አንድነት ፓርቲ በይፋ ህዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄ ጀመረ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ገዥው የፓርቲ ኢህአዴግን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየጣሰ ነው በሚል ዛሬ ሰኔ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ይፋዊ ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው አዲስ አበባ ቀበና በሚገኘው ዋና ፅህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት”(Millions of Voices For Freedom) በሚል መሪ ቃል መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የሚሊዮኖችን ድምፅ በመሰብሰብ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጨውን የፀረ ሽብርተኝነት ህግ በመቃወም እንዲሰረዝ የተቃውሞ ስምምነት ፊርማ(ፒቲሽን) በማሰባሰብ ለእስር ተዳረጉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች እንዲፈቱ እንጠይቃለን ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ በተለያየ ምክንያት ገጠርና ከተማ ያሉ ከአዲስ አበባና ሌሎች ከተማ ያሉ ዜጎች አለአግባብ ከሚኖሩበት ቀዬ ማፈናቀል በተለይም ዘርን መሰረት በማድረግ ከጉራፈራዳና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉ ነዋሪዎች እና በልማት ስም ለውጭ ዜጎች መሬት እየተሰጠ እንደ ጋምቤላ ያሉ ዜጎቻችን መፈናቀላቸው ህገወጥ ተግባር ነው በሚል በማውገዝ የድርጊቱ ፈፃሚዎችን ለፍርድ ማቅረብ እንደተዘጋጀና ለዚህም እንቅስቃሴያችንን የሚደግፉ ኢትዮጵውያን ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ጠይቋል፡፡
ፓርቲው ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ የሰላማዊ ትግል ስልቶችን የቀየሰ ሲሆን በዋነኝነትም በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ህዝባዊ የአዳራሽ ስብሰባዎችን፣የአደባባይ ስብሰባዎችንና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰለፍ ማድረግን እንደሚያካትት ተጠቅሷል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ 6 ህዝባዊ ስብሰባዎችን፣ በክልሎች ለመጀመሪያ ዙር ብቻ 10 ስብሰባዎች ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋ፡፡
እንደ ፓርቲው ገለፃ ከሆነ የህዝባዊ ንቅናቄ ዓላማው፡-
1. የፀረ-ሽብር ህጉ የኢትዮጵያውያንን በርካታ መብቶች የሚገፍ በመሆኑና ከህገ መንግስቱ ጋር የሚፃረር በመሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የተቃውሞ ድምፅ በማሰባሰብ በአስቸኳይ እዲሰረዝ ጥያቄ እናቀርባለን፡፡ የድጋፍ ፊርማ(ፒቲሽን) እናስፈርማለን ፡፡ ይህንንም በሰላማዊ ሰልፍ እንጠይቃለን፡፡ ከዛም የሚሊዮኖችን ድምፅ በመያዝ ወደ ክስ እንሄዳለን፡፡
2. በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው በገጠርና በከተማ የዜጎች መፈናቀልና የመሬት ቅርምት እንዲቆምና መፍትሄ እንዲያገኝ እንጠይቃለን፡፡
3. የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እንዲቀረፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንጠይቃለን፡፡
4. የንግዱ ማኀበረሰብ ውስጥ ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ፣ ማጥላላትና ማዋከብ እንዲቆም፤ ገዥው ፓርቲ ህግ አውጭ እና ነጋዴ የሚሆንበት ስርዓት እንዲያበቃና የግሉ ሴክተር በልማት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው እንጠይቃለን፡፡ ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መሳካት ህዝቡ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ መኀበራት፣ ሚዲያው፣ በውጭ የሚኖሩና ለሀገር ተቆርቋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ የሀገርን ጥቅም ለማስቀደም የሚፈልጉ የኢህአዴግ አባላት እንዲሳተፉ ሀገራዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡ በመግለጨው ዙሪያም ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው ከፓርቲው አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥፋተኛ መሆኑን አመነ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንያህል ተሾመ ሰኔ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ጋር በተደረገው ጨዋታ መሰለፉ ስህተት እንደሆነ አመነ፡፡ ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ከመጫወቱ በፊት ችግር ስለመፈጠሩ ከፊፋ ደብዳቤ ደርሶት እንደነበርም ገልጿል፡፡
የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለችግሩ ተጠያቂ ያላቸውን ግለሰቦች ዝርዝርም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት የብሄራዊ ቡድኑ ቡድን መሪ አቶ ብርሀኑ ከበደ ፣ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ፣ ረዳት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ፣ የቡድኑ ተጨዋች ምንያህል ተሾመ እና የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች ጥፋተኛ ተብለዋል።
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በጥፋተኞቹ ላይ በቅርቡ ተገቢውን ቅጣት በመውሰድ የቅጣት ውሳኔውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው ገልፆ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቋል፡፡
የቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተፈጠረው ስህተት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ፥ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ለሚካሄደው ጨዋታ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጨዋታውም አሸንፈን ወደ አለም ዋንጫ እንደምንሳተፍ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል ፡፡
በፊፋ ህግ መሰረት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋችን ማሰለፍ በጨዋታው የተገኘውን ነጥብ እና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስጥል ይታወቃል፡፡
የ‹‹ደሃው›› አቶ መለስ 3 ቢሊዮን ዶላር የት ነው?
ቴዎድሮስ ባልቻ
አቶ መለስ ዜናዊ የእረፍታቸው ዜና ከተነገረ በኋላ በህይወት ሳሉ የሌላቸውን ባህርይ ሳይቀር በመግለፅ ደጋፊዎቻቸው ጣዖት ማምለክ እስኪመስል ድረስ እንዲመለኩ ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን አቶ መለስ የኢህአዴግ ደጋፊዎች የሚያወሩላቸውን ያህል ግለሰብ ስላለመሆናቸው የማይረሱ በርካታ ስራዎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን አንዳችም ጥሩ ስራ የላቸውም ማለት ሳይሆን በንፅፅር ሲቀርብ ግን ጥሩ መሪ ነበሩ ማለት በገለልተኛ አካላት ሰፊ ጥናት መደረግ ያስፈልገዋል፡፡
አመራሮቹማ ከቤተ መንግስት እስከ ገጠር ቀበሌ የእሳቸውን ሞት ተከትሎ ምስላቸውን የያዙ ፖስተሮች መለጠፋቸው ሰውየውን ‹‹ቅዱስ›› ለማስመሰል ከመሞከር ባለፈ ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ያሳብቃል፡፡ ይህንን ለማርከስም ሆነ ህዝቡ ስለ እሳቸው ትክክለኛ ማንነት እንዲያውቅ አማራጭ የሀገር ውስጥ ነፃ ሚዲያ ያለመኖር በመጋረጃ ውስጥ ያሉት መለስ ተዘንግተዋል፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ ስለሳቸው ትክክለኛ ማንነት የተወሰኑ ተግባራቸው የአደባባይ ምስጢር ቢሆንም እሳቸው ከሚያደንቋቸው የውጭ ሚዲያ መዳሰሱ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በቅርቡ የዓለም መሪዎችንና ባለሃብቶችን ሃብትና የግል ታሪክ በማስነበብ የሚታወቀው ድህረ ገፅ ስለእሳቸው በአጭሩ ያስቀመጠውን እንመልከት፡፡ የመረጃው መረብ ሰውዬውን ከልደት ዘመን እስከሞታቸው ከመግለፁ በተጨማሪ አንድ አስደንጋጭ (ለኢህኢዴግዎች) መረጃም አክሎበታል፡፡ ይህም ያላቸውን የሃብት መጠን ከዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከከል ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትርና የታወቁ ባለሃብት ከሆኑት ሲልቪዮ በርሎስኮኒ በመቀጠል በ3 ቢሊዮን ደላር (56 ቢሊዮን ብር ገደማ) 2ኛ ደረጃን እንደያዙ www. therichest.org በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም http://www.therichest.org/celebnetworth/politician/minister/meles-zenawi-net-worth/ መጎብኘት ይቻላል፡፡
በተለይ ነገሩን አስደንጋጭና አሳፋሪ የሚያደርገው በህይወት ያሉት ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በባህርዳሩ የኢህአዴግ ጉባዔ ሳይጠየቁ የአቶ መለስን ድህነት ሲናገሩ ነበርና፡፡ ያኔ ባለቤታቸው ከመንግስት መደበኛ 6 ሺህ ብር ደመወዛቸው ላይ ተቆራርጦ 4 ሺህ ብር ያህል እንደሚደርሳቸውና በዚህም ይተዳደሩ እንደነበር መግለጣቸው አይዘነጋም፡፡ በርግጥ ያኔ ባለቤታቸው የተናገሩትን ህዝቡ ተቀብሏቸዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም 21 ዓመታትን ሙሉ ያለመላከ ሞት ከቤተመንግስት አልወጣም ብለው የመሸጉትን የህዝብና የሀገርና የወገን ፍቅር ኖሯቸው እንዳልነበረ እንቅስቃሴያቸው ያሳብቅ ነበርና፡፡
‹‹ደሃው ›› አቶ መለስ
ዛሬ እንደጣዖት ፎቶአቸውን በየቦታው ተለጥፎ የምናገኛቸው አቶ መለስ ዝናዊ ምናልባት በመሪ አስተሳሰብ ካልሆነ በቀር በገንዘብ በኩል ደሃ ነበሩ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ያለባህርበር ከማስቀረት አልፈው በታሪክ የኢትዮጵያ እንደሆነ የሚታወቀውን አሰብ ወደብንና አካባቢውን ትውልዱ ያንን እንዳያስብ በማድረግ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስንቶች የሞቱለትን የሀገሪቱን ሰንደቅዓላማ ‹‹ጨርቅ ነው›› ብለው አራክሰዋል፡፡ የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው ሲሉም ከመናገር ያለፈ የአስተሳሰብ ድህነት የለም፡፡
እሳቸውም በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው እንደድሮ (ጫካ ሳሉ) እንደማይርባቸውና የቆሸሸ እንደማይለብሱ ከማስታወስ ውጭ በገንዘብ በኩል ያኔ ደሃ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ እውነታው ግን ያ ስለመሆኑ ህዝቡ መርምሮ እንዲያውቅ ዕድል አልሰጡትም፡፡ ዛሬ ግን ተከታዮቻቸው ከእራሳቸው አልፈው መላው ህዝብ ንፁህና ቅዱስ አድርጐ እንዲመለከታቸው በየመድረኩ የሚነገረው አሰልቺ ወሬ ገመናቸውን ሊደብቅ እንደማይችል የተረዱት አይመስልም፡፡
በተለይ በገንዘብ ደረጃ ምንም ያልነበራቸውና ይሄንንም ራሳቸው የተናገሩ ቢሆንም ስለ እሳቸው ዝርዝር የህይወት ታሪክ በግልፅ በማስቀመጥ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ መሆናቸውን ግን በህይወታቸውም ሆነ በሞታቸው አላስተባበሉም፡፡ ስለዚህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በባዶ እጃቸው ጫካ ገብተው የወጡት አቶ መለስ ነግደው ሳያተርፉ ቢሊየነር ባለጠጋ የሆኑት ከህዝብ ሃብት ዘርፈው ካልሆነ ከየትም ሊያመጡ እንደማይችሉ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሰውዬው ይወራ እንደነበረው ዓይነት እንዳልሆኑ ውሎ ሲያድር እየጠራ ነው፡፡
የግል ማኀደራቸው በአጭሩ
አቶ መለስ (ለገሰ) ዜናዊ በወርሃ ግንቦት 1947 ዓ.ም. በአድዋ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአድዋ ንግስት ሳባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲከታተሉ የሁለተኛ ደረጃን አዲስ አበባ በሚገኘው ጀነራል ዊንጌት ተከታትለው በመጨረስ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በቀድሞ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በሁለተኛው ዓመት አቋርጠው ወደጫካ ከመግባታቸው ውጭ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ማጠናቀቃቸውን የሚገልፅ የምስክር ወረቀት የላቸውም፡፡
ነገር ግን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በምን ዘርፍ፣ ከየትና መቼ እንዳገኙ የሚያሳይ ማስረጃ እስካሁን ባይገለፅም ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር ማስተርስ ዲግሪ ማግኘታቸው ተገልጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከሚገኘው ኤራስመስ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት ከመሆን ውጭ በትምህርት ሌላ ደረጃ እንደሌላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አቶ መለስ ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ጋብቻ በመመስረት ሰናይ፣ ሰመሃል እና ማርዳ የሚባሉ የሶስት ልጆች አባት እንደሆኑም በመካነ ድሩ የመረጃ መረብ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በመጨረሻም ለ21 ዓመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ 57 ዓመታቸው ነሐሴ 14 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም (እንደ መንግስት ገለፃ) መሞታቸውን፤ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ እንደነበሩ ደግሞ http://www.therichest.org›› የተሰኘው ድህረ- ገጽ በግልፅ አስፍሯል፡፡
ሌላው ደቀመዝሙሩ ከመምህሩ እንደሚማር ሁሉ የታችኞቹ ሙሰኞች መሰረት የላይኞቹ ባለስልጣናት ልምድና ተሞክሮ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች›› እንዲሉ የታችኞቹ ሙሰኞች (ከቀበሌ እስከየ መስሪያ ቤቶች ባለስልጣን) ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስን እና መሰሎቻቸውን ፈለግ ተከትለው ባይተማመኑ እነ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በቤታቸው የዶላርና የብር ክምችት ባልተገኘ ነበር፡፡
ስለዚህ በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ተግባር በእጅጉ ለመቀነስ ከተፈለገ ወኔውና ድፍረቱ ካላቸው አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝና የፌደራሉ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ በ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ እንደሆኑ ከተነገረላቸው ከቀድሞው የቤተመንግስት የስልጣን ባህታዊ ከሆኑት ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን እስከ ሚኒስትሮችና የጦር ጀነራሎች መዝለቁ የግድ ይላል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው አቶ መለስ አላቸው ከተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር ውጭ የሃብት ምንጫቸው ያልታወቁ ጊዜ አመጣሽ ከበርቴዎችን መዳሰሱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ በዚህም አለ የተባለው ሃበት እውነትነት መርምሮ ለህዝብ የማሳወቅም ግዴታ አለበት፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሀገሪቱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት በወረቀት በህገመንግስቱ ከማስፈር ውጭ በተግባር የሚረጋገጥ ከሆነ በርካታ የሙስና ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ የኮሚሽኑንና የሌሎች የፍትህ ተቋማትን ስራ ያቀላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከመካላከያ ሚኒስቴር፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች)፣ የከተማ መስተዳድሮች ውስጥን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉ የብልሹ አሰራሮች ምን ያህል ለሙስና እንደተጋለጡም የፌዴራሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት የመረጃ ዘገባዎችን /ሪፖርቶቹን / እንደግብዓት መጠቀም አስፈላጊ ቢሆንም እስካሁን በተግባር የታየ እርምጃ ግን የለም አለበለዚያ እንደ ዳዊት ‹‹ሙስና›› እያሉ መደጋገሙና ትናንሾቹ ላይ ብቻ ጃስ ማለት የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ከማስቀየር ባለፈ ለሀገርና ለህዝብ ሃብት ተቆርቋሪነትን አያሳይም፡፡
እሳቸውስ ሞቱ 3 ቢሊዮን ዶላሩስ?
በተለይ ወደ ፖለቲካው የሀገር አስተዳደርነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የሳይንሱን ትምህርት በርቀት ሳይሆን በመደበኛ ተከታትለው የህግ ምሁሩና ድምፃዊ የነበሩት የኤሲ ሚላኑ እግርኳስ ክለብ ባለቤት ከሆኑት ከ76 ዓመቱ የጣሊያኑ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሎስኮኒ የ6 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ቀጥለው ከጫካ በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን የወጡት አቶ መለስ በ3 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛነትን ይዘዋል፡፡ በመቀጠልም የሊባኖሱ የሐርቫርድና የቤሩት ዪኒቨርስቲ ምሩቅና ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተለያዩ ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት የ57 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ አዝሚ ሚካቲ በ 3 ቢሊዮን ዶላር 3ኛነትን ይዘው ይከተላሉ፡፡
አቶ መለስ ግን ከጫካ ወደ ፖለቲካ ስልጣን ከመውጣት ውጭ የተጠቀሰው ሃብታቸው ከየት መጣ? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ህዝብ ከሚያውቀው እውነታ ውጭ እሳቸውም ምንም እንደሌላቸው ከመሞታቸው በፊት ተናግረዋልና፡፡ በጣም የሚገርመው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ዊሊያም ዶናልድ ካሜሩን እንኳ ያላቸው ሃብት ሲታይ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ እንደሆነ እና የዚህም ሃብታቸው ምንጭ ፖለቲካ እንደሆነ ድህረ-ገፁ ሲጠቁም የአቶ መለስ ዜናዊ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ምንጭም ፖለቲካ እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚህም ሟቹ አቶ መለስ ይህን ያህል ሃብት በፖለቲካ ስራ ባለቤት ከሆኑ የሌሎቹ ባለስልጣናት ቢጣራ ስንት ይሆን የሚል ጥያቄን ከማስነሳቱ በተጨማሪ ሀገሪቷ ምን ቀራት ያሰኛል፡፡
በርግጥ የአቶ መለስንና ባለቤታቸውን ከፍተኛ ባለጠግነትን (ቢሊየነርነትን) በተመለከተ ምስጢራዊ መረጃዎችን በመልቀቅ የሚታወቀው ‹‹wikleaks›› የተሰኘው ድህረ- ገፅ ‹‹Ethiopian Super rich persons›› ሲል የተለያዩ የቅርብ ወዳጆቻቸውን የቃለመጠይቅ ምስክርነት ማስረጃ ሳይቀር አስደግፎ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ‹‹therichest›› ድህረ – ገፅ ያላቸውን የገንዘብ መጠን 3 ቢሊዮን ዶላር ብሎ ባይገልፅም ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለጠጋ መሆናቸውን አልሸሸገም ነበር፡፡
በአሁኑ ሰዓት አቶ መለስ ሞተዋል፤ አላቸው የባለው 3 ቢሊዮን ዶላርስ የት ገባ? ምን እየሰራስ ነው? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ቢሆንም እዚህ ላይ ቀን ከሌት ስለመለስ ሙገሳና አድናቆት አውርተው የማይጠግቡት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያ ደሳለኝ ከባድ የቤት ስራና ፈተና ነው፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ የፌደራሉ የሥነ – ምግባርና ፀረ – ሙስና ኮሚሽን ቁርጠኝነትንና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የአቶ መለስ አላቸው የተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር የት እንዳለና ምን እየሰራ እንደሆነ ከነምንጩ ከመረጃ መረቦቹም ሆነ በራሳቸው ዘዴ አጣርተው የመግለፅ ትልቅ ፈተና ይጠበቅባቸዋል፡፡
የገንዘቡ መገኘት ከተረጋገጠ በኋላም ገንዘቡ ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ ተነጥቆ የተዘረፈ ስለመሆኑ ማንም ሊጠራጠር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከራስ በላይ ምስክር የለምና ሁለቱም የህወሐት ኢህአዴግ እና የሀገሪቱ የስልጣን ቁንጮዎች በገንዘብ አቅም ድሃ ስለመሆናቸው ተናግረዋልና፡፡ ስለዚህ እነኛ ታማኝ የመረጃ ምንጮች የገፁት በተለይ ‹‹therichest›› ያሰፈረው 57 ቢሊዮን ብር (3 ቢሊዮን ዳላር ) ወደ ተዘረፈው ህዝብ ተመልሶ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል፡፡
‹‹ ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው››
አበው ሲተርቱ ‹‹ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው ›› ይላሉ፡፡ ዓሳ ከምግቦች ሁሉ የተሸለና ሁሉንም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ተወዳጅ ምግብ ቢሆንም ለምግብነት ከመሰናዳቱ በፊት ከመኖሪያው ውሃ ውስጥ እንደወጣ የማይወደድ ሽታ አለው፡፡ የዚህ ‹‹መጥፎ ሽታ›› መነሻው ደግሞ ጭንቅላቱ እንጂ ሌላው አካሉ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ በዚህም ዓሳ ከውሃ ውስጥ ከወጣ በኋላ ያለው መጥፎ ጠረን ጭንቅላቱ ስለሆነ ተቆርጦ መጣል እንዳለበትና ያኔም ሌላው አካሉ ከመጥፎ ሽታ እንደሚፀዳ አመላካች ንግግር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስላለው ቅጥ ያጣ የሙስና ተግባርም ሆነ ብልሹ አሰራር መነሻው ገዥው ኢህአዴግና ቁንጮዎቹ እንደሆኑ የሰሞኑ መረጃ በራሱ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ከሚኒስትር አቶ መላኩ ፈንታና ረዳታቸው የሙስና ተግባር መጠርጠር በተጨማሪ በወ/ሮ አዜብ መስፍን ‹‹ድሃ›› ስለመሆናቸው የተመሰከረላቸው ግን በዓለም 2ኛው ባለጠጋ ጠቅላይ ሚኒስትር(በ3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር) እንደሆኑ የተነገረላቸው ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ አለ የተባለው ሃብት ምንነት ካልተጣራና ካልተመለሰ የመንደር ሌቦችን ብቻ ማሳደድ ሙስናን ሊገታ አይችልም፡፡
ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት(ሰኔ በ2005ዓ.ም.)
የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ንብረት እያወዛገበ ነው
1ሚ. ብር አበድሬአቸዋለሁ የሚል ድርጅት ክስ ሊመሰርት ነው የአዋሣው ቤታቸው ተሸጦ ስም መዛወሩ እያነጋገረ ነው
እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ንብረት እያወዛገበ ነው፡፡ አርቲስቱ በሕይወት ሳሉ አንድ ሚሊዮን ብር አበድሬአቸዋለሁ የሚል ድርጅት ለክስ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ በህይወት ሳሉ የስዕል ሥራዎቻቸውን፣ ቪላ አልፋንና ሙሉ ንብረታቸውን ለመንግስት ማውረሳቸውን ተከትሎ፣ መንግስት ንብረቱን ለመረከብ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የእኚሁን ታላቅ አርቲስት ንብረት ለማጣራትና ለመመዝገብም ከፍርድ ቤት፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከሙያ ባልደረቦች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምዝገባና ቆጠራ ቢጀመርም ፍፃሜ ሣያገኝ ተቋርጧል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በህይወት ሣሉ የአክሲዮን ባለ መብት ለመሆን አንድ ሚሊዮን ብር ወስደዋል በሚል የአርቲስቱን ስዕሎች ይሸጥ በነበረ አንድ የማስታወቂያ ድርጅት ክስ ሊመሰረት መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እንዲያገኝ ለኮልፌ ምድብ ችሎት ተመርቶ እየታየ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ለጊዜው የንብረት ምዝገባና ቆጠራው መቋረጡን ገልፀዋል፡፡ በአዋሣ ከተማ የሚገኘውና በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስም የተመዘገበው ቤት በቀድሞ ባለቤታቸው አማካኝነት መሸጡን የጠቆሙት ምንጮች፤ የቤቱ ስም የተዛወረበት አሠራር ሕጋዊነት አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስም በለንደንና በስኮትላንድ ባንኮች ያለ ገንዘብ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በተለያዩ አገራት ያሉ ስዕሎችና ንብረቶችን ለማስመለስም እየተሞከረ ነው ተብሏል፡፡ የአርቲስቱ ንብረት ካለባቸው አገራት መካከልም ንብረቱንና ገንዘባቸውን ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑና በመመለስ ሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቪላ አልፋ፤ በኮሚቴዎቹ ሲከፈት በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ በካዝናቸው ውስጥ መገኘቱንና ይህም በንብረት ዝርዝር ላይ ተመዝግቦ መያዙን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በፍርድ ቤት ጉዳይ የተቋረጠው የሎሬት አፈወርቅ ንብረት ቆጠራና ርክክብ መዘግየት በንብረቱ ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የጠቆሙት ምንጮች፤ እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው
ስዕሎቻቸውና የአርቲስቱ የመኖሪያ ቤትና የስዕል ስቱዲዮ የሆነው ቪላ አልፋም የመበላሸት አደጋ አንዣቦበታል ብለዋል፡፡ የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የቀብር ሥፍራ ምንም አይነት የማስታወሻ ሐውልት ሣይሰራበት መቅረቱን የጠቀሱት ምንጮች፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀብራቸው ሥፍራ ሊጠፋ ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
Written by መታሰቢያ ካሣዬ- http://www.addisadmassnews.com/
በአዲስ አበባ ከ 8 ዓመታት በኋላ ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ
ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን 2005ዓ.ም. በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ከ1997ዓ.ም. ምርጫ 8 ዓመት በኋላ ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ፡፡ ፓርቲው በዋነናነት አንግቦ የተነሳው 4 ጥያቄዎችን ሲሆን እነኚህም ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣታቸው ብቻ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲፈቱ፣ የኃይማኖት ነፃነት ይከበር በሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ የታሰሩ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች እንዲፈቱ፣ በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ከሚኖሩበት ቦታ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ዜጎች ካሳ ተከፍሏቸው በነበሩበት ቀዬ እንዲኖሩና የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለህግ እንዲቀርቡ ፣ ኢህአዴግ በሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ሙስና እና ስራ አጥነት እንዲሁም ብልሹ አሰራሮች በአስቸኳይ እንዲታረሙ የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ሰላማዊ ሰልፉም ከፓርቲው ጽህፈት ቤት ግንፍሌ መነሻ በማድረግ አራት ኪሎ የድል ሐውልት፣ ፒያሳ ከዚያም ቸርችል ጎዳና በማድረግ ወደ መዳረሻው ዋናው ፖስታ ቤት ፊትለፊት በሚገኘው ኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ በሺህዎች የሚቀጠሩ ሰዎች በተገኙበት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡ በሰልፉም ላይ በርካታ መፈክሮች የቀረቡ ሲሆን ከነኚህም መካከል ያለ ነፃ ፕሬስ ዴሞክራሲ የለም፣ ኢቴቪ ሌባ፣ ኢህአዴግ ሌባ፣አንለያይም፣ አንድ ነን(ሙስሊምና ክርስቲያን)፣ አሸባሪ አይደለንም፣ የታሰሩ ይፈቱ፣ ህገመንግስቱን የሚፃረሩ አፋኝ አዋጆች በአስቸኳይ ይሰረዙ፣…የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ በሰልፉ ላይም በርካታ ሙስሊሞችን ጨምሮ የሰማያዊ፣ የአንድነት፣ የመኢአድና የመደኢዴፓ እንዲሁም የመድረክ ወጣቶች በብዛት መገኘታቸውን ለማየት ተችሏል፡፡ በመጨረሻም በሰልፉ መዳረሻ በነበረው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ አቶ አለሙ ጎቤቦ(የጋዜጠኛ ርዕዮት አባት) እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሰልፈኞቹ በሰላማዊና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በማካሄዳቸው አመስግነው በተለይ ኢንጅነር ይልቃል በንግስት አራቱንም ጥያቄ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ካልመለሰ በድጋሚ ለተቃውሞ ሰልፍ እንደሚወጡ በመግለፅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ በተሳካ ሁኔታ ከቀኑ በ 8፡00 ሰዓት ተጠናቋል፡፡
በሰልፉ ወቅትምየታሰሩ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት አለሙ፤ ከፖለቲከኞች አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሌሊሳ በተጨማሪ ከቢኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ የአማርኛ ተናገሪ ኢትዮጵያዊያን ፎቶ በትልቁ ተዘጋጅቶ ይታይ ነበር፡፡