Daily Archives: May 31st, 2015

ከፍተኛው ፍርድ ቤት በብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞች ላይ የቀረቡ የሲዲ መረጃዎችን ውድቅ አደረገ

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ መዝገቡ የተቀጠረው አቃቤ ህግ አሉኝ ባላቸው ሲዲዎች እና ቀሪ ምስክሮቹን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡ ቀሪ ምስክሮቹን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን ለማቅረብ ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ የሰጠውን እድል ባለመጠቀሙ እና ምስክሮቹን ላለማቅረቡ የሰጠው ምክንያትም በቂ ባለመሆኑ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ባለመፍቀድ ከዚህ በኋላ ምስክሮቹን እንደማይሰማ አመልክቷል፡፡

z9

አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት ይዟቸው የቆያቸውን የ12ቱን ሲ.ዲዎች ጉዳይ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሲ.ዲዎቹ በማስረጃ ዝርዝሩ ውስጥ ፕሪንት ተደርገው የተያያዙ ሰነዶችን እንደያዙ ስለተገለጸ ሲ.ዲዎቹ ከማስረጃነትም ሆነ ከኤግዚቢትነት ውድቅ መደረጋቸውን ገልጹዋል፡፡

አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የሲ.ዲ ዶክሜንተሪ ማስረጃ ማቅረቡን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትለት የጠየቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አቃቤ ህግ ሲ.ዲውን በጽህፈት ቤት በኩል እንዲያስገባ በማዘዝ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን ዶክሜንተሪ በቢሮ ዳኞቹና ጠበቆቹ እንዲመለከቱት ከተደረገ በኋላ ሲ.ዲው ሌሎችን ተከሳሾች ይመለከታል ወይስ አይመለከትም የሚለውን አይቶ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾች ጥያቄያቸውን ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት በሞከሩበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ የመናገር እድል ሲነፈጉ የተስተዋለ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ሲጠይቁ ‹‹ስነ-ስርዓት አድርጉ!›› ባለ ጊዜ ጦማሪ አቤል ዋበላ ‹‹እናንተ ራሳችሁ ስነ-ስርዓት አድርጉ….እንናገርበት! ይህ የመብት ጉዳይ ነው…በግልጽ ችሎት ላይ ህገ መንግስታዊ መብታችንን አክብሩ እንጂ…ጥያቄ አለን ተቀበሉን›› ሲል በመናገሩ ችሎት ደፍረሃል ተብሏል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ በአቤል ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ 2007 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት ተዓማኒነት ከወዲሁ ውግዘትና ትችቶች እየቀረቡበት ነው

ባለፈው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤት በገዥው ኢህአዴግ አሸናፊነት መጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ እስካሁን ቦርዱ ደረሱኝ ባላቸው ከ547 ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ፤ 440 መቀመጫ ውጤቶች በሙሉ ኢህአዴግ ማሸነፉን ይፋ አድርጓል፡፡ ቀሪዎቹ 107 መቀመጫ ውጤቶች አሸናፊ በቦርዱ ባይገለፅም፤ የኢህአዴግ ደጋፊ መሆኑን በድረ-ገፁ የገለፀው “አይጋፎረም” ገና ምርጫው ሳይጠናቀቅና በይደር የታለፉ ጣቢያዎች እያሉ በምርጫው ዕለት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ኢህአዴግ 100 ማሸነፉን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

ፕሮፌሰር መረጋ በቃና የወቅቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

ፕሮፌሰር መረጋ በቃና የወቅቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

ይሁን እንጂ ድረ-ገፁ የመድረክ አንጋፋ ተወካዮች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሁሉም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች በመላ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ በኢህአዴግ መሸናፋቸውን ይፋ ያደረገውን መረጃ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ሊያነሳ ችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድም ለጊዜው በቁጥር ካስቀመጠው መቀመጫ በስተቀር ምርጫው ሳይጠናቀቅ ቀድሞ የኢህአዴግን ማሸነፍ ይፋ ካደረገው አይጋ ፎረም የተለየ መረጃ እስካሁን ሊሰጥ አልቻለም፡፡

Medrek press conference

በምርጫው ዋዜማ እና ዕለት በተለይም ከገዥው ኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) እና የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ምርጫ ጣቢያዎች በደህንነት እና ፖሊሶችታስረውና ታግተው እንዳይታዘቡ መደረጋቸውን ፓርቲዎቹ ቀድመው ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫውን ውጤትም ሆነ ሂደቱን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ ኢህአዴግ በምርጫ 1997 ዓ.ም. በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽንፈት ገጥሞት ስልጣኑን ባይለቅም፤ በምርጫ 2002 ዓ.ም. 99.6 በመቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የነበረው የምርጫ ሂደትና ውጤት ላይ በሀገር ውስጥና ከውጭ የተለያዩ ቅሬታዎችን እና ትችቶችን ማስተናገዱ ባይዘነጋም፡፡

Semayawi lection 2015 press conference

ምርጫውን የታዘበው የአፍሪካ ህብረት በሰጠው ጊዜያዊ መግለጫ ታዛቢ ቡድኑ ከታዘባቸው ከ21 በመቶ የማያንሱ የምርጫ ጣቢያዎች ኮሮጆዎች ድምፅ መስጠት ከመጀመሩ በፊት በዶ መሆናቸው ተከፍቶ እንዲታይታዛቢ ቡድኑ ቢጠይቅም፤ በየጣቢያው ያሉ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እና የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎቹ ተከታታይነት ያለው ቁልፎች እንዳልነበሩት በመግለፅ ምርጫው ነፃ ነበር ለማለት እንደሚቸገር አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያያን ሀገር አቀፍ ምርጫ ሲታዘቡ የነበሩት የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካው ካርተር ማዕከል ምርጫ 2007 ዓ.ም. ሂደትን እንዳልታዘቡ ታውቋል፡፡

የእሁዱ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ውጤት ግን ከቀድሞው በባሰ 100 % የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያለምንም አማራጭ ሐሳብ በገዥው ኢህአዴግና አጋሮቹ ሊሞላ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ውጤቱም የህዝብ ድምፅ ዘረፋና ማጭበርበር እንዲሁም የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በደረሰው ተፅዕኖ የመጣ እንጂ በነፃ ምርጫ የተገኘ የህዝብ ድጋፍ አይደለም በሚል ከወዲሁ ውግዘትና ትችት ገጥሞታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ውጤቱ የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነትንም የበለጠ ጥያቄ ውስጥ ቢከትም፤ ውጤቱን አስመልክቶ ከዥው ፓርቲ በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋ መግለጫ የለም፡፡

%d bloggers like this: