ከፍተኛው ፍርድ ቤት በብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞች ላይ የቀረቡ የሲዲ መረጃዎችን ውድቅ አደረገ
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ መዝገቡ የተቀጠረው አቃቤ ህግ አሉኝ ባላቸው ሲዲዎች እና ቀሪ ምስክሮቹን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ ቀሪ ምስክሮቹን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ለማቅረብ ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ የሰጠውን እድል ባለመጠቀሙ እና ምስክሮቹን ላለማቅረቡ የሰጠው ምክንያትም በቂ ባለመሆኑ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ባለመፍቀድ ከዚህ በኋላ ምስክሮቹን እንደማይሰማ አመልክቷል፡፡
አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት ይዟቸው የቆያቸውን የ12ቱን ሲ.ዲዎች ጉዳይ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሲ.ዲዎቹ በማስረጃ ዝርዝሩ ውስጥ ፕሪንት ተደርገው የተያያዙ ሰነዶችን እንደያዙ ስለተገለጸ ሲ.ዲዎቹ ከማስረጃነትም ሆነ ከኤግዚቢትነት ውድቅ መደረጋቸውን ገልጹዋል፡፡
አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የሲ.ዲ ዶክሜንተሪ ማስረጃ ማቅረቡን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትለት የጠየቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አቃቤ ህግ ሲ.ዲውን በጽህፈት ቤት በኩል እንዲያስገባ በማዘዝ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን ዶክሜንተሪ በቢሮ ዳኞቹና ጠበቆቹ እንዲመለከቱት ከተደረገ በኋላ ሲ.ዲው ሌሎችን ተከሳሾች ይመለከታል ወይስ አይመለከትም የሚለውን አይቶ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች ጥያቄያቸውን ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት በሞከሩበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ የመናገር እድል ሲነፈጉ የተስተዋለ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ሲጠይቁ ‹‹ስነ-ስርዓት አድርጉ!›› ባለ ጊዜ ጦማሪ አቤል ዋበላ ‹‹እናንተ ራሳችሁ ስነ-ስርዓት አድርጉ….እንናገርበት! ይህ የመብት ጉዳይ ነው…በግልጽ ችሎት ላይ ህገ መንግስታዊ መብታችንን አክብሩ እንጂ…ጥያቄ አለን ተቀበሉን›› ሲል በመናገሩ ችሎት ደፍረሃል ተብሏል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ በአቤል ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ 2007 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት ተዓማኒነት ከወዲሁ ውግዘትና ትችቶች እየቀረቡበት ነው
ባለፈው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤት በገዥው ኢህአዴግ አሸናፊነት መጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ እስካሁን ቦርዱ ደረሱኝ ባላቸው ከ547 ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ፤ 440 መቀመጫ ውጤቶች በሙሉ ኢህአዴግ ማሸነፉን ይፋ አድርጓል፡፡ ቀሪዎቹ 107 መቀመጫ ውጤቶች አሸናፊ በቦርዱ ባይገለፅም፤ የኢህአዴግ ደጋፊ መሆኑን በድረ-ገፁ የገለፀው “አይጋፎረም” ገና ምርጫው ሳይጠናቀቅና በይደር የታለፉ ጣቢያዎች እያሉ በምርጫው ዕለት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ኢህአዴግ 100 ማሸነፉን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ድረ-ገፁ የመድረክ አንጋፋ ተወካዮች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሁሉም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች በመላ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ በኢህአዴግ መሸናፋቸውን ይፋ ያደረገውን መረጃ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ሊያነሳ ችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድም ለጊዜው በቁጥር ካስቀመጠው መቀመጫ በስተቀር ምርጫው ሳይጠናቀቅ ቀድሞ የኢህአዴግን ማሸነፍ ይፋ ካደረገው አይጋ ፎረም የተለየ መረጃ እስካሁን ሊሰጥ አልቻለም፡፡
በምርጫው ዋዜማ እና ዕለት በተለይም ከገዥው ኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) እና የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ምርጫ ጣቢያዎች በደህንነት እና ፖሊሶችታስረውና ታግተው እንዳይታዘቡ መደረጋቸውን ፓርቲዎቹ ቀድመው ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫውን ውጤትም ሆነ ሂደቱን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ ኢህአዴግ በምርጫ 1997 ዓ.ም. በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽንፈት ገጥሞት ስልጣኑን ባይለቅም፤ በምርጫ 2002 ዓ.ም. 99.6 በመቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የነበረው የምርጫ ሂደትና ውጤት ላይ በሀገር ውስጥና ከውጭ የተለያዩ ቅሬታዎችን እና ትችቶችን ማስተናገዱ ባይዘነጋም፡፡
ምርጫውን የታዘበው የአፍሪካ ህብረት በሰጠው ጊዜያዊ መግለጫ ታዛቢ ቡድኑ ከታዘባቸው ከ21 በመቶ የማያንሱ የምርጫ ጣቢያዎች ኮሮጆዎች ድምፅ መስጠት ከመጀመሩ በፊት በዶ መሆናቸው ተከፍቶ እንዲታይታዛቢ ቡድኑ ቢጠይቅም፤ በየጣቢያው ያሉ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እና የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎቹ ተከታታይነት ያለው ቁልፎች እንዳልነበሩት በመግለፅ ምርጫው ነፃ ነበር ለማለት እንደሚቸገር አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያያን ሀገር አቀፍ ምርጫ ሲታዘቡ የነበሩት የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካው ካርተር ማዕከል ምርጫ 2007 ዓ.ም. ሂደትን እንዳልታዘቡ ታውቋል፡፡
የእሁዱ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ውጤት ግን ከቀድሞው በባሰ 100 % የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያለምንም አማራጭ ሐሳብ በገዥው ኢህአዴግና አጋሮቹ ሊሞላ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ውጤቱም የህዝብ ድምፅ ዘረፋና ማጭበርበር እንዲሁም የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በደረሰው ተፅዕኖ የመጣ እንጂ በነፃ ምርጫ የተገኘ የህዝብ ድጋፍ አይደለም በሚል ከወዲሁ ውግዘትና ትችት ገጥሞታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ውጤቱ የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነትንም የበለጠ ጥያቄ ውስጥ ቢከትም፤ ውጤቱን አስመልክቶ ከዥው ፓርቲ በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋ መግለጫ የለም፡፡
ለቀድሞው የአንድነት አመራር “ እናርድሃለን፣…ራስህን በጥይት እንበትነዋለን….” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው
የመንግሥት ደህንነቶች ለቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ተክሌ በቀለ የመጨረሻያሉትን እናርድሃለን፣…ራስህን በጥይት እንበትነዋለን..የሚል ማሰጠንቀቂ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውና ማስፈራሪው በሌሎቹም የቀድሞው የፓርቲ አመራሮች ላይም የቀጠለ ሲሆን፣በዛው ዕለት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማፀንቱ መታሰሩ ታውቋል፡፡በተለይ የአቶ ተክሌ በቀለ ሁኔታን በተመለከተ ራሳቸው በአጭሩ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡
ለሆነ ጎዳይ ከእንድ ጓደኛየ ጋር ዛሬ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 ላይ ከቦሌ ተነስተን ኮተቤ(02) አካባቤ ሄድን፡፡ የቤት ታርጋ የለጠፈች ነጭ መኪና 4 ጎሮምሶችን ይዛ ትከተን ነበር፡፡ ቦታ ስተን ኑሮ የሆነ መታጠፊያ ላይ ወደ ኋላ ስንዞር ተገጣጠምን፡፡ ባንድ መስመር ስዞር ቦታ የዘጋሁባቸዉ መስሎኝ ይቅርታ ስጠይቃቸዉ የሚነዳው ወንድም መኪናዉን አቁሞ ሳይወርድ የስድብ መዓት አወረደብኝ፡፡ ያ ያገሬ ልጅ! ከዚያም ሄዱ፡፡እነማን እንደ ሆኑም ገባኝ፡፡ ጓደኛየ ወደ ቢሮዉ ገብቶ ጉዳዩን ጨርሶ እስኪወጣ ወርጄ ስጠብቀዉ በመኪኗ ተመልሰዉ መጡ፡፡ በማዶ ላይ የቀን ሰራተኞች ምሳ በልተዉ ሰዓቱ እስኪደርስ ጥላ ላይ ያረፉ ነበሩ፡፡ሁኔታዉን ይከታተሉ ኖሮ ትተዉኝ ሲሄዱ መጥተዉ ጠየቁኝ፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል እንደነበርኩና አሁን እንደሌለሁበት፤የስርኣቱ ደህንነት ነን ባዮች ሲሆኑ እያስፈራሩኝ መሆኑንም ስነግራቸዉ በጣም ተናደዱ፡፡ለምን ግርግር አትፈጥርም ነበር አንለቃቸዉም ነበር…..ክብር ለዜጎች! ውድ ህይወት ተከፍሎበት በነበረ ስርዓት ውስጥ፤ህግ አክባሪና ሃይማኖተኛ በሆነ ማህበረሰብ ዉስጥ ተወልዶ ያደገ፤ከድሃ ግብር ደሞዝ የሚበላ የደህንነት ሰራተኛ ነኝ ባይ “እናርዳሃለን….መንግስት ነን፣ ራስህን በጥይት እንበትነዋለን…የምትሰራዉን ሁሉ እናዉቃለን…እድሉን ተጠቀምበት የመጨረሻህ ነዉ….” የሚሉ ቃላት እንዲናገሩ ሰልጥነዉ ሲላኩ በእዉነት ያሳፍራል፡፡ ዱላ ቀረሽ ስድብ አዝንበዉብኝ መኪናቸዉን አስነስተዉ እብስ አሉ፡፡ የመጀመሪያየ ባይሆንም የከዚህ ቀደሞቹ ግን ጨዋዎች ነበሩ! ግን፤ አርፈንም እንድናርፍ አይፈቀድልንም እንዴ? እኛ እንሰራው የነበረው ፖለቲካ ፍጽም ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ ነበር፡፡ አሁንም መብታችን ነዉ፡፡ የነአሞራዉ ደም የፈሰሰዉ ለዚህም እንደነበር እንረዳለን፡፡ተሸብራችሁ ከሆነ በስራችሁ እንጂ በኛ አይደልም፡፡ እኛ ግን ለግዜው ከጨዋታው ውጪ ስላደረጋችሁን በጨዋታው ሜዳ የለንበትም፡፡ ለማስጠንቀቂያውም ለመረጃውም ስርዓት አለው፡፡ የመንግስት አካል የሆነ ተቋም በፈለገዉ መንገድ ህጋዊ ሆኖ ማናገር ይችላል፡፡ መንግስትነት ትልቅ ሃላፊነትና ተቋም መሆኑን ልንነግራችሁ አቅም የለንም፡፡ የተበተነን የቀድሞ የፓርቲ አመራር ማስፈራራትና ማሰር ተራ ብቀላ ይመስላል፡፡ ተራ ህይወት እየመራንም፤አርፈን ተቀምጠንም ልትተዉን ካልቻላችሁ በግፉ መንገድ ግፉበት፡፡ እኛ ከማን እንበልጣለንና ነው!!!
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ የኢህአዴግ እስር እና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ ቀጥሏል
በኢትዮጵያ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና በመላ ሀገሪቱ ፅህፈት ቤቶች ከፍቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ የኢህአዴግ እስር እና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት 2007 ዓ.ም. ፓርቲው የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ዋነኛ የኢህአዴግ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ መወሰኑን እና ለዚህም ይፋ የምርጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን በማፍረሱ የቀድሞው የአንድነት አመራሮች እና አባላት ከፖለቲካው እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
ይሁን እንጂ የተወሰኑ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ፓርቲያቸው በኢህአዴግ እና በምርጫ ቦርድ በይፋ ተነጥቆ እንዲፈርስ በመደረጉ የተወሰኑ አመራሮች እና አባላት ሰማያዊ ፓርቲን በይፋ ተቀላቅለው የፖለቲካ ትግሉን ቢጀምሩም አሁንም ከኢህአዴግ እስርና ማስፈራሪያ መዳን አልቻሉመ፡፡ በዚህም በርካታ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራሮች እና አባላት ሰማያዊ ፓርቲን ከተቀላቀሉ በኋላ እነ ስንታየሁ ቸኮል በእስር ላይ ይገኛሉ፡:
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲያቸው በምርጫ ቦርድ ፈርሶ፤ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለእኔ ለሚታዘዙልኝ በሚል ራሱ ቦርዱ ለመረጣቸው አካላት ቢያስተላልፍም በርካታ የቀድሞ የአንድነት አመራሮች ከፖለቲካ ድርጅት ትግል እንዲታቀቡ ቢደረግም፤ ማስፈራሪያና እስሩ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡ በዚህም ትናንት ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አለነ ማፀንቱ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመኖሪያ ቤቱ በደህንነት እና በፖሊስ ኃይል ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ በመፈፀም የኢሜይል አካውንቱን የይለፍ ቃል በግድ በደህንነቶች ከተወሰደ በኋላ በአዲስ አበባ ጉለሌ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ በላይ ፈቃዱ እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ ተክሌ በቀለም በተመሳሳይ ዕለት በደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ማስፈራሪ እና ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፓርቲው በምርጫ ቦርድ ከፈረሰ በኋላ የስራ አስፈፃሚ አባል የነበረው አቶ ዳዊትአስራደን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች እስማኤል ዳውድ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ መሳይ ትኩዕ፣ ፋንቱ ዳኜ በደህንነት እና ፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውና መደብደባቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የፓርቲው ወጣት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዳንኤል ሺበሺ እና ሀብታሙ አያሌው በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ አንድነት የፊታችን እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ450 በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ማቅረቡን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በቀጠለው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ምክንያት የካቲት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን አፍርሶ “ለእኔ ለሚታዘዙልኝ…” በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ራሱ ቦርዱ ለመረጠው አመራር የፓርቲውን ስም መስጠቱን ይፋ ማድረጉ አያዘነጋም፡፡
ወጣት ስንታየሁ ቸኮል 6 ወር ሲፈረድበት፤ ፋንቱ ዳኜ ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዶ መታሰሩ ተሰማ
ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ወጣቶች አመራር የነበረውና በአሁን ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አባል ወጣት ስንታየሁ ቸኮል 6 ወር እስራት ተፈረደበት፡፡ ወጣት ስንታየሁ ቄራ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሲቪል በለበሱ ደህንነቶች ተወስዶ ከታሰረ በኋላ የፌደራሉ ፍርድ ቤት ቄራ ምድብ ችሎት ቀርቦ የአካባቢው የኢህአዴግ ካድሬዎች ከመሰከሩበት በኋላ እንደተፈረደበት ታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለቀረበበት ክስ መከላከያ ምስክር አሊያም የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርብ ቢጠይቀውም፤ ወጣት ስንታየሁ “ከሳሼም፣መስካሪየም፣ፈራጁም ኢህአዴግ ስለሆነ የመከላከያ ምስክር ብዬ ሰዎችን አላንገላታም፣የቅጣት ማቅለያም አላቀርም፤የፈለጋችሁትን ፍረዱ” ሲል ችሎት ላይ መናገሩ ትውቋል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ በችሎት የተናገርውና የቀረበበት ክስ ከዓመት በላይ የሚያስቀጣ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ በ6 ወር እስራት እንዲቀጣ መፍረዱ ታውቋል፡፡
ስንታየሁ ቸኮል ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከቀድሞው አንድነት ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የፀጥና ደህንነት ኃይሎች ተደጋጋሚ ሲታሰርና ሲደበደብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በተደረጉ በተለያዩ የስርዓቱ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የስርዓቱን ድርጊት የሚያመለክቱ ልዩ መፈክሮችን ይዞ በመውጣትም ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና ሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ፀሐፊ የነበረው ፋንቱ ዳኜ ሳሪስ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መታሰሩ ታውቋል፡፡ አቶ ፋንቱ በወቅቱ ሳሪስ ፖሊስ ጣቢያ ቢወሰድም እስካሁን ለምን እንደተያዘ እና እንደታሰረ የተገለፀ ነገር እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ወጣት ፋንቱ ከቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ጠንካራ ወጣት አመራሮች መካከል አንዱ እንደነበር ምንጮች አስታውቀዋል፡፡