አቶ ዮናታን ተስፋዬ የቀረበበትን ክስ ለመከላከል ታዋቂና በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች በምስክርነት ተጠርተዋል
*አቶ በቀለ ገርባና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከማረሚያ ቤት ቀርበዋል፤ ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉን ያሰረው አካል ሳያቀርበው ቀርቷል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረውና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፌደራል አቃቤ ህግ የቀረበበትን ሽብር ክስ እንዲከላከል የተወሰነበትን ክስ ለመከላከል የኦፌኮ ፕሬዚደንትና ምክትል ፕሬዚደንትን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸውና ታዋቂ ሰዎች በምስክርነት ተጠርተዋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ዛሬ ህዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም መከላከያ ምስክሮችን ለማስደመጥ በተያዘለት ቀጠሮ መሰረት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቧል፡፡ አቶ ዮናታን በጠበቃው አማካኝነት የምስክሮችን ዝርዝር ለፍርድ ቤት ያስረዳ ሲሆን፣ ከምስክሮቹ መካከል አብዛኞቹ ሲገኙ ሦስቱ ብቻ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተከላከል የተባልሁበትን ክስ በመከላከያ ምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኛል ያላቸውን 10 ምስክሮች ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ እነዚህም ወላጅ አባቱ ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሳ፣ ታናሽ እህቱ ገዳምነሽ ተስፋዬ፣ የቅርብ ጓደኛው ኤፍሬም ታያቸው፣ የኦፌኮ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ በእስር ላይ የሚገኘው ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ እና አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው፡፡
ከእነዚህ መከላከያ ምስክሮች መካከል ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋና ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ በዛሬው ቀጠሮ አልቀረቡም፡፡ በእስር ላይ የሚገኘው በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ዛሬ ያልቀረቡት እንዲቀርቡ፣ የቀረቡትም ተጨማሪ መጥሪያ ሳያስፈልጋቸው በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ታዝዟል፡፡
ተከሳሹ በዚህ መሰረት አብዛኞቹ ምስክሮቹ መገኘታቸውን ችሎት ፊት አቅርቦ በማስረዳት፣ ምስክሮቹን አግኝቶ ስለሚመሰክሩበት ጉዳይ ለመነጋገር ጊዜ እንደሚፈልግ በመግለጽ ተለዋጭ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ከምስክሮች መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹‹የፍርድ ቤት መጥሪያ በእጄ አልደረሰኝም፡፡ ጠዋት ትፈለጋለህ ተብዬ በጽህፈት ቤት ተጠርቼ ነው የመጣሁት፡፡ ስለምመሰክርበት ጉዳይ አሁን ገና ነው የሰማሁት፡፡ የሙያ ምስክርነት እንድሰጥ ስለተጠራሁ ትንሽ የዝግጅት ጊዜ እንዲኖረኝ በተለዋጭ ቀጠሮ ምስክርነቴን እንድሰጥ ይፈቀድልኝ›› ሲል ከተከሳሹ አቤቱታ ጋር የተጣጣመ ማሳሰቢያ ለችሎቱ አሰምቷል፡፡
አቃቤ ህግ በበኩሉ ዛሬ የቀረቡት ምስክሮች እንዲመሰክሩ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ የቀረበውን ማሳሰቢያ በመቀበል ምስከሮቹ ተሟልተውና ስለሚመሰክሩበት ጉዳይ ተረድተው ሲቀርቡ ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለታህሳስ 26 እና 27 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከሰው ምስክሮች በተጨማሪ ሦስት የሰነድ ማስረጃዎችን ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ በዛሬው ዕለት ለምስክርነት ከቃሊቲ እስር ቤት የቀረበው የ18 ዓመት ፍርደኛ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሙሉ ጥቁር ሱፍ ከጥቁር መነጽር ጋር ለብሶ እጆቹ በካቴና ታስረው በከፍተኛ ጥበቃ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ችሏል፡፡ በቃሊቲም ሆነ በቂሊንጦ የሚገኙ እስረኞች የእስረኛ ዩኒፎርም ለብሰው የቀረቡ ቢሆንም እስክንድር ነጋ ብቻ በተለየ በሱፍ ልብስ መቅረቡን ለመመልከት ተችሏል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ከፍርድ ቤት ግቢ በመኪና ሊጫኑ ሲወሰዱ በካቴና የታሰሩ እጆቹን ከፍ በማድረግ በፈገግታ ታጅቦ ‹‹አይዞን እንበርታ!›› የሚል ቃል ሰላምታ ላቀረቡለት ሁሉ መናገሩን ኢጥዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ዘገባ አመልክቷል፡፡
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አቶ ዮናታን ተስፋዬን ፍር ቤት እንዳልቀረበ ተገለፀ
በኦሮምያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀጠል ፌስቡክ ላይ በመጻፍ ተንቀሳቅሰሃል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበበት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ተከሳሹን አላቀረበውም፡፡

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ለዛሬ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሽ በእስር የሚገኝበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሳያቀርበው ቀርቷል፡፡ ተከሳሹን ለምን እንዳላቀረበ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ተወካይ እንዲያስረዳ ተጠይቆ፣ የዕለቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ሳሙኤል ደሚ ‹‹ተከሳሹ ታሞ አላቀረብነውም›› የሚል መልስ በቃል ሰጥቷል፡፡
ከሳሽ የፌደራል አቃቤ ህግ ሁለት ምስክሮቹን ለማሰማት አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ተከሳሹ ባለመቅረቡ ሁለቱ ምስክሮች አቶ አብርሃም ወልዴ እና አቶ መኮንን በላይ በቀጣይ ቀጠሮ ተጨማሪ መጥሪያ ሳያስፈልጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ በዳኞች ተነግሯቸው ተመልሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱን ምስክሮች ለመስማት ለሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ዮናታን ተስፋዬ በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና በእስር ቤት ሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመበት እንዳለ ጠቅሶ አያያዙ እንዲሻሻልለት ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም አቤቱታ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡
ማረሚያ ቤት ለዚህ አቤቱታ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ መልስ ሰጥቷል፡፡ ችሎት ሳይሰየም ጉዳዩን በቢሮ የተመለከቱት ዳኞች የተሰጠውን የጽሁፍ መልስ ለተከሳሽ ጠበቃ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በዚህም ማረሚያ ቤቱ ጨለማ ክፍል እንደሌለው፣ አቶ ዮናታን ከሌሎች እስረኞች በተለየ እንዳልተያዘ በመግለጽ ተከሳሹ ያቀረበው አቤቱታ ከእውነት የራቀና ስም ማጥፋት ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ ይስጥልኝ የሚል መልስ እንደሰጠ የጽሁፍ መልሱ በንባብ ሲሰማ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የሰጠው መልስ ክህደት መሆኑን በመግለጽ፣ ደንበኛቸው ችሎት ያልቀረበው በማመልከቻው ላይ እንደገለጸው የመብት ጥሰት እየተፈጸመበት መሆኑን በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ደንበኛዬ በማመልከቻው የገለጸው የመብት ጥሰት እንደተፈጸመበትና እየተፈጸመበት ስለመሆኑ ማስረጃ አለን›› ብለዋል የተከሳሽ ጠበቃ፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ጉዳዩን ተከሳሹ በአካል ሲቀርብ እንደሚያየው በመግለጽ ለሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ዛሬ ችሎት ያልቀረበው ለሳምንት የዘለቀ የርሃብ አድማ ላይ በመሰንበቱ ሰውነቱ ተዳክሞ ሊሆን እንደሚችል ከቤተሰቦቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተከሳሹ ባለፈው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃሉን በሰጠበት ወቅት፣ ‹‹ክሱ በቀረበበት መንገድ የተገለጸውን የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ግን ጽፌያለሁ፡፡ በመሆኑም የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም›› ማለቱ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ኢሰመፕ
ዮናታን ተስፋዬ ያቀረበው መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ የእምነት ክህደት ቃል ሰጥቷል
“ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ጽፌያለሁ” ዮናታን ተስፋዬ

በኦሮምያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀጠል ተንቀሳቅሰሃል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበበት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሰብዓዊ መብት አራማጅ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያና አቃቤ ህግ ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠውን መልስ መርምሮ ብይኑን ያሰማው ፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የተከሳሹን የእምነት ክህደት ቃል ተቀብሏል፡፡
አቶ ዮናታን የቀረበበት የሽብር ክስ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት በክስ መቃወሚያው መጠየቁ ይታወሳል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ በተከሳሹ ለቀረበው መቃወሚያ መልስ ሰጥቷል፡፡ ግራ ቀኙን ፍርድ ቤቱ እንደመረመረው የገለጹት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ታረቀኝ አማረ የተሰጠውን ብይን በንባብ አሰምተዋል፡፡
ተከሳሹ ‹‹….አመጽና ብጥብጥ ለማስቀጠልና ለማነሳሳት በፌስቡክ ድረ ገጽ ቀስቃሽ ጽሁፎችን መጻፍ ድርጊት›› በተከሳሹ ላይ ከተጠቀሰው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 4 ጋር የተቀራረበ አለመሆኑን የወ/መ/ሕግ/ሥ/ሥ/ቁ.112 ጠቅሶ፣ ከድንጋጌው ውጭ የቀረበና ‹‹የሽብርተኝነት ተግባር›› ስላለመሆኑ ያቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ‹‹የተመለከተውን ድንጋጌ አያሟላም ያሟላል የሚለው በማስረጃ ምዘና የሚታይ ይሆናል›› በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡
ተከሳሹ የቀረበበት አመጽና ብጥብጥ ‹‹….የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር….›› እንጂ የኦ.ነ.ግ ተግባር ያለመሆኑ የህግ ግምት ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበው መቃወሚያ ‹‹ክሱ ተቃውሞውን ስለማስቀጠል በተመለከተ የቀረበ በመሆኑ መቃወሚያውን አልተቀበልነውም›› በሚል ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጽፎታል ተብሎ በማስረጃነት የቀረበው ጽሁፍና ፈጽሞታል ተብሎ የቀረበበት ድርጊት የወንጀል ኃላፊነትን የማያስከትልና ህገ-መንግስታዊ ጥበቃ የተደረገለት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መሆኑን በማስመልከት ክሱ እንዲሰረዝና በነጻ እንዲሰናበት ያቀረበውን ተቃውሞ ደግሞ ‹‹ህገ መንግስቱ አንቀጽ 29(6) ገደቦችንም ያስቀመጠ በመሆኑና አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ንብረት ማውደምን ጠቅሶ ያቀረበው ክስ የተሟላ ስለሆነ በማስረጃ የሚታይ ይሆናል›› በማለት ተቃውሞውን ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
ተከሳሹ የቀረበበት ክስ ግልጽ ያለመሆኑንና የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር ግልጽ አለመደረጉን በተመለከተ ላቀረበው መቃወሚያ በጸረ-ሽብር አዋጁ ላይ የተመለከተውን የምስክሮች ደህንነት ጥበቃ በመጥቀስ ማስረጃ ዝርዝሩ (ምስክሮቹ) እንዲገለጹ የቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጓል፡፡ በዚህም ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን ለመስጠት ዝግጁ ስለመሆኑ ጠይቆ ተከሳሹ ቃሉን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ አቶ ዮናታን የቀረበበት ክስ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸም አለመፈጸሙና ጥፋተኛ ስለመሆን አለመሆኑ ተጠይቆ ‹‹ክሱ በቀረበበት መንገድ የተገለጸውን የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ግን ጽፌያለሁ፡፡ በመሆኑም የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም›› ብሏል፡፡
ተከሳሹ በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት አልፈጸምኩም በማለቱ አቃቤ ህግ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙ እንዲታዘዝለት የጠየቀ ሲሆን፣ ተከሳሹ በበኩሉ ፌስቡክ ላይ ጽፏቸው ከኮምፒውተር ሲገለበጡ አይቻለሁ የሚሉ የደረጃ ምስክሮች ከሆኑ ባልተካደ ጉዳይ ላይ ፍትህን ማጓተት እንዳይሆን ግንዛቤ ይያዝልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክር የማሰማት መብቱ የእኔ ነው በማለት ምስክሮቹ እንዲሰሙለት አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቀርበው እንዲሰሙ ለሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሁለት ሳምንታት በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና ዛሬም ከጨለማ ክፍል እንደሚገኝ ጠቅሶ አያያዙ እንዲሻሻልለት ማመልከቻ አስገብቷል፡፡ ተከሳሹ በማመልከቻው ላይ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ መፍትሄ እንዲበጅለት ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ግን በተሰጠው ቀጠሮ (ሐምሌ 20 ቀን 2008) ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት እናዝዛለን በማለት አልፎታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP
“ሕገ መንግሥቱ በሰጠኝ መብትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረጋገጡት ድርጊት ልከሰስ አይገባም” አቶ ዮናታን ተስፋዬ
ታምሩ ጽጌ
በፌስቡክ አድራሻቸው አመፁና ብጥብጥ ቀስቃሽ ጽሑፎችን በማሠራጨት፣ የኦነግን ዓላማ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የቀረበባቸውን ክስ ተቃወሙ፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ በሰጠኝ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና በክሱ የተጠቀሰው ብጥብጥና አመፅ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረጋገጡበት ሁኔታ ልከሰስ አይገባም፤›› ሲሉም ተቃውሞአቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው ብጥብጥና አመፅ ‹‹የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግር ነው፡፡ የሌላ ሦስተኛ አካል ተሳትፎ የለበትም፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማረጋገጣቸውን ያስረዱት ተከሳሹ አቶ ዮናታን፣ የተለያዩ የፌደራልና የክልል ሥራ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በማጠናከር፣ ዕርምጃ የወሰዱበትና በርካታ ሹማምንትም ከኃላፊነት መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የሚያውቀውና ከማንም ያልተደበቀ በመሆኑ፣ ግልጽ የሆነ የሕግ ግምት (Judicial Notice) የሚወስድበት ጉዳይ መሆኑን አቶ ዮናታን አክለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተደረገው አመፅና ብጥብጥ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑ ተረጋግጦ ሳለ፣ በቀረበባቸው ክስ ላይ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እንደተጀመረና እሳቸው በፌስቡክ ገጻቸው ባሠራጩት መጣጥፍ ለማስቀጠል የተደረገ እንደሆነ መገለጹ፣ ከአዋጁ መንፈስ ውጪ መሆኑን በመጠቆም ክሱ ውድቅ ተደርጐ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ዮናታን በክስ መቃሚያቸው ላይ እንዳብራሩት፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን መተላለፋቸው ተገልጿል፡፡ በአንቀጹ እንደተገለጸው ተላልፈዋል የተባለው ድርጊት ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳትና መሞከር የሚል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በክሱ ያሰፈረው አቶ ዮናታን ኦነግ ያስጀመረውን አመፅና ብጥብጥ ለማስቀጠል በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የተለያዩ ቀስቃሽ ጽሑፎችን ማሠራጨታቸውን የሚገልጽ በመሆኑ፣ በአዋጁ አንቀጽ ሥር ከተመለከቱት ውስጥ በአንዱም የማይሸፈን መሆኑን በመግለጽ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የዓቃቤ ሕግ ክስ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 112 የተደነገገውን ማለትም ‹‹… ወንጀለኛው የፈጸመው ተግባር፣ ወንጀል ከሚያደርገው የሕግ አነጋገር ጋር በጣም የተቀራረበ መሆን አለበት፤›› ከሚለው ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ዮናታን ፈጽመውታል ለተባለው ክስ በማስረጃነት የቀረበው የሰነድ ማስረጃ በፌስቡክ ገጻቸው ተሠራጨ የተባለው መጣጥፍ መሆኑን ገልጸው፣ ፌስቡክ ደግሞ ዘመናዊ የመልዕክት መለዋወጫ ዘዴ መሆኑን፣ ይኼም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ድንጋጌ ከመሆኑ አንፃር፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በየትኛውም ሕግ ገደብና ክልከላ ያልተደረገባቸውና በቀረበባቸው ክስ በተጠቀሰው አንቀጽ ሥር የማይሸፈንና የሽብርተኝነት ተግባር አለመሆኑንም አቶ ዮናታን አክለዋል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስከበር የተቀመጡ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን የማያሟላ ክስ መሆኑን ገልጸው፣ ተሰርዞ በነፃ እንዲሰናበቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክስ ሐሳቡና ይዘቱ አርትኦትና የቃላት ማስተካከል የጎደለው ከመሆኑም በተጨማሪ ለመረዳት የሚያስቸግር፣ በረጃጅም ዓረፍተ ነገሮችና አባባሎች አሳሳች ሆኖ የቀረበ በመሆኑ በወንጀል መዝገብ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 111 ድንጋጌን ማለትም፣ ‹‹… የክስ ማመልከቻ ቀን፣ ዓመተ ምሕረት የተጻፈበትና የተፈረመበት…›› የሚለውን የማያሟላ መሆኑን አቶ ዮናታን ጠቁመው፣ ክሱ ተሰርዞ በነፃ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክሱን የሚያሻሽል ከሆነም በሕጉ አግባብ ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ በሚያቀርበው ክስ ላይ የሚጠቅሰው የሕግ አንቀጽ፣ ከክሱ ጋር የሚቀራረብና የተከሳሹን የመከራከር መብት የማያጣብብ አድርጐ እንዲያዘጋጅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ጉዳዩን ለሚከታተለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ምላሽ ለመጠባበቅ ለግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከኦነግ ጋር ተያይዞ የሽብር ክስ ተመሰረተበት
የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና በምርጫ 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወረዳ 17 የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 የወጣውን አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን ተላልፏል በሚል ክስ ተመስርቶበታል፡፡

ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክሱ በዳኞች ቢሮ በንባብ የተሰማበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተከሳሹ በሚጠቀምበት ድረ-ገፅ በተለይም ፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን “አመፅና ብጥብጥ” ለማስቀጠል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ዓላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ሲል አቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡ የክስ ፋይሉ ሌላ ተከሳሽ ውጭ ለአቶ ዮናታን ብቻ የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር በማኀበራዊ ሚዲያ የለጠፋቸው ፅሑፎች ናቸው፡፡
በዚህም ተከሳሹ የቡድን (ኦነግ) ዓላማን ለማሳካት አመፅና ብጥብጥ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በሚጠቀምበት ድረ-ገፅ (ፌስቡክ) ቀስቃሽ ፅሑፎችን በመፃፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር እና ማነሳሳት ወንጀል ክስ በአቃቤ ህግ እንደቀረበበት ታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተለያዩ ቀናት በግል የፌስቡክ ገጹ ላይ ያስነበባቸው ፅሑፎች ክሱ ላይ ተካተው በማስረጃነት ቀርቦበታል፡፡
ታህሣሥ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በተመለከተ፣ ታህሣሥ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም በሚል የፃፈው፣ ታህሣሥ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲጀመር ምንም ዓይነት መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) የለም በሚል የፃፈው፣ ታህሣሥ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የተቃውሞ ትግሉ ቀጥሏል በሚል የፃፈው፣ ህዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. እነሆ 7 መልዕክት ብሎ በፃፈው እና በሌሎችም ፅሑፎች አማካኝነት ቅስቀሳ አድርጓል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦበታል፡፡
ዮናታን ተስፋዬ በነጠላ መዝገብ ብቻውን ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ በዕለቱ ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ምክንያት በዳኞች ቢሮ መታየቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የክሱን ሂደት ዬናታን ቤተሰቦችም፣ ወዳጆችና ጋዜጠኞች በችሎት መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ አቶ ዮናታንም የክስ መቃወሚያውን ይዞ ለፊታችን ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.