ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ወደብ
ብስራት ወልደሚካኤል
Afrosonb@gmail.com
አንድ መንግስት ዛሬ በሚሰራው ሁሉ ነገንም ያስባል፤ኢትዮጵያ ግን ለዚህ የታደለች አትመስልም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ላለፉት 23 ዓመታት ከተከናወኑ በርካታ ዘመን እና ታሪክ አይሽሬ ስህተቶች መካከል የሰሞኑን የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ስምምነትን ማየት በቂ ነው፡፡ ስምምነቱ በየትኛውም ዓለም ያሉ ሀገሮች ያልተፈፀመ እና ሊፈፀም የማይችል በኢትዮጵያ ግን እውን ሆኗል፤እስካሁን ምክንያቱ በግልፅ ባይታወቅም፡፡
ገዥው ስርዓት ለህዝቡ ቃል የገባውን ላለመፈፀሙ በተደጋጋሚ ከሚገልፃቸው ቃላቶች እና ምክንያቶች መካከል የአፈፃፀም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብኝም የሚለው ነው፡፡ እውነታው ግን ከሚናገረው በተቃራኒ የፖሊሲ እና የአፈፃፀም ችግር ይስተዋልበታል፡፡ በመጀመሪያ ፖሊሲ ሲነደፍ የሀገሪቱን አቅም፣ ፍላጎት፣ ነባራዊ ሁኔታ፣ የህዝቡ ፍላጎትና አኗኗር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የዜጎችን እነ የሀገሪቱን ቁሳዊና ስነልቦናዊ አዎንታዊ ውጤት ታስቦ የሚዘጋጅ የተግባር ሰነድ ነው፡፡ በርግጥ ፖሊሲን ከየትኛውም ሀገር መኮረጅ ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ውጤታማነቱ የሚለካው የፖሊሲው ትግበራ አፈፃፀም ነው፡፡
ፖሊሲ በራሱ ከሌሎች የተለየ ሙያዊ ስነምግባር የሚጠይቅ በመሆኑ የአስፈፃሚውንም አካል አቅምና ብቃት እንዲሁም የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚፈተሽበት ነው፡፡ ስለሆነም የፖሊሲ ችግር የለም፤የአፈፃፀም እንጂ ሚባል ከሆነ ፖሊሲውን ሊያስፈፅም የሚችል ብቃት ያለው አካል የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ችግሩን ለማረም ከሁለቱ አማራጮች አንዱን መውሰድ ግድ ይላል፡፡ ይህም ሚነደፈው ፖሊሲ ከገሪቱ አቅምና ፍላጎት ጋር ሳይሆን ከስራ አስፈፃሚው(ከገዥው ፓርቲ አመራሮች) አቅምና ብቃት ጋር በሚስማማ መልኩ መንደፍ፤ አሊያም ፖሊሲ የማስፈፀም ችግር አለብኝ ብሎ ያለው አካል ፖሊሲ የማስፈፀም አቅምና ብቃት ላለው አካል በሰላም ስልጣን መልቀቅ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ አለበለዚያ በፖሊሲ ንድፍና አፈፃፀም ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘፈቀደ ወዲያው ለማረም መሞከር የበለጠ ሀገርን እና ትውልድን ሊያጠፋ የሚችል ከባድ ስህተት እንዲፈፀም በር ሊከፍት ይችላል፡፡
በተለይ የአንዲት ሀገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተወደደም ተጠላ መሰረታዊ የሚባሉ ሶስት ነገሮችን ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ታሳቢ በማድረግ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም አንዲት ሀገር ፍላጎቷን፣መብትና ጥቅሟን ለማስፈፀም የምትንቀሳቀስባቸው በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሀገሪቱ ሁሉ-አቀፍ ፖሊሲ ግልባጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለየት የሚያደርገው ፖሊሲው ከሀገር ውጭ ትኩረት ማድረጉ ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ነው የሚባለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሐሳብ ደረጃ ከላይ ካለው በተቃራኒ ትኩረቱ ኢኮኖሚ ላይመሰረት ያደረገ ነው መባሉ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ዓለም ሀገርም ሆነ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሳይንስ ንድፈ ሐሳብና ትግበራ አንፃር እጅግ ጎዶሎ መሆኑን ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚ በባህርይው ዛሬን እንጂ ነገን የማይል መሆኑ፣ስለአለውም ሆነ መጪው ጊዜ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እና ግንኙነት ቦታ በጥልቀት ከመገንዘብ ይልቅ ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር ነውና፡፡ ከውጭ የሚገኝ የኢኮኖሚ ትብብር በራሱ ደግሞ ያለ ፖለቲካዊ ስራ እና ግንኙነት ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ገዥው እና አስፈፃሚው ስርዓት አርቆ የማሰብም ሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምንነት ትርጓሜና ተግባር ላይ ምን ያህል የአቅምና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ሀገሪቱንም ሆነ ህዝቡን ለአላስፈላጊ ከፍተኛ መስዋዕትነት መዳረጉ አይቀርም፤ ዳርጓልም፡፡
በቅርቡ 90 ሚሊዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብመካከል 4.5 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልህዝብ ከራሱ የከርሰ ምድር103 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ 800 ሺህ ለሚሆነው የጅቡቲ ነዋሪ ንፁህ የመጠጥ ውሃ በኢትዮጵያ ወጭ ሊቀርብ ነው፡፡ ይህም እ.አ.አ ባለፈው መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ከተፈፀመ የሰነበተውን ለወጉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. መፅደቁ በብዙዎች ዘንድ አግራሞት ፈጥሯል፤ሊፈጥርም ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መኖሩን የሚያመላክት ነገር አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ እስካሁን በደፈናው ፖለቲካዊ ጥቅም ከሚል በስተቀር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለም መባሉ በራሱ፤ ስርዓት እከተለዋለሁ ከሚለው ኢኮኖሚያዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ይጋጫል፡፡
በርግጥ እንኳን ቀጥተኛ ትስስር ካላት ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ቀርቶ ከማንኛውም የውጭ ሀገር መልካም ግንኙነትና ጉርብትና መፍጠር ጠቃሚም ተገቢም ነው፡፡ ይበልጥ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችለው ግን የሁለቱንም ሀገራት ከጥርጣሬ የፀዳ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ካደረገ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ተለመደና ጤናማ ግንኙነትና ጉርብትና ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የራስን ፖለቲካዊ፣ ተፈጥራዊና እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት የሚመሰረት ወዳጅነት በሀገሮቹ መካከል የነበረውን ግንኙነት በማሻከር በጥርጣሬ እንዲመሰረት በማድረግ ያልታሰበ ችግር የመፍጠር አጋጣሚ ይኖረዋል፡፡እስኪ ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል በተደረገው ስምምነት አለ የተባለው ፖለቲካዊ ጥቅምስ እውን አለን? የሚለውን እና ነገ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረውንፖለቲካዊ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በአጭሩ እንመልከት፡፡
ፖለቲካዊ ፋይዳ
በሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች መካከል የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት ሁለቱንም የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ማንኛውም ስምምነት በቀዳሚነት ፖለቲካዊ ፋይዳው ነው የሚታየው፡፡ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል አካል አንዱ፤በድሬዳዋ እና ጅቡቲ አዋሳኝ ከሆነው ሽንሌ ዞን ለ30 ዓመታት በ100 ኪሎ ሜትር የድንበር ርቀት ያለውን 20 ሄክታር መሬት ጨምሮ 4ሺህ ሄክታር የከርሰ ምድር ውሃ ያለበትን የተፈጥሮ ሃብት በነፃ እንድታገኝ ተደርጓል፡፡ ይህም ጅቡቲ ለዓመታት ፈተና የሆነባትን የንፁህ ውሃ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ያለምንም ውጭ ማግኘቷ ከወደብ ጋር በተያያዘ በፖለቲካው ያላትን የበላይነት የሚያመላክት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች ካሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እጥረት እየተሰቃዩ ባሉበት ሰዓት ከ800 ሺህ ለማይበልጥ ጎረቤት ሀገር ሚዛናዊ ያልሆነ ወጪ እንድታደርግ አስገዳጅ ነገር መፍጠሯ እና እየፈጠረች መሆኗ ስምምነቱ አሉታዊ የፖለቲካ ፋይዳ እንዲኖረው አስችሏል፡፡
ሌላው የውሃ ቁፋሮው የሚካሄድበት የሽንሌ ዞን ነዋሪዎች እስካሁን ለ23 ዓመታት ንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በአግባቡ ሳያገኙ ዛሬ በአንድ ጊዜ ለጅቡቲ ህዝብ ጥቅም ሲባል ጭራሽ ነዋሪው እንዲፈናቀል መደረጉ በሶማሌ ክልልም ሆነ በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ስርዓቱ የሀገርና የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በአካባቢው ሌላ ቅራኔ በመፍጠር በቀጠናው ለእስኩኑ በባሰ የፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል፡፡ በርግጥ ገዥው ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ጥቅም ይኖረዋል በሚል የጅቡቲ ወደብን በቀጣይነት በተረጋጋ ሁኔታ በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን በሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ለመጠቀም ለመደለል ማሰቡ መጭውን ጊዜ ያለማገናዘቡን ከማመልከት በስተቀር በቀጣይ ጅቡቲ ውሳኔ ላይ ያን ያህል የጎላ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እዚህ ላይ ኢህአዴግ ያለህዝቡ ፈቃድ ላለፉት 23 ዓመታት የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የሆነውን የአሰብ ወደብን በአሁኑ ለጅቡቲ የሀገሪቱን የተፈጥሮሃብት ከክፍያ ነፃ በሆነ መንገድ እንደሰጠ ያኔ ለኤርትራ መስጠቱ ያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ዛሬም መድገሙ ገዥዎቹ አሁንም ከስህተት ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመማርዝግጁ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡
ሌላው ኢህአዴግ ህዝብ ሳይመክርበትና ሳይወያይበት እንዲሁም ሳይፈቅድ የሀገሪቱን መሬት ከነተፈጥሮ ሃብቱ በነፃ አሳልፎ መስጠቱ ነገ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በሚኖረው ጉርብትና እና ወንድማማችነት መካከል ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ነገ በኢትዮጵያ የፖለቲክ መንግስት ስርዓት ለውጥ ቢፈጠርና ይህ ስምምነት አዲስ በሚመሰረተው የመንግስት ቢሻር፤ ለኢትዮጵያ ሌላ አዲስ የጎረቤት ሀገር በጠላትነት የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም የተደረገው ስምምነት ሁለቱንም ሀገሮችና ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ሚዛናኑን የጠበቀ ስምምነት አልተፈፀመምና፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ በአንድ መነፅር ብቻ በመመልከት ለጅቡቲ የኃይል አቅርቦት መብራት እጅግ በቅናሽ ዋጋ ማቅረቡ እና ይህን ውሃ በነፃ መፍቀዱ በቀጣይ ለሚጠቀምበት የወደብ ኪራይ ማረጋጊያ እንደ ማታለያ ለመጠቀም አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላው የዋህነትና ድፍረት ነው፡፡
ጅቡቲ በቀጠናው ካላት መልካዓ ምድራዊ ፖለቲካ አቀማመጥ አንፃር በአሁን ሰዓት ሁሉ ነገሯን በራሷ ትወስናለች ማለት ዘበት ነው፡፡ ቀጠናው በቀይባህርና እና ህንድ ውቅያኖስ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ እንደመገኘቷ፣ የቀጠናው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምዕራባውያንንም ሆነ እንደ ቻይና እና ኢራን ያሉ እስያ ሀገሮችንም መሳቧ እርግጥ ነው፡፡ በተለይ ፈረንሳይ እና አሜሪካ በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ከአረብ ሀገራት ለሚያጓጉዙት ግዙፍ የቶታል፣ሞቢል እና የመሳሰሉ የነዳጅ ኩባንያዎቻቸው ደህንነት ጅቡቲን በእጅ አዙር መጠበቅና መንከባከብ ስለማይቦዝኑ፤ኢትዮጵያ አሁን ባደረገቸውና ለወደፊቱም ለማድረግ ባሰበችው የማታለል ተግባር ፈረንሳይና አሜሪካንም ጭምር መሆኑን ልታጤን ይገባል፤ይህ ደግሞ የላጭን ልጅ ቅማል በላት ዓይነት ተረት መሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ ሚዛኑን ያልጠበቀውና ነገን ታሳቢ ያላደረገው የጅቡቲ ብቻ ተጠቃሚነት የውጭ ጉዳይ ስምምነት ለኢትዮጵያ አሉታዊ የፖለቲካ ፋይዳ እንጂ ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አኳያ ሲሰላ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ከመተግበሩ በፊት ውሃ የሚቆፈርበት ቦታ ግልፅና ገለልተኛ በሆነ አካል የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በማካሄድ ራስን ከአላስፈላጊ ፖለቲካዊ ኪሳራ ማዳኑ የተሸለ ነው፡፡
ማኀበራዊ ፋይዳ
እንደማዕከላዊ መረጃ ኤጀንሲ ከሆነ ከኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከኦሮሞ እና አማራ ክልል ነዋሪ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ የሚገኘው እና 4.5 ሚሊዮን ነዋሪ ያለው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ በቂ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሳያገኝራሷን ለቻለች ሉዓላዊ ጎረቤት ሀገር በኢትዮጵያ ወጪ መደረጉ ስርዓቱ ገዥነት ለጅቡቲ ነው ወይስ ለኢትዮጵያ ያስብላል፡፡ የሶማሌ ክልል ነዋሪ በ 5.6 እጥፍ ከጅቡቲ ህዝብ ይበልጣል፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ፍላጎትና ፍጆታ ሳያሟላ፤በኢትዮጵያ ወጭ ለጅቡቲ ማኀበራዊ አገልግሎት የሚውል፤ ውሃ ከሚቆፈርበት የሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ለድሬዳዋ እና ሐረር በቅርብ ርቀት ቢገኝም የሀብቱ ባለቤት የሆኑት የአከባቢው ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ችግር ሲሰቃዩ እስካሁን መፍትሄ ያላቸው የመንግስት አካል የለም፡፡
በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ለሚገኙ ነዋሪዎችም ቢሆን ያለው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው፡፡ በሌላ በኩል በመንግስት ይህን የማኀበራዊ አገልግሎት ችግር ለመፍታት ከቃላት ባለፈ በተግባር የተሰጠ መፍትሄ ሳይኖር በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ አካል ላልሆነቸው ጅቡቲ አብዝቶ መጨነቅና ከድሃ ህዝብ ጉሮሮ በጀት ተነጥቆ መመደቡ ትልቅ የሞራል ኪሳራ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ያለው ተቆርቋሪናትና ማኀራዊ አገልግሎት ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነገ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮውን ተከትሎ የሚፈናቀሉ ዜጎች ለማን ተጠቃሚነት በሚል ከቀያቸው ሊነሱ ነው? እኚህ ዜጎች የነሱ ችግር ሳይፈታ አላቂ የሆነውን የተፈጥሮ ሃብታቸውን ያለፈቃዳቸው ተነጥቀው ለተጨማሪ የማኀበራዊ ቀውስ መዳረጋቸው በጅቡቲና በአዋሳኝ ድንበር ባሉ ኢትዮጵያውን መካከል ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ የዚህ ቅሬታ ደግሞ ወደ ግጭት በማምራት ለተጨማሪ ማበራዊ ቀውስ መዳረጉ ከወዲሁ መጤን ያለበት ጉዳይ ቢሆንም፤ በማን አለብኝነት ሊታለፍ መሆኑ ማጣፊያው የሚቸግር ሌላ መዘዝ ይዞ መምጣቱን ካለፉ ስህተቶች መማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በራሷ ወጭ ለጅቡቲ በነፃ በምትሰጠው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ሀገሪቱም ሆነች ዜጎቿ ከማኀበራዊዘርፍ ከሚያገኙት ጉዳት በስተቀር ምንም ጥቅም የለም፡፡
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ከመስጠቷ በተጨማሪ ሌላ የፋይናንስ ወጪ ለማድረግ መፈራረሟ ሊላ የኢኮኖሚ ኪሳራን ያስከትላል፡፡ ይህ መደረጉ በራሱ ሀገሪቱ እከተለዋለሁ፤ እየተከተልኩ ነው የሚለው የኢኮኖሚ ተኮር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር በእጅጉ ይቃረናል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ለተጨማሪ ኪሳራ ከመዳረጓ በስተቀር የሚያስገኝላት አንዳች ጥቅምም የለምና፡፡
ኢትዮጵያ ይህን በማድረጓም ጅቡቲ ለኢትዮጵያ እየሰጠች ባለችው የወደብ ኪራይ
ላይ ተጨማሪ ክፍያ እንዳትጠይቅ የሚከለክል ነገር እንኳ ባለመኖሩ፤ነገ በቅናሽ የቀረበላትን የመብራት ኃይል አገልግሎት እና የጫት ንግድ በነፃ ማግኘት አለብን የሚል ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄንም ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሙሉ 90 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ 800 ሺህ ባላት ጅቡቲ ላይ ጥገኛ መሆኗን ሳትገነዘብ አትቀርም፤በኢህአዴግ የስልጣን አገዛዝ ሌላ የተሻለ አማራጭ የላትምና፡፡
የመገርመው ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ከመክፈሏ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን ያልተሰጠው ከክፍያ ነፃ የኢንቨስትመንት መሬት እና በወደቡ አካባቢ ተገነቡ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በኢትዮጵያ ወጪ መከናወኑ ራሱ ሌላው ያልተመለሰ የኢኮኖሚ ኪሳራ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መቼም ከጅቡቲ ጋር ለሚኖረን ወዳጅነት ጥሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መሰረት ዘላቂ ወዳጅ እና ዘላቂ ጠላት የሚባል የለምና፡፡ ያውም የዓለም የፖለቲካ ስርዓት በፍጥነት እየተቀያየረ ባለበት ሰዓት፤ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መወሰን እና መስማማት አሁን ከወጣውና ሊወጣ ከታሰበው በወጪ በላይ ተጨማሪ የገንዘብ ኢኮኖሚ ጥያቄን ይዞ መምጣቱ የተገመተ አይመስልም፡፡
መፍትሄ
የኢትዮጵያ መንግስት አሁን የተፈራረመው (የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮው መጀመሩ ቢነገርም) ሙሉ ለሙሉ ተጋባራዊ ከመሆኑ በፊት የሚኖረውን ፖለቲካዊ፣ማበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማጤን አለበት፡፡ ሌላው የሁለት ሀገሮችን ጠጋራ ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ማንኛውም ሰምምነት ነገ ማጣፊያው የሚቸግር ሌላ ችግር ማስከተሉ ከወዲሁ በመገንዘብ ወደ ዘላቂ መፍትሄ መሄዱ ብልህነት ነው፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ያኔ ያለ ህዝብ ፈቃድ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን የባህር በር (አሰብ ወደብን) ራሱ አሳልፎ እንደሰጠ በማመን በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ለማስመለስ ግልፅ ውይይት እና ጥረት ማድረግ አለበት፡፡
ሌላው ከህግ አኳያ ስምምነቱ የህገ መንግስት ጥሰትም አለበት፡፡ እዚህ ላይ የሚያሳፍረው የሀገሪቱንና ህዝቧን ጥቅም በህግ ያስጠብቃሉ የተባሉት እንደራሴዎች በግልፅ ገዥ የሆነውን የሀገሪቱን ህግ ከአስፈፃሚው እኩል ጥሰው ስምምነቱን ማፅደቃቸው ነው፡፡ ይህም በህገመንግስቱ አንቀፅ 86(3) ላይ የውጭ ግንኙነት መርሆች በሚለው ስር “የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ::” ይላል፡፡ ነገር ግን ስምምነቱ የማኀበራዊ እሴት መጠበቂያ የሆነው ህገ መንገስት በግልፅ በዚህ መልክ ተጥሶ የጅቡቲን ጥቅም ማስጠበቁን አስፈፃሚዎችም አልካዱትም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ራሱ የህገመንግስት ጥሰትን በመፈፀም ተባባሪ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የፀደቀው አዋጅ ተፈፃሚ ከመሆኑ በፊት የሀገሪቱንም ሆነ የሁለቱን ሀገሮች የጋራ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሊሻሻል አሊያም ሊሻር ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ ህግ ተርጓሚዎች እና አስከባሪዎች ጉዳዩን ወደ ህግ በመውሰድ ተገቢው እርምት እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የገዥው ፓርቲ ወገንተኝነትን ትቶ የሀገሪቱን እና የህዝቡን ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችን፣ የታሪክና የህግ ባለሙያዎችን፣ ሀገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችን እና ፖለቲከኞችን ያካተተ ግብረ ኃይል በማቋቋም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚያዋጣ መንገድ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ማድረግ ፍላጎትና አቅም የለኝም የሚል ከሆነ ስልጣኑን በፈቃዱ ለቆ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በር መክፈት አሊያም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተከታትለው እንዲያስፈፅሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የተሻለና የሰለጠነ አማራጭ መፍትሄ ነው፡፡ ለዚህም ሁሉም ዜጋና እና በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ካለው 90 ሚሊዮን ከአስርና ሃያ ዓመታት በኋላ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ከ120-150 ሚሊዮን ሲደርስ ችግሩ ከአሁኑ እጅግ የባሰ ይሆናል፡፡ ያኔ የጅቡቲን ወደብ በኪራይመጠቀም ቀርቶ፤ ጅቡቲ በፈቃዷ የኢትዮጵያ መንግስት አንዷ ፌደራላዊ አካል ብትሆን እንኳ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ለጅቡቲ አሳልፎ እየሰጡ እሽሩሩ ማለቱ ለሌላ ተጨማሪ ችግር በር ከመክፈቱ በስተቀር ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡
በተደጋጋሚ ተጨማሪ ወጭና ስጋት የማይፈጥር ዘላቂ መፍትው ግልፅና አጭር፤ያም ሀገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ ያጣችውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን የአሰብ ወደብንማስመለስ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እንደ ኬኒያ፣ ሶማሊ ላንድ እና ሱዳን ወደቡን በአማራጭነት ማሰቡ ደግሞ ከጅቡቲ የባሰ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይዞ መምጣቱ የማይቀር ስለሆነ፤መፍትሄው ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በማስመለስ የወደብ ባለቤት መሆን ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስኳር ፕሮጀክት ላይ የተጋረጠው አደጋ
ብስራት ወ/ሚካኤል
ጨዋማው የኢትዮጵያ ሐይቅ 15 እጥፍ ይዘቱና ስፋቱ እየጨመረ በሀገሪቱ ታላላቅ ወንዞች መካከል አንዱ በሆነው ወንዝ ላይ ስጋትን ጭሯል፡፡ ይህ ስጋት በቡና አምራችነቷ ከአፍሪካ ታላቅ በሆነችው ሀገር ላይ አደጋ እያንዣበበ ነው፡፡
ጨዋማው ውሃ ታማኙንና ታላቁን አዋሽ ወንዝን በመበከል በኢትዮጵያ መንግስት ባለቤትነት በሚተዳደረው ስኳር ፋብሪካ እና ከህንድ ድጋፍ በማግኘት ስኳር ወደ ውጭ ላኪ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ያለው ዕቅድ ላይ አደጋ ተጋርጧል፡፡ ስጋትን የጫረው ይህ ጨዋማው ሐይቅ የበሰቃ ሐይቅ ነው፡፡
የበሰቃ ሐይቅ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝና ባለፉት ዓመታትም እጅግ እተስፋፋ ወደ መስኖው ውሃ እየተቃረበ ነው፡፡ ይህ ሐይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ የሚገባ ከሆነ በኢትዮጵያ ግዙፍ የስኳር አምራችነት ዕቅድ ላይ የአደጋ ጥላ ያጠላል፡፡
እዚህ ላይ የውሃና ማዕድን ሚኒስቴር የከርሰ ምድር ውሃ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ታደሰ ‹‹ለወንዙ ነው የምንሰጋው፤ ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ በራሱ ጊዜ ወደ ወንዙ የሚደባለቅ ከሆነ እስከወዲያኛው ወንዙን እየበከለው ይሄዳልና” ሲሉ መስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
አባይ ተፋሰስን ጨምሮ ከሀገሪቱ ከፍታ ቦታዎች የሚመነጩ ወንዞች ኢትዮጵያን ከአህጉራቱ አፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ የውሃ ኃይል ባለቤት አድርጓታል፡፡ መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ ከህንድ የገንዘብ፣ የሳውዲው ቢሊየነር እና ከቻይናው አበዳሪ ስኳር፣ ሩዝ፣ ሙዝና ብርቱካን ምርትን ለማስፋፋትና ወደ ውጭ ለመላክ ያለነዳጅ ዘይት በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አስባለች፡፡
የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን የቴክኒክ ኃላፊ የሆኑት እንደሻው ታደሰ እንዳሉት ከሆነ የሰኔው ወቅታዊ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት ሐይቁ ወደወንዙ እንዳይፈስ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፍሰቱ ከሀገሪቱ ዋና መናገሻ አዲስ አበባ በስተምስራቅ የጎርፍ መጥለቅለቅን በማስከተል በአካባቢው የነበሩትን አርብቶ አደሮች እንደሚያርቅ ይጠበቃል፡፡
በሰቃ ከ954 ሜትር የሚመነጭ ፍልውሃ በ1960ዎቹ ዓ.ም.(እ.ኤ.አ) 3 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሸፍን የነበረው በአሁን ሰዓት 5 እጥፍ በማድረግ ወደ 45 ኪሎ ሜትር ስፋት በመጨመር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ወደብ ዋና የንግድ መስመር የሆነውን መንገድ አቅጣጫ ማስቀየሩም ግድ ይላል፡፡
ያልተሳኩ ጥረቶች
መንግስት ላለፉት 14 ዓመታት በየጊዜው ስፋቱና ይዘቱ እየጨመረ የመጣውን የበሰቃ ሐይቅ የማስቀየሻ ቦይ ግንባታ በመስራት እንዲፈስ ቢያደርግም ሐይቁን እንደባህር ባለበት ማስቀረት አልቻለም፡፡
በዚህ ላይ በ2009 (እ.ኤ.አ) እና ባለፈው ዓመት ጥናታቸውን ያቀረቡት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት መገርሳ ኦኩማና ደንቃ እንዳሉት ከሆነ በአካባቢው የመስኖ ፕሮጀክቱ መጨመር ውሃ ወደ ሐይቁ በመግባት ተመጋጋቢነት ይኖረዋል፡፡ ይህም በሚደረጉ የመስኖ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡
አሁን ባለው የበሰቃ ዕድገት ባህርይ መተሐራ አካባቢ ያለውን መስኖ ከጥቅም ውጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በያዝነው ዓመት የተገዛውና ንብረትነቱ የመሐመድ አል አሙዲ የሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ከመንግስት የገዛው የላይኛው አዋሽ የግብርና ኢንዱስትሪንም አደጋ ላይ ይጥለዋል፡፡ ይህን በተመለከተ የሆራይዘን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ ከሐይቁ ምንጭ ዕድገት ጋር ተያይዞ የተደረገውን ጥናት አላረጋገጥንም፣ ምናልባት በአካባው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይኖር ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
ኢንቨስትመንት
አል አሙዲ የግብርና ምርት ወደሆኑት ሩዝ፣ ሙዝና የተጠናቀቀ ቡና ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ሆራይዘን በላይኛው አዋሽ 432 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ የብርቱካን ምርትን በእጥፍ በማሳደግ ወደ 50,000 ቶን ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ በሰሜን ምስራቅ 380 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከህንድ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በተገኘ 640 ሚሊዮን ዶላር ብድር እየተገነባ ያለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም የበሰቃ ሐይቅ ወደ አዋሽ ወንዝ በመግባት ወንዙ ጨዋማ የሚሆን ከሆነ አደጋ ይገጥመዋል፡፡ እንደሚታወቀው ህንድ በዓለም ሁለተኛ የስኳር አምራችና ከፍተኛ ተጠቃሚ ነች፡፡
ሌላው ወደ 30,000 ነዋሪዎች የሚገኙበት መተሐራ እና አዲስ ከተማ፣ መተሐራ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአፋር ክልል እየተገነባ ያለው ግዙፍ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሐይቁ መስፋት እየቀጠለ ከሄደ ለአካባቢው አደገኛ ነው፡፡
ስኳርና ጥጥ
ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ የመሰረት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ 90 ሚሊዮን የሚደርሰው የሀገሪቱ ነዋሪ ወደመካከለኛ ገቢ እንዲያድግ የጥጥ እርሻን አቅርቦት ተንተርሶ የሚገነቡት የጨርቃጨርቅ እንዱስትሪዎች ማደግ እንዳለባቸው ዕቅድ ነድፈዋል፡፡ ይህ የጥጥ እርሻ ልማት ደግሞ ለመካከለኛው አዋሽ በአሚባራ ቢዝነስ ግሩፕ የሚመራው ኢንዱስትሪም የበሰቃ ሐይቅ ከአዋሽ ወንዝ ጋር በመቀየጥ ጨዋማ የሚሆን ከሆነ እሱም አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ እንደዓለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ተቋም መሰረት ከ1984 ዓ.ም.(እ.ኤ.አ) ጀምሮ በፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረ 2,000 ሄክታር በጨዋማ ውሃ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡
አሚባራ መካከለኛው አዋሽ የግብርና ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ውብሸት ይልማ እንዳሉት ከሆነ ‹‹ከዝናቡ በፊት የሐይቁ መስፋፋት ያሳስበናል፤ ምክንያቱም ሐይቁ ወደ አዋሽ የሚገባ ከሆነ ለአማባራ ጥጥ እርሻ ችግሩ ከፍተኛ ነው የሚሆነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤት መስጠም
በኢትዮጵያ መንግስት ንብረት የሆነውና በአፋር አካባቢ የተቋቋመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በአዋሽ ወንዝ ግድብ ግንባታ ላይ መሰረት በማድረግ ከ600,000 ቶን በላይ የሸንኮራ እገዳ በዓመት ለማልማት የነበረው እቅድ ላይ ጨዋማ ውሃ የሚፈስ ከሆነ አሁንም እቅዱ ይጨናገፋል፡፡
በተለይ አቶ እንደሻው እንደተናገሩት ከሆነ “ዝናብ የሚዘንብ ከሆነ በቃ” ሲሉ ባለፈው ዓመት በሐይቁ ሙላት ምክንያት የሰጠሙ ሁለት ትምህርት ቤቶችን አስታውሰዋል ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሐይቁን ስፋት ተከትሎ በተፈጠረ ድርቅ በተወሰደ እርምጃ በ2008 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ክልላዊው መንግስት በ467 ሚሊዮን ብር የፈንታሌ መስኖ ቦይ ግንባታ መደረጉን የኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት የውሃ ምህንድስና ኃላፊው እንግዳ ዘመዳገኘሁ ተናግረዋል፡፡
በተለይ እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ወንዙ 4 በመቶ የሐይቅ ውሃ የሚይዝ ቢሆን እንኳ በማንኛውም መልኩ አደገኛ ነው፡፡ ለዚህም በሚል በፓንፕ (ውሃ መሳቢያ መሳሪያ) ብዙ ውሃ ለመቀነስ ጥረት ብናደርግም መስፋፋቱን ግን ሊቀንስ አልቻለም ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
በማኛውም አጋጣሚ ሐይቁ እየጨመረ ከሄደ “ሐይቁ ወደ አዋሽ ወንዝ የመፋሰስ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሚቀጥሉት ቅርብ አመታት የመተሐራ ስኳር ፋብሪካን ያወድማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተንዳሆን ጨምሮ በአዋሽ ተፋሰስ በሚገነቡ በሁሉም ግዙፍ መስኖ ልማቶችም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል” ሲሉ ፕሮፌሰር መገርሳ ተናግረዋል፡፡
የእሾሃማ ዛፎች እጣ ፈንታ
በመንግስት ባለቤት ከሚገነባው ተንዳሆ ስኳር ውጭ በኬንያ አቅራቢያ በደቡብ ኦሞ የሚገነቡትን 6 የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች ጨምሮ 10 ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በቻይና ዴቨሎፕመንት ባንክ የሚደረግ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር ድጋፍ በአዋሽ አካባቢ የሚገነባ የከስም ስኳር ፕሮጀክት ይገኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ የስኳር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ ቃል አቀባይ አቶ ይልማ ጥበቡ ከመጋቢት አጋማሸ ጀምሮ አስተያየት ቢጠየቁም ምላሽ እንዳልሰጡ የብሉምበርጉ ዘጋቢ ዳቪሰን አስታውሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ከፍታ ቦታዎች በመመንጨት በሰሜን ምስራቅ ወደ አፋር በመፍሰስ ጅቡቲ አካባቢ ከመድረቁ በፊት አዋሽ ወንዝ 1,200 ኪ.ሜትር ይጓዛል፡፡ ከመተሐራ አካባቢ ጀምሮ ባሉ በአካባቢው ያሉ እሾሃማ ዛፎች(ግራርና ቆንጥር) በተጨማሪ በአካባቢው ሞቃታማ ስፍራ የሚበቅሉ የምግብ እህሎችን ተንተርሰው እየኖሩ ያሉ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡ ለነዚህ ህዝብ በተለይም የአፋር አርብቶ አደሮች ለረጅም ጊዜ ህይወታቸውን እዚህ ወንዝ ላይ መሰረት ያደረጉ ናቸው ፡፡ ስለዚህ የአዋሽ ወንዝ በበሰቃ ሐይቅ ብክለት የሚያጋጥመው ከሆነ ለእነኛ ነዋሪዎች አደገኛ ነው የሚሆነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው የከፍተኛ ባለሙያዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ስብስብ ስለሐይቁ እንዴት እያደገ እንደመጣ ጥናትና ምክክር እየተደረገ ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ግን ምን መደረግ እንዳለበት የተያዘ አቅጣጫም ሆነ የተወሰደ እርምጃ የለም ሲሉ ማከላቸውን ሚያዚያ 24 ቀን 2013 (እ.ኤ.አ) በብሉምበርግ ድህረ-ገፅ ዊሊያም ዳቪሰን አስነብቧል፡፡
አሁንም ቢሆን ከአዲስ አበባ ወደምስራቅ 195 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የመተሐራ በሰቃ ሐይቅ ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘለት በአዋሽ ተፋሰስ ላይ በብዙ ቢሊየኖች ብር ግንባታቸው ተካሂደው በስራ ላይ ያሉ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ፤ በቅርቡ ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ በስራ ላይ ያሉት የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ የግብርና እንዱስትሪዎች እንዲሁም በእቅድ ላይ ያለው የከሰም ስኳር ፕሮጀክት በተጨማሪ የመተሐራን ከተማ ነዋሪዎችና አዋሽ ወንዝን ተጠግተው የሚኖሩ የአፋር ክልል ነዋሪዎችን በነበሩት ዳግም ላናገኛቸው እንችላለን፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የብሎምበርግ ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ ሲያደርግ ከሚፈልገው ገንዘብ ውጭ አካባቢያዊ ጥናት የማድረግ ትኩረትም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መጨው ትውልድ ላይ ጭምር ዕዳ ተጥሎ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የሚጠበቅባቸውን ውጤት ሳያስገኙ በሚደርስባቸው የአካባቢ አደጋ በሀገር ላይ ከፍተኛ የሃብት ውድመት ማስከተላቸው የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት የግብር ውጣ ስራ የሚያደርገውን የዘመቻ የልማት ፕሮጀክቶች ስራ አካባቢውንና ተፈጥሯዊ ሁነቶችን ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ማጤንና ማገናዘብ አለበት፡፡
ተፈጥሮን በማዛባት ልማትን ማምጣት ይቻል ይሆን?
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
በኢትዮጵያ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የደን ሽፋን 40 በመቶ ነበር፡፡ የቀድሞው የሀገሪቱ ኢህዴሪ መንግስት (ደርግ) በነበረ ወቅት ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ይሰጥ የነበረው ግምት ከፍተኛ በመሆኑ በሀገሪቱ ያሉ ደኞች ከነ ዱር እንሰሳቱ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን ምንም እንኳ የአካባቢ ጥበቃ ምንነት በውል የታወቀ ባይሆንም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ እና የዱር አራዊትም እንደልባቸው ይቦርቁበትና ቱሪስቶችም እንዳሻቸው ይጎበኙ እንደነበር ይነገራል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ከደደቢት በረሃ የመጡት ታጣቂዎች ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 1983ዓ.ም. ጀምሮ ያሉት የደን ሽፋኖች እጅግ እየመነመኑ ሄደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ በፊት 40% የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 3% በመውረድ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ወደ 2.5% መውረዱን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ለ21ዓመታት እስካሁንም በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ያለው አመለካከት እጅግ የወረደ በመሆኑ ቀደም ሲል በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ዙሪያ ያሉ ደኖች በካድሬዎች ፈቃድ ለገዥው አባላት ጊዜያዊ ጥቅም ሲባል እየተጨፈጨፈ ቦታው ለመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ለዚህም በአሁን ወቅት የአዲስ አበባን ሰሜንና ምዕራብ(ሳንሱሲ፣ ጉለሌ፣ሽሮሜዳ፣የካ…የመሳሰሉ በደን የተሸፈኑ አካባቢዎች) መመልከት በቂ ነው፡፡
በተለያየ ምክንያት ከፍተኛ የደን ክምችት ያለባቸው እንደ ባሌ ተራራዎች፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ ደኖች እየተቃጠሉ ይዘታቸው ቢመናመንም መልሶ እምዲለሙ ሲደረግ አልተስተዋለም፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንሰሳት ወደሌላ ሀገር እንዲሰደዱ ምክንያት በመሆን ሀገሪቱ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቀርታለች፡፡ በደኖቹ ዙሪያ ያሉ በግብርና ስራ( መሬት በማረስና እንሰሳት በማርባት)የሚተዳደሩ ገበሬዎች በአካባቢያቸው በተፈጠረው የተፈጥሮ መዛባት ምርቶቻቸው እየቀነሰ ወደ ከተማ እንዲፈልሱ አስገድዷቸዋል፡፡
ሌላው ለደኖች ውድመት ገዥው መንግስት ተጠያቂ ከሚሆንበት አንዱ የደን ውጤቶችን ለየ አካባቢው የገዥው ቡድን አመራሮች ሙስና መጠቀሚያ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ገንዘብ እንዲሸጡ መደረጉ ነው፡፡ ለዚህም ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አቅጣጫ 123 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረብርሃን አካባቢ ያለው ደን በ2004ዓ.ም. እያንዳንዱን ዛፍ በ40ሳንቲም ሂሳብ ለመሸጥ የዞኑና የከተማው መስተዳደሮች ከተስማሙ በኋላ በአካባቢው ማህበረሰብ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ አሁን ካሉት የደን ክምችቶችም ከተወሰኑ ብሔራዊ ፓርኮች በስተቀር አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ዙሪያ ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ንብረትነታቸው የመንግስት የሆኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን(የአሁኑ ኢትዮ ቴሌኮም) ለመስመር ዝርጋታ የሚያገለግላቸውን የምሰሶ እንጨት የሚጠቀሙት ከሀገሪቱ ደን በመቁረጥ ቢሆንም በቆረጡበት ምትክ ግን መልሰው ሲያለሙ አይታይም፡፡ ባለፈው 2004 ዓ.ም ደግሞ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ክልል ያሉ ከፍተኛ የደን ክምችቶች መሬቱን ለውጭ ባለሃብቶች ለመስጠት በሚል ተጨፍጭፈው ቢያልቁም መልሶ የተካም ሆነ ዜጎችን አፈናቅሎ ለባለሃብቶቹ ከመከስጠት ያለፈ ለምን ያለ የመንግስት አካል አልነበረም፤የለምም፡፡ ደኑን እንዲመነጠር የፈቀደትና ቦታውን የመሩት የፌደራሉ እና የክልሉ መንግስታት ናቸውና፡፡
በከተሞች ውስጥ ያለውን የተመለከትን እንደሆነ ዕፅዋቶች ሙሉ በሙሉ እንዲወድሙ ተደርጎ የድንጋይ ካብ ህንፃ ብቻ መገንባት እንደስልጣኔና እንደዕድገት እየተወሰደ በመምጣቱ ቀደም ሲል በየከተሞቹ የነበረው የአየር ፀባይ እንዲቀየር አስገድዶታል፡፡ እዚህ ላይ ስለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ አነስተኛ ግንዛቤ ያላቸው ደካማ መሪዎችን ፈለግ በመከተል ነዋሪዎችም የአካባቢውን ተፈጥሮ በማዛባት ትልቅ ሚና መጫወታቸው እሙን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ላይ ያልተለመደ የአየር ፀባይ እየተስተዋለ ቢሆንም ገዥዎች የራሳቸውን ድክመት ሳይቀርፉ የተለመደውን የገንዘብ ሱስ ለመወጣት ሌሎች ላይ ምክንያት ሲደረድሩና የገንዘብ ካሳ ብቻ ሲያባርሩ ይስተዋላል፤ የቤታቸውን የአደባባይ የአካባቢ ጥበቃ ችግር ገመና ግን እየኖረ ያለው የሀገሬው ሰው የሚያውቅ ሐቅ ነው፡፡
የወሬ ዘመቻ የማይታክተው ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2000ዓ.ም.(ሚሊኒየም) ክብረ በዓል ወቅት እያንዳንዱ ሰው ችግኝ እንዲተክል ለማበረታታት በሚል የውሸት ዘመቻ ሁለት ዛፍ በሁለት ሺህ ሲባል ቢከርምም እንክብካቤ ተደርጎላቸው የፀደቁ ችግኞችና ዛፍ የሆኑትን ልናይ አልቻልንም፡፡ በርግጥ በወቅቱ ዓላማው የተፈጥሮ መዛባትን ከመከላከል አኳያ የሚበረታታ ተግባር ቢሆንም ኢህአዴግ በባህሪው ከወሬ ዘመቻ ባለፈ የተግባር ቁርጠኝነት ስለማይታይበት ይባሰ ያሉትም ደኖች እየወደሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ የተነዛበትና ከፍተኛ በጀት የፈሰሰበት “ሁለት ችግኝ ለሁለት ሺህ” የሚለው ፕሮጀክት ከወሬ ባለፈ የታሰበው ሳይሆን ይኸው 5ኛ ዓመት ላይ ደርሰናል፡፡
በአጠቃላይ ተፈጥሮን እያዛቡ ልማት ማምጣት የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን መንከባከብ፣ የተራቆቱ መሬቶችን በደኖች ማልማት፣ በከተሞች የሚሰሩ ህንፃዎች በእያንዳንዳቸው ግቢ እንደየስፋታቸው መጠን ቢያንስ አምስትና ከዛ በላይ ዕፅዋቶችን(ዛፎች) እንዲተከሉ አስገዳጅ ህግ በማውጣት መተግበር ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ተፈጥሮን በማዛባት ልማት ማምጣት ቅዥት ካልሆነ እውን ሊሆን ስለማይችል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮን መንከባከብ ከሰብዓዊ መብት ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡
