Tag Archives: TPLF/EPRDF Ethiopia

መሪ (ሪዳ) እና ገዥ (ሐጉካይ-ሻ) “ገዥ ጉልበት ይፈልጋል፤ መሪ ግን ጥበብ ይፈልጋል”

Daniel Kibret

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

የሩቅ ምሥራቆቹ ጃፓኖች እንዲህ የሚል ለዓለም የተረፈ ታሪክ አላቸው፡፡

በ17ኛው (መክዘ) ላይ በዓይን ሕመም የሚሰቃይ ጎ- ሳይ የተባለ አንድ የጃፓን ንጉሥ ነበረ፡፡ በሀገረ ጃፓን የሚገኙ ሐኪሞችን ሁሉ ጠርቶ ለስቃዩ መድኃኒት እንዲፈልጉለት ቢያዝም ሊያገኙ ግን አልቻሉም፡፡ በኮርያ፣ በቻይና፣ በሞንጎልያና በሩሲያ ሳይቀር ታዋቂ የሆኑ ባለ መድኃኒተኞችን እየጠራ፣ ገንዘብና ሥልጣን ለመሸለምም ቃል እየገባ፣ ሕመሙን ለማዳን ሞከረ፡፡ ግን አልተቻለውም። በመጨረሻም ሞንጎልያ ውስጥ በኡውስ ሐይቅ አጠገብ፣ ዑላንጎም በተባለ መንደር እጅግ የታወቀ ባለ መድኃኒት መኖሩ ተሰማ፡፡

ንጉሥ ጎ- ሳይም ኦይራት የተባሉትን የሞንጎልያ ሲራራ ነጋዴዎች፤ ይህን ባለመድኃኒት እንዲያመጡለት ወርቅ ሰጥቶ ላካቸው፡፡ ከአራት ወራት በኋላም ኦይራት የሚባሉት ሲራራ ነጋዴዎች፤ ባለመድኃኒቱን በድንክየዎቹና ፀጉራሞቹ ግመሎች ጭነው አመጡለት፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ ባለ መድኃኒቱ መምጣቱን ሲሰማ የመዳን ተስፋው ለመለመ፡፡

ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒተኛ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ንጉሡን አገኘው፡፡ ንጉሡም ከሚያሰቃየው የዓይን ሕመም ከፈወሰው የፈለገውን ሁሉ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት፡፡ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒተኛ፤ የንጉሡን ሕመም ለማዳን የሚችል መድኃኒት እንዳለው ነገር ግን ንጉሡ መዳን የሚችለው አንድ ነገር ሲያሟላ መሆኑን ተናገረ። ንጉሥ ጎ-ሳይ የተባለውን ሁሉ ለማሟላት ቃል ገባ፡፡ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒትም ‹‹ሐኩጋይ-ሻ› (ገዥ) ከሆንክ አትድንም፤ ‹ሪዳ› (መሪ) ከሆንክ ግን ትድናለህ› ሲል ነገረው፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይ የባለመድኃኒቱ ነገር ስለገረመው በገዥና በመሪ መካከል ያለውን ልዩነት ጠየቀው፡፡ ባለመድኃኒቱም፤ ‹ገዥ ጉልበቱንና ሀብቱን ብቻ የሚጠቀም አለቃ ነው፤ መሪ ግን አእምሮውንና ክሂሎቱን የሚጠቀም አለቃ ነው› ሲል በአጭሩ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይም መሪ መሆኑን አረጋገጠለት፡፡

ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒት ለዓይን ሕመም የሚሆነውንና በየቀኑ የሚቀባውን መድኃኒት ከሰጠው በኋላ እንዲህ ሲል አዘዘው፡- ‹ሕመሙ እስኪሻልህ ድረስ የምታየው ነገር ሁሉ አረንጓዴ መሆን አለበት፡፡ ከአረንጓዴ ቀለም ውጭ የምታይ ከሆነ ያገረሽብሃል› ሲል አስጠነቀቀው፡፡ ንጉሥ ጎ-ሳይም ያን ማድረግ ቀላል መሆኑን ነግሮት ተለያዩ። ሞንጎልያዊው ባለ መድኃኒትም ከ3 ወር በኋላ ተመልሶ ሊመጣ ቃል ገብቶ፣ ኦይራት ከተባሉት ሲራራ ነጋዴዎች ጋር ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡

ንጉሥ ጎ-ሳይ ባለሟሎቹን ሁሉ ጠራ፡፡ ባለመድኃኒቱ የነገራቸውን በማስታወስም ከቤተ መንግሥቱ ጀምሮ ያሉ ዕቃዎች፣ ግድግዳዎች፣ ዛፎች፣ ተራሮችና ኮረብቶች ሁሉ አረንጓዴ ቀለም እንዲቀቡ አዘዘ፡፡ የከተማው ነዋሪም ቤቶቹን ሁሉ አረንጓዴ እንዲቀባ ዐዋጅ ወጣ፡፡ ከአረንጓዴ ልብስ ውጭ መልበስም ተከለከለ፡፡ እንስሳትም አረንጓዴ ቀለም እንዲቀቡ ተለፈፈ፡፡ ለዚህ ዐዋጅ የሚውል በሚሊዮን የሚቆጠር ወርቅ ወጭ ሆነ፡፡ ከኮርያ፣ ከቻይና፣ ከሩሲያና ከሕንድ ሳይቀር ቀለም በገፍ ወደ ጃፓን ገባ፡፡ ሰውና እንስሳውም መሬት ተተክሎ የበቀለ እስኪመስል ድረስ አረንጓዴ ሆነ፡፡

ከሦስት ወራት በኋላ ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒት ቃል በገባው መሠረት ወደ ጃፓን መጣ፡፡ የንጉሥ ጎ-ሳይ የዓይን ሕመም ለውጥ አላመጣም፡፡ ሀገሪቱ ግን አረንጓዴ በአረንጓዴ ሆናለች፡፡ ባለመድኃኒቱም ወደ ጃፓን ከገባበት ቀን ጀምሮ ባለማቋረጥ ይስቅ ነበር፡፡ በመጨረሻም ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲቃረብ የንጉሡ ልብሶች አረንጓዴ ቀለም ሲቀቡ ደረሰ። ይህንን ሲመለከትም ሳቁን ፈጽሞ መቆጣጠር አልቻለም ነበር፡፡ ንጉሡም የባለመድኃኒቱን ሁኔታ ተመልክቶ ግራ ተጋባ፡፡

ንጉሡ ለምን እንደዚያ እንደሚስቅ ባለመድኃኒቱን ጠየቀው፡፡ ሕመሙም እንዳልተሻለው ገለጠለት። ባለመድኃኒቱም እንደዚያ የሚያስቀው የንጉሡ ሞኝነት መሆኑን ገለጠለት፡፡ ሕመሙ ያልተሻለው ግን ገዥ እንጂ መሪ ባለመሆኑ እንደሆነ ነገረው። ንጉሡም ሞኝነቱንም ገዥነቱንም አብራርቶ እንዲነግረው ሞንጎልያዊውን ባለመድኃኒት ጠየቀው፡፡ ባለ መድኃኒቱም፤ ‹አንተ ሁሉን ነገር በሥልጣንና በገንዘብ ብቻ ነው የምታስበው። ይህ ደግሞ የ‹ሐኩጋይ-ሻ› (ገዥ) መለያ ጠባይ ነው። ሁሉንም በጉልበቱና በገንዘቡ ብቻ ማድረግ እንደሚችል ያስባል፡፡

በርግጥ የምታየው ነገር ሁሉ አረንጓዴ መሆን አለበት ብየ ነግሬህ ነበር፡፡ አንተም አገልጋዮችህንና ሕዝብህን እያስጨነቅህ አገሩን ሁሉ አረንጓዴ ቀለም ለመቀባት ሞከርክ፡፡ ለመሆኑ በዚህ አያያዝህ ቢበዛ ከዚህ ከተማ ውጭ ልትሻገር ትችላለህን? ዓለምንስ ሁሉ አረንጓዴ ቀብተህ ትጨርሳለህን? ሰማዩን፣ ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትንና ታላላቅ ተራሮችን ምን ልታደርጋቸው ነው? ከሁሉም በላይ እሳትን ምን ልታደርገው ነው? አየህ የገዥነት(‹ሐኩጋይ-ሻ›) ትልቁ ችግሩ ሁሉንም ነገር በጉልበቴና በገንዘቤ እቆጣጠረዋለሁ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ይህንን በተወሰኑ ነገሮች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ሲችል፣ ገዥ በዚያ ይታለላል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ይሳካልሃል፡፡ ያም የበለጠ ገዥነትህን ይጨምረዋል። እየቆየህ ስትሄድ ግን በገንዘብህና በጉልበትህ የማትደርስበት ኃይል መኖሩን ታውቃለህ፡፡ ልክ እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃና እሳት፡፡
አእምሮ ቢኖርህ ኖሮ ‹ሪዳ› (መሪ) ትሆን ነበር፡፡ ሪዳ (መሪ) ብትሆን ኖሮ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ጉልበትህንና ገንዘብህን ለመጠቀም ከምትሮጥ ይልቅ አእምሮህን ትጠቀም ነበር፡፡ ዓይንህ አረንጓዴ ነገር ብቻ እንዲያይ ከፈለግህ ነገሩ በጣም ቀላል ነው። ያኔ እኔ አንተን ሳዝህ ‹በጣም ቀላል ነው› ስትለኝ፣ እውነትም አእምሮ ያለህ ‹ሪዳ› (መሪ) ነህ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ አሁን ግን ተሳስቼ እንደነበር ገባኝ።
‹ቀላሉ መንገድ ምን ነበር?› አለ ንጉሥ ጎ-ሳይ በሁኔታው እየተደነቀ፡፡

‹ቀላሉ መንገድ› አለ ሞንጎልያዊው ባለ መድኃኒት፡፡ ‹ቀላሉ መንገድ የምታየውን ነገር ሁሉ አረንጓዴ አድርጎ የሚያሳይ መነጽር በሁለት ‹ስየሶ ገንቦ› ገዝተህ ዓይንህ ላይ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን መነጽር ብታድርግ ኖሮ አገልጋዮችህንና ዜጎችህን ማስጨነቅ፣ ላንተ ሲባል ምድሩን ሁሉ አረንጓዴ ቀለም ማስቀባት፣ አረንጓዴ ልብስ ማስለበስና አገሩንም ማበላሸት አይጠበቅብህም ነበር፡፡ ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስለሆንክ እንጂ መሪ(ሪዳ) ብትሆን ኖሮ ለሀገርህና ለሕዝብህ ስትል አንተ ትሰቃያለህ እንጂ ለአንተ ስትል አገርህንና ሕዝብህን አታሰቃይም ነበር፡፡ ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስለሆንክ እንጂ መሪ(ሪዳ) ብትሆን ኖሮ አገርህን አረንጓዴ ለማድረግ ስታስብ፣ ሕዝብህን ማሳመን ይጠበቅብህ ነበር፡፡
ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስለሆንክ እንጂ መሪ(ሪዳ) ብትሆን ኖሮ ያኔ እኔ ‹አረንጓዴ ነገር ብቻ ማየት አለብህ› ብዬ ሳዝህ ‹ቀላል ነው› ከምትል ይልቅ ‹እንዴት አድርጌ› ብለህ መጠየቅ ነበረብህ፡፡ ገዥ ተገዥ ይፈልጋል፡፡ መሪ ግን አማካሪ ይሻል፡፡ ገዥ ጉልበት ይፈልጋል፤ መሪ ግን ጥበብ ይፈልጋል። ገዥ ሁሉም ነገር ቀላል ነው ይላል፡፡ መሪ ግን እንዴት ቀላል ሊሆን እንደሚችል ያስባል፣ ይጠይቃል፡፡ ገዥ የሚመስለውንና የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። መፍትሔው ቢመጣ ባይመጣ፣ ችግሩ ቢፈታ ባይፈታ፣ ሌላ ችግር ቢመጣ ባይመጣ ግድ የለውም። መሪ ግን ማድረግ የሚችለውንና የሚመስለውን ሁሉ አያደርግም፡፡ ለውጥ የሚያመጣውን ነገር ብቻ እንጂ፡፡ ቢችልም፣ ዐቅም ቢኖረውም፣ ሥልጣን ቢኖረውም ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ካላረጋገጠ አያደርገውም፡፡ ለመሆኑ ይህንን ውሳኔ ስትወስን የሀገርህን ኬንጃ (ጠቢባን) አማክረሃቸዋል፡፡ ብታማክራቸው ኖሮ እንዲህ አገሩን ሁሉ አረንጓዴ አታደርገውም ነበር፡፡

ታድያ አንተ እንዴት ትድናለህ? ራስህን መቀየር ሲገባህ ዓለምን ልትቀይር ተነሣህ፡፡ መቀየር የነበረብህ የምታየውን ነገር ሳይሆን አንተ የምታይበትን መንገድ ነበር፡፡ አረንጓዴውን መነጽር ብትገዛ ኖሮ አንተ ዓለምን አረንጓዴ አድርገህ ታያታለህ። ሌላው ደግሞ እንደሚፈልገው ቀይም፣ ጥቁርም፣ ነጭም፣ ቢጫም አድርጎ ያያታል፡፡ አሁን ግን አንተ አረንጓዴ ስለምትፈልግ ብቻ ዜጎችህ ሁሉ አረንጓዴ እንዲያዩ፣ አረንጓዴ እንዲለብሱና አረንጓዴ እንዲበሉ አደረግካቸው፡፡ ካሚ(ፈጣሪ) ልዩ ልዩ አድርጎ የፈጠረውን ሕዝብ አንተ አንድ ዓይነት ልታደርገው ፈለግክ፡፡ ያውም ላንተ ሲባል፡፡

መሪ(ሪዳ) ለሕዝብ ነው፡፡ ገዥ(ሐኩጋይ-ሻ) ስትሆን ግን ሕዝቡ ያንተ ነው፡፡ እንደፈለግክ ታደርገዋለህ፡፡ ለገዥ ሕዝብና ኪያሜሩ(ግመል) አንድ ነው፡፡ ለገዥ ሁለቱንም እንደፈለጉ ማድረግ ይቻላል። ለገዥ ሁለቱም ሀብት ናቸው፡፡ ገዥ ስለ ሕዝቡ እርሱ ያውቃል፡፡ የሕዝቡም ጭንቅላት በእርሱ ላይ ነው፡፡ እርሱ አሰበ ማለት፣ ሕዝቡ አሰበ ማለት ነው፡፡ እርሱ ፈለገ ማለት፣ ሕዝቡ ፈለገ ማለት ነው፡፡
ታድያ አንተ እንዴት ትድናለህ? ወርቅህን አልፈልግም፡፡ ሽልማትህም ለራስህ ይሁን? እንካ አረንዴውን መነጽር፡፡ ከቻልክ ያበላሸኸውን አስተካክለው፡፡ ያጠፋኸውን መልሰው፡፡ ካልቻልክ ሌላ ጥፋት ሳይደርስ ባለበት እንዲቆም አድርገው፡፡ እኔ ግን ወደ ሀገሬ ወደ ኡቭስ ሐይቅ፣ ወደ ዑላንጎም መንደር እሄዳለሁ፡፡ በረግረጉ ሥፍራም ይህንን ሞኝነትህን እያሰብኩ ስስቅ እኖራለሁ፡፡ ኮክ-ኦህ-ሩኽ (ልቡና) ካገኘህና ከገዥነት ወጥተህ መሪ መሆን ስትጀምር ጥራኝ፡፡ በሕይወት ካለሁ እመጣለሁ። ያኔ ሕመምህን ፈጽሞ እንዲድን አደርገዋለሁ፡፡ ላሁኑ ግን ገን-ኪ-ደ (ደኅና ሁን፣ ራስህን ጠብቅ)፡፡

ሞንጎልያዊው ባለመድኃኒት ከጃፓን እስከ ሞንጎልያ፣ እስከ ኡቩስ ረግረጋማ ሥፍራ ድረስ በየደረሰበት ሁሉ ይህንን የንጉሡን ታሪክ እየተረከው ሄደ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ታሪክ ከኢራን እስከ ጃፓን ድረስ በየቋንቋው ይተረካል ይባላል፡፡

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አቶ ዮናታን ተስፋዬን ፍር ቤት እንዳልቀረበ ተገለፀ

በኦሮምያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቀጠል ፌስቡክ ላይ በመጻፍ ተንቀሳቅሰሃል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበበት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ  ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ተከሳሹን አላቀረበውም፡፡

Yonatan Tesfaye

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ለዛሬ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሽ በእስር የሚገኝበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሳያቀርበው ቀርቷል፡፡ ተከሳሹን ለምን እንዳላቀረበ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ተወካይ እንዲያስረዳ ተጠይቆ፣ የዕለቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ሳሙኤል ደሚ ‹‹ተከሳሹ ታሞ አላቀረብነውም›› የሚል መልስ በቃል ሰጥቷል፡፡

ከሳሽ የፌደራል አቃቤ ህግ ሁለት ምስክሮቹን ለማሰማት አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ተከሳሹ ባለመቅረቡ ሁለቱ ምስክሮች አቶ አብርሃም ወልዴ እና አቶ መኮንን በላይ በቀጣይ ቀጠሮ ተጨማሪ መጥሪያ ሳያስፈልጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ በዳኞች ተነግሯቸው ተመልሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱን ምስክሮች ለመስማት ለሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ዮናታን ተስፋዬ በጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና በእስር ቤት ሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመበት እንዳለ ጠቅሶ አያያዙ እንዲሻሻልለት ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም አቤቱታ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡

ማረሚያ ቤት ለዚህ አቤቱታ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ መልስ ሰጥቷል፡፡ ችሎት ሳይሰየም ጉዳዩን በቢሮ የተመለከቱት ዳኞች የተሰጠውን የጽሁፍ መልስ ለተከሳሽ ጠበቃ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በዚህም ማረሚያ ቤቱ ጨለማ ክፍል እንደሌለው፣ አቶ ዮናታን ከሌሎች እስረኞች በተለየ እንዳልተያዘ በመግለጽ ተከሳሹ ያቀረበው አቤቱታ ከእውነት የራቀና ስም ማጥፋት ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያ ይስጥልኝ የሚል መልስ እንደሰጠ የጽሁፍ መልሱ በንባብ ሲሰማ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የሰጠው መልስ ክህደት መሆኑን በመግለጽ፣ ደንበኛቸው ችሎት ያልቀረበው በማመልከቻው ላይ እንደገለጸው የመብት ጥሰት እየተፈጸመበት መሆኑን በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ደንበኛዬ በማመልከቻው የገለጸው የመብት ጥሰት እንደተፈጸመበትና እየተፈጸመበት ስለመሆኑ ማስረጃ አለን›› ብለዋል የተከሳሽ ጠበቃ፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ጉዳዩን ተከሳሹ በአካል ሲቀርብ እንደሚያየው በመግለጽ ለሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ዛሬ ችሎት ያልቀረበው ለሳምንት የዘለቀ የርሃብ አድማ ላይ በመሰንበቱ ሰውነቱ ተዳክሞ ሊሆን እንደሚችል ከቤተሰቦቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ተከሳሹ ባለፈው ቀጠሮ የእምነት ክህደት ቃሉን በሰጠበት ወቅት፣ ‹‹ክሱ በቀረበበት መንገድ የተገለጸውን የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ግን ጽፌያለሁ፡፡ በመሆኑም የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም›› ማለቱ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ኢሰመፕ

ሁለት ኢትዮጵያውያን ካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በራፍ ራሳቸውን አቃጠሉ

ሁለት ኢትዮጵያውያን ካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በራፍ ራሳቸውን አቃጠሉ። በቅርቡ ኦሮሚያ ከተካሄደው መጠነ ሰፊ ግድያና እስራት ሸሽተው ግብጽ መድረሳቸው የተገለጸው እነዚህ ሁለት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ራሳቸውን ያቃጠሉት በተቃውሞ መሆኑን ተመልክቷል።

UNHCR

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በማቃጠል ተቃውሟቸውን የገለጹት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የካይሮ ቢሮ የስደተኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ በማድረጉ እንደሆነም መረዳት ተችሏል። በግብፅ ካይሮ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በርካታ ኢትዮጵያውያን የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ብዙዎች በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚያደርጉት ጉዞ ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል።

ለጊዜው ስማቸው ያልታወቀው ኢትዮጵያውያን መቃጠላቸውን ተከትሎ ፖሊስ በስፍራው መድረሱን እና ራሳቸውን ካቃጠሉት ኢትዮጵያውያን አንዱ ቆዳው ጉዳት መታየቱን ተጠቁሟል፡፡ የሁለቱም ጤንነት አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እስካሁን ለማወቅ አልተቻለም።

የእነ ኦሞት አግዋ ላይ ዛሬም የአቃቤ ህግ ምስክር ሳይሰማ ተቀጠረ

ከመጋቢት 2007 ዓ.ም ጀምሮ የዋስ መብት በፍርድቤት ተከልክለው በእስር የሚገኙት እነ ኦሞት አግዋ ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. የህግ አማካሪና ጠበቃቸው አመሃ መኮንን በህመም ምክንያት ችሎት ባለመገኘታቸው መዘገቡ የአቃቤ ህግ ምስክር ለመስማት ብቻ ለዘጠነኛ ጊዜ ተቀጥሯል፡፡

Omot Agua

አንደኛ ተከሳሽ ኦሞት አግዋ ጠበቃችን አመሃ መኮንን ታመው ሆስፒታል የተኙ ስለሆነ ያለእርሳቸው ውክልና ምስክር እንዳይሰማብን ፍርድቤቱ አጭር ቀጠሮ ይስጠን ሲሉ ሶስቱንም ተከሳሾች ወክለው ፍርድቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በዕለቱ ችሎት አቃቤ ህግ አሉኝ ካላቸው ሰባት ምስክሮች መካከል ሶስቱ በችሎቱ ምስክርነታቸውን ለመስጠት ቀርበው ነበር፡፡

ከምዕራብ ሸዋ ባኮ ከተማ ለአቃቤ ህግ ምስክር ለመሆን የመጡት ቄስ ሽብሩ ኦጅራ በተደጋጋሚ መጥተው ሳይመሰክሩ ተመልሰውብኛል ስለዚህ እንዲመሰክሩ ይደረግልኝ ብሎ ለተከራከረው አቃቤህግ፣ ዳኛ ታረቀኝ አማረ የስነስርዓት ህጉ ተከሳሾች ያለጠበቃቸው ውክልና እንዲከራከሩ አይፈቅድም በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል፡፡

የአቃቤ ህግ ምስክር ቄስ ሽብሩ ከምዕራብ ሸዋ ባኮ ከተማ ለምስክርነት ለመጡበት የሁለት ቀን ትራንስፖርት እና አበል እንዲከፈላቸው እንዲሁም ዛሬ የቀረቡ ምስክሮች ያለምንም የፍርድቤት መጥሪያ ሌሎች ተጨማሪ የአቃቤህግ ምስክሮች በጠቅላላ በቀጣይ ቀጠሮ ነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ክሳቸው ከነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ. ም ጀምሮ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አየታየ የሚገኛው የእነ ኦሞት አግዋ ሶስት ተከሳሾች ያሉበት(ኦሞት አጉዋ፣ አሽኔ አስቲን እና ጀማል ኡመር ) የክስ መዘገብ ላይ አቃቤ ህግ ምስክሮችን ማሰማት የጀመረው መጋቢት 6 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡
ምንጭ፡- EHRP

መንገድ ለመስራት የተዋዋለ የህንድ ኩባንያ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ ተሰወረ

በቅርቡ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ የሚደርስ የመንገድ ፕሮጄክት ተሰጥቶት የነበረ አንድ የህንድ ስራ ተቋራጭ ኩባንያ የተረከበውን ስራ ሳያጠናቅቅ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ ከሃገር ኮበለለ።

በዚሁ ፕሮጄክት ስር ይሰሩ የነበሩ ከ200 በላይ ሰራተኞች ሊከፈላቸው የሚገባ የአንድ ወር ከግማሽ ደሞዝ ሳይከፈላቸው መቅረቱን በመግለጽ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የ958 ሚሊዮን ብር የመንገድ ፕሮጄክት ተሰጥቶት ስራውን ሳያጠናቅቅ የተሰወረው ኩባንያ ከሃገር ይዞ የወጣውን ገንዘብ ለማስመለስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

ERCA

ኤስ ኢ ደብሊው (S.E.W) የተሰኘው ኩባንያ ከሶስት አመት በፊት 66 ኪሜ ርዝመት ያለው ከሃዋሳ ጭኮ የሚደርስ መንገድ እንዲሰራ ውል ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ መንገዱ በተያዘው ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ታውቋል።

ይሁንና፣ በስራው ላይ ከፍተኛ መጓተት ታይቶበታል የተባለው ኩባንያው እስካሁን ድረስ 22 ኪሎሜርት ብቻ እንደሰራ የመንገዶች ባለስልጣን ድርጅት ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

ድርጅቱ የ958 ሚሊዮን ብር ፕሮጄክት ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን፣ በሶስት አመት ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰደ የተገለጸ ነገር የለም።

የህንዱ ኩባንያ በአጠቃላይ የተሰጠው ገንዘብ ከመግለፅ ተቆጥቦ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ ድርጅቱ በስሩ ለሚሰሩ ሃገር በቀል ድርጅቶች መክፈል የነበረበትን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ከሃገር ይዞ መውጣቱን ይፋ አድርጓል።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር ስራውን ሲሰራ የቆየው የህንዱ ኩባንያ ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሮጄክቱ አጓትቷል ተብሎ የተሰጠው ኮንትራትን እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ታውቋል።

ይሁንንና፣ የኮንትራቱ መቋረጥን ተከትሎ የኩባንያው ሃላፊዎች ገንዘቡን ይዘው ከሃገር እንደወጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ኩባንያው በአጠቃላይ ስለተከፈለው ገንዘብ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ከወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በጋምቤላ ክልል በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ የህንድ ባለሃብቶች የተረከቡትን ብድር ሳያወራርዱ ከሃገር መኮብለላቸውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

በርካታ የህንድ ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት በስኳር ፋብሪካ እና በመንገዶች እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የኢሳት ዘገባ አመልክቷል።