Category Archives: News

በወለጋ ሻምቡ ወህኒ ቤት አንድ ወታደር ሁለት አለቆቹን ገደለ

ትናንት ህዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ በሚገኘው ሆሮጉድሩ ወረዳ ሻምቡ ወህኒ ቤት አንድ ወታደር ሁለት አለቆቹን በመሳሪያ ገድሎ እጁን ሰጠ፡፡

ገዳዩ አለቆቹ በተደጋጋሚ በእስረኞች ላይ እና በሌሎች የበታች ሰራተኞች ላይ ጸደጋጋሚ በደል ሲፈፅሙ ይቃወም የነበረ ሲሆን ትናንት ግን እስካሁን በውል ባልታወቀ ምክንያት ሁለቱነብ አለቆቹን መግደሉን ምንጮቻችን ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ የወረዳው ፖሊሶች ዝርዝር መረጃውን እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡

በአፍሪካ ትልቁ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ በደረሰ የእሳት አደጋ ንብረቶች ወደሙ

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ትልቁ የንግድ ማዕከል መርካቶ ዛሬ ህዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በኋላ በመርካቶ ልዩ ቦታው ከምዕራብ ሆቴል ወደ በርበሬ በረንዳ በሚወስደው መንገድ ሐረር ሜትሮ ሆቴል ዓለም ሽንሽን እና ጌጣጌጥ በሚሸጡባቸው ሱቆች እና በተለምዶ ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በተነሳ የድንገተኛ ችሳት ቃጠሎ እስካሁን ግምቱ ያልታወቀ ንብረት አውድሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ድርጅት እሳቱን ለማጥፋት በቶሎ ባለመድረሱ ብዙ መትረፍ የሚገባቸው ንብረቶች ሊወድሙ መቻላቸው የታወቀ ሲሆን፤ ድርጅቱ በበኩሉ ወደ መርካቶ መሄጃ መንገዶች በመቆፋፈራቸው ለመዘግየቱ እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ በአካባቢው ያሉ እማኞች በበኩላቸው ድርጅተሩ በከተማው መቼም ቢሆን በአፋጣን ደርሶ ውድመትን አድኖ አያውቅም፤ ብዙ ንብረት ማትረፍ ሲቻል ብዙ ጊዜ ሆን ብሎ በሚመስል መልኩ ይዘገያል የሚል ትችትን አቅርበዋል፡፡

Image

በአዲስ አበባ የተጠራው ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ እና እስር ተጠናቀቀ

ሰማያዊ ፓርቲ የሳውዲዓረቢያ መንግስት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያ፣ እስር እና እንግልት ለመቃወም ዛሬ አርብ ህዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሰውዲ ኤምባሲ ሊደረግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ድብደባ እና እስር ተጠናቀቀ፡፡ ሰለፍ 4 ኪሎ ግንፍሌ ከሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ሲጀምር በበፖሊስ እገታ ተፈፅሞ ነበር፡፡ በመቀጠልም አራት ኪሎ ቅድስት ስላሴ ኮሌጅ ፊትለፊት ደግሞ በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ዳግም እገታ ፈፀሙ፡፡

በመጨረሻም በእገታው ያልተበገረው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ አካባቢ ቢያመራም በ3 ፒክአፕ መኪና የመጡ የፈደራል ፖሊሶች የተገኘውን ህዝብ በያዙት ዱላ፣ በእጅ እና በእግር ድብደባ ጀመሩ፡፡ ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት ላይ እዛውም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አቶ ይልቃል ጌትነት፣ አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ አቶ ጌታነህ ባልቻ ፣ አቶ ወረታው ዋሴ፣ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና አቶ ሀብታሙ ደመቀ በፖሊስ ታስረው ተወሰዱ፡፡ በዚሁ ሰዓት ደራሲ አቶ አስራት አብርሃምም መታሰሩ ታውቋል፡፡

በሰልፉ ላይ ከተገኙ ነዋሪዎችም ቁጥራቸው ከ500 የማያንሱ ሰዎች ታፍሰው ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ እና ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ከቀኑ 10፡50 ሰዓት አካባቢ ከታሰሩት መካከል የተወሰኑትን መፍታት መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እስከተዘገበበት ሰዓት ድረስ ከተፈፀመባቸው ድብደባ በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አሁንም እስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

 በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመለስ ከማል እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውን ለማናገር ብንሞክርም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡ በፖሊስ ድብደባ ተፈፅሞባቸው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው በተለይ ከላንቻ አካባቢ ካለው ከፖሊስ ጣቢያ በሚኒባስ እየተወሰዱ መሆናቸውን የዓይን እማኞች የገለፁ ሲሆን፤ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችም ተባባሪ ናችሁ በሚል አሁንም እየተለቀሙ እየታሰሩ መሆኑን ምንጮቻችንን አስታውቀዋል፡፡

ይህ ሁሉ ድርጊት ያበሳጫቸው የሰልፉ ታዳሚዎች እና ታዛቢዎች መንግስት ይሄንን ስፍ እራሱ ማስተባበር የሚጠበቅበትን ዜጎች በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት ድርጊቱን በመቃም መውጣታቸው ሊበረታታ ሲገባ መከልከሉ ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን በሳውዲዓረቢያ መንግስት እና ፖሊስ እደረሰባቸው ያለውን ግድያ፣ እስር እና ስቃይ እንደሚደግፈው በግልፅ ያረጋገጠበት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የፊታችን እሁድ ህዳር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድነት ከሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ ሰልፍ በዚሁ በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የሳውዲዓረቢያ ኤምባሲ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸውም ታውቋል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት የነ አቶ በቀለ ገርባን ይግባኝን እንደማያይ አስታወቀ -እነ አንዱዓለም አራጌም የፊታችን ሰኞ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የኦፌኮ-መድረክ ምክትል ሊቀመንበር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ላይ እና የኦፌኮ ሌላው አመመራር ወጣት ኦልባና ሌሊሳ የጠየቁትን ይግባኝ ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የህግ ስህተት የለውም በሚል ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጎታል፡፡ አቶ በቀለ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በፌደራሉ አቃቤ ህግ በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል 8 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን ፤ ይህን በመቃወምፈደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀው ነበር፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነውን የ8 ዓመት እስራት ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር ዝቅ ማድረጉይታወቃል፡፡ አቶ ኦልባና ሌሊሳም በከፍተኛው ፍርድ ቤት 13 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸውን በይግባኝ ጠቅላይፍርድ ቤቱ ወደ 11 ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ እነ አቶ በቀለ ገርባ የተከሰስነው በሐሰት የፈጠራወንጀል እንጂ ምንም የፈፀምነው ወንጀል ስለሌለ፤ አቃቤ ህግም በከሰሰን ወንጀል ያቀረበው ማስረጃ እርስ በርሱየሚጣረስ በመሆኑ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በነፃ ሊያሰናብተን ይገባል ሲሉ ይግባኝ ቢሉም ፤ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዛሬውጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ውሎው የይግባኝ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

በተያያዘ ዜና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ ፣ሌላው የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ናትናኤል መኮንን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ እናሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰነባቸውንየጥፋተኝነት ውሳኔ በመቃወም ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት 6 ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀነ ቀጠሮ መሰጠቱንጠበቃው አቶ አበበ ጉታ አስታውቀዋል፡፡

ይህም ለነ አቶ አንዱዓለም ቀጠሮ የመጀመሪያው የሰበር ሰሚ ችሎት ቀነ ቀጠሮ መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ አንዱዓለምአራጌ በከፍተኛው እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕድሜ ልከል ፅኑ እስራት ሲፈረድበት ጋዜጠና እስክንድ ነጋ ደግሞ 18 ፅኑ እስራት ፍርድ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መፅናቱ ሲታወቅ የሌሎችም እንዲሁ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለእምነታቸው ዘብ ቆመው ዋሉ!

ከጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘውና ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው 32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ የተለየ ክሥተት አስተናግዷል፡፡ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚል ርእስ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በተካሄደው ውይይት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋራ በተለይም በመቻቻልና በኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ዙሪያ ሲከራከሩና በአንዳንድ ኹኔታዎችም ኤክስፐርቶቹን ሲገሥጹ ውለዋል፡፡

popብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ÷ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስ÷ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተጨባጭ ኹኔታና ከቀረበው ጽሑፍ እየተነሡ በመረጃ፣ በጥያቄና በትችት ስለ መቻቻል ጽሑፍ ያቀረቡ የሚኒስቴሩን ባለሥልጣናት ፈተና ላይ ጥለዋቸው አምሽተዋል፡፡ የሊቃነ ጳጳሳቱ ምስክርነት ‹‹የባዕድ እምነት አራማጆች በቤተ ክርስቲያንና በካህናት ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉና ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ታላቅ ድፍረት እንደሚፈጽሙ›› ቀደም ሲል ለአጠቃላይ ጉባኤው የቀረቡ ሪፖርቶችን በገሃድ የሚያጠናክሩና የሚያጸኑ ናቸው፡፡

የሚኒስቴሩ አማካሪዎችና ባለሞያዎች በበኩላቸው፣ ቅሬታዎቹ በተጨባጭ ማስረጃዎች ተደግፈው በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩል ቢቀርቡላቸው መፍትሔ እንደሚሰጧቸው፣ በሊቃነ ጳጳሳቱ ከተገለጹት በላይ ያልተነገሩ ቅሬታዎች ስለመኖራቸው በየወረዳው ተዘዋውረው መረጃዎችን አሰባስበው ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ በ‹‹ሕግ የተያዙት ጉዳዮች በሕግ እንደተያዙ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ›› ለዚህም የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥንካሬ አስፈላጊ መኾኑን አሳስበዋል፡፡

የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጥያቄ፣ አስተያየትና ትችት በከፍተኛ ጥሞና የተከታተለው የአጠቃላይ ጉባኤው ተሳታፊ የሞቀ ድጋፉን ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የውይይት አጀንዳ አጋጣሚውን እንደ ምቹ ኹኔታ ለመጠቀም ያሰቡ የሚመስሉትና ልዩ ፍላጎት ያላቸው የሚመስሉት አቡነ ሳዊሮስ ውይይቱን ሳይጨርሱ አቋርጠው ሲወጡ ታይተዋል፡፡

‹‹አክራሪነት/ጽንፈኝነት የሚለው ቋንቋ እናንተ ናችኹ ያሰማችኁን፤ ከዚህ በፊት አይታወቅም፤ ዕድሜ ሰጥታችኁም ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችኹ፡፡ አባቶቻችን የእረኛ ሰነፍ ከሩቅ ይመልሳል ይላሉ፤ በሩቅ መቅጨት ሲገባ ታሪካቸው እየተተረከ ብዙ አተራመሱት፤ [የአክራሪነት]መረባቸውን ከላይ ዘርግተዋል፤ መሬት አልነኩም ተባለ፤ መረባቸውን መሬት ዘርግተው፣ ሕዝብ እያተራመሱ ሙስሊሙ ራሱ እኛ አናውቃቸውም እያለ እየጮኸ እንዴት መሬት አልነኩም ይባላል? በእናንተ አነጋገር መሬት ሲነኩ እንዴት ሊያደርጉን ኖሯል? . . . ተቻቻሉ? እስከ ምን ድረስ ነው መቻቻል? ምንድን ነው መቻቻል? አሁን በወለጋ ያለው ኹኔታ መንግሥት በአገሩ ያለ ያስመስላል? ሰው እግሩን እሳት እየበላው ቻል ይባላል? እንድንቻቻል አድርጉን፤ እንችላለን!!›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት በሦስት ወረዳዎች – ነጆ፣ ባቦ ገምቤል፣ ቤጊ – በፖሊቲካና የመናፍቃን አባላት የኾኑ ባለሥልጣናት በሥነ ልቡና ጦርነት ምእመኖቻችንን እየነጠቁን በደል አድርሰውብናል፡፡ አገሩ ለፕሮቴስታንት የተፈቀደና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አታስፈልግም የተባለ ነው የሚመስለው፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/
‹‹ከዚህ በፊት በዚህ መድረክ ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም መጥተው ብዙ ነገር አስጨብጫቸው ነበር፤ ምላሽ አላገኘኹም፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ነገር በጋሞጎፋ ሀ/ስብከት ተፈጥሯል፡፡ የደመራ በዓል በሚከበርበት ቦታ ላይ ምትክ ሳይሰጥ ተወስዶ ሱቅ በመከፈቱ ዘንድሮ በመቶ ወረዳዎች የደመራ በዓል ሳይከበር ሕዝቡ እያዘነ፣ እያለቀሰ ቤቱ ውሏል፡፡ በሴቻ ከተማ ባልተፈቀደ ቦታ ለስምንት ቀን ጉባኤ አዘጋጅተው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ጽላት፣ ቅዱሳን መላእክት እያነሡ ሲቃወሙ ነበር፡፡ ይህ ነዳጅ የተረከፈከፈበት ክብሪት ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ሰልፍ እንውጣ ሲለን ሰላማችንን፣ ልማታችንን እንወደዋለን፤ መብታችንን በሕግ ነው የምንጠይቀው ብለን ከልክለናል፡፡ ጉባኤ ማካሄዳቸውን አንቃወምም፤ ግን ስማችንን ማንሣት ምን ማለት ነው? ይሄ ነው መቻቻል? እኛ ሌላውን አንነካም፤ ስንነካ ግን መብታችንን እንጠይቃለን፤ ቤተ ክርስቲያኗ መሬት መያዟን የወረዳው ባለሥልጣናት መሬቷን ቆርሳችኹ ጉባኤ አድርጉ ይላሉ፤ ይህን እንደ በቀል ነው የሚያዩት›› /ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፤ የጋሞጎፋና ደቡብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹በሶማሌ ክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ የመንግሥት መሥ/ቤቶች ብዙ ሠራተኞች ምእመናን አሉ፡፡ ያሉን አብያተ ክርስቲያናት ግን አምስት ብቻ ናቸው፡፡ በየወረዳው ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ ምእመናን ይጠይቃሉ፡፡ እስከ ክልሉ መስተዳድር ድረስ ለምእመናን የምንጮኸበት፣ መብታችንን የምናስከበርበት ኹኔታ ግን የለም፡፡. . .ምእመናን እምነታቸውን በካሴትና በዘመናዊ መሣርያ ካልኾነ እኛ ተንቀሳቅሰን ለማገልገል የምንችልበት ኹኔታ የለም፡፡ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የምእመናኑን ብዛት ዐውቀንና አጥንተን ያዘጋጀነው ስላለ የሚመለከተው ክፍል መፍትሔ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ የሶማሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹ታሪክ ክፉ ይኹን ደግ እንደ ታሪኩ ነው የሚተረክ፤ ወንድማችን [ከዕለቱ የሚኒስቴሩ ሦስት ተናጋሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ገዛኽኝ ጥላሁን] ይህን ታሪክ ስታቀርብ ምን ያህል ላይሰንስ አለኽ? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ፤. . .ክርስትና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው የሚለው ሌላ ጊዜ እንዳይደገም፣ ዛሬ ግራጁዌት አድርጉት፤ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ክርስቶስ ካረገ ዓመት አልሞላውም፤ ገና ከኢየሩሳሌም አልተወጣም፤ ከሰው አይደለም ደግሞ ከእግዚአብሔር ነው የተቀበለችው፡፡ (የሐዋ.8÷26) ባለሥልጣን ሁሉ አገር የሚጠላ ምንድን ነው? በዓለም በትልቁ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፤ በእግዚአብሔር ማመንንም የተቀበልን ከአይሁድ በፊት ነው፡፡ ታሪኩን አታዛቡ፤ ከዚህም ስትመጡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሠለጠነ፣ ቢቻል ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የኾነ፣ በጳጳሳቱ ፊት ለመናገር የሚገባው መኾን አለበት፤ አታስቆጡን! . . .ቤተ ክርስቲያን እንግዳ ሲመጣ ሃይማኖትኸ ምንድን ነው አትልም፡፡ እግር አጥባ፣ አብልታ ነው፤ ግን ልታስተምሩን ስትመጡ ሳብጀክቱን ግራጁዌት አድርጋችኹ ኑ!›› /ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹. . .ችግሮቹ መፍትሔ አጥተው ቀርተዋል፡፡ ስድስት አድባራት ተቃጥለዋል፤ ሦስቱ በአንድ አካባቢ፣ ሦስቱ በተራራቀ ኹኔታ፡፡ ቢጮኽ የክልሉ መንግሥት አይሰማም፤ መልስም አይሰጠም፤ እንዲያውም ያስተባብላል፤ የተበደለ ሲናገር ፖሊቲካ ነው እያሉ ያተራምሱናል፤ ሐቅ ሲነገር ድብቅ የለውም፤ ሌትም ቀንም ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለ፣ የሚጮኽበት እየታጣ ነው፡፡. . .የመንግሥት ሥልጣን የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት? ለሌላው ብቻ ነው የቆሙት? ይህ የሰላም መደፍረስ አይደለም? መቻቻል የሚባለው አማርኛ ምንድን ነው? አማርኛ ነው እንዴ የምታመርቱት? በየቢሯቸው ሄጃለኹ፣ አንዱ እንደውም ተቆጣኝ፤ ይኸው ዘመን ተቆጥሯል፤ ዐርባ ዓመት ኾኗል፤ ለሕዝቡም ለመንግሥትም የምንኖረው እኛ ብቻ ነን፡፡ ለምንድን ነው በሽፋንነት የምትጠቀሙብን? ሁሉም ሲያጭበረብረን፣ ሲያታኩሰን፣ ሲያቃጥለን የሚኖረው መንግሥትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡ ይቅርታ አድርጉልን፡፡›› /ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/
ምንጭ፡- ሐራ ተዋህዶ