ከ3 ወር በፊት የታፈነው የመኢአድ አመራር የት እንደደረሰ አልታወቀም
የሶስቱ ፓርቲዎች አመራሮች ለታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሮባቸዋል
የገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ከየ ክፍለ ሀገሩ ማሰር በጀመሩበት ወቅት በደህንነትና ፖሊሶች የታፈነው የመኢአድ አመራር የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ መግለፃቸውን የነገር ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የሰሜን ጎንደር አመራር የሆነው አቶ ችሎት ባዜ መስከረም 2 ቀን 2007 ዓ.ም በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች የታፈነ ሲሆን፤ በወቅቱ ቤተሰቦቹ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንደተዛወረ መረጃ ደርሷቸው እንደነበር መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡ ሆኖም በተደጋጋሚ አቶ ችሎት ወደ ማዕከላዊ መዛወር አለመዛወሩን ቢጠይቁም እንዳልመጣ ተነግሯቸዋል፡፡
የታፈነው የመኢአድ አመራር ማዕከላዊ እንደሌለ የተነገራቸው ቤተሰቦቹ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከሆነ በሚል ሪጂስትራል ስሙ እንዳለ ቢያስጠይቁም እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከየ ክፍለ ሀገሩ በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ታፍነው በአሁኑ ወቅት ማዕከላዊ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የመኢአድ አመራሮች በትናንትናው ዕለት አራድ ምድብ ችሎት ቀርበው ለታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሮባቸዋል፡፡
የ9ኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር በወቅታዊ የጋራ እንቅስቃሴያቸው ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የፊታችን ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ስላዘጋጁት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከታች ይመልከቱ፡፤
ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ ዕለታዊ መግለጫ
ዝግጅታችን ተጠናክሮ ቀጥሏል! እርስዎም ይዘጋጁ!
‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› በሚል የአንድ ወር መርሃ ግብር ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ስርዓቱ መርሃግብሮቻችን በማጨናገፍ ለነጻነት የምናደርገውን የትግል ጉዞ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል፡፡ ሆኖም የነጻነት ትግሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚያስከፍል መሆኑን የተረዳው ትብብሩ ለገዥው ፓርቲ አፈና ሳይንበረከክ ስራውን ቀጥሏል፡፡ በተለይ ከመርሃ ግብሮቻችን መካከል ስርዓቱን ያስፈራውን የ24 ሰዓት የአደር ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅታችን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ ለዚህ የአዳር ሰልፍ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ሰው በሰው በመቀስቀስ፣ ወረቀት በመበተን እንዲሁም በየ ፓርቲዎቻችን ስም የታተሙ ቲሸርቶችን በመልበስ ህዝቡን እያነቃቃን እንገኛለን፡፡ ሰልፉ እስከሚደረግበት ህዳር 27/28 2007 ዓ.ም ድረስም ዝግጅታችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ይህን መርሃ ግብር ስንነድፍ ለነጻነት የሚከፈለው መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተንና የቀድሞ አባቶቻችን ካሳዩት ቆራጥነት ተምረን ነው፡፡ በዚህ ለቀጣይ የትግል ጉዞአችን ጭላንጭል ለምናይበት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በውጭም ሆነ አገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት ለምናደርገው ጉዞ የጀመርነውን የሰው በሰው ቅስቀሳ በመደገፍ፣ በገንዘብ፣ በሞራልና በሌሎች ለመርሃ ግብሩና ለአጠቃላይ ትግሉ ይጠቅማል ባሉት መንገድ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ መርሃ ግብሩ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በሞራልና በተለያየ መንገድ መልዕክቶቻችን ለህዝብ እንዲደርሱ ድጋፍ ያደረጋችሁልን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ልባዊ ምስጋናችን ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ አሁንም ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ በመቀጠል ታሪካዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡
በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በኩል ለሰላማዊ ሰልፉ የሚያስፈልገው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ህዝቡ በዝግጅቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በመስቀል አደባባይ በሚኖረን ቆይታ የሚያስልጉት ቁሳቁሶች በተለይም ደረቅ ምግብና ውሃ ከአሁኑ እንዲያዘጋጅ ማስታወስ እንፈልጋለን፡፡ ህዳር 27/28 2007 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የሚደረገው የ24 (አዳር) ሰልፍ ኢትዮጵያውያን ላይ የተጫነውን የፍርሃት ድባብ በመስበር ለነጻነት የምናደርገው ወሳኝ ጉዞ ጅማሬ በመሆኑ በሁሉም የማህረሰብ ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ራሳቸውንና አገራቸውን ነጻ ለማውጣት የትግሉ አካል እንዲሆኑ ጥሪያችን እያቀርባለን፡፡
ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!
ህዳር 23/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
እናታችን ፋናዬና ጋዜጠኛ ተመስገን በዝዋይ…
ታሪኩ ደሳለኝ
(የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም)
ያቺ የስምጥ ሽለቆ ከተማ ይበልጥ መንደድ ከጀማመራት አንድ ወር አልፏታል:: በፍትህ መዛባት ስሜቱ የተጎዳ፣ በወገኖቹ ስቃይ መንፈሱ የታመመ፣ ሀገራቸውን ከስቃይ መታደግ በሚችሉበት እድሜያቸው በታሰሩ፣ በተሰደዱና በተገደሉ ወገኖቹ ልቡ ያዘነ፣ ለሀገሩና ለባንዲራው ያለው ፍቅር ጥልቅ የሆነ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በውስጧ ይዛለች፡፡ ዝዋይ፡፡
ከዚህች ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው የዝዋይ እስር ቤት ለመሄድ የአስፓልት ዱካ እንዳረፈበት በሚያሳብቀው ኮሮኮንቻማ መንገድ ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ከረጅም ዓመታት በፊት ተሰርቶ ዛሬ አስታዋሽ ያጣው ይህ ጎዳና እስረኞችን የመጠየቁን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከፀሐዩ ግለት ትይዩ ያለው የመሬቱ አቧራ በእግሩ ቆሞ ይሄዳል ብል አይበዛበበትም፡፡ ይህን አልፈን ግዞት ቤቱን እናገኛለን፡፡ የእስር ቤቱን መግቢያ ያለበሰው አቧራ ደግሞ ቅጥሩን በቁፋሮ የተገኘ ጥንታዊ ከተማ አስመስሎታል፡፡ የግቢው ገፅታ ለዕይታ በማይስቡ ነገሮች ቢከበብም፣ ተናፋቂውን ብዕረኛ ግን ደጋግሜ እንድጠይቀው ከወንድምነት የሚዘለው ጥንካሬው ይስበኛል፡፡
በአቧራውና በንዳዱ መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀድሞ ይልቅ በጠነከረ ፅናቱ ስለመኖሩ ሳስብ ደስተኛ እሆናለሁ፡፡ እናታችንስ ምን ታስብ ይሆን? የማይበርድ፣ የማይዳፈንና የማይጠፋ የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከአቧራውና ከንዳዱ በላይ መሆኑ ለእርሷ ምን ስሜት ያጋባባታል?
እናታችንና ተሜን ሲገናኙ…
ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 20/07 ዓ.ም ነው፡፡ እናቴ አብረዋት ከኖሩ ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን፣ ዝዋይ እስር ቤት ከከተመ አንድ ወር ያለፈውን ተመስገንን ልታየው ተሰናድታለች፡፡ ዝዋይ ከሄደ ወዲህ አይታው አታውቅም፡፡ እንደናፈቃት ግን የፊቷ ገፅታ ይመሰክራል፡፡ እንደ ልጅነቱ ፀጉሩን ባትደባብሰውም፤ እጁን ልትነካውና በዕርጅና አንደበቷ ‹እንዴት ነህ?› ልትለው ወደዚያው እያቀናች ነው፡፡ ጠዋት ወጥተው ማታ እንደሚገቡት፣ ክፍለ-ሀገር ሰንብተው እንደሚመለሱት እንደ ጓደኞቿ ልጆች ተመስገን እንደማይመለስ የተረዳችው እናታችን ልጇ ጋር እየሄደሰች ነው፡፡
ለሊት 11፡30 ከጀሞ ኮንዶሚኒየም የተነሳችው መኪና ዝዋይ የደረሰችው ከጠዋቱ 2፡20 ላይ ነበር፡፡ አስፋልት መሰል ፍርስራሽ መንገዱን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ዛሬ አልሰጠኝም፡፡ ፍተሻውን አልፈን እስረኛና ጠያቂ የሚገናኘበት ቦታ ላይ ደረስን፡፡ ከነበርነው ሰዎች ይልቅ እናታችን ጉጉት እንዳደረባት ለመናገር ሁኔታዋን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡
እናታችን ተመስገን በልጅነቱ ከዕኩዮቹ ጋር ተጫውቶ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ስራ ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፤ አንዳንዴም ሲያመሽ ደውላ ‹‹አልመሸም፤ የቀረው ለነገ ይቆይህ›› ትለዋለች፤ እርሱም ሁሌ እንደሰማት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ልጇን የምትጠብቀው ከትምህርት ቤት አልያም ከጨዋታ ወይም ከስራ አይደለም፡፡ ከእስር ቤት ውስጥ እንጂ!
እናታችን እስረኞች ከሚወጡበት በር ላይ ከተቀመጠችበት ደቂቃ ጀምሮ አይኗን አላነሳችም፡፡ በሩ ሲከፈት የወታደር ልብስ የለበሰ ወጣት ወጣ፡፡ ከወታደሩ በኋላ ተሜ እስካርፉን እንዳደረገ ተከተለ፡፡ እናቴ ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ ዐይኗቿ እንባ አዘሉ፡፡ በዕስረኛና በጠያቂ መሀል ያለውን አጥር ተደገፈች፡፡ ሌላ ጊዜ አጥሩን መደገፍ የሚከለክሉት ወታደሮች እናታችንን ግን ጥቂት ታገሷት፡፡ ምን ያድርጉ? እነሱም እኮ እናት አላቸው፡፡ ከተመስገን ኋላ ሌላ ወታደር አለ፡፡ በሁለት ወታደሮች መካከል ሆኖ ተሜ እናቱን አያት፤ ፈገግ አለ፡፡ እየቀረበ ሲመጣ ግን ፈገግታው ከፊቱ ላይ ጠፍቶ በሀሳብ ተተካ፡፡ እናቴን በዚህ እድሜዋ አንከራተትኳት ብሎ እንዳላሰበ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ከዚህ ይልቅ ስንትና ስንት እናቶች በየቦታው እየተንከራተቱና እየተሰቃዩ ስለመሆናቸው እያሰበ የተጨነቀ ይመስላል፡፡ እናትና ልጅ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ቆዩ፡፡ ምን አለ ባይለያዩ? እንዲሁ እንዳሉ ወደ ቤት ቢሄዱስ ምን ነበረበት?
ይሄ ግን አይሆንም፤ ይሄ ቦታ ተሜ ለሀገሩ የከፈለውን፣ እየከፈለ ያለውንና የሚከፍለውን መስዋዕትነት ማቅረቢያው ቦታ ነው፡፡ ተሜ ወደ ቤት አይሄድም፡፡
ተሜና እናቴ የተጫወቱት ብዙ ነው ፡፡ ሲገናኙ የነበረው ድባብ ጠፍቶ ሁለቱም ደስ ብሏቸዋል፡፡ ተሜ ትንሽ አይቷት ‹‹ከስተሻል›› ሲላት ፈገግ እንዳለች ‹‹አረ አልከሳሁም፤ አንተ ግን ጤናህ እንዴት ነው?››፤ ‹‹ደህና ነኝ››… እናቴ በየመሀሉ ጨዋታቸውን ገታ እያደረገች በስስት ታየዋለች፡፡ እናትና ልጅ የሆድ የሆዳቸውን እንዲያወሩ የፈቀዱት ወታደሮችም ሁለቱን በስስት የሚያዩ ይመስላሉ፡፡
ሳይታወቀን 6፡00 ሆነ፡፡ የመሰነባበቻ ጊዜ ደረሰ፡፡ እናቴ እየሳቀች አቀፈችው፤ ተሜም እየሳቀ ተሰናበታት፡፡ እንደ አመጣጡ በሁለቱ ወታደሮች መካከል ሲሄድ ከጀርባው ትክ ብላ አየችው፡፡ የሆነ ነገር ልትል የፈለገች ትመስላላች፡፡ ‹‹ተመስገን›› አለች፤ አልሰማትም፡፡ በሩን አልፎ ገባ፡፡ እሱ ፊት የደበቀችውን እንባ ማቆም አልቻለችም፡፡ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ከፈገግታዋ ጋር አለቀሰች፡፡
እሁድ ህዳር 21/07 ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት፡፡ እናቴ ልጇ እስኪፈታ አልጋ ላይ አልተኛም ብላ መሬት መተኛት ከጀመረች 1 ወር ከ17 ቀኗ ነው፡፡ የዛሬውን ለሌት እንዳለፉት ጊዜ አንዴም ተነስታ ‹አይ ልጄ› ወይም ‹እህህ….እህህ….› ሳትል በሰላም ተኝታ በማደሯ ሳልተኛ እያየኋት አደርኩ፡፡ ልክ 12፡10 ሲል ነቃች፡፡ ስታየኝ እያየኋት ነው፡፡ ‹‹ስንት ሰዓት ሆነ?›› ነገርኳት፡፡ አላመነችም፡፡ ተሜ ከታሰረ ጀምሮ እንደ ዛሬ ተኝታ አታውቅም፡፡ ተነሳች፡፡ ‹‹እስከዚህ ሰዓት ስተኛ ዝም ትላለህ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹እንዴት ዝም አልልም?›› አልኳት፡፡ ‹ዛሬ የዓመቷ ማሪያም ነች› አለችኝ፡፡ ፊቷ ላይ ድካም አይታይባትም፡፡ … ከደቂቃዎች በኋላ የሀገር ባህል ጥበብ ቀሚስ ለብሳ አየኋት፤ አምሮባታል፡፡ የደስታ ሲቃ ይዞኝ ‹ትላንት እንዴት ነበር?› አልኳት፡፡ በፈገግታ እያየችኝ ‹‹ልጄ ጀግና ነው፤ ጀግና›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም በመስማማት ራሴን ነቀነኩ፡፡ እናቴ በንጋት ፀሐይ ታጅባ የሀገር ባህል ልብሷን እንደለበሰች ስትሄድ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ይሄ ብርታቷ እስከመቼ እንደሚቆይ እያሰብኩ ነበር፡፡
ተሜ ለሀገሩ ሲልና ሀገሩ እንድትሆን የሚመኝላትን በመፃፉ በግዞት እስር ቤት በአቧራና በንዳድ መሀል እንዲሰነብት ተፈርዶበታል፡፡ ፍትህ የነገሰባት፣ ልጆቿ የማይገደሉባትና የማይሰደዱባት ኢትዮጵያ እንደምትመጣ በተቃጠለ ስሜት እያሰበ፣ በማለዳ የወጣችውን የንጋት ፀሐይ በፈገግታ እያያት እንደሆነ ሳስብ እኔም በደስታ ተሞላው፡፡
ሦስት የፖሊስ መኮንኖች ሰው በማፈን ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ
ታምሩ ፅጌ
-አድራሻቸው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የሆኑ ሦስት የፖሊስ መኮንኖች፣ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት አንድ ሰው አፍነው ወደ ጅግጅጋ በመሄድ ላይ እያሉ ተይዘው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎቹ ዋና ኢንስፔክተር ጐይቶም አረጋዊ ኪዳነ ማርያም፣ ረዳት ኢንስፔክተር አንተነህ አስናቀ ተፈራና ኮንስታብል ዘሪሁን ሲሳይ ሲሆኑ፣ ሁሉም በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለሕግ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በማስገደድና ከሕግ ውጪ የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉትን አቶ አህመድ ኑርን ይይዟቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከሶማሌ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ተበዳዩን የያዟቸው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጐተራ አካባቢ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡
የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉት አቶ አህመድን ከነበሩበት ተሽከርካሪ ላይ ጐትተው በማውረድ፣ በሽጉጥ በማስፈራራት፣ በቦክስ ፊታቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍላቸውን በመምታት ራሳቸውን ሲስቱ፣ ተጠርጣሪዎቹ በያዙት ተሽከርካሪ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ መድኃኔዓለም አካባቢ እንደወሰዷቸውም ተገልጿል፡፡
ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘውና ‹‹የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ ቢሮ›› በመባል በሚታወቀው ጊቢ በሚገኝ ሰርቪስ ቤት ውስጥ በማስገባት፣ ለሦስት ሰዓታት እንዳቆዩአቸውም ክሱ ያብራራል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከሦስት ሰዓታት በኋላ የሰሌዳ ቁጥሩ 0071 በሆነ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ፒክአፕ ተሽከርካሪ ጭነው፣ ወደ ጅግጅጋ ያመራሉ፡፡ ልዩ ቦታው አዋሽ ድልድይ ኬላ ላይ የሚጠብቁ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባላት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸውና ሰውን ከሕግ ውጪ ይዞ ማስቀመጥ ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና የጠየቁ ቢሆንም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ውድቅ አድርጐ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ብይን ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለአዳሩ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ አስገባ
- ቦታው መስቀል አደባባይ እንዲሆን ወስኗል
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 28/2007 ዓ.ም ለሚደረገው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የእውቅና ደብዳቤ አስገባ፡፡
ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የገባው ደብዳቤ በሰማያዊ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ ተፈርሞ የገባ ሲሆን የእውቅና ደብዳቤውንም ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲና የትብብሩ ሊቀመንበር፣ የከንባታ ህዝቦች ሊቀመንበርና የትብብብሩ ም/ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርጌሎ፣ አቶ ግርማ በቀለ ከኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የትብብሩ ፀኃፊ እና የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙደሲር አስገብተዋል፡፡የትብብሩ አመራሮች ወደ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ በሄዱበት ወቅት የአቶ ማርቆስ ተወካይ ለሆኑት አቶ ፈለቀ አበበ ደብዳቤውን ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም ተወካዩ ‹‹የከንቲባ ጉዳዮች ጽ/ቤ ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የለም፡፡ እሱ ካልመራበት መቀበል አንችልም›› በሚል ደብዳቤውን አልቀበልም እንዳሏቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹ ወደ አቶ አሰግድ ቢሮ ቢያቀኑም እንዳላገኙዋቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የትብብሩ አመራሮች ደብዳቤ መስጠት እንጂ ደብዳቤ ማስመራት የሰራተኞቹ እንጂ የእነሱ ስራ እንዳልሆነ በመግለጽ ደብዳቤውን ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ታመዋል የተባሉት የአቶ ማርቆስ ተወካይ የሆኑት አቶ ፈለቀ ቢሮ በአራት ምስክሮች ፊት አስቀምጠው መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ አመራሮቹ የእውቅና ደብዳቤውን አቶ ፈለቀ ቢሮ አስቀምጠው ከመውጣታቸውም ባሻገር በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በፈጣን መልዕክት (ኢ ኤም ኤስ) በሪኮመንዴ ቁጥር eg157416502et መላካቸውን ገልጸዋል፡፡
የአዳር ሰላማዊ ሰልፉ ህዳር 27 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተጀምሮ ህዳር 28 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ቦታውም መስቀል አደባባይ ላይ እንደሚሆን መወሰኑ ታውቋል፡፡
የትብብሩ አመራሮች የእውቅና ደብዳቤውን ለማስገባት በሄዱበት ወቅት በቦታው የትብብሩ አመራሮች የሚያውቋቸው ደህንነቶች ባለ ጉዳይ በመምሰል ይመላለሱ እንደነበርና ፖሊሶችም ይከታተሉ እንደነበር መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡