Tag Archives: Gambella Land grabbing

እነ ኦሞት አግዋ ካቀረቡት አሰራ አንድ የከስ መቃወሚያ አስሩን ፍርደቤቱ ውድቅ አደረገው

ክሳቸው ከነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አየታየ የሚገኛው የእነ ኦሞት አግዋ ሶስት ተከሳሾች ያሉበት(ኦሞት አጉዋ፣ አሽኔ አስቲን እና ጀማል ኡመር ) ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ አቃቤህግ ከሰጠው ምላሽ ጋር መርምሮ ምላሽ ለመስጠት ለዛሬ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም የቀጠረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያዎች ከአንዱ በሰተቀር ሁሉንም አለመቀበሉን እና ውድቅ ማድረጉን የመሃል ዳኛው ታረቀኝ አማረ በንባብ ለችሎቱ አሰምተዋል፡፡

Omot Aguwa et al

እነ አቶ ኦሞት አግዋ አዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታስረው ሲቀርቡ

በፍርድ ቤቱ ከአንድ መቃወሚያ በሰተቀር መቃወሚያዎቹ ውድቅ እንዲሆኑ እና ተቀባይነት እንዳያገኙ ምክኒያት የሆነው አቃቤ ህግ በማስረጃ ማሰማት ሂደት ላይ በዝርዝር እንድንሰማቸው ያደረጋል የሚል ነው፡፡
ተከሳሾች ክሳችን በእያንዳዳችን በተናጠል ቀርቦብን ሳለ አቃቤ ህግ በጋራ የከሰሰን ክስ ተነጣጥሎ ለየብቻ እንድንከሰስ ይደረግ የሚለውን የተከሳሾች መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ህጉን አንቀፅ 211 ቁጥር 7/3 በመጥቀስ ወንጀሎቹ የተለያዩ ቢሆንም የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) የጠራው ስብሰባ ላይ ኬንያ ፣ናይሮቢ ለመሳተፍ ሲሄዱ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን ጠቅሶ ተከሳሾቹ በአንድ መዝገብ ሊከሰሱ ይችላሉ በማለት ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን መቃወሚያ አልተቀበለም፡፡

ተከሳሾች አባል ሆነውበታል በሚል የተጠቀሰው የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ቡድን ህልውና እንዳለው አቃቤ ህግ በክሱ እንዲያስርዳ በተቃውሞቸው የጠየቁት ተከሳሾች፣ ቡድኑ በፍርድ ቤትም ሽብርተኛ ተበሎ አለመሰየሙን ጠቅሰው ከክሱ ላይ እንዲሰረዘላቸው ላቀረቡት መቃወሚያ ፍርድቤቱ የቡድኑን ህልውና እና ዝርዝር ማሰረጃ በክሱ ሂደት የሚሰሙ ናቸው በማለት ተቃውሞውን አለተቀበለም፡፡

በኢሜል አና በስካይፒ የተለያዩ ግንኙነቶችን ፈጥረዋል ብሎ አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ያሰቀመጠውን ተከሳሾች ከማን ጋር ግንኙነት እንዳደርጉ ሰላልጠቀሰ በክሱ ከማን ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው በዝርዝር እንዲጠቀስ በክስ ተቃወሞው ላይ ያቀረቡትንም ተቃውሞ እንድሌሎቹ የክስ መቃወሚያዎች በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ የክሱ መሰረታዊ ስህተት አይደለም፣በማሰረጃ ማሰማት ሂደት ላይ እምንሰማቸው ዝርዝሮች ናቸው በማለት ተቃውሞውን ውድቅ አድርጓል፡፡

በመጨረሻም ተከሳሾች ካቀረቡት አስራ አንድ መቃወሚያዎች ፍርድቤቱ የተቀበለው በክሱ ላይ አንደኛ ተከሳሽ ኦሞት አግዋ አሰቀጠራቸው የተባሉት የፖሊስ አባላት ስም ዝርዝር በክሱ ተካቶ ይቅረብልን በለው ያቀርቡትን ተቃውሞ ሲሆን ፍርድቤቱ አቃቤህግ ለጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በክሱ ላይ የተጠቀሱትን የፖሊስ አባላት ስም ዝርዝር በክሱ አካቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥል፡፡
EHRP

በችግር የተተበተበው የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት

ዮሐንስ አንበርብር

– ከ630 ሺሕ ሔክታር መሬት የለማው 76 ሺሕ ሔክታር ብቻ ነው
– መሬቱን የተረከቡ ባለሀብቶች 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር አግኝተዋል
– የቀረጥ ነፃ መብትን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ተገኝተዋል

picture-11

በጋምቤላ ክልል ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንት በአቋራጭ ለመበልፀግ የጓጉ ባለሀብቶችን የሳበ፣ ከባንኮች የተወሰደውን ብድር ላልተገባ ዓላማ እንዲውል ያደረገና በኪራይ ሰብሳቢነት የተተበተበ እንደነበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥናት አመለከተ፡፡
ጥናቱ እንዲካሄድ የወሰኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሆናቸውን፣ 14 ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተወከሉበትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተውጣጡ ባለሙያዎች ያካሄዱት መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በጥናቱ መሠረት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለ623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት የተላለፈ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 409,706 ሔክታር በጋምቤላ ክልል መተላለፉን፣ ቀሪው 220,812 ሔክታር ደግሞ የፌዴራል የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በውክልና ከወሰደው መሬት ያስተላለፈው መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ከተላለፈው መሬት ውስጥ እስከ 2008 ዓ.ም. በድምሩ መልማት የቻለው 76,862 ሔክታር ብቻ መሆኑን የጥናት ውጤቱ ይጠቁማል፡፡

መሬቱ ላለመልማቱ በጥናቱ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ባለሀብቶች ለልማቱ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ አብዛኛው ባለሀብት መሬት የሚወስደው አልምቶ ራሱንና አገርን ለመጥቀም ሳይሆን ከባንክ ብድርና ከቀረጥ ነፃ መብት ጋር ተያይዞ የሚገኘውን ጥቅም በማጋበስ በአቋራጭ ለመክበር እንደሆነ ይገኙበታል፡፡
የመሬትና የይዞታ ካርታ መደራረብ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉትም ተጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደርና ደን ልማት ቢሮ ከተመዘገቡ 651 ይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ውስጥ 381 የሚሆኑት ካርታዎች በተለያየ መጠን እርስ በርሳቸው የተደራረቡ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
መሬት ከተረከቡት 623 ባለሀብቶች የእርሻ መሣሪያ ያላቸው 226 ሲሆኑ፣ የእርሻ መሣሪያ የሌላቸው 397 መሆናቸውን ተገልጿል፡፡ ከአጠቃላይ የእርሻ ኢንቨስትመንቶቹ ውስጥ 479 የሚሆኑት ሥራ አስኪያጅ እንደሌላቸው ተጠቁሟል፡፡

ባለሀብቶቹ ከቀረጥ ነፃ መብት የመበዝበዝ አዝማሚያ እንዳላቸው የሚገልጸው ጥናቱ፣ ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 29 ባለሀብቶች የት እንደሆኑ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከወሰዱት መሬት በላይ ትራክተሮችን ወይም ሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስገቡ፣ እነዚህ ትራክተሮች እንዲሁም እንደ ፒክአፕና ሲኖትራክ ያሉ ተሽከርካዎች ደግሞ በእርሻ ቦታው እንደሌሉ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ከሁሉም በላይ አሳዛኝ ገጽታን የያዘው ከባንክ ብድር አለቃቀቅ ጋር በታያዘዘ ጥናቱ የደረሰበት ግኝት ነው፡፡ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ባላቸው ስምንት ወረዳዎች በተገኘው የመስክ መረጃ መሠረት ከ623 ባለሀብቶች ውስጥ 200 የባንክ ብድር አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 27 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ 161 ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጅማ ቅርንጫፍና 12 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ጥናቱ ይዘረዝራል፡፡

ከ200 የባንክ ብድር ከተሰጣቸው ባለሀብቶች መካከል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሁለት ተበዳሪዎች በባንክ ዝርዝር ውስጥ ያልተገኙ ቢሆንም፣ በመስክ በተደረገው ማጣራት ተበዳሪ ሆነው መገኘታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ለ200 ባለሀብቶች ለመሬት ልማት፣ ለካምፕ ግንባታ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለማሽነሪ፣ ለሥራ ማስኬጃና ሌሎች ወጪዎች የተፈቀደላቸው ብድር 4.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ እነዚሁ 200 ባለሀብቶች የተረከቡት መሬት 454,261 ሔክታር ሲሆን፣ 194 ለሚሆኑት የዚህ መሬት ባለቤቶች 1.99 ቢሊዮን ብር ብድር መለቀቁን ይገልጻል፡፡ በዚህ ብድር እስከ 2008 ዓ.ም. ብቻ 314,645 ሔክታር መሬት መልማት የሚጠቀምበት ቢሆንም፣ እስካሁን የለማው ግን 55,129 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
ለሥራ ማስኬጃና ለሌሎች ወጪዎች በሚል ርዕስ 1.16 ቢሊዮን ብር ብድር የተለቀቀ ቢሆንም፣ ለምን ዓላማ እንደዋለ ግን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ለካምፕ ማደራጃ ተብሎ የተለቀቀው ብድር 326,876,702 ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 180 ካምፖች በብሎኬትና በቆርቆሮ ሌሎች 19 የሚሆኑት ደግሞ በሳርና በቆርቆሮ መሠራታቸውን ይገልጻል፡፡
በልማት ባንክ ብድር 122፣ እንዲሁም በንግድ ባንክ 62፣ በድምሩ 184 ተሽከርካሪዎች ተገዝተው የተሰራጩ ቢሆንም፣ በመስክ ምልከታ የተገኙት 159 መሆናቸውን ጥናቱ ያስረዳል፡፡

‹‹የብድር ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ስናስገባ በቀጥታ በስልክ ተደውሎ ጉቦ ካልከፈልክ ለሥራ አስኪያጁ አይቀርብልህም፤›› በማለት አጥኝዎቹ ያነጋገሯቸው መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በተመሳሳይም ‹‹መሬቱን ተገኝተው ሳያዩት ውኃ ይተኛበታል፣ በስልክ ጥቆማ ደርሶናል፤›› በማለት ገንዘብ ካልተሰጣቸው ብድር  እንደማይፈቀድላቸው ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

የጥናት ዝርዝሩ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ከኃላፊነታቸው የተነሱትን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህርን ያካተተ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች በውል ተረክቦ የሚያስተዳድረው መሬት ውል እንዲቋረጥና ክልሎች እንዲያስተዳድሩ ወስኗል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሚና ክልሎችን ማገዝ እንዲሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ለባለሀብቶች የሚሰጥ ብድር ጠንካራ ክትትል እንዲደረግበት፣ እንዲሁም ለተባለው ዓላማ ያልዋሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ክትትል በማድረግ ዕርምጃ እንዲወስድ አዘዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ለሪፖርተር ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹በውይይቱ ወቅት የተሰጡን አቅጣጫዎች አሉ፡፡ በእኛ በኩል ያሉ ችግሮችን ገምግመን የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንወስዳለን፤›› ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ ገልጸዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ውድነህ ዘነበ አስተዋጽኦ አድርጓል)

ምንጭ፡  ሪፖርተር ጋዜጣ

%d bloggers like this: