Tag Archives: Ethiopian Federal Police

መንግሥት ራሱ በጠራው ሰልፍ በርካታ ሰዎችን ሲደበድብ፤ ከመቶ በላይ ሰዎች ታስረዋል

ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በሊቢያ፣በደቡብ አፍሪካና በየመን ኢትዮጵያውያን በግፍ መገደላቸውን በተመለከተ በአዲስ አበባ ድርጊቱን ለማውገዝና ለመቃም ሰልፍ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፤ በሰልፍ የተገኙ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ተደብድበው ወደ አካባቢው ሆስፒታሎች የተወሰዱ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም አልጀዚራን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከስፍራው በቀጥታ ዘግበዋል፡፡ በተለይ በአሸባሪው በ አይ ኤስ አይ ኤል (ISIL) ቢያንስ 28 ኢትዮጵያውያን በጭካኔ መገደላቸውና መንግሥትም ለዚህ ያሳየው ቸልተንነት ህዝቡን የበለጠ በማስቆጣቱ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ያለማንም ቀስቃሽ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለተቃውሞ ሰልፍ ቢወጣም መንግሥት ፈቃድ አልሰጠሁም በሚል በርካቶች ከደበደበ በኋላ ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ራሱ ድርጊቱን በመቃወም ሰልፍ ቢጠራም መጨረሻው በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባና እስር ተጠናቋል፡፡ ሰልፉ ከመጀመሩ በፊት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ወደሰልፉ ሲሄዱ የታሰሩ ሲሆን፤ ከሰልፉ በኋላ የመንግሥት ባለሰልጣናት መስቀል አደባባይ ንግግር ሲያደርጊ ህዝቡ በልቅሶ ተቃውሞ ካሰማ በኋላ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ እዛው ሰልፉ ቦታ ሲደበድብ ታይቷል፡፡ ይሄንንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ አሰራጭተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ አሸባሪው ቡድን ISIL በሊቢያ የገደልኩት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ቢልም፤ በአዲስ አበባው ተቃውሞ የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በጋራ ድርጊቱን ሲያወግዙ ተስተውሏል፡፡ በዕለቱም በርካታ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን፤

ታርዷል ወገኔ፣ ታርዷል ወገኔ…(በኡኡታና ልቅሶ)

ሽብርን እንቃወማለን፣እናወግዛለን

መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም

ሞት ለወያኔ፤ ያረደንም ያሳረደንም ወያኔ ነው

ይለያል ዘንድሮ የዌኔ ኑሮ

ውሸት ሰለቸን፤ የወንድሞቻችን ደም ይመለስ

የሀገር ውስጥ ISIL ወያኔ ነው፤…በቃን

ISIL እስልምናን አይወክልም፤ እኛ የኢትዮጵያውያ ሙስሊሞች ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች በአሸባሪ ቡድኑ መገደላቸውን አጥብቀን እናወግዛለን፤ ድርግቱም ሽብር እንጂ እስልምናን አይወክልም (በተለይ በሰልፉ የተገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች)

መንግሠት የሌለው እዚህ ብቻ ነው

የኢትዮጵ አምላክ ይፍረድ (በተለይ የሟቾቹ ቤተሰቦች)

ና ና መንጌ ና ና (የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን)

የቤት አንበሳ የውጭ እሬሳ (መንግሥትን) የሚሉ መፈክሮች ይገኙበታል፡፡

pretest victims2

በሰልፉ ላይ በፖሊስ ከተጎዱት መካከል

በሰልፉ ላይ በፖሊስ ከተጎዱት መካከል

በመጨረሻም በመንግሥት ላይ የህዝቡ ተቃውሞ ተጠናክሮ ሲቀጥል የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር በቅጡ ሳይሰማ የተቋረጠ ሲሆን፤ ፖሊስም ወዲያውኑ ያገኘውን ሁሉ እያሳደደ ሲደበድብ ለማየት ተችሏል፡፡ በቂርቆስ ሰፈር ልቅሶ ቤት አካባቢ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ በስፍራው እጅግ በርካታ ፖሊሶች በስፍራው የነመበሩ ሲሆን፤ በኋላም ከፍተኛ የመሳሪያ ተኩስ ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በተተኮሰው ጥይት በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ስለማደረሱ የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም መስቀል አደባባይ በነበረው የፖሊስ ድብደባ ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሴቶች፣እናቶችና ወጣቶች የታዩ ሲሆን፤ ብዙ ወጣቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በአምቡላንስ እና በሰው እግዛ ወደ ህክምና ጣቢያ ሲሄዱና የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ታይቷል፡፡

protest 2

በሰልፉ ላይ በፖሊስ ከተጎዱት መካከል

በሰልፉ ላይ በፖሊስ ከተጎዱት መካከል

በሰልፉ ላይ በፖሊስ ከተጎዱት መካከል የተወሰኑት የህክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው

በሰልፉ ላይ በፖሊስ ከተጎዱት መካከል የተወሰኑት የህክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው

መንግሥትም በተመሳሳይ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሽብር ድርጊቱን በመቃወም በመዋቅሩ ሰልፍ ማዘጋጀቱና ለዚህም የኢህአዴግ ሊግና ፎረነም አባላት ከየቀበሌው በነበረው መዋቅር ወደሰልፍ እንዲወጡ፣ ሌላ ወደተቃውሞው ሰልፍ የሚመጣ ካለ በደንብ ከበው እንዲከታተሉት፣ መፈክሮችም በኢህአዴግ ብቻ እንዲዘጋጅ ከዛ ውጭ ያለ መፈክር ይዞ የሚመጣ ማንኛውም አካል ካለ ወደሰልፉ መሐል ከመቀላቀሉ በፊት ጥብቅ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ትዕዛዝ መሰጠቱንም ምንጮች ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡

በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቀደም ሲል የሽብር ድርጊቱን በማውገዝ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ በፌስ ቡክ ግድግዳቸው ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢናገሩም፤ በመጨረሻም አሸባሪው ድርጅት ላይ በመንግሥት እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በአዲስ አበባ ሰልፈኛ ላይ እርምጃ ሲወስድ ታይቷል፡፡ መንግሥት በበኩሉ እርምጃ የተወሰደው ፖሊሶች ላይ ድንጋይ ስለተወረወረ ነው የሚል ምክንያት ሰጥቷል፡፡

በተለይ በሊቢያ የሟቾች ማንነት እየተለየ ሲሆን፤ ስማቸውም ኢያሱ ይኮኖአምላክ፣ ባልቻ በለጠ፣ ብሩክ ካሳ፣ በቀለ ታጠቅ እና ኤልያስ ተጫኔ ከአዲስ አበባ ቂርቆስ ሰፈር፤ መንግሥቱ ጋሼ እና አወቀ ገመቹ ከወለጋ ነቀምት፣ በቀለ አርሰማ ከጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ካራቻ አካባቢ፣ የጅማ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የነበረው ዳንኤል ሓዱሽ፣ አለም ተስፋይ እና ዳዊት ሀድጉ ከትግራይ መቀሌ አካባቢ፣  ክርስቲያን ወንድሞቼን ለይታችሁ አትገድሉም፤ በእስልምና የሰውን ህይወት ማጥፋት ኃጥትም ወንጀልም ነው፣ እኔ ከእነሱ አልለይም በማለት ሲከራከር የነበረው ኢትዮጵዊው ሙስሊም ጀማል ረህማንም አብሮ መገደሉ ታውቋል፡፡ በአሸባሪው ቡድን ከተገደሉ ኢትዮጵያውያን ጋር  ተስፋይ ኪዳኔን ጨምሮ ሶስት ኤርትራውያንም እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን፤ በተለይ ተስፋይ ከዚህ በፊት በእስራኤል ጥገኝነት ጠይቆ በመከልከሉ በሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሲሞክር በአሸባሪ ቡድኑ እጅ መግባቱ ተጠቁሟል፡፡

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት በደረሰባቸው ችግር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ

የህዳር 27 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የጠራው የአዳር ሰልፍ ወቅት ተይዘው በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ እና ለሶስት ቀን የስኳር በሽታ መድሃኒት እንዳይገባላቸው በመከልከላቸው ለህመም የተዳረጉት የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ፀኃፊ መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ ከእስር ከተፈቱበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወር ሆስፒታል ከቆዩ በኋላ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ በአዳሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን ለአምስት ቀናት ቀዝቃዛና ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ይዘውት የነበረውን የስኳር በሽታ መድሃኒታቸውን በመቀማታቸው፣ እንዳይገባላቸው በመከልከላቸውና በወቅቱም ህክምናም ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ህመም በመዳረጋቸው ለሁለት ወር ያህል ዘውዲቱ ሆስፒታል ቆይተዋል፡፡

መቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ እስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ዘውዲቱ ሆስፒታል ከገቡበት ታህሳስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ህመም እየተሰቃዩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመቶ አለቃ ተሰማ ወንድሙ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም በቦሌ ሚካኤል እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በፊት ከኬንያ በህወሓት ደህንነት ታፍነው አዲስ አበባ ቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት ታስረው በህወሓት ፖሊሶችና ደህንነቶች በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ድብደባ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ይፋ ያላወጣቸው የተለያዩ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ይታወቃል፡፡

አንድነት ፓርቲ የምርጫ ቦርድን እና የኢህአዴግን ህገወጥ አሰራር አሰራር ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል

እሁድ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. አንድነት ፓርቲ በጠራው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አዲስ አበባ ላይ በፖሊስ ድብደባ ድብደባ ከ26 በላይ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የሰላማዊ ሰልፉ ጅማሮና ፖሊስ ለድብደባ ሲሄድ የሚያሳይ እና በፖሊስ ድብደባው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በከፊል፡-

ud

udj8

udj demon1

udj4

ujd

udj2

udj11

udj9

udj12

udj7

meski

ሦስት የፖሊስ መኮንኖች ሰው በማፈን ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ

ታምሩ ፅጌ

-አድራሻቸው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የሆኑ ሦስት የፖሊስ መኮንኖች፣ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት አንድ ሰው አፍነው ወደ ጅግጅጋ በመሄድ ላይ እያሉ ተይዘው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ 

 በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎቹ ዋና ኢንስፔክተር ጐይቶም አረጋዊ ኪዳነ ማርያም፣ ረዳት ኢንስፔክተር አንተነህ አስናቀ ተፈራና ኮንስታብል ዘሪሁን ሲሳይ ሲሆኑ፣ ሁሉም በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡

jijigaተጠርጣሪዎቹ ለሕግ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በማስገደድና ከሕግ ውጪ የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉትን አቶ አህመድ ኑርን ይይዟቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከሶማሌ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ተበዳዩን የያዟቸው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጐተራ አካባቢ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡

የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉት አቶ አህመድን ከነበሩበት ተሽከርካሪ ላይ ጐትተው በማውረድ፣ በሽጉጥ በማስፈራራት፣ በቦክስ ፊታቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍላቸውን በመምታት ራሳቸውን ሲስቱ፣ ተጠርጣሪዎቹ በያዙት ተሽከርካሪ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ መድኃኔዓለም አካባቢ እንደወሰዷቸውም ተገልጿል፡፡

ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘውና ‹‹የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ ቢሮ›› በመባል በሚታወቀው ጊቢ በሚገኝ ሰርቪስ ቤት ውስጥ በማስገባት፣ ለሦስት ሰዓታት እንዳቆዩአቸውም ክሱ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከሦስት ሰዓታት በኋላ የሰሌዳ ቁጥሩ 0071 በሆነ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ፒክአፕ ተሽከርካሪ ጭነው፣ ወደ ጅግጅጋ ያመራሉ፡፡ ልዩ ቦታው አዋሽ ድልድይ ኬላ ላይ የሚጠብቁ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባላት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸውና ሰውን ከሕግ ውጪ ይዞ ማስቀመጥ ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና የጠየቁ ቢሆንም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ውድቅ አድርጐ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ብይን ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ