የመኢአድ አመራር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሱ
በታምሩ ጽጌ
አቶ ማሙሸት አማረ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራር የነበሩትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለሌሎች አመራሮች ጋር በተፈጠረ ልዩነት ከአባልነት የራቁት አቶ ማሙሸት አማረ፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
አቶ ማሙሸት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን ተላልፈው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማሴር መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. መልምለው ያደራጇቸውንና በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን አስተባብረው፣ በአማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች የሽብር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ማዘጋጀታቸውን በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት ኃላፊነት ወስደው እንቅስቃሴውን ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ለመምራት ኬንያ ለመሄድ ሞያሌ ከተማ እንደገቡ፣ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አባል አማካይነት እንደተመለመሉ የሚገልጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ተልዕኮ በመቀበል ከቡድኑ በሚላክላቸው ገንዘብ የጦር መሣሪያ በመግዛትና ማሠልጠኛ በማመቻቸት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረውን ሁከት እንዲቀጥል ሲያደርጉ እንደነበር ገልጿል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በምርጫ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ማስወገድ እንዲቻል፣ በውጭና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር የሽብር ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አባላት በመመልመልና በማደራጀት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ እንዲልኩም ተልዕኮ እንደተሰጣቸው አክሏል፡፡
ተከሻሹ በ2007 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ለቡድኑ አባላትን መልምለውና ወታደራዊ ቤዝና ማሠልጠኛ ወዳላት ኤርትራ በሁመራ በኩል መላካቸውን፣ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ከተለያዩ አካባቢዎች 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሰብስበው መንግሥትን ከሥልጣን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝባዊ አመፅ መሆኑን፣ አመጽ ለመፈጸም ደግሞ የጦር መሣሪያ ስለሚያፈልግ እያንዳንዱ አባል ሌላ አባላት በመመልመል፣ በማደራጀትና በማስፋፋት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል አንዱን ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ ማድረግ እንዳለባቸው ተልዕኮ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ተከሳሹ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ውስጥ ለሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ቤዝ የሚሆን ቦታ በመምረጥ፣ ከደብረ ብርሃንና አዲስ አበባ የተመለመሉ ዘጠኝ አባላትን ወደ ማሠልጠኛ በመላክ ሥልጠና ማስጀመራቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. አቶ ማሙሸት ዘመነ ምሕረቱ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አመራርና ለገሰ ወልደሀና ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመሰብሰብ፣ በጎንደር ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ሰሜን ሸዋ ጫካ ውስጥ በመግባት፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲደርስ ተልዕኮ መስጠታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
በአጠቃላይ አቶ ማሙሸት የሽብርተኛነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የማቀድ፣ የመዘጋጀት፣ የማሴርና የማነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ቀረቦባቸዋል፡፡ ተከሳሹ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆኑ፣ በግላቸው ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተር
አቶ ማሙሸት አማረ ለውሳኔ ተቀጠሩ
“ምስክርነቱ የሐሰትና የተጠና ነው!” ጠበቃቸው
አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት ለተደረገውና ለዋናው (ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ነሃሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለነሃሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ለውሳኔ ተቀጠሯል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማቅረቡ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
አቶ ማሙሸት በአዲሱ ክስ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለመስማት ከ5 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደተመላለሰ የተገለፀ ሲሆን በተለይ አንዱ ምስክር በፖሊስ ተይዞ እንዲመጣ ቢጠየቅም ፖሊስ ሳያስፈፅም ቀርቷል፡፡ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ዛሬ የመሰከሩ ሲሆን “አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል” ሲሉ መስክረዋል፡፡
ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙ ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሲጠየቁ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ “የግል” ብሎ የነበር ቢሆንም በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡
ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡ ዳኛው “በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?” ሲሉት መልስ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡
የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ አመራባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አይ ኤ አይ ኤልን ለመቃወም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ረብሻ አንስተዋል በሚል በተመሰረተባቸው ክስ ሰዓትና ቀን፤ ፓርቲያቸው መኢአድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሌላ እንዲሰጥ መወሰኑን በመቃወም ፍርድ ቤት ክስ መስርተው ለክርክር በተጠቀሰው ሰዓትና ዕለት ችሎት ላይ እንደነበሩ የሚያስረዳ ደብዳቤ ፍርድ ቤቱ መፃፉ ይታወሳል፡፡