Daily Archives: April 20th, 2015

በሊቢያ ዓለም አቀፉ አይ ኤስ አይ ኤል የተባለው አሸባሪ ድርጅት 28 ኢትዮጵያውያንን በሊቢያ መግደሉን አስታወቀ

በኢራቅና በሶሪያ በሚፈፅማቸው አሰቃቂ ድርጊቶች የሚታወቀው አይ ኤስ አይ ኤል የተባለው አሸባሪ ድርጅት አካል ዛሬ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. 28 ኢትዮጵያውያንን በለመደው አሰቃቂ ግድያ መፈፀሙን የሚገልፅ ቪዲዮና ምስል ለቋል፡፡ 29 ደቂቃ የፈጀው ቪዲዮ መረጃ መሰረት 12ቱ በምስራቃዊ ሊቢያ ባህር ዳርቻ አንገታቸውን ሲቀላ፤ከ16 ያላነሱትን ደግሞ በደቡባዊ ሊቢያ በረሃ ላይ በጥይት ደብድቦ መግደላቸውን ይፋ መደረጉን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ቡድኑም አሰቃቂ ግድያውን ሲፈፅም የጠላታችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመስቀሉ ተከታዮች የሚል ግልፅ ፅሑፍና ንግግር አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ስለጉዳዩ ከሮይተርስ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለቀረበላቸው ጥያቄ በቡድኑ የተገደሉት ኢትዮጵውን ስለመሆናቸው በግብፅ ከሚገኘው የኢትዮጵ ኤምባሲ ማረጋገጫ አላገኘንም የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ ግድያውን የፈፀመው ሊቢያ ውስጥ እንጂ ግብፅ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የሟቾችም የቪዲዮ ምስል ቡድኑ ከገለፀው በተጨማሪ የተለመደው ኢትዮጵያዊ ገፅታ በግልፅ ይታያል፡፡ ቡድኑም ግድያውን የፈፀመበትን ሲናገር ሟቾቹ የነበሩትን የክርስትና ኃይማኖት ክደው እስልምናን እንዲቀበሉና በሊቢያ ለሚገኘው የአሸባሪው ቡድን አካል ልዩ ግብር ቢከፍሉ እንደሚለቀቁ የቀረበባቸው አስገዳጅ ጥያቄ ባለመቀበላቸው እርምጃውን መውሰዱን አስታውቋል፡፡

Ethiopian killed by ISIL

ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ ከ30 ያላነሱ የግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን መግደሉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፤ ግብፅ ብሔራዊ የሀዘን ቀን በማወጅ በሊቢያ የቡድኑ ይዞታ ነው በተባለ ቦታ በአየር ኃይሏ ተደጋጋሚ ድብደባ በማድረግ ፈጣን የአፀፋ መልስ መስጠቷ ይታወቃል፡፡ አይ ኤስ አይ ኤል የተባለው ይህ አሸባሪ ቡድን በኢራቅና በሶሪያ በተመሳሳይ መልክ የበርካታ ክርስቲያኖችን እና ከሱ ወገን አይደሉም ያላቸው ሙስሊሞች ላይ ተመሳሳይ አሰቃቂ ግድያ መፈፀሙና አሁንም በዚህ ተግባሩ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና አሁንም አሸባሪ ቡድኑ በቅርብ ከሚገኝበት ሊቢያ ከ90 በላይ ኢትዮጵያውያን ተሸሽገው የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑን እና፤ ተደብቀው ምግብ ሳይበሉ ከተቆለፈባቸው 3 ቀናት እንደሞላቸው የኢሳት ዘገባ አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከ40 የማያንሱ ኢትዮጵውያን በዛው ሊቢያ የወደብ ከተማ በሆነችው ትሪፖሊ ወደ አውሮፓ ለመሻገር መርከብ በመጠባበቅ ላይ ሲሆኑ፤ በስፍራው በርካታ ኢትዮጵውን ሴቶችና ህፃናትም እንደሚገኙበትና በአቅራቢያቢያው የአሸባሪው ቡድን አካላት ስለሚንቀሳቁ ስጋት ላይ በመውደቃቸው እነሱም የአስቸኳይ የድረሱልን ጥሪ ማሰማታቸው ታውቋል፡፡በትናንትናው ዕለትም ከዚህ ከትሪፖሊ ወደ አውሮፓ 700 አፍሪካውያንን ስደተኞች የያዘች መርከብ መስጠሟን እና እስካሁን በአውሮፓ የነፍስ አድን ሰራተኞች የ28 ሰዎች ህይወት ብቻ ማትረፍ መቻሉ የተዘገበ ሲሆን፤ ተጓዦች ውስጥ ኢትዮጵያውያንም እንደሚኖሩበት ይገመታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በየመን ባለው ጦርነት ምክንያት ባለፈው መጋቢት 2007 ዓ.ም. በስደተኛ መጠለያ ያሉ 46 ኢትዮጵያውን በሳውዲ ዓረቢያ የቶር አውሮፕላን መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታደጋቸው አጥተው አሁንም በየመን ስቃይ ላይ በመሆናቸው የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

በደቡብ አፍሪካ የ7 ሰዎችን ህይወት ያጠፋው የጥላቻ አመፅ ወደሌሎች ከተሞችም መዛመቱ እየተነገረ ነው

በደቡብ አፍሪካ በያዝነው ሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በወደብ ከተማዋ ደርባን ጥቁር የውጭ አፍሪካውያን ነጋዴዎች ላይ የተቀሰቀሰው ጥላቻ የ6 ሰዎች ህይወትን እንዳጠፋ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በሌሎች የአፍሪካ ጥቁር ዜጎች ላይ የተጀመረው ጥላቻ ከደርባን ከተማ ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የተዛመተ ሲሆን፤ ትናንት ቅዳሜ ጆሃንስበርግ ከተማ ላይ አንድ ሞዛምቢካዊ መግደላቸውን የተለያዩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

south africa 3

በጥቃቱ በብዛት ሰለባ የሆኑት የኢትዮጵያ፣ የሶማሌ፣የናይጄሪያ፣የሞዛምቢክ፣የዙምባቤና የማላዊ ዜጎች የገለፀ ሲሆን፤ ከተገደሉት መካከልም 3ቱ ኢትዮጵውን መሆናቸውን የተለያዩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በጥቃቱ ምክንያት ኬንያ፣ ማላዊ እና ዙምባቤ ወዲያውኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ለማስወጣት የሞከሩ ሲሆን፤ በተለይ ዙምባቤ እና ቦትስዋና ዜጎቻቸው በሰላም እስኪወጡ ድረስ ከጥቃቱ ለመከላከል ልዩ የጦር ኃይል ወደስፍራው መላካቸው ተሰምቷል፡፡ ሞዛምቢክ በበኩሏ ዜጎቿና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሌሎች ጥቁር አፍሪካውያንን ለመታደግ ድንበሯን የከፈተች ስትሆን፤ ጥቃቱ ወዳለበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ዜጎቻቿን ለመታደግ ትራስፖርትና አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ስታቀርብ ተስተውሏል፡፡

በተለይ ናይጄሪያና የሶማሊያ መንግሥት ድርጊቱን ከማውገዝ አልፎ፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የተፈጠረውን ቀውስ በአስቸኳይ እንዲቆጣጠርና እንዲያቆም ማስጠንቀቂያ ጠይቀዋል፡፡ በናይጄሪያ በዓለም አቀፍ አሸባሪነት የተፈረጀው ቦኮ ሃራም በበኩሉ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በናይጄሪያውያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በ24 ሰዓታት ውስጥ ማስቆም ካልቻለ በምዕራብ አፍሪካ ባሉ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲና ዜጎቿ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከመዛት በተጨማሪ የደቡብ አፍሪካዋን ጆሃንስ በርግን ባግዳድ አደርጋታለሁ ሲል ማስጠንቀቁ አነጋግሯል፡፡

south africa2

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት በጥቃቱ የሞተው አንድ ኢትዮጵዊ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮረፖሬሽን አስታውቋል፡፡

በደርባን የተቀሰቀሰው በተለምዶ የውጭ ሀገር ዜጋን የመጥላት “ዜኖፎቢያ” ዘመቻ በአሁን ሰዓት ጋብ ያለ ቢመስልም፤ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች መዛመቱንና ችግሩ ከከተማ ውጭ የሚሰሩ ሌሎች ጥቁር የአፍሪካ ዜጎች አደጋ ላይ መሆናቸውንና እስካሁንም የደረሰባቸውን ችግር ለማወቅ እንዳልተቻለም ተጠቁሟል፡፡ ድርጊቱንም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማና የተለያዩ የሀገሪቱ ዜጎች በይፋ ቢቃወሙም፤የአመፁ ዋና ቀስቃሽ ተደርገው የተወሰዱት በደርባን ያሉት የዙሉ ጎሳ ንጉስ ጉድዊል በወቅቱ በአንድ መድረክ ባደረጉት የጥላቻ ንግግር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሬዘዳንቱ ጃኮብ ዙማ ልጅም ድርጊቱን የሚያበረታታ ነገር ከዚህ በፊት በሌላ መድረክ መናገራቸው እየተጠቆመ ይገኛል፡፡ በጥቃቱም ሁለት ጥቁር አፍሪካውያን ከነ ህይወታቸው በደቡብ አፍሪካውያን የተቃጠሉ ሲሆን ሌሎቹ ስለት ባላቸው መሳሪያዎችና በድንጋይ ተደደብድበው መገደላቸው ታውቋል፡፡

በተቀሰቀሰው የጥላቻ አመፅም የኢትዮጵያውንን ጨምሮ የበርካታ የጥቁር አፍሪካውያን ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ከዝርፊው የተረፉትም ተቃጥለዋል፡፡ ድርጊቱን ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ቢያወግዘውም ወደሌሎች ከተሞች መዛሙቱ አሁንም ስጋትን ጭሯል፡፡ በርካቶችም የንግድ ሱቆቻቸውን ጥለው በተለይ በደርባን ከተማ ጊዘየያዊ የስደተኛ መተጠለያ ጣቢያና በፖሊስ ጣቢያዎች እንደተጠለሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በተፈፀመ ተመሳሳይ ጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች በተሰማሩበት የንግድ ስራ ጥላቻ ከ60 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውንና የበርካቶች ሱቆችና ሌሎች የንግድ ተቋማት መዘረፋቸውን መረጃዎች አመለክተዋል፡፡

ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን አነስተኛ የንግድ ሱቅ በሚሰሩ አፍሪካውያን ላይ በጥላቻ ቢዘምቱም፤ለዛሬው ነፃነታቸው ያበቋቸው በዋናነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካውያን ትልቅ ሚና እንደነበራቸው አይዘነጋም፡፡

%d bloggers like this: