የአንድነት ፓርቲ ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት አጀንዳዎችን አፀደቀ
ትናንት አርብ ታህሳስ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) በጠራው ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት አጀንዳዎችን በመወያየት ማፅደቁ ተሰማ፡፡ በመጀመሪያ አጀንዳነት የተነሳው የኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ከፓርቲው ፕሬዘዳንትነት ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሰየመውን ፕሬዝደንት ተወያይቶ ያፀደቀ ሲሆን፤ በሁለተኛ አጀንዳነት የተያዘው እና ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥራችሁን አሳውቁኝ ባለው መሰረት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥርን ወስኗል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው ከሁለቱ አጀንዳዎች በተጨማሪ በተጓደሉ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ምክንያት የማሟያ ምርጫንም ማድረጉ ታውቋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አሁንም በተለያዩ የፓርቲውና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከሩን እንቀጠለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከውይይቱ በኋላም የተለያዩ ተጨማሪ አጀንዳዎችን ከማፅደቅ በተጨማሪ አንገብጋቢ በሆኑ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ አባላትም ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ተጠቁሟል፡፡
9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባና እስር ተቋረጠ
ዛሬ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በ9ኙ ፓርቲዎች ለትብብር ለ24 ሰዓት በመስቀል አደባባይ የተጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በደህንነት፣ ፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ድብደባና እስር ምክንያት መቋረጡ ተገለፀ፡፡ ሰልፉን ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩ በርካታ የፓርቲዎቹ አባላትና ደጋፊዎች ተደብድበው መታሰራቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በተለይም ከአመራሮች የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ አለሳ መንገሻ እና የከንባታ ህዝቦች ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ በፖሊስ ታግተው መታሰራቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ከዋና አመራሮቹ በተጨማሪ አቶ ወሮታው ዋሴ፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ኢየሩስ ተስፋው፣ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ፣ ወይንሸት ሞላ፣ ሳሙኤል አበበ፣ እያስፔድ ተስፋዬ፣ሜሮን አለማየሁ፣ ንግስት ወንዲፍራው፣ ወይንሸት ንጉሴ፣ ምኞት መኮንን፣ አቤል ኤፍሬም፣ ኤፍሬም ደግፌ፣ ኃይለማሪያም፣ ሜሮን፣ ኢብራሂም አብዱልሰላም፣ እና ሌሎችም የትብብሩ አመራሮችና አባላት ከፍተኛ ቁጥር ባለው ፌደራል ፖሊስ መያዛቸውን እና በታገቱበት ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደነበር የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ የታሰሩት አለመለቀቃቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት የታፈሱት አመራሮች ቂርቆስ ፖፖላሬ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከታሰሩት መካከል ወጣት አቤል ኤፍሬም በተፈፀመበት ከፍተኛ ድብደባ ራሱን ስቶ የካቲት 12 ሆስፒታል እንተኛ እና አቶ ይልቃል ጌትነትም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢ ኤን ሬዲዮን ጨምሮ የተለያዩ የማኀበራዊ ገፆች መረጃ አመልክቷል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ አሰግድ ጌታቸው ለከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ውስጥ የ24 ሰዓታት የአዳር ሰልፍ ለማካሄድ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበርና አስተዳደሩ ግን ፍቃድ አለመስጠቱን መናገራቸውን ድሬ-ቲዩብ ዘግቧል፡፡
የመንግስት ሹሙ ለሰልፉ ፈቃድ አልሰጠንም ቢሉም፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 30(1) ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ እንደሆነ እና ሰላማዊ ሰልፍን በተመለተ የወጣው አዋጅ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ለመውጣት ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ ድንጋጌ እንደሌለ ይታወቃል፡፡
በአዲስ አበባ የ24 ሰዓቱ ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል
- 5 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ታስረዋል
ህዳር 27 እና 28 2007 ዓ.ም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የሚያደርጉት የአዳር (24 ሰዓት) ሰልፍ ቅስቀሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን ሰው በሰውና ቲሸርት በመልበስ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደቆየና በተለይ ዛሬ ህዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት ጀምሮ በአዲስ ከተማ፣ ጉለሌ፣ አራዳ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ፣ ኮልፌና ሌሎች የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች ወረቀት በመበተን የተሳካ ቅስቀሳ መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ለአዳር ሰልፉ ሲቀሰቅሱ ከነበሩት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑት ሜሮን አለማየሁ፣ ወይንሸት ንጉሴ፣ ባህረን እሸቱ፣ ማቲያስ መኩሪያ እንዲሁም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲቀሰቅስ የነበረው ሲሳይ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸው ተግልጾአል፡፡
ከአሁን ቀደም ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ቅስቀሳ ላይ ሲያደርጉ በርካታ የፓርቲው አመራሮችና አባላት መታሰራቸውን ያስታወሱት አቶ ዮናታን “ይህ የገዥው ፓርቲ የተለመደ እርምጃ ነው፡፡ በቀጣይነትም ሌሎች አባላትንና አመራሮች መታሰራቸው አይቀረም፡፡ ትግሉ መስዋዕትነት የሚያስከፍል እንደመሆኑ በእስሩ ሳንገታ ትግሉን እንቀጥላለን፡፡” ሲሉ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ የዛሬው ቅስቀሳ 12 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ነገ ጠዋት ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ዘግይቶ በደረሰን ዜና ከታሰሩት 5 ወጣቶች መካከል ሁለቱ ሴቶች መፈታታቸውንና ወንዶቹ ግን ይህ እስከተዘገበ ድረስ አለመለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡
የዞን 9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች ላይ ተሻሽሎ ቀርቧል የተባለው ክስ ተሰማ
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ያሉት የዞን 9 ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ማህሌት ፋንታሁን እና ናትናኤል ፈለቀ እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ ላይ የተመሰረተው ክስ ተሻሽሎ ቀርቧል የተባለው የክስ ዝርዝር ዛሬ በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተሰምቷል፡፡
ዛሬ ህዳር 24 ቀን 2007 ጠዋት በዋለው ችሎት፣ በብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞች ላይ ተሻሽሎ የቀረበው የክስ ዝርዝር በንባብ የተሰማ ሲሆን በክስ ወረቀቱ ላይ ከተመለከቱት ነጥቦች መካከል ግልጽ ያልሆኑ ነጥቦችን አካትቶ እንዲሰጥ ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ሙሉ የክስ ወረቀቱ አርብ ለጠበቆቹ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
በጠቦቆቹ በኩል ክሱ ቀደም ብሎ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መሻሻሉን ለማረጋገጥ ያለፈው የፍርድ ቤቱ ብይን ግልባጭ እስካሁን እንዳልደረሳቸው በመግለጽ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የብይኑ ግልባጭ ሳይደርሰን ተሻሻለ የተባለው ክስ መሰማት የለበትም ብለው የነበር ቢሆንም፣ ክሱን አይታችሁ መቃወሚያ ካላችሁ አስተያየት እንድትሰጡበት እድል እንሰጣለን ያለው ፍርድ ቤቱ ክሱ እንዲሰማ አድርጓል፡፡
ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ ያላቸውን አስተያየት ይዘው እንዲቀርቡ ለታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ከ3 ወር በፊት የታፈነው የመኢአድ አመራር የት እንደደረሰ አልታወቀም
የሶስቱ ፓርቲዎች አመራሮች ለታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሮባቸዋል
የገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ከየ ክፍለ ሀገሩ ማሰር በጀመሩበት ወቅት በደህንነትና ፖሊሶች የታፈነው የመኢአድ አመራር የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ መግለፃቸውን የነገር ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የሰሜን ጎንደር አመራር የሆነው አቶ ችሎት ባዜ መስከረም 2 ቀን 2007 ዓ.ም በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች የታፈነ ሲሆን፤ በወቅቱ ቤተሰቦቹ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንደተዛወረ መረጃ ደርሷቸው እንደነበር መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡ ሆኖም በተደጋጋሚ አቶ ችሎት ወደ ማዕከላዊ መዛወር አለመዛወሩን ቢጠይቁም እንዳልመጣ ተነግሯቸዋል፡፡
የታፈነው የመኢአድ አመራር ማዕከላዊ እንደሌለ የተነገራቸው ቤተሰቦቹ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከሆነ በሚል ሪጂስትራል ስሙ እንዳለ ቢያስጠይቁም እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከየ ክፍለ ሀገሩ በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ታፍነው በአሁኑ ወቅት ማዕከላዊ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የመኢአድ አመራሮች በትናንትናው ዕለት አራድ ምድብ ችሎት ቀርበው ለታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሮባቸዋል፡፡