Tag Archives: Zone9 Ethiopia

አምስቱ የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ይግባኝ ተጠየቀባቸው

ባለፈው ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ፣ጉዳያቸው ለአንድ ዓመት ከ5 ወር በላይ ሲታይ ቆይቶ ከበፈቃዱ ኃይሉ በስተቀር ቀሪዎቹ “መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ” ተብሎ ከሁለት ወራት በፊት የተወሰነላቸው አምስቱ የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ይግባኝ ተጠየቀባቸው፡፡

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በአምስት የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ላይ ባቀረበው ይግባኝ መሠረት ለቃል ክርክር ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ችሎት ማዘዙ ተሰምቷል፡፡

Federal court charge

ፍርድ ቤቱ በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ለሚከራከሩት አምስት የዞን ዘጠኝ አባላት መጥሪያውን ያወጣው ታህሣሥ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን፤ ለቃል ክርክር ቀነ-ቀጠሮ የሰጠው ለፊታችን ታህሣሥ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 መሆኑን መጥሪያው ያስረዳል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ መጥሪያው የደረሰው ለበፍቃዱ ኃይሉ ብቻ ሲሆን፤ በተሰጠው የቃል ክርክር ቀነ-ቀጠሮ እንዲቀርቡ መጥሪያ የወጣላቸው በፈቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ሶሊያና ሽመልስ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም፤ በፍቃዱ ኃይሉ የተቀየረለትን “አመፅ የማነሳሳት” የወንጀል አንቀፅ ለመከላከል ለጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. መቀጠሩ አይዘነጋም።

የዞን 9 ብሎገሮች የ2015 የዓመቱን የፕሬስ ነፃነት ሽልማት ተቀበሉ

በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ዋና ቢሮውን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Committee to Protect Journalists) በዘንድሮው የ2015 የዓመቱ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 ብሎገሮች ሽልማት ተቀበሉ፡፡ በስፍራው ማክሰኞ ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ምሽት የዞን 9 አባላት መካከል እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል እና ሶሊያና ሽመልስ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡

CPJ Zone 9

ሀገር ቤት የሚገኙት ቀሪዎቹ የዞን 9 አባለት ከአንድ ዓመት እስር ቆይታ በኋላ ቢለቀቁም ከሀገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውና የጉዞ ሰነድ የተነጠቁም እንዳሉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሬስ ነፃነት በሀገሪቱ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅዕ ሲፒጄን ጨምሮ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም አቀፍ ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በዕለቱ በእንግድነት የተገኘችው በቅርቡ የተፈረደባትን እስር አጠናቃ ከእስር የወጣችው ርዕዮት ዓለሙ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል፡፡ በያዝነው ዓመት የሲፒጄ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 በተጨማሪ ሶሪያዊ እና ማሌዥያዊ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስቶችም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ ከ አምስት ዓመት በፊት የቀድሞው የአውራምባ ታየምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ሲፒጄ ዓለም አቀፍ የሃዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኞች ላይ የሚወስደውን አፈና አጥብቆ በመኮነን ይታወቃል፡፡

የዞን 9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች ላይ ተሻሽሎ ቀርቧል የተባለው ክስ ተሰማ

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ያሉት የዞን 9 ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ማህሌት ፋንታሁን እና ናትናኤል ፈለቀ እንዲሁም ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ ላይ የተመሰረተው ክስ ተሻሽሎ ቀርቧል የተባለው የክስ ዝርዝር ዛሬ በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተሰምቷል፡፡

zone9ዛሬ ህዳር 24 ቀን 2007 ጠዋት በዋለው ችሎት፣ በብሎገሮቹ እና ጋዜጠኞች ላይ ተሻሽሎ የቀረበው የክስ ዝርዝር በንባብ የተሰማ ሲሆን በክስ ወረቀቱ ላይ ከተመለከቱት ነጥቦች መካከል ግልጽ ያልሆኑ ነጥቦችን አካትቶ እንዲሰጥ ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ሙሉ የክስ ወረቀቱ አርብ ለጠበቆቹ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

በጠቦቆቹ በኩል ክሱ ቀደም ብሎ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መሻሻሉን ለማረጋገጥ ያለፈው የፍርድ ቤቱ ብይን ግልባጭ እስካሁን እንዳልደረሳቸው በመግለጽ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የብይኑ ግልባጭ ሳይደርሰን ተሻሻለ የተባለው ክስ መሰማት የለበትም ብለው የነበር ቢሆንም፣ ክሱን አይታችሁ መቃወሚያ ካላችሁ አስተያየት እንድትሰጡበት እድል እንሰጣለን ያለው ፍርድ ቤቱ ክሱ እንዲሰማ አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ ያላቸውን አስተያየት ይዘው እንዲቀርቡ ለታህሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡

%d bloggers like this: