ድብቁ የኢትዮጵያ እስር ቤት ግፍ እና የወልቃይቱ ተወላጅ ዘካርያስ ገብረፃዲቅ
ለገሠ ወልደሃና
አቶ ዘካርያስ ገብረፃዲቅ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ነው። በአዲስ አበባ በንግድ ስራ ተሠማርቶ ውጤታማ ነገዴ መሆን የቻለ ሰው ነበር። በአዲስ አበባ ላይ ጎጆ ቀልሶ ንግዱን እያከናወነ ይኖር የነበረው አቶ ዘካርያስ ነሐሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በደህንነቶች ቁጥጥር ስር ዋለ። በቁጥጥር ስር ያዋሉት ግለሰቦች መጀመሪያ አዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን (በተለምዶ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ)አሰሩት። ከተወሰነ ወራት በኋላ ወደ ቦሌ ፓሊስ መምሪያ ቀየሩት። እንደገና ከወራት በኋላ አራዳ ክ/ከተማ የሚገኝ ፓሊስ ጣቢያ አዛወሩት። ከዚህም ከወራት በኋላ ልደታ ክ/ከተማ የሚገኝ ፓሊስ ጣቢያ ያዛወራል። ከልደታ ወደ ቃሊቲ ተወስዶ ለወራት ከታሰረ በኋላ ወደ ቅሊንጦ በመጨረሻም አሁን ወደሚገኝበት ቃሊቲ አዛውረው ያስሩታል።
ከእስር ቤት እስር ቤት እያዘዋወሩ ያሰሩት አቶ ዘካርያስ ከሶስት አመት ክርክር በኋላ ፍርድ ቤት ነፃ ይለዋል። “እስካሁን ያሰረኝን ሳላውቅ። ሶስት አመት ተንገላታሁ። አሁን ነፃ ተብያለሁ። ፍቱኝ” የሚል ጥያቄ ያቀርባል። “አዎ! በዚህ ነፃ ተብለሃል። ግን ተጠይቆብሃል ተብሎ ፍች ሲጠብቅ በይግባኝ እስር ቤት ሆኖ ለ2 ዓመት በክርክር ያሳልፋል። ከ5 ዓመት እስር በኋላ ነፃ ይወጣል። “አሁን ነፃ ወጥቻለሁ ፍቱኝ!” የሚል ጥያቄ ያቀርባል። “አዎ በዚህ ክስ ነፃ ተብለሃል!ግን ሌላ የ17 ዓመት ፍርድ አለብህ!” ይባላል።
አቶ ዘካርያስም “ማን ከሶኝ? መቼስ ክስ ደረሰኝ? በየትኛው ፍርድቤት ቀርቤ ተከራክሬ ነው የተፈረደብኝ? የፈረደብኝ ፍርድ ቤት ውሰዱኝ!” የሚል ጥያቄ ያቀርብና ፍርድ ይወስዱታል። ፍርድ ቀርቦ “17 ዓመት የተፈረደብኝ በምን ወንጀል ነው? ክስ አልደረሰኝ። የመሳሰለውን ጥያቄ ያቀርባል። ዳኛው “እኛ አልፈረድንም። የምናውቀው ነጻ መውጣትህን ነው።” ይለዋል። “ታዲያ ማነው 17 ዓመት የፈረደብኝ ማነው? እኔ ተከራክሬ ነፃ ወጥቻለሁ መፍቻ ፃፉል!! የሚል ጥያቄ ለዳኛ አቅርበ። ዳኛው “ያንተ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው። መፍቻ አልፅፍም” የሚል መልስ ይሰጠዋል። ዘካርያስ ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ይጀመራል። ዳኛው ለዘካርያስ መፍቻ ከመጻፍ ይልቅ 6 ዓመት ቅጣት ጨምሮ በድምሩ የ24 ዓመት ፍርድ ተፈርዶበት ወደ ቃሊቲ እስር ቤት በልዩ ቅጣት ኮንቴነር ቤት ወደሚባለው ጨለማ ቤት ይወረወራል።
ዘካርያስ ጉዳዩን የሚከታተሉለት ጠበቆች ቢያቆምም በስውሩ እጅ የሱን ጉዳይ እንዲተው በማስፈራራት 8 ጠበቆች አባረውበታል። በዚህ ሁኔታም ሆኖ ዘካርያስ ተስፋ ሳይቆርጥ ለፍትህ ሚኒስትር አቤቱታ ያቀርባል። ፍትህ ሚኒስቴር በዚህ የመዝገብ ቁጥር ዘካርያስ ገ/ፃዲቅ የሚባል ሰው አናውቅም። “በዚህ መዝገብ ቁጥር አማን ከሊፋ የሚባል ሰው ነበር የተከሰተው እሱም በሽምግልና ጉዳዩ በማለቁ መዝገቡ ተዘግቷል” የሚል መልስ ፍትህ ሚኒስትር ለዘካርያስ ገ/ፃዲቅ ደብዳቤ ይልካል።
ዘካርያስም አቤት የሚልበት ተቋም በማጣቱ ከነሐሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ በልዩ ልዩ እስር ቤት ዛሬም ድረስ የመከራ ጊዜውን እየገፋ ይገኛል። በተለይ ቃሊቲ እስር ቤት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ከሰው ተለይቶ መታሰሩን ገልጿል። ከሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቃሊቲ ዞን 6 ከሰው ተቀላቅሎ ማን እንዳሰረው ማን እንዳሳሰረው ለምን እንደታሰረ ሳያውቅ 11 ዓመታት አስቆጥሯል። የግፍ እስረኛው ምንም እንኳ ከተመሰረተበት ክስ በተደጋጋሚ በፍርድ ቤት ነፃ ቢባልም ይህ እስከተዘገበበት መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ ም ቃሊቲ ወህኒ ቤት አልወጣም። ዘካርያስ ገብረፃዲቅ አሁንም ፍትህ ይሻል።
ለመንግሥት ሀላፊዎች
ላለፉት 27 ዓመታት ልክ እንደ ዘካርያስ ገብረፃዲቅ በግፍ የታሰሩ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው እና በአገዛዙ ሰዎች ቀጭን ትዕዛዝ በርካታ ዜጎች በግፍ ታስረው እንደሚገኙ የታወቀ ነው። በአሁኑ ሰዓት የመንግስትነት ስልጣን የጨበጣችሁ ሰዎች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ እስር ቤቶች ላይ ፍተሻ በማድረግ ያለ አግባብ የታሰሩ ሰዎች ነፃ እንዲወጡ ታደርጉ ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ።
ለሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች
ዘካርያስ ገብረፃዲቅ እና እንደሱ በግፍ የታሰሩ ወገኖችን ጉዳይ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ እስር ቤት የተወረወሩ ወገኖችን ጉዳዩ በማጣራት ከግፍ እስር ነጻ እንዲወጡ ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ አስተላልፋሁ።