የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ሹመት ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሱን እያወዛገበ ነው
- ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያርኩን ምደባዎች በደብዳቤ ተቃውመዋል
- ቋሚ ሲኖዶሱ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡትን አቤቱታ መመልከት ጀምሯል
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ ስኪያጅ መሾማቸውን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገለጸ፡፡ኹለቱ ሥራ አስኪያጆች ለሀገረ ስብከቱ መመደባቸው የተገለጸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በደብዳቤ በተሰጠ መመሪያ ነው፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ኃላፊዎችን የመምረጥና የመመደብ ጉዳይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መያያዙን፣ በዚህም መሠረት ሲሠራ እንደቆየ በመመሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለቱ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆች ምደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲያደርሷቸውና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአድራሻ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጧል፡፡
ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የሥራ አስኪያጆቹ ሹመት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዐዋዲው እና ከሀገሪቱ የሕግ አሠራር ውጭ መኾኑን በመግለጽ ምደባውን በትላንትናው ዕለት ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ የተቃወሙ ሲኾን፣ ፓትርያርኩ ከሕግ አግባብ ውጭ የሰጡትን መመሪያ እንደገና እንዲያጤኑት መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነታቸው ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እንጂ ለፓትርያርኩ ኾኖ እንደማያውቅና ሊኾንም እንደማይችል የገለጹት አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የፓትርያርኩ አካሔድና የሥራ አስኪያጆች ምርጫ “የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ያልተለመደና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ አሠራር በእጅጉ የሚፃረር ነው” ብለዋል፡፡ አቡነ ማትያስ የሰጡት መመሪያ ተቀባይነት የሚኖረውም ተሿሚዎቹ በሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመርጠው ከቀረቡ በኋላ ምርጫቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር የጋራ ስምምነት ተደርሶበት በፓትርያርኩ ሲሾሙ እንደኾነ በተቃውሟቸው አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በሰጡት መመሪያና በሥራ አስኪያጆች ምርጫዎቻቸው እንደማይስማሙና ምደባውንም ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ያስታወቁት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ “ይህ አሠራር ከትዝብት ላይ የሚጥል መኾኑን ተረድተውልን ለቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ አሠራርና ለኹላችንም ሰላም ሲባል ውሳኔዎን እንደገና እንዲያጤኑ በታላቅ አክብሮት አሳስባለኹ” ብለዋል – በተቃውሞ ደብዳቤአቸው፡፡
የፓትርያርኩን መመሪያ እንዲያስፈጽሙ በአቡነ ማትያስ መመሪያ የተሰጣቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ትላንት ከቀትር በፊት በተደረገው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ መመሪያውን በመቃወም አስተያየታቸውን በቃል ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩም አጀንዳው ውሳኔአቸውን የሰጡበት በመኾኑ መታየት የለበትም በሚል ቢቃወሙም ቋሚ ሲኖዶሱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቃውሟቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙ ተገልጧል፡፡ ከትላንት በስቲያ በድንገት ይፋ የኾነው የሀገረ ስብከቱ ተተኪ ሥራ አስኪያጆች ምደባ፥ ‹‹የመልካም አስተዳደር ሒደቱን ማቀላጠፍ›› በሚል ከኹሉ አቀፍ የትምህርት ዝግጅት፣ ከሥነ ምግባርና ከብሔር ተዋፅኦ መስፈርቶች አንጻር ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሳቸውን ላለፉት ሦስት ወራት ሲያወዛግብ መክረሙን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ
ትናንት ምሽት በቡራዩ ከተማ በደረሰ ከባድ የመኪና አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ
በቡራዩ ከተማ ልዩ ስሙ ቀርሳ በተባለው አካባቢ ትላንት የካቲት 9 ቀን 2007 ኣ.ም. ምሽት በደረሰ አሰቃቂ የመኪና አደጋ የ12 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
አደጋው የደረሰው ትላንት ምሽት 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ ሲሆን፥ ወደ አዲስ አበባ ይመጣ የነበረ ሲኖ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ከሚኒባስ ጋር በመጋጨቱ ነው።
በግጭቱ ሳቢያ የተነሳው ከባድ የእሳት አደጋም በመኪናው ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት እንደሆነ ቢነገርም፤ የአደጋውን ምክንያት በተመለከተ ይህ እስከ ተዘገበበት ድረስ ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከፖሊስ ምርመራ የተገኘ ማረጋገጫ የለም፡፡
በከተማ ባቡር መስመር ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ
ታምሩ ጽጌ
– ሰሞኑን ሁለት ተሽከርካሪዎች በመስመሩ ላይ ጉዳት አድርሰዋል
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ተጠቆመ፡፡
የቀላል የባቡር ፕሮጀክቱ የመጨረሻ ምዕራፍ የሙከራ አገልግሎት የተጀመረ ቢሆንም፣ ሰሞኑን በመስመሩ ላይ የተከሰቱ ሁለት አደጋዎች ፕሮጀክቱን በማከናወን ላይ ያሉትን ቻይናውያን ሳይቀር ሥጋት ላይ ጥለዋል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተሽከርካሪዎችና እግረኞች በምን ሁኔታ እንደሚስተናገዱ፣ በተለይ ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳት ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ መረቀቁንና ለውይይት ለሕዝብ ሊቀርብ መሆኑን፣ የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ አስረድተዋል፡፡
የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌሊቱን አንድ የግል ንብረት የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ከነጭነቱ ሳሪስ ኦይል ሊቢያ ዲፖ ፊት ለፊት ያለውን የባቡር ሐዲድ አጥር ጥሶ ገብቷል፡፡ ተሽከርካሪው ምንም እንኳን በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ባያስከትልም፣ እስካሁን በውል ያልታወቀ ኪሳራ ማድረሱ ታውቋል፡፡ አደጋ የደረሰበት የመስመሩ አጥር መልሶ ከተገጣጠመ በኋላ፣ ባቡር እንዲያልፍበት ተደርጎ ጥንካሬው ሲፈተሽ ችግር እንደሌለው መረጋገጡን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ ወጪውን በሚመለከት የኢንሹራንስ ግምት እየተጠበቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በተለይ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረው፣ ወደፊት ባቡሩ ሙሉ በሙሉ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት ምን ያህል የከፋ ነገር ሊገጥም እንደሚችል ጠቋሚ በመሆኑ ሕግ መውጣቱ ተገቢ መሆኑን፣ በፍጥነት ፀድቆ ወደ ተግባር መሄድ እንደሚገባ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱን እንዲለቅ ክስ ቀረበበት
• በወር 40 ሺህ ብር ኪራይና 250,000 ብር ለ‹‹ኪሳራ›› እንዲከፍል ተጠይቋል
ሰማያዊ ፓርቲ የካ ክ/ከተማ በቀድሞው መጠሪያው ቀበሌ 15 እንዲሁም በአዲሱ መጠሪያው ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 460 የሆነውን ጽ/ቤቱን 25000 ሺህ ብር ቅጣት ከፍሎ እንዲለቅ በአከራዮቹ በኩል ክስ ቀረበበት፡፡ በከሳሽ እነ አቶ ሚስጥረ ሽበሽ የተመሰረተው ክስ ‹‹ቤቱን ለቀው ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው …በወር ብር 40,000 (አርባ ሺህ ብር) ሒሳብ ከጥር 16 ቀን 2007 ጀምሮ ቤቱን ለቀው እስከሚያስረክቡ ድረስ ባልተነጣጠለ ኃላፊነት እንዲከፍሉን›› ያሉ ሲሆን ‹‹ከሳሽ ቤቱን ለማደስ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በገባነው ውል መሰረት የደረሰብንን 250 ሺህ ብር ኪሳራ እንዲተኩልን›› ሲሉ ከሰዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሚፈልግባቸው ጊዜያት የቀበሌ ካድሬዎች አከራዮቹና ደላሎቹ ለፓርቲው እንዳያከራዩ ሲያስጠነቅቁ የቆዩ ሲሆን በተለይ በጥር ወር 2007 ዓ.ም ይህ ጽ/ቤት እንዳይከራይ ግፊት የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ድብደባ ከተፈጸመባቸው ሁለት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የአንደኛው ሕይወቱ አለፈ
ታምሩ ጽጌ
–ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ሁለት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሠራተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው አንደኛው ሕይወቱ ማለፉ ተረጋገጠ፡፡
ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት ፈተናቸውን ካጠናቀቁት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል፣ ሙሉቀን ከበደና ታምራት አባተ የተባሉ ተማሪዎች በዕለቱ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናቸውን እንዳጠናቀቁ ከግቢ ወጥተው ሲዝናኑ ካመሹ በኋላ ወደ ማደሪያ ክፍላቸው ሲመለሱ፣ ፀደቀ አድማሱ ከሚባለው ተጠርጣሪ የጥበቃ ሠራተኛ ጋር መጋጨታቸውን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ሊገቡ ሲሉ ተጠርጣሪው እንዲቆሙ ሲያደርጋቸው ተማሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትን መታወቂያ ቢያሳዩም፣ ከተጠርጣሪው ጋር ሊግባቡ ባለመቻላቸው ድብድቡ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው በወቅቱ ይዞት በነበረው የእንጨት ዱላ ደጋግሞ ሲደበድባቸው የተመለከተ ሾፌር፣ ሌሎች የተኙ ጥበቃዎችን በማስነሳቱ የተፈጠረው ድብድብ የቆመ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ በደረሰባቸው ድብደባ ተጎድተው ስለነበር በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
ታምራት አባተ የተባለው ተማሪ በጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገለት ሕክምና የተረፈ ቢሆንም፣ የደረሰበት ድብደባ ከባድ በመሆኑ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር የተደረገው ተማሪ ሙሉቀን፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያለ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡ ፖሊስ በድብደባው ተሳትፈዋል በማለት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ የዩኒቨርሲቲውን የጥበቃ ሠራተኞችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ በምርምራ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡





