አቶ ማሙሸት አማረ ለውሳኔ ተቀጠሩ
“ምስክርነቱ የሐሰትና የተጠና ነው!” ጠበቃቸው
አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት ለተደረገውና ለዋናው (ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ነሃሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለነሃሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ለውሳኔ ተቀጠሯል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማቅረቡ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
አቶ ማሙሸት በአዲሱ ክስ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለመስማት ከ5 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደተመላለሰ የተገለፀ ሲሆን በተለይ አንዱ ምስክር በፖሊስ ተይዞ እንዲመጣ ቢጠየቅም ፖሊስ ሳያስፈፅም ቀርቷል፡፡ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ዛሬ የመሰከሩ ሲሆን “አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል” ሲሉ መስክረዋል፡፡
ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙ ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሲጠየቁ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ “የግል” ብሎ የነበር ቢሆንም በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡
ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡ ዳኛው “በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?” ሲሉት መልስ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡
የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ አመራባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አይ ኤ አይ ኤልን ለመቃወም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ረብሻ አንስተዋል በሚል በተመሰረተባቸው ክስ ሰዓትና ቀን፤ ፓርቲያቸው መኢአድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሌላ እንዲሰጥ መወሰኑን በመቃወም ፍርድ ቤት ክስ መስርተው ለክርክር በተጠቀሰው ሰዓትና ዕለት ችሎት ላይ እንደነበሩ የሚያስረዳ ደብዳቤ ፍርድ ቤቱ መፃፉ ይታወሳል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ ቀበና የሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዋና ጽህፈት ቤት በፖሊስ እና ደህንነቶች ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት በቁጥጥር ስራ የዋለው ምርቻ ቦርድ ለእኔ ይታዘዘኛል በሚል የፓርቲውን ስምና ህልውና ለነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ ማስረከቡን ተከትሎ ነው፡፡ ፖሊስ አርብ ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ጽህፈት ቤቱን ከመቆጣጠሩ በፊት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ተቀምጠው እንደነበርና በዕለቱ ከሰዓት በኋላ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ጉዳይ ለመምከር ወደ ጽህፈት ቤቱ ሲያመሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተረጋግጣል፡፡ በዕለቱ ጠዋት ስራ አስፈፃሚው በጉዳዩ ዙሪያ ከመከረና ከተወያየ በኋላ ለምሳ ወጥተው ለምክር ቤቱ ስብሰባ ሲመለሱ ወደ ቢሮው መግባት የተከለከሉ ሲሆን፤ ቢሮው በፖለስ ቁጥጥር ስር በመዋሉ ቀጠሮ የተያዘለት የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባም ሳይካሄድ መቅረቱ ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች ለምሳ ሲወጡ ትተዋቸው የሄዷቸውን ተሸከርካሪም ሆነ ማንኛውንም ወረቀት ይዘው እንዳይወጡ ከታገዱ በኋላ ፖሊሶቹ በስልክ በተሰጣቸው ትዕዛዝ ስራ አስፈፃሚዎቹ መኪናቸው ብቻ ተፈትሾ እንዲወጣ መደረጉን የፓርቲው ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ግርማ ሰይፉ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ቢሮውን ሲቆጣጠር ከስራ አስፈፃሚው ውጭ በቢሮ ያሉ የፅህፈት ቤት ሰራተኞችና ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች ላልተወሰነ ጊዜ ከቢሮ እንዳይወጡ፣ከግቢ ውጭ የነበሩትም እንዳይገቡ መደረጉን የአይን እማኞች ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ ፖሊስ ቢሮውን በኃይል ሲቆጣጠር ምንም ዓይነት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመያዙ ታውቋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት በምርጫ ቦርድ እነ ትዕግስቱ አወሉ ከተመረጡ በኋላ አሁንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ዜና አዲስ አበባ ቸርችል ጎዳና አካባቢ የሚገኘው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽህፈት ቤትም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቁሟል፡፡ ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፓርቲዎቹን ዋና ጽህፈት ቤት ለምን እንደተቆጣጠረ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም፡፡ የአዲስ ሚዲያ ፖሊስ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ፤ፖሊሶችም የፓርቲዎቹን ቢሮዎች ተቆጣጠሩ የሚል ትዕዛዝ ከመሰጠቱ በስተቀር ለምን እንደተቆጣጠሩ ራሳቸውም ምክንያቱን እንደማያውቁ ተጠቁሟል፡፡ ምርጫ ቦርድ መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ሂደትን ተክትሎ በዋዜማው ሁለት አንድነት እና መኢአድ ፓርቲዎችን በማፍረስ ሌላ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡ ቀደም ሲል “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” ከህወሓት/ኢህአዴግ የተሰጠውን ትዕዛዝ ከማስፈፀም ውጭ ነፃና ገለልተኛ አይደለም፣ቦርዱን የሚመሩት ስራ አስፈፃሚዎችም ተቋሙን ለመምራት የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነት ስለሌላቸው ለተቋሙ አይመጥኑም፣..በሚል በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አሁን ያለው የቦርዱ እንቅስቃሴ በቀጣይ ቀናትም ከምርጫው ዋዜማ እስከ ድህረ ምርጫ አዳዲስ ውሳኔዎችን እና እንቅስቃሴዎችን ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ሰበር ዜና፤ ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድን ፓርቲን ለእነ ትግስቱ አወሉና ለእነ አበባው መሐሪ ሰጠ
- ‹‹እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው›› -ፕሮፌሰር መርጋ በቃና
ምርጫ ቦርድ አንድነትን ለእነ ትግስቱ አወሉ፣ እንዲሁም መኢአድን ለእነ አበባው መሃሪ መስጠቱን ዛሬ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቀ፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹የእነ በላይ በፍቃዱ ቡድን›› በጠቅላላ ጉባኤ እንዳልተመረጠ፣ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ አባላት እንዳልመረጠ፣ የተመረጡበትም 51 ሲደመር አንድ መርህ አለመሆኑን፣ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ ሪፖርት አለማድረጉንና ለአባላቱና ለፓርቲው ክብር የሌለው በመሆኑ ፓርቲውን ማስቀጠል እንደማይችል ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል የትግስቱ አወሉ ቡድን መርህ ይከበር እያለ እየታገለ በመሆኑ፣ የኢ/ር ግዛቸው ካቤኔ አባላት ተገፍተው የወጡ በመሆናቸው፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ለቦርዱ ሪፖርት እንዳደረጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን›› ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንጂ እነሱ ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው እንዲሁም ለአባላቶቻቸውና ለፓርቲው ክብር ስላላቸው እውቅናውን ለእነሱ ሰጥቻለው ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹ምርጫ የሚገባ ፓርቲ በማስፈለጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን ፓርቲውን የሚያስቀጥለው ባለመሆኑና ፓርቲውን እንደ ፓርቲ እንዲቆይ ስለሚፈለግ ዛሬ ጥር 21 ቦርዱ ባደረው አስቸኳይ ስብሰባ እነ ትግስቱ አወሉ ወደ ምርጫ እንዲገቡ ወስኗል›› ብሏል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ ስለመሆኑ በምን ታረጋግጡልናላችሁ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ሁለቱም ችግር አለባቸው፡፡ እኛ ያየነው በአንጻራዊነት ነው፡፡ የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ችግር ቢኖርበትም ከዛኛው የተሻለ ነው፡፡ እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ እነ ማሙሸት አማረ በጠቅላላ ጉባኤ ባለመመረጣቸው፣ ለተከታታይ 3 ወራት ወርሃዊ መዋጮ ያላወጣ አባል ከአባልነት የሚሰረዝ በመሆኑና ከፓርቲ አባልነትም ስለተባረሩ እንዲሁም ህገ ወጥ ማህተም በማሳተማቸው እውቅና እንዳልሰጣቸው ገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል 2005 ዓ.ም ላይ አበባው መሃሪ የተመረጡበት ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ እንዳልነበር ቢታመንም በተደረገ ምርመራ የተሟላ መሆኑ በመታወቁ፣ በትክክለኛው ማህተም ስለሚጠቀም፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ በተባለበት ወቅት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረጉና ሪፖርቱንም ስላቀረበ ወደ ምርጫው እንዲገባ ወስኛለሁ ማለቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ለመሳተፍ መወሰናቸውን ተከትሎ ህወሓት/ኢህአዴግ በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ሊያፈርሳቸው የተለያየ ህገወጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፣ ቦርዱ ገለልተኛ እና ነፃ አለመሆኑን በድርጊቱ እየገለፀ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተቃውሞና ቅሬታ እያቀረቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
“የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!”- የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ጥምረት
በተቃውሞ ሰልፉ በአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት እንዲሁም ሌሎች ዜጎች ላይ በፖሊስ የተፈፀመውን ድብደባ የ9ኙ ትብብር ፓርቲዎች ጥምረት አውግዟል፡፡ የ9ኙ የትብብር ፖለቲካ ድርጅት መኢአድ፣ሰማያዊ፣የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የከንባታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና ሌሎች አባላትን ያቀፈ የፖለቲካ ጥምረት ድብደባውን በፅኑ አውግዟል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይገኛሉ፡-
የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!
ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ ስለመስራትና ሌሎቹም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ በየጊዜው የሚወተውተው አገራችን በዚህ ዘመን በማይመጥን አምባገነንና የጭካኔ ስርዓት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመረዳቱ ነው፡፡ ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነንና ጨካኝ ስርዓት ህዳሩ 27/28 2007 ዓ.ም የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በወጡት አመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና በየጎዳናው የተገኙት ንፁሃን ላይ ከፍተኛ ድብደባና የጅምላ እስር በመፈፀም ስርዓቱን ለመታገል የተነሳነበትን አላማ ትክክለኝነት አረጋግጦልናል፡፡
በዛሬው ዕለትም ገዥው ፓርቲ በፓርቲያቸው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚፈፅመውን ደባ፣ ምርጫ ቦርድንና የህዝብ ሚዲያን ተጠቅሞ ፓርቲውን ለመከፋፈልና አሳንሶ ለማሳየት የሚያደርገውን እኩይ ተግባር በመቃወም ሰልፍ የወጡ የአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና የፓርቲው ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ቤተ ክርስትያን አካባቢ የነበሩ አዛውንት ምዕመናንን ሳይቀር በመደብደብ ጭካኔውን ዳግመኛ አሳይቶናል፡፡ ፖሊስ በትዕዛዝ በአንድነት አባላት ላይ ከፍተኛ የጭካኔ እርምጃ ወስዷል፡፡ አብዛኛዎቹንም በጅምላ አስሯል፡፡
ስርዓቱ በእነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሁንም የጭካኔ እርምጃውን መድገሙ ስልጣኑን የማጣት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳለ እና ከይስሙላ ያለፈ ለሰላማዊ ትግሉ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ትብብራችን የስርዓቱን ጨካኝነት እያወቁም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በስርዓቱ የማይከበረውን ህገ መንግስታዊ መርህ ተከትለው ሰልፍ ለወጡ ቆራጥ የአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል፡፡ መስዋዕትነታችሁ ለነገ ድላችን ስንቅ በመሆኑ ይበልጡን ተጠናክራችሁ በጋራ ትግላችን እንደምናጠናክርም እምነታችን ነው፡፡
በተቃራኒው ገዥው ፓርቲ ህግ የማክበርና የማስከበር ሚናውን ረስቶ ፖሊስ፣ ደህንነትንና ሌሎች ተቋማትን ለራሱ ስልጣን ማስጠበቂያ በማዋል በአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን ለዘመኑ የማይመጥንና በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለጠየቁት ኢትዮጵያውያንም የማይገባ የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
ኢትዮጵያውያንን የማስተዳደር አቅምና ሞራል ያጣው ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ማዳፈን የማይቻል መሆኑንና አገራችን ወደባሰ ችግር እንደሚከታት ተረድቶ ከዚህ የጭካኔ እርምጃው እንዲቆጠብ፣ እርምጃውን የወሰዱትን አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የታሰሩትን በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን፡፡ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያና ሌሎች ተቋማት ገዥው ፓርቲ አላፊ መሆኑን በመገንዘብና ከገዥው ፓርቲ ታዛዥነት በመውጣት ወገኖቻቸሁ ላይ እንዲህ አይነት የጭካኔና አሳፋሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባችሁ ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡
ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!
ጥር 17/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመኢአድ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ዘመነ ምህረት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ፓርቲው ገለፀ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የፓርቲያቸው ምክትል ፕሬዝደንት እና የሰሜን ቀጠና ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘመነ ምህረት እጅግ ዘግናኝ ድብደባ ደርሶባቸው ሲል ፓርቲው ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡ አቶ ዘመነ የመኢአድን ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ወደ መኖሪያቸው ጎንደር ከተማ ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ የደህንነት ክትትልና ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ለፓርቲያቸው አሳውቀው ነበር ያለው ፓርቲው ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ጎንደር ከሚገኘው መኖሪያው ቤታቸው ከባቤታቸውና ከህፃን ልጃቸው ፊት የፖሊስ ልብስ በለበሱ አካላት ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ግልጾአል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓርቲው አባላት ባደረጉት ክትትል አቶ ዘመነ አዘዞ የሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ውስጥ እንደሚኙ አረጋግጠናል ያለው መግለጫው የሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት ከፍተኛ ስቃይና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡
ከአቶ ዘመነ በተጨማሪ ጠቅላላ ጉባኤውን ተሳትፈው የተመለሱት የፓርቲው የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ እያሱ ሁሴን 3 አመት ተፈርዶባቸው እስር ቤት እንደሚገኙ፣ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ መ/አ ጌታቸው መኮንን፣ አቶ ጥላሁን አድማሴ የተባሉትን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው መግለጫው በአመራርና አባላቶቻቸው ላይ የሚደረገው እስር መኢአድ ምርጫውን ተጠቅሞ በገዥው ፓርቲ ላይ ጫና ማሳደር ስለሚችል እንደሆነ ተገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል በአባላቶቻቸው ላይ በሚደርሰው በደልና ጫና ባሻገር ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ከምርጫ 2007 እንዳይሳተፍ የኢህአዴግ ቀኝ እጅ ሆኖ በመስራት ላይ እንዳለ ያወሳው መግለጫው ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከተደረገ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በፓርቲው ላይ የሚፈጽመውን በደል ተከትሎ ፓርቲው በሚደርገው ትግልም ህዝቡ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡