Daily Archives: April 22nd, 2013

በሚዛን 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተዘጋ

 

በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን በሚገኘው ሚዛን 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ መዘጋቱ  ታውቋል፡፡ እንደፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፃ ከሆነ ከሚያዚያ 7 ቀን 2005ዓ.ም. ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና አስተዳደር አካላት በተነሳ አለመግባባት ከፍተኛ እረብሻ በመፈጠሩ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ለረብሻው መንስኤው የትምህርት ቤቱ  ከአሜሪካ በተሰጠው የትምህርት ዕድል የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪዎች መካከል  በተደረገው ውድድር  ከሴቶች ተማሪ መድኃኒት ስታሸንፍ  ከወንዶች ደግሞ በጀመሪያ ተማሪ ጌታመሳይ ማሸነፉ ከተጠቆመ በኋዋላ በተደረገ የውጤት ማጣራት ሂደት ተማሪ ዮሐንስ ማለፉ ተጠቁሟል ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በተለይ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ በወንዶች ተማሪ ዮሐንስና ተማሪ ጌታመሳይ ውድድር  ላይ የውጤት አሰራር  ስህተት በመኖሩን  በተማሪዎችና  በትምህርት ቤቱ መምህራንና አስተዳደር አካላት መካከል  በተፈጠረ አለመግባባት መማር ማስተማሩ ሂደት መቋረጡ ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በተደረገው የውጤት ማጣራት መሰረት በውድድሩ ያለፈው ተማሪ ዮሐንስ መሆኑንም ምንጮቻችን አስታውሰዋል፡፡

ከረብሻው ጋር በተያያዘ ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. በትምህርት ቤቱ አካባቢ ተኩስ መከፈቱና  በተፈጠረ ግጭትም 3 ተማሪዎች ቆስለው ወደህክምና ጣቢያ መወሰዳቸው ተገልፁዓል፡፡ ይህን ዜና  እስከዘገብንበት ድረስም ትምህርት ቤቱ በፌደራል ፖሊስ መከበቡ ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የትምህርት ቤቱ ዋና ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አብዱ ካሣ ስለጉዳዩ ስናነሳላቸው አሁን ስለማልችል ከ30 ደቂቃ በኋላ መልሳችሁ ደውሉ ካሉ በኋዋላ ሽልካቻን በመዝጋታቸው  ምላሻቸውን  ማካተት አልቻልንም፡፡ ምክትላቸው አቶ አበራ ጉልማንም ለማናገር ጥረት ብናደርግም ስልካቸውን ጆሯችን ላይ ዘግተዋል፡፡

 

 

የነ አቶ በቀለ ገርባ ይግባኝ ክስ ለሌላ ጊዜ ተቀጠረ

 

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ(ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ የመድረክ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦፌኮ አመራር አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ ወጣት ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡላ፣ ደረጀ ከተማ፣አዲሱ ምክሬ፣ገልገሎ ጉፉ፣ መሐመድ መሉ እና ወይዘሪት ሐዋ ዋቆ  በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተወሰነባቸውን ክስ በመቃወም ይግባኝ ቢጠይቁም እስካሁን ውሳኔ አላገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት ይግባኝ የጠየቁት ክስ 6 ኪሎ በሚገኘው በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  አቶ በቀለ ገርባ ለሚያዚያ 14 ቀን 2005ዓ.ም. የተቀጠረ ሲሆን የአቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ ለሚያዚያ 16 ቀን 2005ዓ.ም. ክርክር ለማድረግ ተቀጥሯል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ ያሉ ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ይግባኝ ቢጠይቁም እስካሁን የተሰጠ ቀነ ቀጠሮ አለመኖሩ ታውቋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነባቸው ቅጣት 8 ዓመት ሲሆን አቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ 13 ዓመት ፅኑ እስራት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተጠርጥረው በተሸለ በከሺ  የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ተሸለ በከሺ፣ሐሰን መሐመድ፣ አለማየሁ ጋሮምሳ፣ ልጅዓለም ታደሰ፣ ቶሎሳ በቾ እና ወጣት ሙላታ አብዲሳን ጨምሮ 69 ተከሳሾች  ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. የመከላከያ ምስክር ለመስማት ቀነ ቀጠሮ የተሰጠ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 27 ቀን 2005ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ የኦፌኮ አባላትን ጨምሮ  የቀድሞ የፓርላማ አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ ጉቱ ሙሊሳ ይገኙበታል፡፡  ተከሳሾቹ የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ ከሚያዚያ 19 ቀን 2003ዓ.ም. ጀምሮ በፍርድ ቤት እየተመላለሱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን በተደገፈ ማስረጃ አጋለጠ

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም.  አዲስ አበባ በሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ዋና ጽህፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እንዳልሆነ በተደጉ በርካታ ማስረጃዎች አስታውቋል፡፡ ፓርቲው የሚያዚያ 2005ዓ.ም. የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ላይ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ለመወዳደር ወደምርጫው ቢገባም በቅስቀሳው ወቅት አባሎቹ ላይ ኢህአዴግ ከፍተኛ ማስፈራራት፣ እንግልት፣ እስርና ግድያ እየፈፀመ በመሆኑ አቤቱታውን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወዲያው ቢያሳውቅም መፍትሄም ሆነ ምላሽ ሊሰጥ ባለመቻሉ የኢህአዴግ አምባገነንነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውሷል፡፡ በዚህም በዞኑ ለሚገኘው ዳሌ ወረዳ ምክር ቤት ዕጩ ተዋዳዳሪ የሆኑት አቶ ተሸመ ሳታና ባካባቢው ባለስልጣናት ከፍተኛ ማስፈራሪያና ከምርጫው እራሱን እንዲያገል  በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ  በኋላ በጥይት ገድለውት የውሃ ጉድጓድ ውስጥ በመጨመር የአስከሬን ምርመራ እንኳ እንዲደረግ  አጥብቀን ብንጠይቅም ፖሊስ ቶሎ እንዲቀበር አድርገዋል ሲል  የተፈፀመበትን ጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዕጩ ተወዳዳሪ የመንግስት ሰራተኞች ከስራ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፣ ህገወጥ የስራ ቦታ ዝውውርም ተፈፅሞባቸዋል ፣ በግፍ እንዲታሰሩ ተደርገው ተፈርዶባቸዋል፤ በሲአን ስብሰባ ተካፍላችኋል በሚል  3 ሴት ተማሪዎችና 4 ወንድ ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው ታግደዋል፣ ሌሎችም እስራት በመፍራትም  መሰደዳቸውን በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ምርጫ ቦርድ ለአንድ ድምፅ ሰጭ ሁለትና ከዛ በላይ ካርድ ማደል፣ ድምፅ መስጫ ወረቀት ከድምፅ መስጫው ቀን አስቀድሞ ለካድሬዎች ማደል፣ህዝቡ ለድምፁ ዋጋ በመስጠት አዋጁ በሚፈቅደው መልኩ የሰጠውን ድምፅ እንዳይጭበረበር ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር ርቆ እንዳይጠብቅ የምርጫ አዋጅን በመፃረር  ቀጥታ ወደ ቤታችሁ ግቡ በማለት የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤት በማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ትዕዛዝ መስጠቱም ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ልተለያዩበትን ማስረጃ ዋቢ በማድረግ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን ፓርቲው በመግለጨቫው አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው በመግለጫው ወቅት ለማስረጃ ኤግዝቢትነት ካቀረባቸው በርካታ የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃ በተጨማሪ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ለጋዜጠኞች ይፋ ያደረገ ሲሆን ከቀረቡት መካከልም የ3 ዓመት እና የ7 ዓመት ህፃናት የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን፣ አንድ ሰው ሁለትና  ከሁለት በላይ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን፣ የነገ ሚያዚያ 13 ቀን የሚደረገው የቀበሌ የድምፅ መስጫ ካርድ የምርጫ ቦርድ ማህተምና ፊርማ ያረፈበት የድምፅ መስጫ ወረቀት ቀድሞ መውጣቱና መታደሉ፣ ከመደበኛው የተለየ የተጭበረበረ ድምፅመስጫ ካርድ አዘጋጅቶ ማደል፣ ምልክት የተደረገበት የምርጫ ካርድ በማደል ከኢህአዴግ ደጋፊ ውጭ ለሆኑ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ የተበላሸ የመራጮች ካርድ መሰጠቱ፣ ምርጫ ቦርድ የፃፈው መራጮች ድምፅ ከሰጡ በኋላ ወዲያው ወደቤታቸው እንዲሄዱ  ትዕዛዝ ያረፈበት ደብዳቤ፣ አንድ ለአምስት የተደረገ ጥርነፋ ለምርጫ ቃለ መሐላ የተፈፀመበት ሰነድ፣የ አካባቢው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ኢህአዴግ አባል  የሆኑበትንና የአባልነት መዋጮ ያዋጡበትን ሰነድን ጨምሮ በርካታ ማስረጃዎችን ማየት ችለናል፡፡

ፓርቲው በግለጫው  ምርጫው የይስሙላ ያለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲ እና አብዛኛው ህዝብ ያልተሳተፈበት ምርጫ የየትኛውንም የምርጫ መስፈርት የማያሟላ በመሆኑ ምርጫው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ በመጨረሻም በሀገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ሰፍኖ የዜጎች የግልና የቡድን መብት እንዲከበር በእንዲህ በተናጠል በሚደረግ ትግል ውጤት እንዳይመጣ ሲአን ተገንዝቦ 33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ግንባር የሚፈጠርበትን ሁኔታ በአስቸኳይ አመቻችቶና የጋራ ትግል ስልት ቀይሶ ለሰላማዊ ትግል እንዲነሳ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

 

 

%d bloggers like this: