Tag Archives: Yonatan Tesfaye

ዮናታን ተስፋዬ እና ጌታቸው ሺፈራው ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ተደረጉ

በማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እና የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ መደረጋቸውን ሊያነጋግሯቸው ወደ ማዕከላዊ አምርተው የነበሩት ጠበቆቻቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

Yonatan Tesfaye

የሁለቱ ወጣቶች ጠበቆች የሆኑት ጠበቃ አምሃ መኮንን እና ሽብሩ በለጠ ታህሳስ 27 ቀን 2008 ዓ.ም ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ወደ ማዕከላዊ ሄደው የነበር ቢሆንም ‹‹ሰራተኞች ስብሰባ ላይ በመሆናቸው መግባት አትችሉም›› በሚል ከበር መልሰዋቸዋል፡፡

Getachew Shiferaw_Addismedia
በማዕከላዊ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጠበቆች ማግኘት የሚችሉት በሳምንት ሁለት ቀናት፣ ማለትም ዕሮብ እና አርብ መሆኑን ያስታወሱት ጠበቃ አምሃ፣ በእነዚህ ቀናትም እንኳ ደንበኞቻችንን ማግኘት መከልከላችን ግልጽ የህገ-መንግስት ጥሰት ነው ብለዋል፡፡
‹‹ህገ-መንግስቱ በእስር ላይ ስለሚገኙ ሰዎች መብት በግልጽ የሚናገረው በየትኛውም ቀን ከጠበቆቻቸው፣ ከወዳጆቻቸው፣ ከሀይማኖት አባቶቻቸው እና ከወላጆቻቸው ጋር መገናኘት እንደሚችሉ ነው፡፡ ይህ ሆኖ እያለ በሳምንት ሁለት ቀናት ብቻ ደንበኞቻችንን ለማግኘት መገደቡ ሳያንስ ዛሬ ከበር ላይ መከልከላችን የሚያሳየው በግልጽ ህገ-መንግስቱን ለማክበር ቁርጠኝነት እንደሌለ ነው›› ብለዋል ጠበቆቹ፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እና ዮናታን ተስፋዬ ከታሰሩ ከሳምንት በላይ ቢሆናቸውም እስካሁን በአንድም ሰው እንዲጎበኙ አልተፈቀደም፤ በወቅቱ በተመሳሳይ ለእስር የተዳረጉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትም በቤተሰብ እንዳይጎበኙ ተደርገዋል፡፡ በዚህም ታሳሪዎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ባለመቻሉ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡