በችግር የተተበተበው የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት
ዮሐንስ አንበርብር
– ከ630 ሺሕ ሔክታር መሬት የለማው 76 ሺሕ ሔክታር ብቻ ነው
– መሬቱን የተረከቡ ባለሀብቶች 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር አግኝተዋል
– የቀረጥ ነፃ መብትን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ተገኝተዋል
በጋምቤላ ክልል ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንት በአቋራጭ ለመበልፀግ የጓጉ ባለሀብቶችን የሳበ፣ ከባንኮች የተወሰደውን ብድር ላልተገባ ዓላማ እንዲውል ያደረገና በኪራይ ሰብሳቢነት የተተበተበ እንደነበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥናቱ እንዲካሄድ የወሰኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሆናቸውን፣ 14 ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተወከሉበትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተውጣጡ ባለሙያዎች ያካሄዱት መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በጥናቱ መሠረት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለ623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት የተላለፈ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 409,706 ሔክታር በጋምቤላ ክልል መተላለፉን፣ ቀሪው 220,812 ሔክታር ደግሞ የፌዴራል የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በውክልና ከወሰደው መሬት ያስተላለፈው መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡
ከተላለፈው መሬት ውስጥ እስከ 2008 ዓ.ም. በድምሩ መልማት የቻለው 76,862 ሔክታር ብቻ መሆኑን የጥናት ውጤቱ ይጠቁማል፡፡
መሬቱ ላለመልማቱ በጥናቱ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ባለሀብቶች ለልማቱ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ አብዛኛው ባለሀብት መሬት የሚወስደው አልምቶ ራሱንና አገርን ለመጥቀም ሳይሆን ከባንክ ብድርና ከቀረጥ ነፃ መብት ጋር ተያይዞ የሚገኘውን ጥቅም በማጋበስ በአቋራጭ ለመክበር እንደሆነ ይገኙበታል፡፡
የመሬትና የይዞታ ካርታ መደራረብ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉትም ተጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደርና ደን ልማት ቢሮ ከተመዘገቡ 651 ይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ውስጥ 381 የሚሆኑት ካርታዎች በተለያየ መጠን እርስ በርሳቸው የተደራረቡ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
መሬት ከተረከቡት 623 ባለሀብቶች የእርሻ መሣሪያ ያላቸው 226 ሲሆኑ፣ የእርሻ መሣሪያ የሌላቸው 397 መሆናቸውን ተገልጿል፡፡ ከአጠቃላይ የእርሻ ኢንቨስትመንቶቹ ውስጥ 479 የሚሆኑት ሥራ አስኪያጅ እንደሌላቸው ተጠቁሟል፡፡
ባለሀብቶቹ ከቀረጥ ነፃ መብት የመበዝበዝ አዝማሚያ እንዳላቸው የሚገልጸው ጥናቱ፣ ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 29 ባለሀብቶች የት እንደሆኑ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከወሰዱት መሬት በላይ ትራክተሮችን ወይም ሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስገቡ፣ እነዚህ ትራክተሮች እንዲሁም እንደ ፒክአፕና ሲኖትራክ ያሉ ተሽከርካዎች ደግሞ በእርሻ ቦታው እንደሌሉ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
ከሁሉም በላይ አሳዛኝ ገጽታን የያዘው ከባንክ ብድር አለቃቀቅ ጋር በታያዘዘ ጥናቱ የደረሰበት ግኝት ነው፡፡ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ባላቸው ስምንት ወረዳዎች በተገኘው የመስክ መረጃ መሠረት ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 200 የባንክ ብድር አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 27 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ 161 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጅማ ቅርንጫፍና 12 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ጥናቱ ይዘረዝራል፡፡
ከ200 የባንክ ብድር ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሁለት ተበዳሪዎች በባንክ ዝርዝር ውስጥ ያልተገኙ ቢሆንም፣ በመስክ በተደረገው ማጣራት ተበዳሪ ሆነው መገኘታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ለ200 ባለሀብቶች ለመሬት ልማት፣ ለካምፕ ግንባታ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለማሽነሪ፣ ለሥራ ማስኬጃና ሌሎች ወጪዎች የተፈቀደላቸው ብድር 4.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ እነዚሁ 200 ባለሀብቶች የተረከቡት መሬት 454,261 ሔክታር ሲሆን፣ 194 ለሚሆኑት የዚህ መሬት ባለቤቶች 1.99 ቢሊዮን ብር ብድር መለቀቁን ይገልጻል፡፡ በዚህ ብድር እስከ 2008 ዓ.ም. ብቻ 314,645 ሔክታር መሬት መልማት የሚጠቀምበት ቢሆንም፣ እስካሁን የለማው ግን 55,129 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
ለሥራ ማስኬጃና ለሌሎች ወጪዎች በሚል ርዕስ 1.16 ቢሊዮን ብር ብድር የተለቀቀ ቢሆንም፣ ለምን ዓላማ እንደዋለ ግን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ለካምፕ ማደራጃ ተብሎ የተለቀቀው ብድር 326,876,702 ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 180 ካምፖች በብሎኬትና በቆርቆሮ ሌሎች 19 የሚሆኑት ደግሞ በሳርና በቆርቆሮ መሠራታቸውን ይገልጻል፡፡
በልማት ባንክ ብድር 122፣ እንዲሁም በንግድ ባንክ 62፣ በድምሩ 184 ተሽከርካሪዎች ተገዝተው የተሰራጩ ቢሆንም፣ በመስክ ምልከታ የተገኙት 159 መሆናቸውን ጥናቱ ያስረዳል፡፡
‹‹የብድር ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ስናስገባ በቀጥታ በስልክ ተደውሎ ጉቦ ካልከፈልክ ለሥራ አስኪያጁ አይቀርብልህም፤›› በማለት አጥኝዎቹ ያነጋገሯቸው መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
በተመሳሳይም ‹‹መሬቱን ተገኝተው ሳያዩት ውኃ ይተኛበታል፣ በስልክ ጥቆማ ደርሶናል፤›› በማለት ገንዘብ ካልተሰጣቸው ብድር እንደማይፈቀድላቸው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
የጥናት ዝርዝሩ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱትን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህርን ያካተተ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች በውል ተረክቦ የሚያስተዳድረው መሬት ውል እንዲቋረጥና ክልሎች እንዲያስተዳድሩ ወስኗል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሚና ክልሎችን ማገዝ እንዲሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ለባለሀብቶች የሚሰጥ ብድር ጠንካራ ክትትል እንዲደረግበት፣ እንዲሁም ለተባለው ዓላማ ያልዋሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክትትል በማድረግ ዕርምጃ እንዲወስድ አዘዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹በውይይቱ ወቅት የተሰጡን አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በእኛ በኩል ያሉ ችግሮችን ገምግመን የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንወስዳለን፤›› ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ ገልጸዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ውድነህ ዘነበ አስተዋጽኦ አድርጓል)
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ
አብዮት የሚናፍቀው የኢትዮጵያ መሬት
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
መሬት ለኢትዮጵያውያን የሕልውና ጉዳይ ነው። አገሪቱ ከመንግሥት ስርዓት ጋር ከተዋወቅችበት ከክ.ል.በ. 2545 ጀምሮ ለነገሥታቱም ይሁን ለቀሪው ዜጋ መሬት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነበር። የመሬቶቹ ባለቤትነትም ከመደበኛው ከነዋሪው ይልቅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገዥው መደብ አባላት እና አጋሮቻቸው እንጂ የአራሹ ሆኖ አያውቅም ነበር። ይህ መሬት ለየአካባቢው የጭፍራ አለቆችም ሆነ ለመኳንንቱ የርስበርስ መቃቃርና ግጭት ዋነኛ ምክንያት ነበር። ይህ ሁሉ ታሪክ በሀገሪቱ ዘመናዊ የመንግሥት ስርዓት መሥራች በነበሩት ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ አማካኝነት በተወሰነ ደረጃ ለውጥ የታየበት ቢሆንም፤ ሕጋዊና ሁሉንዐቀፍ አልነበረም።
በተለይ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመኳንንቱ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች መሬትን ለማግኘት ከቤተክርስቲያን ይጠጉም ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው ኋላ ቀር የመሬት ይዞታ ፊውዳላዊ ስርዓት በዐፄ ቴዎድሮስ ስላልተወደደ፣ በዜጎች መካከል ከመሬት ጋር በተያያዘ የነበረው የገዥና ተገዥ ስሜት ያበቃ ዘንድ የመኳንንቱን እና በክሕነት ሥም በየቤተክርስቲያኑ ተጠግተው በርካታ መሬቶችን በመያዝ ገበሬውን ያንገላቱ የነበሩ ባላባቶች ሁሉ አብዛኛው መሬቶቻቸው እየተወሰደ መሬት ለሌለውና ሲያርስ ለነበረው እንዲከፋፈል፤ በቤተከርስቲያንም የሚያገለግሉ ካሕናት ቁጥር ውስን እንዲሆን እና ቀሪዎቹ ወደ ግብርና ሥራ እንዲገቡ አዘዙ። ይህ ሁሉ የነበረው በዛው በጎንደርና አቅራቢ አጎራባች አካባቢ በነበሩት ወሎ፣ ጎጃምና ትግራይ እንጂ በሌላ የአገሪቱ አካባቢ በገዥ ሥም ባሉ የጎበዝ አለቆች የተለመደው የመሬት ብዝበዛ ሲያከናወን ነበር። የተጠቀሱ ቦታዎችም ቢሆኑ የተሳካ ወጥ የመሬት ክፍፍልና አዋጅ ተፈፃሚ አልሆነም፤ ምክንያቱም የነበረው ስርዓት የተረጋጋና በሰነድ የታገዘ አልነበረም።
በመጨረሻም በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1966 ዓ.ም. በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የዜጎች በተለይም የገበሬዎች የመሬት ባለቤትነት መብት ይረጋገጥ ዘንድ በይፋ ጥያቄ መቅረብ ጀመረ። ከዓመት በኋላም ለዓመታት የሕዝቡ ጥያቄ የነበረው የመሬት ባለቤትነት መብት ከዘውዳዊ ስርዓት ስንብት ጋር አብሮ ተበሰረ። ይህ የመሬት ባለቤትነት መብት በተለይም የ“መሬት ላራሹ” መብት ጥያቄ የካቲት 25 ቀን 1967 በዘመነ ደርግ ምላሽ አገኘ። ያ ወቅት ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ከፋች ነበር። ምክንያቱም ለረጅም ዘመናት መሬት የኢትዮጵያውን የመብትም የሕልውና ጥያቄ ነበርና። ያ አዋጅም ሆነ የተማሪዎች ጥያቄ ትኩረት የእርሻ መሬት ላይ እንጂ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በነጻነት በእንሰሳት እርባታ የሚተዳደሩትን በተመለከተ ነበር ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ በእንስሳት እርባታ ይተዳደሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መሬታቸውን ማንም ከልካይና የሚቀማ ወይም የባለቤት መብት የነፈጋቸው አካል አልነበረም። በተለይ አርብቶ አደሮች የመሬት እና የውኃ ሀብትን በሚመለከት በአነስተኛ ደረጃ እርስበርስ ከሚኖራቸው አለመግባባት በስተቀር የሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ በነጻነት የሚጠቀሙና የባለቤትነት መብቱም ቢሆን ቢበዛ በጎሳ ይሆን እንጂ እንደ እርሻው መሬት በመኳንንቱና በመንደር የጎበዝ አለቆች ባለቤትነት የሚተዳደር አልነበረም።
ዛሬ ግን ሁሉም ነገር ተቀይሯል። የካቲት 25 ቀን 1967 የታወጀው የመሬት ላራሹም ሆነ የመሬት ባለቤተነት መብት ከሕዳር 1987 ጀምሮ በዘመነ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ተሽሯል። የመሬት ባለቤትነት በእርሻ፣ በእንስሳ እርባታ እና በከተማ ኑሮ የሚተዳደረውን ሁሉ መብት ነው የቀማው። ምክንያቱም የግለሰብ የመሬት ባለቤትነት መብት መነጠቁን 4ኛው እንደሆነ በሚነገርለት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀፅ በግልጽ አረጋግጧል። በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ‹የንብረት መብት› በሚለው ሥር ንዑስ አንቀፅ 3 “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” ይላል።
እዚሁ አንቀፅ ላይ በንዑስ አንቀፅ 6 የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ‹ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል› ይላል። በንዑስ አንቀፅ 4-5 “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው። የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነጻ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው። ዝርዝር አፈፃፀሙ በሕግ ይወሰናል” ይላል።
በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ሕጉን ያወጡት እና ያፀደቁት እንዲሁም አገሪቱን እየመሩ ያሉ አካላት ሊመልሱት ያልቻሉት፤ ነገር ግን ሊመልሱ የሚገባቸው በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ከነዚህም መካከል፦
‹መንግሥት እና ሕዝብ የሚባለው ማነው የሚለው ግልጽ አይደለም። ሌላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚል የቃላት ክምር ልዩነታቸውና አንድነታቸው (ካለ) ምንድነው? እነሱስ እነማን ናቸው? በማንስ ይወከላሉ፣ መብቶቻቸውና ግዴታቸውስ? የሚሉ ጥያቄች እስካሁን በየትኛውም ሕዝባዊ መድረክም ሆነ የመንግሥት ሕጋዊ መዝገበ ቃላት ፍቺም ሆነ ትርጉም ያልተሰጣቸው፤ ግን ደግሞ መልስ የሚያሻቸው ናቸው። ምክንያቱም በድፍኑ የቃላት ድርደራ ከመሆን በዘለለ ለሕዝቡ በሚገባ መልኩ በግልጽ የተቀመጠ ትርጉም የለውም።
ሌላው መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ… የጋራ ንብረት ነው ይልና ወረድ ብሎ ደግሞ መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል ይላል። ይህ የሚያሳየው የማይሸጥ የማይለወጥ የተባለው መሬት መንግሥት መሬት ቸርቻሪ እንዲሆን መብት ሰጥቶታል። አሁን ባለው በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ መንግሥት የሚለውም ትርጉም የሚያስፈልገው ዐብይ ጉዳይ ነው። በአንቀፅ 40 (7-8) ላይ ደግሞ ዜጎች የግል ንብረት ባለቤትነት መብት ያላቸው በመሬቱ ላይ በሚገነቡትና በቋሚነት ለሚያሻሽሉት ቁስ እንጂ መሬቱ ላይ የባለቤትነት መብት እንደሌላቸው ያመለክታል። ይህም ከቦታው በግድ የሚፈናቀል ሰው ካሳ እንኳ ቢያስፈልገው፤ በመሬቱ ሳይሆን መሬቱ ላይ ባለው የተጠቃሚነት መብት ባፈራው ንብረት ብቻ መሆኑን ያመለክታል።
የመሬት ባለቤትነት መብት ያለመኖር ያስከተለው ችግር
በርግጥ ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ባያውላቸውም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና ሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎችን ያካተተ ቢሆን ግልጽ ያልሆኑ፣ ጥያቄ የሚያስነሱ በርካታ ግግር ጉዳዮችንም ይዟል። ይበልጥ ግን የገዥውን ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በተለይም የሕ.ወ.ሓ.ት.ን የፖለቲካ ፕሮግራምና ፍላጎት በስፋት ይገኝበታል። ለዚህም ይመስላል፤ ሕገ መንግሥቱ ከተወሰኑ አንቀፆች (ላለፉት 21 ዓመታት ሥራ ላይ ያልዋሉ) ዓለምዐቀፍ ድንጋጌዎች በስተቀር የሕ.ወ.ሓ.ት./ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የፖለቲካ ፕሮግራምና ፍላጎት የሰፈረበት ሰነድ ነው የሚል ጥያቄ የሚነሳው። በተደጋጋሚ ከሚነሱ ጥቄዎችና ቅሬታዎች መካከል የመሬት ጉዳይ ዋነኛው ነው።
በተለይ ሕ.ወ.ሓ.ት. መሬትን በተመለከተ የሚከተለው የፖለቲካ ፕሮግራም (ፖሊሲ) እና ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው አንድ ነው። ከሕ.ወ.ሓ.ት. ውጭ ያሉ ሌሎቹ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አባላት (ብ.አ.ዴ.ን.፣ ኦ.ሕ.ዴ.ድ. እና ደ.ኢ.ሕ.ዴ.ን.) የተሰጣቸውን ከማስፈፀም በቀር የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ተመሳሳይ ከማድረግ ውጭ ሥልጣኑም ሆነ ሞራሉ ያላቸው አይመስልም። አጋር ድርጅቶች የተባሉት የጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ሐረሪ ክልል ፓርቲዎች ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን. ከማጀብና የሚለውን ከመቀበል ውጭ በየትኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ የመወሰን፣ የመጠየቅም ሆነ ላሉበት ማኅበረሰብ መብትና ጥቅም የመቆም ሕልውናም ሆነ አቅም የላቸውም። ምክንያቱም አጋር እንጂ የገዥው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አባል ስላልሆኑ የተሰጣቸውን ሥራ ከማከናወን ባለፈ በፖሊሲም ሆነ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው የተለየና የራሳቸውን ነገር ይዘው መቅረብ አይችሉም። በዚህም ምክንያት ከመሬት ባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው አልቀረም።
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በፌደራሉ መንግሥት ፍላጎትና ሥልጣን ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶች ከገበሬዎቹ በግድ ተነጥቀው ለባለሀብቶች እንዲተላለፉ ተደርገዋል። ከባለሀብቱ በተጨማሪ ስርዓቱ ለሚከተለው መንግሥታዊ ባለሀብትነት (state capitalism) ትግበራ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከገበሬዎች ነጥቋል። ይሁን እንጂ ከገበሬዎች ያለምንም አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ (Environmental and social impact assessment) ሰፋፊ ለም መሬታቸው ወደ መንግሥታዊና ግል ባለሀብቶች በመተላለፉ አንዳቸውም ፕሮጀክቶች ውጤታማ አልሆኑም። ይልቁንም ያለበቂ ምክክር፣ ካሣና ምትክ ቦታ የተፈናቀሉ በርካታ ገበሬዎች ዛሬም ድረስ ሕይወታቸውን በጉስቁልና እንዲመሩ አስገድዷቸዋል። ከገበሬዎች ማኅበራዊ ችግር በተጨማሪ በአካባቢያዊ የአየር ጠባይ እና የአየር ንብረት ላይ የሚኖረው ጉዳት አገሪቱ በቀላሉ የምታካክሰው አይደለም። ይህ ሁሉ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረው የመሬት ባለቤትነት መብትና ስርዓቱ የሚከተለው የመሬት ፖሊስ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው።
በሰንጠረዡ ላይ እንደሚታየው በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ እና ቤንች ማጂ ዞን አካባቢ ለስኳር ፕሮጀክት መንግሥት የወሰደውን 335,000 ሔክታር መሬት፣ የወልቃይት፣ የከሰም፣ የተንዳሆ ሰፋፊ እርሻዎችን፣ 2,000 ሔክታር እና ከዛ በታች ስርዓቱ የኔ ለሚላቸው ሰዎች የሰጠውን ሳያካትት ነው። መሬቱ ለግል ባለሀብቶች የተላለፈው ከ30-50 ዓመት በሚቆይ ኪራይ ነው። በዚህም ምክንያት በአንድ ሔክታር በዓመት ከ14-135 ብር የሊዝ ኪራይ የተላለፉና መንግሥት በነጻ የወሰዳቸው መሬቶች ላይ የኖሩ ዜጎች ያለ በቂ ምክክር፣ ካሣና ምትክ ቦታ ተፈናቅለዋል። በተለይ በጋምቤላ ክልል ብቻ 225 ሺሕ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ከ8-10 ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ደግሞ አገር ጥለው ሲሰደዱ፤ ከ424 ያላነሱ ተገድለዋል። በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በሚገኘው ደቡብ ኦሞ ዞን 200 ሺሕ ያህል ዜጎች ተፈናቅለዋል።
መንግሥት ለስኳር ልማት፣ ለማዳበሪያ ፋብሪካና ተያያዥ ግንባታዎች ልማት በሚል የወሰዳቸው ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶችና ለግል ባለሀብቶች ከተላለፉት ውስጥ ለአገሪቱም ሆነ ለዜጎች ያመጡት ጥቅም የለም። ከጥቅማቸው ይልቅ በተለይ በምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ደኖችና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ይህም ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ካስከተለው ችግር በተጨማሪ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያስከተለው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም። እዚህ ላይ በቅርቡ የገባበት ያልታወቀውን 77 ቢሊዮን ብር የስኳር ልማት ፕሮጀክት ገንዘብ እና የኢሉ አባቦራ ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የደን ጭፍጨፋን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
ሌላው ችግር ባለሀብቶች ውጤታማ መሆን ባልቻሉበት መሬት ላይ የተጠቀሟቸው ኬሚካሎች በተፈጥሮ ሀብት ላይ በተለይም በአፈሩ፣ በውሃውና በአካባቢው አየር ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደቀላል የሚታይ አይደለም። ገበሬው መሬቱን በሚመለከት ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎችም ሆኑ ቅሬታዎች ከመንግሥት ወገን የሚሰጠው መልስ “መሬት የመንግሥት ነው፤ ወደህ ሳይሆን ተገደህ ትነሳለህ” የሚል ሲሆን፤ ያለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ ከቀዬያቸው መፈናቀላቸውን የተቃወሙ ደግሞ የእስርና ግድያ ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሄ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመሬት ሕጉና ፖሊሲው ካስከተሏቸው ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
በከተማው ያለው የመሬት ችግር ከገጠሩ እጅጉን የባሰ ሲሆን፣ ሕዝቡ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የስርዓቱ ጥገኛ እንዲሆን ካስገደዱት ነገሮች መካከል የመሬት ሕጉና ፖሊሲው ዋነኞቹ ናቸው።
‹መሬት አይሸጥም አይለወጥም›፣ ‹የመሬት ፖሊሲው የሚቀየረው በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መቃብር ላይ ነው›… የሚሉ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መፈክሮች ይበልጥ የሚሰሙት በከተማ ነው። ምንም እንኳ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ቢባልም የአገሪቱን የከተማ መሬቶች እንደጉሊት ንግድ በአደባባይ የሚቸረችረው ደግሞ ራሱ መንግሥት መሆኑን ላስተዋለ፣ መሬትን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውና የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ፖሊሲ እርስበርስ ሲጋጭ ይታየዋል። ከዛም አልፎ የሕጉና የፖሊሲው ዓላማ እንዲሁ በቀላሉ እንደተራ ነገር በትዝብት የሚያልፍ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም መሬት ለኢትዮጵያውን መነሻ ካፒታል ብቻ ሳይሆን፣ የሕልውና ጉዳይም ነው። ነገር ግን አሁን የመሬት ጉዳይ ሌላ አብዮት የሚናፍቅ ጉዳይ የሆነ ይመስላል። አለበለዚያ በተለይ ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬት ያለባቸው አካባቢዎች፣ በከተማ የሚኖሩ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንደሰው የመቆጠራቸውም ጉዳይ ጥያቄ የሚገባ ይመስላል። ምክንያቱም በከተሞች ያለው የመሬት የሊዝ ጨረታ ዋጋ እንኳን በወር ደመወዝ በተቋማት ተቀጥሮ የሚተዳደር ቀርቶ በቂ ገንዘብ አለው የሚባለውን ነጋዴውንም ቢሆን እጅግ የሚፈታተን ጉዳይ ሆኗል። ይህ ታቅዶ፣ ዓላማና ግብ ኖሮት የሚፈፀም ያልተጻፈ ፖሊሲ አካል እንጂ በድንገት እየተከናወነ ያለ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል።
ከሊዝ ጨረታ ውጭ አዲሱ ትውልድም ሆነ ከዚህ በፊት የራሳቸው መኖሪያ ቤት የሌላቸው ዜጎች የከተማ መኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ የማግኘት ዕድላቸው ሙሉ ለሙሉ ከስሟል። በዚህ ምትክ መንግሥት ለፖለቲካ ፍጆታ የሚጠቀምበትን ኮንዶሚኒየም ቤት ደስ ባለው ሰዐትና ራሱ በተመነው ዋጋ ለዓመታት በተስፋ በመጠበቅ የከተሜው ነዋሪ ግዴታ መሆን ከጀመረ እነሆ 10 ዓመት አልፎታል።
በተለይ ከሊዝ አዋጅ በተያያዘ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ 721/2004 መሠረት አይደለም መሬት በሊዝ ጨረታ መግዛት በውርስ ያገኘው የቤተሰብ ንብረትም ሆነ በቀድሞ ስርዓት ሠርቶ የቤት ባለቤት የነበረ ሰው መንግሥት በፈለገው ጊዜ እንደሚያስነሳው፣ ካሣውን የሚተምነው ለተሠራው ቤት ጣሪያና ግድግዳ እንጂ ለመሬቱ እንዳልሆነ በግልጽ አስቀምጦታል።
በተለይ ከከተማ ቦታ ይዞታ ጋር በተያያዘ ቤት ያለአግባብ የፈረሰበት ወይም መብቱን የተነጠቀ ማንኛውም ግለሰብ በከተማ አስተዳደሮቹ ውሳኔ ቅር ቢሰኝ እንኳ ወደፍርድ ቤት ሄዶ አቤቱታ ማቅረብ አይችልም። ምክንያቱም የከተማን ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ 721/2004 መሠረት፤ ከተማ አስተዳደሩ 5 አባላት ያሉት ራሱ ፖለቲከኛው የመረጠውና የሾመው የጉባዔ አባላት አቋቁሞ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። ለዚህም በአንቀፅ 30 (8-9) “ጉባዔው ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ በመደበኛው የፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ሕግ አይመራም። ሆኖም በክልሉ ወይም በከተማ አስተዳደሩ በሚወሰን የተቀላጠፈ ሥነ ስርዓት ይመራል። የጉባዔው አባላት የሥራ ዘመን በክልሉ ወይም በከተማ አስተዳደሩ ይወሰናል” በሚል ያስቀመጠውን መረዳት ይቻላል።
በዚህ የሊዝ አዋጅ መሠረት፤ አንድ የከተማ አስተዳደር አካል የሆነና በፖለቲካ የተሾመ ሰው ከመሬት ይዞታ መፈናቀልና መብት ጋር በተያያዘ የትኛውንም በደል ወይም ጥፋት ቢፈፅም፤ ጉዳዩን የሚያየው ጥፋት የፈፀመው የአስተዳደር አካል የሾመው ሌላ የባለሥልጣናት ስብስብ “ጉባዔ” መሆኑ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል። ይህም መሬት የስርዓቱ የፖለቲካ መቆመሪያ መሣሪያ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ምናልባት ቤት ንብረት ኖሯቸው መንግሥት በፈለገው ሰዐት ለፈለገው ግለሰብ በስጦታም ይሁን በሊዝ ጨረታ መስጠት ቢፈልግ፤ ከይዞታዬ አልነሳም፣ የካሣ ክፍያውም ሆነ የተሰጠኝ ምትክ ቦታ (ዕድለኛ ሆኖ ከተሰጠው) በቂ አይደለም ቢል፣ አስተዳደሩ የፈለገውን ቤት በፖሊስ ኃይል እንዲፈርስ ማድረግ እንዲችል ሥልጣን ሰጥቶታል።
የመሬት ባለቤትነት መብት ችግር መፍትሔ
የመሬትና የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የተለያዩ መፍትሔዎችን ማንሳት ይቻላል።
ሕገመንግሥቱ አንቀፅ 40 ላይ የዜጎችን የመሬት ንብረት ባለቤትነት መብትን የሚነጥቁ ድንጋጌዎች መሻሻል አለባቸው። የሚሻሻሉት ድንጋጌዎችም በማያሻማ መልኩ በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። በተለይም መንግሥት፣ ሕዝብ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚሉ የቃላት ድርድሮች ልዩነታቸውና አንድነታቸው (ካላቸው) በግልጽ መቀመጥና መለየት አላስፈላጊ ድግግሞሽ ወይም የትርጉም አቻ ያላቸው ቃላት መወገድ አለባቸው። በመቀጠልም መሬት በነዋሪዎች ይዞታ ሥር ያለ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት የንብረት ባለቤትነቱ ለራሱ ለግለሰቡ መሰጠት አለበት። መንግሥትም ሆነ የግል ባለሀብቶች የነዋሪዎቹን መሬት ለተለያየ ፕሮጀክቶች ቢፈልጉ በወቅቱ የመሬትና ተያያዥ የንብረት ዋጋ በቀጥታ ከግለሰቡ ጋር ተደራድረው መግዛት አለባቸው። በዚህም ነዋሪው መሬቱን እንደካፒታል በመጠቀም ይንከባከባል፣ ያለማል፣ ቢሸጥ እንኳ ምትክ ቦታ ገዝቶ ቀሪውን ገንዘብ እንደችሎታው የፈለገውን መጠነኛም ሆነ ዝቅተኛ ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይችላል። ለዚህ ደግሞ በንብረቱ ላይ ራሱ እንዲወስን ሙሉ ሥልጣኑ ሊኖረው ይገባል።
በሕዝብ የተያዙ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬቶች የንብረት ባለቤትነቱ የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ መሆን አለበት። የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ሲፈልግ ለልጆቹ መዝናኛ አሊያም ለግጦሽም ሆነ ለሚፈልገው የልማት ፕሮጀክት ማዋል ይችላል። ምናልባት የአካባቢውን ክፍት መሬት መንግሥት ወይም የግል ባለሀብት የሚፈልገው ከሆነ በወቅቱ የመሬት ገበያ ዋጋ ከአካባቢው ነዋሪ ማኅበረሰብ ጋር ተደርድሮ መግዛት ይችላል። መሬቱን የሸጠው የአካባቢው ማኅበረሰብም ገንዘቡን ወደሌላ የገቢ ምንጭ እንዲቀይሩ መንግሥት በነጻ የማማከርና የሙያ ድጋፍ ማድረግ ይችላል፤ ካልሆነ ራሱ ማኅበረሰብ በባለሙያ አስጠንቶ የመረጠውን ሥራ ማከናወን እንዲችል መደረግ አለበት።
በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ያልተያዙ መሬቶች የንብረት ባለቤትነት መብቱ ለመንግሥት ቢሆን፤ መንግሥት ለግል ባለሀብቶችም ሆነ ለተለያዩ ማኅበራዊ ተቋማት ግንባታ ወይም ለመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ማዋል ከፈለገ ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። ነገር ግን ጥቅም ላይ የሚውሉ መሬቶች መጪውን ትውልድ ደኅንነትና የተሻለ ሕይወት ከግምት ያስገባ ሆኖ፣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ ባለሙያዎች የአካባቢ ጥበቃና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናትና ምክር ቢያደርጉ፣ ሕዝቡ በሥራው ላይ በዕውቀት፣ በገንዘብም ሆነ በጉልበት ተሳታፊ እንዲሆን፤ ካልሆነ የሞራል ድጋፍ እንዲሰጥ መመቻቸት አለበት።
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ መሻር ወይም መሻሻል አለበት። ምክንያቱም አዋጁ የግለሰብ የመሬት ንብረት ባለቤትነትን መብት ከመንጠቁ በተጨማሪ መንግሥት ከመደበኛው ሥራው ውጭ የመሬት ቸርቻሪ፣ ካድሬዎችን የሥልጣን መባለጊያ እና የሙስና ምንጭ፣ ለስርዓቱ የመጨቆኛ መሣሪያ፣ ሕዝቡን ደግሞ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥገኛ እንዲሆን አስችሎታልና።
ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶችን በርካሽ ዋጋ ለውጭ ባለሀብት መስጠት የሚያስከትለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ (የአገር ውስጥ የባንክ ብድር ወስደው ስለማይከፍሉ)፣ የማኅበራዊ እና የአካባቢ ጥበቃ ችግር ለመቅረፍ የአገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። በተለይ በአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ የግብርና ሳይንስና ተያያዥ ባለሙያዎች በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት ተደራጅተው ዘመናዊ የግብርና ሥራን እንዲጀምሩ የባንክ ብድርን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ቢደረግላቸው። ምክንያቱም የአገር ውስጥ ባለሙያዎች በግብርና ምርትና ንግድ ዘርፍ ቢሰማሩ፣ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እንዲሁም ፕሮጀክቱን በሚያከናውኗቸው አካባቢ ያሉ ማኅበረሰብን ሕይወት ለማሻሻል እጅግ የተሻሉ ናቸው።
የከተማ ቦታን በሚመለከት መንግሥት ከመሬት ችርቻሮ ወጥቶ የመንግሥትን ሥራ ብቻ እንዲሠራ ቢደረግ፤ የከተማ ነዋሪዎች ራሳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን በሚፈልጉት የሙያ ማኅበርም ሆነ መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሠርተው እንዲኖሩ መደረግ አለበት። መሬትም ከሊዝ ነጻ ቢመቻችና የመኖሪያ ቤት ግንባታን ሊያግዝ የሚችል በረጅም ጊዜ የሚከፈል የባንክ ስርዓትና ብድር ቢመቻች፣ መንግሥት ግንባታዎቹ የከተማውን ደረጃ በጠበቀ መልኩ አካል ጉዳተኞችን እና የአደጋ ጊዜ መከላከልን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎች እንዲከናወኑ ወጥነት ያለው መመሪያ ቢያዘጋጅና መሠረተ ልማቶችን በማመቻቸት ብቻ ቢሳተፍ አሁን ያለውን እና ከዚህ በኋላ የሚኖረውን የቤት ችግር ለመቅረፍ ይረዳል። ከዛ በተጨማሪ በግላቸው ቤት መሥራት ለሚፈልጉና ለሚችሉ መንግሥት የግንባታ ደረጃዎችን በማውጣትና በተመጣጣኝ ዋጋ ነጻ መሬት ቢያቀርብ፣ መንግሥት ነጻ መሬት ማቅረብ ካልቻለ፣ ግለሰቦቹ ከሌሎች ነባር ነዋሪ ከሆኑ የመሬት ባለቤቶች ራሳቸው በቀጥታ ተደራድረው ገዝተው እንዲገነቡና እንዲኖሩ ቢደረግ ሁለቱም አካላት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
መንግሥትም ከዜጎች በሚሰበስበው ግብርና በዜጎች ሥም ከሚያገኘው ብድርና ዕርዳታ የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ ተቋማትን በመገንባት ብቻ እንዲሳተፍ መደረግ አለበት። በግላቸውም ሆነ በማኅበር ተደራጅተው መሥራት ለማይችሉ በመንግሥት ድጎማ እንደየአቅማቸው እንዲደራጁና እንዲመዘገቡ በማድረግ ለግል የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በጨረታ እንዲሠሩ ቢደረግ፣ የሚሠሩ ግንባታዎች ደረጃ ላይም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ቢደረግ፣ የግል የመኖሪያ ቤት ግንባታ ተቋራጭ ድርጅቶች (ሪል ኢስቴቶችም) መሬት በመጠኛ ዋጋ እንዲያገኙ መደረግ አለበት። ድርጅቶቹም በወቅቱ ተመጣጣኝ የገበያ ዋጋ ለቤት ፈላጊዎች እንዲያስተላለፉ ቢደረግ፤ ለዚህም የቤት ግንባታን ብቻ ለማገዝና ለመደጎም የሚችል የባንክ ተቋምና ስርዓት ቢመሠረት ያለውን የቤት ችግር በቶሎ መቅረፍ ይቻላል። መንግሥትም የመኖሪያ ቤት ችግርን የፖለቲካ ፍጆት ከማድረግ ያግደዋል፤ የመንግሥት ግዴታ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በግልፅ እንዲሰፍን ያግዛል የሚል እምነት አለኝ።
በአዲስ አበባ አራዳ ፒያሳን ጨምሮ ከ10 ዓመት በላይ ታጥረው ምንም ዓይነት ግንባታ ያልተከናወነባቸው በርካታ ቦታዎች እያሉ የአቅማቸውን ያህል በከተማ ጥጋጥግ ጎጆ ቀይሰው የሚኖሩ ዜጎችን ክረምት ጠብቆ ለጎዳና ሕይወት መዳረግ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢ ሊሆን አይችልም። ቢቻል በክረምት መኖሪያ ቤት አጥተው ለጎዳና ሕይወት የሚዳረጉትን መታደግ ሲገባ፤ በአዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ በሁለት ወረዳዎች ብቻ 20 እና 30 ሺሕ ነዋሪዎችን ማፈናቀል ከሰብኣዊ መብትም ሆነ ከሞራል አንፃር የሚያስኬድ አይደለም። መንግሥት እየወሰደ ያለው ኃላፊነት የጎደለውን ተግባር ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ቤቶቻቸው ሕገ-ወጥ እንኳ ቢሆን ያለምትክ ቦታና ካሣ እንዲሁም ክረምት ጠብቆ ማፈናቀል የተሳሳተው የመሬት ፖሊሲ ውጤት መሆኑ መታወቅ አለበት።
ስርዓቱን ብቻ አምነው የሕዝቡን የመሬት ባለቤት መብትና ጥቅም ወደጎን በመተው የመሬት ቅርምቱ ላይ የሚሳተፉ የግል ባለሀብቶች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። የስርዓት ለውጥ ቢኖርም ሆነ ያለው ስርዓት ቢቀጥል የሕዝቡ መብትና ጥቅም እስካልተጠበቀ ድረስ መዋዕለ ነዋያቸውን አፍሰሰው ለሚሠሩት ኢንቨስትመንት ዋስትና እንደሌላቸው መረዳት አለባቸው። ምክንያቱም ብዙ የተገፋ ሕዝብ በአንድ ሌሊት ተነስቶ የራሱን እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት የለም። ስለዚህ ቢቻል በቀጥታ ከነዋሪው ካልሆነ የሕዝቡ መብትና ጥቅም መረጋገጡን ሳያረጋግጡ ሕዝብ በተፈናቀለበት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ላይ ገንዘባቸውን ከመበተን ይልቅ ሕዝቡን ባሳተፈ፣ አሊያም የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት ስለመተግበራቸው ቀድመው ቢገነዘቡ ይመከራል።
መንግሥት አሁን ከሚከተለው የመንገድ የተለየ መሻሻልም ሆነ የሕዝብን መብትና ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ለውጥ ማድረግ ካቃተው ወይንም የመንግሥትን ሚና እና ግዴታ መለየት ከተሳነው ሥልጣኑን ለሕዝብ ማስረከብ ብቸኛው አማራጭ መሆን አለበት። አለበለዚያ አሁን በሚከተለው መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ስርዓት በሕዝባዊ ኃይል መፍረስ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል መታሰብ አለበት።
የመሬት ሕጉም ሆነ ፖሊሲው መሻሻል አለበት፤ ካልሆነ ግን መንግሥት ገበሬዎችንም ሆነ የከተማ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉ ይቀጥላል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አለመረጋጋትን ይፈጥራል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በኦሮሚያ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ በአዲስ አበባ እንደክፉ ጠላት ክረምት ጠብቆ እየፈረሱ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን ተከትሎ የሚፈጠረው ቅራኔ ምናልባት ቀኑን እንደነብይ መተንበይ ቢያስቸግርም፤ ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተዛምቶ አዲስ የመሬት ባለቤትነት አብዮት ሊፈጠር ይችላል። ያኔ እንደዛሬው እየሳቁና እያስገደዱ፣ እንዳፈረሱና እንዳፈናቀሉ መቀጠል ላይቀል ይችላል። ምክንያቱም የመሬት ጉዳይ ለስርዓቱ የሥልጣኑ መሠረት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለሕዝብ ደግሞ የመኖርና ያለመኖር የኅልውና ጉዳይ ነው።
የመሬት ቅርምት እና ውጤቱ
ብስራት ወልደሚካኤል
በኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግቢያለሁ ሲል ይሰማል፡፡ በተለይ 11 በመቶ በተደጋጋሚ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግቢያለሁ ፣የምግብ ዋስትናን አረጋግጫለሁ ካለ ሰነባብቷል፡፡ ነገር ግን ተጨባጭ እውነታዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የተባለ ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በመን እና እንዴት እንደመጣ፣ የት ማን ተጠቃሚ ሆነ የሚሉ ጥያቄወች ግን መልስ አይሰጥባቸውም፡፡
በዚህ ሁኔታ ዛሬ ላይ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከ15 ሚሊዮን ወደ 18 ሚሊዮን ማሻቀቡን ዓለም አቀፍ መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡ በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት በኢትዮጵያ የተከሰተው ርሃብ ሀገሪቱ በታሪኳ አይታው በማታውቀው መልኩ ከፍተኛ ህዝብ መራቡን እና አፋጣኝ ምላሽ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገሮችና ተቋማት ካልተሰጠ ችግሩ ከዚህም ሊከፋ እንደሚችል በተደጋጋሚ የተማፅኖ እና ማስጠንቀቂያ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህም በተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮሚ ዕድገት አስመዝግባለች በተባለችው ሀገር ባለሁለት አሀዝ 15 ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ አስፈላጊ መሆኑ አለ6 የተባለውን የቁጥር ዕድገት ገቢራዊ ሳይሆን ምናባዊ ያደርገዋል፡፡
በተለይ ሟቹ አቶ መለስ በስልጣን ላይ በነበሩበት እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ከፍተኛ የሆነ የሀገሪቱን ለም መሬት በሊዝ/በኪራይ ሒሳብ ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡ ከተላለፈው መሬት በተጨማሪ ለግብር እና ኢንዱስትሪ አገልግሎት በሚል ሰፋፊ መሬቶች ከዜጎች ተነጥቀው በመንግሥት የመሬት ባንክ ስር እንዲሆኑ ተደርገው ነበር፡፡
ለሽያጭ የተዘጋጀውና የተሸጠው መሬት መጠን
የማኀበራዊና ተፈጥሮ ሃብት ተመራማሪ ደሳለኝ ራህመቶ 2003 ዓ.ም. (እ.አ.አ. 2011)ጥናት፤ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ ለባለሃብቶች የተዘጋጀው ሰፋፊ ለም መሬት 3, 870, 280 ሄክታር መሬት ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ለባለሃብቶች የተላለፈው/የተሰጠው መሬት በከፊል 1, 342, 370 ሄክታር መሬት ነው፡፡ ይህም በሄክታር በየዓመቱ ከ14 ብር እስከ 135 ብር ዋጋ ከ30-50 ዓመት በሚፈጅ ኪራይ ውል የተላለፈ መሬት ነው፡፡ በመንግሥት እጅ ለሽያጭ/ኪራይ የተዘጋጀው መሬትና ተላልፎ የተሰጠውን መሬት በክልሎች ምን ያህል እንደነበር ያለውን በከፊል እንመልከት፤
ትግራይ ክልል 51, 544 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር ከ30-40 ብር ዋጋ በመንግሥት ቢተመንም፤ በሊዝ የመሬት ኪራይ ለባለሃብት የተላለፈ መሬት የለም፡፡
አፋር ክልል 409, 678 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ እስካሁን ዋጋው ባልታወቀ ሒሳብ ለባለሃብት በሊዝ የተላለፈው መሬት 54, 000 ሄክታር መሬት ነው፡፡
አማራ ክልል 420, 000 ሄክታር መሬት ለባለሃብት በሚል ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር ከ14-79 ብር ዋጋ ተተምኖ ከተዘጋጀው መሬት ላይ ለባለሃብት የተላለፈው 121, 370 ሄክታር መሬት ነው፡፡
ኦሮሚያ ክልል 1, 057, 866 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር ከ70-135 ብር ዋጋ ተተምኖ ከተዘጋጀው መሬት ላይ 380 000 ሄክታር መሬት በሊዝ ተላልፏል፡፡
ደቡብ ክልል 348, 009 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር በዓመት በሄክታር ከ30-117 ብር ዋጋ ተተምኖ 60, 500 ሄክታር መሬት ለባለሃብት ተላልፏል፡፡
ጋምቤላ ክልል 829, 199 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር ከ20-30 ብር ዋጋ ተመን 535, 000 ሄክታር መሬት ለባለሃብት ተላልፏል፡፡
በቤኒሻንጉል ክልል 691, 984 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር ከ15-25 ብር ዋጋ ተመን 191, 500 ሄክታር መሬት ለባለሃብት ተላልፏል፡፡
ኦጋዴን (ሶማሌ) ክልል 26, 000 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ በዓመት በሄክታር ከ16-65 ብር ቢተመንም በሊዝ ለባለሃብት የተላለፈ መሬት የለም፡፡
*ከላይ የተጠቀሰው መረጃ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች (አብዛኞቹ የህወሓት ሰዎች ናቸው) ከ2,000 ሄክታር መሬት በታች በእያንዳንዱ ባለሃብት የተወሰደውን ፣ ለአበባ እርሻ ልማት በየከተሞች አቅራቢያና ገጠር ከገበሬዎች ተነጥቆ የተሰጠውን መሬት ፣ መንግሥት ለስኳር ፕሮጀክት በሚል የወሰደውን 335, 000 ሄክታር መሬት አያጠቃልልም፡፡ መሬቱን ከወሰዱ ባለሃብቶች/ኩባንያዎች መካከል በአፋር ክልል የተሰጠው የግብፅ ብሔራዊ ባንክ እና በኦሮሚያ ክልል ለጥራጥሬ ምርት ከተሰጠው የጅቡቲ መንግሥት በስተቀር እስካሁን ምርታማና ውጤታማ የሆኑ የሉም፡፡ የግብፅ መንግሥት በብሔራዊ ባንኩ አማካኝነት እና የጅቡቲ መንግሥት በቀጥታ የሀገሮቻቸውን የምግብ ፍጆታ ለመደጎም የሚጠቀሙበት እርሻ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የዜጎቹን የምግብ ፍጆታ ለመሸፈን እና የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በመንግሥት ተቋማትም ሆነ በባለሃብቶች በኩል አንዳችም የግብርና መሬት ጥቅም ላይ አላዋለም፡፡ ሰፋፊ ለም መሬት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች የተሰጡትም ቢሆኑ ዋጋቸው እጅግ እርካሽ ከመሆኑ የተነሳ ከውጭ ምግብ ነክ ምርቶችን ወደሀገር ውስጥ ለማስገባት እንኳ የሚበቁ አይደለም፡፡
የአካባቢና ማኀበራዊ ተፅዕኖው
ሁሉም ባለሃብቶች ማለት ይቻላል መሬቶቹን በወሰዱበት አካባቢ የነበሩ ነዋሪዎችን ያለ በቂ ካሳና ምክክር ከማፈናቀላቸው በተጨማሪ ለዘመናት ሲንከባከቡት የነበሩ የተፈጥሮ ደኖች ሙሉ ለሙሉ ተመንጥረው ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፡፡ ይሄም ምናልባት በ10 እና 20 ዓመታት ውስጥ ከማኀበራዊ ተፅዕኖ በተጨማሪ ተፈጥሮን በማዛባት የሀገሪቱ የአየር ንብረትና አካባቢ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ የአካባቢና አየር ንብረት መዛባት ተፅዕኖ ደግሞ እንደ ድርቅ ያሉ ሌላ ተጨማሪ ችግር ይዘው ከመምጣታቸው በተጨማሪ፣ ድርቅን ተከትሎ ምናልባትም ከአሁኑ መላ ካልተዘየደ ሀገሪቱ በታሪኳ አይታ ማታውቀው ርሃብ ሊከሰት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
አስገራሚው ነገር የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም ሆኑ ከውጭ የመጡ ባለሃብቶች ፕሮጀክታቸውን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ ከፍተኛ ብድር ወስደው ያልመለሱና በዛው የጠፉ በርካቶች ሲሆኑ፤ ምንም ሳይሰሩበት/ላይሰሩበት የተፈጥሮ ደኖችን (በተለይ በሰሜን ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢ) መንጥረው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከጥቅም ውጭ አድርገው መሄዳቸው ነው፡፡ ከዚህ ጋ በተያያዘ ሻምፖርጂየተባለ የህንድ ኩባንያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 50 ሺህ ሄክታር ለም መሬት ለግብርና ልማት በሚል ወስዶ የነበረውን ደን መንጥሮና አቃጥሎ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ከሰል ይሸጥ እንደነበርና ከዛም ጥሎ ወደሀገሩ ጠቅልሎ እንደሄደ ይነገራል፡፡ በአካባቢውም ከሰል ነጋዴ ባለሃብቶች በሚል ይተቻሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ተጨማሪ ሌላ ጉዳት ነው፡፡ ይህ ምንግሥት እሰራዋለሁ ላለው ስኳር ፕሮጀክት (ከሰም፣ ደቡብ ኦሞ እና ወልቃይት ) እና ኢሉባቦር ለማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም በሚል ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ያደረጋቸውን ደኖች ሳይካትት ነው፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶቹም ሆኑ የማዳበሪያ ፋብሪካዎቹ የተፈጥሮ ደኖችን ከማውደም እና የአካባቢውን ነዋሪዎቸ ከማፈናቀል ባለፈ እስካሁን የታየ ምንም አዎንታዊ ውጤት የለም፡፡
ከላይ የተጠቀሱ እና ለባለሃብቶች በሊዝ መልክ የተላለፉ መሬቶች ውጤታማ ሆነው ቢታዩ ኖሮ የመንግሥት ዓላማና ግብ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው ሀገሪቱ ላይ እየተተገበረ ያለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና የኢኮኖሚ ፖሊሲው ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ እና መንግሥት እስካሁንም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በስሩ ካሉ የመገናኛ ብዙኃን ከሚነገረው ወሬ በስተቀር በተግባር ይሄ ነው የሚባል ጅማሮም ሆነ ውጤት የለም፡፡
በተለይ ከመሬት ቅርምቱ ጋ በተያያዘ ሶስት ተጨማሪ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡
መንግሥት ሰፋፊና ለም የሆኑ የሀገሪቱን መሬት እጅግ ዝቅተኛ በሆኑ ዋጋ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ድረስ ለመስጠቱ በዋናነት የሚሰጠው ምክንያት ፤
– ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር/የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ
– በግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት
– የግብርና ምርትን በማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት የሚል ነበር፡፡
ነገር ግን ከተጠቀሱት ምክንያቶች ስኬታማ የሆኑ የሉም፡፡ በአንፃሩ በማኀበረሰቡ እና በአካባቢው ላያ ያደረሱት ጉዳት ግን አለ፡፡ በመሬት ቅርምቱ ከደረሱ ጉዳቶች መካከል ጥቂቶቹ፡
ነዋሪዎችን ያለበቂ ካሳና ምክር አገልግሎት ማፈናቀል ይገኝበታል፡፡ ከዚህ ጋ በተያያዘ በዋነኛነት በጋምቤላና ደቡብ ኦሞ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡
በጋምቤላ ወደ 225, 000 የአካባቢው ነዋሪዎች ያለበቂ ካሳና፣ ምክክርና ስምምነት ተፈናቅለዋል፡፡ ይህንም ተከትሎ ከ 8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ተፈናቃዮች ሀገር ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገሮች በተለይም ወደ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ተሰደዋል፡፡ የመሬት መፈናቀሉን ከተቃወሙ ከክልሉ ነዋሪዎች መካከል ፤ ከመንግሥት በተለይም ከወቅቱ ጠቅላ ሚኒስትር በነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል እርምጃ 424 የአኝዋክ ማኀበረሰብ አባላት በተመሳሳይ ቀን በጅምላ ተገድለዋል፡፡ በርካታ ሰዎችም በጋምቤላና አዲስ አበባ በሚገኙ ወህኒ ቤቶች ታስረዋል፡፡ ይህ ድርጊት የተፈፀመው በአብዛኛው በዛው በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ነዋሪዎች ነበሩ፡፡
በትውልድ ኢትዮጵ በዜግነት ሳውዲ ዓረቢያዊ የሆኑት መሐመድ አሊ አላሙዲ ንብረት የሆነው ሳውዲ ስታር ኩባንያ ከዚሁ ከጋምቤላ ብቻ 139 ሺህ ሄክታር መሬት ሩዝ እና አኩሪ አተር አምርተው የሰውዲ ዓረቢዎችን የምግብ ፍጆታ ለመሸፈን ታቅዶ ቢከናወንም ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ 10 ሺህ ሄክታር መሬት ጠይቆ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዛና ፈቃድ ያለ ኩባንያው ፍላጎት 300 ሺህ ሄክታር መሬት ቢሰጣቸውም ውጤታማ አልሆኑም፡፡ ይህ ኩባንያ በቅርቡ 100 ሺህ ሄክታር መሬት መነጠቁን ተከትሎ በኩባንያው ባለቤት ካራቱሪና በመንግሥት በኩል አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ ሁለቱም ኩባንያዎች በርካታ ነዋሪዎችን አፈናቅለዋል፣ የተፈጥሮ ደኖችን ከጥቅም ውጭ አድርገዋል፡፡
በደቡብ ኦሞ ሸለቆ በተለይ በደቡብ ኦሞ ዞን ልክ እንደጋምቤላው ያለበቂ ካሳና ምክክር ከ200, 000 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ማፈናቀሉን ከተቃወሙት መካከል በተለይ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት ግንባታ አካባቢ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነዋሪዎች በተመሳሳይ ወታደራዊ እርምጃ ተገድለዋል፡፡ የመሬት ቅርምቱን የተቃወሙ ተፈናቃዮች መካከል በደቡብ ኦሞ እና ሐዋሳ በሚገኙ ወህኒ ቤቶች በርካቶች ሲታሰሩ፣ ከእስርና ግድያ ያመለጡ ደግሞ ወደጎረቤት ኬንያ ተሰደዋል፡፡
ሰፋፊ ለም መሬቶቹ ለባለሃብቶች ተሰጥተው፣ በመሬቱ ስም ከሀገሪቱ ከፍተኛ የባንክ ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እስካሁን ባሉ መረጃዎች ከጅቡቲ መንግሥት እና ከግብፁ ብሔራዊ ባንክ መሬቶች በስተቀር በሌሎቹ መሬቶች ከባንክ ብድር ተወስዶባቸው በርካቶቹ ብድሮች አልተመለሱም፡፡ የባንክ ብድርንም ሆነ የመሬት ኪራይ ክፍያን ባለመፈፀም መሬት የተሰጣቸው የተለያዩ የህንድ ኩባንያዎችና የህወሓት ሰዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ከዚሁ ሰፋፊ የመሬት ቅርምት ጋር በተያያዘ ዜጎች በግፍ ተፈናቅለዋል፣እየተፈናቀሉም ይገኛሉ፡፡ የባለሃብቶችን ድምፅ የሚሰማ አካል ቢኖርም የዜጎችን ድምፅና አቤቱታ እንዲሁም መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅ አካል ግን አልተገኘም፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር አብይ ምክንያት ከ”ህገ መንግሥት” እስከ ኢህአዴግ ፖሊሲ መሬት “የመንግሥትና የህዝብ ነው፣ መሬት አይሸጥም አይለወጥም” በሚል ፈሊጥ እያንዳንዱ ዜጋ የመሬቱ ባለቤትነቱ በአዋጅ እንዲነጠቅ መደረጉ ነው፡፡
በህወሓት/ኢህአዴግ ቋንቋ መሬት የመንግሥትና የህዝብ ነው፤ መንግሥትና ህዝብ ደግሞ ህወሓት ነው፡፡ ዜጋው እየኖረበት ያለበት መሬት ባለቤትነቱ በመነጠቁና በሱስ ስም “መንግሥት” እና “ህዝብ” የሚል ምናባዊ ተቋም አማካኝነት በላዩ ላይ ቤቱ ከነንብረቱ ያለማንም ከልካይ ይሸጣል፣ ይለወጣል፣ ይሄንን ተቃውሞ ጥያቄ የሚያቀርብ ደግሞ ይገደላል፣ አሊያም ይታሰራል፣ በለስ ቀንቶት ከነኚህ ርምጃዎች ካመለጠ ወደጎረቤት ሀገር ጥገኝነት ፍለጋ ይሰደዳል፡፡
ዜጎች ለምን የመሬታቸው ባለቤት አልሆኑም?
ዜጎች የመሬታቸው ባለቤቶች አለመሆናቸውና በመሬታቸው ላይ ማዘዝና መወሰን አለመቻላቸው ራሳቸውን እንደ ዜጋ የሚያዩበት አሊያም የሀገሪቱ ሉዓላዊ ግዛት ባለቤት ስለመሆናቸው የሚያስችል መብት ሙሉ ለሙሉ በህገ መንግሥቱ አዋጅ ተነጥቋል፡፡ በዚህም ከስነ ልቡና በተጨማሪ የገበሬዎች መሬት ምርታማነት ላይ ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ምክንያቱም መሬቱን የራሱ አድርጎ መወሰንና ማዘዝ እንዲሁም ከባንክ ብድር ማግኘትም ሆነ መሸጥ የሚያስችል መብት በመነፈጉ ከእለት ጉርስ ባለፈ ስለ ምርታማነት የመጨነቅ ስሜት አይስተዋልበትም፡፡ ከባለፈው ህዳር ወር 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ መነሻው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚል ክልል ልዩ ዞን የተቀናጀ መስተር ፕላን ይደረግ እንጂ ዋናው ምክንያት ዜጎች የመሬት ባለቤትነታቸው ተነጥቆ በተደጋጋሚ በግፍ መፈናቀላቸው ነው፡፡ ይሄ ዛሬ በአንድ ክልል ተጀመረ እንጂ ብሶቱ ከልክ እያለፈ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ነገ መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ መፍትሄ ማስት ፕላኑን ማቆም ወይም የስርዓቱን ሰዎች ሰብስቦ የፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ዜና እወጃ ሳይሆን መሰረታዊ የህገ መንግሥትና የፖሊሲ መሻሻል ነው፡፡
በኢትዮጵያ መሬት የእያንዳንዱ ባለ ይዞታ/ባለቤት ንብረት መሆኑን፣መሬትን የሚሸጥም ሆነ የሚሰጥ ራሱ ባለቡቱ እንደሆነ፣ መንግሥት ለከተማ መኖሪያና ማኀበራዊ አገልግሎት ተቋማት መገንባት ቢፈልግ ከባለይዞታቸው ተደራድሮ በገበያ ዋጋ እንዲገዛ ቢደረግ፣ ተቋማቱን ለመገንባት ዜጎች ተገቢውን ግብር እየከፈሉ ስለሆነ፣ በመሬታቸው ላይ የመወሰንና የማዘዝ ሙሉ ስልጣን ለእያንዳንዱ ዜጋ መሰጠት አለበት፡፡ አሁን ባለወ ነባራዊ ሁኔታ የሀገሪቱ መሬት ከፊውዳላዊ ስርዓት እጅግ የከፋ እንጂ የተሻለ ነገር የለውም፡፡ ምክንያቱም በፊውዳሉ ስርኣት ዜጎች የመሬታቸው ባለቤቶች አልነበሩም፣ ዛሬም አይደሉም፡፡ ይሄ ተለወጦ በደርግ ዘመን የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም. የታወጀው የመሬት ላራሹ አዋጅ እንደገና ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ በግለሰቦችና በማኀበረሰቦች(ለግብርና እና ማኀበራዊ አገልግሎት) ያልተያዙ ቦታዎችን መንግሥት ለማኀበራዊ አግልግሎት ለማዋል ቢወስን ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለበት መልኩ እንዲከናወን ግልፅ የሆነ ህጋዊ ማዕቀፍ ሊኖረው ይገባል፡፡ አሁን ያለው የጠባብ ፖለቲካዊ ቤተሰብ ግንኙነት ውርስ አሰራር መቆምና በግፍ የተወሰደው መሬት ለተፈናቃዮችና ባለቤቶች መመለስ እና አሰራሩ መከለስ ይኖርበታል፡፡
በሌላ በኩል የተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች በግብርና ሙያ በርካታ ተማሪዎችን እያስተማሩ ቢያስመርቁም፤ ባለሙያዎቹ የቀሰሙትን እውቀት አሟጠው እንዲጠቀሙ፣ ሀገሪቱንም እንዲጠቅሙ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የመሬት አቅርቦትም ሆነ የባንክ ብድር በመንግሥት አልተመቻቸም ሳይሆን አልተፈቀደላቸውም፡፡ በሌላ በኩል ከግብርናው ጋርም ሆነ ከንግድ ጋ ምንም እውቀት የሌላቸው የህወሃት ሰዎች በፈለጉት ሰዓት የፈለጉትን መሬት ለሚፈልጉት ዓላማ በፈለጉት ቦታ ሲያገኙ፣ የባንክ ብድርም በፈለጉት ሰዓት ያገኛሉ፤ በተመሳሳይ የውጭ ባለሃብቶችም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን መስዋዕት አድርገው ከ16 ዓመታት ያላነሰ በእውቀት ማዕድ ላይ የነበሩና ያሉ ዜጎች አብዛኞቹ ስራ አጥ ሆነው ስራ ለማግኘት መንግሥት እንዲጠብቁ ሲፈረድባቸው፣ በለስ የቀናቸውም ቢሆኑ አውቀታቸው በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋዕል የሚያስችል መንግሥታዊ አገልግሎት ባለመኖሩ ቢሮ ገብቶ ወርሃዊ ደመወዝ በመጠበቅ ሙሉ ለሙሉ መንግሥት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ይገደዳሉ፡፡
በሀገሪቱ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ ኢኮኖሚውን በተመለከተ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚያስችል ፖሊሲ ባለመኖሩ ከሌሎች ሀገረች ሲነፃፀር እንደ ኢትዮጵያ በእውቀትና በትምህርት ኪሳራ የደረሰባትም ሆነ የሚደርስባት ሀገር ስለመኖሯ አጠራጣሪ ነው፡፡ ቢያንስ በግብርና ሙያ የሚመረቁ ባለሙያዎች በየመስካቸው በቂ የመሬት አቅርቦት እና የባንክ ብድር ቢመቻችላቸው ከራሳቸው አልፈው ሀገሪቱን በብዙ መልኩ መጥቀም በቻሉ ነበር፡፡ ምናልባት የተሻለ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ቢያስፈልግ እንኳ እዛው በሚማሩበት የትምህርት ተቋም ማመቻቸት አሊያም ለተጨማሪ አጫጭር የሙያ ስልጠናዎቹን ሊሰጡ የሚችሉ በዘርፉ ውጤታማና ከእኛ ልቀው ካሉ ሀገሮች ባለሙያዎችን አምጥቶ አሰልጥኖ ወደስራ እንዲገቡ ቢደረግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ፣ የዜጎችን መብትና ጥቀምን ለማስጠበቅና ለመጠበቅ እጅግ የተሸሉ ቢሆኑ እንጂ የሚያንሱ አይደሉም፡፡ የአካባቢና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ላይም ቢሆን በተገቢው መንገድ እንዲከናወን በማድረግም ሆነ ጥራት ያለው ምርት አምርቶ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘትም ቢሆኑ ከውጭ ባለሃብቶችም ሆነ በፖለቲካ ወገንተኝነት ከሚደረግ የጥቅም ትስስር በእጅግ የዘርፉ ተማሪዎች ውጤታማ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡
በርግጥ ዜጎች ሁሉ በፖለቲካው፣ በኢኪኖሚውም ሆነ በማኀበራዊ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ስርዓቱ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ከሚሰራ እና ራሱን የአናሳ ብሔር ተወካይ አድርጎ በዘረኝነት ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በተጠመደ ህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን ከላይ የተጠቀሰውን ቀና አስተሰሰብ መጠበቅ የዋህነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ጥቅሙ ለባለሙያዎቹ፣ ለሀገሪቱም፣ ለህዝቡም ሆነ ለራሳቸው የተሻለ ጥቅም ያለውና አዋጭ መፍትሄ ነው፡፡ መፍትሄዎቹ ላለፉት 25 ዓመታት ባለመወሰዳቸው የመሬት ቅርምቱ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል፣ የተለመደው የኪሳራ አካሄድ አሁንም በተጠናከረ መንገድ ቀጥሏል፡፡ የዚህ ሁሉ መዘዝ ግን አንዱን አካባቢ ብቻ ነጥሎ ጉዳት የሚያደርስ ሳይሆን አጠቃላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ማኀበራዊ ጉዳይ ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳረፉ አልቀረም፡፡ የመሬት ባለቤትነት የህግ ማሻሻያ እና የፖሊሲ ለውጥ ካልተደረገ ዜጎች ከመሬታቸው በግፍ የመፈናቀል እና የመሬት ቅርምቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡