Daily Archives: May 17th, 2015

ለቀድሞው የአንድነት አመራር “ እናርድሃለን፣…ራስህን በጥይት እንበትነዋለን….” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

የመንግሥት ደህንነቶች ለቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ተክሌ በቀለ የመጨረሻያሉትን እናርድሃለን፣…ራስህን በጥይት እንበትነዋለን..የሚል ማሰጠንቀቂ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውና ማስፈራሪው በሌሎቹም የቀድሞው የፓርቲ አመራሮች ላይም የቀጠለ ሲሆን፣በዛው ዕለት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማፀንቱ መታሰሩ ታውቋል፡፡በተለይ የአቶ ተክሌ በቀለ ሁኔታን በተመለከተ ራሳቸው በአጭሩ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡

ተክሌ በቀለ

ተክሌ በቀለ

ለሆነ ጎዳይ ከእንድ ጓደኛየ ጋር ዛሬ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 ላይ ከቦሌ ተነስተን ኮተቤ(02) አካባቤ ሄድን፡፡ የቤት ታርጋ የለጠፈች ነጭ መኪና 4 ጎሮምሶችን ይዛ ትከተን ነበር፡፡ ቦታ ስተን ኑሮ የሆነ መታጠፊያ ላይ ወደ ኋላ ስንዞር ተገጣጠምን፡፡ ባንድ መስመር ስዞር ቦታ የዘጋሁባቸዉ መስሎኝ ይቅርታ ስጠይቃቸዉ የሚነዳው ወንድም መኪናዉን አቁሞ ሳይወርድ የስድብ መዓት አወረደብኝ፡፡ ያ ያገሬ ልጅ! ከዚያም ሄዱ፡፡እነማን እንደ ሆኑም ገባኝ፡፡ ጓደኛየ ወደ ቢሮዉ ገብቶ ጉዳዩን ጨርሶ እስኪወጣ ወርጄ ስጠብቀዉ በመኪኗ ተመልሰዉ መጡ፡፡ በማዶ ላይ የቀን ሰራተኞች ምሳ በልተዉ ሰዓቱ እስኪደርስ ጥላ ላይ ያረፉ ነበሩ፡፡ሁኔታዉን ይከታተሉ ኖሮ ትተዉኝ ሲሄዱ መጥተዉ ጠየቁኝ፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል እንደነበርኩና አሁን እንደሌለሁበት፤የስርኣቱ ደህንነት ነን ባዮች ሲሆኑ እያስፈራሩኝ መሆኑንም ስነግራቸዉ በጣም ተናደዱ፡፡ለምን ግርግር አትፈጥርም ነበር አንለቃቸዉም ነበር…..ክብር ለዜጎች! ውድ ህይወት ተከፍሎበት በነበረ ስርዓት ውስጥ፤ህግ አክባሪና ሃይማኖተኛ በሆነ ማህበረሰብ ዉስጥ ተወልዶ ያደገ፤ከድሃ ግብር ደሞዝ የሚበላ የደህንነት ሰራተኛ ነኝ ባይ “እናርዳሃለን….መንግስት ነን፣ ራስህን በጥይት እንበትነዋለን…የምትሰራዉን ሁሉ እናዉቃለን…እድሉን ተጠቀምበት የመጨረሻህ ነዉ….” የሚሉ ቃላት እንዲናገሩ ሰልጥነዉ ሲላኩ በእዉነት ያሳፍራል፡፡ ዱላ ቀረሽ ስድብ አዝንበዉብኝ መኪናቸዉን አስነስተዉ እብስ አሉ፡፡ የመጀመሪያየ ባይሆንም የከዚህ ቀደሞቹ ግን ጨዋዎች ነበሩ! ግን፤ አርፈንም እንድናርፍ አይፈቀድልንም እንዴ? እኛ እንሰራው የነበረው ፖለቲካ ፍጽም ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ ነበር፡፡ አሁንም መብታችን ነዉ፡፡ የነአሞራዉ ደም የፈሰሰዉ ለዚህም እንደነበር እንረዳለን፡፡ተሸብራችሁ ከሆነ በስራችሁ እንጂ በኛ አይደልም፡፡ እኛ ግን ለግዜው ከጨዋታው ውጪ ስላደረጋችሁን በጨዋታው ሜዳ የለንበትም፡፡ ለማስጠንቀቂያውም ለመረጃውም ስርዓት አለው፡፡ የመንግስት አካል የሆነ ተቋም በፈለገዉ መንገድ ህጋዊ ሆኖ ማናገር ይችላል፡፡ መንግስትነት ትልቅ ሃላፊነትና ተቋም መሆኑን ልንነግራችሁ አቅም የለንም፡፡ የተበተነን የቀድሞ የፓርቲ አመራር ማስፈራራትና ማሰር ተራ ብቀላ ይመስላል፡፡ ተራ ህይወት እየመራንም፤አርፈን ተቀምጠንም ልትተዉን ካልቻላችሁ በግፉ መንገድ ግፉበት፡፡ እኛ ከማን እንበልጣለንና ነው!!!

የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ የኢህአዴግ እስር እና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ ቀጥሏል

 በላይ ፈቃዱ

በላይ ፈቃዱ

በኢትዮጵያ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና በመላ ሀገሪቱ ፅህፈት ቤቶች ከፍቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ የኢህአዴግ እስር እና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት 2007 ዓ.ም. ፓርቲው የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ዋነኛ የኢህአዴግ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ መወሰኑን እና ለዚህም ይፋ የምርጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን በማፍረሱ የቀድሞው የአንድነት አመራሮች እና አባላት ከፖለቲካው እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡

ተክሌ በቀለ

ተክሌ በቀለ

ይሁን እንጂ የተወሰኑ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ፓርቲያቸው በኢህአዴግ እና በምርጫ ቦርድ በይፋ ተነጥቆ እንዲፈርስ በመደረጉ የተወሰኑ አመራሮች እና አባላት ሰማያዊ ፓርቲን በይፋ ተቀላቅለው የፖለቲካ ትግሉን ቢጀምሩም አሁንም ከኢህአዴግ እስርና ማስፈራሪያ መዳን አልቻሉመ፡፡ በዚህም በርካታ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራሮች እና አባላት ሰማያዊ ፓርቲን ከተቀላቀሉ በኋላ እነ ስንታየሁ ቸኮል በእስር ላይ ይገኛሉ፡:

አለነ ማፀንቱ

አለነ ማፀንቱ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲያቸው በምርጫ ቦርድ ፈርሶ፤ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለእኔ ለሚታዘዙልኝ በሚል ራሱ ቦርዱ ለመረጣቸው አካላት ቢያስተላልፍም በርካታ የቀድሞ የአንድነት አመራሮች ከፖለቲካ ድርጅት ትግል እንዲታቀቡ ቢደረግም፤ ማስፈራሪያና እስሩ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡ በዚህም ትናንት ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አለነ ማፀንቱ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመኖሪያ ቤቱ በደህንነት እና በፖሊስ ኃይል ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ በመፈፀም የኢሜይል አካውንቱን የይለፍ ቃል በግድ በደህንነቶች ከተወሰደ በኋላ በአዲስ አበባ ጉለሌ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ በላይ ፈቃዱ እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ ተክሌ በቀለም በተመሳሳይ ዕለት በደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ማስፈራሪ እና ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዳዊት አስራደ

ዳዊት አስራደ

ፓርቲው በምርጫ ቦርድ ከፈረሰ በኋላ የስራ አስፈፃሚ አባል የነበረው አቶ ዳዊትአስራደን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች እስማኤል ዳውድ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ መሳይ ትኩዕ፣ ፋንቱ ዳኜ በደህንነት እና ፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውና መደብደባቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የፓርቲው ወጣት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዳንኤል ሺበሺ እና ሀብታሙ አያሌው በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ አንድነት የፊታችን እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ450 በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ማቅረቡን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በቀጠለው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ምክንያት የካቲት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን አፍርሶ “ለእኔ ለሚታዘዙልኝ…” በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ራሱ ቦርዱ ለመረጠው አመራር የፓርቲውን ስም መስጠቱን ይፋ ማድረጉ አያዘነጋም፡፡

%d bloggers like this: