Daily Archives: September 17th, 2013

መብራት ለኤርትራ በነፃ ከተሰጠ ለእኛስ?

 

ብስራት ወ/ሚካኤል

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመችው በዘመነ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ አባ ሳሙኤል በሚባል ስፍራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ጊዜው በ1890 ዓ.ም. ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከውሃ ኃይል ማመንጨት የተጀመረው ግን በ1904 ዓ.ም. ከአቃቂ ወንዝ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ በአሁን ሰዓት ግን አድጎ በርካታ ግድቦች በአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን ተሰርተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

ከውሃ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ግድቦች እየተሰሩ ቢሆንም የአቅርቦት እጥረትና የጥራት አገልግሎቱ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል፡፡ በተለይ አሁን አሁን መብራት ድንገት የመጥፋቱ ነገር ከምን የተነሳ እንደሆነ እስካሁን ባይገለፅም አዲስ አበባን ጨመሮ በተለያዩ የክልል ከተሞችም በተደጋጋሚ ይቋረጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ተጠቃሚዎች መብራት እንደሚጠፋ በኮርፖሬሽኑ ቀድሞውኑ የተነገራቸው ባለመሆኑ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎች ከጥቅም ውጭ እየሆነ ለወጭ የተዳረጉ ቢኖርም ከድርጅቱ የተሰጠም ሆነ የሚሰጥ ካሳ የለም፡፡ በዚህም የንግድ ተቋማት ሆቴሎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ሱቆች፣…ወዘተ ይገኙበታል፡፡power1

አመራሮቹም ቢሆኑ አልፎ አልፎ ድንገት የመብራት መቋረጥ ችግር ከለኃይል አቅርቦት የተፈጠረ ሳይሆን በቴክኒካል ችግር መሆኑን ሲገልፁ ቢሰማም ችግሩ ግን አሁንም ድረስ እንዳለ አለ፡፡ ተቋሙ ምንም እንኳ ከሀገሪቱ አንጋፋ ተቋማት አንዱ ቢሆንም ከዚህ በፊት ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በኢንቨስትመንቱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ቢጠበቅም በተደጋጋሚ ከሚሰጡ ተመሳሳይ የቴክኒክ ችግር ከሚል መልስ ውጭ የተጠቀሰ ችግር የለም፡፡

በነ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የቦርድ ሊቀመንበርነት፣ በነ አቶ ምህረት ደበበ ዋና ስራ አስፈፃሚነትና እና በነ ብርጋዴር ጄነራል ክንፈ ዳኘው የቦርድ አባልነት የሚመራው ይህ ተቋም በውስጡ 12,172 ሰራተኞችን እንደያዘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ካሉት ሰራተኞች መካከልም በቅርቡ ከአስራ አንድ ያላነሱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በሙስና ተግባር ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ ይገኛል፡፡ እንደ አቃቤ ህግ ክስ ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ ከ 25 ሚሊዮን ዶላር (ከ 471 ሚሊዮን ብር) በላይ የህዝብና የመንግስትን ጥቅም ማሳጣታቸውን ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ የኃይል ማመንጫፕሮጀክቶች እየተመረቁ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለፅም አሁን ለሀገሪቱ ጥቅም እየሰጠ ያለው አቅም ግን ከ2000 ሜጋ ዋት እንደማይበልጥ የተቋሙ የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

ዋና መስሪያ ቤቱን አዲስ አበባ ፒያሳ ደጎል አደባባይ ፊትለፊት ያደረገው ይህ ተቋም እስከ ፊታችን 2009 ዓ.ም. ድረስ የሀገሪቱን የመብራት ኃይል ፍጆታ ወደ 10,000 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ቢያቅድም አሁን በቀሩት አራት ዓመታት ውስጥ ግን ቀሪውን 8,000 ሜጋ ዋት ከየት አምጥቶ ጥቅም ላይ እንደሚያውለው እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ምናልባት የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ከፊታችን በቀሩ 4 ዓመታት ውስጥ ቢጠናቀቅ እንኳ የኃይል ፍጆታውን ሊያሳድገው የሚችለው ወደ 8,000 ሜጋ ዋት ሲሆን ግድቡም ወዲያው አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፣ የግድቡ ውሃ ሙላት በራሱ እረጅም ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ፡፡

በሀገሪቱ ያለውን የኢቨስትመንት ሴክተር ከማስፋፋት አንፃር የመሰረተ ልማቶች በአግባቡ መሟላት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ቢታወቅም የህዝቡ ፍላጎትም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ ከአሁኑ ሌሎች የኃይል አቅርቦት አማራጮችም ካልተወሰዱ ነገ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግር መግጠሙ የማይቀር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ከዚህ በፊቱ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሰራተኛ ቅነሳ በር በመክፈት የስራ አጥ ቁጥርንም አሁን ካለው ከእጥፍ በላይ ሊያሳድግ እንደሚችል ይገመታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ለውጭ ምንዛሪ ሲል የዜጎችን ፍላጎትና አቅርቦት በአግባቡ ሳያሟላ ለጎረቤት ሀገሮች በተለይም ለጅቢቲ 200 ሜጋ ዋት በይፋ መሸጡን መረጃዎች ሲጠቁሙ፣ ለሱዳን 200 ሜጋ ዋት ደግሞ ለመሸጥ የመስመር ዝርጋታው ተጠነቆ ሙከራ ላይ እንዳለ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በቀጣይም መንግስት ለኬንያም 500 ሜጋ ዋት ለመሸጥ ስምምነት ላይ መድረሱ የተጠቆመ ሲሆን ይህ መቼ እና እንዴት እንደሚተገበር ወደፊት አብረን የምናየው ነው፡፡ ምክንያት የአሀገሪቱ የኃይል አቅርቦትና ፍላጎት አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተሟልቷል ማለት አይቻልምና፡፡እንደ መንግስት ከሆነ ግን ወደፊትም ለሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካ የመብራት ኃይልን በመሸጥ ከቡና ንግድ በተሻለ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ማቀዱ አይዘነጋም፡፡ ምክንያቱም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ኢትዮጵያ የነፋስና ከእንፋሎት ኃይል ውጭ ከውሃ ግድብ የሚገኝ ብቻ 45,000 ሜጋ ዋት  የመብራት  ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ያሳያልና፡፡

ከሰሞኑን በተለይ ባለፈው ሐምሌ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በተለያዩ መረጃዎች እንደተገለፀው እና ይህንም የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳህል በለንደን ለኤርትራ ማኀበረሰብ ገለፁት እንደተባለው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራ 250 ሜጋ ዋት የመብራት ኃይል በነፃ ለመስጠት በራሺያ፣ በኳታር እና በቱርክ በኩል ድርድር መጠየቁ ተጠቁሟል፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስት የራሱን ዜጋ ፍላጎት ሳያሟላ ከደሃ ህዝብ አንጡራ ሃብት የሚገነቡ ግድቦችን ለኤርትራ ለምን በነፃ መስጠት እንደተፈለገ እስካሁን አልተገለፀም፡፡ይህ እውን የሚሆን ከሆነ በኢትዮጵያ ህዝብ በጀትና ሃብት እራሷን ችላ እንድትገነጠል የተደረገችው የኤርትራ ዜጎች በነፃ ከሚሰጣቸው የትምህርት ዕድል ተጨማሪ መሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች ዓይነት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት 250 ሜጋ ዋት በነፃ የመብራት ኃይል ለኤርትራ ለመስጠት እንደ ድርድር መነሻ አንስቶታል ስለተባለው ጉዳይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጠይቀናቸው “ውሸት ነው፣ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አላቀረበም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እና በየከተሞቹ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ደስንገት እየጠፋ ስላለው የመብራት መጥፋት እንዲሁም ለጅቡቲና ሱዳን

ተሸጧል ስለተባለው የመብራት ኃይል ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደሆኑት አቶ ምስክር ነጋሽ ጋር ብንደውልም በተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ ነኝ በማለታቸው ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም፡፡መንግስት ለኃይል ማመንጫ ግድቦች መስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት እሰየው ከዚህ በተሻለ ይቀጥል እያልን አሉ በሙባሉ እና ከላይ በተነሱ ችግሮች ዙሪያ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችም ሆኑ ሌላ የሚመለከተው አካል ምላሽ ለመስጠት ቢፈልግ የዝግጅት ክፍሉ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በተደጋጋሚ ድንገት የመብራት መጥፋት በንብረትም ሆነ በዕለታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እየፈጠረ ያለውን ችግር ምንነት እስካሁን ከሚመለከተው አካል የተሰጠ ምላሽ ባለመኖሩ በኃይል አቅርቦትና አገልግሎት ላይ ነገ ምን ሊከሰት እንደ ሚችል ለመተንበይም ሆነ ለመዘጋጀት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ እዚህ ላይ ኮርፖሬሽኑም ሆነ ሌላ የሚመለከተው የመንግስት አካል ከወዲሁ ለደንበኞቻቸው የቅድመ ማስጠንቀቂያም ይሁን የእርምት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ መጠቆም እወዳለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስት የመብራት ኃይልን ለውጭ ምንዛሪ መሸጥ እንኳ ቢፈልግ ቅድሚያ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በአግባቡ መሸፈን ያለበት ይመስለኛል፡፡

 

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ማብዛት ምን ይፈይድላቸዋል?

 

ብስራት ወ/ሚካኤል

የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ግብዓተ መሬት ከተፈፀመ በኋላ በእግራቸው የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሀገሪቱን የስልጣን መሪ እየዘወሩ ይገኛሉ፡፡ ምንመ እንኳ በህግ ሙሉ ስልጣን የተሰጣቸው ቢሆንም በፓርቲያቸው ይሁን አሊያም በራሳቸው ፈቃድ የስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ እየሸረሸሩት የሚገኙ ይመስላል፡፡ ለዚህም መንበረ ስልጣናቸውን በይፋ ከተረከቡ በኋላ የብአዴኑን አቶ ደመቀ መኮንንን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሾመው አፀድቀዋል፡፡ በመቀጠልም በትናው የመንግስት መዋቅርና በየትኛው የህግ አግባብ እንደሆነ እስካሁን ባይታወቅም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ በሚል የኦህዴዱን አቶ ሙክታር ከደርን የመልካም አስተዳደርና የሲቭል ሰርቪስ እንዲሁም የህወሓቱን ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የኢህአዴግ ዋነኞቹ አራቱ ድርጅቶች መካከል ከደቡብ ደኢህዴን ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከአማራው ብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከኦሮሞው ኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙክታር ከድር እና ከህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የስልጣን መዘውሩን ይዘውታል፡፡ ይህ የሚያሳየው የስልጣን ቅርምቱ በኮታ እንደሆነ እና በመካከላቸው የስልጣን ሽኩቻ እንዳለ፤ አቶ ኃይለማርምም በህግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የመወሰን አቅማቸው የመነመነ መሆኑን ነው፡፡ ሌሎች አጋር ተብለው የሚጠሩት የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የቤኒሻንጉልና የጋምቤላ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደሮች ከታች ሆነው ትዕዛዝ ለመቀበልና ለማስፈፀም ብቻ ዝግጁ እንዲሆኑ በተጠንቀቅ ላይ ጠብቁ የተባሉ ይመስላሉ፡፡

አቶ መለስ በህይወት ባሉ ሰዓት ብቻቸውን የስልጣን ማማው ላይ ሲጋልቡ ከሚኒስትሮች በተጨማሪ በሚኒስትርነት ማዕረግ አማካሪዎች እና ዳይሬክተሮችን ሾመው ነበር፡፡ያኔ በሚኒስትርነት ማዕረግ አማካሪ አድርገው ከሾሟቸው መካከል ዶ/ር ፋሲል ናሆም ህግ፣ አቶ ንዋይ ገ/አብ የኢኮኖሚ፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን የማኀበራዊ፣አቶ አርከበ እቁባይ የኢኮኖሚና ትራንስፎርሜሽን እና ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ሁሉን ነገር  በራሳቸው ፍላጎት እና አካሄድ ከመከወን በቀር ሰውየው ምክር ይቀበላሉ ተብሎ ባይታመንም፡፡

hail

በአሁን ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ አማካሪ አድርገው ከሾሟቸው መካከል አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና በአዲስ መልክ እንደተቋቋመ የሚነገርለት የፕላንና ኮሚሽን ሚኒስትር አቶ መኮንን ማንያዘዋል አዳዲሶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞዎቹ አቶ ፀጋዬ በርሄ(የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነት አማካሪ)፣ አቶ አባይ ፀሐዬ (የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ)፣ ዶ/ር ፋሲል ናሆም(የህግ ጉዳይ አማካሪ)፣፣ አቶ ንዋይ ገ/አብ(የኢኮኖሞ ጉዳይ አማካሪ)፣ አቶ አርከበ እቁባይ(የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አማካሪ)፣ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ(እስካሁን የስራ ድርሻቸው አይታወቅም፤ግን አማካሪ) በይፋ ተነስተዋል እስካልተባሉ ድረስ አሁንም አማካሪዎቻቸው ናቸው፡፡

ምንም እንኳ አቶ ሬድዋን ከአማካሪነት ተነስተው በአቶ በረከት ስምዖን ቦታ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ተደርገው ቢሾሙም አቶ በረከት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ተደርገው ተሸመዋል፡፡

በዚህም መሰረት አቶ ኃለማርም ደሳለኝ 3 ምክትሎች ጠቅላይ ሚኒስትሮችን እና 7 አማካሪዎችን በብዛት በመሾም ሪከርድ እየሰበሩ ይገኛሉ፡፡ አመራራቸውም በአቶ ኃይለማርያም በበላይነት ሳይሆን በቡድን እየተከናወነ መሆኑን አመላካች ነገሮች ይጠቁሟሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአማካሪዎቻቸው ብዛት ምናልባትም ከምክር ይልቅ ከፍርሃት ስነ ልቦና ጫና አሊያም ፓርቲው በብቃትና በአግባቡ ይመራሉ የሚል እምነት አጥቶባቸው በአስገዳጅ ሁኔታም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ስለዚህ ከአቶ ኃይለማርም ፖለቲካ አስተላለፍ ለውጥ (political reformation) ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም እስካሁን ከቀድሞው ሟቹ  ጠቅላይ ሚኒስትር በአሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማየት አልተቻለም፤ በአንድ ጀምበር ለውጥ ይመጣል ተብሎ ባጠበቅም፡፡

በርግጥ የአማካሪ መኖርና ምክርንም በአግባቡ አመዛዝኖ የሚጠቅመውን ተቀብሎ ስራ ላይ ማዋል ጥሩ ቢሆንም ከብዛታቸው አንፃር በስነ ልቦና አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ግን አያጠያይቅም፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ካሉባት በርካታ ውስብስብ ችግሮች አንፃር የፖለቲካ አስተላለፍ ለውጥን ጨምሮ የፖሊስ አሊያም የስርዓት ለውጥ ካልመጣ በአማካሪ ብዛት ብቻ ወደ ተሸለ ደረጃ መሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ ፖለቲካ፣ የመኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንስኤው ስርዓቱ በመሆኑ፡፡

ምናልባት አቶ ኃይለማርያም ችግሮችን ለመቅረፍ የማኀበራዊና ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጥ ላድርግ ቢሉ በኢህአዴግ አሰራር የፓርቲው የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የውሳኔ ሰጭው የበላይ አካል የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህዴግም ሆነ መሪው አቶ ኃይለማርያም እንደማያደርጉት አስቀድመው ስለተናገሩ ከፓርቲው መፍረክረክ በስተቀር አሁን ባለው ሂደት የባሰ ካልሆነ የተሻለ ለውጥ ሊኖር አይችልም፡፡

ከዶ/ር ፋሲል ናሆም በስተቀር አማካሪዎቻቸውም ሆኑ ምክትሎቻቸው ከሙያ ብቃትና ልምድ ይልቅ በፖለቲካ ወገንተኝነት የተሰበሰቡ አጀቦች በመሆናቸው ይሄ ነው ሚባል የተለየ መልካም ነገር እንዳይጠበቅ ከማድረጋቸው በተጨማሪ በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ከአንድ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ወንዝ የተቀዱ ናቸውና፡፡ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለ ደግሞ የራሱ የኢህአዴግ አባላት (ተገደው ለስራ ቅጥርና ለማዳበሪያ አባል የሆኑትን ሳይጨምር) የሀገሪቱን ነባራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በማጤን የመሻሻያ ለውጥ እንዲደረግ ደፍረው መጠየቅ ከቻሉ የበላይ አመራሮቹ እንዲነቁ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ አመራሮቹ በተናጥል ከኢህአዴግ አባልነት እራሳቸውን እያገለሉ አሊያም ለበላዮቹ ፍፁም ተገዥ በመሆን እንዲቀጥሉ ቢፈቅዱ “ከኑግ ያለህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” አይነት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡

 

ስለዚህ አሁን ያለውን የአቶ ኃይለማርያምን አስተዳደር ወደ ተሸለና ቀና ጎዳና ለመውሰድ የኢህአዴግ የፖለቲካ ለውጥ (political reformation) ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢህአዴግ በሟቹ አቶ መለስ ጥላና መንፈስ ካልሆነ በስተቀር አይቻልም የተባለ ይመስል አመራሮቹ ተረጋግተው ለመምራት የተዘጋጁ አይመስሉም፡፡ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውሳኔ በሚቸገሩበት ሁኔታ ምክትልና አማካሪ ማብዛታቸው የስነ ልቦና ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡ እስካሁን ከሚታየው ሁኔታ እንኳ ተነስተን የነገውን ካሰብን የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክትሎች፣ አማካሪዎችን በሚኒስትርነት ማዕረግ ሹመት በእስካሁኑ የሚያበቃ አይመስልም፡፡

የሹመት አሰጣጣቸውም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እና የመሪነትም ሆነ የሚያ ብቃትን መሰረት ከማድረግ ይልቅ አንችም እንዳይከፋሽ፣ከጠበሉ ቅመሽ ይይነት ነገር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ነገ ከራሳቸው ከኢህአዴግ አልፎ በሀገሪቱ ላይ የሚያመጣው መዘዝ ቀላል ነው አይባልም፡፡ ምክንያቱም መሪ ስልጣንን ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አስቀድሞ ግላዊና ቡድናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ከተዘፈቀ ቀጣዩ ሂደት የስልጣን ሹክቻ ይሆናልና፣ ቢረጋጉ ሳይሻል አይቀርም፡፡

 

 

 

 

 

 

የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ እና የህገመንግስቱ ተቃርኖ

ብስራት ወ/ሚካኤል

ህገመንግስት በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር የህግ የበላይነት ይሰፍን ዘንድ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ሆኖ የሚያገለግል ሰነድ ነው፡፡ ይህ ህግ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ዓይን ከህግ በታች አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የህግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ለህግ የበላይነት መከበር ደግሞ የመንግስት ተቋማት ህዝባዊ አመኔታ ሲኖራቸውና ለህዝቡና ለሀገሪቱ ጥቅም የቆመ የመንግስት አስተዳደር ሲኖር ብቻ ነው፡፡

የህግ የበላይነት ከሌለ አንድ ህገ-መንግስት የቱንም ያህል ጥሩ ሐሳቦችን ያዘለ የመብት ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ የሚችሉ ቃላት ቢኖሩት እንኳ ተግባራዊ ሊደረግ ካልቻለ ዋጋ የለውም፡፡ በተለይ የህገመንግስት የበላይነት ካልተከበረ የመንግስት ለህዝብ ያለው ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከመግባቱም አልፎ ጥቂት ግለሰቦች የበላይነት ብቻ ከህግ በላይ ሆነው ዜጎችን እንዲጨቁኑ በር ይከፍታል፡፡

የህግ የበላይነት አለመከበር ደግሞ በዜጎች መካከል አድሏዊነትና የፍትህ መጓደልን ስለሚያስከትል ዜጎችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስዳቸዋል፡፡ ይህም በሀገር ላይ ስርዓት አልበኝነትን ከማስፈኑ በተጨማሪ የመንግስት የፍትህ ተቋማት በህብረተሰቡ ግብር የጥቂት ባለስልጣናትና ሃብታሞች የጥበቃ ተቋም በመሆን የሆዳቸው ባሪያ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የውጭ ኃይሎች በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ሁለንተናዊ ጥቅም ላይ ጣልቃ እንዲገቡ አዝና ለአደጋ እንዲያጋልጡ ዕድል መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው እንዳይሆን ደግሞ ህገ መንስቱን መሰረት በማድረግ ለዜጎች ከለላና ጥበቃ ሊያደርግ የሚችል አዋጅ ለወጣ ይችላል፡፡ ህገመንግስቱ በአዋጅ እስካልተሻሻለ ድረስ አዋጅ ደግሞ በምንም መልኩ ከህገመንግስቱ ጋር የሚቃረን አንቀጽም ሆነ አንዲት ቃል ሊኖር አይገባውም፡፡ ከህገመንግስቱ ሐሳቦችና አንቀፆች ጋር የሚጋጭ ሓሳብም ሆነ አንቀጽ በአዋጁ ላይ ካለ የህግ የበላይነት ሊኖር አይችልም፡፡

      ኢትዮጵያና ህገመንግስቷ

ኢትዮጵያም እንደማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የራሷ ህገመንግስት አላት፡፡ ወጥ የሆነ የተፃፈ የህገመንግስት ሰነድ መጠቀምና በዚህም መተዳደር የጀመረችው ከዘመነ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ስላሴ፣ በዘመነ ደርግ (የኢህዴሪ ህገመንግስት) እና አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት መንግስት የሀገሪቱን ህዝብ የሚመራበትም ሆነ የሚያስተዳድርበት ሰነድ ከመሆኑ በተጨማሪ ከአድሏዊነት በፀዳ መልኩ የዜጎችን መብትና ጥቅም አክብሮ ማስከበር የሚያማስጠበቅበት ገዥ ሰነድ ነው፡፡ const

ይህን ሰነድ ገዥውን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች አክብረው የሚያስከብሩበትም ጭምር እንጂ የጥቂት ግለሰቦች አሊያም ስራ አስፈፃሚ ባለስልጣናት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ የትኛውም ህግም ሆነ ሰነድ ለሁሉም ሰው ምሉዕ እና ፍፁም ምርጥ ነው የሚባል ባይኖርም የሚሻሻሉ ህጎች በህግ አግባብ እስኪሻሻሉ ድረስ ሁሉም ሰው በእኩል ላለው ህገመንግስት ተገዥ የመሆንና የማክበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህም በህገመንግቱ አዋጅ ቁጥር 1/1987 የህገ መንግስት የበላይነት በሚለው ስር አንቀጽ 9(2) ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ማንኛውም አዋጅ፣ ደንብና መመሪያም ሆነ ትዕዛዝ ከህገመንግስቱ የበላይ ሊሆኑ እንደማይችሉ ያሳያል፡፡ ይህም ማለት የትኛውም አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ተፈፃሚነት ሊኖራቸው የሚችለው የህገ መንግስት ጥሰት ከሌለባቸውና ህገ መንግስቱን ተንተርሰው ከወጡ ብቻ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ተግባራዊ ሊሆኑ እንደማይችሉ እና ሊሆኑም እንደማይገባ በግልፅ ተቀምጧልና፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9(1) ላይ “ህገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው፡፡ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፤ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡” ይላል፡፡ ነገር ግን ይህን ህገመንግስት የሚጥሱ በርካታ አንቀፆች እንዳሉት የሚነገርለት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ የህገመንግስት ጥሰት አለበት በሚል ከሚነሱት መካከል ጥቂቶቹን እንይ፡፡

  የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ  እና ህገ መንግስቱ

ሽብርተኝነት በምንም መመዘኛ በማንነኛውም ሰው ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ድርጊቱም የግለሰብን፣ የማኀበረሰብን፣ የህዝብንና የሀገርን ብሎም የዓለምን ህዝብ ህይወትና ንብረት አደጋ ላይ የሚጥል አሰቃቂ ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር በግለሰብ፣ በቡድን እና በህጋዊነት ጥላ ስር ባሉ የመንግስት ባለስልጣናት ሊፈፀም የሚችል የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ ድርጊቱም አካል ማጉደልን፣ ንብረት ማውደምን ፣ ጤናን ማቃወስን እና የህዝብን ኑሮ ማናጋትን እንደሚጨምር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ያለችበት ቀጠና ለሽብር ተግባር ተጋለጠ ቢሆንም እጅግ ተመራጭ የሆነ የህገመንግስት ጥሰት የሌለበት የቆየ እና እየሰራ ያለ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቢኖራትም በገዥው ኢህአዴግ አማካኝነት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አውጥታ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከገዥው በኩል አዋጁ የወጣው የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ለመጠበቅ ነው ቢባልም በህግ ባለሙያዎች፣ በፖለቲከኞች፣ በጋዜጠኞች እና በበርካታ ሌሎች ዜጎች አዋጁ የህገ መንግስ ጥሰት ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ለማፈን እና የኢህአዴግ ሹማምንትን ስልጣን ለማራዘም ነው በሚል ተቃውሞ ቀርቦበታል፤ እየቀረበበትም ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በህገመንግስቱ አንቀጽ 55(1) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በሚለው ስር “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ህገ መንግስት መሰረት ለፌደራሉ መንግስት በተሰጠው የስልጣን ክልል ህጎችን ያወጣል፡፡” ይላል፡፡ አዋጁም በዚህ መሰረት ከመውጣቱ በስተቀር ህገ መንግስቱን የሚጥስም ቢሆን ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚገልፅ ድንጋጌን አያሳይም፡፡ ስለሆነም አዋጁ መውጣት የነበረበት ህገመንግስቱን መሰረት አድርጎ እንጂ ከህገመንግስቱ ተቃርኖ ያላቸው ድንጋጌዎችን ማውጣት አይችልም፤ ቢወጣ እንኳ ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደማይችል እራሱ ህገ መንግስቱ ያስቀምጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ታዋቂው የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ አሁን መንግስት እየተጠቀመበት ያለው የፀረ-ሽብርተኝነት የህግ ካሉት የህገመንግስት ጥሰቶች በተጨማሪ ሁሉም የወንጀል ድርጊቶች የሀገራችን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ ስለተጠቀሱ አስፈላጊነቱ አይታየኝም ይላሉ፡፡ይሄንንም ሐሳብ አንድነት ፓርቲ እና አመራሮቹም በተደጋጋሚ ሲገልፁት ይሰማል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(መድረክ) ቀደም ባሉት ጊዜያት ሁሉ አዋጁ የኢህአዴግን ለረጅም ጊዜ በስልጣን ለመቆየት ከለላ በመሆን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችን ለማፈን ሆን ተብሎ እንደወጣ ሲቃወሙ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ እውን ህገመንግስቱን ጥሷል? ወይስ  አልጣሰም? የሚለውን መረዳት እንዲያስችል ጥቂት አንቀፆችን እንመልክት፡፡

ህገመንግስቱ አንቀጽ 26(1) የግል ህይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት በሚለው ስር “ማንኛውም ሰው የግል ህይወቱ፣ግላዊነቱ፣የመከበር መብት አለው፡፡ ይህ መብት መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ፣ ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረቱ ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል፡፡” ይላል፡፡

ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 21 ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ በሚለው ስር ደግሞ  “ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጽሑፉን፣የጣት አሻራውን፣ ፎቶግራፉን፣ የጸጉሩን፣ የድምፁን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን( የዘር ፈሳሽን ሊጨምር ይችላል)፤ ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ (ለተጠርጣሪው ጤንነት አይደለም) ሊያዝ ይችላል፡፡ ተጠርጣሪው ለምርመራው ፈቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ኃይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል፡፡” ይላል፡፡ በዚህ ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ  መሰረት  ፖሊስ አቅሙ በፈቀደ ደብድቦ ማሳመን ባይችል እንኳ በእጁ ባለ በጦር መሳሪያ በመታገዝ በሚወስደው እርምጃ የተጠርጣሪውን በህገመንግስቱ የአካል ደህንነት እና ግላዊ ህይወቱ የመጠበቅ መብትን በመግፈፍ አካል ጉዳተኛ እንዲያደርግ ሁሉ እድል ይሰጣዋል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው ከተከሰሰበት ወንጀል ነፃ ተብሎ ቢለቀቅ እንኳ በፖሊስ በተፈፀመበት የኃይል እርምጃ ጤነኛው ሰው አካል ጉዳተኛ ሆኖ ይወጣል ማለት ነው፤ ለዚህ ደግሞ የጉዳት ካሳም ሆነ ይቅርታ የለውም፡፡

ሌላው በህገመንግስቱ አንቀጽ 26(2) ማንኛውም ሰው በግል የሚፅፋቸውና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሚኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29(1-2) የአመለካከትና እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት በሚለው ስር “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለፅ ነፃት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሑፍ ወይም በህትመት፤ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡” ይላል፡፡

ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 14(ሀ-ሐ) መረጃ ስለማሰባሰብ  በሚለው ስር ደግሞ “በሽብርትኝነት የተጠረጠረን ሰው(የተፈረደበት አይልም) የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬዲዮ፣ የኢንተርኔት፣የኤሌክትሮኒክስ፣የፖስታና የመሳሰሉ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል ፤ ጠለፋውን ለማስፈፀም ወደ ማናቸውም ቤት ውስጥ በሚስጥር ለመግባት (የመንደር ሌቦች ተግባር ዓይነት)፤ይህንኑ ለመፈፀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ ወይም ለማንሳት፤ ይችላል፡፡” ይላል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት ደግሞ ዜጎች ከላይ በተጠቀሰው በህገ መንግስቱ መረጃ የማግኘት፣ የመቀበልና የማሰራጨት መብትን ጨምሮ የፈለጉትን አመለካከት ይዘው በፈለጉት የመረጃ ማሰራጫ ዘዴ ሐሳባቸውን እንዲገልፁ የተደነገገውን መብት በግልፅ ይጥሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚለዋወጣቸው መረጃዎች በሙሉ እንዲጠለፉ፣ በቤተሰብ መካከል የሚደረግ ጨዋታና ሌሎች የፆታዊ ፍቅር ግንኙነቶች ጭምር በደህንነት ኃይሎች መሳሪያ እንዲቀረፁ እና የግል ምስጢር በቀላሉ እንዲባክን በማድረግ ተፈጥሯዊና ከላይ የተጠቀሰውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ አንቀጽ 26(2) እና 29(1-2) ጋር በግልፅ ይቃረናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት መብትንም እንዲሁ የሚገድብ እንደሆነ ይነገራል፡፡

     የአዋጁ  መኖር ለህዝቡ ምን ጠቀመ?

በስራ ላይ የዋለው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖው ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ በአዋጁ ስም በዋነኝነትም በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዳይከበርና የገዥው አመራሮች እንዳሻቸው እንዲናኙ ዕድል ሰጥቷል በሚል ውግዘት እየገጠመው ነው፡፡ በዋነኝነት ደግሞ የህገ መንግስት ጥሰት ስላለበት ተፈፃሚ መሆኑ በራሱ ህገወጥ ነው የሚሉ የህግ ባለሙያዎችም አልታጡም፡፡ከዚህም በተጨማሪ ገዥዎች ዜጎችን ፈሪ በማድረግና በማሸማቀቅ በራሳቸውም ሆነ በሀገራቸው ጉዳይ ጉልህ ሚና እንዳይጫወቱ በማድረግ የወደፊት የሀገሪቱን ደህንነትና አንድነት ይንዳል ሲሉ የሰጉም አልጠፉም፡፡ anti...terror

ከላይ እንዳየነው ከሆነ ደግሞ ጎልቶ የሚታይ የህገ መንግስት ጥሰት እንዳለ ያሳያል፡፡ ህገ መንግስቱን የሚጥስ ህግ ያወጡ፣ የተረጎሙና ያስፈፀሙ አካላት ሁሉ ህገ መንግስቱን እንደናዱ ይቆጠራል፡፡ ይሄ ደግሞ በሀገሪቱ ከፍተኛውን የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የሚያስቀጣ ቢሆንም በዚህ የተቀጣ ህጉን አውጥቶ ያፀደቀው የፓርላማ አባል፣ አዋጁን ተንተርሶ ውሳኔ የሰጠ (የፈረደ) ዳኛ፣ አዋጁን ተንተርሶ ክስ ያቀረበ አቃቤ ህግ፣ አስፈፃሚው ፖሊስ፣ሚኒስትርና ጠቅላይ ሚኒስትር የለም፡፡ ይልቁንም አዋጁ ህገመንግስታዊ መብቶችን የሚጥስ በመሆኑም የህገመንግስት ጥሰት ነው በሚል ሲቃወሙ የነበሩና በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን መብት ሲጠቀሙ በአዋጁ ወንጀል ናቸው በሚል ለእስር፣እንግልትና ስቃይ እንዲሁም ለስደት የሚዳረጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየተበራከተ እንደሚገኝ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች እንደሚገኙበት ይጠቀሳል፡፡

አዋጁ የዜጎችን ሰላምና ደህንነትን ለመጠበቅ ነው ቢባልም እስካሁን በአዋጁ የቅጣት ሰለባ የሆኑት ኢትዮጰረያውያን እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከውጭ ዜጎች ሁለት ሲውድናውያን ጋዜጠኖች የእስር ሰለባ ቢሆኑም በስውዲን መንግስትና በአውሮፓ ህብረት ጫና ከአንድ ዓመት እስር ቆይት በኋላ በይቅርታ ተለቀው ወደ ሀገራቸው ሲገቡ በተመሳሳይ ወቅት ታስሮ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ የይቅርታ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን በእስር መማቀቁ ህጉ ዜጎችን ለማፈን የወጣ ነው በሚል በአስረጂነት መቅረቡ አሌ አያስብለውም፡፡

መንግስት እስካሁን ጠረጠርኳቸው ያላቸውን ገና ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ሳይበይንባቸው አሸባሪዎች በሚል በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን መስኮት ቢናገርም የሚከሳቸው ሰዎች ፈፀሙት የተባለውን የሽብር ተግባር ግን በግልፅ ሊያሳይ አልቻለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተከሰሱት ሰዎች በሀገሪቱ በተለያየ መስክ በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው በመታየታቸው መንግስት በተለይም ገዥው ኢህአዴግ የራሱን የስልጣን ስጋት የሀገር ስጋት አድርጎ ከማቅረቡ ውጭ እስካሁን አሳማኝ ነገር አለማቅረቡ መንግስት በህዝቡ ዘንድ እምነት እንዲያጣ አስችሎታል በሚል እየተብጠለጠለ ይገኛል፡፡ ስለሆነም አዋጁ ለህዝቡ ጠቅሟል የሚባል ተጨባጭ ነገር ባይታይም ዜጎችን በፍርሃት ድባብ ውስጥ ከትቶ በማሸማቀቅ፣ ለእስርና እንግልት በመዳረግ ጉዳቱ በግልፅ ይታያል፡፡

ለአብነትም በነ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ ላይ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት “አኬልዳማ “በሚል ዘጋቢ ፊልም የ1984/85 ዓ.ም. ኢህአዴግና ኦነግ ሀገሪቱን በጋራ ሲያስተዳድሩ የተፈፀመን ወንጀል በወቅቱ ያልነበሩትን እነ አንዱዓለምን አያይዞ በማቅረቡ እና በቅርቡ ደግሞ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮቴዎች ጋር በማያያዝ “ጅሃዳዊ ሃረካት” በሚል የግብፅና የሌሎች መካከለኛ ምስራቅ ሀገሮችን ድርጊት በማሳየቱ የበለጠ መንግስት ተዓማኒነት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ እስካሁንም ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች( አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣…) ፤ ከጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙና የሱፍ ጌታቸው፣… ከኃይማኖት አባቶችና የኃይማኖት ነፃነት ይከበር ከሚሉት መካከል የዋልድባ ገዳም መነኮሳትና የሙስሊሙ ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ ከዩኒቨርስቲ ተማሪና ወጣቶች መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሴና መረራ፣ ይገኙበታል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የህገ መንግስት ጥሰት ነው፣ አዋጁ ሰለባ ያደረገውም ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎችን በመሆኑ ሊዘረዝ ይገባዋል ሲል ፒቲሽን እያስፈረመ ይገኛል፡፡ ከ4 ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን  ድርጅት በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ዙሪያ የኢህአዴግ፣ የመድረክ፣ የአንድነት/መድረክ፣ የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮችን በቴሌቪዥን መስኮት አወያይቶ ነበር፡፡ ውይይቱ ይብዛም ይነስም የኢህአዴግን ዜጎችን አምታቶ ለመኖር ያለውን ምኞት በግልፅ ያሳየ ይመስላል፡፡ነገር ግን በአዋጁ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለማካተት ቢሞከር ጥሩ ቢሆንም፤ አልተደረገም፡፡ አሁንም ቢሆን አዋጁ ዜጎችን በማፈን የኢህአዴግን ያለአግባብ ስልጣን ለማራዘም ካልሆነ እስካሁን ይሄ ነው የሚባል ጠቀሜታ ሊታይ አልቻለም፡፡

%d bloggers like this: