Tag Archives: Eyerusalem Tesfaw

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ መከላከል አትችሉም ተባሉ

ማህሌት ፋንታሁን

የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ( ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ) አቃቢ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በአንድ የሰው ምስክር ማስረጃዎች አስረድቷል በሚል ተከሳሾች መከላከል ይገባቸዋል ሲል ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

Eyerusalem Tesfaw

ውሳኔውን ተከትሎም መከላከያ ማስረጃዎች ያቀርቡ እንደሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ጠይቆ፣ ተከሳሾች 200 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በጋራ እንደሚያቀርቡ አሳውቀው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በነበሩ ቀጠሮዎችም ምስክሮቻቸውን በዝርዝር አስገብተው ነበር፡፡ እንዲሁም ከዛሬ ግንቦት 30 እስከ ሰኔ 8 ቀን 2008ዓ.ም. ድረስ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፤ የቀጠሯቸው ቀን ሳይደርስ፤ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበው ጭብጥ እንዲያሲዙ ተጠይቀዋል። እነሱም የምስክርነት ጭብጥ ምስክሮች መሃላ ሳይፈፅሙ መያዝ እንደሌለበት ለፍቤቱ አስረድተው ውሳኔውን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥረው ነበር።

Birhan Tekleyared, et.al

ይሁን እንጂ አራት ወር ሙሉ ፍርድ ቤቱ ሲሰጥ ከነበረው ትዕዛዝ በተለየ “መከላከያ ምስክር ማሰማት የለባችሁም ስለዚህ ለፍርድ ብይን ሃምሌ 13, 2008 ቅረቡ” የሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
ምንጭ፡-ከማህሌት ፋንታሁን ፌስቡክ ገፅ የተወሰደ

ነባር የኢሕአዴግ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለመከላከያ ምስክርነት ተቆጠሩ

ምሁራንና ፖለቲከኞችም ተካተዋል

በታምሩ ጽጌ

TPLF_EPRDF Juntas

ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ማይካድራ በተባለ ቦታ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተለገጸውና በሽብር ድርጊት ወንጀል የተከሰሱ አራት ተጠርጣሪዎች፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ ስብሀት ነጋ (አቦይ ስብሃት)፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ ጄነራል ሳሞራ የኑስንና ሌሎችንም ነባር ታጋዮችንና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ 141 ሰዎች በመከላከያ ምስክርነት ቆጠሩ፡፡

መከላከያ ምስክሮቹን የቆጠሩት ተጠርጣሪዎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት የነበሩት አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ሪት እየሩሳሌም ተስፋውና አቶ ፍቅረማርያም አስማማው ናቸው፡፡ በክሱ ከላይ የተጠቀሱትን ተጠርጣሪዎች ወደ ኤርትራ ድንበር እንዲሻገሩ በመምራት የተጠረጠረው አቶ ደሴ ካህሳይም ተካቷል፡፡
ተከሳሾቹ ከዓመት በፊት የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ወንጀል ሆኖ የተደነገገውን ለሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍን ተላልፈዋል በሚል ነው፡፡

ተከሳሾቹ ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ፖለቲካዊ ሥልጣን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ካለው የግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት መዘጋጀታቸውም ተጠቅሷል፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስተው በባህር ዳር፣ በጎንደርና በሁመራ አድርገው ወደ ኤርትራ ለመሻገር ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የመረመረው ፍርድ ቤቱ፣ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን (141) በዝርዝር ጽፈው አቅርበዋል፡፡ ከምስክሮቻቸው መካከል ለአቶ በረከት ስምዖን፣ ለአቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ለአቶ አዲሱ ለገሰ፣ ለወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ ለአቶ ተፈራ ዋልዋ፣ ለአቶ ስብሀት ነጋ (አቦይ ስብሀት)፣ ለወ/ሮ ፍሬ ሕይወት አያሌው፣ ለዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ለጄኔራል ሳሞራ የኑስና ለአቶ ቴዎድሮስ ሐጐስ እነሱ መጥሪያ ለማድረስ እንደማይችሉ (ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመሆናቸው) በፍርድ ቤቱ በኩል እንዲደርሳቸው እንዲደረግ አመልክተዋል፡፡

ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ለዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ለአቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ ለአቶ ገብሩ አሥራት፣ ለወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ (ቃሊቲ)፣ ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ቃሊቲ)፣ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ዝዋይ)፣ ለአምስት ጦማሪያን፣ ለጠበቃ ተማም አባቡልጉ፣ ለኢንጂነር ይልቃል ጌትነት (ሰማያዊ ፓርቲ) ጨምሮ በድምሩ 141 የመከላከያ ምስክሮችን በመቁጠር ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ ረቡዕ ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ተከላከሉ ተባሉ

*ተከሳሾች 200 የሰው መከላከያ ምስክሮች አሉን ብለዋል

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን አቋርጠው ኤርትራ የሚገኘውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ ሊቀላቀሉ ከአዲስ አበባ ተነስተው ሲጓዙ ማይካድራ የሚባል የድንበር ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሶ የፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የመሰረተባቸው እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ዛሬ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾቹ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ሪት እየሩሳሌም ተስፋው፣ አቶ ፍቅረማርያም አስማማው እና አቶ ደሴ ካህሳይ አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን ክስ በሰነድና በአንድ የሰው ምስክር ማስረጃዎች አስረድቷል በሚል ተከሳሾች መከላከል ይገባቸዋል ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

Birhanu Tekleyared, et.al

ተከሳሾች 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታ አቅርበው እንደነበር በማስታወስ ይህ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ችሎቱ ብይኑን እንዳያሰማ ቢጠይቁም፣ ችሎቱ ‹‹አቤቱታው ቶሎ ብይን እንዲሰጣችሁ የሚጠይቅ ነው፣ በመሆኑም ብይኑ ተሰርቷል›› ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ተከሳሾች ብይኑ አይሰማብን የሚለውን ጥያቄ ባለመቀበል ችሎቱ ብይኑን በንባብ አሰምቷል፡፡

እነ ብርሃኑ ተከላከሉ መባላቸውን ተከትሎ መከላከያ ማስረጃዎች ያቀርቡ ከሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ጠይቆ፣ ተከሳሾች 200 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በጋራ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መከላከያ ማስረጃዎችን ለማድመጥ ለመጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች እያዘጋጁት የነበሩት የተከሳሽነት ቃል ጽሁፍ በማረሚያ ቤት ፖሊሶች እንደተወሰደባቸው ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ ከዚህም በኋላ ተመሳሳይ ለችሎት የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ማዘጋጀት እንዲችሉ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ችሎት የቀረቡት እነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን እና እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ 14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀየርላቸው አቤቱታቸውን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ብይን ለማሰማት ለየካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

%d bloggers like this: