ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ “ስለ ኦሮሞና አማራ ትክክለኛ የዘር ምንጭ” ያብራራሉ!!
ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ “ስለ ኦሮሞና አማራ ትክክለኛ የዘር ምንጭ” ያብራራሉ!!
• ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ የአንድ አባትና እናት ልጆች ነው
• አዳም የተፈጠረው ጎጃም፤ ኖህ መርከቡን ያሳረፈው አራራት ተራራ ላይ ነው
• ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አጥንቼ አለሁ ይላሉ …
ኑሮአቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ታዋቂው የሥነፅሁፍ ምሁር ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሣ፤ የፃፉት‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› የተሰኘ አዲስ አነጋጋሪ የታሪክ መፅሐፍ ዛሬ ለገበያ ይቀርባል፡፡ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ ማን እንደሆነ በጥናት ደርሼበታለሁ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ እስከ ዛሬ የተለያዩ የታሪክ ምሁራን ከተናገሩት ፍፁም የተለየና አዲስ የጥናት ውጤት ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ የሁለቱ ቋንቋዎች አመጣጥም በጥናቱ ተካቷል ብለዋል፡፡ በሊንከን ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የትምህርት ዘርፍ የሚያስተምሩት ፍቅሬ ቶሎሳ ፤ከዚህ ቀደም ‹‹Heaven to Eden›› እና ‹‹The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians›› የሚሉ መጽሐፍትን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሳተሙ ሲሆን ሁለቱም በኢንተርኔት
“አማዞን” በተባለ የመፅሃፍ ሽያጭ ድረገፅ ላይ ከተፈላጊ መፃህፍት ተርታ ተሰልፈዋል፡፡ በሙያቸው
ፀሃፌ-ተውኔትና የሥነ ፅሁፍ ምሁር ሲሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን
በማድረግም ይታወቃሉ፡፡
አንጋፋው ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በቅርቡ ለንባብ ባበቁት
“አዳፍኔ” የተሰኘ መፅሃፋቸው ላይ፤“የኦሮሞን ታሪክ ሙሉ አደርጎ ሊፅፍ የሚችለው ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ብቻ ነው” ሲሉ ለብቃታቸው ምስክርነትና ዕውቅና መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሣ በርካታ ቲያትሮችን ለደረክ ያበቁ ሲሆን ከእነዚህም መካከል “ጓደኛሞቹ”፣ “ፍቅር በአሜሪካ” እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በቅርቡም ‹‹ላሟ›› የተሰኘ ባለ ሁለት ገቢር ቲያትር ፅፈው ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሠሩ ለአጭር ጊዜ ዕረፍት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ ሲሆን ወደ አሜሪካ ከመመለሳቸው በፊት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በታሪክ ጥናቶቻቸው ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡
በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሳተሟቸው “Heaven to Eden” እና “The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians›› የሚሉት መፃህፍት በአለማቀፍ ደረጃ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙበት ሚስጥር ምንድነው? በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩሩት?
የመፅሐፍቱ ይዘት ነው ወሳኙ፡፡ ተቀባይነት ያገኙት በቋንቋ አጠቃቀም ለአንባቢያን ምቹ ስለሆኑ ይመስለኛል፡፡
በአይሁዶች ታሪክ ላይ የሚያተኩረው መፅሐፍ፤በጉዳዩ ላይ ከተጻፉ ሌሎች መጻህፍትና በተለምዶ ስለ አይሁዶች ከሚታወቀው ምን የተለየ ነገር ይዟል?
ብዙ ጊዜ ስለ አይሁዳውያን ሲወራ፣ቀዳማዊ ሚኒልክ የዛሬ 3ሺህ ዓመት፣ 40ሺህ አይሁዳውያንን ይዞ መጣ የሚለውን ነው የምናውቀው፡፡ ከመጡት መካከል 12ሺህ ያህሉ ንፁህ እስራኤላውያን ናቸው። 28ሺህ ያህሉ እነሱን በሥራ ያገለግሉ የነበሩ ኢያቡሳውያን የሚባሉ ነገዶች ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ሚኒልክ ለ12 ሺህዎቹ ልዩ ቦታ ሰጥቷቸው፣ በሀገሪቷ ላይ ካህናት አድርጎ ታቦት እያስቀረፀ፣ ኢትዮጵያ ላይ በዚህ መልክ ሾሟቸው ነበር፡፡ ኢያቡሳውያን ደግሞ ንጉሱን በእጅ ስራና በውትድርና ያገለግሉት ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ አይሁዳውያን ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ሁለተኛው ፍልሰት ነው፡፡
የመጀመሪያውና ብዙም የማይነገረው የአይሁዳውያን ፍልሰት፣ የእስራኤላውያኑ መሪ ሙሴ በህይወት እያለ አባ ብሄር የሚባል ልኡል ነበር። የሙሴ አማች ነው፡፡ አባ ብሄር የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሊሆን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣አይሁዳውያን ተከትለውት መጥተው ነበር፡፡ ምክንያቱም አባ ብሄር ያገባት ልጅ የሙሴ እህት ነበረች፡፡ ሙሴ በወቅቱ ለአባ ብሄር ፅላት ቀርፆ እንዲሁም ቀይ ባህርን የከፈለባትን በትር ሰጥቶት፣ወደ ሳባ ከተማ መጥቶ ነግሷል፡፡ በወቅቱ ብዙ አይሁዳውያንም ተከትለውት መጥተው ነበር፡፡
ሶስተኛው ፍልሰት የምንለው፣የኢራቁ ናቡከደነፆር አሸንፏቸው በሚያሳድዳቸው ጊዜ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ አይሁዳውያን ወገኖች አሉን” ብለው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ አይሁዳውያን በነዚህ መንገዶች ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡
ትክክለኛዎቹ አይሁዳውያን በኢትዮጵያ ያሉት ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ…?
የሃይማኖታቸውን ስርአት፣ መፅሃፍትና ህግጋት ከመጠበቃቸው አንፃር ከሌላ ህዝብ ጋር ስላልተደባለቁ ትክክለኛው ያለው እነሱ ጋ ነው፡፡ ሌሎቹ ወደ አውሮፓ፣ እስያ፣ አሜሪካ የተሰደዱት እነዚህን ነገሮች በተለያዩ ጫናዎች የተነሳ ሙሉ ለሙሉ ጠብቀው አላቆዩትም፡፡ ወደዚህ የመጡት ግን በግድ ባህላችሁን ሃይማኖታችሁን ለውጡ ተብለው በኢትዮጵያውያን አልተረበሹም፤ነፃነት ነበራቸው፡፡ መሬትና ሁሉ ነገር የተመቻቸላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ ሌላ አገር ላይ ቦታ እንዳይኖራቸው ተደርገው በየጊዜው ይሰደዱ ነበር፡፡ እንደውም በሩሲያ ውስጥ በድንገት አይሁዳውያንን የመግደል ድርጊት ይፈፀም ነበር። ሩሲያውያኑ ተሰባስበው፤“ዛሬ አይሁዳውያንን ገድለን እንምጣ” እያሉ ይዘምቱባቸው ነበር፡፡ ወደ መንደራቸው ሄደው አውድመዋቸው ይመለሳሉ፡፡ ማንም ስለማይበቀልላቸው ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ ነበር የሚቀረው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከተሰጣቸው ክብር የተነሳ በትንንሽ ንጉስነት ጭምር ይሾሙ ነበር፡፡ በርካቶቹም ካህናትና ሊቀ-ካህናት ተደርገው ለአይሁድ እምነት ተሹመል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የሰለሞን ዘር ነን በሚሉት ውስጥም ገብተው፣ ስርወ መንግስት እስከ መመስረት የደረሱ ነበሩ፡፡ በዓለም ላይ አይሁዳውያን ደልቷቸው የኖሩት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ነው፡፡ በጠቅላላው በኢትዮጵያ ሀገራት ማለትም፡- በግብፅ፣ የመን፣ ኑቢያ—ኢትዮጵያ ባስተዳደረቻቸው አካባቢዎች በሙሉ በክብር ተይዘው ነው የኖሩት፡፡ ትልቁ ማስረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ፣ እናቱ ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ በስደቱ ዘመኑ እኛ ጋ ብቻ ነው ጥገኝነት ያገኙት። በወቅቱ ግብፅ ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ አንዱ ክፍል በሮማውያን ቁጥጥር ስር ነበር፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ክፍል ነው፡፡ ኢየሱስ ከመወለዱ ከ880 ዓመት በፊት አማራዎች፤ አማሩላ ደልታ ወደሚባል ቦታ ሄደው፣ አክሱማይት የተባለውን ህፃን ልጅ ዙፋን በመጠበቅ ያገለግሉ ነበር፡፡ በኋላ በ800 ዓመታት ውስጥ አማሩላ ደልታ የሚባል መንደር መስርተው ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋርና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ሲሸሹ፣ እዚያ ነው ማረፊያ ያገኙት፡፡ ይሄ መፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፤እኛ ግን ከተለያዩ መዛግብት እናገኘዋለን፡፡ በወቅቱ የአካባቢው ንጉስ አማናቱ ተትናይ ይባላሉ፡፡ ከጎጃም ከጣና አካባቢ ነው ወደዚያ የሄደው፡፡ ሌላው አይሁዳውያኑ መፅሐፍ ቅዱሳቸው ሲጠፋባቸው ከኛ ነው የወሰዱት፡፡ አፄ ደንቀዝ የተባለው ንጉሰ ነገስት ነው ከግዕዝ ወደ እብራይስጥ አስተርጉሞ የሰጣቸው፡፡
ትክክለኛውን የአይሁድ ባህልና እምነት በመጠበቅ በኢትዮጵያ ያሉት አይሁዳውያን ብቸኞቹ ናቸው ማለት ይቻላል?
አዎ! ኦሪትን ይዘዋል፡፡ ግን በደማቸው ከኛ ተደባልቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሃበሻ የተባሉት። ሃበሻ ማለት የተደባለቀ ነው፡፡ “አበሳ” ያለበት ወይም እንከን ያለበት ማለት ነው፤ ሃበሻ ማለት፡፡ በቀዳማዊ ሚኒልክ ጊዜ የመጡት ከኛ ጋር ተደባልቀው 560 ዓመት ከቆዩ በኋላ በባቢሎን ስደት ጊዜ ሶስተኛዎቹ ሲመጡ፣ነባሮችን ሲያዩአቸው በመልካቸው አይሁዳውያንን አልመስል አሏቸው። ስለዚህ፤“እናንተማ ክልስ ናችሁ፤አበሳ አለባችሁ” ብለው ይሰድቧቸዋል፡፡ ነባሮቹ አይሁዶች ደግሞ፤ “እናንተ ፈላሾች፤እኛ ሀገር አለን” እያሉ ይሰድቧቸው ነበር፡፡ በዚህም “አበሻ” እና “ፈላሻ” የሚለው መጠሪያቸው ሆነ፡፡ “ሀበሻ” የሚለው ቃል እኛን አይወክለንም የምለው ለዚህ ነው፤ሀበሻ አይሁዳውያኑን ነው የሚወክለው፡፡ እኛ የኢትዮጰያ ልጆች ነን፤ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡
“በሃበሻነቴ እኮራለሁ” ስንል የከረምነውስ—–ቀለጠ ማለት ነው?
አዎ! እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሀበሻ አይደለሁም። ሀበሻ የሚለው ቃል የስድብ ቃል ነው፡፡ እኛን አይወክለንም፡፡ አይሁዳዊ ካልሆነ በስተቀር አንድ ሰው ራሱን “ሀበሻ ነኝ” ብሎ ሊጠራ አይገባውም። ስድብ አያኮራም፡፡ ብዙ ሰው ስለማያውቅ ነው በሀበሻነቴ እኮራለሁ የሚለው፡፡ በአረብኛም ብናየው “የተደባለቀ”፤ “ንፁህ ያልሆነ” ማለት ነው። ይሄ መልካም ቃል አይደለም፡፡ ግን ሀበሻ የሚለው “አበሳ” ከሚለው እንጂ ከአረብኛ የመጣ አይደለም። ሁለቱ አይሁዳውያን መሃል ያለ የመሰዳደቢያ ቃል ነው እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያንን አይመለከተንም፡፡
‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውስ ከየት የመጣ ነው?
ኢትዮጵያ የሚለው ‹‹ኢትዮጵ›› ከተባለው ሰው የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵ ማን ነው ካልን፣ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው መልከፀዴቅ የሚባል የሳሌም ንጉሰ ነገስትና ሊቀካህን ነበር፡፡ ይህ ሰው ሃገር ያስተዳድራልም፤ሃይማኖትም ይመራል፡፡ እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር፡፡ ይሄ እንዴት ይሆናል ከተባለ፣ኢየሱስ በምፅአት ቀን ሲመጣ፣ የንጉስ ንጉስ፣ የካህን ካህን ሆኖ ነው፤መልከፀዴቅም የዚህ ምሳሌ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከዚሁ ጋር ምን ያገናኛታል ሊባል ይችላል፡፡ በጣም የሚያኮራ ግንኙነት አለው፡፡ የመልከፀድቅ ልጅ ኢትኤል ይባል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ኢትኤልን ካለህበት የሳሌም ምድር ለቀህ ጣና ላይ ስፈር አለው፡፡ ‹‹ከዚያም ያንተ የልጅ ልጆች፣ እኔ ከ2000 አመታት በኋላ በምወለድበት ጊዜ በኢትዮጵያ ግዛት ላይ ስለ መወለዴ ኮከብ አሳይሃለሁ” ይለዋል (እንደኔ ምርምር፤ይሄ ኮከብ የተባለው መልአኩ ገብርኤል ነው) በዚህ ሁኔታ ኢትኤል አሁን ወዳለችው ኢትዮጵያ ሲደርስ እግዚአብሔር፤‹‹ኢትዮጵ›› ተብለህ ተጠራ አለው፡፡ ‹‹ኢት›› – ስጦታ ማለት ነው፡፡ ‹‹ዮጵ” – ማለት ደግሞ ቢጫ ወርቅ ነው፡፡ ስለዚህ “ቢጫ ወርቅ ስጦታ” ተባለ፡፡ በኋላ ሃገሪቷን ኢትዮጵያ አሠኛት፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠቀሰው ስም የትኛዋን ኢትዮጵያ ነው የሚወክለው?
እሱ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን ነው የሚወክለው፡፡ ግን ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ እስከ 13ኛው ክ/ዘመን ድረስ ለመላዋ አፍሪካ መጠሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በኋላም የመጣው አፍሪካ የሚለው ስም ከዚሁ ከኢትዮጵያ የተገኘ ነው፡፡ ከአፋሮች ነው አፍሪካ መጠሪያዋን ያገኘችው፡፡ በመፅሃፈ እዝራ ምዕራፍ ስድስት ላይ፤‹‹አፍሪካንሳውያን›› ይላል፡፡ ይሄ አፋሮችን ነው የሚወክለው፡፡ በመርከብ ስራ በቀይ ባህር ላይ የተራቀቁ ሰዎች ነበሩ፡፡ የዛሬ 3ሺህ አመት ንጉስ ሰለሞን ቤተመቅደሱን ሲሰራ፤ልዩ እንጨት፣ እጣን፣ ወርቅ (ኦፊር የተባለ ታዋቂ ወርቅ- በነሱ የተሰየመ) ጭምር ይነግዱና ለንጉሡ ያቀርቡ ስለነበር፣ስማቸው የገነነ ሆኖ አፍሪካንሳውያን የተባሉት፡፡ በሳይንሱም አፋር የሰው ዘር መገኛ እያልን ነው፡፡ ኢስያውያንም ስያሜያቸውን ያገኙት ከሣባ ቀድሞ ከነገሰው ‹‹ኢስአኤል›› ከተባለው ንጉስ ነው፡፡ ምድሪቱን ያስተዳድር ስለነበር ኢስያ ተባለች፡፡ ‹‹አፄ” የሚለውም ከዚህ የመጣ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለውስ —?
ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለው ውሸት ነው፡፡ ይሄን አጣርቻለሁ፡፡ በነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ይሄ ቃል የለም፡፡ ‹‹ፊቱ የተቃጠለ›› የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሳይሆን ሌላ ትርጉም ነው የሚኖረው፡፡ ግሪኮቹ ከኛው ሰምተው ነው መልሠው ኢትዮጵያ ያሉን፡፡ እኛ ከነሱ በፊት ነበርን እንጂ እነሱ ከኛ በፊት አልነበሩም፤ ስማችንን ሊያወጡልን አይችሉም፡፡
በምርምርዎ አዳምና ሄዋን የተፈጠሩበት ቦታ የት ሆኖ አገኙት?
ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ጎጃም፤ ዳሞትና ጣና አካባቢ ያለ ቦታ ነው፡፡
ለዚህ ድምዳሜ ማስረጃዎ ምንድን ነው?
አንደኛ ኤደንን ከሚያጠጡ አራት ወንዞች ውስጥ አባይ የምንለው ነው ኤፌሶን የሚባለው። በኦፌር ወርቅ ዙሪያ የሚዞር መሆኑ ተፅፏል፡፡ በኔ ድምዳሜ፣የኤፌሶን ወንዝ የአሁኑ ዋቢ ሸበሌ ነው። ጤግሮስና ኤፈራጥስ ደግሞ ጊዮን ራሱ ጥንት ሜዲትራኒያን ባህር ይገባ ነበር፡፡ ድሮ ሜድትራኒያን “ኪቲ” ይባል ነበር፡፡ ጥንት ጊዮን ወንዝ ሜድትራኒያን ሲደርስ ተራራ ስለነበር ተጋጭቶ ይመለስ ነበር፡፡ ከዚያ ነው መሬት ተነቃንቆ፣ቦታው ተቆራርጦ አሁን ወዳለበት ኢራቅ የሄደው እንጂ አካባቢው እዚሁ ነበር፡፡
አዳም የት ተፈጠረ ለሚለው በመፅሃፈ ሄኖክ ላይ “ኤልዳ” በሚባል ቦታ ተፈጠረ ይላል፡፡ ኤልዳ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም አስሌዳውያን ወይም ኤልዳውያን የሚባሉ አሁንም ድረስ ጎጃም ውስጥ አሉ፡፡ ሄኖክ በመፅሃፉ ኤልዳ ነው የተፈጠረው ይላል፡፡ ከዚያ ወስዶ ነው እግዚአብሄር በ40 ቀኑ ወደ ኤደን ገነት የከተተው ይላል፡፡ ሄዋንን ደግሞ ከአዳም ጎን አውጥቷት ነው በ80 ቀኗ ወደ ኤደን ገነት የከተታት፡፡ ከዚህ ተነስቶ ነው ወንድ በ40፣ ሴት በ80 ቀን ክርስትና የሚነሱት። ይሄ አይነቱ ስርአት በዓለም ላይ የትም የለም፤እና ይሄ በሄኖክ መፅሃፍ የተፃፈውና አሁን ያለው እውነታ ይገኛል፡፡
ሌላው ኮሬብ የሚባል ዋሻ ውስጥ አዳም ተቀበረ ይላል፡፡ በእርግጥ በሲናይ በረሃ አካባቢ ኮሬብ የሚባል ቦታ አለ፤ ግን በተመሳሳይ ይህ ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥም አለ፡፡ ሌላው ኖህ መርከቡን ያሳረፈው አራራት ተራራ ላይ ነው ይላል፡፡ አራራት ተራራን ለመፈለግ ወደ ቦታው ሄጄ ነበር፤ በታንኳ ጣናን አቋርጬ፡፡ አራራት ተራራ የሚባለውን ሳገኘውና አቀማመጡን ሳጠናው፣ ለመርከብ ማሳረፊያነት በአናቱ ላይ ምቹ ሜዳ አለው፡፡ ኖህ ወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር ይላል፤መፅሃፍ ቅዱስ፡፡ በእርግጥም ቦታው የወይን ጠጅ ፍሬ ለማብቀል ተስማሚ ነው፡፡ አሁንም አትክልቶችና ጌሾ ይበቅልበታል፡፡ ከዚሁ ማስረጃ ሳልወጣ፣አዲስ አመትን አበቦች አብበው አከበረ፤የእንጨት መስዋዕትም አደረገ ይላል፡፡ ይሄ እንግዲህ ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ ያለው የአዲስ ዓመት መቀበያ ስርአት፣ ከየት መጣነትን ሊያስረዳ ይችላል። በኋላ ወደ ክርስትናው የመስቀል በዓል ደመራነት ተለወጠ እንጂ በፊት ደመራ የሚነደው በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው አሁንም ድረስ ክርስቲያን ያልሆኑ የሀገራችን ሰዎች የደመራ ስርአት አላቸው። ይሄ የአባታቸው የኖህ ትዝታ (ማስታወሻ) ነው ሲወረስ ሲዋረስ የመጣው፡፡ በዚህና በኖህ ጉዳይ ሰፊ ጥናት እያደረግሁ ነው፤ወደፊት ይፋ ይሆናል፡፡ አንድ እዚህ ላይ ልጠቅሰው የምፈልገው፣ሌላ አራራት የሚባል ተራራ አርመን ውስጥ አለ፡፡ ተራራው ግን በረዶ ያለበት፣ ገደላገደል፣ እንኳን መርከብ ሊያሳርፍ ለሰው ልጅ የማይመችና የማያብብ ቦታ ነው፤ ስለዚህ ያ ሊሆን አይችልም፡፡
በሰንደቅ አላማው ላይም የተለየ መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ስጦታ ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ሰንደቅ አላማው ለኖህ ከተሰጠው ምልክት የመጣ ነው፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የጎሉበት ቀለማት ሰማይ ላይ ታይተዋል፡፡ እነዚያ ቀለማት ናቸው ዛሬ ያሉት፡፡ ከንግስት ሳባ በፊት የነገሰው አፄ ኢሲአኤል ነው ሰንደቅ አላማ እንዲውለበለብ ያደረገው፡፡ ሰንደቅ አላማ የሚለው የመጣው የኢስአኤል መንግስት “ሰንደቅ አለማ” ከሚለው ነው፡፡ ከዚያ የመጣ ነው። እሱ በወቅቱ የመረጠው፡- አረንጓዴ ቢጫ፣ቀይና ሰማያዊ ቀለማት ነበር፡፡ ለሰንደቅ አላማው ያልተገዛና ያላውለበለበ ይቀጣል ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ አስገዳጅ ህግ ያወጣውም እሱ ነበር፡፡ በሰንደቋ አናት ላይ ኮከብ ነበር የሚቀመጠው፡፡ ኢየሱስ ሲወለድ የሚጠቁመውን ኮከብ ለማስታወስ ይጠቀም ነበር፡፡ በዓለም ላይ ሰንደቅ አላማን የፈለሰፈ የመጀመሪያው ሰውም ሊሆን ይችላል፡፡
የኢትዮጵ የልጅ ልጅ የሆነው ኢስአኤል ከፈለሰፈው ሰንደቅ አላማ ነው፣ዛሬ ያሉት የሰንደቅ አላማ ቀለማት የመጡት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰንደቅ አላማው ላይ ከዚህ ተነስቶ አንድ አይነት አቋም ቢይዝ መልካም ነው፡፡ ኢስአኤል ለኦሮሞውም፣ ለአማራውም፣ ለትግሬውም፣ለአፋሩም ለሌላውም ብሄረሰብ ሁሉ አባት ነው፡፡ ከአባቶቻችን የወረደ ሰንደቅ አላማ እንጂ ከባዕድ የመጣ አይደለም፡፡
ሰውየው እጅግ ጠቢብ ነበር፤ልእለ ሰብዕ (superman) ነበር፡፡ 150 አንበሳ መግደሉን ለማስታወስ ጭምር አፄ ኢስአኤል የሰብዕ እና የአውሬዎች ንጉሰ ነገስት ብሎ ነበር ራሱን የሚጠራው፡፡ ሰውየው እጅግ ጠቢብ ከመሆኑ የተነሳ የጀነቲክ ኢንጅነሪንግን የፈለሰፈውም እሱ ነው፡፡ እንስሳን ከእንስሳ፣ ዘርን ከዘር እየቀላቀለ የፈለሰፈ የመጀመሪያው የጀነቲክ ኢንጅነር ነበር። በቅሎን የፈጠረውም እሱ ነው፡፡ አህያንና ፈረስን አዳቅሎ፡፡ ይህ ሰው የሁሉም ኢትዮጵያውን አባት ነው፡፡ የኢትዮጵ ልጅ ነው፡፡ የኢትዮጵ 10 ወንዶች ልጆች ናቸው፤ አሁን የምናያቸውን የኢትዮጵያውያን ጎሳዎች ሁሉ የፈጠሩት፡፡
ሰሞኑን ለአንባቢያን የሚቀርብ መፅሃፍ እንዳዘጋጁም ሰምቼአለሁ፡፡ የመፅሐፉን ይዘት በአጭሩ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
መፅሐፉ፤“የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የሚል ነው፡፡ አሁን ያሉት ኢትዮጵያውያን በሞላ የኢትዮጵ ልጆች መሆናቸውን ከላይ አስረድቻለሁ፡፡
አሁን እንደምናው በሁላችንም ላይ የማንነት ቀውስ አለ፡፡ የማንነት ቀውሱ የመጣውም እኛ ማን እንደሆንን በትክክል ባለማወቃችን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ መፅሐፍ እኛ ማን እንደሆንን፣በርካታ ታሪካዊ ማስረጃዎችና ሰነዶችን አስደግፎ፣ግልጥልጥ አድርጎ ያስረዳናል፡፡ ይህ የማንነት ቀውሳችን ከተስተካከለና ራሳችንን ካወቅን፣ በመካከላችን ግጭቶች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ መፅሐፉ፤ፍቅር፣ ሰላምና ህብር ሊፈጥር ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ የትልቅ ሰው ዘር ነን የሚለውን በማስረጃ የሚያሳየን ነው፡፡ የሰው ዘር ምንጭ ናሙናዎች መሆናችን ይተነትናል፡፡ ማንነታችንን በትክክል ተረድተን፣ አንድ ላይ ለመጓዝ ያስችለናል ብዬ አስባለሁ – ይህ ብዙ የተደከመበት የምርምር ውጤት፡፡
የኦሮሞና የአማራ የዘር ሀረግ አንድ ነው የሚለውን ነው መፅሃፉ የሚያስረዳው?
አማራና ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በኢትዮጵያ ግዛት ያለው ብሄር፣ ጎሳ ከ10ሩ የኢትዮጵ ልጆች ነው የመጣው፡፡ ዝቅ ሲል ደግሞ የኢትዮጵ የልጅ ልጅ የሆነ፣ ጎጃም ላይ አዳምና ሄዋን ተፈጥረዋል ብዬ ባልኩት አካባቢ አንድ ጠቢብ ሰው ነበር፡፡ “ደሴት” ወይም “ደሸት” ይባላል፡፡ እሱ ነው የኦሮሞና የአማራ አባት፡፡ የዛሬ 3600 ዓመት 4 ወንዶች ልጆች ወለደ፡- መንዲ፣ መደባይ፣ ማጂ፣ ጅማ የሚባሉ፡፡ እነዚህ 4ቱም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገር መጠሪያ ሆነዋል። ማጂ ደግሞ ማራ እና ጀማን ይወልዳል። ዛሬ አማራ የምንለው ማራ ነው፡፡ “ማራ” ማለት “እውነተኛ ብርሃን” ማለት ነው፡፡ አማራ ያሉት አጋዚያን ወይም የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ማጂ ማራን ወለደ ካልን፤ ጀማ እና ማራ ወንድማማቾ ናቸው፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች በአካባቢው ካሉት ጋፋቶች ጋር መዋጋት ሰልችቷቸው፣ ሃገር ለቀው ወደ ሸዋ ሲመጡ አንድ ወንዝ ያገኛሉ፡፡ ወንዙን ጀማ አሉት። አሁን የጀማ ወይም የ“ዠማ” ወንዝ ማለት ነው። ከአካባቢው እየራቁ ሲሄዱ የጥንት አባቶቻቸውን ቋንቋ “ሱባ”ን ትተዉ አማርኛን መፈልሰፍ ጀመሩ፡፡ መደባይ፣ ጅማና መንዲ ደግሞ ግማሾቹ ጎጃም ላይ ቀሩ፤ ግማሾቹ ወለጋ ሄዱ፤ሌሎቹም እየራቁ በምስራቅ አፍሪካ ተሰራጩ፡፡ ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚባለውንም ፈጠሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ዛሬ ያሉት ኦሮሞና አማራ የመጡት፡፡ ዘረ ደሸት ይባላሉ፡፡ የደሸት ልጆች ናቸው። የዘር ሀረጋቸው አንድ ነው፡፡ ቋንቋቸው የተለያየ የሆነው በሂደት ነው፡፡
ኦሮሞው የኩሽቲክ፣ አማራው የሰሜቲክ ዘር ናቸው፤ የመጡትም ከውጭ ነው የሚለው ለዘመናት የዘለቀ ታሪክስ …?
እሱ ፈፅሞ ውሸት ነው፡፡ ሁለቱም ከውጭ አልመጡም፡፡ እንዳስረዳሁት እዚሁ የበቀሉ ናቸው። የአማራም የኦሮሞም አባት ደሸትም ሆነ ታላቁ አባት ኢትዮጵ ኩሽ ነው፡፡ መልከፀዴቅም ኩሽ ነው። ኦሮሞና አማራ ሁለቱም ኩሽ ናቸው፡፡ አማራ ሴም አይደለም፤ ኩሽ ነው፡፡
እስከ ዛሬ ሲነገር የነበረው ውሸት ነው። ምናልባት የአማርኛ ቋንቋ ከሌሎች ጋር ሲደበላለቅ ሴሜቲክ ቤተሰብ ውስጥ ተገኝቶ ሊሆን ይችላል። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የኩሽ ዘሮች ናቸው። በዚሁ መፅሐፌ ላይ ስለ ቋንቋም አስረድቻለሁ፡፡ በእብራይስጥም ሆነ በአረቢክ የሌሉ እንደ ጨ፣ቀ፣ፀ ያሉ ድምጾች በአማርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋ ውስጥ አሉ። ይሄን በዝርዝር በመፅሐፉ አስቀምጫለሁ፡፡
ኦሮሞና አማራ አንድ ነው የሚለው አመለካከት በተለይ በኦሮሞ ምሁራን ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም፡፡ በግድ ኦሮሞን አማራ ለማድረግ ነው በሚል ወቀሳ የሚሰነዝሩ አሉ …
እንዲህ የሚሉት ሁሉም ከኢትዮጵ ዘር የመጣው የደሸት ልጆች መሆናቸውን ባለማወቃቸው ነው። ይሄ መረጃ ስለሌላቸው ራሳቸውን እንደ ባዕድ አግልለው ስለሚያዩ ነው እንጂ አሁን ይሄ እኔ ያቀረብኩትን ማስረጃ በቅን ልቦና አገናዝበው ለመረዳት ከሞከሩ፣ የትልቁ ሰው የኢትዮጵ፣ የጠቢቡና የሊቀካህናቱ የደሸት ልጅ እንደሆኑ በሚያውቁ ጊዜ፣ እነሱ እንደተሳሳቱ ተገንዝበው ወደ ማንነታቸው ላይ አተኩረው ይኮሩበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ የመጣነው ከትልቅ ዘር ነው፡፡ ኦሮሞውም አማራውም የመጣው ከዚህ ትልቅ ሰው ነው፡፡ በዚህ ሁላችንም ልንኮራ ይገባናል፡፡
የአሁኗ እና የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ልዩነታቸውና አንድነታቸው ምንድን ነው?
በግዛት ከሄድን ጥንት መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ነው የሚባለው፡፡ ከየመን አልፎ ሁሉ ይሄዳል፡፡ ግብፅ ውስጥ ፈርኦኖች የሚባሉት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአባይ ላይ ከመርከብ ወርደው ሜዳ አግኝተው የሰፈሩበት ቦታ ነው፤ ግብፅ፡፡ የአፍሪካ ሁሉ ነገር ከኛ አይወጣም፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ የ3ሺህ ዘመን ነው ይባላል፡፡ እርሶ የደረሱበት የጥናት ውጤት ምን ይላል?-
አዎ፤ በተለምዶ 3ሺህ አመት ይባላል እንጂ ከ7ሺ በላይ ነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፡፡ ኖህ ኢትዮጵያ ላይ ነግሷል፤ ከዚያ ጀምሮ 7ሺህ አመት ነው፡፡
እስካሁን በነገሩን ታሪክ ውስጥ መፅሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው በማስረጃነት የሚጠቅሱት፡፡ መፅሐፍ ቅዱስን ብቻ የታሪክ ምንጭ ማድረግ ይቻላል?
መፅሐፍ ቅዱስ ብቻ አይደለም፡፡ 42 ሰነዶችን አሁን በሚወጣው መፅሐፌ ላይ በግልፅ አስቀምጫለሁ። እነዚህ ሰነዶች በተለያዩ ሰዎች በጥንት ጊዜ የተፃፉ ናቸው፡፡ ኑቢያ ውስጥ ጀበል ኑባ በተባለ ቦታ ተቀብረው የቀሩ፣በጥንት ፍርስራሽ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን (ከእስልምና በፊት የነበረ) ድንጋይ ሳጥን ውስጥ ተቀብረው የነበሩ የብራና ሰነዶች አግኝቻለሁ፡፡ በዚያ ላይም የተመሰረተ ነው። ከመፅሐፍ ቅዱስ ውጪ 42 ተጨማሪ የታሪክ ሰነዶችን ተጠቅሜያለሁ፤ይሄን መፅሐፍ ሳዘጋጅ፡፡
ቀጣይዋ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት ይላሉ?
አሁን ማንነታችንን አውቀን፣ የማንነት ቀውሳችንን ፈትተን፣ሁላችንም የኢትዮጵያ ዘር፣ የአንድ አባትና እናት ልጆች—–መሆናችንን ተገንዝበን፤ በፍቅር፣ በሰላም፣ በመከባበር፣ በእኩልነት መኖር አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁላችንንም ኢትዮጵ ያገናኘናል፡፡
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ
ለሱዳን ሊሰጥ ነው ስለተባለው መሬት
(ምክር-ለበስ አስተያ)
ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ (ፒ ኤች ዲ)
(የሁማኒቲስ ፕሮፌሰር)
መንግሥት ለሱዳን ሊሰጣቸው ነው የተባሉት አሁን በጎንደር አና በቤንሻንጉል አካባቢ የሜገኙት የእነ ኦሜድላና ጋምቤላ መሬቶች በአውነት የማን ናቸው? ያለጥርጥር የኢትዮጵያ ናቸው። ለምን እንደዚህ እንዳልኩ ዝቅ ብዬ አስረዳለሁ። መሬቶቹ በታሪክ የሱዳን ነበሩና ለሱዳን ይሰጡ የሚሉት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መሬቶቹን ለሱዳን ለመስጠት የሚያቀርቡት ምክንያት “በ በሱዳን የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ጊዜ የእንግሊዝ መንግሥት ተወካይ የሆነ አንድ ሻለቃ የወሰን ምልክቱን የተከለው እዛ አካባቢ ነው፤ቀድሞ አፄ ምንይልክ በዚህ ተስማምተው፥ በሁዋላ ደግሞ አፄ ኅይለሥላሴ እና ደርግም ይህን አፅድቀውታል፤” የሚል ነው። በሌላ አነጋገር፥ በታሪካዊ ምክንያት ነው። እዚህ ላይ አንድ አስቂኝ ታሪክ ታወሰኝ። አንድ እንግሊዛዊ ከሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ የዱር እንስሳና አውሬ ለማደን በሚል ፈሊጥ ሲዘዋወር ለስለላ ነው ብለው በጠረጠሩት የሃገሬው ተወላጆች ተገሎ እዛው ተቀበረ። ታዲያ ይህን ሰበብ አድርጎ አንድ እንግሊዛዊ መኮንን (ምናልባትም እላይ የተጠቀስው እብድ ሻለቃ) ያ አካባቢ በሞላ ለእንግሊዝ መንግሥት ሊሰጥ ይገባል፤አለ። በምን ሂሳብ ተብሎ በአባ መላ (ፊታውራሪሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ) ተጠየቀ። አንድ የእንግሊዝ ዜጋ ሞቶ እዚህ ስለተቀበረ፤ሲል መለሰ። አባ መላም ከትከት ብለው ስቀው፥እሺ ደግ ነው፤አንድ የእንግሊዝ ዜጋ ሞቶ እዚህ ስለተቀበረ ይሄን ሁሉ መሬት ለናንተ እንሰጣችሁአለን። የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ለንደን ውስጥ ሞቶ እዛው ለንደን (ዌስትሚኒስትር አቢ) ስለተቀበረ እኛ ደግሞ ለንደንን እንረከባችሁአለን። በዚህ ከተስማማህ ውል መፈራረም እንችላለን፤ብለው አሾፉበት። ከዛ ቦታ በቅፅበት ዳብዛው ጠፋ።
ስለታሪክ ካወሳን ዘንድ፥ ይሄ ዛሬ ሱዳን የተባለው ምድር ሁሉ ቢያንስ ለ 4000 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ግዛት ነበር።ጥንት የሚታወቀው ኑብያ ተብሎ ነበር። ኖባ በተሰኘው የኩሽ ዘር ስም።መናገሻውም መርዌ ነበር። የዛሬ 2900 ዓመት ግን ሱዳን ይባል ጀመር። ይህ ስም የወረደው ከአፄ አክሱማይት እናት ከንግሥት ሳዶንያ ነው። እሱ በህፃንነቱ የግብፅ ፈርኦን ሆኖ እስከሚያድግ ድረስ እስዋ በ 350,000 የአማራ ሰራዊት ታጅባ ዙፋኑን እየጠበቀች በሱ ስም ግብፅን፥ ሊብያን እና የዛሬውን ሱዳን ታስተዳድር ነበር። በዚህ ምክንያት፥ ከሳሃራ በርሃ በታች የአለው ምድር በሞላ ሳዶንያ ተባለ። ቀስ በቀስ ደግሞ ሱዳን። እንዳውም ኑብያ ውስጥ የነበረው መርዌ ለዛ አካባቢ እንደ ዋና ከተማ ሆኖ ያገለግል ነበር። ቢያንስ 14 የኢትዮጵያ ሴቶች ህንደኬ በሚል ማእረግ በንግሥትነት በተከታታይ ዛሬ ሱዳን፤ ግብፅና ሊብያ የሚባሉትን ሃገሮች ለ 1000 ዐመት ያህል ገዝተዋል። ለመጨረሻ ጊዜ የኑብያ ንጉሥ የነበሩት በ 16ኛው ክፍለ ዘመን የኖሩት አፄ ፋሲል ነበሩ። ከኑብያ ብቻ ሳይሆን ከስናር (ከካርቱምብዙያልራቀ ስፍራ) ድረስ የወርቅ ግብር ይመጣላቸው ስለነበር አዝማሪ አንዲህ ሲል የሱዳን ገዥነታቸውን አረጋግጦላቸው ነበር፤-
ጎንደር ቢያጉረመርም ፋሲል ፈረስህ
ኑብያና ስናር ወርቁን ጫኑልህ፥
ሳሩን ተጠየፈ የፋሲል ፈረሱ፥
ክምር የሱዳን ወርቅ ገፈራው ነው ለሱ።
“ገፈራ” ማለት የፈረስ ምግብ ነው። ዛሬ ፉርሽካ የምንለው ዐይነት። እንግዲህ ይህ ግጥም፥ ሱዳን አስከ የዛሬ 500 ዐመት የኢትዮጵያ ግዛት አንደነበረች ይመሰክራል። በሁዋላ በዘመነ መሳፍንት አና ከዛ ትንሽ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ አየተዳከመች ስትሄድ ቱርኮች ያዝዋት። ቱርኮች ተዳክመው ለእንግሊዝ ለቀቁላት። እንግዲህ ከእጅ የወጣ ሃገር በታሪክ ሰነድ ወይም ማረጋገጫ የሚመለስ ቢሆን ኖሮ፥ መላው ሱዳን ለኢትዮጵያ በተመለሰ ነበረ። ከላይ አንደ ተረዳነው ሱዳን የኢትዮጵያ እንጂ ኢትዮጵያ የሱዳን ሆና አታውቅም። ታዲያ በምን ምክንያት ነው አሁን የኢትዮጵያን መሬት የጠየቀችው? እስዋ አፍዋን ምን ቁርጥ አርጉዋት ጠየቀችና? እስዋ በራስዋ ተነሳስታ ደፍራ መሬት አለኝ አላለችም። አሁን በአመራር ላይ የአሉት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ደርግን በሚዋጉበት ሰዐት ሱዳን ለዋለችላቸው ውለታ ወሮታውን ሊመልሱላትና አሁንም ተቀዋሚዎቻቸውን እንዳታስተናግድ የሚከፍሉዋት ዋጋ መሆኑ ነው። ወዲህም መሬቱ ያለው በአማራ፥በቤንሻንጉል፥ በጋምቤላና በአሮሞ ክልሎች ስለሆነ የእኛን ምድር ስለማይመለከት ችግር የለውም ዐይነት ነው። ብሄራዊ ስሜት የሚባል ነገር ስለሌለ። መሬት በነፃ እንካ ከተባለ ማን ይጠላል? ስለዚህ ሱዳኖቹ እየፈነጠዙ ሊወስዱ አኮብኩበዋል።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት 1600 ኪሎሜትር ለም መሬት ለሱዳን ይገባታል ብሎ ጠበቃ የቆመላት እላይ የተጠቀሰው ቅኝ-ገዢ መኮንን በቸከለው ድንበራዊ ችካል ክሆነና በእንግሊዝ ቅኝ ገዥነት አገር ቅርጫ አንዲሆን ከተፈቀደ፥ እንዲሁም እንግሊዝ ያቀናው መሬት ሁሉ ለሱዳን ይቸር ዘንድ ከተፈረደ፥ የቀድሞው የአንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች የነበሩት እነ ዩጋንዳና ሱዳን፥ ካስፈለገም እነ ናይጀሪያ ሁሉ ለሱዳን መሰጠት ይገባቸዋል ማለት ነዋ!!! የሆነ ሆኖ፥ ያ ሆፈፌ ቅዥተኛ እንግሊዝ ምኞታዊ ህልም አልሞ የፈለገውን ያህል የወሰን ድንጋይ ቢተክልና አፄ ምኒልክም አልተስማሙም እንጂ ቢስማሙለትና መሬት ቆርሰው ቢሸልሙትም አንኩዋን ያ ውል የሞተ ነው። ለምን ቢባል፥ ሱዳንን ዐለምና የተባበሩት መንግሥታትም ያወቃትና በታሪኩዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ራስዋን ችላ የራስዋን ባንዲራ ያውለበለብችበት ዳር ድንበር አሁን የአለው ነውና። እኤአ በ 1953 ዐመተ ምህረት እንግሊዝ ግዛቴ ይሄ ብቻ ነውና ያንቺም ግዛትሽ ይሄው ነው ብሎ በዐስር ጣቱ ፈርሞ የተወላት መሬት ነው። እሱውም ከመከፈልዋ በፊት የነበረው የቆዳ ስፋቱ 2,505,813 ስኩዌር ኪሎሜትር የሆነው ነው። ከመከፈልዋ በፊት ሱዳን በቆዳ ስፋት ከአፍሪካ አንደኛ ነበረች። አሁን ሶስተኛ ነች። አሁንም ከኢትዮጵያ ትልቃለች ማለት ነው። የያዘችው ይበቃት ነበር።
የኢትዮጵያን መሬት ለግሰናት በደቡብ ሱዳን የተወሰደባትን መሬት እንተካላት ካልተባለ በቀር። ሰጭና ነሽው አንግሊዝ ከተደረገና የእንግሊዝ መንግሥት ለክቶ፥ “አበጥሮ”፤ “አንጥሮ” ሁሉን አጣርቶ ራሱ በመጨረሻ ያረጋገጠው የሱዳን ምድር እላይ የተጠቀሰው ስፋት ከሆነ በምን ሂሳብ ነው አንግሊዝም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት የማያውቁትን የኢትዮጵያን መሬት በ ህቡዕ ለሱዳን የሚለገሳት? አይገባትም አንጂ በ እርግጥ ሱዳን ይገባኛል የምትለው መሬት ከአላት ወደ ተባበሩት መንግሥታት ሄዳ ነው አንጂ አቤቱታዋን የምታቀርበው በስርቆሽ በር ነው እንዴ መሬት ቆርሳ የምትሮጠው? ወይንስ መሬቱን ከቦጨቀች በሁዋላ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ቀርባ መርቁልኝ ልትል ይሆን? እስዋ ግን ወደ እዛ እስካሁን ያልሄደችው እኤአ በ 1953 እንግሊዝ ካስረከባት በቀር ሌላ መሬት ስለማይገባት “ወይጅ ወዲያ አትቀልጅ!” ይሉኛል፤ ብላ ፈርታ ነው። አለዛ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጀምሮ መሪዎችዋ ከ ኢብራሂም አቡድ ጀምሮ እስከነ ኑሜሪ አና አሁን ያለውም አል በሺር የይገባኛሉን ጥያቄ ገና ድሮ ባቀረቡ ነበር። ሰብብ ፈጥረን ስለቀድሞ ውለታዋ እና ተቀዋሚዎቻችንን ስለምትገታልን እንዲሁ በነፃ እንቸራት ካልተባለ በቀር እንደ እውነቱ ከሆነስ ሱዳን፥ “ኢትዮጵያ ያዘችብኝ፥ ይገባኛል፤” የምትለው አንዲት ስንዝር መሬት የላትም። ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በሁዋላ የአፍሪካ ሀገራት በሞላ የያዙት ድንበርና ወሰን የቅኝ ገዥዎችቸው አነዚህ ናቸው፤ ብለው ያረጋገጡላቸውን ብቻ ናቸው። ስለዚህ ሱዳን ከሌሎቹ የአፍሪካ ሃገራት በምንም አትለይም። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ልቀበል ይገባኛል ልትል የሚያስችላት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጥሪኝ አፈር የላትም። ስለ ኦሜድላ ብቻ እንኩዋን ብንዘክር፥ አፄ ኅይለሥላሴ በሱዳን በኩል ከስደታቸው ሲመለሱ ከ 5 ዐመታት በሁዋላ ለመጀመሪይ ጊዜ የኢትዮጵያን ሰንደቅአላማ ሰቅለው የአውለበለቡት ኦሜድላ ላይ ነበር። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜም የ እንግሊዝ የቅኝ ገዢ ትልቅ ባለስልጣናት ለ ሰንደቅአላማዋ አክብሮት በተጠንቀቅ ቆመው መሬቱ የኢትዮጵያ መሆኑን ተቀብለው ይመለከት ነበር እንጂ “የሱዳን መሬት ላይ እንዴት ባንዲራ ያውለበልባሉ!” ሲል በንጉሱ ላይ ቅዋሜ አላሰሙም።
ኦሜድላ የኢትዮጵያ ለመሆንዋ ከዚህ በላይ ምን ማረጋገጫ አለ? ታዲያ በምን ምክንያት ነው አሁን ይቺ ታሪካዊ ስፍራ ለሱዳን የምትሸለመው? ቀዳማዊ ኅይለሥላሤ ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅአላማ ሲያውለበልቡ ጦሩን እንዲያቀነባብር በእንግሊዝ መንግሥት ተሹሞ አብሮአቸው በሱዳን በኩል የገባው ሜጄር ዊንጌትም ታዛቢ ሆኖ እጎናቸው ነበረ። ንጉሡን ተሽቀዳድሞ አዲስ አበባ የገባው ሎርድ ካኒንግሃምም እሳቸው ኦሜድላ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅአላማ እንዳውለበልቡ አሳምሮ ያውቅ ነበር። እነዚህም ሁለት ታላላቅ የእንግሊዝ መንግሥት ተወካዮች ኦሜድላ የኛ ናት አላሉም። የሆነ ሆኖ እውነት እንግሊዝ ከ አፄ ምንይልክ ጋር ተዋውሎ ከነበር እሱው እንግሊዝ የመሬት ይገባኛል ጥያቄውን ያቅርብልን እንጂ ያልተዋዋልናት ሱዳን ምን አገባት? ከሱዳን ሳንዋዋል እንዴት ሱዳን የተዋዋልነው ይከበርልኝ፥ ልትል ትደፍራለች? ይህን ጥያቄ ሊያነሳ የሚችል አንግሊዝ ብቻ ነው። ነበርም። ግን እንግሊዞች አላነሱም። ምክንያቱም ቀላል ነው። የዚህ ዐይነት ውል ከአፄ ምንይልክ ጋር ስላተፈራረሙ። ተፈራርመው ቢሆን ኖሮ መጠየቅ ብቻ አይደለም፥የተፈራረሙበት ቀለም ሳይደርቅ መሬቱን እጃቸው ያስገቡ ነበር። ስላልተፈራረሙ ይህን አላደረጉም። የሱዳንን ነፃነት እንግሊዞች ሲፈቅዱም የተባለውን መሬት የኔ ነበር ብለው ወደ ሱዳን አላዘዋወሩም። አሁን ያለውን መሬት ብቻ ነው ትተውላቸው የሄዱት።አሱም ለሁለት ተከፍሎባቸዋል። ከአንግሊዝ የተረከቡትን መሬት እንኩውዋን በቅጡ መያዝ አቅቶአቸው “የቆጡን አወርድ ብላ የብብትዋን ጣለች፤” የተባለው ተረት በነሱ ላይ ተፈፅሞባቸዋል። የራሳችውን አጥብቀው መያዝ ሳይችሉ የኛን መሬት መከጀላቸው ማስቆጣት ብቻ ሳይሆን ያስደንቃል። እንግዲህ እንግሊዝ ከአፄ ምንይልክ ጋራ መሬትን አስመልክቶ ላለመዋዋሉ ሶስት ማስረጃዎች አሉ ማለት ነው። አንደኛ፥ የተባሉትን መሬቶች ቀደም ሲል እጁ ባለመክተቱ፤ ሁለተኛ፥ ንጎሱ ኦሜድላ ላይ ሰንደቅአላማችንን ሲሰቅሉ አለመቃወሙ፥ ሶስተኛ፥ ሱዳንን ለቆ ሲሄድ ለሱዳን ከተወላት የተባበሩት መንግሥታይ ባፀደቀላት ዳር ድንበር ውስጥ እነዚህን ሁሉ የኢትዮጵያ መሬቶች በካርታም ሆነ በፅሁፍ ባለማካተቱ። በነዚህ ሶስት ማስረጃውች ምክንያት እሩቅ ሳንሄድ፥ ሰነድ ለማግኘት አፈር ሳንቆፍር እና ድንጋይ ሳንፈነቅል ምንይልክ እና እንግሊዝ አንዳችም የመሬት ውል እንዳልተፈራረሙ እናረጋግጣለን። ተፈራርመዋል የሚል እስቲ ሰነዱን ያቅርብልን!! ደግሞም ቢፈራረሙም እንኩዋን ውሉ የቅኝ ገዥዎች ሰለሆነና ምንይልክም ሆነ ማንኛውም መሪ የአትዮጵያ መሬት የግል ንበረቱ ስላልሆነ መሬት ለባእዳን ሰጥቻለሁ ቢል አይፀናም።
አፄ ምንይልክ ተስማምተውበት፥ አፄ ኅይለሥላሴ እና ደርግ ያፀደቀውን ነው እኛ በተግባር የምናውለው፤ ሲል ኢህአዲግ ደጋግሞ ተናግሮአል። ይህን መሰረት በማድረግ እኔ ብዙ ምርምር አካሂጄ ሁለቱ አፄዎችና የደርግ ሊቀመንበር የነበሩት ኮረኔል መንግሥቱ ኅይለማርያም ለሱዳን መሬት ለመስጠት የተዋዋሉበት አንድም ሰነድ አላገኘሁም።ምክንያቱም ስላልነበረ። ስለ ሌለም። አሁን በህይወት የአሉት ኮሎኔል መንግሥቱም አንድም የዚህ ዐይነት ውል ከሱዳን ጋር እንዳልተፈራረሙ አበከረው መስክረዋል። ይልቁንም አኔ ያገኘሁት መረጃ፥ አውሮፓውያን መንግሥታት ለብቻቸው ተሰብስበው አፍሪካን ለመቀራመት ያደረጉትን ውል ለአፄ ምንይልክ ነግረው የኢትዮጵያን ነፃነት ግን አንደሚያስጠብቁ ቢገልፁላቸው፥ “እኔ በሌለሁበት እናንተ ተሰብስባችሁ ያደረጋችሁትን ውል በፍፁም አልቀበልም፤ የኢትዮጵያን ነፃነት አናስጠብቃለን ሰለአላችሁት ግን አመሰግናለሁ፤” በማለት ተንኮላቸውን ውድቅ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ነው። በነገራችን ላይ፤ አፄ ምንይልክ እንኩዋን ለሱዳን መሬት ሊሰጡና በሰላም ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የውጭ ሀገር ሰዎች መሬት አንዲገዙ አይፈቅዱላቸውም ነበር። አላደረጉትም እንጂ ሶስቱም መሪዎች አድርገውትም እንኩዋን ቢሆን፤የኢትዮጵያን ህዝብ መሬት አንስተው ለባእዳን ለመቸር ምንም መብት አልነበራቸው። ኢትዮጵያ፥ እንዲያስተዳድሩዋት አደራ የተሰጠቻቸው ምድር እንጂ እንዳሻቸው ለፈለጋቸው አገር ገፅበረከት አድርገው የሚለግስዋት የግል ንብረታችው አልነበረችምና። አሁን ያለውም መንግሥት አንዲሁ የኢትዮጵያን መሬት ገምሶ ለባእዳን ለመቸር ከቶም አንድም ህገመንግሥስታዊ ነፃነት ወይም ስልጣን የለውም። በጉልበቱ ካልሆነ በቀር። ረጅሙን ታሪካችንን ወደ ሁዋላ መለስ ብለን ብናስተውል፥ ባለፉት 5300 ዐመታት ኢትዮጵያን የመሩት መንግሥታት ድንበር ከማስፋት በቀር መሬታቸውን እንደ አንጀራ ቆርሰው ለባእዳን ሲቸሩ በፍፁም ተስተውሎ አያውቅም። አሁን ከአለው መንግሥት በስተቀር።
እዚህ ላይ ባድመ ይታወሰናል። ባድመ ባድማው ደረቁ መሬት ከአትዮጵያና ኤርትራ በኩል ወደ 150000 ገደማ ወይም ከዛ በላይ ምስኪን ሰዎች በከንቱ አስጨረሰ። ከዚያ አልጀርስ ላይ ለኤርትራ ይገባታል ይሰጣት፤ ተብሎ ተፈረደላት።ባድመ እስካሁን በ ኤርትራ እጅ ውስጥ አልገባችም። ለምን? የትግራይ መሬት ውስጥ ስለሆነች የማትነካ፥ የማትገሰስና የተቀደስች ሆና ወይስ በሌላ ምክንያት? ሰፊ መሬት አለኝ ብሎ ከማውራት በቀር ለማንም የማይጠቅመውን ጠፍ መሬት አንሰጥም ብሎ ይዞ፥ ለመሬት ብላ ከኛ ላልተዋጋችው ሱዳን ለምለም ምድር ገምጦ ለመቸር መቸኮል ምን ይባላል? ይህ ለሰሚው ግራ ነው። ባድመም በኤርትራ ላትወስድ የቻለችው፥ “ትግራይ ሀገርህ ተወራለችና የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ተነሳ!” ተብሎ በተጠራው የሀገር ማዳን ጥሪ መሰረት፥ “ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም ይህ የትገራይ መሬት ነው፤” ሳይል በብሄራዊ ስሜት የነደደው ቆራጡ የኢትዮጵያ ህዝብ አጥንቱን ከስከሶ፤ ደሙን አፍሶ፤ንብረቱን አጉድሎ ባደረገው ተጋድሎ ነው። ትግራይ ስትወረር የኢትዮጵያ ህዝብ ፥ “ወይኔ ሃገሬ!” ብሎ ደሙን ሲያፈስ ባድመ የመጨረሻው እንጂ የመጀመሪያው አይደለም። ከዛ በፊት ጣልያን ከማንም አስቀድሞ ትግራይን በወረራት ጊዜ በመቀሌ፥ በአምባላጌ፥በአድዋ እና በማይጨው በ 40 ዐመታት ልዩነት ውስጥ ሁለቴ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎአል። ለዚህ ሁሉ ውለታው አፃፋው ይሄ ነውን? እባካችሁ ሰከን ብላችሁ ነገሩን አስቡበት።
ይህ ድርጊት በትውልድ ያስወቅሳችሁአል። ጠንቁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ፤ እንዲሁም ለዘራችሁ ይተርፋል። ለስልጣን ያበቃችሁ የትግራይ ህዝብ ሳያቀር በአደራጎታችሁ ያፍርባችሁአል። የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ አቅም ባይኖረው ነገ ሊጠነክር ይችላል። ሳይወድና ሳይፈቅድ መሬቱን ሱዳን አሁን ብትወስድበት እንኩዋን ነገ ሲጠነክር ተዋግቶ ያስመልሰዋል። በዚህ ሳቢያ አሁን ልትጠቅምዋት ያሰባችሁአት ሱዳንም ሰላም አታገኝም። የ እናንተም ስም በክፉ ተነስቶ አፅማችሁም ሲወቀስ ይኖራል። ስለዚህ ሱዳንን በሌላ በሌላ ነገር ካስዋት እንጂ የስንት ሰማአታት ወገኖቻችን ደም እና ላብ የአለማውን መሬታችንን አሳልፋችሁ በብላሽ አትስጡ። ለሱዳን ካሳ፥ አፍንጫዋ ስር የተገነባላት የአባይ ግድብ መች አነሳት? በዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘቡን በከሰከሰበት ግድብ ከማንም በላይ ተጠቃሚዋ ሱዳን አይደለችንምን? ግድቡ ይበቃታል፤ መሬቱ ይቅርባት። ብቻችሁን ይህን መወሰን ካስቸገራችሁ ደግሞ ፓርላማችሁና የኢትዮጵያ ህዝብ ይምከርበት። ለይስሙላስ ቢሆን ፓርላማ አለ አይደል? እንዲህ ዐይነቱ ትልቅ የሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ሀገር ሳይመክርበትና ህዝብ ሳይወስንበት አንዴት በዝግ ጉዋዳ ይካሄዳል? ባድመ አንዳትወሰድ የተረባረባችሁትን ያህል አና ለኤርትራ አንዳይሰጥ የምትተጉትን ያህል፥ እባካችሁ አሁን ሱዳንን የሚያዋስናትን ሁሉ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ለሱዳን ከመቸር ታቀቡ። በውኑ ከዚህ ከታቀባችሁ፥እናንተም፤ ልጆቻችሁም፥ ዘራችሁም፥ አንዲሁም በመቃብር ውስጥ የሚኖረው አፅማችሁም ከመወቀስና ከመረገም ይተርፋል። ጆሮ ያለው ይስማ። ልብ የአለው ልብ ይበል።
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የ The Hidden and Untold History of the Jewish People and Ethiopians እና የ Heaven to Eden መፃህፍት ደራሲ ነው። ሁለቱም መፃህፍት በ amazon.com ቢፈለጉ ይገኛሉ። አስተያየት ለማቅረብ በ fiktolo@gmail.com ይጠቀሙ።