ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ሆነ
በሽብርተኝነት ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበትና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት (PEN Canada’s One Humanity Award) ሽልማት ተሸላሚ መሆኑን ፔን ካናዳ ይፋ አድርጓል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በፈረንጆቹ ግንቦት 2012 የባርባር ጎልድ ስሚዝ ሽልማት እንዲሁም በሰኔ 2014 የጎልደን ፔን ሽልማት ተሸላሚ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በካናዳ ቶሮንቶ እየተደረገ በሚገኘው 36ኛው ዓለም አቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲባል የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት ሽልማትን ተሸልሟል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የአረብ አብዮትን ተከትሎ መንግስት ለውጥ የማያደርግ ከሆነ ተመሳሳይ ህዝባዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያም ሊከሰት ይችላል የሚል አስተያየቱን ማንጸባረቁን ተከትሎ ለእስር የተዳረገውና በፀረ ሽብር ህጉ ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በበርካታ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ዓለማቀፍ መብቱን መጠቀሙን በማስታወስ እስክንድር የህሊና እስረኛ እንደሆነ በመግለፅ ከእስር እንዲለቀቅ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ከእስር እንዲለቅ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእስር ቤቱ ከሚደረግበት ከፍተኛ ቁጥጥርና ጫና ባሻገር ከቤተሰብ ውጭ እንዳይጠየቅ ተከልክሎ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ
የነ አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ ውሳኔ በድጋሚ ተቀጠረ
በእነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እንዲሁም እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም፣አቶ ዮሐንስ ተረፈ፣አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ እና አቶ ምትኩ ዳምጤ ውሳኔ ለዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጥሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ 6 ኪሎ የሚገኘው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኙን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም ውሳኔውን ሳይሰጥ ለአምስተኛ ጊዜ ለሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጠረ፡፡
ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን ሊሰጥ ያልቻለበትን ምክንያት ሲገልፅ የክሱን ሂደት ገና መርምሬ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ በወቅቱ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ሽመክት አሰፋ፣ በላቸው አንሺሶ እና ዳኜ መላኩ ተሰይመው ሲሆን ከከሳሽ በኩል አቃቤ ህግ ብርሃኑ ወንድማገኝ እንዲሁም ከተከላካይ ጠበቆች አቶ አበበ ጉታ፣ አቶ ደርበው ተመስገን እና አቶ ሳሙኤል አሰፋ ተገኝተዋል፡፡ ተከሳሾችም በሰዓቱ የቀረቡ ቢሆንም የነበረው በበርካታ ያልተለመደ የጦር መሳሪያ አጀብ አዲስ ያልተለመደ ክስተት ቢሆንም በተለይ የአቶ አንዱዓለም አራጌ በከፍተኛ ደረጃ መጎሳቆል የችሎት ታዳሚዎችን ሐዘን ውስጥ ከቶ ተከሳሾቹ የውሳኔ ፍርዱ ሳይሰጥ ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ወደ የመጡበት እስር ቤት ተመልሰዋል፡፡
