Daily Archives: July 11th, 2013

ሰበር ዜና አሁድ የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የቀበሌ ሰራተኞች በየቤቱ እየቀሰቀሱ መሆኑ ተገለፀ

Bisrat Woldemichael

አንድነት ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ የከተማው መስተዳደሮችና የፀጥታ ኃይሎች ፓርቲው ህጋዊ የማሳወቅ ስራውን መስራቱን ገልፀው ሰልፉን መከልከል እንደማይችሉ ካረጋገጡ በኋላ በከተማው ያሉ የቀበሌ ሰራተኞች መደበኛ ስራቸውን ጥለው በሰላማዊ ሰልፉ ዙሪያ በየቤቱ እየዞሩ ማስፈራራትና ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ማንም እንዳይገኝ፣ ሰልፉ ህገወጥ ነው በሚል ቅስቀሳ እየሰሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ነዋሪው በበኩሉ የፓርቲው ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ስለሆነ በሰልፉ ላይ እንገኛለን፣ ፓርቲው የሚያካሂደው ሰላማዊ ሰልፍ ህገወጥ ከሆነ እነሱን (ፓርቲውንና ቅስቀሳ የሚሰሩትን ) ለምን አታግዷቸውም የሚል ጥያቄ ሲያነሱባቸው፤ ለቅስቀሳው የተሰማሩት የቀበሌ ሰራተኞች እምቢ ብለው የሚወጡ ካሉ እስራት ይጠብቃቸዋል፤ በሚደርስባቸው ችግር ኃላፊነቱን አንወስድም ሲሉ ማስፈራሪያና ዛቻ መፈፀማቸው ተጠቁሟል፡፡ 

 የደቡብ ወሎ ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ብስራት አቢ ቅስቀሳ በማድረግና በራሪ ወረቀት ሲበትኑ መጀመሪያ የደሴ ከተማ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያለምንም ምክንያት አስሯቸው የጣቢያው አዘዦች ከሰዓታት በኋላ ሲለቋቸው 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ በድጋሚ ምክንያቱን ሳይገልፅላቸው ለአንድ ሰዓት አስሮ እንደለቀቃቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ብስራት አሁንም ድረስ መስተዳደሩ ከፈቀደ በኋላ በጎን ህገወጥ ስራ መስራቱ እንዳሳዘናቸውና ሰላማዊ ሰልፉ ህገወጥ ነው ካለም ደብዳቤ መፃፍና እንዲቀር ማድረግ ሲችሉ ከላይ ፈቅደው እታች ላሉት መመሪያ አላስተላለፉም፤ ይሁን እንጂ ሰላማዊ ሰልፉ ህጋዊና ሰላማዊ ስለሆነ እንቀጥልበታለን፣ ህገወጥ ናችሁ የሚል አካል ካለ ሰልፉን ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊ ሰነድ የያዙ መሆናቸውን በመግለፅ አሁንም ቅስቀሳ ላይ እንደሆኑ ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ የከተማው ፅጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ በላይ በበኩላቸው እኛ ሰልፉን ለማደናቀፍ ያሰርነው የለም፣ እኔ አሁን ከከተማ ውጭ ስለሆንኩ አረጋግጬ እነግርሃለው፤ የእውነት የታሰረ ካለም አንተም አረጋግጥ ቢሉኝም ዳግም ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡

የከተማው ከንቲባ አቶ አለባቸው የሱፍን በጉዳዩ ዙሪያ ትናንት ሐምሌ 3 ቀን 2005ዓ.ም. ሳናግራቸው ምንም የሚፈጠር ችግር እንደሌለና ከፓርቲው አመራሮች ጋርም ለመመካከርና ለመወያየት ቀጠሮ ይዘናል፣ ፓርቲው ህጋዊ በሆነ መንገድ አሳውቆናል፣ መከልከልም ሆነ ማገድ አንችልም፤ ነገር ግን በፀጥታው ጉዳይ ለመነጋገር ነው ያሰብነው ሲሉ ነግረውኝ ነበር፡፡ ዛሬ በቀበሌ ሰራተኞችና በየቀጠናው ባሉ ፖሊሶች እየተደረገ ስላለው ምላሽ እንዲሰጡኝ ወደ ቢሮአቸው ባቀናም ከቢሮ ውጭ ስብሰባ ላይ መሆናቸው ስለተነገረኝ ከሰዓት በኋላ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ብደውልም ሊያነሱልኝ አልቻሉም፤ስለዚህ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልኩም፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የመጨረሻው ዙር ከአዲስ አበባ አቶ ግርማ ሰይፉ(ብቸኛው የተፎከካሪ ፓርቲ የፓርላማ አባል)፣ አቶ በላይ ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ለእሁዱ ሐምሌ 7 ቀን 2005ዓ.ም. ሰላማዊ ሰልፉ ዛሬ ደሴ ከተማ ገብተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሼህ ኑሩ ይማም መገደል ጋር በተያያዘ በርካት ወጣቶች አሁንም እየታሰሩ መሆኑን 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የተመለከትኩ ሲሆን ይህ በሌሎችም ጣቢያዎች እየተከናወነ መሆኑም በከተማው ያነጋገርኳቸው ነዋሪዎች አረጋግጠውልኛል፡፡

%d bloggers like this: