እውን የሀገሪቱ ችግር እንዲህ በቀላሉ ይፈታ ይሆን?
ብስራት ወልደሚካኤል
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ከዕለት ወደዕለት እየባሰበት በመሄዱ የችግሮቹን ውስብስብነት ከመባባሱ በስተቀር ለነዋሪው የፈየደ አንዳች የመፍትሄ ሐሳብም ሆነ ተግባር የለም፡፡ ችግሮቹ በገጠርም ሆነ በከተማ ተባብሰው በመቀጠላቸው ከብዛታቸው አንፃር በተናጥል መጥቀሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሉ ከሚባሉት መካከል የተወሰኑትን ችግሮች እንኳ ለማየት እንሞክር፡፡
በአዲስ አበባ ያለው የመጓጓዣ እጥረት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱ እስካሁን መፍትሄም ሆነ ትኩረት ስላልተሰጠው የሀገሪቱ ሃበት ላይ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበትና የሞራል ኪሳራ ማድረሱ አይቀሬ ቢሆንም “እኛን ብቻ አድምጡን፣ ችግራችሁን ደብቁትና ቁጭ በሉ፣ ግዴታችሁን ተወጡ እንጂ መብታችሁን አትጠይቁ!” በሚል ግትር አቋሙ የፀናው የኢህአዴግ መንግስት ችግሩን የመፍታት አቅም እንደሌለው ያረጋገጠ ቢመስልም የስልጣን ጥሙ ግን ቀፍድዶ ይዞታል፡፡ በዚህም ምክንያት የታክሲ ሰልፉ፣ የከተማ አውቶቡስ፣ የሎንችንና የሃይገር ግፍያን ጨምሮ የመንገዶች መጨናነቅን ላየ እውን በሀገሪቱ መንግስት አለን? ያስብላል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ የመጣ እንጂ ቅፅበታዊ ክስተት አይደለም፡፡
ምናልባት አሁን እየተሰራ ያለው የከተማ ውስጥ ቀላል የባቡር ሃዲድ ግንባታና አገልግሎት እየተካሄደ ነው፣ ይሄ ሲጠናቀቅ ችግሩ ይፈታል የሚል መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ሊኖሩ ቢችሉም የባቡር አገልግሎት ቢጀመርም የነዋሪው ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሩን ሊፈታ የሚችለው ብቃት ያለው አመራር መኖርና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ህዝብን ያላማከለና ያላሳተፈ ስራ ግልፀኝነት ስለሌለው ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር ውጭ የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ለመፍትሄው ከህዝብ ጋር በግልፅ መድረክ መወያየቱ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱ አንዱ ዋነኛ ችግር ሲሆን ለዚህም መንግስት እንዳሻው የሚያደርገው የገበያ ጣልቃ ገብነትና የዋጋ ተመን ዕቃ እንዲጠፋና ጥራታቸው የጎደሉ ሸቀጦች ለህዝቡ ኢንዲደርሱ ከማድረጉ በተጨማሪ ወደፊት በውድድር ገበያ ዋጋቸው የሚወርዱ ዕቃዎች ባሉበት በመቀጠል ወደፊት በዛው ዋጋቸው እየጨመረ እንዲሄድ ያስገድዳል፡፡ ስለዚህ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣትና መንግስት እጁን ከገበያ ማውጣት ካልቻለ ችግሮቹ ከአሁን በባሰ እንደሚቀጥሉ ጥርጥር የለውም፡፡
በክልል ከተሞችና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ያለው የኢህአዴግ ቅጥ ያጣ አፋኝነት(በአዲስ አበባ የለም ማለቴ አይደለም) ህዝቡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጭ መብቱን እንዳይጠይቅ በመደረጉ ችግሮች ሳይባባሱ በጊዜ እንዳይታረሙ በመደረጉ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሰቆቃ ህይወት እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በተለይ ገበሬው ያልፍላጎቱና ያለ አቅሙ ለግብርና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች( ማዳበሪያ፣ አረም ማጥፊያ፣ ዘር) ኢህአዴግ በተመነው ከፍተኛ ዋጋ እንዲገዙ በመደረጉ ምርቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ሸጠው ለኢህአዴግ በመክፈል፤ መሬት እያላቸው እንደሌላቸው በመሆን የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገበሬውም በንብረቱ የማዘዝ ስልጣኑ በመገፈፉ የእኔነት ስሜት ስለማይኖረው ውጤታማ ስራ ሊሰራ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡ የዚህ ችግር ደግሞ ከባዶ የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ በስተቀር በምግብ እራሷን እንዳትችል ያደረጋት ከመሆን ባለፈ ድሬ በምግብ እራሳቸውን የቻሉ ገበሬዎች ዛሬ ለልመና ወደ አዲስ አበባና ትላልቅ የክልል ከተሞች ጎዳና በመውጣት ለልመና ተዳርገዋል፡፡
በሀገሩቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ከፍተኛ አምራች ኃይል የሆኑት ወጣት ምሁራን ከዩንቨርስቲ ተመርቀው ወጥተው በሙያቸው እራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ማኀበረሰቡንና ሀገራቸውን ማገልገል ሲገባቸው አነስተኛ የትምህርት እድል ያላቸው ዜጎች ሊሰሩት የሚገባውን የድንጋይ ፈለጣ(ኮብልስቶን ስራ) ላይ እንዲሰማሩ በመደረጉ ለትምህርት ያወጡት፣ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ሞራል በከንቱ እንዲባክን ተደርጓል፡፡ የዚህም ውጤት የሀገሪቱ ዜጎች ተስፈኛ ከመሆን ይልቅ ተስፋ ወደመቁረጥ በመዳረጋቸው ለተለያዩ ጎጂ ሱሶች ተጋልጠው በየመንገዱ ሲንቀዋለሉ ላየ “የየት ሀገር ቱሪስቶች ናቸው?” ሳያስብል አይቀርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ አስከፊ የስደት መንገዶችን ምርጫ በማድረግ የሚሞቱ ወጣት ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ በመሄዱ “ሀገሪቱ እውን መንግስት አላትን?” ያስብላል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ምክንያት ገዥው ኢህአዴግ የሚከተለው የተሳሳተ ፖሊሲና ግትር አቋም መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
በመላው ሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከትን እንደሆነ በዓለም ላይ እጅግ አምባገነንና ጨቋኝ መንግስት መኖሩን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ቢቻልም ይበልጥ ግን ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሊያገለግሉ የሚገባቸው፣ ከየትኛውም የፖለቲካና የግለሰብ ተፅዕኖ ገለልተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው የዴሞክራሲያዊ ተቋማት (የፍትህ አካል የሆኑ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃይሎች፣…) በኢህአዴግ መዳፍ ወድቀው ወገንተኝነታቸው ለፍትህ፣ ለህግና ለህዝቡ ከመሆን ይልቅ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወገንተኛ በመሆናቸው የሀገሪቱን ችግር ይበልጥ ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል፡፡ በዚህም በህግ የተሰጣቸውን መብት የተጠቀሙና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የጠየቁ በርካቶች ወደ ወህኒ ቤት ተወርውረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ጋዜጠኞች(እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፣ የሱፍ ጌታቸው፣…)፣ፖለቲከኞች(አንዱዓለም አራጌ፣ናትናኤል መኮንን፣በቀለ ገርባ፣ኦልባና ሌሊሳ፣…)፣ የኃይማኖት ነፃነት መብት እንዲከበር የጠየቁ (የሙስሊሙ ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ የዋልድባ መነኮሳት፣…) ይገኙበታል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ኢህአዴግ “ለስልጣኔ ያሰጉኛል” በሚል ብቻ በሀገር ስም ክስ ስለመሰረተ ሁሉም ተከሳሾች ወንጀለኛ የሚባሉ ሲሆን በአንፃሩ በኢህአዴግ ባለስልጣናትና አባላት በደል ተፈፅሞባቸው “የፍትህ ያለ” የሚሉ “ፍትህ በኪሴ ብይን” ተሰጥቷቸው በኋላ ወንጀለኛ እንባላለን በሚል በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት በማጣታቸው “የማርያም ጠላት” የሚባሉ በርካቶች ናቸው፤እነኚህንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ የተፈቀዱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ የመሰብሰብ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞን የመግለፅ፣…በሙሉ ባልተፃፈና ባልታወቀ ህግ የተሻሩ ሲሆን ይበልጥ እነኚህ እንዳይተገበሩ ለገዥዎች ብቻ በሚመች ህገመንግስቱን በግልፅ የጣሱ በርካታ አንቀፆችን የያዘ የፀረ ሽብር አዋጅ በማውጣት ተጨማሪ የአፈና ገደቦች ተጠለዋል፡፡ የእነኚህ አፈናዎች ውጤት ችግሮች በጭሩና በቀላሉ እንዳይፈቱ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ እጅግ የታፈነ ቁጣ እንዲኖር አስችሎታል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ወደፊት በሀገሪቱ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግልፅ ቢሆንም ኢህአዴግ በያዘው ግትር አቋም ችግሮች እየተባባሱ ከመሄድ በስተቀር የሀገሪቱን ውስብስብ ችግር ሊፈታ አይችልም፤ምክንያቱም ኢህአዴግ አቅሙም ቁርጠኝነቱም የለውምና፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የታፈኑ ጩኸቶች ድምር ውጤት ድንገት ከፈነዳ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን(ምስራቅ አፍሪካን) ሊያናውጥ ስለሚችል ኢህአዴግና አመራሮቹ ከጭፍንና ግትር አቋም ወጥተው የህዝቡን ጥያቄ ማድመጥና ተገቢውን መልስ መስጠት፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ የተቆለፈበትን ነፃ ፕሬስ በተግባር ላይ እንዲውል ከፍተኛ የሆነ የወረቀት ታክስን ከማስቀረት በተጨማሪ ህዝቢ መረጃ የማግኘት መብቱ ያለምንም ገደብ እንዲከበር ማድረግ፣ ለአፈና የዋሉ ህገወጥ ህጎችን ማሻሻል/መሻር፣1 ለ 5 እያሉ የሚጠቀሙባቸውን ህገወጥ የአፈና መዋቅር መበተንና ማቆም፣ በህገመንግስቱ የተቀመጡ ያወጧቸውን ህጎች በማክበር ለሌሎች አርዓያ በመሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ በባዶ ሜዳ “በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እየሰራሁ ነው…” በሚል የእንቁልልጭ ፈሊጥ የዜጎችን መብት ማዳፈን የዲያቢሎስ የህልም ሩጫ ካልሆነ ለፖለቲካ ፍጆታ ተጀምረው ከመቆም ያለፈ ተፈፃሚ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከምንም ከማንም ቀድሞ መልማት ያለበት የዜጎች ነፃነት የተላበሰ የአስተሳሰብ አድማስ እንጂ ቁስ አይደለም፤ ቁሳዊ ልማቶች ሊሰሩ የሚችሉት በነፃና ጤናማ የዳበረ አስተሳሰብ ባለው የሰው ኃይል ነውና፡፡ ያኔ የምንመኘውና የሚዘመርለት ቁሳዊ ልማትም እውን ይሆናል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፐርቲዎችም ሆኑ ድርጅቶች ከእርስ በርስ መጠላለፍና ከፍርሃት ተላቀው ከቢሮ ፖለቲካ በመውጣት ሰላማዊ ትግል ምን እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ወደህዝቡ መውረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በየቢሮው በሚደረግ የድርጊቶች መቃወሚያ ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ለህዝብና ለሀገር ቆሜያለሁ ማለት ከቀን ቅዥት ባለፈ ጠብ የሚል ነገር ማምጣት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ትግል የተጠና ስልታዊ የተግባር ስራ እንጂ የወንበር ማድመቂያ አይደለምና፡፡ እዚህ ላይ ፖለቲከኞች አምነውበት እችላለሁ ብለው ወደፖለቲካው ትግል እስከገቡ ድረስ በሚከተሉት የትግል ስልት የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻል አለባቸው፤ ካልሆነ ግን ከትግሉ እራሳቸውን ማግለልና ለሚሰራ ሰው መስጠቱ ለፖለቶከኞችም ሆነ ለሀገሪቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን ወደባሰ ችግር ከመሄድ እራሱን ከፍርሃት ድባብ በማውጣት ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመቃወም ከድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋር ባለመተባበር የራሱን እርምጃ በመውሰድ ለመብቱ ሊሎች እንዲቆሙለት ከመጠየቅ ይልቅ ራሱ መታገል አለበት፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እያንዳንዱ ሰው እገሌ ምን ሰራ ከማለት በተጨማሪ እኔ ምን ሰራሁ በሚል ሁሉም የድርሻውን ካልተወጣ የችግሩ ማዕበል ሁሉንም እንደሚያጠቃ እሙን ነው፡፡ አሁን ባለው የመጠባበቅና የማጉረምረም እንዲሁም የመፈራራት ሁኔታ ችግሮችን ከማባባስ ባለፈ የሀገሪቱ ችግር በቀላሉ ይፈታል ማለት የህልም እንጀራ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱ ችግር ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ስለሄደ ሁሉም ዜጋ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊነጋገርና መፍትሄውን በማስቀመጥ ለተግባራዊነቱ ሊተጋ ይገባል፤አለበለዚያ የችግሮቹ መንስኤ ኢህአዴግም ሆነ ተጠቂው ህብረተሰብ ከሚመጣው አስከፊ የፖለቲካ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማምለጥ ስለማይቻል ስለሀገራችን ሁኔታ በግልፅ ሊመከርበትና መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፡፡