በአዲስ አበባ የኮሌራ በሽታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የውስጥ መልዕክት ልውውጦች አጋላጡ
(አዲስ ሚዲያ) በአዲስ አበባ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የአካባቢ ንፁህና ጉድለት ችግር ምክንያት ከተከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) የከተማዋ ነዋሪዎችን ጤና ማናጋት ከጀመረ ሶስተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል፡፡ በንፁህ የውሃ አቅርቦት እና በአካባቢ ንፁህና ጉድለት ምክንያት የሚከሰተው የኮሌራ በሽታ በከተማው መዛመት፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰራተኞችን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎችን ለከፋ በሽታ መዳረጉ ታውቋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በከተማዋ ለሚገኙ ለሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች ባሰራጨው የውስጥ መልዕክት መሰረት፤ ሰራተኞቹ የኮሌራ ክትባት እንዲወስዱ አሳስቧል፡፡ በተለይ ኮሌራ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት የሚዛመትና በንፁህና ጉድለት የሚከሰት በሽታ ሲሆን፤ ወዲያውኑ ተገቢውን ህክምና በጤና ተቋማት ማድረግ ካልተቻለ፤ በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የሰውነትን ፋሳሽ በመሳጣት ለሞት እንደሚዳርግ ይታወቃል፡፡
በሽታውን በተመለከተ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሀገር ቤት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ አተት የተከሰተው የወንዝ ውሃ በሚጠቀሙ ዜጎች ላይ እንደሆነ እና ለዚህም በወንዝ ዳር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የመፀዳጃ እና ፍሳሽ ማስወገጃዎቻቸውን ከወንዝ በማገናኘታቸው እንደሆነ በቃል አቀባዩ አህመድ ኢማኖ በኩል አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የንፁህ የመጠጥ ውሃ ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል ባለመደረጉ እና በከተማዋ በተከማቸው ቆሻሻ አማካኝነት እንደሆነ የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምንጮች ማረጋገጣቸው ተነግሯል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥራት ባልተጠበቀበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የከተማው ነዋሪ በመጪው 2009 ዓ.ም. ከዚህ ቀደም ከሚከፍለው የቧንቧ ውሃ ተጨማሪ ክፍያ ማሻሻያ ሊጣልበት እንደሆነም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃነት በ1 ቢሊዮን ወጪ በሰንዳፍ ተገንብቷል ቢባልም፤ ሰራ የተባለው ግንባታ ወጪ ከግንባተው ጋር አብሮ ሊድ እንዳይመችል የተጠቆመ ሲሆን፤ ይልቁንም በአካባቢው ያሉ የሰንዳፋ ነዋሪዎች ከአካባቢ ብክለት በሚመጡ በሽታዎች እንዲጋለጥ በማድረጉ፤ የአዲስ አበባ ቆሻሻ በከፍተኛ ወጪ ተሰራ በሚባለው ሰንዳፋ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ እንዳይደፋ ተቃውሞና እገዳ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ አስተዳደር ለደረቅ ቆሻሻ መጣያ ባለመኖሩ መፍትሄ ባለማበጀቱ ከዚህም በኋላ አዲስ አበባን ለውሃና አየር ወለድ በሽታ ሊያጋልጥ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ የከተማው መስተዳደር ከሰንዳፋ ነዋሪዎች ጋር ቀደም ሲል ያለምንም ድርድርና ምክክር አለመገንባቱ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የጥራት ችግር ያለበት በመሆኑ ነዋሪውን ለበሽታ በማጋለጡና ተቃውሞ በመቅረቡ አስተዳደሩ ሌላ መፍትሄ እስኪያዘጋጅ የአዲስ አበባ ቆሻሻ በየመንደሩ ባለበት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ ይህም ከወቅቱ የክረምት ዝናብ ጋር ተዳምሮ በቀላሉ ወደተለያዩ የከተማው ወንዞችና ጉዳት ወደደረሰባቸው የንፁሃ ውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች በመቀየጥ፤ አሁን ከተከሰተው የኮሌራ በሽታ በተጨማሪ ለተለያየ ውሃ ወደለድ በሽታ ሊያደርግ እንደሚችል የአስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ ከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ገለፃ ከሆነ፤ በከተማ እየሰሩ ባሉ መሰረተ ልማት እና የተለያዩ የግል ግንባታዎች ምክንያት በርካታ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች ከጥቅም ውጭ ሆነው ከከተማ ፍሳሽ ማስወገጃ ጋር በመገናኘታቸው እንደሆነ እና ችግሩንም በአጭር ጊዜ ለማስተካከል አስቸጋሪ እንደሆነ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ አስታውቀዋል፡፡ ስለሆነም፤ ችግሩ እስኪቀረፍ የከተማው ነዋሪ አቅሙ የፈቀደ ከከተማው የባንቧ ውሃ ከመጠቀም ተቆጥቦ ሌሎች አማራጮችን አሊያም ውሃን በደንብ አፍልቶ በማቀዝቀዝ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም፤ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ምልክት የታየባቸው ሰዎች በአስችኳይ በአቅራቢያቸው ወዳለ የህክምና ጣቢያ እንዲሄዱና ተገቢውን የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡
በተከሰው የኮሌራ ወረርሽን በሽታ በርካታ ህፃናትና እናቶች ሰለባ ሆነው በከተማዋ ባሉ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ተኝተው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በበሽታው ታመው የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው ከሚገኙ የከተማው ነዋሪዎች በስተቀር ህይወታቸው ያለፈ ስለመኖሩ እስካሁን የተገረጋገጠ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ መንግሥት በስታውን እና መንስዔውን ከመገናኛ ብዙኃን ለመደበቅ ቢሞክርም፤ ዓለም ተቋማት የሚሰሩትን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች የችግሩ ሰለባ በመሆናቸው በየ ህክምና ተቋሙ የሚሰጡ ውጤቶች ላይ ኮሌራ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ እንዳይወጣ ያደረገው ጥረት በህክምና ባለሙያዎች ሊጋለጥ ችሏል፡፡ መንግሥት ችግሩን ለመሸፋፈን ከመሞከርና ከማስተባበል ባለፈ እየወሰደ ስላለው የማስተካከያ ርምጃ በግልፅ ያለው ነገር የለም፡፡