መዝገቦችም ተመሳሳይ አቤቱታ ቀርቦ ኮምሽኑ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን በእስረኞች ላይ የተፈፀመውን በደል በሚገባ በሪፖርቱ አላጠቃለለም ተብሏል።
በደል የተፈፀመባቸው እስረኞች ካለመጠቀሳቸውም በተጨማሪ በሪፖርቱ የተጠቃለሉ እስረኞች የደረሰባቸው በደል በሚገባ አልተጠቀሰም ተብሏል። በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ የተከሰሱ 38 ተከሳሾች ሸዋሮቢት ተወስደው በደል በተፈፀመባቸው 175 እስረኞች ላይ ከተፈፀመው በደል መካከል ኮምሽኑ 6 በመቶውን ብቻ በሪፖርቱ ማጠቃለሉን ተከሳሾቹ በችሎት ተናግረዋል። ኮምሽኑ የተፈፀመውን በደል በሚገባ በሪፖርቱ ባለማጠቃለሉና ገለልተኛ አይደለም በሚል ሌላ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ የተፈፀመባቸውን አስከፊ በደል እንዲያጣራ እስረኞቹ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት እያቀረቡ ነው።
ኮምሽኑ በእስረኞች ላይ በደል ፈፀሙ የተባሉ አካላትን ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንዲያጣራ በምክረ ሀሳብ ያስቀመጠ ሲሆን እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ኃላፊዎች ድብደባ እንደፈፀሙባቸውና እንዳስፈፀሙባቸው የኃላፊዎችን ስም ጭምር በመጥቀስ ገልፀዋል። በመሆኑም በደል የፈፀመው አካል ጉዳዩን እንዲያጣራ መታዘዙ የደረሰብን በደል ተሸፋፍኖ እንዲቀር ስለተፈለገ ነው የሚል ቅሬታ አቅርበዋል። ከተከሳሾቹ ባሻገር ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረባቸውና ያዘጋጃቸው ምስክሮች በምርመራ ወቅት በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ተገደው ለምስክርነት እንደቀረቡና ተገደው ምስክር በሆኑት ላይ የተፈፀመው በደልም እንዲጣራ ተከሳሾች ለፍርድ ቤት አመልክተዋል።