Daily Archives: March 19th, 2014

በሐረር የተከሰተው ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ጥያቄ ማስነሳቱን ቀጥሏል

 

በታሪካዊቷ ሐረር ከተማ ባለፈው ካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. በሸዋበር የንግድ ሱቆች ላይ በተደጋጋሚ የደርሰው የእሳት አደጋ የከተማው ነዋሪና የአካባቢው የንግድ ማኀበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ በመፍጠሩ ጥያቄ ማስነሳቱ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶስት ጊዜ ሱቆቻቸው የተቃጠለባቸው እና አሁንም ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረጉም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የከተማው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በተደጋጋሚ ስለሚነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት አደጋው የደረሰባቸው መንግስት ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም በሚል ሰልፍ ከመውጣታቸው ጋር ተያይዞ መንግስት አደጋው ለደረሰባቸው ነጋዴዎች ምን እንዳሰበ በጋዜጠኛ ተጠይቀው፤ ሰልፍ የወጡት የጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው፣እርምጃ እንወስድባቸዋለን ማለታቸው ይበልጥ ቁጣመቀስቀሱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳ እስካሁን የእሳት አደጋው መንስኤ ተጣርቶ ይፋ ባይሆንም እንደምንጮች ገለፃ ከሆነ ከተፈጠረው እሳት አደጋ ጀርባ የመንግስት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም በሚል የህዝብ ግንኙነቷን መልስ ዋቢ በማድረግ ነዋሪዎቹ ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡hara

በከተማው የንግድ ሱቆች ላይ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ስላለው የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ የጠየቅናቸው አቶ አብዱላሂ እንዳሉት ከሆነ፤ አደጋውን የክልሉ ባለስልጣናት ሆን ብለው እንዳደረጉትና መሬቱን ለራሳቸው ሰዎች ለመስጠት አስበው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ያስቀጠረችና እና በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበች ታሪካዊ ከተማ ያውም በንግድ ሱቆች ላይ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ መከሰቱ ከመንግስት ሌላ እጅ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፣ ይህም በከተማው ወደፊት ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ዜጎችንም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች የሚያበራታታ አይደለም ብለዋል፡፡har

በአደጋው እስካሁን በቁጥር ተለይቶ ባይታወቅም እጅግብዙ ንብረቶች መውደማቸውም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙራድ አብዱላሂ በአደጋው ንብረቶቻቸው ለወደመባቸው ነጋዴዎች መንግስት በጀት መመደቡን ማስታወቃቸው የተነገረ ሲሆን፤ አንዳንድ ነጋዴዎች ግን ስለተግባራዊነት ጥርጣሬ እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡

በሆሳዕና ከተማ የመብራት ኃይል ገመድ ተበጥሶ የሰው ህይወት አጠፋ

 

power1በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ የኤልክትሪክ ገመድ ተበጥሶ የ13 ዓመት ልጅ ህይወት ማጥፋቱ ተገለፀ፡፡ አደጋው የደረሰው በጎፈር ሜዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ቦቢቾ በተባለ ቀበሌ ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ለረጅም ጊዜ ምሰሶው ሊወድቅ የደረሰ የኤሌክትሪክ ገመድ ተበጥሶ አንድ የ13 ዓመት ልጅ ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ሳለ በደረሰ አደጋ ወዲያው ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡ hossana

አዲስሚዲያ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት ከሆነ ምሰሶው በመንገድ ጥገና ቁፋሮ ምክንያት በመላላቱ የኤሌክትሪክ ገመዱ ረግቦ እንደነበርና ይህንንም በመፍራት በተደጋጋሚ ለከተማው መስተዳደርና በከተማው ለሚገኝ የመብራት ኃይል ዲስትሪክት ቅሬታ ቢያቀርቡም ሰሚ ባለማግኘታቸው አደጋው መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ ከሟቹ ልጅ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ላደረሰው የቸልተኝነት አደጋ ምን ምላሽ እንዳለው ለማጣራት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደ ሆኑት አቶ ምስክር ነጋሽ ደውለን ለማጣራት ብንሞክርም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡

አንድነት እና መኢአድ የፊታችን ሐሙስ ውህደት ሊፈራረሙ ነው

 

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ነገ ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ቅድመ ውህደት ሊፈራረሙ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ እስካሁን በተናጠል የሚደረገው ፖለቲካ ትግል ለሀገሪቱም ሆነ ለህዝቧ እንዲሁም ለራሳቸው አዋጭ አለመሆኑን በማመን ተዋህደው አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ማኀበር መስርቶ ለመታገል የሚያስችላቸውን ስምምነት በመጨረስ ቅድመ ውህደቱን ለመፈራረም ቀነ ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ዋናው የውህደት ስምምነት የሚጠናቀቀው የሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ተደርጎ ሲፀድቅ ሲሆን፤ከዚህ ቀደም የሁለቱም ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ውህደቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ውሳኔ ማሳለፋቸው አይዘነጋም፡፡ በዚህም ምክንያት ስምምነቱ ተጠናቆ የፊታችን ሐሙስ ድርድሩን ሲያካሂዱ የነበሩት አካላትና የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት የአንድነት ፓርቲ ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው እና የመኢአድ ፕሬዘዳንት አቶ አበባው መሐሪ ፓርቲያቸውን በመወከል ስምምነቱን እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፡፡udj

ሁለቱም ፓርቲዎች የፕሮግራም ልዩነት እንደሌላቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይ አንድነት ፓርቲ ከዚህ ቀደም ከብርሃን ፓርቲ ጋር በመዋሃድ በፖለቲካው እንቅስቃሴ ለውጥ መፍጠር ችሏል፡፡ አሁን ደግሞ ከመኢአድ ጋር በመዋሃድ ጠንካራ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ አንድነት ከመኢአድ በተጨማሪ ከሌሎችም ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፍጠር አንድ ግብረኃይል በማቋቋም ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑንና በቅርቡም ሌሎች ፓርቲዎችም አብረውት ሊዋሃዱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አንድነት ከመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር በግንባር ተጣምሮ እስካሁን ቢቆይም በአባላቱ የሚጠበቀው ለውጥ ባለመምጣቱ ውህደት ላይ ማተኮሩ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚመለክተው ከሆነ፤ በአሁን ወቅት ተመዝግበው የእውቅና ሰርተፍኬት የተሰጣቸው 66 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከአራት ፓርቲዎች ውጭ ሌሎቹ ከምርጫ ወቅት በስተቀር የት እንዳሉና ምን እየሰሩ እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝቡ በተለያየ ጊዜ በጥቂቱም ቢሆን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከተናጥል ይልቅ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ሆነው እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወሳል፡፡