Daily Archives: April 15th, 2013

በጎንደር እስከ ሐሙስ የመራጮች ካርድ ይታደል እንደነበር ተገለፀ

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተለይም በጎንደር ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ  እና አደባባይ ኢየሱስ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ  የመራጮች ካርድ  እየሰጠ መሆኑን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን በብሔረዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ካርድ መውሰጃ ቀን የተጠናቀቀው የካቲት 1 ቀን 2005ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አርብ ሚያዚያ 4 ቀን 2005ዓ.ም. ለምርጫ ታዛቢዎች በሚል በጎንደርና በመቀሌ ከተሞች ያሉ የቀበሌ ሰራተኞች እየዞሩ ገንዘብ ለመሰብሰብ መሰማራታቸውን የከተሞቹ ነዋሪዎችም በመታዘብ “ተወዳዳሪ በሌለበት የምርጫና ታዛቢ ለምን ያስፈልጋል?” በሚል ፊት እየነሷቸው እንዳባረሯቸው ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን ባደረግነው የማጣራት ሙከራ በጎንደር ከኢህአዴግ ውጭ ምንም ዓይነት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሌለና ብቻውን ለውድድር እንደቀረበ ከስፍራው ምንጮቻንን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጠን ጸደጋጋሚ ፅረጽ ብናደርግም አልተሳካም፡፡

በሀዲያ ዞን የፍትህ ስርዓቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ

 

በሀዲያ ዞን ያለው የፍትህ ስርዓት የህዝብ አመኔታ እያጣ በመምጣቱ  ወደፍርድ ቤቶች ከመሄድ የሽምግልና ስርዓትን እንደሚመርጡን ባለው የፍትህ ስርዓት መዳኘት እንደማይፈልጉ ምንጮቻችን ከስፍራው ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የሌሞ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት  ህግ ከማስከበር ይልቅ የህግ ጥሰት በመፈፀም በደል ያደረሱብኝ የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛም አንዱ ናቸው የሚል ጥቆማ ተሰምቶ ጉዳዩ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስነስርዓት ጉዳይ ላይ እንዲታይ አቤቱታም መቅረቡን ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

በተለይ  በሌሞ ወረዳ ሲታይ የነበረው በመዝገብ ቁጥር 06066  በወይዘሪት ቤተልሔም ወልደመስቀል እና በአቶ ጌትነት በላቸው በተባሉ ግለሰቦች መካከል በሆሳዕና ከተማ ጎፈር ሜዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሄሜ ኢንተርናሽናል ሆቴል አጠገብ በሚገኝ 400 ካሬ ሜትር ላይ ያለው ቤትና ቦታ ወራሽነት ይገባኛል በሚል በሚደረገው ክርክር ላይ የካቲት 26 ቀን 2005ዓ.ም.  በዳኛ ወ/ዮሐንስ  ለውሳኔ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡ይሁን እንጂ ጉዳዩ የማይመለከታቸው በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ሰጦሬ ተነጥቆ ውሳኔው እንዲስተጓጎል በማድረግ ህግ ተላልፈዋል በሚል ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ቀርቦባቸው በፕሬዘዳንቱ  የተነጠቁት ዳኛ ወ/ዮሐንስ አይተው ውሳኔ እንዲሰጡ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተላለፈው  መሰረት የክሱ  መዝገብ  መጋቢት 11 ቀን 2005ዓ.ም. ውሳኔ መሰጠቱ ታውቋል፡፡ ነገር ግን በተደረገው  ክርክር ላይ “ወራሽ ነኝ ያሉት ግለሰብ አቶ ጌትነት በላቸው እስካሁን በአካል ያልቀረቡና በወራሽነት ያለችውን ግለሰብ መብት ለማሳጣት  የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ሆን ብለው ከህግ አግባብ ውጭ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ተከራካሪ  ወገኖችን እያጉላሉ ነው” በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ቀርቦባቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ውሳኔ የሰጡት ዳኛ ወልደዮሐንስ ሐንዲሶ “በርግጥ የህግ ስርዓትን ያልተከተለ ትዕዛዝ መጥቶ አላይም ብዬ በኋላ የወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ጋር ከተወያየን በኋላ ማየት እንዳለብኝ ሲነገረኝ አይቼ ለውሳኔ በተዘጋጀሁበት ወቅት ተቃውሞ በመቅረቡ ውሳኔ ሳልሰጥ ቀርቻለሁ እንጂ አልተነጠኩም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከመረመረ በኋላ ውሳኔውን እኔ እንድሰጥ በመደረጉ በድጋሚ አይቼ ውሳኔውን ሰጥቻለሁ ” ብለዋል፡፡ የወይዘሪት ቤተልሔም  ጠበቃ አቶ ተካልኝ ጴጥሮስ በበኩላቸው “ጉዳዩን የህግ ስርዓት ያልተከተለ አሰራር በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አሰራር ላይ ቅሬታ ስላለን አቤቱታችንን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማረም ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት በማይመለከታቸው ጉዳይ እንደ ፍትህ አካል ሳይሆን እንደባለጉዳይ ከህግ አግባብ ውጭ እየተንቀሳቀሱና እያስፈራሩ  በመሆኑ አሁንም ለሚመለከተው አካል ቅሬታችንን አቅርበን ውሳኔ እየጠበቅን ነው” ሲሉ  ገልፀዋል፡፡

በደል ፈፅመዋል የተባሉት የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ሰጦሬ በበኩላቸው “እኔ ከችሎት ላይ የነጠኩት የውሳኔ መዝገብም የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ እንዲህ ዓይት አሰራር ከዛሬ 20  እና 25 ዓመታት በፊት እንጂ በዚህ ስርዓት የለም፡፡ በዳኞች ላይ ተቃውሞ ሲቀርብ ግን በህግ አግባብ እንዳይታይ አድርጌ ነበር፤ በመጨረሻ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን መሰረት ጉዳዩን የያዙት ዳኛ ወ/ዮሐንስ ውሳኔ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አስፈራርተሃል የተባለውን በተመለከተ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው እንጂ ያስፈራራሁት አካል የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ለማ ገ/እግዚአብሔር  በበኩላቸው ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆንም በወረዳው ህጋው አሰራርን ያልተከተለ አሰራር ነበር ፤ በኋላ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ እርማት ሰጥቶ ቀደም ሲል የያዙት ዳኛ ውሳኔ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በይግባኝ ጉዳዩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደርሶ እየታየ ይገኛል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ከጉዳዩ ጋር እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ግርማ አበበ ከህግ አግባብ ውጭ የወራሽነት መብት ላይ እግድ ጥለዋል ከሚል ቅሬታ በተጨማሪ ከወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ጋር የጥቅም ትስስር ስላላቸው ጉዳዩ ላይ እግድ ጥለዋል የሚል ቅሬታ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ግርማ በበኩላቸው “እግድ የጣልኩት  ንብረት እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ እንዲሁም ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ እንዳይሰጥ እንጂ የወራሽነት መብት ላይ እግድ አልጣልኩም” ሲሉ  ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም የአቶ ጌትነትን ጠበቃ አቶ ኤርጃቦን ለማናገር ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች በርካታ የፍትህ መጓደል በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ እንደሚስተዋልና የአንዳንድ ዳኞች ሹመትም ቢሆን ከሙያ ብቃትና አገልግሎት ይልቅ የጎሳ ዝምድና ትስስር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ዙሪያ የዞኑ ፍትህ ጽህፈት ቤትን ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡

ኢህአዴግ ብቻውን እየተወዳደረም ህገወጥ ስራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ

በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለሃብቶች “ኢህአዴግ ለሚያዚያ 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ብቻውን እየተወዳደረም ለምርጫ ቅስቀሳ በሚል በግዳጅ ገንዘብ እየጠየቀ ህገወጥ ድርጊት እየፈፀመ እንደሆነና ድርጊቱም እንዳማረራቸው ለአዲስ ሚዲያ ገለፁ፡፡ “በተለይ እኛ ሳንፈልግ ለኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ የሚሆን ገንዘብ አዋጡ የሚል እደምታ ያለውና የመንግስት መስሪያ ቤት ማኀተም ያረፈበት አስገዳጅ ደብዳቤ በየድርጅታችን ስም እየላኩ የመኖርና የመስራት ነፃነታችንን እየተጋፉ ነው “ ሲሉ ቅሬታ የተሰማቸው ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ለአዲስ ሚዲያ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት መጋቢት 20 ቀን 2005ዓ.ም. በወረዳው ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጽህፈት ቤት ማኀተም ባረፈበትና የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስልክ አድራሻን በመጠቀም የተላከው ደብዳቤ “…ባለድርሻ አካላት” ላላቸው “የኢህአዴግ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ታዋቂ ካምፓኒዎች፣ ሪል ስቴቶች፣ ግለሰቦች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት” በሚል ከተላከው አስገዳጅ ደብዳቤ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተላከው ደብዳቤ ማጠቃለያ ላይ አስገዳጅነቱን በግልፅ በሚያሳይ ማስፈራሪያ “የዚህ ፕሮግራም ማጠቃለያ የሚሆነው ለሚመለከተው አካል ጊዜውን የጠበቀ ዘገባ ማድረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢህአዴግን መምረጥ የሀገራችንን ህዳሴ ወደ ሌላ ምዕራፍ ማሸጋገር ስለሆነ አገረ ባለሃብቶችና ጥያቄ የቀረበላችሁ አካላት አስፈላጊውን ታደርጉ ዘንድ ማሳወቅ ነው::” በሚል ከፈቃደኝነት ይልቅ አስገዳጅነት ያለው ደብዳቤ በመላክ ምላሽ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል ሲሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ባለሃብቶች ከተደገፈ መረጃ ጋር አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ብቻውን ሆኖ ይህን ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ የከዚህ በፊቱ ልምዱን ነው የሚያሳየው፣ ይህ አዲስ አይደልም፤ እንደውም ይባስ ብሎ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንኳ የእሱ አጋር መሆናቸውን መግለፁ ኢህአዴግ ህገወጥ ስራ መስራቱን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልፀውልናል፡፡

ይህንንም በሚመለከት ምርጫ ቦርድ ምን ይላል የሚለውን ለማረጋገጥ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፤ ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት ማኀተምና አድራሻ የኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ ደብዳቤ በትነዋል ከተባሉት መካከል በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ስለሺ ካሳ መልስ እንዲሰጡን ብንሞክርም ያልተሳካ ሲሆን በወረዳው የመንግስት ቢሮ ውስጥ የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ በህዝብ ደመወዝ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ስራን የሚሰሩት አቶ በረከት ዮሐንስ በበኩላቸው እኛ እንዲህ አላደረግንም ቢሉም ሰነዱ ግን በዝግጅት ክፍላችን የሚገኝ ሲሆን ቅጂው ለምርጫ ቦርድ ህዝብ ግንኙነት ክፍል እንደደረሰም ተጠቁሟል፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ወንድሞ ጎላ በበኩላቸው ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት ተፈፅሞ ከሆነ የእርምት እርምጃ እንወስዳለን ፤ መረጃውን ግን እስካሁን አላየሁትም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

የአፋር ክልላዊ መንግስት 3 ባለስልጣናት ተሰናበቱ

 

በአፋር ክልላዊ መንግስት ገዥው ፓርቲ አብዴፓ ባካሄደው ጉባዔ የክክሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል ውቲካ እና የአብዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ መሐመድ ቡልቡል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም  በሚል ሙሉ በሙሉ ከስልጣናቸው ሲነሱ የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ ያዮ ከኃላፊነታቸው ዝቅ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ በጉባዔው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እስማኤል አሊሴሮ ከክልሉ ህዝብ ጥቅም ይልቅ ለኢህአዴግ ስልጣን ጥቅም ብቻ ይሰራሉ በሚል እየተወቀሱ ውስጥ ውስጡን ከስልጣናቸው እንዲነሱ ቢፈለግም በኢህአዴግ ባለስልጣናት ፍላጎት ሳይወርዱ መቅረታቸውን የአዲስ ሚዲያ ምንጮቻችን ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአፍር ክልል ዞን ሶስት  በሚገኙ ገዋኔ፣ አሚባራ እና ጉሩመዳች ወረዳ ከሚገኙ አርብቶ አደሮች በፌደራል ፖሊስ  ለከብቶቻቸው ጥበቃ የሚገለገሉበት የጦር መሳሪያ በፌደራል ፖሊስ ተነጥቆ ሲወሰድ የአጎራባች የሶማሌ ክልል ወረዳ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ተነጥቆ ከፍተኛ ቁጣን በመቀስቀሱ ወዲያው ሲመለስላቸው የአፋሮች ግን ሳይመለስ በመቅረቱ ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች 80 ፍየሎችና 17 የቀንድ ከብቶች እንደተሰረቁባቸው ምንጮቻችን በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባልደረባ የሆኑት አቶ መሐመድ ያዮ የተደረገው ሹም ሽር አስመልክቶ፣  የአርብቶ አደሮቹ መሳሪያ መነጠቅ ላይ እና ተፈፀመባቸው ስለተባለው ዝርፊያ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

%d bloggers like this: