ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ወደብ

ብስራት ወልደሚካኤል
Afrosonb@gmail.com

አንድ መንግስት ዛሬ በሚሰራው ሁሉ ነገንም ያስባል፤ኢትዮጵያ ግን ለዚህ የታደለች አትመስልም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ላለፉት 23 ዓመታት ከተከናወኑ በርካታ ዘመን እና ታሪክ አይሽሬ ስህተቶች መካከል የሰሞኑን የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ስምምነትን ማየት በቂ ነው፡፡ ስምምነቱ በየትኛውም ዓለም ያሉ ሀገሮች ያልተፈፀመ እና ሊፈፀም የማይችል በኢትዮጵያ ግን እውን ሆኗል፤እስካሁን ምክንያቱ በግልፅ ባይታወቅም፡፡

ገዥው ስርዓት ለህዝቡ ቃል የገባውን ላለመፈፀሙ በተደጋጋሚ ከሚገልፃቸው ቃላቶች እና ምክንያቶች መካከል የአፈፃፀም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብኝም የሚለው ነው፡፡ እውነታው ግን ከሚናገረው በተቃራኒ የፖሊሲ እና የአፈፃፀም ችግር ይስተዋልበታል፡፡ በመጀመሪያ ፖሊሲ ሲነደፍ የሀገሪቱን አቅም፣ ፍላጎት፣ ነባራዊ ሁኔታ፣ የህዝቡ ፍላጎትና አኗኗር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የዜጎችን እነ የሀገሪቱን ቁሳዊና ስነልቦናዊ አዎንታዊ ውጤት ታስቦ የሚዘጋጅ የተግባር ሰነድ ነው፡፡ በርግጥ ፖሊሲን ከየትኛውም ሀገር መኮረጅ ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ውጤታማነቱ የሚለካው የፖሊሲው ትግበራ አፈፃፀም ነው፡፡

ፖሊሲ በራሱ ከሌሎች የተለየ ሙያዊ ስነምግባር የሚጠይቅ በመሆኑ የአስፈፃሚውንም አካል አቅምና ብቃት እንዲሁም የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚፈተሽበት ነው፡፡ ስለሆነም የፖሊሲ ችግር የለም፤የአፈፃፀም እንጂ ሚባል ከሆነ ፖሊሲውን ሊያስፈፅም የሚችል ብቃት ያለው አካል የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ችግሩን ለማረም ከሁለቱ አማራጮች አንዱን መውሰድ ግድ ይላል፡፡ ይህም ሚነደፈው ፖሊሲ ከገሪቱ አቅምና ፍላጎት ጋር ሳይሆን ከስራ አስፈፃሚው(ከገዥው ፓርቲ አመራሮች) አቅምና ብቃት ጋር በሚስማማ መልኩ መንደፍ፤ አሊያም ፖሊሲ የማስፈፀም ችግር አለብኝ ብሎ ያለው አካል ፖሊሲ የማስፈፀም አቅምና ብቃት ላለው አካል በሰላም ስልጣን መልቀቅ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ አለበለዚያ በፖሊሲ ንድፍና አፈፃፀም ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘፈቀደ ወዲያው ለማረም መሞከር የበለጠ ሀገርን እና ትውልድን ሊያጠፋ የሚችል ከባድ ስህተት እንዲፈፀም በር ሊከፍት ይችላል፡፡

በተለይ የአንዲት ሀገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተወደደም ተጠላ መሰረታዊ የሚባሉ ሶስት ነገሮችን ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ታሳቢ በማድረግ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም አንዲት ሀገር ፍላጎቷን፣መብትና ጥቅሟን ለማስፈፀም የምትንቀሳቀስባቸው በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሀገሪቱ ሁሉ-አቀፍ ፖሊሲ ግልባጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለየት የሚያደርገው ፖሊሲው ከሀገር ውጭ ትኩረት ማድረጉ ብቻ ነው፡፡
dddበኢትዮጵያ እየተተገበረ ነው የሚባለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሐሳብ ደረጃ ከላይ ካለው በተቃራኒ ትኩረቱ ኢኮኖሚ ላይመሰረት ያደረገ ነው መባሉ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ዓለም ሀገርም ሆነ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሳይንስ ንድፈ ሐሳብና ትግበራ አንፃር እጅግ ጎዶሎ መሆኑን ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚ በባህርይው ዛሬን እንጂ ነገን የማይል መሆኑ፣ስለአለውም ሆነ መጪው ጊዜ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እና ግንኙነት ቦታ በጥልቀት ከመገንዘብ ይልቅ ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር ነውና፡፡ ከውጭ የሚገኝ የኢኮኖሚ ትብብር በራሱ ደግሞ ያለ ፖለቲካዊ ስራ እና ግንኙነት ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ገዥው እና አስፈፃሚው ስርዓት አርቆ የማሰብም ሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምንነት ትርጓሜና ተግባር ላይ ምን ያህል የአቅምና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ሀገሪቱንም ሆነ ህዝቡን ለአላስፈላጊ ከፍተኛ መስዋዕትነት መዳረጉ አይቀርም፤ ዳርጓልም፡፡

በቅርቡ 90 ሚሊዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብመካከል 4.5 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልህዝብ ከራሱ የከርሰ ምድር103 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ 800 ሺህ ለሚሆነው የጅቡቲ ነዋሪ ንፁህ የመጠጥ ውሃ በኢትዮጵያ ወጭ ሊቀርብ ነው፡፡ ይህም እ.አ.አ ባለፈው መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ከተፈፀመ የሰነበተውን ለወጉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. መፅደቁ በብዙዎች ዘንድ አግራሞት ፈጥሯል፤ሊፈጥርም ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መኖሩን የሚያመላክት ነገር አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ እስካሁን በደፈናው ፖለቲካዊ ጥቅም ከሚል በስተቀር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለም መባሉ በራሱ፤ ስርዓት እከተለዋለሁ ከሚለው ኢኮኖሚያዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ይጋጫል፡፡

በርግጥ እንኳን ቀጥተኛ ትስስር ካላት ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ቀርቶ ከማንኛውም የውጭ ሀገር መልካም ግንኙነትና ጉርብትና መፍጠር ጠቃሚም ተገቢም ነው፡፡ ይበልጥ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችለው ግን የሁለቱንም ሀገራት ከጥርጣሬ የፀዳ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ካደረገ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ተለመደና ጤናማ ግንኙነትና ጉርብትና ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የራስን ፖለቲካዊ፣ ተፈጥራዊና እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት የሚመሰረት ወዳጅነት በሀገሮቹ መካከል የነበረውን ግንኙነት በማሻከር በጥርጣሬ እንዲመሰረት በማድረግ ያልታሰበ ችግር የመፍጠር አጋጣሚ ይኖረዋል፡፡እስኪ ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል በተደረገው ስምምነት አለ የተባለው ፖለቲካዊ ጥቅምስ እውን አለን? የሚለውን እና ነገ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረውንፖለቲካዊ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በአጭሩ እንመልከት፡፡

ፖለቲካዊ ፋይዳ

በሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች መካከል የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት ሁለቱንም የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ማንኛውም ስምምነት በቀዳሚነት ፖለቲካዊ ፋይዳው ነው የሚታየው፡፡ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል አካል አንዱ፤በድሬዳዋ እና ጅቡቲ አዋሳኝ ከሆነው ሽንሌ ዞን ለ30 ዓመታት በ100 ኪሎ ሜትር የድንበር ርቀት ያለውን 20 ሄክታር መሬት ጨምሮ 4ሺህ ሄክታር የከርሰ ምድር ውሃ ያለበትን የተፈጥሮ ሃብት በነፃ እንድታገኝ ተደርጓል፡፡ ይህም ጅቡቲ ለዓመታት ፈተና የሆነባትን የንፁህ ውሃ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ያለምንም ውጭ ማግኘቷ ከወደብ ጋር በተያያዘ በፖለቲካው ያላትን የበላይነት የሚያመላክት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች ካሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እጥረት እየተሰቃዩ ባሉበት ሰዓት ከ800 ሺህ ለማይበልጥ ጎረቤት ሀገር ሚዛናዊ ያልሆነ ወጪ እንድታደርግ አስገዳጅ ነገር መፍጠሯ እና እየፈጠረች መሆኗ ስምምነቱ አሉታዊ የፖለቲካ ፋይዳ እንዲኖረው አስችሏል፡፡

ሌላው የውሃ ቁፋሮው የሚካሄድበት የሽንሌ ዞን ነዋሪዎች እስካሁን ለ23 ዓመታት ንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በአግባቡ ሳያገኙ ዛሬ በአንድ ጊዜ ለጅቡቲ ህዝብ ጥቅም ሲባል ጭራሽ ነዋሪው እንዲፈናቀል መደረጉ በሶማሌ ክልልም ሆነ በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ስርዓቱ የሀገርና የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በአካባቢው ሌላ ቅራኔ በመፍጠር በቀጠናው ለእስኩኑ በባሰ የፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል፡፡ በርግጥ ገዥው ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ጥቅም ይኖረዋል በሚል የጅቡቲ ወደብን በቀጣይነት በተረጋጋ ሁኔታ በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን በሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ለመጠቀም ለመደለል ማሰቡ መጭውን ጊዜ ያለማገናዘቡን ከማመልከት በስተቀር በቀጣይ ጅቡቲ ውሳኔ ላይ ያን ያህል የጎላ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እዚህ ላይ ኢህአዴግ ያለህዝቡ ፈቃድ ላለፉት 23 ዓመታት የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የሆነውን የአሰብ ወደብን በአሁኑ ለጅቡቲ የሀገሪቱን የተፈጥሮሃብት ከክፍያ ነፃ በሆነ መንገድ እንደሰጠ ያኔ ለኤርትራ መስጠቱ ያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ዛሬም መድገሙ ገዥዎቹ አሁንም ከስህተት ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመማርዝግጁ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡

ሌላው ኢህአዴግ ህዝብ ሳይመክርበትና ሳይወያይበት እንዲሁም ሳይፈቅድ የሀገሪቱን መሬት ከነተፈጥሮ ሃብቱ በነፃ አሳልፎ መስጠቱ ነገ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በሚኖረው ጉርብትና እና ወንድማማችነት መካከል ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ነገ በኢትዮጵያ የፖለቲክ መንግስት ስርዓት ለውጥ ቢፈጠርና ይህ ስምምነት አዲስ በሚመሰረተው የመንግስት ቢሻር፤ ለኢትዮጵያ ሌላ አዲስ የጎረቤት ሀገር በጠላትነት የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም የተደረገው ስምምነት ሁለቱንም ሀገሮችና ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ሚዛናኑን የጠበቀ ስምምነት አልተፈፀመምና፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ በአንድ መነፅር ብቻ በመመልከት ለጅቡቲ የኃይል አቅርቦት መብራት እጅግ በቅናሽ ዋጋ ማቅረቡ እና ይህን ውሃ በነፃ መፍቀዱ በቀጣይ ለሚጠቀምበት የወደብ ኪራይ ማረጋጊያ እንደ ማታለያ ለመጠቀም አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላው የዋህነትና ድፍረት ነው፡፡

ጅቡቲ በቀጠናው ካላት መልካዓ ምድራዊ ፖለቲካ አቀማመጥ አንፃር በአሁን ሰዓት ሁሉ ነገሯን በራሷ ትወስናለች ማለት ዘበት ነው፡፡ ቀጠናው በቀይባህርና እና ህንድ ውቅያኖስ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ እንደመገኘቷ፣ የቀጠናው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምዕራባውያንንም ሆነ እንደ ቻይና እና ኢራን ያሉ እስያ ሀገሮችንም መሳቧ እርግጥ ነው፡፡ በተለይ ፈረንሳይ እና አሜሪካ በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ከአረብ ሀገራት ለሚያጓጉዙት ግዙፍ የቶታል፣ሞቢል እና የመሳሰሉ የነዳጅ ኩባንያዎቻቸው ደህንነት ጅቡቲን በእጅ አዙር መጠበቅና መንከባከብ ስለማይቦዝኑ፤ኢትዮጵያ አሁን ባደረገቸውና ለወደፊቱም ለማድረግ ባሰበችው የማታለል ተግባር ፈረንሳይና አሜሪካንም ጭምር መሆኑን ልታጤን ይገባል፤ይህ ደግሞ የላጭን ልጅ ቅማል በላት ዓይነት ተረት መሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ ሚዛኑን ያልጠበቀውና ነገን ታሳቢ ያላደረገው የጅቡቲ ብቻ ተጠቃሚነት የውጭ ጉዳይ ስምምነት ለኢትዮጵያ አሉታዊ የፖለቲካ ፋይዳ እንጂ ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አኳያ ሲሰላ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ከመተግበሩ በፊት ውሃ የሚቆፈርበት ቦታ ግልፅና ገለልተኛ በሆነ አካል የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በማካሄድ ራስን ከአላስፈላጊ ፖለቲካዊ ኪሳራ ማዳኑ የተሸለ ነው፡፡

ማኀበራዊ ፋይዳ

እንደማዕከላዊ መረጃ ኤጀንሲ ከሆነ ከኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከኦሮሞ እና አማራ ክልል ነዋሪ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ የሚገኘው እና 4.5 ሚሊዮን ነዋሪ ያለው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ በቂ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሳያገኝራሷን ለቻለች ሉዓላዊ ጎረቤት ሀገር በኢትዮጵያ ወጪ መደረጉ ስርዓቱ ገዥነት ለጅቡቲ ነው ወይስ ለኢትዮጵያ ያስብላል፡፡ የሶማሌ ክልል ነዋሪ በ 5.6 እጥፍ ከጅቡቲ ህዝብ ይበልጣል፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ፍላጎትና ፍጆታ ሳያሟላ፤በኢትዮጵያ ወጭ ለጅቡቲ ማኀበራዊ አገልግሎት የሚውል፤ ውሃ ከሚቆፈርበት የሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ለድሬዳዋ እና ሐረር በቅርብ ርቀት ቢገኝም የሀብቱ ባለቤት የሆኑት የአከባቢው ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ችግር ሲሰቃዩ እስካሁን መፍትሄ ያላቸው የመንግስት አካል የለም፡፡

በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ለሚገኙ ነዋሪዎችም ቢሆን ያለው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው፡፡ በሌላ በኩል በመንግስት ይህን የማኀበራዊ አገልግሎት ችግር ለመፍታት ከቃላት ባለፈ በተግባር የተሰጠ መፍትሄ ሳይኖር በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ አካል ላልሆነቸው ጅቡቲ አብዝቶ መጨነቅና ከድሃ ህዝብ ጉሮሮ በጀት ተነጥቆ መመደቡ ትልቅ የሞራል ኪሳራ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ያለው ተቆርቋሪናትና ማኀራዊ አገልግሎት ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነገ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮውን ተከትሎ የሚፈናቀሉ ዜጎች ለማን ተጠቃሚነት በሚል ከቀያቸው ሊነሱ ነው? እኚህ ዜጎች የነሱ ችግር ሳይፈታ አላቂ የሆነውን የተፈጥሮ ሃብታቸውን ያለፈቃዳቸው ተነጥቀው ለተጨማሪ የማኀበራዊ ቀውስ መዳረጋቸው በጅቡቲና በአዋሳኝ ድንበር ባሉ ኢትዮጵያውን መካከል ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ የዚህ ቅሬታ ደግሞ ወደ ግጭት በማምራት ለተጨማሪ ማበራዊ ቀውስ መዳረጉ ከወዲሁ መጤን ያለበት ጉዳይ ቢሆንም፤ በማን አለብኝነት ሊታለፍ መሆኑ ማጣፊያው የሚቸግር ሌላ መዘዝ ይዞ መምጣቱን ካለፉ ስህተቶች መማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በራሷ ወጭ ለጅቡቲ በነፃ በምትሰጠው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ሀገሪቱም ሆነች ዜጎቿ ከማኀበራዊዘርፍ ከሚያገኙት ጉዳት በስተቀር ምንም ጥቅም የለም፡፡

                    ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ከመስጠቷ በተጨማሪ ሌላ የፋይናንስ ወጪ ለማድረግ መፈራረሟ ሊላ የኢኮኖሚ ኪሳራን ያስከትላል፡፡ ይህ መደረጉ በራሱ ሀገሪቱ እከተለዋለሁ፤ እየተከተልኩ ነው የሚለው የኢኮኖሚ ተኮር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር በእጅጉ ይቃረናል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ለተጨማሪ ኪሳራ ከመዳረጓ በስተቀር የሚያስገኝላት አንዳች ጥቅምም የለምና፡፡
ኢትዮጵያ ይህን በማድረጓም ጅቡቲ ለኢትዮጵያ እየሰጠች ባለችው የወደብ ኪራይ

ላይ ተጨማሪ ክፍያ እንዳትጠይቅ የሚከለክል ነገር እንኳ ባለመኖሩ፤ነገ በቅናሽ የቀረበላትን የመብራት ኃይል አገልግሎት እና የጫት ንግድ በነፃ ማግኘት አለብን የሚል ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄንም ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሙሉ 90 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ 800 ሺህ ባላት ጅቡቲ ላይ ጥገኛ መሆኗን ሳትገነዘብ አትቀርም፤በኢህአዴግ የስልጣን አገዛዝ ሌላ የተሻለ አማራጭ የላትምና፡፡

የመገርመው ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ከመክፈሏ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን ያልተሰጠው ከክፍያ ነፃ የኢንቨስትመንት መሬት እና በወደቡ አካባቢ ተገነቡ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በኢትዮጵያ ወጪ መከናወኑ ራሱ ሌላው ያልተመለሰ የኢኮኖሚ ኪሳራ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መቼም ከጅቡቲ ጋር ለሚኖረን ወዳጅነት ጥሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መሰረት ዘላቂ ወዳጅ እና ዘላቂ ጠላት የሚባል የለምና፡፡ ያውም የዓለም የፖለቲካ ስርዓት በፍጥነት እየተቀያየረ ባለበት ሰዓት፤ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መወሰን እና መስማማት አሁን ከወጣውና ሊወጣ ከታሰበው በወጪ በላይ ተጨማሪ የገንዘብ ኢኮኖሚ ጥያቄን ይዞ መምጣቱ የተገመተ አይመስልም፡፡

                መፍትሄ

የኢትዮጵያ መንግስት አሁን የተፈራረመው (የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮው መጀመሩ ቢነገርም) ሙሉ ለሙሉ ተጋባራዊ ከመሆኑ በፊት የሚኖረውን ፖለቲካዊ፣ማበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማጤን አለበት፡፡ ሌላው የሁለት ሀገሮችን ጠጋራ ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ማንኛውም ሰምምነት ነገ ማጣፊያው የሚቸግር ሌላ ችግር ማስከተሉ ከወዲሁ በመገንዘብ ወደ ዘላቂ መፍትሄ መሄዱ ብልህነት ነው፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ያኔ ያለ ህዝብ ፈቃድ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን የባህር በር (አሰብ ወደብን) ራሱ አሳልፎ እንደሰጠ በማመን በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ለማስመለስ ግልፅ ውይይት እና ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

ሌላው ከህግ አኳያ ስምምነቱ የህገ መንግስት ጥሰትም አለበት፡፡ እዚህ ላይ የሚያሳፍረው የሀገሪቱንና ህዝቧን ጥቅም በህግ ያስጠብቃሉ የተባሉት እንደራሴዎች በግልፅ ገዥ የሆነውን የሀገሪቱን ህግ ከአስፈፃሚው እኩል ጥሰው ስምምነቱን ማፅደቃቸው ነው፡፡ ይህም በህገመንግስቱ አንቀፅ 86(3) ላይ የውጭ ግንኙነት መርሆች በሚለው ስር “የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ::” ይላል፡፡ ነገር ግን ስምምነቱ የማኀበራዊ እሴት መጠበቂያ የሆነው ህገ መንገስት በግልፅ በዚህ መልክ ተጥሶ የጅቡቲን ጥቅም ማስጠበቁን አስፈፃሚዎችም አልካዱትም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ራሱ የህገመንግስት ጥሰትን በመፈፀም ተባባሪ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የፀደቀው አዋጅ ተፈፃሚ ከመሆኑ በፊት የሀገሪቱንም ሆነ የሁለቱን ሀገሮች የጋራ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሊሻሻል አሊያም ሊሻር ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ ህግ ተርጓሚዎች እና አስከባሪዎች ጉዳዩን ወደ ህግ በመውሰድ ተገቢው እርምት እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የገዥው ፓርቲ ወገንተኝነትን ትቶ የሀገሪቱን እና የህዝቡን ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችን፣ የታሪክና የህግ ባለሙያዎችን፣ ሀገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችን እና ፖለቲከኞችን ያካተተ ግብረ ኃይል በማቋቋም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚያዋጣ መንገድ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ማድረግ ፍላጎትና አቅም የለኝም የሚል ከሆነ ስልጣኑን በፈቃዱ ለቆ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በር መክፈት አሊያም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተከታትለው እንዲያስፈፅሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የተሻለና የሰለጠነ አማራጭ መፍትሄ ነው፡፡ ለዚህም ሁሉም ዜጋና እና በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ካለው 90 ሚሊዮን ከአስርና ሃያ ዓመታት በኋላ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ከ120-150 ሚሊዮን ሲደርስ ችግሩ ከአሁኑ እጅግ የባሰ ይሆናል፡፡ ያኔ የጅቡቲን ወደብ በኪራይመጠቀም ቀርቶ፤ ጅቡቲ በፈቃዷ የኢትዮጵያ መንግስት አንዷ ፌደራላዊ አካል ብትሆን እንኳ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ለጅቡቲ አሳልፎ እየሰጡ እሽሩሩ ማለቱ ለሌላ ተጨማሪ ችግር በር ከመክፈቱ በስተቀር ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡

በተደጋጋሚ ተጨማሪ ወጭና ስጋት የማይፈጥር ዘላቂ መፍትው ግልፅና አጭር፤ያም ሀገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ ያጣችውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን የአሰብ ወደብንማስመለስ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እንደ ኬኒያ፣ ሶማሊ ላንድ እና ሱዳን ወደቡን በአማራጭነት ማሰቡ ደግሞ ከጅቡቲ የባሰ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይዞ መምጣቱ የማይቀር ስለሆነ፤መፍትሄው ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በማስመለስ የወደብ ባለቤት መሆን ብቻ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: