የመንዝ ወረዳ ፖሊስ የአንድነት አባላትን አሰረ
በአማራ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አቶ ካሳዬ ዳኜን እና ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ደግሞ አቶ አዲሱ ተመሰለው የተባሉ የአንድነት ለዴሞክራደሲና ለፍትህ (አንድነት) የወረዳው አመራሮች በወረዳው ፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ምንጮቻችን በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ የታሰሩት የአንድነት ፓርቲ አባላት በወረዳው መሐል ሜዳ ከተማ በሚገኘው የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡
በጣቢያው አዛዥ የሆኑት ኢንስፔክተር ጥላሁን ወደስራ ሲሄዱ የተያዙትን ወጣቶች በቢሮአቸው ጠርተው መንግስትን እንለውጣለን ብላችሁ ህዝቡን እያስፈራራችሁ ነው የሚል ውንጀላ ሲያቀርቡባቸው ወጣቶቹ እኛ በሰላማዊ ትግል አስከፊውን የኢህአዴግን ስርዓት በህጋዊ መንገድ ለመቀየር የምንታገል የአንድነት ፓርቲ እንጂ ወንጀለኞች አይደለንም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ታሳሪዎቹ አዎ አባሎቻችንን በወረዳው በህጋዊ መንገድ እያደራጀን ነው ፤ይሄም መብታችን ስለሆነ በግልፅ ነው የምንሰራው እንጂ በድብቅ አይደለም፣ ከዚህ ውጭ ወንጀል ሰርታችኋል የሚል አካል ካለ ክስ ሊመሰርትብንና ሰርታችኋል የሚባል ወንጀልም ካለ በማስረጃ በማቅረብ ወደ ፍርድ ቤት ልትወስዱን ትችላላችሁ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ በመጨረሻም ለአንድ ቀን ካሰሯቸው በኋላ ፖሊስ ጣቢያው ምንም ምክንያት ሳይሰጥና ክስ ሳይመሰርት ለቋቸዋል፡፡
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጥላሁንን በጉዳዩ ዙሪያ ጠይቀናቸው ወጣቶቹ የታሰሩት ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው፣ የታሰሩትም እርስ በርስ በተፈጠረ ጠብ በመሆኑ ለቀናቸዋል፤ ከዛ ውጭ ምንም ዓይነት መረጃ ልሰጥ አልችልም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወጣቶቹ በበኩላቸው ወደስራ ስንሄድ ያዙን እንጂ እኛ ከማንም አልተጣላንም፤ እኛን ሲይዙ የነገሩን ምንግስትን እንቀይራለን ብላችሁ አስፈራራታችኋል ችንጂ ከግለሰብ ጋር ተጣልታችኋል በሚል አይደለም፤ ይሄ ሐሰት ነው፣ ተጣልተዋል የተባሉትንም ግለሰብ ማቅረብ ይችላሉ ሲሉ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡