Category Archives: Human Rights

የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

∙ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል

z9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 6ቱ የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለ20ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም ተከሳሾች ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ ያቀረቡባቸው ሰብሳቢ ዳኛ ሳይቀየሩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጀምሮ እያንዳንዳቸው ‹‹በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?›› የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን የሽብር ክስ እንዳልፈጸሙ ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ተከሳሾቹ ክሱን በተደጋጋሚ ቢያነቡትም ግልጽ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ቢገልጹም የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት እንዳለባቸው ተገልጾ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ የተጠቀሰውን ክስ እንዳልፈጸመ በመግለጽ “ህግ የተከበረበት ሀገር ቢሆን ኖሮ በእኔ ቦታ ከሳሾቼ ነበሩ መቆም ያለባቸው” ብሏል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ በበኩሉ፣ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ጋዜጠኝነት ወንጀልም ሽብርም አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ከመጋቢት 21-23  ቀን 2007 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አቤቱታ ላይ ቀጠሮ ሰጠ

prisoners

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘላለም ወርቃገኘው ክስ መዝገብ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡ በዛሬው ችሎት የተከሳሾቹ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ‹‹ህዳር 12 ለ 13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የተጠርጣሪዎቹ ንብረት ተወስዶባቸዋል፣ የሰብአዊ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፣ ድንገተኛ ፍተሻው ህገ ወጥ ነው›› በሚል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ላቀረቡት አቤቱታዎች ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ ሰምቷል፡፡

የማረሚያ ቤቱ መልስ በጽሁፍ ከቀረበ በኋላ በቃልም እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮ ማረፊያ አስተዳደር አስተዳዳሪ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አምባዬ ክቡር ፍተሻው መካሄዱን አምነው ነገር ግን፤ ‹‹ፍተሻው የተከናወነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከጠዋቱ 12 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ፍተሸውም በአቤቱታው ላይ እንደቀረበው ባልታወቁ ሰዎች ሳይሆን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥበቃዎች ነው የተከናወነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የፍተሻውን አላማም ‹‹የታራሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተከለከሉ ነገሮችን ፈትሾ ለማስወገድ ነው፡፡ በፍተሸውም ሚስማር፣ ስለት ነገሮች፣ እንዲሁም ብጥብጥ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡

ባለፈው የአብዛኛዎቹ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሲደረግ የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን፣ እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ የተወሰኑ የክስ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ አቃቤ ህግ ይዞ ቀርቦ በንባብ አሰምቷል፡፡

በመጨረሻም በፍተሻው ወቅት ተፈጽሟል በሚል በተከሳሾቹ ጠበቃ የቀረበውን አቤቱታና ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም፤ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ማሻሻያ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ‹‹ተሸሽለዋል ወይንም አልተሸሻሉም›› የሚለውን ለመወሰን ለየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ቀጠሮ መሰጠቱን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ትናንት ምሽት በቡራዩ ከተማ በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በቡራዩ ከተማ ልዩ ስሙ ቀርሳ በተባለው አካባቢ ትላንት የካቲት 9 ቀን 2007 ኣ.ም. ምሽት በደረሰ አሰቃቂ የመኪና አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡

አደጋው የደረሰው ትላንት ምሽት 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ ሲሆን፥ ወደ አዲስ አበባ ይመጣ የነበረ ሲኖ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ከሚኒባስ ጋር በመጋጨቱ ነው።

በግጭቱ ሳቢያ የተነሳው ከባድ የእሳት አደጋም በመኪናው ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት እንደሆነ ቢነገርም፤ የአደጋውን ምክንያት በተመለከተ ይህ እስከ ተዘገበበት ድረስ  ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከፖሊስ ምርመራ የተገኘ ማረጋገጫ የለም፡፡

በአደጋው ወቅት በመኪናዎቹ ላይ የደረሰ ቃጠሎ

በአደጋው ወቅት በመኪናዎቹ ላይ የደረሰ ቃጠሎ

የመድረክ እጩ ተወዳዳሪ በትግራይ ተምቤን በፖሊስ ተደበደበ

አቶ ዜናዊ ኣስመላሽ

አቶ ዜናዊ ኣስመላሽ

የወርቃ ኣምባ ምርጫ ክልል መድረክን ወክሎ ለክልል ምክርቤት በእጩነት የቀረበው ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ በፖሊስ ተደብድቦ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶታል።
ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ ትናንት ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት የወርቃ ኣምባ ከተማ ኣስተዳዳሪ ተስፋይ ሃይሉ “..ይዛቹ ኣምጡት ብሎናል..” በማለት ሃፍተ ኪሮስ የተባለ ፖሊስና ገብረተኽለ ወለቸኣልና ገብረጀወርግስ ሙሉ የተባሉ ሚሊሻዎች ወደ ፖሊስ ኮሚኒቲ እየደበደቡ ወስደውታል። በወቅቱ በርካታ ህዝብ እየተመለከተ የነበረ ሲሆን ድብደባው በህዝቡ እርዳታ እንዲቆምና ወደ ዋና ፖሊስ ጣብያ ወስደው እንዲያስሩትና ድብደባው እንዲያቋርጡት ተቃውሞው በማሰማቱ ድብደባው ተቋርጧል።

ተደባዳቢው ፖሊስና ሚልሻዎቹ ለምን እንደደበደቡት ሲጠየቁ “..ወደ ፖሊስ ጣብያ ስንወስደው ቀስ እያለ ሲሄድ ፈጠን በል ስንለው ቀስ እያለ በመሄዱ ነው..” ሲሉ መልሰዋል።
ፖሊስ ኣዛዡ ያለ ምንም ምክንያት እንደተደበደበ ካረጋገጠ በሗላ “..ፖሊሱ ሰካራም መሆኑና ቅር ሊለው እንደማይገባው..” ነግሮ ማታ ሰዎስት ሰዓት ከእስር ቤቱ ኣስፈትቶታል።
ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ ከእስር ከተለቀቀ በሗላ በጤና ኬላ የህግምና እርዳታ ተደርጎለታል።

ማታ 5 ሰዓት ኣከባቢ ፖሊስ ሃፍተ ኪሮስ ከ3 ሚልሻዎች በመሆን ወዳረፈበት ቤት በመሄድ ለባለ ቤቱ ማስፈራራት ኣድርሰዋል።
የህወሓት መንግስት በሑመራና ሽረ የሚገኙ ኣባሎቻችንም ተመሳሳይ ድብደባ ኣድርሰዋል ሲል በመቀሌ የመድረክ አመራር አባል ገልፀዋል፡፡

ድብደባ ከተፈጸመባቸው ሁለት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የአንደኛው ሕይወቱ አለፈ

ምሩ ጽጌ

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ሁለት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሠራተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው አንደኛው ሕይወቱ ማለፉ ተረጋገጠ፡፡

 aastu

ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት ፈተናቸውን ካጠናቀቁት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል፣ ሙሉቀን ከበደና ታምራት አባተ የተባሉ ተማሪዎች በዕለቱ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናቸውን እንዳጠናቀቁ ከግቢ ወጥተው ሲዝናኑ ካመሹ በኋላ ወደ ማደሪያ ክፍላቸው ሲመለሱ፣ ፀደቀ አድማሱ ከሚባለው ተጠርጣሪ የጥበቃ ሠራተኛ ጋር መጋጨታቸውን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ሊገቡ ሲሉ ተጠርጣሪው እንዲቆሙ ሲያደርጋቸው ተማሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትን መታወቂያ ቢያሳዩም፣ ከተጠርጣሪው ጋር ሊግባቡ ባለመቻላቸው ድብድቡ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው በወቅቱ ይዞት በነበረው የእንጨት ዱላ ደጋግሞ ሲደበድባቸው የተመለከተ ሾፌር፣ ሌሎች የተኙ ጥበቃዎችን በማስነሳቱ የተፈጠረው ድብድብ የቆመ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ በደረሰባቸው ድብደባ ተጎድተው ስለነበር በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡

ታምራት አባተ የተባለው ተማሪ በጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገለት ሕክምና የተረፈ ቢሆንም፣ የደረሰበት ድብደባ ከባድ በመሆኑ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር የተደረገው ተማሪ ሙሉቀን፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያለ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡ ፖሊስ በድብደባው ተሳትፈዋል በማለት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ የዩኒቨርሲቲውን የጥበቃ ሠራተኞችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ በምርምራ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡