Category Archives: Social and Culture

ሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ

የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማ

የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማ

ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትን እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በጽሑፍ ይቅርታ ይጠይቅ በማለት የተላለፈው ውሳኔ ከሕግ አግባብ ውጪ ስለሆነ ተቃውሞውን በመግለጽ ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታወቀ፡፡

የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ባለፈው ሐሙስ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድን ስም አጥፍቷል ብለዋል፡፡ ‹‹በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አንቀጽ 102 (4)ሀ፣ ለ እና ሠ እንዲሁም 102 (6) ሐ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ሥልጣን መቀበል፣ ሕጋዊ ትዕዛዙንና መመርያውን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የጋራ የምክክር መድረኮች ወይም ሌሎች መድረኮች ላይ ወኪል የመላክ ኃላፊነት እንዳለባቸውና በሐሰት ስም ከማጥፋት መቆጠብ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ግን ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት ያዘጋጃቸውን የጋራ ምክክሮች እንዲበተኑ ሙከራ አድርጓል፣ እየረገጠ ወጥቷል፣ በሐሰት ቦርዱን ወንጅሏል፡፡ እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርጓል፤›› በማለት ፓርቲው በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ ቦርዱ ወስኗል በማለት አስታውቀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ውሳኔውን አስመልክቶ፣ ‹‹እኛ ይህን የምንረዳው የምርጫ ቦርድ የራሱ አቋም ሳይሆን ኢሕአዴግ በቦርዱ ውስጥ ምን ያህል ሚና እንዳለው ያጋለጠ ውሳኔ መሆኑን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰጠነው አስተያየትና ስብሰባ ረግጠን መውጣታችን ዘለፋ መስሎ ከተሰማቸው አትዝለፉን እንነጋገር ማለት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ይቅርታ ጠይቁኝ ብሎ ማስፈራራት አገራችንን አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ይቅርታ መቀለጃ አይደለም፡፡ እኛም በዚህ ምክንያት አናስተናግደውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም በመሠረቱ እኛ አንድ ድርጅት ነን፡፡ ምርጫ ቦርድም እንዲሁ አንድ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሊግባቡ የሚችሉት ደግሞ በሕግና በደንብ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ካጠፋ ወይ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፣ ወይም ቦርዱ ባለው ሥልጣን ችግሩ ይፈታል፡፡ ቦርዱም ካጠፋ እንዲሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ይቅርታ ጠይቀኝ ብሎ መጠየቅ ፍፁም ተቋማዊ አሠራር አይደለም፤›› በማለት ውሳኔውን ፓርቲያቸው እንደሚቃወም አስታውቀዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ በድጋሚ በጠራው አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዘዳንቱን በመምረጥ ተጠናቀቀ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዓርማ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዓርማ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በመጪው ምርጫ ግንቦት 2007 ዓ.ም. ለመሳተፍ መወሰኑን እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ 450 ዕጩዎቹን በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ማቅረቡን ይፋ ካደረገ በኋላ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ የፓርቲውን ፕሬዘዳንቱን ካለተመረጠ ምርጫው ላይ እንዳይሳተፍ አደርጋለሁ ባለው መሰረት ዛሬ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቀበና በሚገኘው የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት አዳራሽ ጠቅላላ ጉባዔው መካሄዱ ታውቋል፡፡ ፓርቲውን ለመምራት በዕጩነት ቀርበው የተወዳደሩት አቶ በላይ ፈቃዱ፣ አቶ አለነ ማህፀንቱ እና አቶ ዳግማዊ ተሰማ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ለፕሬዘዳንትነት የተወዳደሩት ሶስቱም ዕጩዎች በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በትምህርታቸው የማስተርስ ድግሪ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ ሶስቱም በአንድነት ፓርቲ በተለያየ ከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በሙያቸውም የተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ማገልገላቸው ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በነበረው ውድድር አቶ አለነ ማህፀንቱ ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከውድድሩ ውጭ በማድረግ በአቶ በላይ ፈቃዱና በአቶ ዳግማዊ ተሰማ መካከል በተደረገ የምረጡኝ ቅስቀሳና ውድድር የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ባደረጉት የምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መሰረት አቶ በላይ 183 ድምፅ በማግኘት የአንድነት ፕሬዘዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አንድነት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የጠቅላላ ጉባዔው አባላት 320 ሲሆን፤አቶ በላይም የአባላቱን 57.2 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተደረገው የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በከፊል

ውጤቱን ተከትሎም ተፎካካሪያቸው የነበሩት አቶ ዳግማዊ ተሰማ ለአቶ በላይ ፈቃዱ የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት በማስተላለፍ መጪውን ምርጫ አንድነት ፓርቲ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በጋራ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውና ለዚህም በፓርቲው የሚሰጣቸውን የስራ ድርሸና ተልዕኮ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ መግለፃቸውን ከስፍራው የአዲስሚዲያ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ በላይ ፈቃዱ ፓርቲውን በፕሬዘዳንትነት ለመምራት ቃለ መሐላ መፈፃማቸው ታውቋል፡፡

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ተመራጭ ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ተመራጭ ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

በጉባዔው ላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዦች የተገኙ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ህግ መሰረት ሂደቱን መታዘብ የነበረበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን ለመታዘብ እንደማይገኝና ወኪልም እንደማይልክ ቀደም ሲል ከፓርቲው ለተደረገለት ጥሪ በደብዳቤ ማሳወቁ ተጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲል ታህሳስ 2006 ዓ.ም. የፓርቲው ፕሬዘዳንት የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ለፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ካስረከቡ በኋላ አቶ በላይ ፈቃዱ ያለፉት 3 ወራት የፓርቲው ፕሬዘዳንት ሆነው ማገልገላቸው አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ታሪካዊ የሆነው ጣይቱ ሆቴል የእሳት አደጋ ደረሰበት

አዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኘው ጣይቱ ሆቴል በእሳት ሲቃጠል

አዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኘው ጣይቱ ሆቴል በእሳት ሲቃጠል

ዛሬ እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ከረፋዱ 5 ሰዓት አካባቢ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆቴል የሆነው ጣይቱ ሆቴል የእሳት አደጋ ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ ሆቴሉ ነሐሴ1898 ዓ.ም. በንጉሱ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ብጡል አማካኝነት ጣይቱ ሆቴል በሚል በአዲስ አበባ መሐል ፒያሳ ተመስርቶ ኢህአዴግ ስልጣን እስኪይዝ ድረስ በመንግስት ስር የሚተዳደር ሆቴል የነበረ ሲሆን ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን ወደ ግል በማዞር አቶ ፍፁምዘዓብ አስገዶም ለተባሉ ግለሰብ መሸጡ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በርካታ የታሪክ ባለሙያዎችና የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አባላትና አመራሮች የሀገሪቱ ታሪክ ቅርስ አካል ተደርጎ የተመዘገበን ሆቴል በርካሽም ሆነ በውድ መሸጥ ተገቢ እንዳልሆነ አጥብቀው ቢከራከሩም በኢህአዴግ ተቀባይነት ሳያገኝ ቢቀርም ዛሬ ከባድ የሚባል የእሳት አደጋ ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ከሆቴሉ ያለው ርቀት ከ1 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ቢሆንም በፍጥነት መጥቶ መከላከል ባለመቻሉ ሆቴሉን ጨምሮ ከአደጋው መትረፍ የሚችሉ በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን ከስፍራው የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

በአሁን ወቅት የጣይቱ ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ፍፁምዘዓብ አስገዶም የቀድሞ የህወሃት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ስየ አብርሃ ታናሽ ወንድም የአቶ አሰፋ አብርሃ ባለቤት ወንድም ሲሆኑ፤ ከአቶ አሰፋ አብርሃ ጋር በተያያዘ ሆቴሉን ሲገዙ ሙስና ፈፅመዋል በሚል ለ6 ዓመታት ታስረው መለቀቃቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ በሆቴሉ ላይ ከባድ የሚባል የእሳት አደጋ መድረሱ የታወቀ ቢሆንም፤የአደጋው መንስኤ፣በአደጋው የወደመው ንብረት በአሀዝም ሆነ በዓይነት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

ሰበር ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ተከሰከሰ

አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

ዛሬ ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ ከቶጎ ሎሜ ተነስቶ ጋና አክራ ይጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-400F ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ተከሰከሰ፡፡ አውሮፕላኑ አደጋ የደረሰበት በመጥፎ የአየር ፀባይ መሆኑን በመጥቀስ አብራሪው በጋና ኮቶካ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሰላም ለማሳረፍ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት መሆኑ የጋና አየር ማረፊያ ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር ኒውማን ኳርቴይ ተናግረዋል፡፡

ኦፊሰሩ እንደተናገሩት ከሆነ የበረራ ቁጥር  ET –AQV46 መሆኑን ጠቅሰው፤ የአውሮፕላኑ አብራሪን ጨምሮ በውስጡ የነበሩ 3 ሰራተኞች ከአደጋው ህይወታቸው መትረፉንና በጋና 37 ሚሊተሪ ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአደጋውም 3ቱ ሰረተኞች የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ከመግለፅ በስተቀር ከአውሮፕላኑ መከስከስ በስተቀር በሌላ የሰው ሕይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት ስለመኖሩ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ የተገለፀ ነገር የለም፡፡

አደጋው የደረሰበት የጋና አክራ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም የሀገሪቱ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የጦር ኃይል፣ፖሊስ፣ የደህንነትና የአቭየሽን ባለስልጣን በአካባቢው ተገኝተው ከሚያደርጉት ማጣራት በስተቀር መደበኛው ስራ መቀጠሉን ማረጋገጣቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

በምርጫ 2007 ዓ.ም. ኢህአዴግ የፈራውን ህዝባዊ አብዮት እየጠራ ነው

ብስራት ወልደሚካኤል

ከዚህ በፊት ኢህአዴግ ጠንካራ የሰላማዊ የፖለቲካ ታጋይ አመራሮችንና አባላቱን አሰረ፡፡ በመቀጠልም ጋዜጠኞችና የዞን 9 ብሎገሮችን አሰረ፡፡ ይህም አልበቃ ሲለው አሁን ደግሞ በራሱ ምርጫ ቦርድ ተወዳድረን እናሸንፍሃለን ብለው የቆረጡ ተፎካካሪዎችን ከምርጫ ለማስወጣት ባትሏል፡፡ ለዚህም ማሳያ አንድነት ፓርቲን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ጥሩ ምናም…መኢአድን ደግሞ እናንተም ችግር የውስጥ ችግራችሁን ፍቱ፣…ሰማያዊ ፓርቲን ደግሞ ምርቻ ቦረድ በጠራው ስብሰባ ላይ ረግጣችሁ ጥታችኋልና ይቅርታ ካልጠየቃችሁኝ፣…ኃይማኖታዊ በዓል በሆነውና ከጥር 10-12 በሚከበረው የጥምቀት በዓል ዋዜማና ስነስርኣት ሰማያዊ ልብስ እንዳይለበስ የሚል ትዕዛዝ መስጠት፣…ዛሬ ደግሞ ለነገ ጠቅላላ ጉባኤ የጠራውን አንድነት ፓርቲ ላይ ለመሳተፍ የተንቀሳቀሰውን የአንድነት ፓርቲ የምስራቅ ቀጠና አደራጅ አዳማ/ናዝሬት ላይ ማገት፣…እያለ ጠንካራ የተባሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ አባላትንና አመራሮችን ማገትና ማሰሩን ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በፊት ከ200 ያላነሱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣አባላት፣ጋዜጠኞች፣ብሎገሮችንና አክቲቪስቶችን በግፍ ማሰሩ አይዘነጋም፡፡

eprdf

በርግጥ ኢህአዴግ ድሮም ፈሪ ነው፡፡ የሚፈራው የኢትዮጵያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ሐሳብን በራሱ ይፈራል፡፡ ለዚህም ነው ከእስክሪብቶና ወረቀት ውጭ በእጃቸው ምንም የሌላቸውን ንፁሃንን አሸባሪ እያለ ሚያስረው፡፡ አምባገነንቱና ጨካጭነጹ ከፍርሃትና ከድንቁርና የመኘጨ እንጂ የፖለቲካ ስትራቴጂ ሆኖ አይደለም፡፡ ይህ ግን በስልጣን ለመቆየት ዋስትና ሊሆን አይችልም፤ሆኖም አያውቅም፡፡ ይልቅ ጭቂና እና ጭካኔ በገዥዎች በተበራከተ ቁጥር ገና ወደፊት ይመጣል ተብሎ የተፈራውን ህዝባዊ አብዮት ራሱ ኢህአዴግ እያቀረበ ያለ ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳ የምርጫ እንቅስቃሴ መኖሩና ተፊካካሪዎች ወደ ውድድሩ ቢገቡ እንደ አንድ መልካም ነገር ቢታይም፤ ምርጫው ላይ ከበፊቱ የተለየ ውጤት ይኖራል ተብሎ ላይጠበቅ ይችላል፡፡ የምርቻ ሂደቱ በራሱ ግን ህዝቡን የፖለቲካ መብቱን እንዲጠይቅና እንዲጠቀም ከማድረግ አኳይ አዎንታዊ ሚና መኖሩ እሙን ነው፡፡

ህዝባዊ አብዮት ምንጊዜም የሚፈጠረው በገዥዎች ምክንያት ድንገት እንጂ በህዝቡ ታቅዶና ተፈልጎ አይደለም፡፡ ህዝቡ የአብዮቱ ምክንያት በሆኑ ገዥዎች ህዝባዊ እምቢተኝነት አንዱ አፀፋ ምላሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በርካታ የጦር መሳሪያ አለኝ ብሎ በአፈሙዝ አስቦና ተመክቶ ህዝባዊ አብዮትን ቢፈራም በራሱ ጊዜ እያፈጠነውና እየጠራው ያለ ይመስለኛል፡፡

አሁን ግን ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድን፣ ፍርድ ቤትን፣ ደህንነትን፣ ፖሊስን፣ መከላከያን፣ሚዲያውን እና ኢኮኖሚውንም ይዞ ሊረጋጋ አልቻለም፡፡ የሚገርመው ህዝባዊ ደጀን ከጀርባቸው እንዳለ በማመን እስክሪብቶ፣ወረቀትና ሐሳብ የያዙትን ከጦር በላይ መፍራቱ እርግጥ ነው፡፡ ግን በመፍራት፣ ጭካኔና ኃላፊነት በጎደለው ስሜት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ከፈሩት ነገር ለማምለጥ ዋስትና ከመሆን ይልቅ የፈሩትን ነገር የማምጣት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

ኢህአዴግ አሁን እያደረገ ያለው የእውር ድንብር ተግባሩ በራሱ ጊዜ የፈራውን ህዝባዊ አብዮት ከምን ጊዜውም በላቀ ሁኔታ እየጠራው ነው፡፡ ይሄም በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣አባላትና አመራሮች፣ በአክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ሳይሆን በራሱ በኢህአዴግ የከበረ ጥሪ እየተደረገለት ነው፡፡ በርግጥ ህዝባዊ አብዮት ድንገት የሚፈጠር ህዝባዊ አመፅ/እምቢተኝነት በመሆኑ አምባገነኖችን ድንገት ሳያስቡ ከስልጣን በማውረድ በበጎ ጎኑ ቢታይም የጦርነት ውጊያን ያህል ባይሆንም የሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ራሳቸው አምባገነኖች በሚፈጥሩት ቅጥ ያጣ ጭቆና የሚመጣ በመሆኑ በፀጋ ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡ እነደ ሌሎቹ ስልጡናን የመንግስት ስርዓት ከጦርነት ክህዝባዊ አብዮት ይልቅ በሰለጠነው ነፃና ፍትሃዊ በሆነ የህዝብ ምርጫ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን የዚህ ሁሉ ዕድል ከተዘጋ የታፈነ ህዝብ ነገ ባልታሰበ ጊዜ ህዝባዊ እምቢተኝነት ወይም አመፅ ውስጥ መግባት አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ተጠያቂ ደግሞ ራሱ ኢህአዴግና የበኩር ልጁ ምርጫ ቦርድ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡

nebe

አሁን አብዮቱን እየጠራ ያለው ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ልጁ ታማኝ ልጁ ምርጫ ቦርድ በመሆናቸው በሀገሪቱና በህዝቡ ላይ ለሚፈጠሩ ጥፋቶች ተጠያቂዎቹ ተቋማቱ ብቻ ሳይሆኑ የኢህአዴግ አመራሮችና የምርጫ ቦርድ ዋና አመራሮችና እንደ የደረጃቸው ሌሎች የቦርዱና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚዎች እንደየስራቸው ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይችሉ ከወዲሁ ራሳቸውን መመርመርና የዓለማችንና የህዝባንን ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ እንደ ከዚህ ቀደሙ በንፁሃን ደም ነግዶ መኖርና ማላገጥ፣ ሀገርና ትውልድ አጥፍቶ አመልጣለሁ ማለት የማይቻልበት ጊዜ ላይ መድረሳችንንም ሊረሳ አይገባም፡፡ ስለዚህ በሀገሪቱ ላይ እስካሁን ከፈፀሙት በደል በተጨማሪ አሁንም ለመፈፀም ለተዘጋጁ ጥፋቶች ምርጫ ቦርና ኢህአዴግ ከነተባባሪዎቻቸው መቼም ቢሆን ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ መረዳት አለባቸው፡፡ ምንክንያቱም እንደከዚህ ከቀደሙ በዝምታም ሆነ በፍራቻ የሚታለፍበት ጊዜ አልፏልና፡፡ ምናልባት ለመተንበይ አስቸጋሪ ቢሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ለውጡ የማይቀር እውነት ነው፡፡

መቼም በአሁን ጊዜ እንደቀድሞ በተጭበረረበር ምርጫና በካድሬ ውዳሴ ከንቱ ዳንኪራ ምርጫ አድርጌ አሸንፊያለሁ ማለት ለምርጫው የወጣውን ወጪ ከየትኛውም የኢኮኖሚ ኪሳራ በላቀ አጉልቶ ከማሳየት በስተቀር በስልጣን ለመቆየት ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ምርጫ አንዱ የዴሞክራሲያዊ የመነግስት ስርዓት ሽግግር መገለጫ እንጂ ብቸኛው ህዝብን የስልጣን ባለቤት ማድረጊያና አምባገነኖችን ከሚንደላቀቁበት ስልጣን ማስወገጃ መንገድ አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ባይኖሩ እንኳ በርካታ የሰላማዊ ትግል ስልቶች እንደየወቅቱ፣እንደየሀገሩና ህዝቡ የሚተገበሩ አሉና፡፡ ስለሆነም መጪውን ጊዜ ስለሀገራችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በተለይም የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሚደረገው ምርጫ ሂደትና ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ውጤት ከወዲሁ በጉጉት እንድንጠብቀው ግድ ብሎናል፡፡