Daily Archives: April 4th, 2015

የት ሂዱ ነው?

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ዓለም ሁሉ ጠላን፤ በየትም አገር እየሄድን ‹‹የሙጢኝ!›› ከራሳችን መሬት በጉልበት እየተነቀልን፣ ከራሳችን ቤት እየተባረርን፤ ከተወለድንበትና ከአደግንበት አካባቢ እየተፈናቀልን፣ ጭራውን ቆልምሞ እንደሚሮጥ ባለቤቱ እንዳባረረው ውሻ በአገኘነው አቅጣጫ እየሮጥን፣ እጃችንን እያርገበገብን ‹‹የሙጢኝ!›› እንላላን፤ የፈራነውን ሞት በየመንገዱ እናገኘዋለን፤ ሞትን ሸሽተን ሞትን ያጋጥመናል፤ የሞቱ ልዩነት አይታየንም፤ በየመንገዱ የሚያጋጥመው ሞት የውርደት ሞት ነው፤ የብቸኛነት ሞት ነው፤ ዘመድ-ወዳጅ ለቀብር የማይገኝበት ሞት ነው፤ ሠለስት፣ አርባ፣ ሙታመት የማይወጣበት ሞት ነው፤ ባዕድ ምስጥ ያላሳደገውን አካል የሚበላበት ነው፤ የሞት ሞት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከአገር አስወጥቶ ባዶ መሬት ብቻ ይፈልግ ይመስል የወያኔ ሎሌዎች በማስፈራራት ሁሉም አገሩን እየተወላቸው እንዲሄድ ያቀዱ ይመስላል፤ ጥንት ኢሰመጉ በምሠራበት ጊዜ በየጊዜው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎችን በማስፈራራት ሰላማቸውን ለመረበሽ ወደስደት ወይም ወደወንጀል ተግባር የሚመሩ የወያኔ አባለች ነበሩ፤ አሁን እንደገና ብቅ ማለት ጀምረዋል፤ ሕጋዊ ሥርዓት እየላላ ጉልበተኞች በግላቸው ለዘረፋና ለቅሚያ እየተሰማሩ ይመስላል፡፡
ስለራሴ ላውራ፤ ከእኔ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የሚፈልጉት የምኖርበትን አፓርትመንት እንደሆነም አላውቅም፤ በእኔ ቤት ያለ ሀብት የሚባል ለወያኔ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለት የገብረ ክርስቶስ ስዕሎች ብቻ ናቸው፤ (በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስዕሎች ለመግዛት የሚፈልግ ያነጋግረኝ)፤ ከዚህ ሌላ ለወያኔ ዋጋ የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ስለዚህም አሁን በእኔ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እኔን ወደስደት ለመግፋት የሚደረግ ሙከራ ይሆናል፤ በ1992 ግድም ተሞክሮ ነበር፤ አልሠራም፤ ዛሬ ይበልጥ አይሠራም፤ ለማናቸውም ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ባልችልም በእኔ ላይ ዘመቻ መጀመሩን አንድ በቅርብ ከማውቀው ወያኔ በትክክል ተረድቻለሁ፤ ይህንን ዘመቻ በመምራት ላይ ያለውንም ሰው ማንነት ተነግሮኛል፡፡
ይህ አገር የአንድ ጉልበተኛ ቡድን ነው ብዬ አልቀበልም፤ የአባቶቼና የእናቶቼ፣ የኤቶቼና የቅድማያቶቼ አጥንትና ደም የገነባው አገር ነው፤ ማንም ለስደት አይዳርገኝም፤ ማንም አስፈራርቶ ኢትዮጵያዊነት መብቴን መግፈፍ አይችልም፤ አልፈቅድለትም፤ በግልጽ በማያጠራጥር ቋንቋ ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም፡፡
እኔን ለማጥቃት ላሰፈሰፉት ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው አንድ እውነት ልንገራቸው፤– በፈለጉትና በተመቻቸው መንገድ በእኔ ላይ በጉልበታቸው ግፍ ቢፈጽሙ ነገ በነሱ ላይ የባሰ ግፍ እንደሚደርስባቸው ይወቁት፤ ሁልጊዜም ከሕግ የወጣ ጉልበተኛነት ጉልበተኛነትን ያነግሣል፤ በመግደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ወያኔዎች ትንሽ ቆም ብለው ያስቡ፤ በመሞትም ድል ይገኛል፤ በመሞትም ማሸነፍ ይቻላል፡፡
በእኔ ላይ የዘመተው ወያኔ ወይም ሎሌ ማናቸውም ሥራ ውጤት እንዳለው ማወቅ አለበት፤ አንድ ነገር አድርጎ ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ ይህ የሳይንስ ሕግ ነው፤ For every action there is a reaction ይላል!

በኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ በአል-ሸዓባብ በተፈፀመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 147 ደርሷል

Garissa-University-College attack

በኬንያ ሰሜን ምስራቅ  በምትገኘው ጋሪሳ የሶማሊያው ታጣቂ አል-ሸዓባብ ሐሙስ ጠዋት መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ በመግባት በከፈተው ጥቃት ሁለት የዩኒቨርስቲው ጠባቂዎችን፣ሶስት የፖሊስ ኦፊሰሮችን እና 142 ተማሪዎች በአጠቃላይ 147 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጆሴፍ ነካይዘሪ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡ በጥቃቱ ከሟቾች በተጨማሪ 79 ተማሪዎች የቆሰሉ ሲሆን፤ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ በታጣቂው ኃይል ታግተው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በፖሊስ እጥረት ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል የለብንም በማለት ከፍተኛ የፖሊስ ቁጥር እንዲጨምርና ወደስልጠና እንዲገቡ  ትዕዛዝ መስጠታቸውን አደጋው በደረሰ ቀን ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡ የሶማሊው ታጣቂ አልሸዓባብ በኬንያ ንፁሃን ላይ የሚያደርሰው ጥቃት እየተበራከተ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በናይሮቢ ዌስትጌት የንግድ ማዕከል ውስጥ በፈፀመው ጥቃት 67 ሰዎች መግደሉ ይታወሳል፡፡ ከዛም በኋላ የሐሙሱን የጋሪሳ ዩኒቨረድስቲ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ጥቃቶችን መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ የጥቃቲ ኢላማዎችም ሙስሊም ያልሆነ ማንኛውም አካል ሲሆን፤ በተለይ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃቱ መጨመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እንደ ሀገሪቱ ፖሊስ መጃ መሰረት ከ2004 ዓ.ም. እስከ ታህሳሥ 2007 ዓ.ም. ብቻ የአልቃይዳ ክንፍ በሆነው በሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ አልሸዓባብ የተገደሉ ኬኒያውያን ቁጥር 312 ደርሶ ነበር፡፡ በጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተፈፀመውን የጅምላ ግድያ ጨምሮ በሶማሊያው ታጣቂ አል-ሸዓባብ የተገደሉ ኬንያውያን  459 ደርሷል፡፡

Garissa-University-College attack

በዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ተማሪዎች ላይ ታጣቂው  ከፈፀመው የጅምላ ግድያ በኋላ አራት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሲገደሉ፣ አምስት ተጠርጣሪ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር  መዋላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥ የተገደሉ ሰዎችን ማንነት ለመለየትና ወደ የቤተሰቦቻቸው ለመላክ አሰከሬናቸው ወደ ናይሮቢ መላኩም ታውቋል፡፡

ጋሪሳ ከናይሮቢ ሰሜን ምስራቅ 367 ኪሎ ሜትር ስትርቅ፤ ከኬንያ ሶማሊያ ድንበር ያላት ርቀት  ደግሞ 147 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የታጣቂ ቡድኑ በተመሳሳይ መልኩ በዩጋንዳ የትምህርት ተቋማት ላይ ጥቃት ለመፈፀም ዕቅድ እንዳለው ተጠቁሞ፤ የዩጋንዳ የደህንነትና ፀጥታ አካላት የሀገሪቱን ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በላቀ በተጠንቀቅ ላይ ሆነው እንዲጠብቁ መደረጉንም የዩጋንዳ ከፍተኛ ፖሊስ ኦፊሰርን ጠቅሶ የአውስትራሊያው ኤቢሲ ዘግቧል፡፡

በኬንያ መንግሥት ተፈላጊው መሐመድ መሐሙድ

በኬንያ መንግሥት ተፈላጊው መሐመድ መሐሙድ

በተለይ ከጥቃቱ በስተጀርባ ዋና አቀናባሪና በጋሪሳ ከተማ የእስላማዊ ትምህርት ቤት መምህር እንደነበር የተጠቆመው መሐመድ መሐሙድ የገደለ ወይም ያለበትን የጠቆመም እንዲሁም ይዞ ለሚያስረክብ የኬንያ መንግሥት ፖሊስ 215 ሺህ የአሜሪካን ዶላር (200 ሚሊዮን የኬንያ ሽንልንግ)እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል፡፡ ጥቃቱን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነ ፀሐፊ ባን ኪ ሙንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማኀበረሰቦች ያወገዙት ሲሆን፤ ታጣቂው አልሸዓባብ በበኩሉ ድርጊቱ የፈፀመው ከኬንያ ጋ ጦርነት ውጊያ ላይ ስለሆንን ነው ማለቱን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

%d bloggers like this: