Monthly Archives: May, 2013

“ሙሰኞቹ” የተያዙት በሟቹ አቶ መለስ ጥቆማ ከሆነ፤ ነገስ?

አየነው በጊዜው

(ከአዲስ አበባ)

 

Melaku

 

የኢትጵያ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሚኒስትርነት ማዕረግ የትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ መላኩ ፈንታንና ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስን፣ የኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ እና የኬኬ ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደን ጨምሮ 12 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡ እነኚህ ሰዎች ደግሞ ሊያዙ የቻሉት ከዛሬ 3 ዓመት በፊት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጥቆማና ትዕዛዝ መሰረት መሆኑን ኮሚሽነሩ እግረ መንገዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነኚህ ተጠርጣሪዎችም ወዲያው ለፍርድ እንዲቀርቡ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ኮሚሽኑም እንደትልቅ ጀብዱ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ግንቦት 6 ቀን 2005ዓ.ም. ለፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርብ የተያዙትን ተጠርጣሪዎች እንደ ትልቅ ስኬታማ ናሙና ስራ ሲጠቅስ ነበር፡፡ በርግጥ የሃገር ሃብት የሚመዘብሩ መያዛቸው ባይከፋም እስከዛሬ ትላልቅ ባለስልጣናት ላይ ለምን ዝምታን መርጦ ዛሬ እንደ ድል ይቆጥረዋል? የሚል ጥያቄን ማጫሩ አይቀሬ ነው፡፡

እንደኮሚሽኑ ገለፃ ከሆነ በአሁን ወቅት በቁጥጥር ስር ያሉት የመንግስት ሹመኞችና ነጋዴዎች ከመታሰራቸው በፊት ለሶስት ዓመታት ክትተል እየተደረገባቸው እንደነበርና ተግባራዊ ክትትሉም ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አሳሳቢነት ዛሬ ላይ መድረሳቸውን ኮሚሽነሩ በይፋ ተናግረዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ዛሬ አቶ መላኩን ጨምሮ የመንግስት ሹመኞችን ብልሹ አሰራር በማጋለጣቸው ጭለማ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አቶ መላኩና ምክትላቸው ከልማታዊ ባለሃብቶቹ ጋር የዚህ ሰለባ ሆነዋል፡፡

እነኚህ ተጠርጣሪ ሙሰኞች ትናንት ሲወደሱና ሲመሰገኑ ከርመው ዛሬ ለረጅም ጊዜ ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር መግለፁ ከበስተጀርባ ሌላ ነገር እንዳለ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም እንደ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ከሆነ እስከዛሬ ንብረትነቱ በውል የማን እንደሆነ የማይታወቀውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው ኤፈርት ኦዲት ተደርጎ ባለማወቁ ሙስና ከተባለ የድርጅቱ ባለቤቶችና አንቀሳቃሾች መቅደም ነበረባቸው ሲሉ ግምታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በተለይ የሃብታቸው ምንጭ ምን እንደሆነ ያልታወቁት አብዛኞቹ አዳዲሶቹ የአዲስ አበባ ህንፃዎች ከባለስልጣና ጋር በመሞዳሞድ በሙስና የተሰሩ ሊሆኑ ስለሚችሉ እስካሁን በፌደራሉ ስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምንም የተደረገ አመላካች እርምጃ ባለመታየቱ አሁን በባለሃብቶቹና በባለስልጣናቱ ላይ የተወሰደው እርምጃ ከሙስና ይልቅ የፖለቲካ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል አመላካች እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ለዚህም ድምዳሜ መሰረቱ የሙስናው ክትትል ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሟቹ አቶ መለስ ዜናዊና በስፋት በዚሁ ተግባር ከሚታሙት ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን መጀመር እንደነበረበት በመጠቆም፡፡

በተለይ ሌላው አስገራሚው ነገር ኮሚሽኑ አሁን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተጠርጣሪዎች ከዓመታት በፊት በሟቹ አቶ መለስ ጥቆማ መሆኑ እስከ ዛሬስ ለምን ቆየ; አሁንም ቢሆን ኮሚሽኑ ዛሬ መድፈሩን ያሳየን በራሱ ተነሳሽነትና ጥረት ሳይሆን በፖለቲካ ስልጣን የበላዩ በመጠቆሙ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ኮሚሽኑ በነፃነት ስራውን የመስራት አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው አመላካች ከመሆኑም በተጨማሪ ለዛሬው ድል መሳካት ትልቅ ሚና የተጫወተው እሱ ሳይሆን ሟቹ ግለሰብ መሆናቸውን በተደጋጋሚ መግለፁ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ምንም እንኳ 10 ዓመት ቢሆነውም ሀገሪቱ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ 11.2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር(ከ207 ቢሊዮን ብር በላይ) የተዘረፈች መሆኗንና በተለይ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ዓመት አንስቶ ደግሞ ወደ 8.2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር(ወደ 152 ሚሊዮን ብር ገደማ) መዘረፉን መረጃዎች ቢጠቁሙም ኮሚሽኑ የመንደር ሌቦችን ብቻ እያሰሰ የፖሊስን ስራ ይሰራ እንደነበር የሚያወሱ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ማዳን የነበረባትን ዝርፊያና የአባሕ ግድን የሚያህሉ ከሁለት በላይ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ሊገነባ የሚችል የሀገሪቱ ሃብት ሲዘረፍ በተለያ የመረጃ አውታሮች ቢነገርም ኮሚሽኑ እስካሁን ያለው ነገር ባለመኖሩ እራሱ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከሙስና ፀድቶ ነው ወይ የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን እንኳ ብንተው በሀገር ውስጥ ምን ያህል ህገወጥ ስራ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደሚፈፀምና ለሙስና የተጋለጡ በርካታ ተቋማትን ኦዲት በማድረግ ይፋ የሚያደርገው የፌደራሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት በራሱ በቂ ማስረጃ ነበር፡፡ ነገር ግን ፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ በቅርቡ እንደገለፀው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሳቢነትና ጥቆማ ካልሆነ በይፋ ለሙስና የተጋለጡ ጸቋማት ላይ የሚያደርገው ክትትልና ምርመራ እንደማይሰራም በተዘዋዋሪ መንገድ መግለፁ ከነ አቶ መላኩ ፈንታ እስር ጀርባ የፖለቲካ ጉዳይ እንዳለበት ቢያመላክት ስህተት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሲባል ግን ተጠርጣሪዎቹ ንፁኃን ናቸው፣ ሙስና አይፈፅሙም ማለት ሳይሆን ኮኮሚሽኑ እስካሁን የሚጠበቅበትን ምን ያህል ሰራ ብንል እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ጉዳዩ የሙስና ከሆነ አንድም የኢትዮጵያ ባለስልጣን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከሙስና ተግባር ሊነፁ እንደማይችሉ፤ ይህም የስርዓቱ መለያ ባህርይ በመሆኑ የፖለቲካ ልዩነት ሲያንፀባርቁ ብቻ ካርታ ለመምዘዝና የፖለቲካ ባርያ ለማድረግ በማሰብ ሙስና እንዲፈፅሙ እንደሚመቻች አንዳንድ የቀድሞ ታጋዮች ዛሬም ድረስ ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም በ1993 ዓ.ም. በህወሓት መካከል የነበረውን ክፍፍል መሰረት በማድረግ ከነ ወንድሞቻቸው እንዲታሰሩ የሙስና ካርታ የተመዘዘባቸው የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩትን አቶ ስየ አብርሃን እስር የሚያስታውሱ አልታጡም፡፡

በርግጥ የሙስና ተግባር ለሀገርና ለህዝብ ጠንቅ መሆኑ ቢታወቅ ኖሮ ህዝቡ ዛሬ የስቃይ ኑሮ ገፈት ቀማሽ ባልሆነ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገዥው ኢህአዴግ አባላቱን ሲመለምል ቀድሞውንም ቢሆን ርዕዮተ ዓለሙን ሸጦና አሳምኖ ሳይሆን በፍቅረ ንዋይ የነደዱትን በማማለል እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በሀገራችን የተማሩ አብዛኞቹ ወጣቶች በሙያቸው ሰርተው ተዓምር ለመፍጠር ከመሞከር ይልቅ የኢህአዴግ አባል በመሆን ትልቅ ስልጣን ላይ መውጣትን የሚሹት፡፡ የዚህም ምስጢር ያሉት የመንግስት ተቋማት በስርዓቱ ቸልተኝነት ለሙስና በመጋለጣቸው ነው፡፡

በአጠቃላይ ዛሬ የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙሰኞች ሲል የያዛውን ሰዎች በአቶመለስ ጥቆማ መሆኑን ከነገረን ነገ አቶ ኃይለማርያም ካልጠቆሙ ስራውን ሊያቆም ነው ማለት ነው ወይስ እንደለመደው ትናንሽ ዓሳዎችን ጃስ በማለት ጊዜውን ሊያባክን ነው; ይህን ወደፊት አብረን የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፊት ለፊታቸው ምንም ያህል ሙስና በባልስልጣኖቹ ቢፈፀም እርምጃ እንዲወሰድባቸው የመጠቆምና የማዘዝ ድፍረቱ ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም፤ አቶ ኃ/ማርያም በራሳቸው አዲስ የአመራር ዕቅድ ከመከተል ይልቅ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ሌጋሲ ለማስጠበቅ እየተጉ ነውና፡፡

ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት(ግንቦት 2005ዓ.ም.)

የመከነው የአፍሪካ ራዕይ

 ብስራት ወልደሚካኤልau

ልክ የዛሬ 5ዐ ዓመት እ.አ.አ. በ1963 ዓ.ም የአፍሪካ ጥቁሮች ከባርነት ቅኝ ግዛት ለመውጣት የተወሰኑ መሪዎቿ ሽር ጉድ እያሉ ነበር፡፡ ሽርጉዱም የአፍሪካ ምድር በአውሮፓውያን ጨካኝ አገዛዝ መዳፍ ውስጥ የወደቁትን ሀገሮች ነፃ ለማውጣት በጥቂት ጥቁር መሪዎች ምክክር ሊካሄድ ነው፡፡

ይሄን የሰሙት ገዥዎች በተለይም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ፖርቹጋልና፣ ጣሊያን ይበልጥ በጥቁሮች ላይ በደል መፈፀምን ተያያዙት፡፡ ይህን የተመለከቱት የአፍሪካ የአብራክ ልጆች በቁጭት በመንገብገብ ወገኖቻቸውን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ መዘየድ ጀመሩ፡፡ ያኔ ግን የተለያዩ ሀገሮች በተለይም ጋና፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካውያነ በየሀገሮቻቸው የተናጥል ትግል ያደርጉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትግሉ ፈቀቅ አላለም፡፡ ምክንያቱም ብቻቸውን ነበሩና፡፡

በወቅቱ ፈረንሳይ የሰሜን አፍሪካ ሀገሮችን በተለይም ግብፅ፣ ቱኒዚያ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮን እንዲሁም በምዕራብ እንደ ማሊና ኮትዲቫርን በምስራቅ ጅቡቲን ይዛ ነበር፡፡ እንግሊዝ በበኩሏ በምስራቅ አፍሪካ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሯንዳ፣ ክፊል ሱማሊያ በምዕራብ ናይጄሪያ፣ ጋና በደቡብ የቀድሞ ሮዴዥያ (ዙምባቤና ዛምቢያ)፣ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ ሀገሮችን በቅኝ ግዛት ይዛ ነበር፡፡ ፖርቹጋል ደግሞ በደቡብ ምዕራብ አንጐላን ስትቆጣጠር ጣሊያንም እንዳቅሟ ሊቢያንና ምስራቅ ሶማሊያን ተቆጣጥራ ነበር፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ለናሙና እንጂ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት የወደቁ ሌሎችም በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ነበሩ፡፡

          ነፃ ሀገር

በተፈጥሮ የበለፀገችዋ እማማ አፍሪካ ምንም እንኳ በልጆቿ ስቃይ ማቅ ብትለብስም በወቅቱ እንደሀገር ሉዓላዊነት ያላቸው ሁለት ሀገሮች ነበሯት፡፡ እነኚህም በስተምስራቅ ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ እና በምዕራብ የአልማዝ ምድር የሆነችው ላይቤሪያ ናቸው፡፡ በርግጥ ላይቤሪያ እንደሀገር ብትታይም ከነ ሰንደቅዓላማዋ ከአሜሪካ ቁጥጥር ስር ውጭ ነበረች ማለት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እንደ ሀገር ከመመስረቷ በፊት የማንም ያልነበረች በኋላ ግን አሜሪካ በባርነት ከአፍሪካ ተወስደው በሀገሯ እየተባዙ የመጡትን የጥቁሮች ቁጥር ስጋት ላይ እንዳይጥላት በማሰብ ወደዛሬዋ ላይቤሪያ አብዛኞቹን ጭና በማራገፍ የዛሬዎቹ ላይበሪያውያን መኖሪያ አድርጋለች፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1888 እና በ1928 ዓ.ም በጣሊያን የቅኝ ግዛት ሙከራ ቢደረግም በጥቁር አናብስት ትግል ሳይሳካ በመቅረቱ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ነፃ ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ መሪነት የጥቁር አናብስት በጣሊያን ላይ በተቀዳጁት ድል ለሌሎችም ፋና ወጊ በመሆን የነፃነት ትግል እንዲቀጣጠል ፈር ቀዷል፡፡

         የነፃነት ናፍቆት ህብር

 

አፍሪካውያን የነፃነት ናፍቆት ቢያንገበግባቸውም ትግሉ በተናጥል ስለሆነ በተፈለገው ፍጥነት ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ለዚህም የናይጄሪያውን ኢቦ ኢቢቦ፣ የጋናው አሻንቲ እና የደቡብ አፍሪካውን የነ ባሱቶ ዙሉ ትግልን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ትግሉ እንዲሰምር በገዥዎች ሀገር ይኖሩ የነበሩ የጥቁሮች የአብራክ ክፋይ እነ ኩዋሜ ኑኩሩማ፣ ጆሞ ኬንያታ የመሳሰሉት በጋራ መታገሉ የተሻለ እንደሆነ በማሰብ በነፃይቱ የጥቁር አናብስት ምድር ንጉስ ከሆኑት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ስላሴ ጋር መከሩ፡፡

ምክክራቸውንም በማጧጧፍ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ገፉበት፡፡ በዚህም ጥቁሮች ሲነቃቁ ቅኝ ገዥ አውሮፓውያን ግን ድንጋጤ ወሯቸው ነበር፡፡ በተቃራኒው ጥቁሮች ደግሞ ከፍተኛ የአሸናፊነት ወኔን ተላብሰው ለልጆቻቸው ከጭቆና ነፃ የሆነ ምድር ለማውረሰና ለራሳቸውም ነፃነት ተግተው ተፋለሙ፡፡

ይሄን የተረዱት የትግሉ ውጤት ናፋቂዎች እነ አፄ ኃ/ስላሴና ኩዋሜ ኑኩርማን ጨምሮ ሌሎች የወቅቱ የአፍሪካ የቁርጥ ቀን ልጆች አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ይላቀቁ ዘንድ አፍሪካውያን በአንድ ስም ተጠርተው የሚጠለሉበትን ተቋም መመስረት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ የዚህም ተቋም ዋነኛ ዓላማ አፍሪካውያንን ከቅኝ ግዛት ነፃ ማውጣት ነበር፡፡

        የአፍሪካ አንድነት ድርጅት

አፍሪካውያንን የነፃነት ድል ለማቀዳጀት ሲባል የዛሬ 5ዐ ዓመት እ.አ.አ ግንቦት 1963 ዓ.ም በነፃይቱ ታሪካዊት ሀገር አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ፡፡ ድርጅቱ ሲመሰረትም ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢትዮጵያው ንጉስ አጼ ኃ/ስላሴ ነበሩ፡፡

በወቅቱ ተቋሙ ምንም እንኳ ቢመሰረትም ወዲያው የራሱን ቢሮና ለምክክር የሚሆን አዳራሽ መገንባት የማይቻል ቢሆንም ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃ/ስላሴ መንግስታቸውና መላው የሀገራቸው ህዝብ አፍሪካውያን ወገኖቹ ነፃ እንዲወጡ እንደሚሻ ተናገሩ፡፡ በዚህም ሳያበቁ በመንግስታቸውና በህዝባቸው ስም ዛሬ የህብረቱ አሮጌው ህንፃ ለፖሊስ ጽህፈት ቤት ተብሎ የተሰራውን ከነሙሉ ግቢው በነፃ ለድርጅቱ አስረከቡ፡፡ ድርጅቱም በነፃይቱ ምድር ያለማንም ከልካይ በነፃነት በመምከር የአፍሪካውያንን መፃኢ ተስፋ ብሩህ ለማድረግ ተግቶ ይሰራ ጀመር፡፡

በድርጅቱ ያላሰለሰ ጥረትም ጋና ቀድማ ከእንግሊዞች ቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ ሌሎችም ተከታትለው ነፃ ወጥተዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ግን ከአሰቃቂው የአፓርታይድ ዘረኝነት አገዛዝ ነፃ የወጣችው ዘግይታ ነበር፡፡

ያኔ በአዲስ አበባ የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋነኛ ዓላማ አፍሪካውያንን ከባርነት ቅኝ አገዛዝ ነፃ ማውጣት በተጨማሪ የአህጉሪቱ ሃብት በአውሮፓውያን ተወስደው ዜጐቿ እንዳይራቆቱ ነበር፡፡ የአፍሪካ አንጡራ ሃብት በቅኝ ገዥዎች ከልጆቿ ጉሮሮ ተነጥቆ እንዳይወሰድና ልጆቿ በእናት ምድራቸው በነፃነት እንዲቦርቁ ታስቦ በቀድሞው አባቶች መልካም ፈቃድ የተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት /አ.አ.ድ/ ዛሬ ስሙ ተቀይሯል፡፡ ይህም የሆነበት ምከንያት ድርጅቱ የተቋቋመለትን አፍሪካውያንን ከባርነትና ጭቆና ነፃ ማውጣት የሚለውን አሳክቶ ጨርሷል በሚል ነው፡፡

የጨነገፈው ፅንስ

የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች ያነገቡት ወገኖቻቸውን ነፃ የማውጣት መልካም ራዕይ በአሁኖቹ የአስተሳሰብ አድማስ እሳቤ ተሳክቷል በሚል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬ 12 ዓመት ግንቦት 2ዐዐ1 (እ.አ.አ) ደቡብ አፍሪካ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ወደ አፍሪካ ህብረት ተቀይሯል፡፡ እውነት ለመናገር ዛሬም ድረስ አፍሪካውያን ነፃ ወጥተዋል ማለት አይቻልም፤ ነፃ የነበሩትም በአብራኮቻቸው ክፋይ ቅኝ ግዛት ውስጥ ገብተዋልና፡፡

በተለይ በዛሬዎቹ መሪዎች ድርጅቱ ዓላማውን አሳክቷል፤ ግቡን መቷል በሚል የአህጉሪቱን ልማት መሰረት በማድረግ የአፍሪካ ህብረት ተቋቁሞ መቀመጫውንም እዚሁ አዲስ አበባ አድርጓል፡፡

ያኔ ቅኝ ገዥዎች ባላገሮቹን በግፍ ይጨቁኑ ነበር፣ ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲያቀርብ በጥይት እሩምታ በመረሸን የቀሩትን ወደ አሰቃቂ እስር ቤት ይከቱ ነበር፡፡ ይህ ግን ነፃዋን ኢትዮጵያን አይመለከትም ነበር፡፡ ምክንያቱም ንጉሷም መሪዋም ባዕድ ሳይሆኑ ያው ያብራኳ ክፋይ አፄ ኃ/ስላሴና ኢትዮጵያውያን ናቸውና በመካከል የቅኝ ገዥነት እሳቤ የለም፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያውያን በንጉሱ ስርዓት ቅሬታ ሲሰማቸው በነፃነት ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ነበር፡፡ ለዚህም እ.አ.አ በ197ዐ ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረውን የነዳጅ ጭማሪ ዋጋ በመቃወም የነበረውን ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል፡፡ ከዛም በፊት ወጣቶች መሬት ላራሹ ተቃውሞን በነፃነት አሰምተዋል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ግን የማይቻል ነው፤ ቅኝ ገዥዎች ናቸውና፡፡

ዛሬ ግን ምናልባት አንፃራዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር ያላቸው ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ካልሆነ በስተቀር አፍሪካውያን በራሳቸው ጥቁር ገዥዎች የጭቆና ቀንበር ስር ወድቀዋል፡፡ ለዚህም በግብፅ፣ በሊቢያ፣ በኮትዲቫር፣ በቱኒዚያ፣ በሞሮኮና በአልጄሪያ ያሉትን ጨቋኝ አስተዳደሮች በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የወጡት ከቅኝ ገዥዎች በባሰ በአሽከሮቻቸው ታጣቂዎች በአደባባይ የጥይት እራት ሆነዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያም የተመለከትን እንደሆነ አፍሪካውያን ነፃ ወጥተዋል በሚል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ ህብረት ከተቀየረ በኋላ በቅኝ ያልተገዙት ኢትዮጵያውያን የመንግስት ገዥዎች በርካታ እኩይ ተግባራትን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቢፈልጉም ለመጨረሻ ጊዜ በሚል ይመስላል እ.አ.አ በ2ዐዐ5 (በ1997 ዓ.ም) በምርጫ ወቅት ነበር የተደረገው፡፡ ከዚያም የምርጨውን ውጤት ተከትሎ በተፈጠረ ተቃውሞ አሁን በስልጣን ላይ ባለው ገዥው ቡድን መሪ በነበሩት በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ጨቅላ ህፃናትን ጨምሮ ከ86ዐ በላይ ዜጐች የጥይት ናዳ አርፎባቸው እስከወዲያኛው አሸልበዋል፡፡

በኬንያና በሱዳንም ሆነ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገሮች በተመሳሳይ መልኩ ገዥዎችን ለመደገፍ ካልሆነ ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ለሞት ይዳርጋል፡፡ ይህንን ደግሞ ቅኝ ገዥዎች ያደርጉት የነበረው አስከፊ ድርጊት በጥቁር ቆዳ ካባ በለበሱ አምባገነን መሪዎች መደገፍ አፍሪካውያንም ሆኑ አፍሪካ ነፃ ወጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የድጋፍ የድጋፍማ ቅኝ ገዥዎችም አሳምረው በመፍቀድ መፈክር እና ሌላ ወጭ በመሸፈን ይከናወን ነበር፤ ተቃውሞ ባይቻለም፡፡

ሌላው ያኔ በቅኝ ገዥዎች ወቅት የአፍሪካ አንጡራ ሃብት ተዝቆና ተሸጦ ወደ አውሮፓ ካዝና ይገባ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ በእራሳቸው በአፍሪካውያን መሪዎች ከአህጉሪቱ ህዝብ ጉሮሮ ተነጥቀው አንጡራ ሃብቷን ዝቀውና ሸጠው ወደ አውሮፓና እስያ ሀገሮች ካዝና ያስገባሉ፤ አፍሪካውያን ግን ዛሬም ይራባሉ፣ይታሰራሉ፣ ይገረፋሉ፣ ይጨቆናሉ፣ይሰደዳሉ፣ይገደላሉ፣ይዘረፋሉ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመለትን ዜጐቿን ነፃ የማውጣት ራዕይ ግቡን ሳይመታና ሳያሳካ የነፃነት ፅንሱ በዚህ መልክ ጨንግፏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእስያዎቹ ቻይና፣ ህንድና የአረብ ሀገራትን ጨምሮ አሜሪካና አውሮፓ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸውን አላወጡም፣ ዛሬም በዘመናዊው እጅ አዙር ቅኝ ጋዛት ቀፍድደው ይዘዋልና፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዓላማ ተጨናግፋል እንጂ ተሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡

       በትረ ከረባት ነዳያን

የቀድሞ ለነፃነት ቀናዒ የሆኑ የአባቶቻችንን ዓላማ ተሳክቷል በሚል ክህደት የዛሬዎቹ በትረ ከረባት ነዳያን የአፍሪካ ህብረትን አቋቁመዋል፡፡ የህብረቱም ዓላማ በአፍሪካ ልማትን ማምጣትና ማፋጠን እንዲሁም ማስተሳሰር የሚል ነው፡፡ በዚህም ስም በስልጣን ላይ ያሉት የአህጉሪቱ መሪዎች የራሳቸውን ሆድና ስልጣን ታሳቢ በማድረግ በአህጉሪቱ ህዝብ ስም ከረባት አስረው ለምነው የሚያመጡትን ገንዘብ በሌላ መንገድ በስማቸው ወደ ለጋሽ ሀገሮች ካዝና ይቋጥራሉ፡፡

ለዚህም የሊቢያ፣ የግብፅ፣ የቱኒዚያና የኢትዮጵያ መሪዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የዚህ ባለሟል ናቸው፡፡ አብዛኞቹ መሪዎችም እጃቸው ከዜጐቻቸው የግፍ ደምና የህዝቡ አንጡራ ሃብት ዝርፍያ የፀዳ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ዜጐቻቸውን እጅግ ከቅኝ ገዥዎች በባሰ መልኩ በመጨቆን አንዳንዶቹ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሌሎቹ ደግሞ በምርጫ ስም ህዝብን በማጭበርበር በትረስልጣናቸውን እያደላደሉ ይገኛሉ፡፡

አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የአፍሪካ ማሪዎች የእነሱ የስልጣን ዕድሜ እስከረዘመና ዝርፊያውን እስኳጧጧፉ ድረስ የአህጉሪቱን አንጡራ ሃብት ጥቅም በማዘረፍ ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ በዚህም ለዜጐቻቸው ያላቸው ቀናዒነትና ተቆርቋሪነት ከቀድሞዎቹ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች ጋር ሲነፃፀር እጅግ አናሳ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ የበትረ ከረባት ነዳይ ሆነው የአህጉሪቱን ሃብት እያዘረፉ  የዜጐቻቸውን ነፃ አስተሳሰብና ነፃ ሚዲያን በማፈን ከፍተኛ ጭቆና እያደረጉ ስለመሆኑ የህብረቱ ዋና መቀመጫ የሆነችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛው  አፍሪካ ሀገሮችን ማየት በቂ ነው፡፡

በአጠቃላይ አሁን እ.አ.አ. በያዝነው ግንቦት 2ዐ13 የአፍሪካ ህብረት ምስረታ 5ዐኛ ዓመት ክብረ በዓል ለመሪዎቹ ብቻ ካልሆነ በቀር ለአህጉሪቱ ህዝብ ይሄ ነው የሚባል የፈየደው ነገር አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም እየተሰሩ ያሉት መሰረተ ልማቶችና ሌሎች የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታ ሰብዓዊ ልማትን ወደጐን በመተው እየተደረገ ያለው ቅኝ ገዥዎች በጊዜያቸው ሲያደርጉት ከነበረው እምብዛም የተለየ አይደለምና፡፡ በዚህም አፍሪካ ቀድሞ የነበራት ራዕይ በአሁኖቹ በትረ ከረባት ነዳይ መክኖ ቀርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ያኔ ቅኝ ገዥዎች ሰብዓዊ መብትን በመርገጥ በቁሳዊ ልማት ህዝቡን ለመደለል ይሹ እንደነበረው ዛሬም እንዲሁ ነው፡፡

አንዱዓለም አራጌ በእስር ቤት…

Aneduየአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ የመጀመሪያ ልጁን የሩህ አንዱዓለምን 5ኛ ዓመት የልደት በዓል እሁድ ግንቦት 11 ቀን 2005ዓ.ም. አከበሩ፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌ የልጃቸውን የልደት በዓል እቤታቸው ማክበር ባለመታደላቸው እሁድ ከቀኑ 4፡00 ሰዓት ለባለቤታቸው ሳያሳውቁ ለመጠየቅ ሲሄዱ በድንገት ለማስደሰት ሲሉ ተዘጋጅተው በመጠበቃቸው በሰዓቱ ባለቤታቸው ዶ/ር ሰላም አስቻለው፣ልጃቸው ሩህ አንዱዓለም፣እህታቸው ወ/ት አበሩ አራጌ በተገኙበት በመጠየቂያ ጠባብ ክፍል በጋራ የልጃቸውን ልደት አክብረዋል፡፡

ይህ ልጃቸው ያኔ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2003ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት ልኮት ማታ ሲመጣ ውሎውን ለማዳመጥ በናፍቆት እየጠበቀና ይህንንም ለባልደረቦቹ ለአንድነት ፓርቲ አመራሮችና ሰራተኞች የነገረ ቢሆንም በዕለቱ የልጁን ውሎ እንደናፈቀ ከቀኑ 9፡20 ሰዓት ላይ በፖሊሶች ከሚሰራበት ከፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት አቅራቢያ ካለ ካፍቴሪያ ከአንድ የፓርቲው ወጣት አመራር ጋር በመሆን ሻይ ቡና ብለው ሲወጡ ተይዘው መታሰራቸው ይታወቃል፡፡

በዕለቱ የዛሚ ሬዲዮ ባለቤት ሚሚ ስብሐቱ የእነ አንዱዓለም ፓርቲ ልሳን የሆነውን ፍኖተ ነፃት ጋዜጣን ዋቢ አድርጋ በመጥቀስ ብጥብጥ እየቀሰቀሱ ነው፤ ዝም ሊባሉ አይገባም ብላ በተለመደቀው በቀትር የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በሚል የሬዲዮ መርሃ ግብር አቅርባ የነበረ ሲሆን አንዱዓለምም ይህንን ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር አዳምጦ ጨርሶ ከወጣ በኋላ መያዛቸው አዘነጋም፡፡ በአሁን ወቅትም ወጣቱ ፖለቲከኛ አቶ አንዱዓለም አራጌ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው በቃሊቲ እስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት(ግንቦት 2005ዓ.ም.)

በኢትዮጵያ ስኳር ፕሮጀክት ላይ የተጋረጠው አደጋ

ብስራት ወ/ሚካኤል

awash

ጨዋማው የኢትዮጵያ ሐይቅ 15 እጥፍ ይዘቱና ስፋቱ እየጨመረ በሀገሪቱ ታላላቅ ወንዞች መካከል አንዱ በሆነው ወንዝ ላይ ስጋትን ጭሯል፡፡ ይህ ስጋት በቡና አምራችነቷ ከአፍሪካ ታላቅ በሆነችው ሀገር ላይ አደጋ እያንዣበበ ነው፡፡

ጨዋማው ውሃ ታማኙንና ታላቁን አዋሽ ወንዝን በመበከል በኢትዮጵያ መንግስት ባለቤትነት በሚተዳደረው ስኳር ፋብሪካ እና ከህንድ ድጋፍ በማግኘት ስኳር ወደ ውጭ ላኪ ሀገሮች ተርታ  ለመሰለፍ ያለው ዕቅድ ላይ አደጋ ተጋርጧል፡፡ ስጋትን የጫረው ይህ ጨዋማው ሐይቅ የበሰቃ ሐይቅ ነው፡፡

የበሰቃ ሐይቅ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝና ባለፉት ዓመታትም እጅግ እተስፋፋ ወደ መስኖው ውሃ እየተቃረበ ነው፡፡ ይህ ሐይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ የሚገባ ከሆነ በኢትዮጵያ ግዙፍ የስኳር አምራችነት ዕቅድ ላይ የአደጋ ጥላ ያጠላል፡፡

እዚህ ላይ የውሃና ማዕድን ሚኒስቴር የከርሰ ምድር ውሃ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ታደሰ ‹‹ለወንዙ ነው የምንሰጋው፤ ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ በራሱ ጊዜ ወደ ወንዙ የሚደባለቅ ከሆነ እስከወዲያኛው ወንዙን እየበከለው ይሄዳልና” ሲሉ መስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

አባይ ተፋሰስን ጨምሮ ከሀገሪቱ ከፍታ ቦታዎች የሚመነጩ ወንዞች ኢትዮጵያን ከአህጉራቱ አፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የውሃ ኃይል ባለቤት አድርጓታል፡፡ መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ ከህንድ የገንዘብ፣ የሳውዲው ቢሊየነር እና ከቻይናው አበዳሪ ስኳር፣ ሩዝ፣ ሙዝና ብርቱካን ምርትን ለማስፋፋትና ወደ ውጭ ለመላክ ያለነዳጅ ዘይት በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አስባለች፡፡

የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የቴክኒክ ኃላፊ የሆኑት እንደሻው ታደሰ እንዳሉት ከሆነ የሰኔው ወቅታዊ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት ሐይቁ ወደወንዙ እንዳይፈስ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፍሰቱ ከሀገሪቱ ዋና መናገሻ አዲስ አበባ በስተምስራቅ የጎርፍ መጥለቅለቅን በማስከተል በአካባቢው የነበሩትን አርብቶ አደሮች እንደሚያርቅ ይጠበቃል፡፡

በሰቃ ከ954 ሜትር የሚመነጭ ፍልውሃ በ1960ዎቹ ዓ.ም.(እ.ኤ.አ) 3 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሸፍን የነበረው በአሁን ሰዓት 5 እጥፍ በማድረግ ወደ 45 ኪሎ ሜትር ስፋት በመጨመር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ወደብ ዋና የንግድ መስመር የሆነውን መንገድ አቅጣጫ ማስቀየሩም ግድ ይላል፡፡

ያልተሳኩ ጥረቶች

መንግስት ላለፉት 14 ዓመታት በየጊዜው ስፋቱና ይዘቱ እየጨመረ የመጣውን የበሰቃ ሐይቅ የማስቀየሻ ቦይ ግንባታ በመስራት እንዲፈስ ቢያደርግም ሐይቁን እንደባህር ባለበት ማስቀረት አልቻለም፡፡

በዚህ ላይ በ2009 (እ.ኤ.አ) እና ባለፈው ዓመት ጥናታቸውን ያቀረቡት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት መገርሳ ኦኩማና ደንቃ እንዳሉት ከሆነ በአካባቢው የመስኖ ፕሮጀክቱ መጨመር ውሃ ወደ ሐይቁ በመግባት ተመጋጋቢነት ይኖረዋል፡፡ ይህም በሚደረጉ የመስኖ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡

አሁን ባለው የበሰቃ ዕድገት ባህርይ መተሐራ አካባቢ ያለውን መስኖ ከጥቅም ውጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በያዝነው ዓመት የተገዛውና ንብረትነቱ የመሐመድ አል አሙዲ የሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ከመንግስት የገዛው የላይኛው አዋሽ የግብርና ኢንዱስትሪንም አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ ይህን በተመለከተ የሆራይዘን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ ከሐይቁ ምንጭ ዕድገት ጋር ተያይዞ የተደረገውን ጥናት አላረጋገጥንም፣ ምናልባት በአካባው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖር ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ኢንቨስትመንት

አል አሙዲ የግብርና ምርት ወደሆኑት ሩዝ፣ ሙዝና የተጠናቀቀ ቡና ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ሆራይዘን በላይኛው አዋሽ 432 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ የብርቱካን ምርትን በእጥፍ በማሳደግ ወደ 50,000 ቶን ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ 380 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከህንድ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በተገኘ 640 ሚሊዮን ዶላር ብድር እየተገነባ ያለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም  የበሰቃ ሐይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ በመግባት ወንዙ ጨዋማ የሚሆን ከሆነ አደጋ ይገጥመዋል፡፡ እንደሚታወቀው ህንድ በዓለም ሁለተኛ የስኳር አምራችና ከፍተኛ ተጠቃሚ ነች፡፡

ሌላው ወደ 30,000 ነዋሪዎች የሚገኙበት መተሐራ እና አዲስ ከተማ፣ መተሐራ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአፋር ክልል እየተገነባ ያለው ግዙፍ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሐይቁ መስፋት እየቀጠለ ከሄደ ለአካባቢው አደገኛ ነው፡፡

ስኳርና ጥጥ

ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ የመሰረት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ 90 ሚሊዮን የሚደርሰው የሀገሪቱ ነዋሪ ወደመካከለኛ ገቢ እንዲያድግ የጥጥ እርሻን አቅርቦት ተንተርሶ የሚገነቡት የጨርቃጨርቅ እንዱስትሪዎች ማደግ እንዳለባቸው ዕቅድ ነድፈዋል፡፡ ይህ የጥጥ እርሻ ልማት ደግሞ ለመካከለኛው አዋሽ በአሚባራ ቢዝነስ ግሩፕ የሚመራው ኢንዱስትሪም የበሰቃ ሐይቅ ከአዋሽ ወንዝ ጋር በመቀየጥ ጨዋማ የሚሆን ከሆነ እሱም አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ እንደዓለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ተቋም መሰረት ከ1984 ዓ.ም.(እ.ኤ.አ) ጀምሮ በፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረ 2,000 ሄክታር በጨዋማ ውሃ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡

አሚባራ መካከለኛው አዋሽ የግብርና ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ውብሸት ይልማ እንዳሉት ከሆነ ‹‹ከዝናቡ በፊት የሐይቁ መስፋፋት ያሳስበናል፤ ምክንያቱም ሐይቁ ወደ አዋሽ የሚገባ  ከሆነ ለአማባራ ጥጥ እርሻ ችግሩ ከፍተኛ ነው የሚሆነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ቤት መስጠም

በኢትዮጵያ መንግስት ንብረት የሆነውና በአፋር አካባቢ የተቋቋመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአዋሽ ወንዝ ግድብ ግንባታ ላይ መሰረት በማድረግ ከ600,000 ቶን በላይ የሸንኮራ እገዳ በዓመት ለማልማት የነበረው እቅድ ላይ ጨዋማ ውሃ የሚፈስ ከሆነ አሁንም እቅዱ ይጨናገፋል፡፡

በተለይ አቶ እንደሻው እንደተናገሩት ከሆነ “ዝናብ የሚዘንብ ከሆነ በቃ” ሲሉ ባለፈው ዓመት በሐይቁ ሙላት ምክንያት የሰጠሙ ሁለት ትምህርት ቤቶችን አስታውሰዋል ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐይቁን ስፋት ተከትሎ በተፈጠረ ድርቅ በተወሰደ እርምጃ በ2008 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ክልላዊው መንግስት በ467 ሚሊዮን ብር የፈንታሌ መስኖ ቦይ ግንባታ መደረጉን የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት የውሃ ምህንድስና ኃላፊው እንግዳ ዘመዳገኘሁ ተናግረዋል፡፡

በተለይ እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ወንዙ 4 በመቶ የሐይቅ ውሃ የሚይዝ ቢሆን እንኳ በማንኛውም መልኩ አደገኛ ነው፡፡ ለዚህም በሚል በፓንፕ (ውሃ መሳቢያ መሳሪያ) ብዙ ውሃ ለመቀነስ ጥረት ብናደርግም መስፋፋቱን ግን ሊቀንስ አልቻለም ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

በማኛውም አጋጣሚ ሐይቁ እየጨመረ ከሄደ “ሐይቁ ወደ አዋሽ ወንዝ የመፋሰስ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሚቀጥሉት ቅርብ አመታት የመተሐራ ስኳር ፋብሪካን ያወድማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ  ተንዳሆን ጨምሮ በአዋሽ ተፋሰስ በሚገነቡ በሁሉም ግዙፍ መስኖ ልማቶችም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል” ሲሉ ፕሮፌሰር መገርሳ ተናግረዋል፡፡

 የእሾሃማ ዛፎች እጣ ፈንታ

በመንግስት ባለቤት ከሚገነባው ተንዳሆ ስኳር ውጭ በኬንያ አቅራቢያ በደቡብ ኦሞ የሚገነቡትን 6 የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች ጨምሮ 10 ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በቻይና ዴቨሎፕመንት ባንክ የሚደረግ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር ድጋፍ በአዋሽ አካባቢ የሚገነባ የከስም ስኳር ፕሮጀክት ይገኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ የስኳር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ ቃል አቀባይ አቶ ይልማ ጥበቡ ከመጋቢት አጋማሸ ጀምሮ አስተያየት ቢጠየቁም ምላሽ እንዳልሰጡ የብሉምበርጉ ዘጋቢ ዳቪሰን አስታውሷል፡፡

ከኢትዮጵያ ከፍታ ቦታዎች በመመንጨት በሰሜን ምስራቅ ወደ አፋር በመፍሰስ ጅቡቲ አካባቢ ከመድረቁ በፊት አዋሽ ወንዝ 1,200 ኪ.ሜትር ይጓዛል፡፡ ከመተሐራ አካባቢ ጀምሮ ባሉ በአካባቢው ያሉ እሾሃማ ዛፎች(ግራርና ቆንጥር) በተጨማሪ በአካባቢው ሞቃታማ ስፍራ የሚበቅሉ የምግብ እህሎችን ተንተርሰው እየኖሩ ያሉ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡ ለነዚህ ህዝብ በተለይም የአፋር አርብቶ አደሮች ለረጅም ጊዜ ህይወታቸውን እዚህ ወንዝ ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው ፡፡ ስለዚህ የአዋሽ ወንዝ በበሰቃ ሐይቅ ብክለት የሚያጋጥመው ከሆነ ለእነኛ ነዋሪዎች አደገኛ ነው የሚሆነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው የከፍተኛ ባለሙያዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ስብስብ ስለሐይቁ እንዴት እያደገ እንደመጣ ጥናትና ምክክር እየተደረገ ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ግን ምን መደረግ እንዳለበት የተያዘ አቅጣጫም ሆነ የተወሰደ እርምጃ የለም ሲሉ ማከላቸውን ሚያዚያ 24 ቀን 2013 (እ.ኤ.አ) በብሉምበርግ ድህረ-ገፅ ዊሊያም ዳቪሰን አስነብቧል፡፡

አሁንም ቢሆን ከአዲስ አበባ ወደምስራቅ 195 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የመተሐራ በሰቃ ሐይቅ ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘለት በአዋሽ ተፋሰስ ላይ በብዙ ቢሊየኖች ብር ግንባታቸው ተካሂደው በስራ ላይ ያሉ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ፤ በቅርቡ ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ በስራ ላይ ያሉት የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ የግብርና እንዱስትሪዎች እንዲሁም በእቅድ ላይ ያለው የከሰም ስኳር ፕሮጀክት በተጨማሪ የመተሐራን ከተማ ነዋሪዎችና አዋሽ ወንዝን ተጠግተው የሚኖሩ የአፋር ክልል ነዋሪዎችን በነበሩት ዳግም ላናገኛቸው እንችላለን፡፡

ከላይ የተጠቀሰው የብሎምበርግ ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ ሲያደርግ ከሚፈልገው ገንዘብ ውጭ አካባቢያዊ ጥናት የማድረግ ትኩረትም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መጨው ትውልድ ላይ ጭምር ዕዳ ተጥሎ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የሚጠበቅባቸውን ውጤት ሳያስገኙ በሚደርስባቸው የአካባቢ አደጋ በሀገር ላይ ከፍተኛ የሃብት ውድመት ማስከተላቸው የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት የግብር ውጣ ስራ የሚያደርገውን የዘመቻ የልማት ፕሮጀክቶች ስራ አካባቢውንና ተፈጥሯዊ ሁነቶችን ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ማጤንና ማገናዘብ አለበት፡፡

እውን የሀገሪቱ ችግር እንዲህ በቀላሉ ይፈታ ይሆን?

ብስራት ወልደሚካኤል

afrosonb@gmail.com

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ከዕለት ወደዕለት እየባሰበት በመሄዱ የችግሮቹን ውስብስብነት ከመባባሱ በስተቀር ለነዋሪው የፈየደ አንዳች የመፍትሄ ሐሳብም ሆነ ተግባር የለም፡፡ ችግሮቹ በገጠርም ሆነ በከተማ ተባብሰው በመቀጠላቸው ከብዛታቸው አንፃር በተናጥል መጥቀሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሉ ከሚባሉት መካከል  የተወሰኑትን ችግሮች እንኳ ለማየት እንሞክር፡፡

በአዲስ አበባ ያለው የመጓጓዣ እጥረት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱ እስካሁን መፍትሄም ሆነ ትኩረት ስላልተሰጠው  የሀገሪቱ ሃበት ላይ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበትና የሞራል ኪሳራ ማድረሱ አይቀሬ ቢሆንም “እኛን ብቻ አድምጡን፣ ችግራችሁን ደብቁትና ቁጭ በሉ፣ ግዴታችሁን ተወጡ እንጂ መብታችሁን አትጠይቁ!” በሚል ግትር አቋሙ የፀናው የኢህአዴግ መንግስት ችግሩን የመፍታት አቅም እንደሌለው ያረጋገጠ ቢመስልም የስልጣን ጥሙ ግን ቀፍድዶ ይዞታል፡፡ በዚህም ምክንያት የታክሲ ሰልፉ፣ የከተማ አውቶቡስ፣ የሎንችንና የሃይገር ግፍያን ጨምሮ የመንገዶች መጨናነቅን ላየ እውን በሀገሪቱ መንግስት አለን? ያስብላል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ የመጣ እንጂ ቅፅበታዊ ክስተት አይደለም፡፡

ምናልባት አሁን እየተሰራ ያለው የከተማ ውስጥ ቀላል የባቡር ሃዲድ ግንባታና አገልግሎት እየተካሄደ ነው፣ ይሄ ሲጠናቀቅ ችግሩ ይፈታል የሚል መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ሊኖሩ ቢችሉም የባቡር አገልግሎት ቢጀመርም የነዋሪው ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሩን ሊፈታ የሚችለው ብቃት ያለው አመራር መኖርና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ህዝብን ያላማከለና ያላሳተፈ ስራ ግልፀኝነት ስለሌለው ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር ውጭ የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ለመፍትሄው ከህዝብ ጋር በግልፅ መድረክ መወያየቱ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡

የኑሮ ውድነቱ አንዱ ዋነኛ ችግር ሲሆን ለዚህም መንግስት እንዳሻው የሚያደርገው የገበያ ጣልቃ ገብነትና የዋጋ ተመን ዕቃ እንዲጠፋና ጥራታቸው የጎደሉ ሸቀጦች ለህዝቡ ኢንዲደርሱ ከማድረጉ በተጨማሪ ወደፊት በውድድር ገበያ ዋጋቸው የሚወርዱ ዕቃዎች ባሉበት በመቀጠል ወደፊት በዛው ዋጋቸው እየጨመረ እንዲሄድ ያስገድዳል፡፡ ስለዚህ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣትና መንግስት እጁን ከገበያ ማውጣት ካልቻለ ችግሮቹ ከአሁን በባሰ እንደሚቀጥሉ ጥርጥር የለውም፡፡

በክልል ከተሞችና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ያለው የኢህአዴግ ቅጥ ያጣ አፋኝነት(በአዲስ አበባ የለም ማለቴ አይደለም) ህዝቡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጭ መብቱን እንዳይጠይቅ በመደረጉ ችግሮች ሳይባባሱ በጊዜ እንዳይታረሙ በመደረጉ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሰቆቃ ህይወት እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በተለይ ገበሬው ያልፍላጎቱና ያለ አቅሙ ለግብርና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች( ማዳበሪያ፣ አረም ማጥፊያ፣ ዘር) ኢህአዴግ በተመነው ከፍተኛ ዋጋ እንዲገዙ በመደረጉ ምርቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ሸጠው ለኢህአዴግ በመክፈል፤ መሬት እያላቸው እንደሌላቸው በመሆን  የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገበሬውም በንብረቱ የማዘዝ ስልጣኑ በመገፈፉ የእኔነት ስሜት ስለማይኖረው ውጤታማ ስራ ሊሰራ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡ የዚህ ችግር ደግሞ ከባዶ የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ በስተቀር  በምግብ እራሷን እንዳትችል ያደረጋት ከመሆን ባለፈ ድሬ በምግብ እራሳቸውን የቻሉ ገበሬዎች ዛሬ ለልመና ወደ አዲስ አበባና ትላልቅ የክልል ከተሞች ጎዳና በመውጣት ለልመና ተዳርገዋል፡፡

በሀገሩቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ከፍተኛ አምራች ኃይል የሆኑት ወጣት ምሁራን ከዩንቨርስቲ ተመርቀው ወጥተው በሙያቸው እራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ማኀበረሰቡንና ሀገራቸውን ማገልገል ሲገባቸው አነስተኛ የትምህርት እድል ያላቸው ዜጎች ሊሰሩት የሚገባውን የድንጋይ ፈለጣ(ኮብልስቶን ስራ) ላይ እንዲሰማሩ በመደረጉ ለትምህርት ያወጡት፣ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ሞራል በከንቱ እንዲባክን ተደርጓል፡፡ የዚህም ውጤት የሀገሪቱ ዜጎች ተስፈኛ ከመሆን ይልቅ ተስፋ ወደመቁረጥ በመዳረጋቸው ለተለያዩ ጎጂ ሱሶች ተጋልጠው በየመንገዱ ሲንቀዋለሉ ላየ “የየት ሀገር ቱሪስቶች ናቸው?” ሳያስብል አይቀርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ  አስከፊ የስደት መንገዶችን ምርጫ በማድረግ የሚሞቱ ወጣት ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ በመሄዱ “ሀገሪቱ እውን መንግስት አላትን?” ያስብላል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ምክንያት ገዥው ኢህአዴግ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲና ግትር አቋም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በመላው ሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከትን እንደሆነ በዓለም ላይ እጅግ አምባገነንና ጨቋኝ መንግስት መኖሩን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ቢቻልም ይበልጥ ግን ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሊያገለግሉ የሚገባቸው፣ ከየትኛውም የፖለቲካና የግለሰብ ተፅዕኖ ገለልተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው የዴሞክራሲያዊ ተቋማት (የፍትህ አካል የሆኑ  ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃይሎች፣…) በኢህአዴግ መዳፍ ወድቀው ወገንተኝነታቸው ለፍትህ፣ ለህግና ለህዝቡ ከመሆን ይልቅ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወገንተኛ በመሆናቸው የሀገሪቱን ችግር ይበልጥ ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል፡፡ በዚህም በህግ የተሰጣቸውን መብት የተጠቀሙና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የጠየቁ በርካቶች ወደ ወህኒ ቤት ተወርውረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ጋዜጠኞች(እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፣ የሱፍ ጌታቸው፣…)፣ፖለቲከኞች(አንዱዓለም አራጌ፣ናትናኤል መኮንን፣በቀለ ገርባ፣ኦልባና ሌሊሳ፣…)፣ የኃይማኖት ነፃነት መብት እንዲከበር የጠየቁ (የሙስሊሙ  ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ የዋልድባ መነኮሳት፣…) ይገኙበታል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ኢህአዴግ “ለስልጣኔ ያሰጉኛል” በሚል ብቻ በሀገር ስም ክስ ስለመሰረተ ሁሉም ተከሳሾች ወንጀለኛ የሚባሉ ሲሆን  በአንፃሩ በኢህአዴግ ባለስልጣናትና አባላት በደል ተፈፅሞባቸው “የፍትህ ያለ” የሚሉ “ፍትህ በኪሴ ብይን” ተሰጥቷቸው በኋላ ወንጀለኛ እንባላለን በሚል በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት በማጣታቸው “የማርያም ጠላት” የሚባሉ በርካቶች ናቸው፤እነኚህንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ የተፈቀዱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የመሰብሰብ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞን የመግለፅ፣…በሙሉ ባልተፃፈና ባልታወቀ ህግ የተሻሩ ሲሆን ይበልጥ እነኚህ እንዳይተገበሩ ለገዥዎች ብቻ በሚመች ህገመንግስቱን በግልፅ የጣሱ በርካታ አንቀፆችን የያዘ የፀረ ሽብር አዋጅ በማውጣት ተጨማሪ የአፈና ገደቦች ተጠለዋል፡፡ የእነኚህ አፈናዎች ውጤት ችግሮች በጭሩና በቀላሉ እንዳይፈቱ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ እጅግ የታፈነ ቁጣ እንዲኖር አስችሎታል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ወደፊት በሀገሪቱ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግልፅ ቢሆንም ኢህአዴግ በያዘው ግትር አቋም ችግሮች እየተባባሱ ከመሄድ በስተቀር የሀገሪቱን ውስብስብ ችግር ሊፈታ አይችልም፤ምክንያቱም ኢህአዴግ አቅሙም ቁርጠኝነቱም የለውምና፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የታፈኑ ጩኸቶች ድምር ውጤት ድንገት ከፈነዳ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን(ምስራቅ አፍሪካን) ሊያናውጥ  ስለሚችል ኢህአዴግና አመራሮቹ ከጭፍንና ግትር አቋም ወጥተው የህዝቡን ጥያቄ ማድመጥና ተገቢውን መልስ መስጠት፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ የተቆለፈበትን ነፃ ፕሬስ በተግባር ላይ እንዲውል ከፍተኛ የሆነ የወረቀት ታክስን ከማስቀረት በተጨማሪ ህዝቢ መረጃ የማግኘት መብቱ ያለምንም ገደብ እንዲከበር ማድረግ፣ ለአፈና የዋሉ ህገወጥ ህጎችን ማሻሻል/መሻር፣1 ለ 5 እያሉ የሚጠቀሙባቸውን ህገወጥ የአፈና መዋቅር መበተንና ማቆም፣ በህገመንግስቱ የተቀመጡ ያወጧቸውን ህጎች በማክበር ለሌሎች አርዓያ በመሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ በባዶ ሜዳ “በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እየሰራሁ ነው…” በሚል የእንቁልልጭ ፈሊጥ  የዜጎችን መብት ማዳፈን የዲያቢሎስ የህልም ሩጫ ካልሆነ ለፖለቲካ ፍጆታ ተጀምረው ከመቆም ያለፈ ተፈፃሚ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም  ከምንም ከማንም ቀድሞ መልማት ያለበት የዜጎች ነፃነት የተላበሰ የአስተሳሰብ አድማስ እንጂ ቁስ አይደለም፤ ቁሳዊ ልማቶች ሊሰሩ የሚችሉት በነፃና ጤናማ የዳበረ አስተሳሰብ ባለው የሰው ኃይል ነውና፡፡ ያኔ የምንመኘውና የሚዘመርለት ቁሳዊ ልማትም እውን ይሆናል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፐርቲዎችም ሆኑ ድርጅቶች ከእርስ በርስ መጠላለፍና ከፍርሃት ተላቀው ከቢሮ ፖለቲካ በመውጣት ሰላማዊ ትግል ምን እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ወደህዝቡ መውረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በየቢሮው በሚደረግ የድርጊቶች መቃወሚያ ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ለህዝብና ለሀገር ቆሜያለሁ ማለት ከቀን ቅዥት ባለፈ ጠብ የሚል ነገር ማምጣት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም  የፖለቲካ ትግል የተጠና ስልታዊ የተግባር ስራ እንጂ የወንበር ማድመቂያ አይደለምና፡፡ እዚህ ላይ ፖለቲከኞች አምነውበት እችላለሁ ብለው ወደፖለቲካው ትግል እስከገቡ ድረስ በሚከተሉት የትግል ስልት የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻል አለባቸው፤ ካልሆነ ግን ከትግሉ እራሳቸውን ማግለልና ለሚሰራ ሰው መስጠቱ ለፖለቶከኞችም ሆነ ለሀገሪቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን ወደባሰ ችግር ከመሄድ እራሱን ከፍርሃት ድባብ በማውጣት ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመቃወም ከድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋር ባለመተባበር የራሱን እርምጃ በመውሰድ ለመብቱ ሊሎች እንዲቆሙለት ከመጠየቅ ይልቅ ራሱ መታገል አለበት፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እያንዳንዱ ሰው እገሌ ምን ሰራ ከማለት በተጨማሪ እኔ ምን ሰራሁ በሚል ሁሉም የድርሻውን ካልተወጣ የችግሩ ማዕበል ሁሉንም እንደሚያጠቃ እሙን ነው፡፡ አሁን ባለው የመጠባበቅና የማጉረምረም እንዲሁም የመፈራራት ሁኔታ ችግሮችን ከማባባስ ባለፈ የሀገሪቱ ችግር በቀላሉ ይፈታል ማለት የህልም እንጀራ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱ ችግር ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ስለሄደ ሁሉም ዜጋ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊነጋገርና መፍትሄውን በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ ሊተጋ ይገባል፤አለበለዚያ የችግሮቹ መንስኤ ኢህአዴግም ሆነ ተጠቂው ህብረተሰብ ከሚመጣው አስከፊ የፖለቲካ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማምለጥ ስለማይቻል ስለሀገራችን ሁኔታ በግልፅ ሊመከርበትና መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፡፡